[the_ad_group id=”107″]

የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር የእምነት መግለጫ

ሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር ከዚህ በታች በተጠቀሱ የክርስትና አእማድ የእምነት አቋሞች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ አገልግሎቱም በእነዚህ መሠረታውያን የእምነት አናቅጽ ውስጥ በተካተቱ አስተምህሮዎች የተገራ ነው፡፡

  1. መጽሐፍ ቅዱስ:- መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፉት እንደ ሆነ ይህም መጽሐፍ የእግዚአብሔር እስትንፋስ እንዳለበት፣ ስሕተት እንደሌለበት፣ እውነተኛና ትክክለኛ ቃል እንደ ሆነ እንዲሁም ለሰዎች ልጆች እምነትና ሕይወት፣ መጽናናትን፣ ምሪትን፣ ጽድቅን፣ በቅድስና ለመኖር ድጋፍንና ምክርን የሚሰጥ ብቸኛና የመጨረሻ ሥልጣን ያለው የአምላክ ቃል መሆኑን እናምናለን፡፡

  2. ሥላሴ:- በሦስት የተለያዩ አካላት፡- አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ተገልጾ ለዘላለም በሚኖር በአንድ፣ እውነተኛ በሆነ አምላክ እናምናለን፡፡ እነዚህ ሦስቱ የሥላሴ አካላት በግጻዌ መለኮት እግዚአብሔር መሆናቸውን፣ ሁሉም ፍጹም ሙሉእ እና እኩል በሆነ መለኮታዊ ባሕርይ እንዲሁም ደረጃ አምልኮን እንደሚቀበሉ እናምናለን፡፡

  3. እግዚአብሔር አብ:- እግዚአብሔር አብ፣ ዘላለማዊ፣ የማይለወጥ፣ ሁሉን የሚችል፣ ሁሉን የሚያውቅ፣ በጥበብ የላቀ፣ ሁሉን የሚወድድ፣ ፍጹም ቅዱስ፣ ሉዓላዊ ገዢ እና ዓለምን በእጁ የያዘ መሆኑን እንዲሁም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና የአማኞች ሁሉ አባት መሆኑን እናምናለን፡፡

  4. እግዚአብሔር ወልድ:- ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ አንድያ ልጅ መሆኑን እንዲሁም ለዘላለም በአንድ አካል ውስጥ የማይነጣጠልን ባሕርይ በመያዝ ፍጹም ሰው – ፍጹም አምላክ መሆኑን እናምናለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተኣምራዊ ሥራ ከድንግል ማርያም የተፀነሰ፣ የተወለደ፣ ያለ አንዳች ኀጢአት የኖረ፣ ለሰው ልጆች ኀጢአት ሁሉ ምትክ መሥዋዕት በመሆን በመስቀል ላይ የሞተ፣ የተቀበረ፣ በአካለ ሥጋ ከሙታን የተነሣ፣ ወደ ሰማይ ያረገ፣ በአባቱ ቀኝ የተቀመጠ፣ ፍርድን ለመስጠት በአካል ዳግም ተመልሶ ወደ ምድር የሚመጣ መሆኑን እናምናለን፡፡

  5. እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ:- መንፈስ ቅዱስ በግጻዌ መለኮት ውስጥ ሦሰተኛው አካል መሆኑን እንዲሁም ከአብ እና ከወልድ እኩል ፍጹም አምላክ እንደ ሆነ፣ ስለ ኀጢአት እንደሚወቅስ፣ ዳግም ልደት እንደሚሰጥ፣ በአማኙ እንደሚኖር፣ አማኙን ወደ እውነትና ሕይወት እንደሚመራ፣ እንደሚቀድስ እንዲሁም አማኞች ፍሬ እንዲያፈሩ በኀይል እንደሚያስታጥቅ እና መንፈሳዊ ሥጦታዎችን ለአማኞች እንደሚሰጥ እናምናለን፡፡

  6. ሰው:- ሰው በመጀመሪያ በእግዚአብሔር መልክ እና በምሳሌው መፈጠሩን፣ ነገር ግን ባለ መታዘዝ ኀጢአት መውደቁን፣ በመውደቁም ለሥጋዊ እና መንፈሳዊ ሞት መዳረጉን፣ በዲያቢሎስ መገዛቱን፣ ከዚህም የተነሣ በገዛ ችሎታው ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ ድነትን መቀበል የማይችል መሆኑን እናምናለን፡፡

  7. ድነት:- ሰው ድነት ሊያገኝ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች ኀጢአት መሞቱን፣ በውጤቱም ሥርየትን ማስገኘቱን ንስሓ በመግባት ሲያምን መሆኑን እንዲሁም ከኀጢአት በራቀ ሕይወት ሲመላለስ የሚያጸናው እንደ ሆነ እናምናለን፡፡ ድነትን የተቀበለ አማኝም በመንፈስ ቅዱስ ዳግም እንደሚወለድ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ በመሆን የክብሩ መንግሥት ወራሽ እንደሚሆን እናምናለን፡፡

  8. ቤተ ክርስቲያን:- ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ የተዋጀች አካሉ መሆኗን፣ እርሱም ራስዋ መሆኑን፣ አንዲትና ዓለም አቀፋዊት እንደሆነች፣ አማኞችም በደሙ እንደ ነጹ፣ ዳግም ልደት እንዳገኙ፣ በመንፈስ ቅዱስ እንደታተሙ፣ ከዚህ የተነሣ ሊያመልኩትና ሊያገለግሉት እንደሚችሉ፣ ቅድስና የተሞላው ሕይወት መኖር እንዳለባቸው፣ በአንድ መንፈስ፣ በአንድነት ልብ እና የሁሉ ማሰሪያ በሆነ በፍቅር መኖር እንዳለባቸው እናምናለን፡፡

  9. መላእክት:- መላእክት ዕለት በዕለት፣ በቀንና በሌሊት እግዚአብሔርን ለማምለክ፣ ለማክበር እና ለማገልገል የተፈጠሩ መሆናቸውን፣ እነዚህም “ቅዱሳን” እና “ርኩሳን” መላእክት በሚል ለሁለት እንደሚከፈሉ፣ ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሰው ልጆች መልእክትን በማምጣትና ቅዱሳንን በመጠበቅ እንደሚያገለግሉ እናምናለን፡፡ ዲያቢሎስ አካላዊ ሕልውና እንዳለው፣ አሳች፣ አታላይ፣ ከሳሽ፣ አጥፊ እንዲሁም የዚህ ዓለም ገዢ መሆኑን፣ በመጨረሻም በፍርድ ወደ እሣት ባሕር ለዘላለም እንደሚጣል፣ ነገር ግን አማኝ በእግዚአብሔር ቃል፣ በእምነትና በጽድቅ ሕይወት እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በመታመን ሊቃወመው እንደሚችል እናምናለን፡፡

  10. ዳግም ምፅዓት እና የዓለም መጨረሻ:- ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ ፊት ወደ ሰማይ እንዳረገ ሁሉ፣ ዓይን ሁሉ እያየው በአካል፣ በታላቅ ክብር ዳግም ወደ ምድር እንደሚመጣ፣ በታላቁ ዙፋን ላይ ተቀምጦ በሰው ልጆች እና በርኩሳን መላእክት ሁሉ ላይ ፍርድን እንደሚፈጽም፣ በእርሱ ያመኑትን ሊያከበር፣ በእርሱ ያላመኑት ከክብሩ ተለይተው እንዲጠፉ፣ ሰይጣንና ሰራዊቱም በእሣት ባሕር ለዘላለም ይጣሉ ዘንድ ፍርድን እንደሚሰጥ፣ በመጨረሻም በጽድቅ የሚገዛበት ዘላለማዊ መንግሥት እንደሚሆን እናምናለን፡፡

ሕንጸት መጽሔት

ሕንጸት መጽሔት የሚኖረው ይዘት ከአሳታሚው እምነትና ፍልስፍና የሚመነጭ ነው፡፡ መጽሔቱ በወንጌል አማኝ ማኅበረ ሰቡ ዘንድ ትልቅ ተነባቢነትና ተኣማኒነት ያለው፣ አገልግሎቱም ዘመን ዘለቅ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም፣ ተቀባይነትና ዘላቂ ዕድሜ ያለው አገልግሎት ለመስጠት በሥራ ልዕቀት የሚያምን፣ ከክርስትና እምነት ጋር የሚጣጣም የጋዜጠኝነት ተግባራትን የሚጠቀም፣ የአማኝ ማኅበረ ሰቡን ውስጣዊም ሆኑ ውጫዊ ተግዳሮቶች በድፍረትና በጥበብ የሚያነሣ፣ ለአመክንዮ ትልቅ ስፍራን የሚሰጥና አማኝ ማኅበረ ሰቡን በዚህ መንገድ ለመቅረጽ እንዲሁም የአማኝ ማኅበረ ሰቡ ድምፅ የመሆን ግብ ሰንቆ የሚዘጋጅ ነው፡፡

ጥናት እና ምርምር

ይህ የአገልግሎት ክፍል የሚተገብረው፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን በሚመለከቱ ማናቸውም ጉዳዮች ላይ የምርምርና የጥናት ሥራዎችን ማከናውን ነው። ማኅበሩ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ውስጥ የተሰማሩ ወገኖችን በማሳተፍ፣ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችና ምርምሮች እንዲደረጉ ያመቻቻል፤ የተደረጉ ጥናቶችና ውጤቶቻቸውን ለሚመለከታቸው አካልት ያቀርባል፤ ያሳትማል።

ሕንጸት የመጽሐፍ ክበብ

የሕንጸት የመጽሐፍ ክበብ፣ በክርስቲያን ማኅበረ ሰቡ ዘንድ የንባብና የውይይት ባሕል እንዲዳበርና ብርቱ ጸሐፊያን እንዲጎለብቱ በሚል በወር አንድ ጊዜ የሚደረግ የመጽሐፍ ግምገማ/ውይይት ያካሄዳል፡፡

የእምነት መግለጫ

ሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር ከዚህ በታች በተጠቀሱ የክርስትና አእማድ የእምነት አቋሞች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ አገልግሎቱም በእነዚህ መሠረታውያን የእምነት አናቅጽ ውስጥ በተካተቱ አስተምህሮዎች የተገራ ነው፡፡

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.