[the_ad_group id=”107″]

እንኳን ተጋጨን!

እንተዋወቅ

ቻይኖች ግጭትን የሚመለከት አስደማሚ አባባል አላቸው። “ተጋጭታችሁ የማታውቁ ከሆነ አትተዋወቁም።” ይላሉ። መጋጨትን ሲያስቡ የሚጎላባቸው ችግርነቱ ሳይሆን፣ ተከትሎት የሚመጣው ጥልቅ ትውውቅ እና ትሥሥር ነው። ቻይኖቹ እውነት አላቸው፤ አያያዙን ላወቀበት እንደ ግጭት ያለ አግባቢ የለም። ከግጭት እንዳናተርፍ ካደረጉን ነገሮች መካካል አንዱና ዋንኛው፣ ግጭትን እንደ ተፈጥሯዊ ክስተት አድርገን ለመመልከት ካለመፍቀዳችን ጋር ይያያዛል። ተደጋጋሚውን ክስተት እንደ እንግዳ መመልከታችን እጅግ ይደንቃል። እንኳን ከሌላ ሰው ጋር ይቅርና፣ ከራሳችን ጋር በየዕለቱ የምንጋጭስ አይደለንምን? ልባችን እና አእምሯችን እርስ በእርስ ይቀዋወሙስ የለምን? ውስጣዊ ግጭቶቻችን ተከትሎ ራሳችንን ይበልጡኑ አላወቅንምን?

መጋጨትን የቱን ያህል ልናስወግደው ብንጥር፣ የማናመልጠው ከሆነስ መጋጨትን ከናካቴው ለማስወገድ ስለ ምን በከንቱ እንለፋለን?

መጋጨትን የቱን ያህል ልናስወግደው ብንጥር፣ የማናመልጠው ከሆነስ መጋጨትን ከናካቴው ለማስወገድ ስለ ምን በከንቱ እንለፋለን? ዐሳባችን ተቃውሞ ሲገጥመው፣ ከዚህ ቀደም የተመቸንን አሠራር ላይ ጥያቄ ሲነሣ፣ ነገሮችን የምንከውንበት ነገር ላይ ለየት ያለ አስተያየት ሲሰጥ እና ጕድለቶች ተነቅሰው ሲወጡ፣ የለውጥ ጽንስ መጀመሪያ መሆኑን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ።[1] ይህን ጽንስ በሚገባ ካስተናገድን እና ከትሩፋቱ ከተጎነጨን፣ ግጭቱ ይዞት የመጣውን መከራ እንረሳዋለን፤ ‘እንኳን ተጋጨንም’ እንላለን። እኛው ጋር ጎልቶ የሚሰማው እንደ ቻይኖ ግጭት ያዘለው ዕድል ሳይሆን፣ ችግርነቱ ነው፤ ምክሩ ሁሉ ግጭትን ሽሹ ባይ ነው። ስንጋጭ ሌሎችን እንደ እኵይ እኛን ደግሞ እንደ ተጠቂ ማየቱ ከልጅነት እስከ ዕውቅት ዐብሮን አድጓል።  ከዚህ ገሚስ አተያይ የተነሣም ግጭት የምንሸሸው እንጂ፣ ተፈጥሮዋዊ ክስተት ሆኖ እንዳይታየን ሆኗል።

ግጭት አሉታዊ ተደርጎ መታየቱ ባሕላችን ላይ ሁሉ አጥልቷል። የግጭት ሥጋታችንም ንግግራችንን ተጋፋጭ እንዳይሆን አድርጎታል፤ ነገሮችን የምናለሰልስበት መልክም ነገሩ በልባችን ያለውን ቦታ ሌሎች አሳንሰው እንዲመለከቱት መንገድ ይከፍታል። የምንፈልገውን ቀጥታ ከመናግር ይልቅ፣ ሌላው አንብቦን እንዲረዳን እንጠብቃልን፤ ፍላጎታችንን የምንገልጸውም በዘወርዋራው እንጂ በቀጥታ አይደለም። በተጋጨን ቍጥር ሰማዩ የወደቀ ያህል እንበረግጋለን፤ ራስንም ሆነ ሌሎችን ከግጭት ጋር አያይዞ መውቀስ ተለምዷል።

በተጋጨን ቍጥር ሰማዩ የወደቀ ያህል እንበረግጋለን፤ ራስንም ሆነ ሌሎችን ከግጭት ጋር አያይዞ መውቀስ ተለምዷል።

እንዲህ ዐይነቱ አመለካከት አላስፈላጊ ዋጋ አስከፈለን እንጂ፣ ማናችንንም አልጠቀመንም፤ አይቀሬው ግጭት ይዞልን የሚመጣውን ዕድል እንዳንጠቀመውም ሆነናል። በዚህ ዐጭር መጣጥፍ ግጭትን የምንመለከትበትን መንገድ እድንቀይር እና ግጭቶች ሹክ የሚሉንን የለውጥ ጥያቄን ልብ እንድንል እጎተጉታለሁ።

ጥያቄያችንን እናስተካክል

ግጭት ሲነሣ በአእምሯችን የሚግተለተሉት ቃላት እና ተያያዥ ስሜቶች በአብዛኛው ደስ አይሉም። ግጭት ፈጥኖ የሚያያዝብን እንደ ጥፋት ካሉ አሉታዊ ነገሮች ጋር ነው። የተጋጨን ሰው ያልፈለገን፣ የማይወድደን እና ስለ እኛ ግድ የሌለው ይመስለናል። ግድ የሌለው ሰው ዐይቶ እንዳላየ ማለፍ እየቻለ ስለ ምን ይጋጨናል?  ግጭቶቻችን እንደውም ግድ መሰኘታችንን እንጂ ግድ የለሽነትን አያመለክቱም። በእኛ ባሕል ግጭትን በአዎንታዊ መልኩ የምንመለከት ካለን ከሺሕዎች አንድ ነን፤ እንደ ጎንታይ እና እንደ ነገረኛም እንታያለን። ሰክነን ካሰብነው ግን ግጭት ያለመፈላለግ ምልክት ሳይሆን፣ በተደጋጋፊነት ውስጥ ለውጥን መፈለግ መሆኑ ይገባናል። ይህን የተረዱ እና በግጭት አፈታት ዙሪያ አንቱታን ያተረፉ ምሁራን፣ መጠነኛ ግጭት ከሌለ ተቋማት ውስጥ ሆን ብለን ልንፈጥረው ያስፈልጋል እስኪሉ ደርሰዋል። ለእነዚህ ምሁራን ግጭት የተቋማት መፈራርስ ምልክት ሳይሆን፣ የበጎ ለውጥ ጅማሮ ተደርጎ ይታያል። [2] ነገሩ “ካልደፈረሰ አይጠራም” ከሚለው የአገራችን ብኂል ጋር ይስማማል።

መገረም ካለብን ባለመጋጨታችን እንጂ በመጋጨታን ሊሆን አይገባም።

የምንጋጨው በተደጋጋፊ እና በሚያድጉ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ውስጥ መጋጨት ተፈጥሮዋዊ ሰለ ሆነ ነው። ስለዚህም መጋጭትን በራሱ ችግር አድርገን መበየናችንን እናቁም፤ መገረም ካለብን ባለመጋጨታችን እንጂ በመጋጨታን ሊሆን አይገባም። የግጭትን ተደጋጋሚነት በመካከላችን ያዩ አበው፣ “እግር እንኳን ይጋጫል” ብለዋል። በአንድ አእምሮ የሚመሩት ሁለት እግሮች ከተጋጩ፣ በተለያየ አእምሮ የሚመሩ እና በተለያየ ዐውድ ያደጉ እንዴት አብልጠው አይጋጩም? እንደውም በዐብሮነት መንገድ ፈጽሞ ተጋጭተው የማያውቁ ግድ የለሾች እንጂ፣ ልበ ሰፊዎች አለመሆናቸውን እንገንዘብ። ልበ ሰፊዎች ግጭትን ከመሸሽ ይልቅ ግጭቶች መርሕ መር በማድረግ ለተሻለ የእርስ በእርስ ግንኙነት ግንባታ ይጠቀሙባቸዋል።

መርሕ መር ግጭቶች ግባቸው ለቅያሜ እልባት መስጠት እንጂ መቃቄም አይደለም።

መርሕ መር ግጭቶች ግባቸው ለቅያሜ እልባት መስጠት እንጂ መቃቄም አይደለም። ከሚለያይ ነገር ባሻገር የጋራ ነገሮቻችንን እውቅና መስጠትም ይጎላባቸዋል፤ የተግባቦት ክፍተቶችን በውይይት ለመሙላትም ያቅዳሉ። ችግርን በውይይት ብቻ ለመፍታት ያሰቡ ስለሆኑ ሌሎችን በምንም መልኩ ማጥቃት አይሹም። የሕይወት ወሳኙ ጥያቄ ለምን እንጋጫለን ሳይሆን፣ ስንጋጭ ምን ዐይነት ምላሽ እንስጥ ነው፤ የመፍትሔውም ጅማሬ የግጭትን አይቀሬነት ከመገንዘብ ይጀምራል። 

ጎረቤት ቀድሞን ይተኛ

ስንጋጭ የምናሳያቸውን ምላሾቻችንን ላፍታ እናስብ። የአብዛኞቻችን የመጀምሪያ ምርጫ፣ ግጭቱ ሁለተኛ እንዳይሞከር አይቀጡ ቅጣት መቅጣት ነው። ካልሆነ ራሳችንን እና ክብራችንን ለማስጠበቅ በምንችለው አቅም መከላከል እንመርጣለን። መከላከል ካልተሳካ ከጉዳት ለማምለጥ ከግጭቱ መሸሽ እንሻለን። እነዚህ እርምጃዎች ምንም የተለያዩ ቢመስሉም፣ ራስ ተኰርነታቸው ያመሳስላቸዋል። የተጋጨንን ሰው በበጎ የሚመለከቱም አይደሉም። አይቀጡ ቅጣት ይሆናል በሚል የሰነዘርነው የጕልበትም ሆነ የቃላት ጡጫ ያቃቂመን ይሆናል እንጂ፣ ለችግሮቻችን እልባት አያበጅም። ተከላካይነትም ጆሮዋችንን ስለሚደፍነው ገንቢ ትችቶችን እንዳንሰማ በማድረግ የመለወጥ ዕድላችንን ያመክነዋል። የሚያጋጩ ርእሶችን መቀየር ሆነ መሸሽ ደግሞ እንደ ግድ የለሽ ያስቈጥረናል።

እኛን ብቻ ያማከሉ ራስ ተኰር መፍትሔዎች ግን በዐብሮነት መንገድ የትም አያደርሱም። ይህን እውነት፣ “መተኛት ከፈለግህ፣ ጎረቤትህ በቅድሚያ እንዲተኛ አድርግ” በሚለው አገርኛ ብኂላቸው ውስጥ ተጋሩዎች ከትበውት እናገኛለን። ምክራቸው ግልጽ ነው፤ በዐብሮነት ውስጥ ስለ ራስ ብቻ ማስብ የምንፈልገውን አያስገኝልንም። በእኛ ጕዳይ እኛን ብቻ ዐስበን እና ሌላውን እንዘንጋ የሚለው አካሄድ፣ የአሸናፊነት መንገድ ቢመስልም የትም አያደርስም። በመሠረቱ ግጭት በአንዱ አሸናፊነት በተቋጨ ቍጥር ሌላ ግጭት መረገዙን ርግጠኞች መሆን አለብን።

ሰዎች መገናኘትን እስካልተውን ድረስ ግጭት አይቀሬነቱን ማመን አለብን። ሰዎች ማኅበራዊ ፍጡራን እና ተደጋጋፊ ስለሆን፣ አንዳችን ሌላችንን መፈለጋችን አይቀርም። ከፍጥረታችን በግንኙነት የተወለድን እና በትሥሥር ውስጥ የምናድግ የመሆናችንን እውነት መቀበል ከመጠን ያለፈ ልዕልናን እንዳንሻ ያደርገናል።  በዐብሮነት እና በተደጋጋፊነት ውስጥ ደግሞ መጋጨታችን አይቀርም። መጋጨት ከዐብሮነት ጋር የተጣመረበት ምክንያት የሚነሣው አንዳችን ከሌሎቻችን ጋር አንድ ዐይነት ብቻ ሳይሆን፣ የተለያየን ከመሆናችን ጋር ይያያዛል። መዝሙረኛው (139፥4) እንደሚቀኝ የሁላችንም አፈጣጠር ድንቅ እና ለየቅል ስለ ሆነ፣ አስተሳሰባችን እና አተያያችን በብዙ ጕዳዮች ለየቅል ነው። አያንዳንዳችንን ዓለምን እና ክስተቶችንን የምንመለከትበትም ሆነ የምንተረጕምበት መንገድ ለየቅል መሆኑ እስከ ቀጠል ድረስ መጋጨት ዘላቂ ጎረቤት ይሆናል።

የመለያየታችንን እውነት መገንዘብ በተጋጨን ቍጥር ሌሎችን በአሉታዊ መንገድ ፈርጆ መሸሽ እና መክሰስ የሚፈልገውን ሰዋዊ ድካማችንን አደብ እንድናስይዘው ይረዳናል። ልዩነቶቻችን የግጭት ምክንያቶች እንደሆኑ ስንረዳ የተጋጨን ሁሉ ችግር እና አንዳች ጕድለት ያለው አድርገን መቍጠራችንን እናቆማለን። የተጋጨንን ሁሉ ፍቅር አልባ እና ሰላም የማይፈልግ ብለንም አንከስስም። ልዩነቶቻችን እንደሚያጋጩን ስናውቅ የእኛ ጥሩነት እና የሌላው መጥፎነት አለመሆኑ ይገባናል፤ በውሳኔዎቻችን ተለያይተን እንኳ ዐብሮነቱን እና መከባበሩን ግን ላፍታም ቢሆን አናጣውም። መጋጨት የሕይወት አካል እንደ ሆነ ስንቅበል፣ አንክደውም፤ ተባብሶም እንዲያሻክረን አንፈቅድም።

ልዩነት የግጭቶቻችን መሠረታዊ መነሾ መሆኑን ካመንን ለግጭት የምንሰጠውም ምላሽ ዐብሮ መለወጡ አይቀርም።  ትግላችንም ግጭት እንዳይፈጠር መጣር መሆኑ ይቀርና ለግጭት የምንሰጠው ምላሽ ማስተካከል ላይ ያተኩኵራል። አብዛኞቹ ግጭቶቻችን ወደ ጦርነት የተለወጡት ግጭቶታችንን ተከትሎ አንዳችን ሌላችንን የምንመለከትበት መንገድ ስለ ተለወጠ ነው እንጂ፣ ግጭቶች በራሳቸው ችግር ከመሆናቸው ጋር እንደማይያያዝ ይገባናል። ግጭት ከምንም በፊት ‘የስሙኝ’ ልመና መሆኑን ስንረዳ መጯጯህ አቁመን መደማመጥ እንጀምራለን። 

ግጭት ዋንኛ መልእክቱ ስሙኝ መሆኑን ከተገነዘብን ደግሞ ሌላውን መታገል፣ ራስን መከላከል ወይም መሸሽ ዋንኛ ቅኝታችን አይሆንም። ግጭት የስሙኝ ልመና መሆኑን ስንገነዘብ ልባችንን ከመዝጋት ይልቅ በእርስ በእርስ ግንኙነታችን ውስጥ ተደጋግሞ የተነገረኝ ነገር ግን ልብ ያላልኩት አንዳች ነገር አለ ማለት እንጀምራለን።  ጠቢቡም ከመናገር በፊት መስማት እጅግ መፈለጉን አጽኖት ሲሰጥ፣ “ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል።” ይለናል (ምሳሌ 18፥13)። ብናውቅበት በግጭት ውስጥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ለመሆን አንጣደፍም፤ ነገሮቻችንንም በአቋም መልክ ሳይሆን በጥያቄ መልክ ወደ ማቅረብ እናዘነብላለን፤ የሌላኛውን ዕይታ ሳንጋራም ለመፍረድ አንቻኮልም።

ወደ ውስጥ መመልከት

ግጭት በለሆሳስ ሲነገረን ያልሰማነው ነገር ጎልቶ የመምጣቱ ምልክት መሆኑን ስንገነዘብ ምላሻችን ይለወጣል። ስንጋጭ “ግጭቶቻችን ምን እየነገሩን ነው?”፣ “በአሁኑ ግንኙነቶቻችን ውስጥ ያልተመቹን ነገሮች ምንድን ናቸው?”፣ “ከዚህ በፊት ተነጋግረን ያልተደማመጥናቸው ጕዳዮች አሉን?”፣ “ከዛሬው ግንኙነታችን ውስጥ ምን መለወጥ አለበት?” እያልን ራሳችንን አንጠይቃለን። ግጭትን በአሉታዊ መንገድ ብቻ መመልከት አቁመን እነዚህን ወደ ውስጥ ተመልካች ጥያቄዎች ስንጠይቅ እናተርፍበታለን።[3] ግጭት የበለጠ መተዋወቂያ መንገድ መሆኑ ይገባናል፤ ግጭቶችን በአይበገሬነትስ ናልፍ ግንኙነቶቻን በእሳት እንደተነጠረ ወርቅ እጅጉን ይፈለጋሉ፤ ግንኙነቶቻችንም ማስመስል  የተሞሉ መሆናቸው ያበቃል። ግንኙነቶቻችን ከቀድሞ የበለጠ ጥልቀት ይኖራቸዋል፤ ከግጭት መልስ የምንወሰናቸው ውሳኔዎች ከቀድሞው ይልቅ ሁሉም ያዋጣባቸው እና የሁሉንም አተያዮች አጣጥመው የያዙ ናቸውና በብዙ እጥፍ ይሻላሉ።

ውስጥ ተመልካች ጥያቄዎች ለለውጥ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፤ ግጭቶቻችን በውስጥ ተመልካች ጥያቄዎች ስንፈትሽ ግጭቶች የመጯጯህ መድረኮች ሳይሆኑ፣ የመደማመጫ ዕድሎች ይሆናሉ። መጽሐፍስ የሚመክረን “ከሌላው ጕድፍ” በፊት መጀመሪያ የራስህን “ምሰሶ” ተመልከት አይደለምን? (ማቴዎስ 7፥5)። ግንድን የሚያህል ነገር በራስ ዐይን ሰንቅሮ የሌላውን ጕድፍ መመልከት እችላለሁ የሚል ተላላነትን ምንስ ይባላል? የብዙዎቻችን ችግር ግጭት የሆነ ዐይነት ለውጥ እኛ ጋር የመፈለጉ ምልክት መሆኑን ዘንግተን፣ ሌሎች ከእኛ ቀድመው እንዲለወጡ ከመፈለጋችን ጋር ይያያዛል። ግጭት እኛም የችግሩ አካል መሆናችንን በማሳየት የእኛውኑ ምሰሶ ለማውጣት እንድንተጋ ያበረታናል።

ውስጥ ተመልካች ጥያቄዎች ለለውጥ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፤ ግጭቶቻችን በውስጥ ተመልካች ጥያቄዎች ስንፈትሽ ግጭቶች የመጯጯህ መድረኮች ሳይሆኑ፣ የመደማመጫ ዕድሎች ይሆናሉ።

መፍትሔ

ልዩነት የፈጠረውን ግጭት በመሰማማት እንግጠመው የሚለው አካሄድ ለአንዳንዶቻችን ሞኝነት ይመስለናል። እንዲህ የምናስብ፣ የማድመጥን አስፈላጊነት በቅጡ ያሰብነው አይመስለኝም። ማድመጥ የግጭቶች የመፍትሔ አቅጣጫ ጅማሮ እና መንገድ የሚሆንበት ምክንያት ማድመጥ የሌላውን ሰው ፍላጎት እና አተያይ ዕውቅና መስጠት መጀመር ስለ ሆነ ነው። ነገሩ በእኔ ፊት ቦታ የሚያገኘው የእኔ አተያይ ብቻ አይደለምና አተያያችሁን አከብራለሁ ማለት ነው። ከዕውቅናው መልስ ያለው ነገር ደግሞ እዳው ገብስ ነው፤ የቀረው ዝርዝር እንጂ ዋናው ጭብጥ አይደለም።

አብዛኞቻችን ግጭቶች መነሿቸውም ሆነ መፍትሔዎቻቸው በጭብጦች ዙሪያ ይመስሉናል። እውነታው ግን ከተጋጭንባቸው ጭብጦች ባሻገር፣ ሥነ ልቦናዊ እና የአካሄድ ጥያቄዎቻችን ግጭቶቻችን ገንቢ ወይም አውዳሚ መሆናቸውን በመወሰን ሂደት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። ግጭቶታችን ከጭብጦች ባሻገር አንዳችን ሌላችንን ካየንበት እና ካስተናገድንበት መንገድ ጋር በርግጥም ይያያዛሉ። በግንኙነቶቻችን ውስጥ እንዳልተከበርን ከተሰማን፣ ጥያቄዎቻችን ዕውቅና ካልተሰጣቸው፣ ድምፃችን እንደታፈነ ካሰብን ግጭቱ ይጋጋላል፤  ችግሮችንም ለመፍታት የሄድንበት መንገድም ፍትሐዊ መስሎ ካልተሰማን ነገሩ ይባባሳል። [4]የግጭቶቻችን መፍትሔም ካጋጨን ጕዳይ ባሻገር፣ ሥነ ልቦናዊ እና የአካሄድ ጕዳይ መሆኑን መገንዘብ ከክርክር ይልቅ በግጭቶች ውስጥ የማዳመጥን አስፈላጊነት እጅጉን ያጎላዋል።

አብዛኞቻችን ግጭቶች መነሿቸውም ሆነ መፍትሔዎቻቸው በጭብጦች ዙሪያ ይመስሉናል። እውነታው ግን ከተጋጭንባቸው ጭብጦች ባሻገር፣ ሥነ ልቦናዊ እና የአካሄድ ጥያቄዎቻችን ግጭቶቻችን ገንቢ ወይም አውዳሚ መሆናቸውን በመወሰን ሂደት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ።

ሰዎች እንደተከበርን ሲሰማን ከዚህ ቀደም በብርቱ የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ከናካቴው ልንተወው እንችላለን፤ እንደተናቅን ስናስብ ደግሞ የማያስፈልገንን ሁሉ ከሌላው ተናጥቀን ማከማቸት ያምረናል። መከበር እና መሰማት የሰው ውስጣዊ ፍላጎት እንደ ሆነ የተገነዘበው የአገሬ ሰው ሲመርቅ ወይ ሲያመሰግን፣ “እግዚአብሔር ያክብርልኝ!” ይላል።  ያለመሰማትን ያህል ሰውን የሚጎዳ መጥፎ ስሜት አለመኖሩን የደረሰብን ሁላችንም እናውቀዋለን። ትልቁ በቀልም ሆነ በደል ሰው እያለ እንደሌለ መቁጠርስ አይደለምን? በመደማመጥ ውስጥ የሚገኝ መከባበር የጠላት ዐይነቱ ውድድርን በወዳጅነት መተባበር ይተካል፤ መተባበርም ለፈጠራ ዕድል ይሰጣል።

ግጭትን መጯጯህ ሲያግዘው ትኵረት ይሳታል፤ አቅማችንን አሰባስበን በትብብር ግጭቱን የወለደውን ጕዳይ ከመግጠም ይልቅ አንዳችን ሌላችንን ችግር ማድረግ እንጀምራለን። ዋናውን ችግር ወደ ጎን ትተን አንዳችን ሌላችንን የማሸነፍ ፍላጎት ያድርብናል። ያኔም “ዋናው ነገር፣ ዋናውን ነገር ዋና ማድረግ ነው!” የሚለውን የጀርመኖችን ምክር እንዘነጋለን። አንዳችን በሌላችን ላይ ያለን መቃቃር ከከፋ ደግሞ ሌላኛውን መቅጣት ግባችን ይሆናል፤ ግጭቱ ሲዘልቅ የመቅጣት ፍላጎታችን ሌላውን ከናካቴው ወደ ማጥፋት ሁሉ ያድጋል፤ በቅርብ ጊዜም በአገራችን እየተመለከትን ያለነው ይህንኑ ነው። አንዳችን በሌላችን ላይ መጠቋቀሙ ግን አንዳች አይረባንም። ካወቅንበትም ግጭት መጠፋፊያ ሳይሆን የመለወጫ ዕድል መሆኑን በመገንዘብ በልበ ሰፊነት እና በአዳማጭነት እንቀርበዋለን።

ግጭትን ሁሉ እንደ ጥቃት ስንመለከት ከአድማጭነታችን ይልቅ ራስን ወደ መከላከል ያዘነብላል። ራስን ለመከላከል በሚል ሌላውን መስማት ነገር ያባብሳል። ስንሰማ ተከላካይ እንጂ አድማጭ አለመሆናችንን የምናውቀው ስናደምጥ ውስጣችን “ያልገባህን ነገር ላስረዳህ”፣ “ሳትረዳ አትተቸኝ”፣ “ሳብራራልህ ይገባሃል” ዐይነት ድምፆችን ግጭቶችን ተከትሎ በተደጋጋሚ ሲያስተናግድ ነው። የተከላካይ አሰማም የመነጋገር ግቡ ራስን ማስረዳት እና መከላከል እንጂ፣ ሌላውን እና ራስን ከሌላው አንጻር መረዳት አይደለም። ሁሉም ራሱን ማስረዳት ላይ ካተኰረ ደግሞ ማንም አይደመጥም፤ ሳንደማመጥም የሚመጣ አንዳች መፍትሔም የለም።

ተከላካይ አድማጭ ስንሆን የምንሰማውን ሁሉ እናዛባለን። እያንዳንዱን አስተያየት በእኛነታችን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት አድርገን እንወስደዋለን። የሰማነውን ነገርም የምንጠቀመው ሌላውን ለማጥቃት እንጂ ራሳችንን ለማስተካከል መሆኑ ያበቃል። ስንናገር የእኛን መተንፈስ እንጂ በሌላው ላይ ንግግራችን የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለማሰብ ጊዜ እናጣለን። በሂደቱም ሌላው እኛን የሚረዳበትን መንገድ የመገንዘብ ዕድላችንን እናመክናለን። የሌሎች ዕይታ እና አመለካከት ታሳቢ አለማድረግ ደግሞ ራሳችንን እንዳናስተካክል ያደርገናል፤ ግጭቶቻችንም ተባዝተው የማንቆጣጠርበት ደረጃ እንደርሳለን።

በግጭቶቻችን ውስጥ የሚያዋጣው የአድማጭነት መንገድ ነው። አድማጭ ስንሆን ግጭት ጆሯችንን በሌላው ላይ እንድንጠረቅም አያደርገንም። ይልቁን ግጭቶቻችን ስለ ሌላው ሰው አተያይ፣ አመለካከት እና ፍላጎት እየነገሩን ያሉትን እና እየፍጠሩ ያሉትን ስሜት ለመረዳት እንጥራለን። ሰዎች ምንም ነገር ከንግግራቸው ሳናጠል ከሰማናቸው አንዳች ነገር ሳናደርግላቸው ግንኙነቶቻችን መለወጥ ይጀምራሉ፤ እነርሱ ዘንድ ሃጢአታቸው የማይቈጠርባቸው ሰዎችም እንሆናለን። የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖረን ማድመጣችን በራሱ እንዳከበርናቸው ስለሚቈጠርልን ዐብረውን የመፍትሔው አካል ለመሆን ይተጋሉ።  እስክንጋብዛቸው ሳይጠብቁ ዐብረውን እኵል ሲብሰለሰሉ እና ዐሳብ ሲያቀብሉ እናገኛቸዋለን። ቅኝታችን በልበ ሰፊነት ማድመጥ ሲሆንም ስንናገር የመደመጥ ዕድላችን ዐብሮ ይመነደጋል። ግጭቶቻችንን ተከትሎ እነኝህን ትሩፋቶች አፈስን ማለት በግጭቶቻችን ውስጥ ዐደግን ማለትስ አይደለምንም?

ግጭቶቻችን በርግጥም በረከቶቻችን እንዲሆኑ ከፈለግን፣ ግጭትን የምንመለከትበት እና የምናስተናግድበት መንገድ መለወጥ አለበት። ግጭት ልብ ላለው የለውጥ ዕድል መሆኑንም እንገንዘብ። ግጭትን የአድምጡኝ ግብዣ አድርገን እንመልከት። ያኔም ከተከላካይ ሰሚነት ወደ ልበ ሰፊ አድማጭነት እናድጋለን። አዎንታዊ በሆነ መልኩ ግጭቶቻችን ተመልክተን ካስተናገድ፣ እኛንም ነገሮቻችንን ግጭቶቹ ለበጎ ለውጠውት ስለምናገኝ፣ ‘እንኳንም ተጋጨን’ የምንልበትን አቅም እናገኛለን። አምላክ ግጭቶቻችንን ‘እንኳንም ተጋጨን’ የምንልባቸው ሰብእና እንድንገነባ እና ከግጭቶች እንድናተርፍ ያድለን።


[1] Robbins, Stephen P. ““Conflict management” and “conflict resolution” are not synonymous terms.” California management review 21, no. 2 (1978): 67-75.

[2] Rahim, M. Afzalur. Managing conflict in organizations (Taylor & Francis, 2023), 1943.

[3] West, Richard, and Lynn H. Turner, Understanding interpersonal communication: Making choices in changing times (Cengage learning, 2010), 313.

[4] Picard, Cheryl A., Mediating interpersonal and small group conflict. (Dundurn, 2002), 25.

Share this article:

ለግብ መብቃት

“መጽሐፍ ቅዱስ ከነገር ጅማሬ ይልቅ ለነገር ፍጻሜ ከፍተኛ አጽኖት ይሰጣል። ለፍጻሜ ትኵረት የመስጠቱም ምክንያት ብዙዎች ከጠራቸው ከእግዚአብሔር ጋር ጕዞ እንደሚጀምሩ፣ ነገር ግን በጀመሩበት ፍጥነትም ሆነ ቅናት እንደማይቀጥሉ፣ ከዚያም ዐልፎ ከመሥመር እንደሚወጡ ለማሳየት ነው።” ይልቃል ዳንኤል

ተጨማሪ ያንብቡ

ጤነኛ ቤተ ክርስቲያን እንዲኖረን ኀላፊነታችንን እንወጣ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስትና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በፈተና ውስጥ እንዳለ እናምናለን፡፡ እነዚህ ፈተናዎች ደግሞ የወንጌላውያኑን ማንነት እያደበዘዙ፣ በማኅበረ ሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እያጠፉ፣ የአማኞችን የሕይወት ጥራት እየቀነሱ፣ ቤተ ክርስቲያን ምድራዊና ራስ ተኮር ብቻ እንድትሆን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህ በዚህ ከቀጠለ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ምን ዐይነት መልክ ሊኖረን እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

“ታሪካዊ” የተባለው የኅብረቱ ውሳኔ እና የተሰጠው ምላሽ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ከመጋቢት 21-22፣ 2009 ዓ.ም. ድረስ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በአስተምህሮ ዝንፈት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ልምምዶች እና በሞራል ውድቀት ላይ እጅግ ጠንካራ ነው የተባለለት የአቋም መግለጫ አወጣ፡፡ መግለጫው የወጣው በተጠቀሱት ጕዳዮች ላይ ኅብረቱ ያዘጋጀው ጥናት ለጠቅላላ ጉባኤው ከቀረበና ውይይት ከተካሄደበት በኋላ እንደ ሆነም ተነግሯል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.