[the_ad_group id=”107″]

የማይናወጥ ሐሴት

የኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ (1)

“እግዚአብሔር አምላክህ
ከጓደኞችህ ይልቅ
በደስታ ዘይት ቀባህ፥”
ዕብራውያን 1፥9

“መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ …
ወደ ጌታህ ደስታ ግባ:”
ማቴዎስ 25፥21

የማይናወጥ ሐሴት
የኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ
ትርጕም በአማረ ታቦር

ከከፋ አደጋ ያዳኖት ሰው ኮስታራ ቢሆን ግድ አይሰጥዎትም። ከአደጋው በመዳንዎ ከቤተ ሰብዎ ጋር ሐሴትን ሲያደርጉ፣ ያዳንዎ ሰው ጸባይ ምንነት ከቁም ነገር አይገባም። በኢየሱስ መዳን ግን ነገሩ ከዚህ በጣም የተለየ ነው። ኢየሱስ ያዳነን ለቤተ ሰቦቻችን ብሎ ሳይሆን፣ ለእርሱ ራሱ እንድንሆን ነው። በዚህም ደስተኛ ካልሆነ፣ ድነታችን አሳዛኝ ይሆናል። እርሱም፣ ታላቅ መዳን አይሆንም።

ሽልማታችን ኢየሱስ ራሱን፣ በእርሱም እግዚአብሔር ለእኛ የሆነው ሁሉ ነው። ከዚህ ያነሰ አይደለም። “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም። በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።” (ዮሐንስ 6፥35፤ 7፥37) ። መዳን ማለት የኀጢአት ምሕረት ብቻ አይደለም። ዋናው ነገር ከኢየሱስ ጋር ኅብረት ማድረግ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 1፥9) ። ምሕረት ሁሉንም በማስወገድ ይህ እንዲሆን ያደርጋል። ይህ ኅብረት ሙሉ ርካታን ካልሰጠ፣ ታላቅ መዳን አይኖርም። ኢየሱስ ኮስታራና ስሜት የለሽ ከሆነ፣ ዘላለም እጅግ በጣም ረዥም ትካዜ ይሆናል።

ሆኖም፣ የኢየሱስ ክብርና ጸጋው ሁሌም የማይናወጥ ደስተኛ መሆኑ ነው። ክብር ነው ያልኩበት ምክንያት፣ ኮስታራነት ክብር ስላልሆነ ሲሆን፤ ጸጋ የሆነበት ምክንያት ደግሞ፣ ከሁሉ ይልቅ የሰጠን ነገር የእርሱን ደስታ በመሆኑ ነው። “ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ” (ዮሐንስ 15፥11፤ በተጨማሪ 17፥13 ይመልከቱ)። ኢየሱስ የእኔን ደስታ ከፍ አድርጎ፣ የእርሱን ካሳነሰው የከበረ አይሆንም። የእኔ የመደሰት አቅም በጣም የተገደበ ነው። ስለዚህ፣ ክርስቶስ ለእኔ ደስታ መለኮታዊ ‘ዕቃ’ አድርጎ ራሱን መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን የመደሰት አቅም በእኔ ውስጥ ያፈስሳል። በዚህም፣ በእግዚአብሔር ደስታ ሐሴትን አደርጋለሁ። ይኼ ክብር ነው፤ ጸጋም ነው።

ኮስታራ መሆን ክብር አይደለም። ስለዚህም፣ ኢየሱስ ኮስታራ ሆኖ አያውቅም። ከዘላለም ጀምሮ የአምላክ ወሰን የለሽ ደስታ ማሳያ መስታወት ነው። የእግዚአብሔር ጥበብ ምሳሌ 8፥30 ላይ፣ “የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፤ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ” በማለት ይናገራል። የአምላክ ደስታና በፍጥረት ውስጥ ተወካይ የሆነው ዘላለማዊው ክርስቶስ፣ በእግዚአብሔር ፊት ሐሴትን የሚያደርግና የአምላክ ደስታም ነበር። አዲስ ኪዳን ውስጥ፣ ይህን ሁለት ቦታ እናየዋለን።

ዕብራውያን 1፥8-9 ላይ እግዚአብሔር ለመላእክት ሳይሆን ለልጁ፣ “ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤… ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ” በማለት አስደናቂ ቃላትን ይናገራል። በሁለንታ ደስተኛ ‘ነገር’ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የእርሱ ደስተኝነት ከመላ የሰማይ መላእክት ደስተኝነት እጅግ ይበልጣል። እርሱ ለወሰን የለሹ፣ ለቅዱሱና ለማይበገረው የአባቱ ደስታ ፍጹምነት ማሳያ ነው።

እንደገናም፣ የሐሥ ሥራ 2፥25-31 ላይ [ሐዋርያው] ጴጥሮስ፣ መዝሙር 16 ክርስቶስን እንዲያመለክት አድርጎ ይተረጕመዋል፤ “ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፤ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፣ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።… ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።” ከሞት የተነሣው ኢየሱስ፣ የሞትን ጥላ በማስወገድ፣ በእውነተኛው የእግዚአብሔር ደስታ ሐሴትን ያደርጋል። የክርስቶስ ክብር፣ በእግዚአብሔር ፊት የሆነው ወሰን የሌለው፥ ዘላለማዊና የማይናወጥ ደስተኝነቱ ነው።

ኮስታራነት ክብር ካልሆነ፣ ስሜታዊነትም ክብር አይደለም። በሰርግ ላይ መፈጠዝና በእስር ጒድጓድ ውስጥ ሊቋቋሙት የማይቻል ደስታን ማግኘት የተለያዩ ናቸው። አንደኛው የሚጠበቅ ነው። ሌላኛው ድል ነሺነት ነው። አንደኛው ስሜት ነው። ሌላኛው ክብር ነው። ሕመምን የማያውቅ ተለጣፊ ደስታ አለ። ይህም ለመልካም መጋቢ ወይም ለትልቅ አዳኝ አይሆንም። ክርስቶስ ግን ታላቅ አዳኝ ነው።

ስለዚህም፣ ይህ የማይናወጥ ደስታ ያለው ሰው፣ “የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው” (ኢሳይያስ 53፥3)። “‘ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዘነች፤ በዚህ ቈዩ ከእኔም ጋር ትጉ።’ አላቸው” (ማቴዎስ 26፥38)። ይህ “ትልቅ ሊቀ ካህናት” እንደ ሰው በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ስለ ሆነ፣ በድካማችን ሊራራልን የማይችል አይደለም (ዕብራውያን 4፥14-15)። ከሚያለቅሱት ጋር አንብቷል (ዮሐንስ 11፥35)፣ ደስ ከሚላቸውም ጋር ተደስቷል (ሉቃስ 10፥17፣ 21)፣ ተርቧል (ማቴዎስ 4፥2)፤ ደክሞታል (4፥6)፣ ብቻውን ተትቷል (ማቴዎስ 26፥56)፣ ተከድቷል (ማቴዎስ 26፥45)፣ ተገርፏል (ማቴዎስ 27፥26)፣ ተዘብቶበታል (ማቴዎስ 27፥31)፣ እንዲሁም ተሰቅሏል (ማቴዎስ 27፥35)።

የማይሰበር ደስታ ማለት፣ ደስታ አለ ብቻ ማለት አይደለም። ታዲያ፣ [ኢየሱስ] በደስታና በሕመም መኻል የተከፈለ ነበር ማለት ነውን? ወሰን የሌለው ነፍስ ሊጨነቅ ይችላልን? አዎ፤ የተጨነቀ፣ የተሰበረ ወይም የተከፈለ ግን አይደለም። ክርስቶስ ሊረዱት የማይችሉት ነበር፤ ግራ የተጋባ ግን አልነበረም። ነፍሱ ውስጥ ተቃራኒ ድምፆች ነበሩ። ውጤታቸው ግን ጥዑም ዜማ ነበር። አንድ የጦር መሪ፣ በጦርነት ውስብስብ ዕቅዱ ውስጥ፣ ጠላት ጊዜያዊ ድልን እንዲያገኝ የሚያደርግ አታላይ ብልኀትን ሊያካትት ይችላል። እንዲህ የሚያደርገው ግን፣ በመጨረሻው ታላቅ ድልን ለመቀዳጀት ነው። ይህ የጦር መሪውን የአእምሮ ግራ መጋባት የሚያሳይ አይደለም። ጦር ሜዳውን በከፊል ለሚያዩት ግን እንደዚያ ሊመስል ይችላል። ለእርሱ ግን ክብሩ ነው። ሰላማዊው (ፓስፊክ) ውቅያኖስ በውስጡ ብዙ ሺሕ የማዕበል ነውጦች አሉበት። ከብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ከላይ ከሰማይ ሲታይ ግን፣ አንድ ታላቅ፣ የረጋና ገራሚ የብዙ ውኆች ሙላት ነው።

ኢየሱስ በጌቴሴማኒና በጎልጎታ ስቃዩ ውስጥ፣ በማይጠፋው ደስታ ተደግፏል። “እርሱ ነውርን ን፣ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧልና” (ዕብራውያን 12፥2)። ለመሆኑ እስከ መጨረሻው የደገፈው ደስተኝነት ምን ነበር? የእርሱ ደስታ፣ በእግዚአብሔር እንዲደሰቱ ለማድረግ ከሞተላቸው አምልኮን መቀበሉ ነው። መልካሙ እረኛ በጠፋው በግ ደስ ይለዋል (ማቴዎስ 18፥13)። በተዋጁት በማይቈጠሩት ሠራዊት ደግሞ ምንኛ ይደሰት!

ከዚህ እኛ መከራን እንዴት መቀበል እንዳለብን የሚያስተምረን ነገር ይኖር ይሆን? የጌታን መከራ ብቻ ሳይሆን፣ ደስታውንም መከተል እንዳለብን አስተውለዋልን? [ሐዋርያው] ጳውሎስ ለተሰሎንቄውያኑ፣ “ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፤ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ” (1ኛ ተሰሎንቄ 1፥6) ይላቸዋል። ይህችን አዲስ ቤተ ክርስቲያን የሞላት በስቃይ ውስጥ የነበረው የጌታ ደስታ ነበር።

ይህ አሁንም ለእኛ ጥሪ ነው። ክርስቶስን ለማግኘት መከራን እንቀበል ይሆን? ደስታ የለሽነትን ሳይሆን፣ መከራን። የዕብራውያን 11፥13፣ “በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፤ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን።” የሚለው ጥሪ ጆሯችን ይሰማልን? መልሱ ከሰው ልጆች ከተማ ይልቅ የእግዚአብሔርን ከተማ ይበልጥ ናፋቂዎች በመሆናችን ውስጥ ነው። “በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፤ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን።” (ዕብራውያን 13፥14) ብለን መልስ እንሰጥ ይሆን? ወይስ ዐላፊ የሆነው የግብፅ ደስታ ላይ አሁንም ተንጠላጥለናል (ዕብራውያን 11፥25-26)?

የኢየሱስን ደስታ የቀመሱት፣ “መልካም፤ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ … ወደ ጌታህ ደስታ ግባ።” (ማቴዎስ 25፥21) የሚለውን በድንቅ ተስፋ የተሞላ የመጨረሻ ቃሉን ከመስማት የሚበልጥ ምንም ነገር የለም። የእግዚአብሔር ከተማ፣ የደስታ ከተማ ነው። እርሱም፣ የኢየሱስ የማይናወጥ ደስታ ነው።

ጸሎት

አባት ሆይ፤ አንተና ልጅህ በጭራሽ ስሜታዊና ኮስታራና አለመሆናችሁ ለእኛ ትልቅ መጽናኛችን ነው። በስቃያችን እየራራህልን ወሰን በሌለው ደስታ ውስጥ የመሆንህ እውነት ያስደስተናል። የኢየሱስ የደስታ ብርሃን ዕንባ በሸፈነው ፊቱ ላይ ቀስተ ደመና መፈጠሩ ያስደንቀናል። እኛም እንደዚህ እንድንሆን እንናፍቃለን። በእምነታችን ውስጥ ባለው ደስታችን ብርቱና የማንናወጥ መሆንን እንፈልጋለን። ይህም ሆኖ፣ የራሳችንን ኀጢአት አሳዛኝነትና የሌሎችን የስቃይ ሕመም ልንረሳ አንሻም። አምላክ ሆይ፤ የልጅህ ደስታ ለእኛም እንዲሆን ቃል ገብተህ፣ ደስታችንን ሙሉ አድርገህ፣ እርሱ የመጣበትን ዐላማ በእኛ ፈጽመው። የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ደስታ፣ በሕይወታችን እንዲያብብ አድርግ። በፍቅርህ እንድንደሰትና በአንተም ሐሴት እንድናደርግ፣ ጽኑ የሆነውን የፍቅርህን ርካታ በንጋት ስጠን። የተኙትን ነፍሶቻችንን ከድንዛዜ እንቅልፋቸው ቀስቅስልን። የልባችንን በራድ ወይም ትኵስ አለመሆንን አንሣልን። ለስምህ ክብር እንዲሆን የቅንኣት ነበልባልን አቀጣጥለው። ዕለት ተዕለት የእርሱን ደስተኛ አምሳል እንድንመስል፣ ክርስቶስ ከማይናወጠው ደስታው ጋር በእኛ እንዲኖር አድርግ። በኢየሱስ ክርስቶስ በኵል የሚገኘውን የአምላክን ክቡር ደስታ ለተራቡ ሰዎች፣ እንዲሁም ተስፋ ለሌለውና ደስታ ፈላጊው ዓለም መጠለያና ዘላለማዊ መጽናኛ እንድንሆን አድርገን።
ይህንም በስሙ ጸለይን። አሜን።

  1.  John Piper, “Seeing and Savoring Jesus Christ, (Desiring God Foundation: 2004), pp.34-40.

Amare Tabor


አማረ ፈቃደ ታቦር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በስታትስቲክስ፣ ሁለተኛውን በኮምፒውተር ሳይንስ የሠሩ ሲሆን፣ መጻሕፍትን የማንበብ ልምድና የመተርጎም ዝንባሌ አላቸው። በተለይ በክርስትና ዙሪያ የተለያዩ መጣጥፎችን በመጻፍና በመተርጎም ይበልጥ ማገልገልን ይሻሉ። 
E-mail: taboramare@gmail.com

Share this article:

መከራው እስካለ

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ እንደ ሆነች እየታየኝ ነው። መከራው ግን ስውር ነው። . . . ስደትን የወንጌላውያን ብቻ አድርጌ ሳስብ መኖሬና ቀድሞ ዘመን ‘ባደረገችው ነገር እግዚአብሔር እያስተማራት ይሆን እንዴ?’ የሚለው መልስ የማይፈልግ ጥያቄዬ ነበር። ይሁን እንጂ፣ እየሆነባት ያለው ከስደት ጋር አንድ መሆኑን በጭላንጭልም ቢሆን . . . እየተረዳሁት ነው።” ባንቱ ገብረ ማርያም

ተጨማሪ ያንብቡ

የክርስቶስ ወንጌል እና ሳምራውያን

“እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሓደ፣ በዐዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፣ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስ ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ፣ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፣ ጥልንም በመስቀል ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” (ኤፌ. 2፥14-18)።

ተጨማሪ ያንብቡ

የማይናወጥ ሐሴት

“እግዚአብሔር አምላክህከጓደኞችህ ይልቅበደስታ ዘይት ቀባህ፥”ዕብራውያን 1፥9 “መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ …ወደ ጌታህ ደስታ ግባ:”ማቴዎስ 25፥21 የማይናወጥ ሐሴትየኢየሱስ ክርስቶስ ደስታትርጕም በአማረ ታቦር ከከፋ አደጋ ያዳኖት

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.