[the_ad_group id=”107″]

ለክቡር ጥሪ የሚመጥን ክቡር ሕይወት

አንዳንዶች ሰዎች በሕይወታቸው ትርጉም ላለው፣ ብሎም ዓላማቸው ላደረጉት ጉዳይ እስከ ሞት ሊደርስ በሚችል መከራ ውስጥ ያልፋሉ፡፡ ማዕበሉ የሚንጥና የሚያንገላታ ቢሆንም፣ የሕይወት ምስቅልቅሎሹ ቢበረታም ዓላማቸውን ግን የሙጥኝ ይላሉ፡፡ በእውነቱ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ተፈትነው ያልተረቱና የማይናወጥ ጠንካራ ሰብዕናን የተላበሱ ናቸው፡፡

በክርስትና ሕይወታችን ለተጠራንለት የከበረ ሕይወት የሚመጥን ኑሮን መኖር መለኮታዊ ትእዛዝ ነው፡፡ የክርስትና ሕይወት  መሥዋዕትነት የተከፈለበት በመሆኑ ዋጋው እጅግ የከበረ ነው፡፡ አማኒያን የሆንን እኛ ምንም ዋጋ ሳንከፍል ወይም በማመን ብቻ ያገኘነው በመሆኑ ይህንን ሕይወት እንደ ቀላል ነገር ልንቆጥረው የተገባ አይደለም፡፡ እጅግ ለከበረው ለዚህ ሕይወት የሚመጥን የጽድቅ ኑሮን ለመኖር ደግሞ በዚህ ዓለም ምናምንቴ የማይሸረሸር የጀገነ ልብ ያሻናል፡፡ ለዓላማው ጨክኖ የሞተ ብርቱ ጌታ ስላለን እኛም ደግሞ ለተጠራንለት የሕይወት ዓላማ ለመሞት የተዘጋጀን ልንሆን ይገባል፡፡ ለመሆኑ ለዚህ ለተጠራንለት የከበረ ሕይወት እንደሚገባ ለመኖር አስፈላጊና ዋነኛ የሆኑ ነገሮች ምንድናቸው?  ከኤፌ4፥1-5፥4 ላይ ሁለት ነገሮችን እመለከታለን፡-

1. አንድነት 41-16

እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ፦

ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ

ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።

በዚህ ክፍል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን አማኞች አስቀድሞ የሚናገረው “በተጠራችሁበት ጥሪ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ…” የሚል ነው፤ ይኸውም ስለ ቅዱሳን ኅብረትና አንድነት ነው፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ መለያየትንና ጥላቻን ደምስሶ አንድ አዲስን ሰው ወይም መሲሐዊ ማኅረ ሰብን በራሱ ፈጥሯል (2፥14)፤ ይህንን ማኅበረ ሰብ መጠበቅ የሚቻለው ደግሞ በቅዱሳን አንድነት ነው፡፡ እኛ ዛሬ የምንፈጥረው አዲስ አንድነት የለም፤ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ጨርሶታልና፡፡ የተሰጠንን አንድነት የመጠበቅ ኀላፊነቱ ግን የእኛ ነው፡፡ የዚህ አዲስ ማንነት መታያው ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ከነገድና ከቋንቋ በደሙ ታጥበውና የኀጢአትን ስርየት አግኝተው የተሰበሰቡ ቅዱሳን መገኛ ናት፡፡

ታዲያ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ማናቸውም ዐይነት ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ የቅዱሳን ትጋት መጨመር እንዳለበት ይመክራል፡፡ አያይዞም ይህንን አንድነት ለመጠበቅ የምንችልባቸውን መንገዶች ያሳያል፡-

  • አንድነታችን በተለወጠ ባሕርይ ላይ የተመሠረተ ነው፤ በትዕግስት፣ በፍቅርና በትኅትና እንዲሁም አንዳችን ከሌላው ጋር በሚኖረን ግንኙነት በመቻቻልና በመረዳዳት በመኖር (ቁጥር 2) አንድነታችን ይጠነክራል፤
  • አንድነታችን በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፍጹም አንድነት ላይ የተመሠረተ ነው (ቁጥር 3-6)፤ ይህንንም ስንል ወደ አካሉ ያስገባን አንድ መንፈስ (መንፈስ ቅዱስ)፣ ተስፋውን ይዘን ያመንነው አንድ ጌታ (ክርስቶስ) እንዲሁም ሁሉ አባት የሆነና በሁሉ የሚሠራ አንድ አምላክ (እግዚአብሔር) ነው፡፡ ይህ ለአንድነታችን ምሳሌያችንም መሠረታችንም ነው፡፡
  • አንድነታችን በተለያዩ ስጦታዎች የበለጸገ ነው (ቁጥር 8-16)፤ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣው ጌታ ለቤተ ክርስቲያን (ለመሲሑ ማኅበረ ሰብ) ሎሌ የሆኑ መሪዎችን እንደ ስጦታ ሰጥቷል፤ በዚህም ምክንያት ሰዎች ሁሉ ወደ ሙላቱ ልክ ደርሰው ጌታን ያውቁት ዘንድ ፈቃዱ ሆኗል፡፡

እንግዲህ ጸሐፊው የሚነግረን ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ በከበረ ደሙ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን ወደ እርሱ ሙላት ልክ እንድታድግ የአማኒያን አንድነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡

በርግጥ ይሄ ምሥጢር ምን ያህል ገብቶን ይሆን? አንድነታችንንስ ለመጠበቅ ምን ያህል እንተጋለን? የአንድነታችን ጉዳይ ለአፍታ ልንዘነጋው የማይገባና እስከሞት ድረስ እንኳ ዋጋ ልንከፍልለት የተገባ ነው፡፡ ያለንበት ዘመን ሲመዘን ግን ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት የራቀ ይመስላል፡፡ ለአንድነትና ለኅብረት ከሚከፈል ዋጋ ይልቅ፣ ስለገዛ ፍላጎትና ጥቅም የሚሮጠው ሩጫ ብዙ ሆኖ ይታያል፡፡ ስንቶቻችን ነን በዘር፣ በጎጥ ተከፋፍለንና ጎራ ለይተን በክርስቶስ ሞት የተገኘውን የተቀደሰ አንድነት በዐመፅ ሰይፍ የምንቆራርጥ? አንዳንዶች ቤተ ክርስቲያንን ከባለቤቱ ከክርስቶስ ነጥለው የራሳቸው አድርገዋል፤ ራሳቸውንም ከሌላው የተሻሉ አድርገው በመቁጠር የቅዱሳን ኅብረት ፀር ሆነዋል፡፡ ኀያሉ እግዚአብሔር ከወንድሞች ፍቅር፣ በክርስቶስ ሥራ ከተገኘው አንድነትና ኅብረት ፈጥኖ ከሚነጥል ሐሳብም ሆነ ግብር በምሕረቱ ይከልለን፡፡ አሜን፡፡

2. ቅድስና (4፥17-54)

እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ። እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ። እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥  ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።

ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።

እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ፥ ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ። ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ፥ ይልቁን ምስጋና እንጂ።

የተጠራንበት ሌላው ዋነኛው ዓላማ በቅድስና ለመኖር ነው፡፡ የጠራን እርሱ ቅዱስ ስለሆነ እኛም በእርሱ መንገድ እንድንሄድና ለእርሱ ብቻ እንድንሆን እንጂ በአስተሳሰባቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱት አህዛብ እንዳንኖር ይመክረናል፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር ሕልውና ውጭ ያሉና ልቦናቸው የጨለመ፣ ኅሊናቸውም የደነዘዘ ነው፡፡ ቀድሞ የኖራችሁበትን፣ በእርኩሰትና አጉል ምኞት የረከሰውን የአሮጌውን ሰው ልምምድ አውልቃችሁ ጣሉና አዲሱን ሰው ልበሱ ይላል (ቁጥር 24)፡፡ ይሄ አዲሱ ሰው እግዚአብሔርን ለመምሰል የተፈጠረና እውነተኛ የሆነውን ጽድቅና ቅድስናን የሚሻ አዲስ ማንነት ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከአሮጌው ማንነት ተለይቶ ጽድቅን የሚከተል ሰው ሊያደርጋቸው የሚገቧቸውን ተግባራት ምን እንደሆኑ ያሳያል፤ እነዚህም፡-

  • ውሸትን በማስወገድ እውነትን መነጋገር፤
  • በቁጣችን ኀጢአትን አለመሥራት፤ ይልቁን ፈጥኖ መታረቅ፤
  • ስርቆትን መተውና በገዛ እጅ መልካምን ሥራ ሠርቶ ሌላውን መርዳት፤
  • ከንቱ ንግግርን ማስወገድና ሌሎችን የሚያንጽ ንግግር መናገር፤
  • መራርነትና ቁጣን፣ ጭቅጭቅንም አስወግዶ ቸርና ሩኅሩኅ መሆን፤
  • ከዝሙት ጋር የተያያዘ ፌዝና ዋዛ፣ ንግግርንም ትቶ ጌታን ማመስገን ናቸው፤

እንግዲህ በዚህ ክፍል መሠረት ለእርሱ ብቻ የተቀደስን መሆናችን የሚታየው እነዚህን ተግባራት መፈጸም ስንችል ብቻ ነው፡፡ ቅድስና በክርስትና ሕይወታችን ለአፍታ እንኳን ልንዘነጋው የማይገባ የሕልውናችን መሠረት ነው፡፡ ቅድስና ጌታን የምናይበት መነፅራችንም ጭምር ነው፡፡ ቅዱሱ ጌታችን ባልተቀደሰ ማንነት ፈጽሞ አይሠራምና ለሚቀድሰው ጌታ ራሳችንን አሳልፈን እንስጥ፡፡ ካለንበት ንጹሕ ያልሆነ ሕይወት ጎትቶ እንዲያወጣን የጌታን ክንድ እንማጸን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ወደ መንፈሳዊ ብልጽግናና ጌታን ወደሚያስከብር ልምምድ ውስጥ መግባት የምትችለው ንጽሕናዋን የጠበቀች እንደ ሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ፈጽሞ ልንዘነጋው አይገባም፡፡ ውሸትን፣ ተንኮልንና የማያንጽ ንግግርን ከሰፈራችን አርቀን እንጣልና ገርነትና የዋህነት ያለበትን መልካሙን ሥራ ለመፈጸም እንትጋ፡፡ ለዚህም የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ልባችን ይበርታ፡፡

የጌታ ጸጋ የበዛልን ይሁን!

Share this article:

ይህን ማንነቴን ምን ልበለው?

ባንቱ ገብረ ማርያም በዚህ ዐጭር ጽሑፋቸው፣ የሕይወታቸውን ዙሪያ ገባ ይቃኛሉ፤ ቃኝተውም አንድ መለያ ብቻ የሌለው ማንነት የተጎናጸፉ መሆኑን ይገነዘባሉ። አንድ ጥያቄ ግን ማንሣታቸው አልቀረም፤ “ይህን ማንነቴን ምን ልበለው?” የሚል።

ተጨማሪ ያንብቡ

“የክርስቲያን ሚዲያዎች ሲታዩና ተግባራቸው ሲገመገምም አብዛኛዎቹ አንባቢውንም ሆነ ተመልካቹን የማይመጥኑ…ሆነው እናገኛቸዋለን” – ቃለ መጠይቅ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር

ሚክያስ በላይ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡን በሚመለከት ስለ ኮሙኒኬሽንና የመገናኛ ብዙኅን አጠቃቀም፣ አብያተ ክርስቲያናት ከኅብረተ ሰቡ ጋር ስላላቸው መስተጋብር እንዲሁም በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያንን አመራር ጋር ሊያያዙ በሚችሉ ጭብጦች ዙሪያ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

እግዚአብሔር – አለ!

“የሰላም መረበሽና የፍትሕ ቀውስ እየከረረ በመጣበት በዚህ ዘመን፣ እንደ ክርስቲያን ተስፋ የምናደርገው የታሪክን አቅጣጫ በልጓም የያዘውን ልዑል እግዚአብሔርን ነው።” መጋቢ ግርማ በቀለ (ዶ/ር) “እግዚአብሔር አለ!” በተሰኘው በዚህ ዐጭር አጽናኝ መልእክት ያስተላለፉትን ያንብቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.