[the_ad_group id=”107″]

“የዘመናችን” ቤተ ክርስቲያንና የተሐድሶ ጥያቄ፦ ተግዳሮቶችና ዕድሎች!

በሄኖክ ሚናስ

በመጀመሪያ “የዘመናችን” ቤተ ክርስትያን ስንል ምን ማለታችን ነው? እንደ አዲስ ኪዳን አቀራረብ ከሆነ፣ ቤተ ክርስትያንን በድፍን ቅሉ በዘመንና በአገር በሚያኽሉ ሰፋፊ ዳርቻዎች መከፋፈል አልተፈቀደም ወይም ትርጕም አይሰጥም። ምንም እንኳ ቤተ ክርስቲያን እንደ ክርስቶስ አካል አጽናፈ ዓለም (Universal) የሆነ ገጽታ ቢኖራትም፣ ጳውሎስ ለምሳሌ በሮሜ፣ በቆሮንቶስ፣ በገላትያ፣ በኤፌሶን፣ በፊልጵስዩስ፣ በቈላስይስ፣ በተሰሎንቄ፣ ወዘተ. ከተሞች ለነበሩ ቤተ ክርስቲያኖች በ‘ምላጭ’ ትኵረት በመልእክቶቹ ጊዜ ወስዶና ጕዳያቸውን በሚገባ ተረድቶ በእርጋታ ሊያበረታቸው፣ ሊያስተምራቸው፣ ሊያቀናቸው፣ ሊገሥጻቸው ይሞክር እንደ ነበር ከመጽሐፍ ቅዱስ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በአብዛኛው ማስረጃዎቻችን ናቸው።

የቤተ ክርስቲያንን የተሐድሶ ጥያቄ በተመለከተ ደግሞ ስንለጥቅ፣ በአዲስ ኪዳን የምናገኘው አንዱ ወሳኝ ምሳሌያዊ አቀራረብ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእዩ መጽሐፍ ምዕራፍ ሁለትና ሦስት ላይ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ከጌታ ተቀብሎ መልእክትን ያስተላለፈበት መንገድ ነው። ምንም እንኳ ለሁሉም የተላኩት መልእክቶች በማጠናቀቂያቸው፣ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን፣ ጆሮ ያለው ይስማ የሚል ማሳሰቢያ በመኖሩ ቢያመሳስላቸውም፣ ጌታ ኢየሱስ ለእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ራሱን የገለጠበት መንገድ ልዩ ልዩ ነበር። ለምሳሌ፣ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን “ሰባቱን ከዋክብት በቀኝ እጁ የያዘው፣ በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚመላለሰው” ሲል፣ ለሰምርኔሷ ደግሞ “የመጀመሪያውና የመጨረሻው፣ ሞቶም የነበረውና ሕያው የሆነው” እያለ ለሰባቱም ራሱን በልዩ በልዩ መንገድ ይገልጻል።


የቤተ ክርስቲያን
ተሐድሶ ጥያቄ ከመቼ ጀምሮና ለምን?

በዮሐንስ ራእይ የተጠቀሱት ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በአብዛኛው የሚያመሳስላቸው ከጌታ ኢየሱስ መንፈሳዊ አቅጣጫን (spiritual direction) በሦስት መልኩ መቀበላቸው ነው። እነዚህም፣ ማጽኛ ውዳሴ (affirmation)፣ ነቀፋና የተግሣጽ ቃል (correction) እንዲሁም ቃል ኪዳን (promises) ናቸው። “የመጀመሪያውም የመጨረሻውም እኔ ነኝ፤ እኔ ሕያው ነኝ…” ብሎ ራሱን በራእይ ምዕራፍ አንድ ላይ ከገለጠው ጌታና መድኃኒታቸው መንፈሳዊ አቅጣጫን (spiritual direction) ሰባቱም አብያተ ክርስቲያናት አግኝተዋል ማለት ነው።

በመጀመሪያ የተወደሰው የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ለምሳሌ፣ “ሥራህን፣ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ። ክፉዎችንም ችላ ብለህ እንዳላለፍሃቸው… ደግሞም በትዕግሥት መጽናትህንና ስለ ስሜም መከራ መቀበልህን ዐውቃለሁ፤ በዚህ ሁሉ አልታከትህም።” ተብሎ ተመስክሮለታል፤ ሰምርኔስ መከራን በመቀበል ውስጥ በመጽናቱ ተሞግሷል። በተጨማሪ ጴርጋሞን “ስሜን አጥብቀህ ይዘሃል” ሲባልለት ትያጥሮን ደግሞ “ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ ዐውቃለሁ።” ሲል ጌታ አወድሶታል። በመሆኑም ሰርዴስና ሎዶቂያ ሲቀሩ ሌሎቹ ዐምስቱ አብያተ ክርስቲያናት ውዳሴን ወይም ምስጋናን ከጌታ ተቀብለዋል።

ነቀፋን ወይም የተግሣጽ ቃልን በተመለከተ ደግሞ፣ ከሰምርኔስና ከፊላደልፊያ በስተቀር ሌሎቹ ዐምስቱ አብያተ ክርስቲያናት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተሐድሶ የሚያስፈልጋቸው ሁኔታ ላይ እንደ ነበሩ በግልጽ የሚያመለክቱ ውድቀቶቻቸው ላይ ነቀፋ ተሰንዝሮባቸዋል። እንዲታረሙ ሲል ጌታ የሰጣቸው ትዕዛዛት (corrective disciplines) አሁንም ለእያንዳንዱ አብያተ ክርስቲያናት የተለያየ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ መንፈስ ቅዱስን ጥለው በአምልኮ መልክ ብቻ እርቃናቸውን የቀሩ በመሆናቸው በዋናነት ይመሳሰሉ ነበር። ኤፌሶን “የቀድሞውን ፍቅርህን ትተሃል” ተብሎ ሲነቀፍ፣ ጴርጋሞን በመካከሉ ሥር የሰደደውን የኑፋቄ ትምህርቶችን በመታገሱ ተወቅሷል። በተጨማሪም ትያጥሮን ነውርንና ርኵሰትን ችላ ብሎ ነበርና ተግሣጽ ደርሶታል፤ ሰርዴስ ለሞት በመተኛቱ፣ ሎዶቂያ ደግሞ “ለብ ያልህ ብቻ እንጂ ትኵስ ወይም ቀዝቃዛ ስላልሆንህ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው” በመባሉ፣ ስለዚህም በአጓጉል ለብታነት ወይም በለዘብተኝነት እጅግ ተነቀፉ። እንግዲህ ሰባቱ አብያተ ክርስትያናት ከጌታ የሰላ ተግሣጽን ሲቀበሉና ለተሐድሶ ሲጠሩ የአዲስ ኪዳንም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገና ኀምሣ ዓመታት እንኳን አልሞላውም ነበር። እንግዲያውስ ለቤተ ክርስቲያን የተሐድሶ ጥሪ መድረስ  የጀመረው ገና የመጀመሪያው ክፍለ ዘመንም ሳያበቃ ጀምሮ ነበር ማለት ነው።

በመጨረሻም በማጽኛ ውዳሴ (affirmation) የሚጀምሩትና በተግሣጽ ቃል (correction) የሚያርሙት እነኚህ የሐዋርያው ዮሐንስ መልእክቶች ለሰባቱም አብያተ ክርስቲያናት በሦስተኛ ደረጃ ተስፋን (promises) ሲሰጡ እናያለን። ምንም ዐይነት ውዳሴ፣ ምንም ዐይነት ተግሣጽና ነቀፋ ያለ አትጊ (motivating) ቃል ኪዳን እና ተስፋ በዘላቂነት ገንቢ ሊሆን አይችልም። ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠው ተስፋ የዘላለም ሕይወት ሆኖ፣ ለእያንዳንዱ ግን በተለያየ ምሳሌ የተገለጸ ነበር። ለኤፌሶን “የሕይወት ዛፍ”፣ ለሰምርኔስ “የሕይወት አክሊል”፣ ለጴርጋሞን “ነጭ ድንጋይ”፣ ለትያጥሮን “የንጋት ኮከብ”፣ ለሰርዴስ “ነጭ ልብስ”፣ ለፊላደልፊያ “የቤተ መቅደስ አምድ”፣ በመጨረሻም ለሎዶቂያ ከክርስቶስ ጋር እራትን መብላትና ከእርሱ ጋር በዙፋኑ ዐብሮ መቀመጥን ቃል ሲገባላቸው እናያለን።

ዛሬም እያንዳንዱን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጌታ እንዲህ በቅርበት ያውቃቸዋል፣ ይመረምራቸዋል። እንደየመንፈሳዊ ቁመናቸው እያወደሰ ያበረታቸዋል፤ እየወቀሰና እየነቀፈ ተስፋን ይለግሳቸዋል። ውድቀት ላይ ስላሉ ብቻ ስለ ስሙ አጥብቀው የያዙትን በተመለከተ ከማመስገን አይሰስትም። አንዳንዶቹ ከውድቀታቸው የተነሣ ተስፋ የሌላቸው ቢመስሉ እንኳ፣ ተግሣጹንና ምክሩን እየሰጠ ተስፋን ያስታጥቃቸዋል እንጂ ወርውሮ አይጥላቸውም። ጌታ ለእያንዳንዱ በየአካባቢው ለሚገኝ ቤተ ክርስቲያን በቂ ትኵረት፣ ጊዜና ጸጋ አለው። በዐይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር “የተራቆተና የተገለጠ” (ዕብ. 4፥13) የሆነለት ሕያው ጌታ፣ ስለ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የሚያስመሰግን ብርታት ያውቃል፤ የሚያስነቅፋቸውን ድካምና ውድቀትም መርምሮ ይለያል። እንዲሁም ለሁሉም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይሰጣል (Peterson, 1988)

ስለዚህም አንድ ነገር አሥምረን እንለፍ፦ አጕል ችኩሎችና ደፋሮች ካልሆንን በቀር፣ ‘የዘመኗ ወይም የአሁኗ ቤተ ክርስቲያን’ ብለን በጣም ትርጕም ባለው መንገድ (meaningful) እና አዲስ ኪዳናዊም በሆነ መንገድ ተግዳሮቶችንም ሆነ ዕድሎችን ማንሣት አይቻልም እንኳ ባይባል፣ በጣም ጥንቃቄንና ትኵረትን የሚጠይቅ እንዲሁም በከፍተኛ የኀላፊነት ትጋት በበሳል ሰዎች ሊደረግ ብቻ የሚገባው ነው። በርግጥ እንደ ወንጌል አማኝነታችን ከወንጌላውያንም ሆነ ከመላ በክርስትና ጥላ ሥር ካሉ ሁሉ ጋር በአንድነት የሚመለከቱንና የሚያገናኙን ፈተናዎችና ዕድሎች በየጊዜው ይኖራሉ። ነገር ግን፣ እንደ አንድ አማኝ ለእያንዳንዳችን በጣም ወሳኙ ነገር መሆን ያለበት በሰማያዊው ጎዳና እንደ ቅዱሳን ማኅበር ዐብረውን እንደ ቤተ ሰብ የሚጓዙት፣ ሕይወትንም በቅርበት የሚካፈሉት የየአካባቢያችን ወይም የኅብረታችን ወንድሞችና ቶች ናቸው።


የቤተ ክርስቲያን
ተሐድሶ እንዴት?

ተሐድሶ ያስፈለገው ውድቀትና ሽንፈት ስላለ ነው። መነቃቃት ያስፈለገው መታለልና ማንቀላፋት በየዘመኑ ያለች ቤተ ክርስቲያን በየአካባቢዋ ፈተናዋ ስለ ሆነ ነው። ስለዚህ በውድቀት ወስጥ ሳለን፣ በዐመፅ ወይም በቸልተኝነት አንቀላፍተን እንዳንቀር ተሐድሶና መነቃቃት በየቤተ ክርስቲያኖቻችን እንዲመጣ ምን እናድርግ? ተቃራኒ ቢመስሉም እንቅልፍና ተሐድሶ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ። በየዕለቱ ዐልጋዎቻችን ላይ ማታ ስንተኛ ምንድን ነው የምናደርገው? በየተቀመጥንበት እንተኛለን? ጋደም ብለንስ ሌሊቱን እናነጋለን? ርግጠኛ ነኝ፤ አናደርገውም! የምናደርገው ዐልጋችን ውስጥ በተለመደ የምንተኛበት ሰዓት እንገባለን፤ ብርድ ልብሳችንን እንለብስና እንቅልፍ እስኪወስደን አነሰም በዛ እንጠብቃለን። ሁልጊዜ በተመሳሳይ ደቂቃና ሰከንድ እንቅልፍ ባይወስደንም በተኛንበት እናሸልባለን፤ ራሳችንን ለእንቅልፍ አመቻችተን እንጠብቀዋለን፤ እንቅልፍም አባብሎ ይወስደናል። ተሐድሶ መቼና በምን መልክ፣ ማንን ተጠቅሞ እንደሚመጣ አናውቅም፤ ነገር ግን በሕያዉ ጌታ ምክርና ቃል መሠረት እየተዘጋጁ፣ በጸጋው ኀይል እየበረቱ የያዙትን ሳይለቅቁ፣ ነቀፌታችንን እያስወገዱ፣ በዘላለም ሕይወት ተስፋ ሁልጊዜም መጠባበቅ ይቻላል። በልዩ የሚነጥቅ ዐይነት አውሎ ነፋስ ጌታ በምንተጋበት ሥፍራ ይመጣል። የዘገየ ቢመስለንም እንኳ ቀኑንና ሰዓቲቷን እርሱ ያውቃልና እንደ ማለዳ ፀሓይ እስኪመጣ ከነቢዩ ኢሳይያስ ጋር እንዲህ እንላለን፦

እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም። ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጕልበት ይጨምራል። ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ። እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ አይደክሙም።(ኢሳ. 40፥28-31)

መነቃቃት ያለ ተሐድሶ!

እዚህ ጋር አንድ ነገር መለየት ይኖርብናል፦ መነቃቃት (revival) እና ተሐድሶ (renewal or reformation) የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በርግጥ በተሐድሶ ውስጥ መነቃቃት መኖር አለበት፤ መነቃቃት ስላለ ብቻ ግን ተሐድሶ ልንለው አንችልም። የሚነቀፍ ነገር ያለባቸው አብዛኞቹ እነኚያ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በቅድሚያ መነቃቃት ሳይሆን፣ ሥር ነቀል ተሐድሶ ነበር የሚያስፈልጋቸው። ያለ ተሐድሶ፣ ያለ መነቃቃት ንስሓ የሌለበት፣ መታዘዝ ችላ የተባለበት፣ እውነት በፊደል ቅርጹ ብቻ የቀረበት፣ ሰዋዊና ምድራዊ፣ ሲብስም አጋንንታዊ ይሆናል። ተመልከቱ! አሁን አብዛኞቹ የቆዩትም (mainline churches) ሆኑ፣ ዘበናዮቹ “ቤተ ክርስቲያኖች”፣ በተለይ በአውሮጳና ከአንዳንድ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖች አንጻር በልዩ መነቃቃት ላይ ያሉ ነው የሚመስለው።

በእኛ አገር በብዙ ትላልቅ ከተሞቻችን ውስጥ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ሰዎች ይጎርፋሉ! አዳዲስ አማኞችም በብዛት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደሚፈልሱና እንደሚድኑም ይነገራል። ይዘመራል፣ ይጨፈራል! (ምንም እንኳ ብዙ ቦታ እንደ ዳንኪራ ቤቶች ተቈጥረን የአካባቢው ነዋሪዎችን ከማስቆጣትም ወርደን ተንቀን ብንተውም) የቀደሙት የሸራና የድንኳን የአምልኮ መሰብሰቢያ መጠለያዎቻችን ወይም አክርሚኞቻችን (መክረሚያዎቻችን) አሁን በሰፋፊና ጌጠኛ አዳራሾች እንዲሁም ሕንጻዎች እየተተኩ ነው። ከፍተኛ መነቃቃት ላይ ያለን ነው የምንመስለው። እስልምና አገራችንን ጨምሮ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች በከፍተኛ መነቃቃት ላይ ነው። ግብረ ሰዶማዊነት ከምዕራቡ ዓለም ዐልፎ አሁን አሁን በበለጸጉ የእስያ አገሮችም ውስጥ በከፍተኛ መነቃቃት ላይ ነው። መነቃቃት አጃቢ የበዛለት፣ አያሌ ገንዘብንና ሀብትን የሚጠቀም፣ ምንም የሞራልና የእውነት አቅም ሳይኖረው የሰዎችን የወደቀ ማንነት ተከትሎ በአንድ ሰሞን የሚጎርፍ የጥፋት ጅረትም ሊሆን ይችላል ማለት ነው (Tozer, 1988)።

በአንጻሩ ደግሞ የአንድ ዘመን የተሐድሶና የመነቃቃት ታሪካቸው አመድ ለብሶ የምናገኛቸው፣ በተለይም ደግሞ በአውሮፓ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያኖች ናቸው። አገራትን የለወጠ ረጅም ክርስቲያናዊ ታሪክ ያላቸው በአውሮፓና በተለያዩ አገራት ከተሞች ከተገነቡ እጅግ ብዙ መቶ ዓመታት የሆናቸው፣ በጣም የተዋቡ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች በአሁኑ ጊዜ ወና የጎብኚዎች መዳረሻ ብቻ ሳይሆኑ ወደ ምሽት ክበብ ቤት፣ ምግብ ቤት፣ አንዳንዶቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና ወደ መስጊድነት ጭምር እየተለወጡ መሆኑን ሰምተን ይሆን?[1] በሰሜን አሜሪካ ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ግዙፍ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች የተለያየ ከፍተኛ ወጪያቸውን ለመሸፈን በመቸገራቸው ዕዳ ውስጥ እየተዘፈቁ መቸገራቸውንም እንሰማለን። ለምሳሌ፣ በሰሜን አሜሪካ በዕዳ ጫና ሥር የወደቀ የአንድ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ የሆነ ሰው ስለ ጕዳዩ ሲጠየቅ፣ “ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን አይሠራም። የምንቀጥለበትን መንገድ እናገኛለን።” ሲል መናገሩ ተዘግቧል።[2]

ከአውሮፓውያኑና ከሰሜን አሜሪካውያኑ በተቃራኒ መልኩ ጨቋኝ መንግሥታት ባሉባቸው ለምሳሌ በቻይና፣ በኢራንና በሰሜን ኮርያ ቤተ ክርስቲያን ትጋቷንና ጥራቷን ጠብቃ፣ ውስጥ ለውስጥ እያደገችና እየሰፋች ያለችው ያለ ምንም ሕንጻ በቅዱሳን ንጹሕ ፍቅርና እውነተኛ ኅብረት በህቡዕ ነው። በመሆኑም፣ ሕንጻ ለቤተ ክርስቲያን ዋና እና የግድ እንዳልሆነ ምስክሮች ናቸው። የቤተ ክርስቲያን መውደቅ ወይም መነሣት ዋና ምክንያት ቅዱሳን ራሳቸው እንጂ መንግሥታት ወይም ሌላ ውጭያዊ ኀይልና ምድራዊ ነገሮች አይደሉም ማለት ነው።[3] በተጨማሪም፣ እነኚህ በጨቋኝ መንግሥታት ሥር ያሉ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያኖች ለአደባባይ ያልበቃ፣ በድብቅ የሆነ መነቃቃታቸውን እየጠበቁ መጓዝ እንጂ የተሐድሶ ጥያቄ ውስጥ እንኳ የገቡ ናቸው ለማለት ይከብዳል።

የእግዚአብሔርና የሰው ሚና ለተሐድሶ

የተሐድሶንና የመነቃቃትን ልዩነትና አንድነት እንዲህ ካስቀመጥን፣ ለተሐድሶ የእግዚአብሔርንና የሰውን ሚና ልዩነት እንመልከት። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ “ደቂቀ እስጢፋኖስ” በተሰኘው ታዋቂ መጽሐፋቸው ላይ፣ “አሕይዎና (ወይም መነቃቃት ልንለው እንችላለን) ተሐድሶ (Revival and Renewal or Reformation) ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠው ሥርዓት (Establishment) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥዎ ካላቸው ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሐሳቦች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ‘መለወጥ አለበት’ የሚሉትን ለመለወጥ ቆርጠው ሲነሡ ደግሞ ታላቅነታቸው ወደ ገናናነት ያድጋል። ትውልድም አገሪቱ የነጻ ሐሳብና የምርምር ሰዎች እንደነበሯት ሲያውቅ ይኮራል።” (ጌታቸው፣ 2010) ብለው በመጽሐፉ መግቢያ ላይ የጻፏት የአንቀጽ ክፍል፣ በአንዳንድ የወንጌላውያንና ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም በሚነሡ የቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ናፋቂዎች ትጠቀሳለች።

ፕሮፌሰሩ ተሐድሶ የሚያስፈልግበትን ምክንያት “ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠው ሥርዓት (Establishment) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ የሚያይበማለት በጥሩ ቢገልጹትም፣ ጕዳዩን ሁሉ ግን በሰው የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥዎ ላይ ማድረጋቸው የእግዚአብሔርን ዋነኛ ሚና የሚያሳንስ ይመስላል። ተሐድሶን የሚቀጥር፣ የሚቀሰቅስ፣ የሚጠብቅና የሚያበዛ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። የክርስቶስ ሙሽራ ቅንነቷ፣ ንጽሕናዋ፣ ተልእኮዋ ተጠብቆ እንዲኖር ክርስቶስ ራሱ በመንፈሱ ሁልጊዜ ሊያድሳት ይቀናል፤ ይሠራል። ከእኛ የሚጠበቀው ከላይ እንዳልነው ራሳችንን በትጋት እያዘጋጁ መቆየትና መጠባበቅ ብቻ ነው።

ስንጠብቅ ግን ምን እናድርግ? የእግዚአብሔር ሚና እንዳለ ሁሉ የሰውም ሚና አለ። በተለይ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከተከሰቱ እውነተኛ የተሐድሶና የመነቃቃት ወቅቶች የእኛን ሚና ማንሣትና ዘመናችንን መፈተሽስ ይቻል ይሆን? አዎን ይቻላል! ሪቻርድ ላቭሌስ የተባለ አንድ የሥነ መለኮት አጥኚ ሰው፣ የቤተ ክርስቲያንን የተሐድሶ ታሪክ በስፋት አጥንቶ ያቀረበው ጠቅለል ያለ የተሐድሶ ማዕቀፍ (model or framework) በጥቂቱ ምን ምን ነገሮችን ቤተ ክርስቲያን በጥንቃቄ ልትጠብቅ እንደሚገባ መንገድ ጠቋሚ ነው (Lovelace, 1979)። ይህ ሰው ያቀረበውን ሙሉውን መዋቅር ሳይሆን ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው ጥቂት ስናነሣ የየቤተ ክርስቲያኖቻችንን አኗኗርና አገልግሎቶች መፈተሻ መነጽር አድርገን የሚከተሉትን ዋና ዋና የተሐድሶ አላባውያን/መዋቀሪያዎች መውሰድ ይቻላል፦

የማይቋረጥ ተሐድሶ ቅድመ ሁኔታዎች (preconditions of continuous renewal)ለወንጌል መልእክት ዝግጁ መሆን

 1. ፈርሃ እግዚአብሔር (awareness of the holiness of God)፦ የእግዚአብሔርን ጽኑ ፍርድና ብርቱ ፍቅር በሚገባ መረዳት፤
 2. በግልም ሆነ እንደ ማኅበር በጋራ የኀጢአታችንን ግዝፈትና ጠንቀኛ መዘዝ መረዳት (awareness of the depth of sin)፤

የማይቋረጥ ተሐድሶ ቀዳሚ አላባውያን/መዋቀሪያዎች (Primary conditions of continuous renewal) ወንጌልን በጥልቀት መረዳት

 1. በክርስቶስ መጽደቅ (justification)፦ ከክርስቶስ የተነሣ እግዚአብሔር እንደተቀበለን መረዳት፤
 2. በክርስቶስ መቀደስ (sanctification)፦ ከክርስቶስ የተነሣ ከኀጢአት እስራት ነጻ መሆን፤
 3. የመንፈስ ቅዱስ ዐብሮነትና ሙላት (the indwelling Spirit)፦ ከክርስቶስ የተነሣ በምድር ላይ ብቻችንን እንዳልተተውን መረዳት፤
 4. ለመንፈሳዊ ውጊያ የተሰጠ ሥልጣን (authority in spiritual conflict/warfare)፦ ከክርስቶስ የተነሣ በጨለማው ኀይል ላይ ሥልጣን እንደተሰጠን ማወቅ፤

የተሐድሶ ሁለተኛ አላባውያን/መዋቀሪያዎች (Secondary elements in Renewal) የወንጌል ይል በቤተ ክርስቲያን ሲገለጥ

 1. ተልእኮ፦ በማኅበራዊ ጕዳዮች ተሳትፎና በምስክርነት ክርስቶስን ለዓለም ማቅረብ፤
 2. ጸሎትና አምልኮ፦ በግልም ሆነ በጋራ እግዚአብሔርን እያመለኩ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል፣ በጸሎትና በምልጃ የእርሱን ጣልቃ ገብነት በየሁኔታዎች ሳይታክቱ ማቅረብ፤
 3. የቅዱሳን ማኅበር፦ በአውራ ጕባኤዎችም ሆነ በንዑሳን ማኅበሮች ከክርስቶስ አካል ጋር ኅብረትን ማድረግ፤

እነዚህ የተሐድሶ መሠረታዊ አለቶችና መዋቀሪያ ጡቦች፣ እያንዳንዳቸው በብዙ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ ችግር ላይ እንዳሉ የሚካድ አይደለም። የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ አስፈሪነት፣ ጻድቅ ፈራጅነት፣ አፍቃሪነት፣ ወዘተ. ምን ያህል ጊዜ እንሰማለን? የሰውን የኀጢአት ክብደትና መዘዝስ ከስንት ሰባኪ እንሰማለን? ጽድቅን ስለምናገኝበት የክርስቶስ መስቀል፣ በእግዚአብሔርና በዓለም ፊት በንጽሕናና በቅድስና ስለመኖር፣ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ታጥቆ፣ በስጦታዎቹም ተሳስሮ እንደ አንድ አካል ስለመገንባት ስንት አስተማሪዎች ያስተምራሉ? ስለ መንፈሳዊ ውጊያና በአጋንንት ሥራ ላይ ድልን ስለ መቀዳጀት? በመንፈስ ቅዱስ አሠራሮች ዙሪያ በየቤተ ክርስቲያኑ ጤናማ ልምምዶችስ ምን ያህል ናቸው? እነኚህ ሁሉ ብዙ ውጥንቅጣቸው የወጣና የምንሸማቀቅባቸው ጕዳዮቻችን ናቸው፤ የምንነቀፍባቸውም ነጥቦች ናቸው። ተግዳሮቶቻችን ናቸው።

ቅርብ የተሐድሶ መነሻ ዕድል

“ዕድሎቻችን ያሉት ታድያ ምኑ ጋ ነው?” ብሎ አንድ ሰው ግራ በመጋባት ሊጠይቅ ይችላል። ዕድሎቻችን እያንዳንዱ አማኝ በቅርብ በእጆቻችን ካለው፣ ቀጥለን ወዲያውኑ ወይም ዛሬ ምሽት ልናደርግ ከምንችለውና ከሚጠበቅብን የእምነት እርምጃና መታዘዝ የሚጀምር መሆን ይኖርበታል። ስለ ኀጢአታችን ግዝፈትና ስለ እግዚአብሔር ጽኑ ፍርድ የሚሰብኩንን እንደ ካቶሊኩ ቄስ ማርቲን ሉተር ወይም እንደ ጆናታን ኤድዋርድስ ዐይነት ያሉ ታላላቅ የተሐድሶ አውራዎችን የግድ ሁልጊዜ የሚጠይቅ አይደለም። መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በተለያየ መንገድና ሰዎች እየተጠቀመ ሰዎችን ከኀጢአት ይታደጋል። ስለ እግዚአብሔር ብርቱ ፍቅርም ሆነ በክርስቶስ የመስቀል ሥራ በኵል ስለሚገኝ ጽድቅና ቅድስና እንዲሁም ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች፣ እንደ ክርስቲያኖች በጨለማ አሠራር ላይ ስለተሰጠን ሥልጣን አጥብቀው ሳያዛንፉ የሚገልጡልንና የሚያስተምሩን የወንጌል ሰባኪዎችና አስተማሪዎች በየመድረኮቻችን በጣሙኑ ያስፈልጉናል። ቍጥራቸው ይነስ እንጂ ዛሬም በየቦታው አሉን። ነገር ግን፣ የክርስትና ኑሮና ምልልስ በወንጌል ሰባኪዎችና በእግዚአብሔር መንግሥት አስተማሪዎች ላይ የተወሰነ አይደለም፤ ሊሆንም አይገባም። 

ስለዚህ ለማይቋረጥ ተሐድሶ በእጃችን ያለ የቅርብ መነሻ ዕድላችን ምን ላይ ነው ያለው? እላይ ለተሐድሶ መዋቀሪያ ከተዘረዘሩ ነጥቦች ውስጥ በሁለተኛው የተሐድሶ አላባውያን ሥር በመጨረሻ የተቀመጠውና ብዙውን ጊዜ ዋጋውን አሳንሰን የምናየው ከቅዱሳን ማኅበር ጋር ተያይዞ ያለው ጕዳይ ከፍተኛ ትኵረት የሚሻበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የክርስትና ጕዟችንንና መላ ማንነታችንን በተለያየ አቅጣጫ ቅርጽ በማስያዝ ከሆነ፣ ከቅዱሳን ጋር ያለ ቤተ ሰባዊ ማኅበር የላቀ ዋጋ እንዲሰጠው ያደርገዋል። በተጨማሪም እንደ ክርስትያን አማኞች የተቀበልነውን ክቡር ጸጋ ‘ከንቱ’ የማድረግና የማቃለል ፈተና ውስጥ ስለመውደቃችን በግላዊነት የተሞላውና ውድቀት የዋጠው ኑሯችን ያሳብቃልና ነው (2ኛ ቆሮ. 6፥1)። አስቀድሞ በእግዚአብሔር ቤት ጌታ ከሰጠን ወገኖች ጋር፣ በመቀጠልም በዓለም ካሉ ሰዎች ጋር  በተለያየ መንገድ ያሉን ግንኙነቶች እውነተኛ መንፈሳዊነትን የምንለማመድባቸውና ጸጋውን ሥራ ላይ የምናውልባቸው ጎዳናዎች ናቸው። ለምሳሌ የወንጌል ተልእኮ ብዙውን ጊዜ ለውጪው ዓለም ብቻ እንደ ሆነ ስለምናስብ፣ ወንጌልን ይዞ ወደ ውጭ መሮጥን ቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ ሰጥታ ስትተጋበት ትታያለች። ነገር ግን፣ “ታላቁ ተልእኮ” የሚመነጨው ከ“ታላቁ ትዕዛዝ” መሆኑን እንዘነጋለን። “… ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ” ያለው ጌታ አስቀድሞ፣ “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዞች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” (ማቴ. 22፥37-40) ሲል አስረግጦ ነግሮናል።

በቅዱሳን መካከል የቤተ ሰባዊ ንዑሳን ማኅበራት ወሳኝነት

በመሆኑም በክርስቶስ ያገኘነውን ድነትን ማጽናትና መንፈሳዊ ስጦታዎችን በአግባቡ መለማመድ እውነተኛ መንፈሳዊነትን በመከታተል የሚመጡ ናቸውና እውነትን የምንነጋገርባቸው፣ በጸሎትና በምልጃ የምንሸካከምባቸው፣ ያለንን ሁሉ በበጎነትና በቸርነት የምንከፋፈልባቸው፣ እውነተኛ ፍቅርን የምንለማመድባቸው ንዑሳን ማኅበሮች እውነተኛ የመታደሻችን ምንጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ አድምቀን እናሥምርበት። ከውጭ ተልእኮ ባልተናነሰ፣ ምናልባትም በበለጠ መንገድ የውስጥ ተልእኮ (internal mission) ሁላችንም አለብን፤ በተለይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አለባቸው። ወጣቶቻችን ከታላቅነት ይልቅ መልካምነትን፣ ከታይታና ችኩልነት ይልቅ ታማኝነትን እንዲማሩ ከአዋቂዎችና ከእኩዮቻቸው ጋር በአንድ መካከለኛ የቤተ ሰብ ቍጥር ልክ እያዘወተሩ ኅብረትን እንዲያደርጉና ከጕባዔ ወጥመድ እንዲድኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኀላፊነት አለባቸው። ሁላችን በመጨረሻ ከጌታ መስማት የምንፈልገው “አንተ በጎና ታማኝ ባሪያ” የሚለውን ድምፅ መሆን አለበት።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተጨማሪ ኅብረቶችን የሚመሩ፣ የሚያስተባብሩ፣ የሚመግቡ፣ በሙሉ ልባቸው ራሳቸውን ያቀረቡ ወጣቶችን ማሠልጠንና ማብቃት ይጠበቅባቸዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ አለ፦ “እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል።”  (1ኛ ጴጥ. 4፥10-11) ታማኝነት፣ ልዩ ልዩ ጸጋ፣ መጋቢ፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ማገልገል የቅዱሳን ሁሉ ክህነት (The Priesthood of all saints) ከተሐድሷዊው የማርቲን ሉተር ጽንሰ ዐሳቦች አንዱ የነበር ቢሆንም፣ ይኸውና እስከ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የምትቸገርበት ጕዳይ እንደ ሆነ ቀጥሏል።

ስለዚህ ትርጕም ባለው ሁኔታ ግድ ልንሰኝና ልንተጋ የሚገባው ስለየትኛው ቤተ ክርስቲያን ይመስላችኋል? ስለ የትኛው ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ነው አስቀድመን ልንቀና የሚገባው? በውስጡ ስላለንበት፣ ስለምንኖርበት፣ እንደ ቤተ ሰብ ስለቀረብነው ቤተ ክርስቲያን ነው መሆን ያለበት። ቤተ ክርስቲያናችን የምንለው በሕንጻዎቿ በትልቅ ቍጥር የምንሰበሰብባት፣ በአዳራሾቿ የምናመልክባት፣ በመድረኮቿ የምናገለግልባት፣ ዐሥራት የምናወጣላት አውራ ጕባዔ (macro-community) ብቻ ሆና፣ በውስጧ እንደ ወንድምና እኅት፣ እንደ ቤተ ሰብ የምንቀርባቸው፣ ኀጢአታችንን የምንናዘዝባቸው፣ ደስታችንንም ሆነ ፈተናዎቻችንን የምንካፈልባቸው፣ ቅዱስ ቃሉን የምንመረምርባቸው፣ ፍቅርን፣ ይቅርታን፣ ትሕትናን፣ በጎነትን፣ የዋህነትን፣ እውነተኛ መንፈሳዊነትን የምንከታተልባቸው፣ የምንለማመድባቸው ንዑሳን ማኅበሮች (micro-community) ከሌሉበት በጣሙኑ ከስረናል። በንዑሳን ማኅበራት ነዶ ታስሮ ያልጠበቀ የአውራ ጕባዔ መስክ፣ ብቻውን ቤተ ክርስቲያን ለመባል ብዙ ርቀት ይቀረዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ተያይዞም በቤተ ክርስቲያን ኑሯችን ውስጥ ልናዘወትር፣ ልንተጋበትና በቀዳሚ ትኵረት ልናደርጋቸው የሚገቡንን ትጋቶች (regular and frequent church practices) ዐልፎ ዐልፎ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ  ማድረግ ከሚያስፈልጉን እንቅስቃሴዎች (occasionally and as needed events) መለየት የግድ ይለናል። አለበለዚያ በጋራ የመንፈሳዊ ምልልሶቻችን ውስጥ ፍሬ የሌለበት ወይም ኪሳራ የበዛበት መንፈሳዊ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች ልናበዛ እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች ሲጽፍ ምን አለ?

አንተ የተኛህ ንቃ፤

ከሙታን ተነሣ፤

ክርስቶስም ያበራልሃል ተብሏል።

እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ። በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና። በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም።  በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ አመስግኑ። ለክርስቶስ ካላችሁ አክብሮታዊ ፍርሀት የተነሣ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ።(ኤፌ. 5፥14-21)

ዛሬ የምንባክንባቸው ‘መጠጦቻችን’ ምን ይሆኑ? የሙዚቃ መሣሪያዎች ብዛትና ዐይነት? አዳራሾች? ሕንጻዎች? መድረኮች? ምርጥ ምርጥ (‘ሐዋርያትና ነቢያት’ ተብዬዎች) የምንላቸው አገልጋዮች? ፈውስና ታምራት? የመሳሰሉት፣ እንጃ! እንጠያየቅበት። ነገር ግን የጤንነታችን ወሳኙ መፈተሻ እነኾ፦ “በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችን ከመነጋገር አንጉደል! የጥበብን መንገድ ለመምረጣችን ማሳያ ሌላ አትፈልጉ፤ ለክርስቶስ ካላችሁ አክብሮታዊ ፍርሀት የተነሣ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ።እርስ በእርስ በተቀደሰ ማኅበር ዐብሮ መኖርንና መተናነጽን እንወቅ!

ማጠቃለያ

ስናጠቃልል ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በሐዋርያው ዮሐንስ እንደተጻፉት መልእክቶች ባለ መንገድ በተሟላ ጥናት ወይም በልዩ መገለጥ ባይሆንም፣ በምናባዊ ምሳሌነት ከከተሞቻችን በአንድ አካባቢ ለሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ቢጻፍ ከሞላ ጎደል የማይመለከተው ቤተ ክርስቲያን ይገኝ ይሆን? በምናባዊ ስሌት የተከተበ መልእክት መሆኑ ሳይዘነጋ፣ ይህ መልእክት የተጻፈለት ቤተ ክርስቲያን ለምሳሌ በሳሪስ አንድ ልዩ አካባቢ ያለ እንደ ሆነ እናስብ፤ በውስጡ እንደምትገኙ ወጣቶችና አዋቂዎች እንዲሁም ሌሎች አማኞች ራሳችሁን በመቍጠር በዋናነት ስለየቤተ ክርስቲያናችሁ እየቀናችሁ፣ አስቀድመን እንዳየነው የያላችሁበትን የየራሳችሁን ድል፣ ነቀፋና ተስፋ እንድትመረምሩ ዐደራ በማለት በ‘ሳሪስ’ አካባቢ ላለችው ምናባዊ ቤተ ክርስቲያን በተጻፈው መልእክት እንቋጭ።

ሳሪስአካባቢ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ (ወይም መልእክተኛ) እንዲህ ብለህ ጻፍ

በትንኤውና በአብ ቀኝ ክብሩ የምታዩትና የምትወዱት ነገር ግን እንደ ተሰቀለ ሆኖ በፊታችሁ ሊሳል የሚገባው የሰው ልጅ ኢየሱስ እንዲህ ይላል

መንፈሳዊ ቅናትህን፣ ሕጻናትና ወጣት ልጆችህን በሚገባ መንከባከብህንና በጸሎት የሚተጉ እናቶችን ማበረታታህን፣ ለመንፈስ ቅዱስ በርህን ወለል አድርገህ መክፈትህን እነህን ሁሉ ዐውቃለሁ። ለጠራ የወንጌል እውነትና ለሚድኑ ነፍሳት የምታሳየውም ትጋት ከፊቴ የተሰወረ አይደለም።

ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ለመንፈሳዊ ስጦታዎች እንጂ አስቀድመህ ለእውነተኛ መንፈሳዊነት በበቂ አልቀናኽምና የምገጽህ ነገር አለኝ። ከታላቁ ዛዝ ይልቅ ታላቁ ተልኮን ማስቀደመህ ከፈረሱ ጋሪውን እንደማስቀደም ሆኖብሃልና የፍቅር ድካምን እንድትጨምር፣ የእምነት ሥራን እንድታዘወትር፣ የታይታና የችኩልነት ትህን ጣጥለህ የታማኝነትን ካባ ከእኔ እንድትገዛና እንድትለብስ ዝሃለሁ። ትልቅነትንና ስምን ከሚያስቀድሙ አትዋል፤ መልካምነትን ገንዘብህ አድርግ። የመጨረሻው ከጌታ አምላክህ ልትሰማው የምትቀናለት ድምፅ፣ አንተ ታማኝና በጎ ባሪያ፣ ወደ ጌታህ ዕረፍት ግባየሚለው ይሆንልህ ዘንድ የተገባ አልነበረምን? የሚዘወተሩና የሚተጋባቸውን መንፈሳዊ ሩጫዎች አስቀድም። ወደ ያትር ቤት ለመዝናናትና ለአስተያየት እንደሚጎርፍ ሕዝብ አድርገህ የእግዚአብሔርን መንጋ አታቅልል፤ ይልቁኑ እንደ ወንድማማቾችና ትማማቾች እንዲኖሩ ማደራጀትን ተማር። በተኩላዎች መካከል ድል እንዲበዛልህ የዋኾችን አትናቅ፣ ብልኾችንም ጠቢባን የሆኑትንም ፈልግ። ያን ጊዜ እንደ ሞት በበረታ፣ እንደ መቃብር በጨከነ የፍቅር ቅንዓት የተባረከ ትውልድ ከመካከልህ አስነለሁ።

መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፤ ድል ለሚነሳውም ሕያንና የጠራውን ምንጭ ከሆዱ አፈልቃለሁ! መንፈሴንም ሳልሰፍር አፈስበታለሁ።

አሜን!

ዋቢ መጽሐፍት

Lovelace, Richard F. (1979). Dynamics of Spiritual Life: An Evangelical Theology of Renewal. Exeter, U.K.: The Paternoster Press.

Peterson, Eugene H. (1988). Reversed Thunder: The Revelation of John & the Praying Imagination. San Francisco: Harper & Row .

Tozer, A. W. (1988). Keys to the Deeper Life. Michigan: Zondervan.

ጌታቸው ኃይሌ (2010). ደቂቀ እስጢፋኖስ፡በሕግ አምላክ“. አዲስ አበባ: አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ.


[1] Underhill, W. (2007, Feb. 12). Good God! Why Europe is turning Churches into Gyms, Pizzerias and Bars. Newsweek, 50.

[2] Banjo, S. (2011, January 25). Churches Find End Is Nigh: The Number of Religious Facilities Unable to Pay Their Mortgage Is Surging. Retrieved from The Wall Street Journal: http://online.wsj.com/article/SB10001424052748704115404576096151214141820.html?mod=WSJ_hp_MIDDLENexttoWhatsNewsSecond

[3] Gospel Fellowships (2013). Principles for the gathering of believers under the headship of Jesus Christ. -:-.

Henok Minas

ሔኖክ ሚናስ ከኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት (EGST) Post-Graduate Diploma በTheology and Biblical Studies የተቀበለ ሲሆን፣ በUK Italy እና Sweden ከሚገኙ ሦስት የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች በStrategic Project Management የMaster of Science ዲግሪውን አግኝቷል። የመጀመርያ ዲግሪውን ደግሞ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ተቀብሏል። ሔኖክ በማኅበራዊና አገራዊ ጕዳዮች፣ እንዲሁም ወንጌላውያንን በሚመለከቱ ጕዳዮች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ዐጫጭር ጽሑፎችን የሚጽፍ ሲሆን፣ ለአነስተኛ ክርስትያናዊ ማኅበራት ጥቅም ላይ የሚውሉ የጥናት መንፈሳዊ መጻሕፍትንም ይተረጕማል፣ ያዘጋጃል። በሥራው ዓለም ደግሞ በተለያዩ መንግሥታዊ፣ የግል እና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ሠርቷል። በአሁኑ ጊዜ፣ በቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት (TBI) በአፍሪካ ኅብረት በተቋቋመው ለአፍሪካ CDC የዴሊቨሪ አማካሪና የፕሮግራም ኀላፊ ሆኖ እየሠራ ይገኛል።

Share this article:

እሣቱ በጭስ እንዳይታፈን

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ዕድገት የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ ወንጌላዊቷ ቤተ ክርስቲያን ስትተከል፣ ስታብብና ስትጎመራ፣ ፍሬም ማፍራት ስትጀምር የዕርሻው ባለ ቤት እግዚአብሔር አብሯት ነበር፡፡ ከታየው ዕድገት ጀርባ የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ጌታ ክርስቶስ በሰጣቸው ጸጋ ብዙ የደከሙ ታማኝ አገልጋዮቹ ነበሩ፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን እዚህ እንድትደርስ ማዕረግ ያላቸውም ይሁኑ፣ ስም ያልወጣላቸው፣ ታሪክ የዘከራቸውም ይሁኑ እርሱ አንድዬ ብቻ የተመለከታቸው ብዙ የወንጌል አማኞች አሉ፡፡ እነሱ የከፈሉት ዋጋ በላይ በሰማይ፣ በከበረው መዝገብ ሰፍሯል፡፡ በዚህ ሁሉ ግን የመንግሥቱ ንጉሥ፣ የቤቱ ጌታ፣ የሥራው አለቃ እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይሁን!

ተጨማሪ ያንብቡ

ኢየሱስ ይልቃል

“ኢየሱስ ይልቃል” የተሰኘው ይህ ጽሑፍ በዕብራውያን መልእክት ላይ መሠረቱን ያደረገ ሲሆን፣ የመልእክቱ ማጠንጠኛ “በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” በሚለው ሐሳብ ላይ የሚመሠረት መሆኑን ጸሐፊው ሳምሶን ጥላሁን በሚከተለው ፍታቴው ያስቃኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ

One Nation of Sisters and Brothers

In this article, Dr Desta Heliso discusses shared national identity – an identity that formed the current Ethiopia. He argues that Ethiopianness is a unifying state of mind developed by people of different ethnic groups, cultural backgrounds and religious persuasions.

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

 • የጥንት መዛግብት ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ተከስቶ ስለ ነበረው ተሐድሶ በፃፉት ላይ አምስት ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፦ 1/ ግብጽ፣ ነገረ መለኮት (ከ1943 እስከ 1949 ዓም) ተምረዋል፤ ከዝነኛው ቱቢንገን ዩኒቨርሲቲ ጀርመን በ1954 ዓም በፒኤችዲ ተመርቀዋል። ከኦርቶዶክሱ ሌላ ስለ ፕሮቴስታንት ሪፎርሜሽን ጥሩ ግንዛቤ እንዳላቸው ግልጽ ነው 2/ The Missionary Factor in Ethiopia መጽሐፍ ላይ (እ አ አ 1996) ለፕሮቴስታንት ሚሲዮናውያን/አማኞች ያላቸውን አሉታዊ ሚዛን (በሌሎች ጽሑፎቻቸው ጭምር) አልደበቁም 3/ ፕሮፌሰሩ፣ “የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥዎ ካላቸው ታላላቅ ሰዎች” ሲሉ ጀርመናዊውን ፕሮፌሰር (ቄስ) ማርቲን ሉተርን ሳያስቡ አይደለም (ሉተር የተረጎመው የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ የታተመው እ አ አ በ 1591 ቱቢንገን ነበር) 4/ በተሐድሶ ቲኦሎጂ የሚመሩ አብያተ ክርስቲያናት ዛሬም “በአእምሮ ችሎታ እና ተሰጥዎ ባላቸው ታላላቅ ሰዎች” እንደሚመሩ እያየን ነው (ለመንፈስ ቅዱስ ልምምድ እና ለወንጌል ስርጭት ያላቸውን “አናሳ” አመለካከት መታዘብ ይቻላል) 5/ “ደቂቀ እስጢፋኖስ” ላይ (1996 ዓም ታተመ) ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከፕሮቴስታንቱ ተሐድሶ በሠላሳ ዓመት ቀድማለች የሚል አሳብ ሠንዝረዋል። ለቤተ እምነታቸው ማድላታቸው አይደንቅም። ትኩረቱ ግን፣ አንተም እንዳነሳኸው፣ የመቅደምና ያለመቅደም ሳይሆን፣ የክርስቶስን ፈቃድ ተረድቶ መፈፀም ላይ ነው።

  “መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በተለያየ መንገድና ሰዎች እየተጠቀመ ሰዎችን ከኀጢአት ይታደጋል … በጋራ የመንፈሳዊ ምልልሶቻችን ውስጥ ፍሬ የሌለበት ወይም ኪሳራ የበዛበት መንፈሳዊ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች ልናበዛ እንችላለን” እናስተውል ያልከው ጥሩ ትዝብት፣ ጥሩ እርምት ነው። ይህም በአእምሮ መታደስን ማደግን እንደማይቃረን፣ ጌታን ተግተን እንድናገለግል እና ይህን ዓለም እንዳንመስል ያስተምረናል።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.