[the_ad_group id=”107″]

ይህን ማንነቴን ምን ልበለው?

አስቀድሞ የእግዚአብሔር ሰላም ይድረሳችሁ። ለማንነታችሁ ስም ለመስጠት እንደ እኔ ተቸግራችሁ ይሆን? አርሲ ተወለድሁ፤ የልጅነትና የወጣትነት ዕድሜዬን በባሌ አሳለፍሁ። በዚያን ጊዜ በክርስቲያንና በሙስሊም መኻል ጋብቻ አይኑር፣ የቀብርና የአምልኮ ሥፍራ ይለያይ እንጂ በጡት ጥቢ በመዛመድ፣ ጅጌና ወንፈል በመሳሰለው ተጋግዞ በመሥራት፣ ያለው ለሌለው በማሟላት (በመዋዋስ) የባሌ ኗሪዎች በፍቅር እንኖር ነበር። ሁላችንም “እጆሌ ባሌ” በመባባል የአንድ ወንዝ ልጆች ሆነን የምንታወቅ ነበርን። እኔ አካባቢውን ከለቀቅሁ በኋላ፣ እንደውም “ደርግ” በመንደር ምሥረታ አንድ ላይ ያሰፈራቸው ጊዜ የክርስቲያኑና የሙስሊሙ ግንኙነት የቤተኝነት ጭምር ሆኖ ነበር። የልጅነቴንና የወጣትነቴን ዘመን ጣፋጭ ላደረገው ለባሌ ሕዝብ ለሙስሊም-ለክርስቲያኑ ምስጋና ይግባውና፣ በባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ጌታ ኢየሱስን የግል አዳኜና ጌታዬ አድርጌ እስከተቀበልኩበት ጊዜ ድረስ ስለማንነቴ የነበረኝ አስተሳሰብ ይኸው “እጆሌ ባሌ” የሚለው ነበር።

ጌታ ኢየሱስን ጌታዬና አዳኜ አድርጌ ከተቀበልሁ በኋላ ግን ማንነቴ በስፋት በሚታወቀው ስያሜው ወንጌላዊ ክርስቲያን ሆነ። ሰዎችንም በጌታ ያሉና በጌታ ያይደሉ በሚል መነጽር ማየት ጀመርሁ። ዘራቸውና ቋንቋቸው እንዲሁም አስቀድሞ የነበራቸው ሃይማኖት ሳይታሰበኝ (እነርሱም የእኔ ይታሰባቸው የነበረ አይመስለኝም)፣ በጌታ የሆኑት ሁሉ ለእኔ ወንድሞቼና እኅቶቼ ሆነው ኖርሁ። ሌላው ቀርቶ የተዋወቅኋቸውን በጣት የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ዜግነት የሌላቸውን ወንጌላውያን አማኞች እንደ ወገኖቼ አየኋቸው። ይህንም ስል በጌታ ያልሆኑትን በክፉ አስባቸው ነበር ማለት አይደለም። በጌታ የሆኑት ሁሉ ግን በሰማይ ባለ ርስቶች፣ ከቅዱሳን ጋራ ባላገሮችና ሰማያዊ ዜጎች ነንና ወገንተኝነቴንና ማንነቴን ከእነርሱ ጋር ሆኖ ተመላለስኩ።

ይህንን ዐይነት አኗኗር ለመጀመሪያ ጊዜ የተለማመድኩት በደቡብ ኢትዮጵያ በ“ዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ” ወቅት እንደ ነበር አስታውሳለሁ። (ለአዲሱ ትውልዳችን የዚያን ዘመቻ ምንነት መግለጥ ያስፈልግ መስሎኛል። ያ ዘመቻ 10ኛ ክፍልና ከዚያ በላይ የነበሩ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችና አስተማሪዎች እንዲሁም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና አስተማሪዎች በገበሬው መኻል ተገኝተው፣ በዝርዝር ተጠቅሰው የነበሩ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ደርግ ያሰማራበት መርሐ ግብር ነበር)። በዚያ ዘመቻ ወቅት እነዚያ የደቡብ ክርስቲያኖች (የሻሸመኔዎቹንና የኮፈሌዎቹን) ጨምሮ የመንፈስ ቅዱስ ሥራን ስላስተማሩኝና ፍቅርን ስላሳዩኝ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወድዳለሁ። በኋላም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ክርስቲያን ኅብረት (EUSCF) አገልግሎትን በተካፈልኩበት ጊዜ ክርስቲያኖቹ እንደ ወንድማቸው ተቀበሉኝ። በፖለቲካ ዶክትሪናቸው ውስጥ “አምላክ የለሽነት”ን ወይም ከ“አምላክ በላይነት”ን የጨመሩበት ወገኖች በግራ በቀኝ በሚያዋክቡበት በዚያ በማይመች ዘመን፣ በክርስቲያን ኅብረት የመኖርን በረከት አካፈሉኝ። በኅብረታቸው ለባረኩኝ ለእነዚያ የዩኒቨርስቲዎችና የነርስ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክርስቲያን ተማሪዎች አድናቆቴን ለመግለጽ ይህን አጋጣሚ በማግኘቴ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል። ተሳክቶልኛል ለማለት ባልደፍርም በዚያን ጊዜ የኑሮ ዘይቤዬን ጌታ እንዳበረታኝ መጠን ከዚሁ ማንነቴ ጋር የሚስማማ ለማድረግ ተጣጥሬአለሁ። በነገራችን ላይ በጊዜው የፖለቲካ ሥራ ይሠሩ የነበሩ እኩዮቼ ላመኑበት ነገር ቢያሰፈልግ ለመገደልና ለመዋጋት የነበራቸው ድፍረትና ዲስፕሊ እስከ ዛሬ ያስደምመኛል። በርግጥ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባለመፈለጋቸው፣ በዚያ የትርምስ ዘመን ብዙ የልጅነት ጓደኞቼን በማጣቴና ስለደረሰውም መጠን የለሽ ጥፋት ዐዝኛለሁ። ዛሬ ላይ ከሆነ አይቀር ምነው ሥራቸውና ፕሮፓጋንዳቸው ለሁሉም ወገን በእኩል የሚያስደስትና በተመዛዘነ ልክ የሚባርክ ውጤት አስገኝቶ ቢሆን ኖሮ እላለሁ።

ከትምህርት ክፍሌ ከተመረቅሁ በኋላም በዚሁ ባደግሁበት ሁል አቀፍ ቤተ እምነት አገልግሎትና ግንኙነት ቀጠልሁ። ለዚህ አንዱ ምክንያት ለሥራ በተመደብኩበት በትግራይ ክፍለ ሀገር፣ ቤተ እምነቴ ማለትም የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን አለመኖሩ ነበር። ምስጋናዬ ይድረሰውና በዚያ የመቀሌ መካነ ኢየሱስ ሆስቴል የተማርኩትን ለማካፈል በር ከፈተልኝ። የመቀሌ ክርስቲያኖችም አድቬንቲስቶቹን ጨምሮ ታናሽነቴን ሳይንቁ የማካፍለውን በትዕግሥት አደመጡ። በዚያን ጊዜ በካልቪኒዝም ትምህርት የፈነጠዝኩበት ጊዜ ነበርና ይኸንኑ ፈንጠዝኛዬን ተካፈሉልኝ። ለዚህም ጭምር ነው የመቀሌን ፕሮቴስታንት አማኞች በበጎ ትዝታ እስከ ዛሬ የማስታውሳቸው። ደግሞም በተከበበች ከተማ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መኖርንና ሁልጊዜ በጌታ ደስ መሰኘትን አሳይተውኛል። እግዚአብሔር ይባርካቸው።

በአዲስ አበባ ተመልሼ በኖርኩባቸው ጥቂት ዓመታት ግን ከሞላ ጎደል በራሴ ቤተ እምነት ተወስኜ አገልግዬአለሁ። በአሁኑ ጊዜ ሁል አቀፍ ቤተ እምነቶች በሚመስሉ ቤተ ክርስቲያኖች እየተገኘሁ የምገለገልባቸው ጊዜያት አሉ። የማንነት ጉዳይ መነሻ ሆኖ የክርስትና ጉዞዬን ካነሣሁ አይቀር፣ በዚህ ጉዞዬ ባለማስተዋል ያሳዘንኳቸው ወይም የጎዳኋቸው ወይም እንደ ጠበቁኝ ሆኜ ያላገኙኝ ቢኖሩ ሁሉንም ይቅርታ እጠይቃለሁ።

በዚህ የክርስትና ጉዞዬ ላይ እያለሁ ወንጌላዊ ማንነቴን እንድመረምረው የተደረግሁባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ትግርኛ መናገር ከሚችል ከአንድ ድንቅ ወንድሜ ጋርና ከተመረቅሁ በኋላ ኦሮምኛ መናገር ከሚችል ከሌላ ቅንና ሰው ወዳድ ወንድሜ ጋር የነበሩኝ ሁለት የግል ጭውውቶች የመጀመሪያዎቹ ናቸው። በእነዚህ ጭውውቶች ምክንያት፣ ‘እነርሱ ዐማራ አይደሉም፤ እኔ ግን ተለይቼ ዐማራ ነኝ’ ማለት ነው የሚል ሐሳብ በአእምሮዬ ተጫረብኝ። ‘በወንጌላዊ ማንነት ውስጥ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ዐማራ ወዘተርፈ የሚባል ሐሳብ አለ እንዴ?’ ብዬም ተገረምሁ። ‘በልጅነቴ ክርስቲያን ስል የነበረውም ስሕተት ነበር ማለት ነው?’ ብዬ ጠየቅሁ።

በኋላ ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም “ዐማራ ማለት ደገኛ ነው” አሉና አሳረፉኝ። ምን ያደርጋል ታዲያ ብዙም ሳይቆይ ፕሮፌሰር መስፍን “ዐማራ የለም” ሲሉ ሰማኋቸው። በዚያን ጊዜ “እንዴት ዐማራ የለም ይባላል?” ብሎ በመደነቅ ሲጠይቅ አንድ ኦሮምኛ መናገር የሚችል የሥራ ባልደረባዬን ሰማሁት። “ዐማራ ነን” የሚሉት ይህን ሲጠይቁ ሳልሰማቸው ይህ የሥራ ባልደረባዬ ሲጠይቀው በመስማቴ፣ ጠላት ፍለጋን ለማክሸፍ ያደረጉት ብልሃት መስሎኝ የፕሮፌሰር መስፍን አባባልን ወደድኩት። ከዚህም የተነሣ ልጆቼ በጠየቁኝ ጊዜ ዘራቸውን አልነገርኳቸውም።

እውነትም ታዲያ ከዚያን ወዲህ ከምሰማቸውና ከማነብባቸው እንደተረዳሁት፣ ዐማራ ማለት ያለፉት የኢትዮጵያ ነገሥታት ዛሬ ላይ ተሁኖ አጉድለውታል ስለሚባለው ሁሉ የሚኮነኑት፣ ነገር ግን ስለሠሩት መልካም ሥራ የማይመሰገኑት ወገኖች በጋራ የሚጠሩበት ስም መስሎ ታይቶኛል። “ቀድመን የሠፈርን ነን” የሚሉ ኋላ የሠፈሩ የሚሏችውን የሚጠሩበት የጥቅል ስም እንደ ሆነ የሚያመለክቱ ድምፆችም በቅርቡ ከአንዳንድ አካባቢዎች ሰምቼአለሁ። ማንነቷን መግለጥ ያልፈለግኋት የተከበረች እኅቴ “ዐማራ ማለት’ኮ ከተሜ ማለት ነው” ስትልም ጆሮዬ ጥልቅ ብሏል። አሁን ደግሞ “ዐማራ አለሁ” ማለት ጀምሯል። በቅንነትና በሐቀኝነት የተናገሩት መሆኑን በማያጠራጥር ሁኔታ አላሳመኑኝም እንጂ፣ በተቃራኒው ዐማራ የለም የሚሉ አዳዲስ ወገኖችም ብቅ ብለዋል።

ወንጌላዊ ክርስቲያን ማንነቴን በደምብ እንድመለከት ያደረገኙን ሌሎች ሁኔታዎች ልጨምር፤ የልብ ጓደኛዬ የነበረ አንድ የኤርትራ ተወላጅ ወንድሜ ከማንም ቀድሞ ‘ኤርትራዊ ነኝ’ ብሎ ሳይሰናበተኝ እንኳ ሲሄድ፣ ከኦሮሞ ወንድሞቼም አንዳንዶቹ የኦሮሞ ቤተ ክርስቲያን እያሉ የቀደመ ኅብረታችንን ሲተውት ወንድሞቼ የጣሉኝ (የራቁኝ) እንደ ሆነ እየተሰማኝ ሄደ። ምንም እንኳ በኅብረታችን የቀጠሉት እልፍ አእላፍ ቢሆኑም፣ ስሜት የሚጎዳው በሚለየው ሆኖ ነው መሰለኝ ፣ እኔም ወደ ዘር ማንነቴ ለመሰብሰብ ከጀለኝ።

እነዚህ ልምምዶቼና ግንኙነቶቼ ሁሉ ስለማንነቴ ያለኝን ሐሳብ በመቅረጽ ላይ ሳሉ በቅርቡ በነበረ ልቅሶዬ ምክንያት አንድ ተጨማሪ ነገር አስተዋልሁ። አያቶቼና ልጆቻቸው በሕይወት የሉም። የልጅ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ልጆች ከሆኑት ብዙዎቹ ግን ከተለያየ ቦታ በመምጣት በዚያ ልቅሶዬ ላይ ተገኝተው ነበር። ለካንስ ከዐሥራ ሁለት ነገድ (ብሔረ ሰብ) ሰዎች ጋር በመዋደድና በመመራረጥ ተጋብተውና ወልደው አጎት፣ የአያት ወንድምና የእነዚህ ሁሉ የሥጋቸው ክፋይ አድርገውኛል። እኔም ያገባኋት ባለቤቴ ከራሴ ነገድ አይደለችም። ልቅሶው ላይ ሁሉም ዘመድ ስላልተገኘ እንጂ “እኛ የአንድ አያት ልጆች” ምናልባት ከዐሥራ ሁለቱ ነገዶች በተጨማሪ ከሌሎች ነገዶች ጋርም የተዋለድን ሊሆን ይችላል። በሃይማኖት በኩልም ኦሮቶዶክስ፣ ወንጌላዊ ክርስትና፣ ሙስሊምና ከእነዚህ የማይመደቡ ሃይማኖቶች ያሏቸው ይገኙባቸዋል።

ለካስ በእነዚህ ተወላጆቼ ሳቢያ እነዚህ ሁሉ ዘመዶቼ ሆነዋል፤ እኔም ዘመዳቸው ሆኜአለሁ። ልማታችንም ጥፋታችንም ተቆራኝቷል። ሁሉም የምቆረቆርላቸውና የሚቆረቆሩልኝ፣ ሰለ እነርሱ ኀላፊነት የሚሰማኝ ስለ እኔም ኀላፊነት የሚሰማቸው ሆነናል። ይህ ኀላፊነት “በዘራቸው ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት በማንም ወገን በጉልበት ወይም በሸፍጥ እንዳይዋከቡና እንዳይጠቁ፣ አድልዎ እንዳይፈጸምባቸው መተባበርን፣ በዘሩ ወይም በሃይማኖቱ ምክንያት ማንንም ወገን እንዳያዋክቡና እንዳያጠቁ እንዲሁም በማንም ወገን ላይ አድልኦ እንዳይፈጽሙ ማከላከልን ይጨምራል። ዝምድና እንዲጸና እና እንዲበዛ መሥራትም አለ። በዚህ ዐይነት ሂደት ማንነቴን ልደርስበት ተጋሁ። አዎ፤ ማንነቴ የራሴን “ዘር” ማካተቱ አያጠራጥርም፤ ነገር ግን እነዚህን ዐሥራ ሁለት ባለ ልዩ ልዩ ሃይማኖት ነገዶችንም ይጨምራል። ከራሴ ዘርና ከእነዚህ ነገዶች ጋር ያለኝ ግንኙነት በምን ይለያል? አዎ የራሴን ዘር ነኝ፤ ነገር ግን የእነርሱንም ነኝ። በዚህ ምክንያት እንደዚሁ ለመታወቅ ወድጄአለሁ። ይሁን እንጂ ለዚህ ማንነቴ ስም አላገኘሁለትም። ይህን ማንነቴን ምን ልበለው? ስም በማውጣቱ እባካችሁ ተባበሩኝ።

Bantu Gebremariam

ባንቲ ገብረ ማርያም በፋርማሲ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በፋርማኮሎጂ የማስተርስ ዲግሪ እንዲሁም በቢብሊካል ካውንስሊንግ ማስተርስ ዲፕሎማ የሠሩ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም “Comparative Theology” - “የነገረ መለኮት ንጽጽር” በሚል እንዲሁም “Forgiveness to Let Go” - “ይቅር ማለት- ለመተው ነጻነት” የተሰኙ መጻሕፍትን ወደ አማርኛ መልሰዋል። E-mail: bantge@yahoo.com

Share this article:

የአዲሱ ጅምር “አብዮት” ዕጣ ፈንታ

ምኒልክ አስፋው በዚህ ዘለግ ባለ ጽሑፉ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ክርስቲያናዊ የሆነ ዕይታውን ያካፍላል። በዚህም በተለይ ብዙዎች የሚመኙት “ዴሞክራሲ” እውን እንዲሆን መሠረታውያን ያላቸውን መስፈርቶች ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ጋር እያመሳከረ ምክረ ሐሳቡን ያካፍላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ጥልቅ ዐሳቢው ጳጳስ

ስመ ጥር ካደረጉትና ዝናን ካጎናጸፉት መጻሕፍቱ መካከል፣ “ኑዛዜ” የተሰኘውን ጥራዝ ሳይጠቅስ የሚያልፍ ጸሐፊ አለ ለማለት ያስቸግራል፤ “ጌታ ሆይ፤ ለራስህ ስትል ስለ ፈጠርከን ልባችን በአንተ ላይ እስኪያርፍ ድረስ የትም ይባክናል” የተሰኘውና ተደጋግሞ የሚነሣው ኀይለ ቃልም ከዚሁ መጽሐፍ ነው ተመዞ የወጣው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.