[the_ad_group id=”107″]

“ማን ኦፍ ጋድ” መባል ያማራት ነፍስ

ነፍሰ ጡር ይመስል የማያምረው ነገር የለም፤ የሲዲ ገበያ በደራበት ወቅት ዘማሪ ካልሆንኩ ብሎ እንደ እንጨት መሰንጠቂያ ማሽን፣ እንደ ብረት መሞረጃ ሞረድና እንደ ቮልስዋገን መኪና ዐይነት የሚመስል ድምፅ እያወጣ ጆሮዬን መጫወቻ አድርጎት ሰንብቶ ነበር። ለሳሚ ጠርማሹ ሰቅጣጭ ድምፅ ሲባል “የኮፒ ራይት ጥሰት ዕድሜ ይርዘም!” ማለት ያምረኛል። ትንሽ ቆይቶ ካሴት ቤቶች “ሜሞሪ ላይ መዝሙር እንጭናለን” የሚል ማስታወቂያ ለጥፈው ሞባይል መቸርቸር ሲጀምሩ አምሮቱ ለቀቀውና እረፍት አገኘሁ።

ከሰሞኑ ሁኔታው አላማርኝም። እሱ ግን ያማረው ነገር እንዳለ ከማሳበቅ አልፎ አምሮቱን አፈነዳው፤ “ማን ኦፍ ጋድ መባል አማረኝ” አለ። መቼም ባያምረው ነበር የሚገርመኝ፤ ቲቪ ላይ ማፍጠጥ፣ ኮት በሰደሪያ መልበስ፣ ጸጉሩን እንደ አክሱም ሐውልት ማቆም፣ ድምፁን ማጎርነንና መንጎራደድ አብዝቶ ነበረና። ከሳሚ ሁኔታ በኋላ እነዚህ ምልከቶች የታዩበት ሰው “ማን ኦፍ ጋድ” የመሆን አምሮት ውስጡ እንዳደረበት ከድምዳሜ ላይ ደርሻለሁና ምልክቱ የታየበት ሰው በአጠገባችሁ ያለ እንደ ሆነ በአስቸኳይ ሰፋ ያለ ቤት ፈልጉና አከራዩት። ሰበብ እንዳያገኝ ግን ʻለቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አትንገሯቸውʼ የሚል ማስታወቂያ በየበታው መናገር አምሮኝ ነበር።  ኋላ ግን የአከራያችን ልጆች ገና በዐሥርና በዐሥራ ሁለት ዓመት ዕድሜያቸው እንኳን ምኞታቸው “ማን ኦፍ ጋድ” መባል እንደ ሆነ ሳውቅ ነገሩ እንደ ወረረሽኝ የሚዛመት መሆኑ ገባኝና ተውኩት።

ጩጬዎችን ከሥራ መልስ አስጠናቸዋለሁ፤ እናም አንድ ቀን ወደ ፊት ምን መሆን እንደሚፈልጉ በኩራት ጠየኩ፤ ምክንያቱም አድገው የሀገር መሪ ቢሆኑ፣ ዶክትር ኢንጂንየር ቢሆኑ፣ ተመራማሪ ተቆርቋሪ (ዐርበኛ ወይም የልማት ሠራዊት) ቢሆኑ ʻኮትኩቼ ያሳደኳቸው እኔ ነኝʼ እያልኩ ጉራዬን በየሚዲያው ለመቸርቸር ይመቸኛል ብዬ ነበር። ባቢዬ ግን ቆፍጠን ብሎ “እኔ ማን ኦፍ ጋድ ነው የምሆነው” አለኝ። “ለምን ባቢዬ፤ ማን ኦፍ ጋድ ምን ማለት እንደ ሆነ ታውቃለህ?” “አዎ፤ አዎ አውቃለሁ፤ ማን አፍ ጋድ ከሆንክ ሁሌ በቲቪ ትታያለህ፣ ሰዎችን ትፈውሳለህ፤ በቃ ሀብታም ትሆናለህ”:: እሰይ … ሳሚ ሳለውቀው ደቀ መዝሙር አፍርቶልኝ ኖሯል ለካ።

“አይገርምም?” አልኩት ግርምቴን የሚጋራ መስሎኝ፤ “ምኑ ነው የሚገርመው? እና ዶክተር እንዲልህ ነበር የጠበከው? ቁስል እያጠበ ጄሶ እየቀባና ሆድ እየቀደደ፣ ሃያ አራት ሰዓት እየለፋ፣ ለአቅመ መባ ያልደረሰች ደመወዝ እየተከፈለው እንደ ተራራ የገዘፈውን ይህን ኑሮ ይግፋ ብለህ ትፈርድበታለህ? አሁን ታምሩንና አክሊሉን ተመልከታቸው፤ አክሊሉ በሕክምና ዱክትርናውን ሲይዝ ታምሩ ያችን የምናውቃትን ሥልጠና እንኳን አቋርጦ ነው የወጣው። አሁን ግን ተመልክት በመኻላቸው ያለውን ልዩነት፤ ታምሩ ትናንት የለበሰውን የጣሊያንን ቶክሲዶ ዛሬ አይደግመውም። አክሊሉስ? እንኳን እንዲሁ መንገድ ላይ ሲንከላወስ ይቅርና፣ ጋዋኑን ለብሶ ሰው ቢያየውም ልኳንዳ ዐራጅ እንጂ ዶክተር አይለውም። ታምሩ የሚይዘውን መኪና ብነግርህ ስሙንም አታውቅም። አክሊሉስ? ነጋ ጠባ ሰልፍ፣ ቢሮው ከምታገኘው ሰዓት ይልቅ ታክሲ ተራ የሚገተርበት ጊዜ ይበዛል። አሁን እሱ ምን ልሁን ብሎ ነው ግን እነዚያን እንኳን ተነበው፣ ተቀደው የማያልቁ መጻሕትን የጻፈው? ማን ያውቀዋል? ማንስ ያነብብለታል? ታምሩን ግን ተመልከተው እንኳን ጴንጤው ይቅርና ሌላውም በዝና ያውቀዋል (የሃያ አራት ሰዓት የቴለቪዥን ጣቢያ አለው)። አክሊሉስ? እንኳን በቲቪ እየሰበከ ሊታይ ይቅርና “ጤናዎ በቤትዎ” ላይ ቀርቦም አያውቅም፤ ኸረ እንዲያው ትልቅ ጉባዔ ላይ ሰብኮ ያውቃል?”

ከልቡ እያወራ ስለ መሆኑ ጥርጣሬ ዐድሮብኛል። ሳፈጥበት፣ “የምሬንኮ ነው የምልህ፤ ʻማን ኦፍ ጋድʼ መባል ጥቅሙ የትየለሌ ነው። ተመልከት እኔ ʻማን ኦፍ ጋድʼ ብሆን እንዲህ ቆሞ ቀር እሆን ነበር? በድሮው ዘመንና በአንተ ሒሳብ አንዲት ሴት እንደ እኔ ያለውን ʻማን ኦፍ ጋድʼ የመባል ፍላጎት ያለውን ሰው ብታገባ፣ ሴቶቹ ተሰብስበው ʻእንግዲህ ምን ይደረግ፤ የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልንʼ ነበር የሚሉት፤ ʻብላ ብላ ወንጌላዊ ላይ ወደቀች? ድሮም መራጭ ምራጭ ላይ ይወድቃልʼ እያሉ ይተርቱባታል። ዘንድሮ ግን ሴቷ ሁላ በሚስትህ ላይ እንኳን እየደረብካት፣ ʻምን የመሰለ ዘናጭ ባል አገባች መሰለሽ፤ ብታዪው የራሱ ቸርች አለው፣ የሚይዘው መኪና፣ ጸጋው፣ ፌሙ…ʼ ብቻ ለስሙ ክብር መዘመር ነው የሚቀራቸው።

ʻማን ኦፍ ጋድʼ ብባል ከአንተ ጋር እዚህ ቶንሲሌ እንደ ምላሴ እስኪረዝም ድረስ ስለ ጸጋ ስጦታ፣ ስለ አገልግሎት ሹመትና ስለ ሥነ ምግባር እከራከር ነበር? አልከራከርም።” እራሱ ይጠይቃል እራሱ ይመልሳል። “ማንም አንተን የመያዝ አቅም የለውም፤ ʻጸጋው ምንድነው?ʼ ብሎ የሚጠይቅህ የለም ʻማን ኦፍ ጋድʼ ነሃ። ሰዎች ትሕትና ይመስላቸው ይሆናል፤ ታይትል ምናምን አይፈልግም ይሉሃል። እንዳንተ ዐይነቱ ሥራ ፈት፣ ʻነቢይ ነው? መጋቢ ነው? ወይስ ሐዋርያ?ʼ እያለና መሥፈርት እየደረደረ እንዳያስቸግርህ ʻማን ኦፍ ጋድ ነኝʼ ትላለህ፤ ʻሁሉን ነኝ፣ በሁሉም ነኝʼ እያልክ አፍ ታዘጋለህ። ሁሉን ትመረምራለህ እንጂ በማንም አትመረመርም። ʻተለውሰሃልʼ (“ተፈውሰሃል” ሊል ፈልጎ እውነተኛውን ቃል አለ) ብለህ ሰውዬው ቢሞት አንተ አትጠየቅም፤ በማንም ጎዶሎ እምነት ለምን ብለህ ትጠየቃለህ? አንተ እንደ ሆነ ቃል አውጥተሃል። ማመን ነበረበት! አላየህም እንዴ፤ እንኳን ʻትፈወሳለህʼ ብለኸው ሞቶ ይቅርና፣ ʻየአይጥ መርዝ ብትጠጣ አይገድልህምʼ ብትለው፣ ‘ጠበል ቅመሱልኝ’ ያልህ ይመስል ወደ ሞቱ የሚጣደፍ ስንት አልህ መሰለህ።”

“ፈቃደኛ ሆኖ የመጣን ሰው አድርግ የምትለውን ሁሉ ያደረግልሃል፤ እንደ እረኛ ርኅራኄ ምናመን ብልህ አንገትህን ደፍተህ ብትቅለሰለስ የሚያዝንልህ የለምና ጨከን ማለት ነው ያለብህ። የሚመጣው ሰው አጃቢ እንጂ ቋሚ የቤተ ክርስቲያን አባል ስላልሆነ ስብሰባ እንደ ጠራኸው የቀበሌ ነዋሪ ብታስብ ምንም ማለት አይደለም። ስጦታ ስትሰበስብም እንደ መዋጮ አድርገህ፣ ካልሆነም የፍቅር ስጦታ ብልህ አጣፍጠህ ታራግፈዋለህ። ለምን መሰልህ፤ ይሄ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የወረሰው ወረት የሚባል ቋሚ ቅርስ በልቡ ተሸክሞ ነው የሚያሞቅልህ። ሲዝኑ ያንተ በሆነበት ጊዜ ካልተጠቀምክ ዛሬ መኪናህ ያለፈበትን መንገድ የሳመ፣ ነገ ዘጭ ብትል ‘ተቀላቅሎበታል’ እያለ ደጅህ ላይ ቆሞ መጪውን ይመልሳል።”

“ʻማን አፍ ጋድ ለመባልʼ ነገረ መለኮት መማር አያስፈልግህም፤ ብትፈለግ የተማሩትን ልክ እንደ አንድ ሳንቲም ከገበያ ውጪ ማድረግ ትችላለህ። ʻቃሉ መንፈስ ነው፤ የሚተረጎመውም በመንፈስ ነው። የዛሬ አንድ ሺ ዓመት አንድ መነኩሴ ዋሻ ውስጥ ሆኖ ከጂኒ ይቀበል ከላይ ይቀበል በማይታወቅ ፍቺ አንመራምʼ ብትል ማንም ያምንሃል። ዐውዳዊ ፊቺ፣ ሥነ አፈታት፣ ገለመሌ እያሉ የሚፈላሰፉትን፣ ʻየተቆሉ ገብሶችና አሻሮ ናቸውʼ እያልክ ብታብጠለጥልና የእነሱን ያረጀ ያፈጀ ትርጕም ወዲያ ብለህ ለሕዝቡ፣ ‘አሁን ከሰማይ የመጣውን ፍሬሽና ትኩስ ቃል ትፈልጋላችሁ? ወይስ እንደ ሽማግሌዎቻችሁ ማስጠንቀቂያና ማስታወቂያ የበዛበትን ልሰበካችሁ?’ ትላለህ። ያው መልሱ ግልጽ ነው፤ ማንም ቢሆን ፍሬሽ ፍሬሹን፣ ትኩሱን ትኩስን ይፈልጋል።”

“በየጊዜው የሚነሣው ጀማሪ ʻማን ኦፍ ጋድʼ አሮጌ እንዳያደርግህ መናፈቅ ያስፈልግሃልና፣ አንድ ሁለት ሳምንት ወደ ዱባይ ሄድ ትልና እግረ መንገድህንም እሑድ ሁለት ቦታ ፍሬሽ ጁስህን ትጨምቅና ትመለሳለህ። ማን ይጠይቃሃል ʻማን ኦፍ ጋድ ተመልሷልʼ የሚል ማስታወቂያ ታስለፍፋለህ፤ በአዲስ ቅባት እንደምትገለጥ ነጋሪት ታስጎስማልህ። እንደ ማስታወቂያ ያሉ ስብከቶችን የሚያምነው ሕዝብ ከሃያ አራት ሰዓት በፊት አዳራሹን መልቶ ይቆይሃል። ይሄ ሁሉ ʻማን ኦፍ ጋድʼ በመሆን የምትቀዳጀው ሥልጣንና እልቅና ነው።” 

መስተወቱ ፊት ተገተረ። የፍራሽ ጨርቅ የሚመስል አበባ የበዛበት ሸሚዝና ሰደሪያ ከነኮቱ ለብሶ፣ ጸጉሩን ወደ ላይ ገትሮ አቆመው። ከዚያም ለአምሮቱ ስኬት መንገድ ወደሚጠርግለት፣ ወደ አንድ አዲስ ወደ ተከፈተ ጉባዔ በከፋች አባልነት ሊመዘገብ እንደ ሆነ ነግሮኝ ሄደ። አዲሱ ከፋች ከታዋቂ ዘማሪነት ወደ ታዋቂ “ማን ኦፍ ጋድነት” ለመቀየር ተፍ ተፍ በማለት ላይ ያለ ሲሆን፣ ሁሌ የሰው መድረክ ማሞቅ የሰለቸው ይመስላል፤ የራስ ነገር ምንም ብትሆን የራስ ናትና። ሳሚ፣ ለአዲስ ቤተ ክርስቲያን ከፈታ ሲወጣ እኔ ደግሞ ‘ቃና ውስጤ ነው’ን ከፈትኩ፤ “የተቀማ ሕይወት ክፍል 41” ይላል፤ ተደላድዬ ተቀመጥኩ።

Asnake Endrias

ለሚድን በሽታ የሚገድል መድኃኒት መውሰድ ይብቃ! (ደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ)

“አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፣ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል። አንዱ ብሔሩን ሲያስቀድም፣ ሌላኛው ዜግነቱን ያስቀድማል። አንዱ የብሔር ዘረኛ የራሱን ብሔር ለብቻው ሊያገንን ሲፈልግ፣ ለኢትዮጵያ ዐብሮነት መሠረት ውጋት ይሆናል። እንደዚሁም የዜግነት ዘረኛ ኢትዮጵያን ለብቻዋ እንድትገን ሲፈልግ፣ በጨለማ ላለ ጥቁር አፍሪካ ሕዝብ አንድነት ውጋት ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.