[the_ad_group id=”107″]

ዕቅበተ እምነትና ውግዘት

በቅጡ ካልተረዳናቸውና ፋይዳቸውን ልብ ካላልናቸውና በማደግ ላይ ካሉ አገልግሎቶች መካከለ ዕቅበተ እምነት አንዱ ነው። ያም ቢሆን አገልግሎቱ አሁን ላይ በሕፃን ጉልበቱ ለክርስቲኑ ማኅበረ ሰብ እያበረከተ ያለው አዎንታዊ አሰተዋጽኦ የሚናቅ አይደለም። የአገራችን የዕቅበተ እምነት አገልግሎት እያደገ እንዲሄድ፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የታየውን የዕቅበተ እምነት መልክ እንዲይዝ ችግሮቻችን ላይ ብዙ ማለትና መሥራት እንዳለብን አስባለሁ። 

አገልግሎቱን እያስተዋወቅን ያለን አንዳንድ ወገኖች፣ ካሉብን መሠረታዊ ሊባሉ ከሚችሉ የዕውቀት ዝንፈቶች የተነሣ በሰሚና በተመልካቹ ልቦና “ዕቅበተ እምነት” የሆነውን ሳይሆን፣ ያልሆነውን ቅርጽና መልክ እንዲይዝ ምክንያት መሆናችንን መጠቀስ ይቻላል። ሊነሡ ከሚችሉ አዕማድ የዕውቀት ዝንፈቶቻችን ውስጥ አንዱ፣ በውግዘትና በዕቅበተ ዕምነት መካከል ያለውን ልዩነት አለመረዳታችን ሲሆን፣ ይህ ደግሞ መልከ ጥፉ የዕቅበተ እምነት ገጽታ እየፈጠረ ነው። በዚህም ምክንያት የዕቅበተ እምነት ሙግትን  እውነት በሚሹ ጭመር የማይወደድ፣ የሳቱትን ማቅረብና ማቅናት የማይችል፣ የተናቀና ሥልጣን አልባ ሥራ እንዲሆን አድርጎታል። ዕቅበተ እምነት የሚያርምና የሚያንጽ መልክ እንዲኖረው፣ ግለ ሰቦችን በአደባባይ ሐሜት ማብጠልጠል፣ ማጥላላትና መሳደብ እንዳልሆነ ማወቅ እንዳለብን ሁሉ፣ “ማውገዝ” ዕቅበተ እምነት ቢሆንም፣ ዕቅበተ እምነት ግን ማውገዝ እንዳልሆነ ማወቅ አለብን።

ውግዘትና ዕቅበተ እምነት ልዩነት አላቸውን?

ውግዘትና ዕቅበተ እምነት እጅግ የሚቀራረቡና ዐብረው የሚሄዱ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ማቀብ ከትምህርትና ከሙግት ጋር ሲገናኝ፣ ማውገዝ ግን ከመሪዎች ውሳኔ ወይም ፍርድ ጋር ይያያዛል። ውግዘት ዕቅበተ እምነትንና የአመራር ሥልጣንን መሠረት ሲያደርግ፣ ዕቅበተ ዕምነት ከውግዘት በፊት ቀድሞ የሚመጣ፣ ቃሉንና የአመክንዮ ዕውቀትን መሠረት የሚያደርግ ነው። ከውግዘት በኋላ ሲሆን ደግሞ ውግዘትንም መሠረቱ ያደርጋል። ውግዘት ካለዕቅበተ እምነት አይኖርም፤ ዕቅበተ እምነት ግን ካለ ውግዘት ይኖራል። ስለዚህም ዕቅበተ እምነት ለማረምና ለማስተካከል የሚቃወመው ስሑት ትምህርትና ግለ ሰብ ሁሉ ውጕዝ የማይሆንበት ጊዜ አለ። የተወገዘ ግን ዕቅበተ እምነታዊ ትችትና ትምህርት የተሰጠበትና የሚሰጥበትም ነው። በሌላ ቋንቋ ከውግዘት በፊት የሚሠራ ጠንካራ ዕቅበተ እምነት፣ ለጠንካራ ውግዘት መሠረቱ ነው። ጠንካራ ውግዘትም ከውግዘት በኋላ ለሚሠራ ዕቅበተ እምነት መሠረቱ ነው።

ዕቅበተ እምነት ከኑፋቄ ጋር እንደሚገናኝ ሁሉ ውግዘትም ከኑፋቄ ጋር ይገናኛል። ስለዚህም በቅዱስ ቃሉ መለኪያ ተለክተው የተበየኑ ኑፋቄዎች ፈጽመው የተወገዙ ስለ ሆኑ፣ ተጠንተው የሚበየኑና የሚታወቁ ወይም የመሪዎችን ውግዘት እስክንሰማ የምንጠባበቅባቸው ስላልሆኑ ፈጽመን በጽኑ የምንቃወማቸው ናቸው። ነገር ግን፣ ከታሪክ እንደምናስተውለው ውግዘት በመሪዎች መማክርት ጕባኤ ውሳኔ መሠረት፣ የስሕተት ትምህርቱንና አስተማሪውን ለመነጠልና ከክርስቲያን ማኅበረ ሰቡ ወይም ቤተ ክርስቲያን ለማግለል የሚወሰድ እርምጃ ነው።  


ውግዘትና ሥልጣኑ

ፋቄን ኑፋቄነቱን ተንትኖ መቃወም፣ ይፋ ማድረግ ወይም መተቸት መንፈሳዊ ሸክም የተሰማው፣ መረጃውና ዝግጅቱ ያለው አገልጋይ ሁሉ በተናጥል ወይም በኅብረት ሊያደርገው ይችላል። ስሕተትንም ይሁን የሳተን “ውጕዝ ከመአርዮስ” ብሎ “ማውገዝ” ግን የመሥራች ሐዋርያት ሥልጣን ወይም የአጠቃላይ አመራር ሥልጣን እና በበቂ መረጃና ምክንያት ወይም ጥናት ላይ የተመሠረተ ይፋዊ ውሳኔ ይፈልጋል።

ኑፋቄው አገራዊ ስርጭት ካለው አገራዊ የመሪዎች የመማክርት ጕባኤ የጋራ ግንባር ተጋድሎ ይፈልጋል። . . . ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው የኑፋቄ ትምህርቶችንና ሐሰተኛን አሠራር ለመመከት ይህን መሰል ተደጋጋሚ ጕባኤዎች ተደርገዋል። አንድ ትምህርት “ኑፋቄ” ተብሎ የሚፈረጀውም በዚሁ ጕባኤ ሥልጣን ሲወገዝ ብቻ ነው። ለምሳሌም፦ የኒቂያን፣ የቊስጥንጥንያን፣ የኤፌሶንን፣ የኬልቄዶን፣ የዌስት ሚኒስተርንና የሉዛንን ዓለም አቀፍ የጥናትና የመማክርት ጕባኤ እንዲሁም በአገራችን በ2009 ዓ.ም በመጋቢ ጻድቁ አብዶ የተመራው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት 32ተኛ አገራዊ የመሪዎች የመማክርት ጕባኤ ያቀረበውን ዐቃቤ እምነታዊ የዐቋም መግለጫ ኑፋቄን ያወገዘበትን ታሪክ መጥቀስ ይቻላል። 

በአጠቃላይ ውግዘት የግለ ሰብ ወይም የጥቂት ቡድኖች ተግባርና ሥራ አይደለም።

ውግዘት በሐሰተኛ ትምህርትና በመምህራኑ ላይ

ውግዘትሁለትአቅጣጫዎችን ሊከተል ይችላል። ይኸውም በግለ ሰብ ላይ የሚደረግና በትምህርትና ልምምድ ላይ የሚደረግ ውግዘት ነው። የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት 32ተኛ የመሪዎች ጕባኤ የእምነት እንቅስቃሴ መምህራን ከማውገዝ ይልቅ፣ ትምህርቱንና የሐሰተኛ ነቢያትን ልምምድ ያወገዘ ነበር ማለት ይቻላል። ጕባኤው በትምህርት ላይ ባደረገው ውግዘት፣ የእምነት እንቅስቃሴን ትምህርት መልክና ይዘት በመጠኑም ቢሆን ለይቶ አመልክቷል። ይህን ሲያደርግ ግን የመምህራኑን ስም ጠቅሶ አይደለም። ሆኖም ግን፣ የጥቂቶቹን ብቻ ማንነት ሊጠቁም በሚችል መለኩ በማውገዝ ከክርሰቲያኑ ኅብረተ ሰብና ከክርስትና ጋር እንዳይቀየጡና እንዲገለሉ አድርጓል። ይህም ካለው የትምህርትና የጥናት፣ የመረጃና ርግጠኝነት ውስንነት የተነሣ በጥንቃቄ የተደረገ ነው። በተጨማሪም ጕባኤው በውግዘት መግለጫው የበርካቶችን ስም ሳይጠቅስ ከስሑት ትምህርታቸውና ልምምዳቸው እንዲመለሱ በጥቅሉ አስጠንቅቆ ያለፈ ነው። 

ርግጥ የእምነት እንቅስቃሴን ከወንጌላውያን ክርስትና ለመለየት ውግዘት ብቸኛ መፍትሔ አይደለም። ምክንያቱም ትምህርቱ እግሩን ያላስገባበት ቤተ እምነት የለምና፤ መጠኑ ይለያይ እንጂ ያልነካካው አገልጋይም የለም የምንልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።  ስለዚህም ግለ ሰቦችን ከማውገዝ በፊት አስቀድሞ ትምህርቱን ማውገዝና መለየት ይቀድማል። 

በአጠቃላይ፣ ስሑት ትምህርትን የመለየት ያህል በትምህርቱ የተጠመዱትን መለየት ቀላል አይሆንም። ስለዚህም በትምህርቱ ተጠምቀው “የእኔ ነው” ብለው በሚከራከሩለትና እርመት ለመውሰድ በሚፈቅዱት መካከል ለመለየት በጥንቃቄ መሥራትና ጊዜ መስጠት አግባብ ነው። ስለ ሆነም፣ አመራሩን “ፍየሉን ከበጎች ቀየጥክ” በሚል መውቀስ አዋቂነት ነው የሚል እምነት የለኝም። እንዳይቀየጥ ከመከላከል የተቀየጠውን በብልሃት መለየት ቅድሚያ የሚሰጠው የአመራሩ ጕባኤም ይሁን የዕቅበት እምነት አገልጋይ ትልቅ የቤት ሥራ ስለ ሆነ፣ ኅብረቱ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉበት በማስተዋል በጅማሬው ላይ የታየውን በጎ እርምጃ እንዲገፋበት ማበርታት ይገባል። ስሑት ትምህርትን፣ ልምምድንና መሪዎቻቸውን ለውግዘት በሚያቀርብ ወይም በሚያጭ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በተመሠረተ የዕቅበተ እመነት ሥራ አብዝተን መጋደል አለብን። ከዚህ ይልቅ የአመራሩ ሥልጣን በሚጋፋና ባልተቀበልነው ሥልጣን ሐሰተኞችን ከማቀብ ይልቅ ለማውገዝ መሞከር፣ በፀሓይ ላይ ቀስት የመለጠጥ ያህል አስቂኝ የልጅ ጨዋታ ነው የሚሆንብን።

አንዳንድ ጊዜ በእውቀት ያልተያዘ መንፈሳዊ ቅናት የሚፈጥረው ስሜት ገንፍሎ የሚቆጣጠረን ይመስለኛል። እምነትን ለማቀብ የመሪዎች ጕባኤ የማውገዝ ሥልጣን አስፈላጊነትንና ፍቱንነትን አንገነዘበውም፤ ለግል ሙግታችን የምንሰጠው ግምት ከፍተኛ ይሆናል ወይም ገደብ የለሽና ከመሪዎች ጕባኤ በላይ የናረና ከፍ ያለ ይሆናል። በእንዲህ ዐይነቱ መተላለፍ የተጀቦነ ሥልጣን አልቦ ውግዘት፣ በአጃቢና በላይክ የጀግና ስም ቢያሰጠን እንኳ፣ ዶሮንሲያታልሏትበመጫኛጠልፈውጣሏት የሚለውን ብኂል ሊያስታውሰንና ከመውደቃችን በፊት አስቀድመን ሊያነቃን ይገባል። የቱንም ያህል ትልልቅ ሥራዎችን መሥራት ብንችልና ከዚህም የተነሣ ቍጥሩ ከፍ ያለ ሕዝብ ቢያውቀን ወይም በፌስ ቡክ ገጻችን ቢከታተለን፣ “አውጋዥና ገናዥ” ልንሆን አንችልም! ስለ ሆነም እምነትን በአንድም በሌላም መንገድ የማቀብ ሸክሙ አለን የምንል ወገኖች፣ ሥልጣናችን እስከ ምን ድረስ እንደ ሆነ ማወቅና ትችቶችን የምንሰነዝርበትን ገደብና ቃላት መለየት ይኖርብናል።

ዕቃቤ ያልፈታውን ውግዘት ይፈታዋል

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የመሪዎች ጕባኤን ጨምሮ፣ ከላይ ያነሣናቸው የመሪዎች ጕባኤዎች የተደረጉት በኢየሩሳሌም በተደረገው የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን መማክርት ጕባኤ ሞዴልን በመከተል ነው። 

የጳውሎስና የበርናባስ ተሞክሮ የሚያሳየን በማኅበረ ምዕመናኑ መኻል ጆሮ ያገኘና ግራ መጋባት የፈጠረ እንደ እምነትእንቅስቃሴ ዐይነት ያለን ኑፋቄ ለማቀብ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የውግዘት ሥልጣን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው።

ዕቅበተ እምነት ላይ እየሠራን ያለን ማናችንም ብንሆን፣ ሐዋርያቱ በመልእክቶቻቸው ሐሰተኞችንና ትምህርታቸውን እንዳወገዙ የምናወግዝበት ወይም በመሪዎች ጥምር ጕባኤ ላይ የምንሠለጥንበት ዕቅበተ እምነታዊ ሥራዎቻችንን ግለ ሰቦችን ወደሚያገልል ውግዘት ሊያሻጋግር የሚችል ሐዋርያዊ ወይም የመሪዎች ጠቅላላ ጕባኤ ሥልጣን አልተቀበልንም። በአንጻሩ የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አመራር ውግዘት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ከመሆኑም በላይ ኑፋቄን ለማምከን አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የኅብረቱ ዕቅበተ እምነታዊ የውግዘት ውሳኔ የአንድ ግለ ሰብ ስሜት መገንፈል ወይም ከጠበበ ምልከታ የሚነሣ ባለመሆኑና መዋቅራዊ ተደራሽነቱ ሰፊ ስለ ሆነ ነው። የሚወሰደው ውሳኔ (በተለይ የኑፋቄና የመናፍቃን ውግዘት) በአመራርና በዕውቀት የዳበረ ልምድ ያላቸው የበርካታ ምሁራን መሪዎች ምክር ስምምነት ውጤት የሚሆንበት ሰፊ ዕድል አለው። ይህ ሲሆን ውግዘት ከግል ፍለጎትና የጠበበ ምልከታ የመመንጨት ዕድሉ ጠባብና የጠለለ ስለሚሆን ሁሉ የሚቀበለው አሳማኝና ፍትሓዊ ይሆናል። 

ይፋ ውግዘትና የአደባይ ንስሐ

ውግዘት ከዕቅበተ እምነታዊ ሙግት ይልቅ፣ የሰፋ ጥናትና በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ተብራርቶ የሚቀርብ ግንዛቤና ግልጽነት ይፈልጋል። ውግዘት ፍርድ እንደ መሆኑ መጠን በእንቅስቃሴ፣ በድርጅትና በግለ ሰብ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት ጥንቃቄና አርቆ ማሰብ ያለበት፣ ፍትሓዊ ውሳኔ መልክ እንዲኖረው በሚያስችል አቅም መሠራት ይኖርበታል። ይፋ የሆነ የአደባባይ ውግዘት በክርስትና ላይ አደገኛ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ኑፋቄን ከመመከት ባሻገር ለይፋዊ ንስሐ መድረክ ይፈጥራል። በሌላ በኵል አስቀድሞ በመሪዎች የጋራ ጕባኤ አደገኛነቱ ታይቶና ተመርምሮ የተወገዘና ያልተነጠለ  አንድ ትምህርት ወይም ግለ ሰብ የትምህርትና የልምምድ ዕርምት ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ዐይነቱን አስቀድሞ በይፋ ያልተወገዘንና ያልተገለለን ግለ ሰብ “የአደባባይ ይቅርታ” ወይም ይፋዊ ንስሐ ያስፈልገዋልና እኛ ሳናውቅ ሊቀየጠን አይገባም በማለት የምንሞግትበት አግባብና አመከንዮዊ መሠረት አይኖረንም፤ አስቀድሞስ መቼ ተለየና። ይህን እናድርግ ብንል እንኳን እርምት የሚወሰድባቸው ስሕተቶቻች የትየለሌ ስለሆኑ ለይፋዊ የአደባባይ ንስሐ የሚያገለግሉ ጕባኤዎችን በየዕለቱ ማዘጋጀት ይኖርብናል። በአንጻሩ፣ የመሪዎች አጠቃላይ ጕባኤ ያወገዛቸውን ትምህርቶችና መምህራኖቻቸውን ካለ ምንም ይፋዊ እርምትና የመሪዎች ጕባኤ ዕውቅና ውጪ ወይም ካለ ምንም የአደባባይ ንሰሓ መልሶ ማቀፍና መለሳለስ ማሳየት፣ የጕባኤውን ሥልጣን አለማክበር ከመሆኑ በላይ፣ አመራሩ በኑፋቄ ላይ ያለውን አቅም ማዳከምና የውግዘትን ትርጕምን ማጥፋትና ክርስትናን ለአደጋ የተጋለጠ እንዲሆን ማድረግ ጭምር ስለ ሆነ አደገኛ ነው። 

በማጠቃልያዬም፣ ሐሰተኛ ትምህርቶችንና መምህራኑን ለይተው የሚያሳዩና የሚያገልሉ ውግዘቶች፣ የመሪነት ሥልጣን ባለው ጕባኤ  እንዲደረጉና ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው በጌታ ቃልና በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ግፊትና የተናበበ ሥራ መሥራት ከእምነት ዐቃብያን የሚጠበቅ ልከኛ ተግባር ነው። በቀረው፣ ከሰሕተቶቻችን ልንማርና መጽሐፍ ቅዱሳዊውንና ታሪካዊውን ዕቅበተ እምነት ልናስተዋውቅ ይገባል። በተናጥል እያበረከትን ያለነው ዕቅበተ እምነታዊ ሥራ ልክና ገደብ እንዳለው በማወቅ፣ ለአጥቢያዎችና ለአብያተ ክርስቲያናት አመራር አካላት የማውገዝ ድርሻ ግብአት በሚሆንበት ቅርጽ፣ መዋቅራዊ የአጥቢያዎችና የጠቅላላ መማክርት ጕባኤ ሰንሰለትና አግባብ እንዲሠራ ጥረት ማድረግ ጠቃሚ አካሄድ እንደ ሆነ እምነቴ ነው።

“ለእነዚህ ሰዎች ለአንድ አፍታ እንኳ አልተገዛንላቸውም፤ ይኽውም፣ የወንጌል እውነት ከእናንተ ጋር ጸንቶ አንዲኖር ነው።” (ገላ. 2፥5)

ጸጋና ሰላም ይብዛልን!

Johnnson Ejigu

ጆንሰን እጅጉ በመጽሐፍ ቅዱስ ነገረ መለኮት የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩ ሲሆን፣ “የአማልክቱ ዐዋጅ!” እና “የመለኪያ ያለህ!” በሚል ርእስ የተዘጋጁ የዕቅበተ እምነት ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ጸሐፊ ናቸው።

Share this article:

የትንሣኤው ዐዋጅ

ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱ የሚታሰብበት የትንሣኤ በዓል በክርስቲያኖች ኹሉ ዘንድ በምስጋናና በዝማሬ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በኢኦተቤ ትውፊት መሠረት ከዘጠኙ የጌታ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱና ታላቁ በዓል የትንሣኤ በዓል ነው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ዘንድ በዓሉ አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመውን ጾም በማሰብና በመጾም፥ በመጨረሻም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም በአይሁድ እጅ የተቀበለውን መከራና ሥቃይ የሚያስታውሰውን ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሳምንት) በማስቀደም፥ በመጨረሻም ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውን ጌታ በዝማሬዎች በመወደስና ትንሣኤ ክርስቶስን በማወጅ ይከበራል። ልዩ ልዩ ሃይማኖታውያንና ባህላውያን ሥነ ሥርዐቶችም የበዓሉ አካላት ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ

ቅዱስ መንፈስም ይለያል!

በደግም ቀን ሆነ በክፉዉም ዘመናት ክርስቶስን እና እውነተኛ ትምህርቱን የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሊሆን ይገባል ስንል በብዙ ምክንያቶች ነው። አንድም ዙሪያችን በብዙ እንቅስቃሴዎች የተሞላ በመሆኑ በተፈጥሮውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም ብቻችንን አይደለንምንና ነው። አንድም በአንዱ መንፈስ ቅዱስ የማይገዛ ሕይወት፣ ትምህርት እና አገልግሎት ለሌሎች ብዙ መንፈሶች ጥቃት ስለሚጋለጥ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

“አትብሉ – ብሉ”

በዔድን የነበረው ሕይወት “መልካም” እጅግ ያማረም ነበር። ከምድር ዐፈር የተበጀው ሰው በዚህ ውብ ስፍራ ተቀመጠ፤ እንዲኖር፣ እንዲያለማ፣ እንዲንከባከብም። በዚያ የነበረው ዛፍ ሁሉ “የሚያስደስት ለመብልም መልካም” ነበር (ዘፍ 2፥9)። ሕይወት አካላዊ (ውጪአዊ) ብቻ ስላይደለ ከመኖርና ከመደሰት ያለፈ ደርዝ አለው፤ ነፍሳዊ፣ መንፈሳዊ ገጽታ። ይህም ደግሞ የተሟላ እንዲሆን በሚታየውና በሚበላው መካከል ምጡቅና ረቂቅ የሆነው አምላክ እንዲታሰብ፣ እንዲከበርም ታሰበ።

ተጨማሪ ያንብቡ

4 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.