[the_ad_group id=”107″]

ዕቅበተ እምነት እና ተግዳሮቶቹ

መግቢያ

ዕቅበተ እምነት፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በክርስትና እምነት እውነት ላይ የበቃ ግንዛቤና ሸክም ያለቸው ጥቂቶች፣ ትክክለኛውን የክርስትና ሥነ ምግባርና የቀና ዐላማ አንግበው የሚከውኑት ተግባር ነበር። ይሁን እንጂ፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ፣ በተለይም ማኅበራዊ ድረ ገጽ የሰጣቸውን ዕድል በመጠቀም በርካቶች ይህን ዘርፍ ለመቀላለቀል በቅተዋል። ይህ ክስተት ደግሞ ለቤተ ክርስቲያንና ለክርስትናው እምነት በረከትና መርገም ይዞ መምጣቱ አልቀረም። በረከቱ ብዙም ትኵረት የማይሰጠውን፣ በበርካቶች ችላ የተባለውንና ትዕግሥትን፣ ጽናትንና ጥንካሬ የሚጠይቀውን ዘርፍ ለመቀላቀል በርካቶች መነሣሣታቸው ነው።

ይህም ከታሪካዊው የክርስትና እምነትና ልምምድ የተፋታ እምነትና ልምምድ የክርስትና ካባ ለብሶ እጅጉን በተንሰራፋበት፣ የሐሰት አስተምህሮ እንደ አሸን መፍላት ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ የወንላጌውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ አገልጋዮችና ምእመናን ልዩ ርኅራኄ እያሳዩ ባለበት በዚህ ወቅት ይህን ኀላፊት የተቀበሉ ጥቂት ቀናዒ አማኞችን ማግኘት ትልቅ በረከት ነው።

መርገሙ ደግሞ ራሳቸውን “ዐቃቤ እምነት” ብለው የሰየሙ ወይም “ዐቃቤ እምነት” ተብለው በሌሎች የተሰየሙ የተወሰኑ ግለ ሰቦች ለዚህ ሥራ ክብር በማይመጥን መልኩ ሥራውን ለራሳቸው ገጽታ ግንባታ፣ ስምና ክብር ማግኛ እንዲሁም ዐልፎ ዐልፎ ለገንዘብ ምንጭነት መጠቀማቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጥቂት በማይባሉት ዘንድ የሥነ ምግባርና የአቀራረብ ችግሮች መስተዋሉ፣ እንዲሁም ሥራው የእርስ በእርስ መነቋቆር፣ ፉክክርና ክፍፍል ምንጭ መሆኑ በእጅጉ የሚስተዋሉ ጥቂት ተግዳሮቶች ነው። ከዚህም የተነሣ ዕቅበተ እምነት በትብብር ሳይሆን በፉክክር የሚሠሩት እስከ መሆን ደርሷል። ከዚህም በተጨማሪ ከክርስትናው እምነት እንዲሁም ከዕቅበተ እምነት ሥነ ምግባር በማይጠበቅ መልኩ እስከ መሰዳደብና የሌሎችን ክብርና ማንነት እስከ መንካት መደረሱ፣ “እውነትን በፍቅር መግለጥ” የሚለው መርሕ ተፋልሶ፣ “እውነትን በስድድብ በመነቋቆር መግለጥ” በሚል የተተካ መምሰሉ ከምንሟገትለት እምነትና ከክርስትናው ባሕርይ ጋር የማይገጥም ሆኖ ተስተውሏል።

በሌላ መልኩም ከምናቅበው እውነት ይልቅ በዐቃብያኑ መካከል ያለው ውዝግብ ጎልቶ ይወጣና እውነቱን ይሸፍነዋል። በውጤቱም ደግሞ የሚታቀበው እውነት ሐሳውያንና ተከታዮቻቸው ጋር ሳይደርስ በራሳችን አድማስ ውስጥ እንደ ገደል ማሚቶ ተስተጋብቶ ይቀራል። ይህም ደግሞ፣ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በቤተ ክርስቲያን ብዙም ዋጋና ስፍራ ባልተሰጠው፣ በብዙዎች ዘንድ እንደማይገባ የንትርክና ጭቅጭቅ ሱሰኞች ተግባር ተደርጎ በሚብጠለጠለው በዚህ ሥራ ላይ ትልቅ ተግዳሮትን ሊያሳርፍ ችሏል።

ከላይ ከተዘረዘሩት ተግዳሮቶች በተጨማሪ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወጣት ዕቅበተ እምነታውያንና በወንጌላውያን ዘንድ ጕምቱ ሆነው በሚከበሩ ጥቂት አገልጋዮች መካከል ያለው እሰጥ አገባ እየተካራራ ሲመጣ ተስተውሏል። ይህም ክሥተት ወጣት ዐቃብያንን የጎሪጥ ለሚያዩ የወንጌላውያን አገልጋዮችም ሆነ የአገልጋዮችን አካሄድ በጥርጣሬ ለሚመለከቱ ለወጣት ዐቃብያኑ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ለዕቅበተ እምነት ሥራና ለወንጌላዊው ክርስትና ትልቅ ተግዳሮት መሆኑ አይቀሬ ነው።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ዕቅበተ እምነት መነሻ[1]

የክርስትና እምነት የራሱ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ መሠረት ያለው ነው። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ታሪካዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ላይ ቆማ እምነትና ልምምዷን ታካናውናለች። በዚህም መሠረት የቤተ ክርስቲያንና የአማኞች አምልኮ፣ ኑሮና ልምምድ በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮና በታሪክ ምስክርነት ይዳኛል። በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች የዕቅበተ እምነት መነሻው በመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና ታሪካዊ መሠረት ላይ ቆሞ፣ ከዚህ እውነትና መሠረት ባፈነገጠ መልኩ በስሕተት አስተምህሮና ልምምድ ውስጥ ያሉ ተቋማትንና[2] ግለ ሰቦችን ከስሕተታቸው በንስሓ እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረብ ነው።

ይህ የዕቅበተ እምነት መነሻ በአብዛኛው ከምዕራባውያኑ ዕቅበተ እምነት (መነሻ) ይለያል።[3] የምዕራባውያን ዕቅበተ እምነት በአብዛኛው መሠረቱን ያደረገው ከእግዚአብሔር የለሾችና ፈላስፎች በሚነሡ ጥያቄዎችና ተግዳሮቶች ላይ ነው። የኢትዮጵያ ዕቅበተ እምነት መነሻው ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምሮና ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያፈነገጠ አስተምህሮና ልምምድ ያላቸው ተቋማትና ግለ ሰቦች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዕቅበተ እምነት ሥራ በዚህ እውነት ላይ ትኵረት ያደረገ ቢሆንም፣ የወንጌላዊው ክርስትና ውስጥ የሚስተዋለው አስተምህሮ የለሽ መደበላለቅ የእምነት ተቋማቱን በአስተምህሮ መሠረት ለይቶ ለመፈረጅ እጅግ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል። በመሆኑም፣ ጤናማ የወንጌላውያን አስተምህሮና ልምምድ ያለው ቤተ ክርስቲያን የትኛው ነው? የሌለውስ የትኛው ነው? ብለን ብንጠይቅ እጅግ አስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ እንገባለን። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት ከዚህ በፊት “ወንጌላውያን”ተብለው የሚጠሩት፣ ግልጽ በሆነ አስተምህሮና ልምምድ ተለይተው የሚታወቁ ሲሆን፣ አሁን አሁን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ቤተ ክርስቲያንናት የሚተከሉት የአስተምህሮ ልዩነት መሠረት አድርገው ሳይሆን፣ በተለያዩ የልምምድና አስተዳደራዊ ጕዳዮች ልዩነት መሠረት አድርገው በመሆኑ ምክንያት፣ በወንጌላውያን መካከል እንኳ ያለውን ልዩነት ማወቅ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ ለዓመታት የወንጌላዊው ክርስትና አገልጋዮች ተደርገው በሚወሰዱ ዘማሪዎች፣ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች አማካይነት ከሐሳውያን ጋር የሚደረገው የመድረክ መጋራት፣ እንዲሁም በተለያዩ ኅብረቶች አማካኝነት የሚፈጠሩ ግንኙነቶች በሐሳውያንና በወንጌላውያን መካከል ያለውን መሥመር እያጠበበ መጥቷል። ይህ ደግሞ ምእመኑ ያለ ልዩነት ሁሉንም እንደ ጤናማው የክርስትና እምነት እንዲቀበል፣ እዚህም እዚያም እንዲሄድ በማድረጉ ምክንያት የዕቅበተ እምነት ሥራ ላይ ትልቅ ተግዳሮት ሊፈጥር ችሏል።

በመጨረሻም ማካል ያለብኝ ጥቂት እውነቶች አሉ። ከታች እንደምናየው የዕቅበተ እምነት ሥራ የሁሉም አማኝ ድርሻ ቢሆንም፣ ትልቁን ሚና መወጣት ያለባቸው ግለ ሰቦች ሳይሆኑ ቤተ ክርስቲያን ናት። ቤተ ክርስቲያን የዕቅበተ እምነት ሥራን ከወንጌል ሥርጭት፣ ከእረኝነት፣ ከትምህርት፣ ከስብከትና ከዝማሬ ባልተናነሰ መልኩ ትኵረት ሰጥታና ቢሮ ከፍታ የመሥራት ትልቅ ኀላፊነት አለባት። አንድ ግለ ሰብ የዕቅበተ እምነት ሥራ ላይ ተሳታፊ የሚሆን ከሆነ ከአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጋር ጤናማ ኅብረት ያለውና ስለ ሕይወቱ ንጽሕናና አገልግሎቱ መልካም ምስክርነት ቤተ ክርስቲያኒቱ ልሰትጠው የምትችል ቢሆን ይመረጣል። አንድ ከቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ሥር ያልሆነ፣ የሕይወት ምስክርነቱ ምን እና እንዴት እንደ ሆነ የማይታወቅ ግለ ሰብ የተገኘውን የማኅበራዊ ድረ ገጽ ዕድል ተጠቅሞ የቱንም ያህል ዐቃቤ አማኝ ነኝ ቢል፣ በዋናነት እምነቱን እንዲያቅብ ያስገደደው የትኛውን ዐይነት አስተምህሮ የምትከተል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሆነና ለየትኛው መንጋ ሸክም ተሰምቶት እንደ ሆነ ስለማይታወቅ፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ሥነ ምግባሩ ምን ዐይነት እንደ ሆነ ምስክርነት ማግኘት ስለሚቸግር፣ ሥራው በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘቱ ጕዳይ አጣራጣሪ ከመሆኑም ባሻገር እንዲህ ዐይነት ግለ ሰቦች ለዕቅበተ እምነት ሥራው ትልቅ ተግዳሮት ይሆናሉ።

በተጨማሪም ደግሞ ዕቅበት እምነት ሐሰተኛ ነቢያትና መምህራንን ከመቃወም የሰፋ አድማስ ያለው ነው። በመሆኑም፣ ዕቅበተ እምነት ለመሥራት ተነሣሽነቱ ያለው ሰው በክርስትና እምነት ውስጥ ስላለው ተስፋ ከሌሎች ሃይማኖት፣ ፋላስፎችና አላማኞች ለሚነሡ ጥያቄዎችም ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ መሆን አለበት። ኬቨን ሙሪቲ የተሰኘ ኬኒያዊ የዕቅበተ እምነት ምሁር፣ የአፍሪካ ዕቅበተ እምነት ሊያተኵርባቸው ከሚገባቸው ሁለት ጕዳዮች አንዱ[4] ድኅረ ዘመናዊነት ስለ መሆኑ አውስቷል። ድኅረ ዘመናዊነት ካመጣቸው አስተሳሳቦች መካከል አንዱ ደግሞ፣ “ወደ ጥንቱ ባሕላዊ ሃይማኖታችን እንመለስ” የሚል ዘመቻ ይገኝበታል። ይህ እውነት በኢትዮጵያም በብሔር ፖለቲካ ካባ ተጀቡኖ በባሕላዊ ሃይማኖትና ዘመን መለወጫ ሽፋን መምጣቱ የማይታበል ሃቅ ነው።

ይህ ዐጭር መጣጥፍ በተለይም 1ኛ ጴጥሮስ 3፥15-17 ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንባብ እንደ ዋና መሠረት በመጠቀም የዐቃቤ እምነት ሥራና ተግዳሮቶችን ለመፈተሸ ይጥራል።

የዕቅበተ እምነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት

“በርካታ ዐቃቤያንን አንድ ክፍል ውስጥ ሰብስባችሁ፣ ‘ለዕቅበተ እምነት ሥራችሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ምንድን ነው?’ ብላችሁ ብትጠይቋቸው፣ 1ጴጥሮስ 3፥15ን ይጠቅሳሉ” ይላል ኬቨን ሙሪቲ።[5] ሐዋርያው ጴጥሮስ ከእምነታቸው የተነሣ መከራ ውስጥ እያለፉ ላሉ፣ እንዲሁም በክርስቶስ ያለው እምነትና ኑሯቸው በከንቱ እየታማ ለነበረ አማኞች፣ እምነታቸውን በተግባራዊ ኑሮ እንዲያሳዩ ብቻ ሳይሆን፣ በአእምሯዊ አመክንዮም እያስረዱ እንዲሞግቱና እንዲያቅቡ ጭምር፣ “ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና አክብሮት አድርጉት፤ በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ” በማለት ያሳስባቸዋል (1ጴጥ. 3፥15-16፤ አመት)።

ከዚህ የጴጥሮስ ማሳሰቢያ ውስጥ ጤናማ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለሆነ ዕቅበተ እምነት ጠቃሚ መመሪያዎችን ማውጣት እንችላለን።

  • መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ መሆን

ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚያወሳው ስለ ተራ የሃይማኖት ክርክርና ውዝግብ አይደለም። የመልእክቱ ተደራሲያን መከራን በጽናት እየተቀበሉለት ያለ እውነትና ተስፋ አለ። ለዚህ የማይጨበጥ ለሚመስል ተስፋ ወደር የለሽ መከራ መቀበል ደግሞ በወደረኞቻቸው ዐይን አስቂኝ ሞኝነት ነው። በመሆኑም፣ ስለ እምነታቸውና ተስፋቸው ስደትና መከራ መቀበል ብቻ ሳይሆን ጥያቄ ይጠየቃሉ። ተቃዋሚዎቻቸው ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ከክርስቶስ ሕይወት የተነሣ እያሳዩ ያለውን መልካም ጠባይ እንኳ በሐሜት እያክፋፉ ስማቸውን ከማጠልሸት የማይመለሱ ጨካኞች ጭምር ናቸው።

በዚህ ምንባብ “መልስ ለመስጠት መዘጋጀት” እምነትንና ተስፋቸውን በአመክንዮ ማስረዳትና ማቀብ ሆኖ ነው የቀረበው። ይህም በፍርድ ፊት ቀርቦ ስለ ተጠየቁበት ጕዳይ በቂ የሆነ ማስረጃ በማቅረብ ከመሟገት ጋር፣ ወይም ደግሞ በተለያዩ ዘመናት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚታወቀው ስለ እምነትና ተስፋቸው የአደባባይ ሙግት ከማቅረብ ጋር ተካካይ ነው። ይህ ሙግት በብዙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች የተሞላ ነው። ምናልባትም እምነትና ተስፋቸውን የማስረዳት ሙግቱ እየተካረረ ሄዶ ሕግ ፊት እስከ መቅረብ ሊያደርስ ይችላል። ለዚህም የሐዋርያው ጳውሎስን ታሪክ መጥቀስ በቂ ማስረጃ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም ሕግ ፊት ቀርቦ እንዲሟገት፣ እንዲታሰርና በመጨረሻም እንዲሞት ያደረገው በትንሹ አዳባበይ የተጀመረው የእምነት ሙግት ነው።

ሐዋርያው ይህን ትእዛዝ የሚሰጠው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና አመራር ለተሰማሩ ጥቂት ሰዎች፣ እንዲሁም ለነገረ መለኮት ተማሪዎችና ምሁራን ሳይሆን፣ ለአማኞች በሙሉ ነው። እምነትና ከእምነት የሆነው ተስፋ የሁሉም አማኝ እስከ ሆነ ድረስ፣ የሚያምነው እውነት ጥያቄ ሲያመጣና አደጋ ውስጥ ሲሆን መልስ መስጠትና መከላከልም የሁሉም አማኝ ኀላፊነት ነው።

ሐዋርያው በዚህ ሥፍራ ላይ የሚያነሣው ዕቅበተ እምነት የአንድ ጊዜ፣ ወይም የአንድ ወቅት ሙግት ሳይሆን፣ ከዕለት ዕለት የክርስትና ሕይወትና ኑሮ ጋር የተያያዘ እምነትን የመመከት ትግል ነው። ሙግቱ በማንና መቼ፣ እንዴት እንደሚጀመር፣ አሊያም ተቃዋሚዎቻቸው በየትኛው ጊዜ ምን ዐይነት ተቃውሞ ይዘው መጥተው እምነትና ተስፋቸውን እንደሚያጠቁ አይታወቅም። በመሆኑም፣ ዘወትር መልስ ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

  • በትሕትናና አክብሮት መሟገት

የጴጥሮስ ተደራሲያን በዓለማዊው ልማድ የፖሊቲካና ፍልስፍናዊ ሙግት እየገጠሙ አይደለም። በአደባባይ ሙግት ላይ ባለጋራን አስደማሚ በሆነ ብቃት በመዘረር፣ ስማቸውን በአሸናፊነት በደማቅ ቀለም የማስጻፍ ፉክክር ላይም አይደሉም። የጴጥሮስ ተደራሲያን የክርስቶስን ወንጌልና ከወንጌሉ የተገኘውን ተስፋ ከጥቃትና ከአደጋ የመከላከል ተጋድሎ ላይ ናቸው። በጥበብ ጕድለት፣ መሃይምነትና ከስሜታዊ ግፊት በሆነ ግብታዊነት እንደ ተከተሉ ተደርጎ ለሚብጠለጠው እምነትና የእምነት እውነት፣ አመክንዮአዊ ሙግት በማቅረብ ምላሽ እየሰጡ ነው። ይህም ሙግት የራሱ ባሕርይና ሥነ ምግባር ያለው ነው። ስለዚህም ነው ሐዋርያው፣ “ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት” የሚለው። በልባቸው ክርስቶስን ጌታ አድርገው ቀድሰው እምነታቸውን በታማኝነት የሚያቅቡ ሰዎች ዋና ግባቸው፣ በልባቸው የቀደሱትን ክርስቶስን ማለቅና ማጕላት ነው።

የሚጎሉት፣ የሚታዮ፣ የሚታወቁትና የሚገንኑት እነርሱ አይደሉም፤ ክርስቶስ ነው። በሌላ አነጋገር ሙግቱን የሚመራውና የሚገራው በልባቸው ያነገሡትና የቀደሱት ኢየሱስ እንጂ፣ የእነርሱ የዕውቀት፣ ብቃትና ስሜት አይደለም። ይህ ክርስቶስ ደግሞ በእርሱ ሞትና ትንሣኤ ተመሥርቶ የጸናው እውነትና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ከእርሱ ባሕርይ አንጻር እንጂ ከወደቀው ስሜታዊ፣ ግብታዊና እብሪተኛ ሰው ስሜትና ፍለጎት አንጻር እንዲመራ አይፈቅድም። ዕቅበተ እምነታችን ግቡ ራሳችንን ከፍ በማድረግ ጌታ አድርገን ማሳየት ሳይሆን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጌታ አድርጎ መቀደስ ነው። በዚህም ምክንያት ነው ሐዋርያው ጴጥሮስ ዕቅበተ እምነታችሁን በትሕትናና በፍርሀት አድርጉት የሚለው።

ነገር ግን በየዋህነትና በፍር ይሁን የሚለው የጴጥሮስ መመሪያ (1954 ዕትም) እንደ ልጓም የዐቃብያንን ባሕርይ የሚገራ ነው። ይህን መመሪያ አዲሱ መደበኛ ትርጉም፣ “ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና አክብሮት አድርጉትይላል። ይህን ምንባብ ከተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕሞች ጋር ስናነጻጽር፣ “በየዋህነት ወይም ትሕትናና በፍርሀት ወይም አክብሮት አድርጉት” የሚል ይሆናል።

መመሪያው ባለ ሁለት አቅጣጫ ነው። ይህም ሁለት አቅጣጫ ተቃዋሚዎችንና እግዚአብሔርን የሚመለከት ነው። ዕቅበተ እምነትን በየዋህነት ወይም ትሕትና ማድረግ ለሌሎች ሰዎች ሊኖረን የተገባው አመለካከት ሲገራ፣ ዕቅበተ እምነትን በፍርሀት ማድረግ ደግሞ ሙግቱን በፈርሃ እግዚአብሔር እንድናደርግ ያደርገናል።

ዕቅበተ እምነት በየዋህነት ወይም ትሕትና ማድረግ ከአማኞች የሚጠበቅ ትልቅ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ነው። የዐቅበተ እምነት ሥራ ለትእቢት፣ ለእኔነት፣ ለጀብደኝነት፣ “እኔ ከእውነት ጎን ነኝ፤ ንጹሕና ጻድቅ ነኝ” ለሚያስብል ራስ ጸደቅነት በጣም ቅርብ ነው። ከዚህ ዐይነት የእኔነትና ትምክህት ኀጢአት ተጠንቅቀው እውነትን በትሕትናና የዋህነት ማቀብ የሚችሉት ከላይ እንዳየነው፣ ክርስቶስ ጌታ አድርገው በልባቸው በመቀደስ የክርስቶስ ልዩ መገለጫ የሆነውን ትሕትናና የዋህነት እንደ ልብስ የለበሱ ብቻ ናቸው።

እኛ ራሳችን የቆምነው በእግዚአብሔር ጸጋና ምሕረት እስከ ሆነ ድረስ ሌሎችን ወደዚህ ጸጋ፣ ምሕረትና እውነት የምናመጣው የእምነት ዐቅበታችንን በዚህ መልኩ ስናደርግ ብቻ ነው። የክርስቶስ ባሕርይ የሆነውን ትሕትና ያልተላበሰ ተሟገች፣ የክርስቶስን እውነት በትክክለኛው መንገድ መግለጽ አይችልም፤ ቢያቀርብም ቅቡልነት አይኖረውም። በሌላ ጎኑ ዕቅበተ እምነትን በዋህነትና ትሕትና ማድረግ የተገባበት ምክንያት ጉዳዮ ተሟጋችን የመዘረርና የክርክር የበላይነት የማግኘት ያለመሆኑን ያሳያል። ትሕትናና የዋህነት በክርክሩ ውስጥ የሚንጸባረቀውን ኀይል የተቀላቀለበትን የአሸናፊነት ስሜት የሚገሩ ባሕርያት ናቸው።

ዕቅበተ እምነትን በፍርሀት ወይም አክብሮት ማድረግ ሌላኛው ዐቃቤ አማኝ ሊኖረው የተገባ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ ምግባር ነው። በዚህ ስፍራ “ፍርሀት” የሚለው ሐሳብ ፈሪሓ እግዚአብሔርን እንጂ፣ ሰውን መፍራት የሚገልጽ አይደለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን ከማለቱ በፊት ተደራሲያኑ ተቃዋሚዎቻቸውን እንዳይፈሩ ደጋግሞ ያስጠነቅቃል። ከፍርሀት ጋር አቻ ሆኖ በሌሎች ቅጂዎች የተተረጐመው “አክብሮት” የሚለውንም ዐሳብ ከዚህ ጋር አያይዘን ነው መረዳት ያለብን። ይህ ዐሳብ በሙግት ውስጥ ስንሆን ተሟጋቾቻችንን እንድናከብር የሚያወሳ ቢመስልም፣ ትክክለኛው ፍች ፈርሃ እግዚአብሔርን ወይም አክብሮተ እግዚአብሔርን የሚያመለክት ነው። ይህም እውነት ዐቃብያን፣ እውነትን በፍቅር የሚያቀርቡ የዋሆችና ትሑታን እንጂ፣ ሐሳውያን ላይ የዘላለም ሞት ፍርድ የሚያስተላልፉ ፈራጅ ዳኞች ባለመሆናቸው ጕዳዩን በከፍተኛ ፍርሀት እንዲያደርጉት የሚያወሳ ነው። በክርክሩ ጕዳይ ሐሰተኛው ላይ የመጨረሻውን ዳኝነት የሚሰጠው እግዚአብሔር ብቻ ነው። 

  • በጎ ኅሊና መያዝ

ዕቅበተ እምነት ታማኝነት ያለው እንዲሆን በጎ ኅሊና ሊኖረን ይገባል። ትሕትና ለተሟጋች፣ ፍርሀት ለእግዚአብሔር እንደ ሆነ ሁሉ፣ በጎ ኅሊና ደግሞ ለራሳችን ነው። እውነተኛ ዐቃቤ አማኝ ሥነ ምግባሩ ወደ እግዚአብሔር፣ ወደ ተቃዋሚና ወደ ራሱ በሚጠቁሙ በእነዚህ ሦስት ልጓሞች የታጠረ ነው። በበጎ ኅሊና ዕቅበተ እምነታችንን ግብዝነት በሌለበትና ከተግባሩ የትኛውንም የግል ጥቅም ፍለጋ እያደረግን ያለመሆናችንን ለራሳችን ምስክርነት የሚሰጥ ውስጣዊ ድምፅ ነው። በተለይም በጎ ኅሊና ለዕቅበተ እምነት ያለን አነሣሽ ምክንያቶችን ፈትሾ እያሳየ፣ የሥነ ምግባር ጉድለቶቻችንን ነቅሶ እየጠቆመ ይሞግተናል።

በጎ ኅሊና የበጎ ባሕርይ ውጤት ነው። በዚህ ምንባብ ውስጥ የሀሜት ተቃራኒ ሆኖ ነው የቀረበው። የጴጥሮስ ተደራስያን በክርስቶስ ያለው ንጹሕ ኑሯቸው እንኳ በተቃዋሚዎቻቸው እየታማ ነው። ይህን አሉባልታና የሐሰት ክስ ማምከን የሚቻለው በአመክንዮአዊ ክርክርና በትሕትና ብቻ ሳይሆን፣ በጎ ኅሊናን ጭምር በመያዝ ነው። ሐሜት፣ ውሸት፣ የሐሰት ክስና ስም ማጥፋት እውነትን የሚያቅብ አማኝ ባሕርያት ሳይሆን የሐሰተኞች ነው። በጎ ኅሊና የምንሟገትለትን እውነት በተግባር በትክክል መኖር ያለመኖራችንን እየመዘነ ለንስሓ የሚጠራን ውስጣዊ ማስጠንቀቂያ ነው። በተጨማሪም፣ የዕቅበተ እምነት እውተኛውን መነሻ ሰበባችንን እየጠቆመ እኔነትና ትእቢት የተገኘብን ከሆነ፣ ውስጣዊ ልጓም ሆኖ እየጎሰመ ይገራናል።

የዕቅበተ እምነት ወቅታዊ ተግዳሮቶች

ከላይ ከጴጥሮስ መጽሐፍ እንዳየነው፣ ዕቅበተ እምነት ትልቅ ግንዛቤ፣ ጨዋነት፣ ትሕትናና የላቀ መንፈሳዊ ሥነ ምግባር የሚጠይቅ ተግባር ነው። በዚህ መመዘኛ ካየነው የእኛ አገር ዕቅበተ እምነት ሥራ ላይ የተሳተፉ ሰዎችና ቤተ ክርስቲያን ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል ማለት ነው። የዕቅበተ እምነት ሥራ፣ “ፍቅርን ጥሎ እውነትን አንጠልጥሎ” በአንጻሩም “እውነትን ጥሎ ፍቅርን አንጠልጥሎ” መሆን የለበትም። ዕቅበተ እምነት በእምነታችን ውስጥ ያለውን ተስፋ በፍቅር፣ በየዋሕነት፣ ቅንነትና ፍርሀት የምናሳውቅበት፣ ይህ እውነት ሲጣስ ደግሞ በዚያው ተመሳሳይ ሥነ ምግባር ወደ እውነት ለመመለስ ለሆነ ንስሓ ጥሪ የምናቀርብበት ነው። ዕቅበተ እምነት የእውነትውቀት ብቃታችንን ማሳያ የፊልሚያ ሜዳ ሳይሆን፣ የተቀደሰውን እውነት ከሐሰት ተፋልመን ናጸናበት መንፈሳዊ ተጋድሎ ነው። ዕቅበተ እምነት ርኅራኄ አልባ በሆነ ጭካኔ ሌሎች ላይ ፍርድ የምናስተላልፍበት ሸንጎ ሳይሆን፣ ፍቅር፣ ርኅራኄና ቅንነት በሞላበት መልኩ ወደ ጥፋት እየሄዱ ያሉትን ከጥፋት የምንናጠቅበት ተጋድሎ ነው። ዕቅበተ እምነት አንድ የተመቸንን ጥግ ይዘን ድንጋይ መወራወር ሳይሆን፣ በትሑት ልብ፣ በአንድነት፣ ለውይይት መግባባት ዝግጁ በሆነ መንፈስ እርስ በርሳችን የምንናጋገርበት፣ የምንመካከርበት፣ እምነትን በጋራ የምንመክትበት የጋራ ጦር ሜዳ ነው።

ይሁን እንጂ፣ አሁን በአገራችን እየሆነ ያለው ይህ ሳይሆን፣ ሌላ መልክ ያለው እጅግ አሳዛኝ ተግባር ነው። በወንጌላውያኑ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው ከዐቃብያን በኵል የሚስተዋሉ ችግሮች ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ከወንጌላውያን አማኞች፣ አገልጋዮችና አብያተ ክርስቲያናት በኵል የሚስተዋሉ ናቸው። በሁለቱም በኩል ያለው መነቋቆር የቤት ውስጥ ጦርነት በመሆኑ ለወደረኞች፣ ሐሰተኞችና ተቃዋሚዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሥነ ምግባር መርሕን በመከተል የሚሠራ ዕቅበተ እምነት ጭምር ጕዳዮ የሚመለከታቸው አደገኛ ሐሰተኞችና በእነርሱ ወደ ተጭበረበሩ የዋህ ምእመናን ጋር ሳይዳርስ የውስጥ የገደል ማሚቶ ሆኖ የሚቀርበት ምክንያትም ይኸው ነው።

በሌላ ጎኑ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣው ውስጣዊ ክስ፣ ዕቅበተ እምነት በአንድ ጎራ ብቻ ባመዘነ አመለካከት እንደሚሠራ የሚያወሳ ነው። በፍቅርና አንድነት ስም እውነትና እምነትን ማቀብ የማይወድዱ በርካታ ሰዎች ባሉበት ዘመን፣ ዕቅበተ እምነት በከፍተኛ ደረጃ አሉታዊ በሆነ መንገድ በሚወሰድበት ዘመን፣ የዐቃብያ ሥነ ምግባር ለሥራው ደንቃራ በሆነበት ዘመን እንደዚህ ዐይነት ማስረጃ አልባ አሉባልታ እየተቀባበሉ ዕቅበተ እምነትን የተወሰነ አመለካከት የሚጋሩ ጥቂት ግለ ሰቦች ሥራ አድርጎ ማሳነስ ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው።

የችግሩ ውስብስብነት ከዚህ በላይ ሊያስወራ የሚችል ቢሆንም፣ ዐሳቤን በዚሁ ብቋጭ ይሻለኛል። እግዚአብሔር ለሁላችንም ጥበብና ማስተዋል ያድለን። ቸር እንሰንብት!


[1] ይህ ንዑስ ርእስ፣ ጕዳዩን አገራዊ ለማድረግ ያለመ ነው። እውነታው ደግሞ ከምዕራባውያን ዕቅበተ እምነት መነሻው ከአፍሪካ፣ ኤዢያና ላቲን አሜሪካ ዕቅበተ እምነት መነሻነት የተለየ መሆኑ ነው። የምዕራባውያን ዕቅበተ እምነት ዋና መነሻው (በአብዛኛው) ከእግዚአብሔር የለሽነትና ከፍልስፍናዊ ዕሳቤ የሚመጭ ሲሆን፣ የአፍሪካ፣ ኤዢያና ላቲን አሜሪካ ዕቅበተ እምነት መነሻውን በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ካላው የቃል እምነት ትምህርት፣ የብልጽግናና ጤንነት አስተምህሮና መሠረቱን አዲሱ ሐዋርያዊ ንቅናቄ (The New Apostolic Movement) ካደረገው የነቢያትና ሐዋርያት ልምምድ ያደርጋል (በርግጥ የእነዚህ አስተምህሮዎችና ልምምዶች መነሻቸው ምዕራባውያን መሆኑም ይሰመርበት)። በተጨማሪም ዕቅበተ እምነት በዙሪያችን ካሉ ሥላሴውያን ከሆኑና (ካቶሊክና ኦርቶዶክስ) እንዲሁም ሥላሴያውያን ካልሆኑ (እንደ ኢየሱስ ብቻዎችና ይሆዋ ምስክሮች) አንጻር ሰፋ ባለ መኩ መሠራት አለበት፡፡ እንዲሁም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በወንጌላውያኑ ዘንድ እጅግ አከራካሪ እየሆነ የመጣው የባላዊ እምነቶች ጕዳይም የዕቅበተ እምነት የትኵረት አቅጣጫ ሊሆን ይባዋል፡፡

[2] ቤተ ክርስቲያን በሚል ቃል ያልተጠቀምኩት በስሕተት ትምህርትና ልምምድ ውስጥ ያሉ በርካታ ድርጅቶች ከቤተ ክርስቲያንነት ይልቅ ወደ ግል ተቋምነት ያዘነበለ አንድምታ ስላላቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን በቃሉ እውነትና በታሪካዊ የቤተ ክርስቲያን መሠረት ላይ የቆመች ናት ብዬ አምናለሁ።

[3] ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያ ዕቅበተ እምነት መነሻ የሆኑ ችግሮች ምዕራባውያን ዘንድ የሉም ማለት አይደለም። አብዛኛው የምዕራባውያን ዐቃቤ እምነት ሥራ ትኵረቱን ያደረገው ግን እነርሱ ላይ አይደለም። ለዚህ ደግሞ የምዕራባውያንን ዕቅበተ እምነት መጻሕፍትና የቪዲዮ ሙግቶችን ማየት በቂ ነው።

[4] ሁለተኛው ከእምነት እንቅስቃሴ፣ ከብልጽግናና ጤንነት ትምህርት የሚመጫ ኑፋቄ ነው።

[5] Muriithi, Kevin: Apologetics in Afriica: Introduction (TGC Africa, October, 2019)

Alex Zetseat

አሌክስ ዘፀአት በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት (EGST) የስልታዊ ነገረ መለኮት ተማሪ ነው።

Share this article:

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ክብር ነው

አማረ ታቦር፣ “Seeing and Savoring Jesus Christ” ከተሰኘው የመጋቢ ጆን ፓይፐር መጽሐፍ እየቀነጨበ የሚያቀርበውን ንባብ ሦስተኛ ክፍል እዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል። በዚህኛው የትርጉም ክፍል፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ መለኮትነት ሐተታ የተሰጠበት ሲሆን፣ ይህም መለኮታዊ ማንነት በስሞቹ መንጸባረቁን ያስቃኛል።


ተጨማሪ ያንብቡ

ክፉ ነገር ለምን በሰዎች ላይ ይመጣል?[1]

አማረ ታቦር፣ “ክፉ ነገር ለምን በሰዎች ላይ ይመጣል?” በተሰኘው በዚህ ምጥን መጣጥፉ፣ ‘ጥሩ ሰዎች ላይ ክፉ እንዲደርስ ለምን እግዚአብሔር ፈቀደ?’ የሚለው ጥያቄ ወደ አእምሯችን ሲመጣ፣ ልናስባቸው የሚገቡ አራት ነጥቦች አሉ ይላል። ሙሉውን ጽሑፍ ያንብቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ

2 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • ጥሩ ምልከታ ነው። ሌላኛው አጽንኦት መሰጠት ያለበት ጉዳይ ምን ይታቀብ የሚለው ነው፤ ብዬ አስባለሁ። አሁን ላይ እየበዛ የመጣው ከእምነት ይልቅ ራስን መከላከል ሆኗል።

  • አሌክስ ወቅታዊውን ተጨባጭ ሁኔታ ከነባራዊው ታሪክና ከቃሉ መለኪያ አንጻር ለመቃኘት የሄደበት ጉዞ ድንቅና አስተማሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ዕቅበተ እምነት መጽሐፍ ቅዱሳዊና አገራዊ አውድና መልክ ያለው ሰፊ ከገልግሎት እንደሆነ በጠራ መንገድ ያመላከተ ጹሑፍ ነው። ዕቅበተ እምነት ላይ የሚሠሩ የአገራችን ጸሓፍት ግልጽ ምልከታ ቢታከልበት ደግሞ የበለጠ ይሆናል ብዬ አምናለሁ (ፈረንጅ መጥቀሱ እንዳለ ሆኖ)። አሌክስ በቀጣይ ሥራዎቹም ብዙ የሚያርሙና የሚያንጹ ሰፋፊ ምልከታዎችን እንደሚያበክትልን ተስፋ አደርጋለሁ።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.