አባይ ሚዛን
በማኅበራዊ ትሥሥራችን በብርቱ የምንፈልገው፣ በአንጻሩ የመስጠቱ ተራ የእኛ ሲሆን ንፉግነት የሚታዩብን ነገሮች አሉ። ከእነዚህ ዋንኞቹ ስንበድል ይቅርታ መጠየቅ (apology) እና ስንበደል ይቅርታ መስጠት (forgiveness) ናቸው። ስንበደል ይቅርታ መጠየቅ የመፈለጋችንን ያህል፣ ይቅርታን በመስጠት ቸር መሆን የምንቸገር ጥቂት አይደለንም። ይቅርታ እንዳንጠይቅ የሚተናነቁን በርካታ ውስጣዊ እና ማኅበራዊ ገደቦችን አልፈን ይቅርታ የጠየቅን ቀን እንኳ መንገዳችን የማይቀናልን አለን። ይቅርታችን፣ በበደላችን የፈረሰውን የመተማመን ድልድይ ጠግኖ የተራራቁ ልቦችን ከማቀራረብ ይልቅ፣ ይበልጡኑ አስቆጥቶ፣ አለመተማመናችንን እና መቃቃራችንን ይበልጡኑ የሚያጠናከረበት ጊዜ አለ። በዚህች መጣጥፍ ይቅርታን እናሰላስላለን። የይቅርታ ማኅበራዊ ፋይዳው ምንድነው? መገለጫውስ? ለምንስ ይቅርታ መጠየቅ እንቸገራለን? ይቅርታችን ውጤታማ እንዲሆንስ ምን እናድርግ? “እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል” ሲል ጌታችን ያስተማረን ጸሎት፣ መበደል የሰው ልጅ ድካማ ጎን አንዱ መሆኑን ያስታውሰናልና ይቅርታን ማሰላሰል ለተግባራዊነቱ ያዘጋጀናል። የዚህን መጣጥፍ ምልከታ ወሰን፣ እኛ በዳይ እና ሌሎች ተበዳይ እንዲያመለክት ተደርጎ ተገድቧልና የምንመለከተው ይቅርታን ስለመጠየቅ (apology) ብቻ እንጂ ይቅርታን ስለመስጠት (forgiveness) አይደለም።
የማይቀበሉት ይቅርታ
የጠየቅነው ይቅርታ፣ ከመጠገን ይልቅ ለበለጠ የልብ መሻከር ምክንያት ሲሆን እናስተውላለን። ይህ ደግሞ በአብዛኛው የሚሆነው፣ የጠየቅነው ይቅርታ የሰጠው ትርጉም እኛ ካሰብነው ሲለይ ነው። ተባዳዮች ይቅርታችን ከቅንነት የጎደለ (insincere) እና የእኛኑ ጥቅም ያሰላ (self-serving) ድርጊት አድርገው ባሰቡት ቁጥር ተቀባይነቱ ያንሳል። ይቅርታችን ከቅንነት ጎደለ የሚያሰኙት ምክንያቶች በርካታ ናቸው። ይቅርታችን መነሾው እውነትን ከመግለጥ ይልቅ እውነትን ለመደበቅ ከሞከረ፣ ቅን ነው ለማለት ያስቸግራል። ይቅርታ በእውነት ዙሪያ የሚደረግ የድብብቆሽ ጨዋታ መሆን የለበትም። ይቅርታችን እውነትን ከሐሰት ቀላቅሎ ከቀረበም እንዲሁ አደጋ ነው። አድማጫችን የቀላቀልነውን ሐሰት ያወቀ ቀን፣ ሌሎቹ እውነት እንደ ነበሩ ማመን ይቸገራል። ‘ሰላም እናውርድ’ በሚል ሰበበብ፣ ይቅርታው በሐሰት ላይ ከተመሠረተም፣ እውነት ተሰውታለችና ይቅርታችን እውነተኛ ሊሆን አይችልም። ይቅርታ ስንጠይቅ ያጠፋነውን ምክንያት ከማመን ይልቅ አላስፈላጊ ሰበብ ከደረደርን፣ ይቅርታችን መጠቀሚያ መሣሪያ እና እኛ ጥፋተኛ እንዳልሆንን ለማብራራት የተጠቀምንበት ሌላ ዘዴ ይሆናል። በሠራነው በደል ኀፍረት እና ሓዘን ካልተሰማን፣ ይቅርታችን እውነተኛ ነው ብሎ ማመን እንዲሁ ያስቸግራል።1
ይቅርታችን ተበዳዮች እንዲቀበሉት ከተፈለገ፣ ከምንም በፊት ለእውነት የምንሰጠው ከፍ ያለ ዋጋ ጎልቶ መታየት ይኖርበታል። በበደል ውስጥ ከምንም በፊት የተናቀችው እና የረከሰችው እውነት ናትና፣ እውነት ከወደቀችበት ተነሥታ ከፍ ብላ መውለብለብ ካልጀመረች ይቅርታ አጠያየቃችን ችግር አለበት። እውነትን አናንቆ እና አራክሶ የቀረበ ይቅርታ በርግጥም ጎደሎ ነው። ከላይ የጠቀስናቸውን ምክንያቶች ከይቅርታችን ጋር አያይዘን ባደረግን ቁጥር፣ ይቅርታ የሚጠይቀን ሰው በእኛ ላይ ያለው እምነት ስለሚሸረሸር፣ የእርስ በእርስ ግንኙነታችን ይበልጡኑ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም። አንዳንዴ እንደውም ከቅን ልብ የጎደለ ይቅርታ፣ በውስጣችን እየተንበለበ ያለውን የበቀል ምላሽ ከመግታት ይልቅ፣ ለድርጊት እንዲነሣሣ መንገድ ሊከፍትለት ይችላል።
ማኅበራዊ ፋይዳው
ይቅርታ አለማድረግ የተበደለ ሰው መብት ተደርጎ እንደማይታሰብ መገንዘብ ያስፈልጋል። ‘ተበድያለሁኝና ይቅር አልልም’ ማለት አያዋጣም። ይቅርታ ተጠይቀን መንፈግ፣ ሌሎች ስለ እኛ ያላቸውን ምልከታ ከተበድላችኋል ርኅራኄ ወደ ‘በድላችኋል’ ፍርድ ይቀይረዋል። እንዲህ ዐይነቱ ለይቅርታ ከፍ ያለ ቦታ የመስጠት ማኅበራዊ ምልከታ የደረጀው ያለ ምክንያት አይደለም። ከምክንያቶቹ መካከል ሁለት የይቅርታ ፋይዳዎች ጎልተው ይጠቀሳሉ።2 የይቅርታ ጥየቃ ከምንም በፊት ስለ ማኅበራዊ ሕግጋት የሚያስተላልፈው መልእክት አለ። ይቅርታ መጠየቅ ማኅበረ ሰቡ ላወጣቸው ሕግጋት የመገዛትን አስፈላጊነት ማሳያ መንገድ ጭምር ነው። እነዚህን ሕግጋት ጥሰን እንዳሻን እንሆናለን ካለን፣ የሕግጋቱን አስፈላጊነት እየተፈታተንና እየተገዳደርን፣ ብሎም በእርስ በርስ ግንኙነታችን ላይ አሉታዊ አሻራ እየጣልን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ያለ ማኅበራዊ ሕግጋት፣ ማኅበረ ሰብን ማሰብ እጅጉን ያስፈራል። ይቅርታ በጠየቅን ቁጥር ግን ከዚህ ቀደም የተላለፍናቸው ሕግጋት በርግጥም አስፈላጊ እንደ ነበሩ ማመናችን ያመለክታልና በማኅበረ ሰባችን ውስጥ ለይቅርታ ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው ያደርጋል።
ሁለተኛው ይቅርታ ተፈላጊ የሆነበት ምክንያት፣ ይቅርታ በመጠየቅ ሂደት ውስጥ፣ በበደላችን ተጠቂው ሰው ልክ እንደ እኛው ክቡር ሰው መሆኑን ማመናችን ያመለክታል። በመሠረቱ፣ የማናከብረውን እና ስለ እርሱ ግድ የማይለንን ሰው ልባዊ ይቅርታ ለመጠየቅ እንቸገራለን። ጥፋታችንን ስናምን፣ በበደልነው ሰው ላይ ሊደርስ የማይገባ ነገር ፈጽመናል ማለታችን ብቻ አይደለም። ከበደልነው ሰው ይቅርታን መፈለጋችን የሚያስተላልፈው ማኅበራዊ መልእክት የበደልነው ሰው ልክ እንደ እኛው ዋጋ ያለው እና ያደረስንበት ጉዳት ቀድሞውኑ ሊደርስበት የማይገባ መሆኑን ያመለክታል። ይቅርታ ስንጠይቅ፣ የበደልነው ሰው እና ከዚያ ሰው ጋር ያለን ትሥሥር ከእኛ ጥቅም በፊት እጅጉን የከበረ ቦታ እንዳለው ማመናችንንም ያመለክታል።
ልባዊ ይቅርታ
በማኅበራዊ ትሥሥራችን ይቅርታ የከበረ ዋጋ ካለው፣ ‘ይቅርታችን ተቀባይነት እንዲኖረው ምን ሊመስል ያስፈልጋል?’ የሚለውን መጠየቅ ያሻል።3 የእውነተኛ ይቅርታ ጅማሬው፣ ከምንም በፊት በዳይ የፈጸመውን በደል ከመገንዘብ ይነሣል። ይቅርታ ስንጠይቅ፣ ድርጊቶቻችን “ትክክል” እና “ስሕተት” በሚል የሚዳኙ መሆናቸውን እውቅና ሰጥተናል እንደ ማለት ነው። የይቅርታችን መነሾው የትላንት እኛነታችን የፈጸመውን ስሕተት ከመገንዘብ እንደመጀመሩ፣ በደላችንን ሳናምን የምንጠይቀው ይቅርታ ትርጉም አይኖረውም። ከልብ የመነጨ ይቅርታ፣ በደላችን አስመልክቶ የጥፋተኝነት ስሜት ውስጣችን ከማስተናገድ ይጀምራል፤ ስለዚህም እንጸጸታለን፤ እናዝናለን፣ እናፍራለንም። በድርጊታችን የምናፍርበት ምክንያት፣ የፈጸምነው ተግባር ልንሆን ከምንፈልገው ከሳችን ሚዛን (aspirations and ideals) አጉድሎ ከማሳየቱ አንጻር ነው። እፍረታችን የሚጠቁመው በግብረ ገብ ሚዛናችን፣ እኛነታችን ሌሎችን በመበደል አያምንም እንደ ማለት ነው። ሓዘናችን እና ጸጸታችን የሚያመለክተው ወደ ጎደልንበት ሚዛን ለመስተካከል ያለንን ዝግጁነትም ጭምር ነው።
ይቅርታችን ከልባችን ሲሆን ከጥፋታችን ተያይዞ ሊመጣ የሚችለውን ማኅበራዊም ሆነ ሕጋዊ ውጤት ለመቀበል እንዘጋጃለን። የይቅርታችን መነሾም በደላችን ሊያደርስብን የሚችለውን ውጤት ለመሸሽ ከማሰብ አይመነጭም። በዚህ ዐይነት የሕይወት ቅኝት ስንንቀሳቀስ፣ ምስክር ባለበትና በሌለበት የፈጸምነው በደል ውስጣችንን በተመሳሳይ መልኩ ይቆጠቁጠዋል። በዚህ መልኩ ይቅርታ ስንጠይቅ፣ እብሪታችን (arrogance) አከርካሪውን ተመትቶ፣ በትኅትና ድካማችንን መቀበላችንን ያመለክታል። የአጥፍቻለው ግንዛቤ፣ የጣስነውን ሕግ እና በደላችንን በትክክል በዳዮም ሆነ ይቅርታ ሰጪው እንዲያውቁት ይጠብቃል።
በደላችንን አስመልክቶ የተፈጠረብን ሓዘን እና እውቀት በውስጣችን አብሰልስለን የምናስቀረው ብቻ ግን አይደለም፤ ራሳችንን አዘጋጅተን፣ የበደልነው ሰው “ያደረኩህ ነገር ልክ አልነበረም፤ በድርጊቴም ጎድቼሃለው” በማለት ኀላፊነት የምንወስድበት ጉዳይ ነው። የደረሰው በደል የሚነገረው፣ ከተበደለው ሰው ውጭ ላለ ሦስተኛ አካል አይደለም። ይህ ከሆነ ነገሩ ኑዛዜ እንጂ ይቅርታ አይሆንም። ይቅርታ ከኑዛዜ በተለየ፣ በደለኛነት የሚታመነው ለበደልነው ሰው በመሆኑ ነው። ይቅርታ ስንጠይቅ “የመጎዳት ስሜት ስለተሰማህ አዝኛለሁኝ” ሳይሆን የምንለው፣ “ስለጎዳሁህ አዝኛለሁኝ” ይሆናል። ሁለተኛው አባባል ከመጀመሪያው የሚለየው በኀላፊነት ስሜት ስለተነገረ ነው። “የመጎዳት ስሜት ስለተሰማ አዝኛለሁኝ” የሚለው ንግግር ግን ትኩረቱ ጥፋት መሥራታችን ላይ ሳይሆን፣ ስሕተታችን ስለ እኛ የፈጠረው አሉታዊ ስሜት ለማረም የሚጥር ነውና ለተበደለው ሰው አይዋጥም።
የበደልነውን ሰው ይቅርታ ስንጠይቅ ሾላ በድፍን አይደለም፤ ነገር በድፍንፍን አይታለፍም፤ በዝርዝር ይነገራል። ማን ማንን እና በምን እንደ በደለ በማያምታታ መልኩ ግልጽ ይደረጋል። ዝርዝርን ማንሣት የሚያስፈልገው በምክንያት ነው። አንደኛው፣ ይቅርታችን ካልተዘረዘረ እኛ ባልፈለግነው መንገድ የጠየቅነው ይቅርታ ሊተረጎም ይችላል። ሁለተኛው፣ ተበዳይ ድርጊቱ የተፈጸመው ከምን ልብ እንደ ሆነ ለማወቅ ስለሚጓጓም ነው። ይቅርታ ስንጠይቅ፣ ለምን ቀድሞውኑ ጥፋቱን እንደ ፈጸምነው ተበዳይ ማወቅ ይፈልጋል። የበደልንበት ምክንያት በግልጽ ከተነገረ፣ ነገሩ ለምን ሆነ በሚል ከሚያብሰለስሏቸው አላስፈላጊ ግምቶች ተበዳዮች እንዲድኑ እና ልባቸው እንዲያርፍ እንረዳቸዋለን። ይህ ያስፈለገው በደሎች በብዙ ምክንያት ስለሚፈጸሙ ነው። አንዳንዴ ከቸልተኝነት፣ ሌላ ጊዜ ሳናውቅ ወይም ሆን ብለንና አስልተን ልንፈጽማቸው እንችላለን። በዳይ በዝርዝር ነገሩን ሲያስረዳ ተበዳይ፣ የመነሻ ሰበቡን ለመመርርና የራሱን ዳኝነት መስጠት የሚያስችለውን ግብኣት ይኖረዋል። በደላችንን በዝርዝር ስናነሣ፣ ራሳችንን እየተከላከልን ወይም ከኀላፊነት እየሸሸን እንደ ሆነ የሚያመለክቱ ማብራሪያዎችን ከመስጠት መቆጠብ ይኖርብናል። የምንጠቃቅሳቸው ዝርዝር ጉዳዮች እኛን ለመከላከል ያሰቡ ሳይሆኑ፣ የበደሉን ጥልቀት እና የእኛን ጉዳት አጉልተው ለማሳየት ያሰቡ መሆን ይገባቸዋል። አንዳንድ ሰዎች በደላቸውን በሽፍንፍን እንዲሸፈን ይፈልጋሉ፤ ከዚህም የተነሣ በዝርዝር ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ የሚያደሉት ስጦታ ወደ መስጠት ይሆናል።
እውነተኛ ይቅርታ፣ ከዚህ ቀደም ያጠፋነውን ጥፋት ለመካስ የሚያሳየው ፍቃደኝነት አለ። ለበደላችን ካሳ ለመክፈል የምንዘጋጅበት ምክንያት፣ በደላችንን እና ያደረስነውን ጉዳት በቀላሉ አለመመልከታችንን ለመጠቆም እና ነገሩን ለማረም ያለንን ውስጣዊ ዝግጁነት ለማሳየትም ጭምር ነው። የበደልነው በደል መካስ የሚችል ከሆነ፣ የምንችለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የማስተካከያ እድል ኖሮ ጥፋታችን ለመካስ አለመፍቀድ፣ ይቅርታችን ርካሽ ነው የሚል ስሜትን ለተበዳይ መፍጠሩ አይቀርም። ከዚህም የተነሣ፣ ያደረግነውን ጉዳት ለመካስ ምን ላደርግ እችላለሁኝ የሚለውን ማሰላሰል እና ለተግባራዊ ርምጃው ዋጋ ከፍለን መንቀሳቀስ ያስፈልገናል።
ይቅርታ ስንጠይቅ ለበደላችን ቀጥተኛ ኀላፊነት እንወስዳለን እንጂ ምክንያት እየደረደርን ራሳችንን ነጻ ለማውጣት አንጥርም። ይቅርታ የጠየቅንበት ምክንያት በደላችን ሊያስከትልብን የሚችለውን ነገር ተመልክተን፣ ከፍርድ በአቋራጭ ለማምለጥ በማሰብ አይደለም። ይቅርታ፣ የበደልነው ሰው ይቅርታ ከጠየቅነው ፍርዳችንን ያቀልልናል በሚል ስሜት የምንፈጽመው ተግባር አይደለም። ይቅረታችን ፍርዳችን ሊያቀልል የሚችልበት እድል ቢኖረውም፣ የይቅርታችን መሠረቱ የእኛኑ ፍጻሜ ማስተካከል ሳይሆን፣ ለበደልነው ሰው ከማሰብ የሚመነጭ ነው። ይቅርታ ከኮራ ልብ ውስጥ የሚቀዳ ድንፋታ ሳይሆን፣ ከተሰበረ ልብ ውስጥ የሚመነጭ የጥፋተኝነት ስሜት ነው። ይቅርታ የሚጠይቅ ሰው ካደረገው ነገር የተማረ እና ለወደፊት ያንኑ ላለመድገም የጨከነ ነውና ይቅርታ ስንጠይቅ ለወደፊት ተመሳሳይ ድርጊት ላለመፈጸም ቃል እየገባን እና ከስሕተታችንም እየተማርን ነው።
ለምን ይቅርታን እንሸሻለን
ሰዎች ይቅርታ መጠየቅን የሚሸሹባቸው ምክንያቶች አሏቸው።4 አንደኛው፣ ካደግንበት ማኅበረ ሰብ ባሕርይ ጋር የሚያያዝ ነው። ይቅርታ መጠየቅን የድካም እና የመጠቃት ምልክት ተደርጎ የሚያስብ ማኅብረ ሰብ አለ። ጥፋተኝነትን ለማመንን የምንቸገርበት ሌላኛው ምክንያት፣ ስሕተት መሥራትን እንድንፈራ ተደርገን ከማደጋችን ጋር ይያያዛል። ስሕተት መሥራት የተሸናፊነት ምልክት አድርገን እንድናስብ ሆነናልና። ስለዚህም፣ ሁልጊዜ እኛ ትክክል እንደ ሆንን ለማሳየት ስንል፣ ስሕተታችንን አናምንም። ይቅርታ ስንጠይቅ የሆነ ዐይነት ጉድለት (imperfection) እንዳለብን ማመናችንን ስለሚያመለክት፣ እንሸሸዋለን። እውነታው ግን፣ ይቅርታ ለመጠየቅ የሚቸገሩ ሰዎች ሥነ ልቦናቸው ደካማ እና ራሳቸውን በድፍረት (courage) መጋፈጥ የማይችሉ መሆናቸውን ያሳያል። በሥነ ልቦናቸው ያልጠነከሩ ሰዎች እውነተኛ ማንነታቸውን ይቅርታ መጠየቅ ስለሚያጋፍጣቸው ይሸሹታል።
የእኛ ዐይነቱ ኅብረተ ሰብ ይቅርታን ለመጠየቅ የሚከብደው ነው። በተለይ ደግሞ በዳይ ከተበዳይ ሲልቅ፣ በዳይ ዝነኛ እና ታዋቂ ሲሆን፣ ይቅርታን መጠየቅ አይታሰብም። ከዚህም የተነሣ አጥፍተው እንኳ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን፣ አሠሪዎች ሠራተኞቻቸውን፣ በግልጽ ቋንቋ ‘ይቅር በለን’ ሲሉ ማድመጥ ታምር ይሆናል። ታላላቆች ታናናሾቻቸውን ይቅርታ ለመጠየቅ ኩራት ይይዛቸዋል። ይቅርታ ከጠየቁ እልቅናቸውን አሳልፈው የሰጡ ወይም የተናቁ ሁሉ ይመስላቸዋል። አንዳንዱ ጋር እንደውም የቤቱ አለቃ የሚታወቅበት መንገዱ፣ አጥፍቶም ይቅርታ ባለመጠየቅ ጭምር ሆኗል። እንዲህ ዐይነት ሰዎች አገልጋዮች እና ልጆች ሲያጠፉ ግን ይቅርታን መጠየቅ እንዳለባቸው ያስባሉ። ለእነርሱ ይቅርታ ራስን በማዋረድ የአለቆችን ንዴት የማብረጃ ዘዴ ይሆናል። እውነታው ግን ይቅርታ አጥፍቶ ይቅርታ አለመጠየቅ፣ የምንፈልገውን ልባዊ ከበሬታ ከሰዎች ያሳጣናል እንጂ አያስገኝልንም።
ይቅርታን የምንፈራበት ሌላው ምክንያት ከመታበይ ጋርም ይያዛል። ትኅትና ሳንላበስ ማናችንም በደላችንን ማሰብ እንቸገራለን። ይቅርታ ለመጠየቅ መፍቀዳችን ሰው መሆናችንን ማመናችንን ያመለክታል። ሰዎች ለወዳጅነት የሚፈልጉት ደግሞ የማያጠፋ ፍጹም ሰውን ሳይሆን ስሕተቱን ተገንዝቦ ይቅርታ የሚጠይቅን ነው። ይቅርታ በጠየቅን ቁጥር፣ ከቀደመው ስሕተታችን ለመማር ያለን ዝግጁነት ያድጋል። በአንጻሩ ይቅርታ ለመጠየቅ ምክንያት በደረደርን ቁጥር ጥሩ ተምሳሌት የመሆን አጋጣሚ ያሳጣል።
ከይቅርታ ለጥቆ የሚመጣውን ነገር መፍራት እንዲሁ ይቅርታ ላለመጠየቅ ወጥመድ ነው። በደላችን ቢታወቅ ምን ሊከሰት እንደሚችል ለመገመት በመቸገር፣ ይቅርታን እንሸሻለን። ሰዎች ይቅርታችን ከመቀበል ይልቅ ‘ለበቀል ቢነሡሥስ’፣ ስንል እንሰጋለን። ይቅርታችን ተዛምቶ የአደባባይ ምሥጢር ሆኖ ከዚህ በፊት የነበረን ተቀባይነት ያሳጣናል የሚለው ስጋት እንዲሁ ማነቆ ይሆንብናል። የሕይወት ቅኝታችንም እጅጉን ራስ ተኮር በሆነ ቁጥርም፣ በሌላው ላይ ያደረስነው በደል መመልከት የምንችልበት አቅም አይኖረንም። ራስ ተኮር ምልከታ ዐይኑ የሚከፈተው ሌሎች ሲገፉት እንጂ ሌሎችን ሲገፋ አይደለም። ራሳችንን በሌሎች ጫማ አስቀምጠን የመመልከት አቅም ካላዳበርን፣ ጥፋታችንን መመልከትም ስለማንችል፣ ይቅርታን ከሌሎች መጠየቅን የምናስበው አይሆንም።
ሰው ይቅርታ መጠየቅ የሚችለው፣ ነገርን የሚመለከትበት መነጽሩ ራስ ተኮር መሆኑ ሲያበቃ እና ከሌላ ሰው ጋር ያለ ኅብረትን ቦታ መስጠት ሲቻል ብቻ ነው። ለኅብረት ዋጋ ከመስጠት ባነሰ ልብ ይቅርታ የሚጠይቅ ሰው፣ እድሉን ለሌላው ሰው ርኅራኄ ከማሳየት ይልቅ ራሱን ለመዋጀት (personal redemption) መጠቀሙ አይቀርም። ይቅርታ በመሠረቱ የራስን ጥቅም አስቦ የሚደረግ ነገር ሳይሆን፣ ከራስ በፊት ለእርስ በእርስ ግንኙነት ትልቅ ቦታ ከሚሰጥ ልብ ውስጥ የሚመነጭ ነው። ይቅርታ ስንጠይቅ፣ ተበዳዩን እና ከእርሱ ጋር ያለን ትሥሥር ምን ያህል ቦታ እንደሰጠነው የምናመለክትበት መንገድ ጭምር ነው። ይቅርታ ለመጠየቅ፣ ‘ነገሩን ማን ጀመረው?’ የሚለው ትልቅ ቦታ ሊሰጠው አያስፈልግም። የሌላው እኛን መበደል የእኛን በደል ስለማያስቀረው የመጀመሪያውን የይቅርታ ጥየቃ ርምጃ ለመውሰድ ማንንም አንጠብቅ። በምንም መልኩ፣ ይቅርታችንን ምክንያት በመደርደር እናደፍርሰው። ነገር ማድበስበስ ጥቅም የለውም። ስለዚህም፣ ያጠፋነውን ነገር ነቅሶ የማውጣት ባህል እናዳብር። በደሎቻችን እንዳልተደረጉ ቆጥረን ብንረሳቸው ይጠቅማል ከሚል ስሌትም እንዲሁ እንጠንቀቅ። ራሳችንን ይቅር የማለት ልምድ ካለን፣ ሌላው ሰው ላይ ለመፍረድ የማንቸኩል ከሆነ፣ ይቅርታን ለመጠየቅ አንቸገርምና ራሳችን ይቅር በማለት እንዲሁም ለሌሎች ባለን የምልከታ ቸርነት እንደግ።
- Lazare, Aaron. On apology. Oxford University Press, 2005, 117
- De Cremer, David, Madan M. Pillutla, and Chris Reinders Folmer. “How important is an apology to you? Forecasting errors in evaluating the value of apologies.” Psychological Science 22, no. 1 (2011): 45-48, 46
- Taft, Lee. “Apology subverted: The commodification of apology.” Yale LJ 109 (1999): 1135.
- Engel, Beverly. The power of apology: Healing steps to transform all your relationships. John Wiley & Sons, 2002፣ 37-43
Add comment