[the_ad_group id=”107″]

ክፉ ነገር ለምን በሰዎች ላይ ይመጣል?

በአማረ ታቦር

በጥሩ ሰዎች ላይ ክፉ ነገር እንዲደርስባቸው እግዚአብሔር ለምን ፈቀደ?” የመጽሐፍ ቅዱስ “ጥያቄ አልዎትን?” (Got Questions) የተሰኘው ድረ ገጽ፣ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይሞክራል[2] የድረ ገጹ መልስ እንዲህ ጠቅለል ተደርጎ መቅረብ ይችላል፦

“በጥሩ ሰዎች ላይ ክፉ ነገር ለምን ይደርሳል?” የሚለው ጥያቄ በሥነ መለኮት ጥናት እጅግ ከባድ ከሚባሉት ጥያቄዎች ዋነኛው ነው። ምንም እንኳን እግዚአብሔር አምላክ ክፋትና መከራ በዓለም ላይ እንዲከሰቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባያደርግም፣ እንዲሆኑ እርሱ የፈቀዳቸው መሆን ግን አለባቸው። ምክንያቱም እርሱ በሁሉ ላይ ሉዓላዊ አምላክ ስለ ሆነ! ከሁሉ አስቀድመን ግን፣ እኛ ዘላለማዊ፣ ወሰን የለሽ ወይም ሁሉን ቻይ ያይደለን የሰው ልጆች፣ የእግዚአብሔርን ዐላማ፣ አሠራርና ዐሳቦቹን በሙላት መረዳት እንደማንችል ራሳችንን እናሳምን።

ክፉ ነገር በጥሩ ሰዎች ላይ እንዲደርስ እግዚአብሔር ለምን ፈቀደ? ስለሚለው ጠያቂ ርእስ፣ መጽሐፈ ኢዮብ የሚለው አለው። ጻድቁ ኢዮብ እጅግ በጣም ተሰቃይቷል። ከነፍሱ ውጭ የፈለገውን እንዲያደርግበት በእግዚአብሔር የተፈቀደለት ሰይጣን፣ ኢዮብን ያለ ርኅራኄ አጥቅቶታል። ይህም ሆኖ ግን፣ የኢዮብ መልስ “እነሆ፤ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ”፤ “እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን” የሚል ነበር (ኢዮ.13፥15፤ 1፥21)። እግዚአብሔር ያደረገውን ለምን እንደፈቀደ ኢዮብ ባይገባውም፤ መልካም መሆኑን ስለሚያውቅ ግን፣ በእርሱ መታመኑን ቀጠለ።

በጥሩ ሰዎች ላይ ክፉ ነገር ለምን ይደርስባቸዋል? ልናምነው የሚከብድብንን ያህል፣ ቃሉ በፍጹማዊው አንጻር ሲታይ፣ “ጥሩ” የሚባሉ ሰዎች የሉም። ሁላችንም በኀጢአት የተበከልን እና የታመምን ነን (መክብብ 7፥20፤ ሮሜ 3፥23፤ 1ኛ ዮሐንስ 1፥19)። ኢየሱስም፣ “ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም” (ሉቃስ 18፥19) እንዳለው ነው። የሁላችንም የኀጢአት ኀይል በግራም ይሁን በቀኝ በኵል የታወቀ ነው። አንዳንዴ የእኛው የራሳችን ግላዊ ኀጢአት ነው፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ የሌሎች ኀጢአት ይሆናል። የምንኖረው በወደቀ ዓለም ውስጥ ነው፤ እኛም የዚህ ውድቀት ክስተት ተካፋዮች ነን። ከእነዚህ ክስተቶች አንዱ፣ ግፍና የማይረባ መሳይ መከራ ነው።

ጥሩ ሰዎች ላይ ክፉ እንዲደርስ እግዚአብሔር ለምን እንደሚፈቅድ ስናስብ፣ የሚከተሉትን አራት ነገሮችንም ማሰብ መልካም ነው፦

  1. ክፉ ነገር በዚህ ዓለም ሊፈጠር ይችላል፤ ሆኖም፣ ይህ ዓለም መጨረሻ አይደለም። “ለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 4፥16-18)። አንድ ቀን ሽልማት ይኖረናል። ይህም ታላቅ ይሆናል።

  2. ክፉ ነገር በጥሩ ሰዎች ላይ ይመጣል፤ ሆኖም እግዚአብሔር ክፉ ነገሮችን ለመጨረሻና ለዘላቂ መልካም ይጠቀምባቸዋል። “እግዚአብሔርንም ለሚወድዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” (ሮሜ 8፥28)። ዮሴፍ ጥፋት ስለሌለበት ንጹሕ ሆኖ፣ ካሰቃዩት መከራዎቹ በመጨረሻ ሲወጣ፣ የእግዚአብሔርን መልካም ዕቅድ ማየት ቻለ (ዘፍጥረት 50፥19-21 ይመልከቱ)።

  3.  ክፉ ነገር በጥሩ ሰዎች ይመጣል፤ ሆኖም እነዚህ ክፉ ነገሮች አማኞችን ለሰፊ አገልግሎት ያዘጋጇቸዋል። “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ … እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን። የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና” (2ኛ ቆሮንቶስ 1፥3-5)። በውጊያ ውስጥ ያሉትን ይበልጥ ሊረዷቸው የሚችሉት፣ በጦርነት የቆሰሉ ናቸው።

  4. ክፉ ነገሮች በጥሩ ሰዎች ላይ ይመጣል፤ በጣም መጥፎ ነገሮች የሚመጡት ግን፣ በጣም ምርጥ በሆኑ ሰዎች ላይ ነው። እውነተኛ ጻድቅ አንዱ ኢየሱስ ብቻ ነው። ይህም ሆኖ ግን፣ ከምናስበው በላይ ተሰቃይቷል። “ኀጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኀጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤” (2፩ኛ ጴጥሮስ 2፥20-23)። ኢየሱስ ለመከራችን ባዕድ አይደለም።

ሮሜ 5፥8፣ “ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” በማለት ያውጃል። የዚህ ዓለም ሰዎች በኀጢአት መበከል ውስጥ ሆነን እንኳ፣ እግዚአብሔር ይወድደናል። ኢየሱስ ለኀጢአታችን ቅጣት ለመውሰድ የወደደን፣ እሰከ መሞት ድረስ ነው (ሮሜ 6፥23)። ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛችን አድርገን ከተቀበልን (ዮ ሐንስ 3፥16፤ ሮሜ 10፥9) ምሕረት ይደረግልናል፤ በሰማይም የዘላለማዊ ቤት ተስፋ ይኖረናል (ሮሜ 8፥1)።

እግዚአብሔር ነገሮች እንዲሆኑ የሚፈቅደው በምክንያት ነው። የእርሱን ምክንያት ብንረዳው ወይም ባንረዳውም፤ እግዚአብሔር መልካም፣ ጻድቅ፣ ፍቅርና መሐሪ መሆኑን ማስታወስ አለብን (መዝሙር 135፥3)። በምንም ልንረዳቸው የማንችላቸው መጥፎ ነገሮች ብዙ ጊዜ ይደርሱብናል። በእዚህ ወቅት የእግዚአብሔርን መልካምነት ጥያቄ ውስጥ ከማስገባት ይልቅ፣ መልሳችን እርሱን መታመን ሊሆን ይገባል። “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” (ምሳሌ 3፥5-6)። እምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና!


[1] ይህ መጣጥፍ፣ “የራቢ ሃሮልድ ኩሽነር ጥያቄና መልስ” የሚለው ጽሑፍ ተከታይ ነው።https://hintset.org/articles/harold-kushners/

[2] https://www.gotquestions.org/bad-things-good-people.html


Amare Tabor


አማረ ፈቃደ ታቦር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በስታትስቲክስ፣ ሁለተኛውን በኮምፒውተር ሳይንስ የሠሩ ሲሆን፣ መጻሕፍትን የማንበብ ልምድና የመተርጎም ዝንባሌ አላቸው። በተለይ በክርስትና ዙሪያ የተለያዩ መጣጥፎችን በመጻፍና በመተርጎም ይበልጥ ማገልገልን ይሻሉ። 
E-mail: taboramare@gmail.com

Share this article:

የጸሎት ኀይል ለአእምሮ ተሓድሶና ለውጥ

እግዚአብሔርን ያስደነቀና ያስገረመ ነገር ካለ በርግጥም አስገራሚና አስደማሚ ጕዳይ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በኢሳያስ 56፥19 ላይ እንዲህ ይላል፡- “ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም …”፡፡ እግዚአብሔር በምንም የማይገረምና የማይደነቅ አምላክ ነው። ታድያ በሰው ልጆች አለመጸለይና አለመማለድ ስለ ምን ይሆን የተደነቀው? የምር ልብ ብለን ብናየው እርሱን ያስደነቀ ነገር እውነትም ድንቅ ነው። በጸሎት ውስጥ ያለው ኀይል ወሰን የማይገኝለት ነው፤ አምሳያም የሌለው ነው። ፀሓይንና ጨረቃን በስፍራቸው ያቆመና ባህርን ከፍሎ እንደ ግድግዳ ያቆመ ኀይል ከጸሎት ውጪ ከየት ሊያገኝ ይችላል? ሙታንን ማስነሣትና አጋንንትን ማስወጣት የሚችል ጉልበት በየትኛውም የምርምር ጣቢያና ዩኒቨርስቲ ውስጥ እንዳለ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም። መናን ከሰማይ የሚያወርድና ውሃን ከዐለት ለማፍለቅ የሚችል ኀይል በታሪክ ውስጥ አልተመዘገበም። ጸሎት ለደካማ ሰዎች የተሰጠ ብርቱ መለኮታዊ ክንድ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

የራቢ ሃሮልድ ኩሽነር ጥያቄና መልስ

“የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ፣ የክፋትን ኀይል በሙላት መቆጣጠር እንደማይችል እና ክፋት/መከራ ከእርሱ ፈቃድ ውጭ ሊሆኑ እና ሊከሰቱ እንደሚችል በድፍረት ደመደሙ። ለእዚህ ዐይነት መልሶቻቸው ብዙ እጆች አጨበጨቡላቸው፤ የብዙዎችንም ልብ ‘አሳረፉ’።”

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.