
ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ – መፍቀሬ አፍላጦን ካህን
በብርታቱ ኀያልነት ያስገበራቸውን አገራት በግሪክ ፍልስፍናና ባህል ማጥመቅን እንደ ዐቢይ ተግባሩ አድርጎ ይዞታል፡፡ እናም የመከከለኛው ምሥራቅ፣ የአውሮፓና የሰሜን አፍሪካ ግዛቶችን በእጁ ባስወደቀ ጊዜ በጽርዕ ባህልና ፍልስፍና ከመንከር ወደ ኋላ አላለም፡፡
[the_ad_group id=”107″]
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን በመሠረታዊ አቋሞቿ ላይ የአመለካከት ለውጥ እያመጣች እንደ ሆነ ይስተዋላል፡፡ ለውጡም ከእምነት ወደ ስሜታዊነት፣ ከተጨባጭ እውነት ወደ ሕልመኝነት እንዲሁም ከምክንያታዊነት ወደ ምሥጢር ናፋቂነት ዞራለች፡፡ ግን ለምን? ለምን በመጣው የትምህርት ንፋስ ሁሉ እንወሰዳለን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱ ዘርፈ ብዙ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእነዚህም ጥቂቶቹን ለማንሣት ያህል፡- እግዚአብሔርን ወደ መምሰል የሚያመራውን ንጹሕ የእግዚአብሔር ቃል ከማስተማር ይልቅ የራሳችንን ገድል በየምስባኩ ማውራታችን፣ ሕዝባችንን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሳይሆን የግለ ሰቦች ተከታይ ማድረጋችን እንዲሁም አማኙ ማኀበረ ሰብ ከምንም ነገር በላይ የተኣምራት ናፋቂዎች እንዲሆን ማድረጋችንና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ድኽነት፣ መከራ፣ ጉስቁልና፣ በሽታ ወዘተ… በሞላበት ምድር ውስጥ መኖራችን እሙን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች ለችግራቸው መፍትሔ ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ መሄዳቸውን የማይቀር ያደርገዋል፡፡ ያመንነውም ወንጌል ከእነዚህ ሁሉ ሊያድነን የታመነ ነው፤ ድነታችን ሁለንተናዊ ነውና፡፡ ነገር ግን ተስፋችን ምድራዊ አይደለም፤ ዘላለማዊ እንጂ፡፡ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ እነዚህ ሁሉ ችግሮች አይኖሩም፡፡ ፍጹም በሆነ ዓለም ውስጥ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እግዚአብሔር ለወደ ፊት የምትመጣውን ፍጹም ሕይወት ምንነት የሚያሳይ ቅምሻ የሆነ ቸርነቱን ሰዎችን ከበሽታቸው በተኣምራዊ መንገድ በመፈወስና አልፎ አልፎ ለችግራቸው መፍትሔ በመስጠት የተስፋይቱን ምድር በናፍቆት እንድንጠባበቅ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን በዚህች ምድር ውስጥ ስንኖር የሚገጥመንን መከራ ሁሉ አሁን፣ እዚሁ ሊያስወግድልን ቃል አልገባልንም፡፡ ስለዚህ በመካከላችን የሚደረግ ማንኛውም ዐይነት ተኣምር የመጪው ተስፋ ቅምሻ እንጂ ዋናው ሕይወት አይደለም! ሕዝባችን ግን ቅምሻው ላይ የቀረ መስሏል፤ መጪውን ዘመን መናፈቁን አቁሟል፡፡ የችግራችን መሠረቱ እግዚአብሔርን ተስፋ የምናደርገው ስለ ዘላለማዊው ሳይሆን ስለ ምድራዊው ሕይወት መሆኑ ይመስላል፡፡ ይህም እጅግ ከንቱ ነው!
በቅርቡ በመዲናችን ተፈጸመ የተባለው ክስተት ከማስደንገጥም አልፎ የሚያስቆጣ ሆኗል፡፡ ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፡- “ሜጀር ፕሮፌት ሼፐርድ” ቡሽሪ የተባሉ ግለ ሰብ ተጋብዘው በሚሌንየም አዳራሽ የሦስት ቀን ኮንፍራንስ ያደርጋሉ፡፡ በእነዚህ ቀናትም ብዙ ተኣምራት እንደፈጸሙ እየተወራላቸው ነው፤ ወርቅ እና አልማዝ ከሰማይ አንጠባጥበዋል፣ የዶላርና የብር ኖቶችን አዝንበዋል እንዲሁም ለአንዳንዶች የባንክ ደብተራቸውን ዳጎስ አድርገውላቸዋልም ተብሏል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የተኣምራቱ መፈጸምና አለመፈጸም ሳይሆን፣ ʻበርግጥ እኚህ ሰው ከእግዚአብሔር ናቸው ወይስ አይደሉም?ʼ የሚለውን ማሳየት ብቻ ይሆናል፡፡
በኮንፍራንሱ ላይ የተገኙ የዐይን እማኞች እንደገለጹት ከሆነ የድኽነት እርግማንን ሊሰብር የሚችል፣ ከበሽታ የሚፈውስ፣ ለትዳር መሰናክል ፍቱን መድኃኒት የሚሆን በአጠቃላይ ለሁሉም ችግር መፍትሔ የሚሆን “ውሃ” በዝግጅቱ ላይ በብዙ ሺህ ዶላር ይሸጥ ነበር፡፡ “ነቢይ” ቡሽሪ ይህን ተግባር በሚሌንየም አዳራሽ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሀገራቸው በቋሚነት የሚያደርጉት ተግባር እንደ ሆነ “የቤተ ክርስቲያናቸውን” ድረ ገጽ በግልጽ ይዘግባል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የእርሳቸው የፎቶ ምስል ያለበት “ቡሽሪ ዘይት”፣ “ቡሽሪ ሳሙና”፣ “ቡሽሪ ቅባት” እና “ቡሽሪ ቅዱስ ውሃ”ን በገበያ ላይ አቅርበዋል፡፡[i] “ቡሽሪ ሳሙና” የንግድ ችግር ላጋጠማቸው ነጋዴዎች ገበያ ሳቢ፣ በትዳራቸው ችግር ላለባቸው ባለ ትዳሮች የችግራቸው መፍትሔ፣ በገንዘብ እጥረት የሚቸገሩ የተትረፈረፈ ገንዝብ የሚያስገኝ፣ ለሕሙማን ፈውስ የሚሰጥ እንዲሁም መንፈሳዊ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ነፍስ ከኀጢአት የሚያነጻ እንደ ሆነ፣ ዘይቱም ቢሆን ለነፍስ ድነትን እንደሚያስገኝ ነው ቡሽሪ የሚናገሩት፡፡[ii] በነገራችን ላይ ሰውዬው የሚሸጡት ውሃ፣ ሳሙናና ቅባት የሰዎችን ሁለተናዊ ችግር ሊፈታ የሚችለው በግዥ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ የሰው ልጆችን ኀጢአት ከሚያነጻው ከኢየሱስ ደም ሌላ ተገኘ ማለት ነው?(ዕብ. 9፡7-13፡20፤ 1ኛ ዮሐ. 1፡7 ይመልከቱ) እዚህ ላይ የቡሽሪን ኑፋቄና ሐሰተኛ ነቢይነት ልብ ይሏል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ስለመሰለው ጉዳይ ምን እንደሚል እንመልከት፡፡
በሐዋርያት ሥራ ላይ እስጢፋኖስ በአይሁዳዊያን እጅ በድንጋይ ተወግሮ ከሞተ በኋላ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት በመነሣቱ ምክንያት ከሐዋርያት በስተ ቀር አማኞች ሁሉ በሰማርያ ባሉ ሀገሮች ተበተኑ፤ ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ሄዶ የእግዚአብሔርን መንግሥት በኢየሱስ ስም ይመሰክርላቸው ነበር፤ ብዙ ሰዎችም አምነው እንደ ተጠመቁ በዚሁ መጽሐፍ እናነባለን፡፡ በከተማዋ ውስጥም “ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ፥ እየጠነቈለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ።” (የሐዋ. 8÷9) ይላል፡፡ ይህም ሰው አምኖ ተጠምቋል፤ በፊልጶስ እጅ “የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተኣምራት ባየ ጊዜ” ተገርሟል፡፡ ሐዋርያቱ ከኢየሩሳሌም መጥተው በሰዎች ላይ እጅ ሲጭኑ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሞሉ ሲሞን በተመለከተ ጊዜ ይህንን ስጦታ እርሱም በገንዘቡ ለማግኘት ተመኘ፡፡ “ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና፡- ʻʼእጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ።” (የሐዋ. 8÷18-19) ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፡- “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ” የሐዋ. 8÷20 (አጽንዖት የጸሐፊው)፡፡ በገንዘባቸው ከእግዚአብሔር የሚገኝን ስጦታ ለማግኘት ስለሚጥሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው እንዲህ ነው፡- “ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሓ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና።” (የሐዋ. 8÷ 21-23)
ዶላር እየመነዘሩ የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘባቸው ለመግዛት የሚጥሩ የሀገራችን ሰዎች ተግባራቸው ከሲሞን ተግባር ጋር ተመሳሳይ ነውና ስለፈጸሙት በደል እግዚአብሔር ይቅር ይላቸው ዘንድ ሊለምኑ ይገባል፡፡ ዳሩ እግዚአብሔር የልባቸውን ስስት ዐይቶ ለበላተኞች አሳልፎ ሰጥቶአቸው እንደሆነስ ማን ያውቃል?
ሌላው ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ፣ ከውሃና ሻሽ ሽያጭ ጀርባ የሚተላለፈው መልእክት ለፍጹም ስሕተት የሚመራና ሰውን በአምላክ መንበር የሚያስቀምጥ ተግባር መሆኑን ነው፡፡ አድራጊ ፈጣሪ፣ አዳኝ ፈዋሽ የሆነውን ሁሉን ቻይ እግዚአብሔርን በአንዲት ቢልቃጥ ውስጥ ባለ ፈሳሽ ወይም ቁራጭ ጨርቅ ለመተካት የሚደረግ ድፍረትም ጭምር ነው፡፡ ይልቁንም ፈውስ ቢያስፈልገን፣ ለችግራችን መፍትሔ ቢያሻን ʻአቤቱ አምላካችን ፈቃድህስ ቢሆን በሚፈውሰው እጅህ ዳሰንʼ ብለን እንማጠናለን እንጂ፣ ሕያውን አምላክ በግዑዝ እንለውጠው ዘንድ የምንደፍር እኛ ማን ነን?!
ሌላኛው በጣም አስገራሚው ነገር ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ተዘጋጅቶ የነበረው ፕሮግራም ሲሆን፣ ይህም እንደ ቲያትር ቤት የመግቢያ ክፍያ ነበረውም ተብሏል፡፡ አገልግሎት በክፍያ የሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ “ነቢይ” ቡሽሪ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ስጦታ (ከእግዚአብሔር ከሆነ) ገንዘብ እያስከፈሉ፣ ከፍለው ለገቡ ሰዎች ሲያከፋፍሉ ዋሉ አሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህን እናደርግ ዘንድ የመርሕም ሆነ የምሳሌ ፈለገ አልተወልንም፤ ይልቁን ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ገንዘብ ማስከፈል ይቅርና ከቤተ ክርስቲያን ድጋፍን ለመቀበል አንዳንድ ጊዜ አሻፈረኝ ይል እንደ ነበረ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን (1ቆሮ. 9ን ያንብቡ)፡፡ ታዲያ “ነቢዩ” እንዴት በክፍያ የሚገባበት የተለየ ጉባኤ ለማዘጋጀት ቻሉ? በወንጌልም ይነገዳል እንዴ? በርግጥ የግል አውሮፕላናቸውን የገዙት የተዋጣላቸው “ነጋዴ” በመሆናቸው ሳይሆን አይቀረም፡፡[iv] አገልግሎት በክፍያ ከሆነ ከፍለው መግባት የማይችሉ ክርስትያኖች ይህንን የእግዚአብሔር ጸጋ መካፈል አይችሉም ማለት ነውን? አማኝ ማኅበረ ሰቡንስ ደኻ ሀብታም ብሎ መክፈልስ አይሆንም?
የወንጌላውያን መሠረታዊ የእምነት መገለጫ ከሆኑት መካከል መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን እና በአስተምህሮአችን ላይ ፍጹም ሉዓላዊ ነው የሚል ነው፡፡ የአስተምህሮአችንና የትምህርታችን ትክክለኝነት የሚዳኘውም በመጽሐፍ ቅዱስ መመዘኛ ብቻ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ልምምዶቻችን እና ትውፊቶቻችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ሊጋጩ አይገባም፤ መጽሐፉ በሕይወታችን፣ በእምነታችን እንዲሁም በአስተምህሯችን ላይ ላዕላይ ባለ ሥልጣን ነው ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን “ነቢይ” ቡሽሪ “እኔ ከሄድኩ በኋላ የምታሙኝ እንዲሁም የምትቃወሙኝ ትኖራላችሁ፤ በእግዚአብሔር ሰው ላይ አንዳች ነገር ብትናገሩ ትሞታላችሁ” በማለት አስፈራርተዋል ተብሏል፡፡ በርግጥ እውነተኛ ከሆኑ ትምህርታቸውም ይሁን ድርጊታቸው እንዳይመረመር ለምን ፈለጉ? መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈስን ሁሉ መርምሩ”የሚለውን ትእዛዝ እንዳንፈጽም ለምን ያስፈራሩናል? ይህ ፈጽሞ ራስን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ማስተካከል፣ እንዲያውም ለማስበለጥ የሚደረግ ሙከራ ነውና ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ በሌላ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ እናደርገው ዘንድ የሚያደፋፍረን “መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና” በማለት ነው፡፡
የማንኛውም ሰው አገልግሎትና ኑሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ሊዳኝ ይገባዋል፡፡ አንድ ነቢይ ከእግዚአብሔር ይሁን አይሁን የሚታወቀው ተግባሩ እና አስተምህሮው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ ይህንን እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠውን የመመርመር መብት መንፈግ ራስን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ማስተካከል ነውና ትክክል አይደለም፡፡ አገልግሎቱ በእግዚአብሔር ቃል የማይፈተሽ አገልጋይ ሊኖር ፈጽሞ አይገባም፡፡ በመሆኑም፣ ባላቸው “መንፈሳዊ ሥልጣን” ተጠቅመው አገልግሎታቸው እና ድርጊታቸው በእግዚአብሔር ቃል እንዳይፈተሽ ለማስፈራራት ያደረጉት ሙከራ ተቀባይነት የለውም፡፡ በሚሌኒየም አዳራሽና በአዲስ አባባ ያደረጉት ተግባር በእግዚአብሔር ቃል ሲፈተሽ እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡ የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ የሆነውን በኢየሱስ ደም የሚገኘውን የኀጢአት ስርየት፣ ፈውስንና ተኣምራትን በውሃና በሻሽ ሽያጭ ለውጠውታል፤ የእግዚአብሔርን ነጻ ስጦታ በገንዘብ ለመሸጥ ሞክረዋል፤ “እግዚአብሔር በሰጣቸው ስጦታ” ሕዝቡን ማገልገል ሲገባቸው እንደ ቲያትር ቤት ገንዝብ እያስከፈሉ “አገልግለዋል”፤ በመጨረሻም አገልግሎታቸው በእግዚአብሔር ቃል እንዳይፈተሽ አስፈራርተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩት ሰውዬው ሐሰተኛ ነቢይ መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡
አሁን አሁን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አካሄድን ለተመለከተ ሰው ʻእዚያም ሠፈር ጸበል ፈለቀʼ በሚል ብኂል የሚመራ ይመስላል፡፡ ሰኞ እገሌ የተባለ ሰው የፈውስ ፕሮግራም ስላለው ሰው ሁሉ ወደዚያ ይጎርፋል፤ ማክሰኞ እነ እንትና ቤተ ክርስቲያን፣ ረቡዕ … ሐሙስ … ዓርብ ወዘተ…፡፡ ክርስትናችን ከአንዱ “ጸበል” ወደ ሌላኛው መንከራተት ሆኗል፤ የእግዚአብሔርን ቃል ዘንግተን ኑሮአችን ወዲያና ወዲህ ተመሳቅሏል እውነተኛውን አምላክ ማመን ትተን ተኣምራት ናፋቂዎች ብቻ ሆነን ቀርተናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኖቻችን የሕክምና መስጫ ተቋማት ልዩነቱ እስኪጠፋን ድረስ አገልግሎታችን ሁሉ ለሰዎች አካላዊ ሕመም መፍትሔ መፈለግ ማዕከል መስሏል፡፡ በርግጥ እግዚአብሔር አምላክ ፈዋሽ አምላክ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህች ምድር ላይ ስንኖር የፈቀደውን እንጂ ሁሉንም አይፈውስም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እምነት ʻቢፈውሰኝም ባይፈውሰኝም እግዚአብሔርን አምነዋለሁʼ የሚል ነው፡፡ እግዚአብሔር ʻለችግሮቻችሁ ሁሉ አሁን መፍትሔ እሰጣለሁʼ የሚል ተስፋ ቃልን አልገባልንም፡፡ እርሱ የሰጠን ተስፋ “እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ፤ አሮጌው ነገር ሁሉ ያልፋል” የሚል ነው፡፡ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ መከራችን፣ ጉስቁልናችንና በሽታችን ፈጽሞ ይወገዳል፡፡ ከእርሱ ጋር ለዘላለም በደስታ እንኖራለን፡፡ ይህ ነው ትክክለኛ ተስፋችን! ይህንን የተስፋ ቃል አጥብቀን ይዘን እስከ መጨረሻው ድረስ በእምነት ልንሮጥ ይገባል እንጂ፣ እንዲሁ እዚያም እዚያም ʻጸበል ፈለቀʼ ብለን ልንንከራተት አይገባም፡፡ እግዚአብሔር ሊፈወሰንና ሊባርከን ከፈለገ ባለንበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊያደርገው ይችላልና፡፡
የ“ነቢይ” ቡሽሪን አገልግሎት በእግዚአብሔር ቃል ስንፈትሽ በርግጥም እኚህ ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመሆናቸው ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡ ይልቁንም ሐሰተኛ ነቢይ እንደሆኑ የሚጠቁሙ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የውሃና የሻሽ ሽያጩ፣ አገልግሎትን በክፍያ እንዲሁም ቃሌንና ተግባሬን አትመርምሩ የሚል ማስፈራሪያቸው በግልጽ ሰውዬው ከእግዚአብሔር ዘንድ ላለመሆናቸው ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ የሰውዬው ትልቁ ግብ ብር መሰብሰብ ነበር፤ ይህም ተሳክቶላቸዋል፡፡ ምን ያድርጉ? እረኛ ያጣ ሕዝብ አግኝተዋላ! ኧረ እባካችሁ አገልጋዮች እንንቃ፤ ሕዝባችን የእግዚአብሔርን ቃል ተጠምቷል፤ የሚጠብቀው እረኛ አጥቷል፤ የሚያሰማራው እረኛ ይፈልጋል፡፡ አሁንም መጋቢያን እና አገልጋዮች ሁላችንም እግዚአብሔር በዐደራ የሰጠንን ሕዝብ በእውነተኛው ቃል በተገቢው መንገድ ካልመገብነውና ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ካልጠበቅነው የተሰጠንን ዐደራ ባለመወጣታችን ተጠያቂዎች ከመሆን አናመልጥም፡፡ በዚህች አጭር ጽሑፍ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችን የምንማጸነው ሕዝባችንን የበግ ለምድ ለብሰው ከሚበዘብዙ “ሐሰተኛ ነቢያት” ይታደጉ ዘንድ ነው፡፡
ልዑሉ አምላክ በቸር ያሰንብተን!
Tekalign Duguma
Beware of False Prophet: An evolution of the ministry of “Major Prophet Shepard” Bushiri in Addis Ababa, Ethiopia.
[i] http://www.nyasatimes.com/2014/02/01/prophet-bushiri-launches-holy-soap-and-anointed-oil/ http://www.malawiana.net/new/?p=2301
[ii]http://www.malawivoice.com/2014/02/01/major-prophet-shepard-bushiri-introduces-holy-anointed-soap-it-will-wash-all-your-demons/
[iii] http://www.nyasatimes.com/2014/02/01/prophet-bushiri-launches-holy-soap-and-anointed-oil/
[iv] http://www.urbanlifemalawi.com/prophet-shephered-bushiri-gets-an-18-seater-private-jet/
Share this article:
በብርታቱ ኀያልነት ያስገበራቸውን አገራት በግሪክ ፍልስፍናና ባህል ማጥመቅን እንደ ዐቢይ ተግባሩ አድርጎ ይዞታል፡፡ እናም የመከከለኛው ምሥራቅ፣ የአውሮፓና የሰሜን አፍሪካ ግዛቶችን በእጁ ባስወደቀ ጊዜ በጽርዕ ባህልና ፍልስፍና ከመንከር ወደ ኋላ አላለም፡፡
ክርስትና በአፍሪካ ውስጥ በስፋት በመስፋፋት ላይ እንደ ሆነ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን ʻእየተስፋፋ ያለው ክርስትና ምን ዐይነት ገጽታ አለው?ʼ የሚለው ትኩረት የሚያሻው ጥያቄ ነው። የቁጥር ዕድገት ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያላትን መገኘት በማግዘፍ የሚኖራትን ሚና ያጎላዋል። በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ዕድገቱ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ይዞ ይመጣል። ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ዕድሎች የማትጠቀም ወይም ለተግዳሮቶች ምላሸን የማትሰጥ ከሆነ በምትኖርበት ማኅበረ ሰብ ውስጥ ያላት ፋይዳ እጅግ አናሳ ይሆናል።
መጋቢ በድሉ ይርጋ (ዶ/ር)፣ ‘የሐሰተኛ ነቢያት እና መምህራን አድራሻ የት ነው?’ ሲሉ ይጠይቃሉ፤ ምላሹንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈልገው ያቀርባሉ፤ የሐሰተኞቹ መገኛ ምካቴውን አስቸጋሪ እንዳደረገውም ያመለክታሉ።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment