[the_ad_group id=”107″]

ለምን ተወለደ?

‘ለምን ተወለደ?’ የሚለው ጥያቄ የሕይወት ጥያቄ ነው። ሆኖም ግን በአዲስ ኪዳን “ተወለደ” የሚለው ቃል፣ ወልድ ፍጹም ሰው ስለ መሆኑ (ስለ ነገረ ትሥጉት/incarnation) ከሚነግሩን ገለጻዎች አንዱና ዋነኛው ይሁን እንጂ፣ “ብቸኛው” ግን አይደለም። በአዲስ ኪዳን የትሥጉት ነገረ መለኮት በብዙ ቃላት ያሸበረቀ ነው። “ተወለደ” ከሚለው ዕሳቤ በተጨማሪ፣ በአዲስ ኪዳን እኩል አጽንዖት ተሰጥቷቸው የምናገኛቸው ተጨማሪ ነገረ መለኮታዊና ሙያዊ የሆኑ ገለጻዎች አሉ። በእነዚህ ገለጻዎች የነገረ ትሥጉት ግንዛቤያችን ሊዳብር ይገባዋል።

የዚህ ዐጭር ጽሑፍ ዐላማ፣ ስለ ልደቱ (ስለ ገና) በግል በአምልኮ ጊዜ ስናሰላስል ይሁን፣ በኅብረት ስንዘምረው፣ በስብከታችን ስናውጅ ወይም በአስተምህሮ ስናብራራ፣ የዳበረና የፋፋ የነገረ ትሥጉት መረዳት እንዲኖረን ይረዳን ሐሳብ ለማቀበል ነው።

የአዲስ ኪዳን የነገረ ትሥጉት ትርክት በሚከተሉት ቃላት/ሐረጎች ያሸበረቀ ነው፦

  • “ተወለደ” (ሉቃ 2፥10)
  • “ሥጋ ሆነ” (ዮሐ 1፥14)
  • “በመካከላችን ዐደረ” (ዮሐ 1፥14)
  • “ራሱን ባዶ አደረገ”
  • “ተገለጠ” (1ዮሐ 3፥8)
  • “ከሰማይ ወረደ” (ዮሐ 3፥11–13)
  • “ተላከ” (ገላ 4፥4፤ ሮሜ 8፥3)
  • “የባሪያን መልክ ያዘ” (ፊል 2፥5–7)
  • “መጣ” (1ጢሞ 1፥15)
  • “በሥጋና በደም ተካፈለ” (ዕብ 2፥24–25)
  • “በኀጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ” (ሮሜ 8፥3) ወዘተ.

እነዚህን ቃላት/ሐረጎች በሦስት መደብ እናስቀምጣቸው፦

የመጀመሪያው መደብ ተጸንሶ ከመወለዱ አንጻርና እና የሰውን ባሕርይ ሙሉ ገንዘቡ አድርጎ መውሰዱን የሚያስገነዝቡን ናቸው (ተወለደ፣ ሥጋ ሆነ፣ የባሪያን መልክ ያዘ፣ በሰው አምሳል ሆነ፣ በኀጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ…)።

ሁለተኛው መደብ ከሞላ ጎደል፣ ሰው ከመሆኑ በፊት ስለ ነበረው ቅድመ ሕላዌ የሚያስገነዝቡን ናቸው (ከሰማይ ወረደ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፣ ተገለጠ፣ በመካከላችን ዐደረ…)።

ሦስተኛው መደብ ደግሞ የመወለዱን ዐላማ ያሳዩናል (ተላከ፣ መጣ…)።

እነዚህ መደቦች “ለምን ተወለደ?” የሚለውን ጥያቄ የሚመልሱ ሲሆን፣ ነገረ ትሥጉትን እና ነገረ ድነት የተያያዙ መሆናቸውን ያመለክቱናል።

ተወለደ (τίκτω, γεννάω)

“መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” (ሉቃ 2፥10–11)።

የገና በዓል በደረሰ ጊዜ፣ ስለ ሕፃኑ ኢየሱስ ከሚመጡልን ምስሎች የተለመደ ሆኖ የሚነገረው፣ “በግርግም የተኛ” ሕፃን የሚለው ነው። ይህ በርግጥ አስደናቂ እውነት ነው። ለዘመናት የሚጠበቀው የምሥራች ቃል አሁን ታወጀ። ምድር ደስ ይበልሽ፤ የዓለም መድኃኒት የሆነ “ሕፃን”፣ እርሱም የዳዊት ልጅ ክርስቶስ ተወልዷልና። የንጋት ጎህ ቀደደ። ተስፋው ተገለጠ።

በመጀመሪያ ይህ “ተወለደ” የሚለው ቃል አስረግጦ የሚያሳየን፣ የሕፃኑ መወለድ በአንድ እጅ አስቀድሞ እግዚአብሔር ከሰጠው የድነት ታሪክ ፍጻሜ ጋር መያያዙን ነው። ለዚህ ነው በሉቃስ ወንጌል ላይ ከክርስቶስ መወለድ ጋር ተያይዞ “ተስፋው ተፈጸመ” የሚለው ዕሳቤ እንደ አዝማች የሚደረደረው።

• የማርያም መዝሙር፤ “ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።” (ሉቃ 1፥55)፤
• የዘካርያስ ትንቢት፤ “ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው … ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣ ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣ ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሓላ ለማሰብ …” (1፥72–73)፤
• የስምዖን ባርኮት፤ “ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና”፤
የነቢዪቱ ሐና ስብከት፤ “የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ” ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች፤

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ተወለደ” የሚለው ቃል ኢየሱስ ፍጹም ሕፃን ልጅ መሆኑን ያሳየናል፤ “በጥበብና በቁመት፣ በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት” ማደግ ያስፈልገው ነበር። በሰው ስም “ኢየሱስ” ተብሎ ተሰይሟል። ትውልዱ በዳዊትም ቤት ተቆጥሯል። እንደ ማኛውም ሕፃን ጡት ጠብቷል፤ ፊደል ቆጥሯል፤ ተርቧል፤ አልቅሷል…። ሕፃኑ ለዐደጋ ግሉጥ ከመሆኑ የተነሣ፣ ዮሴፍ ወደ ግብፅ ይዞት ሊሰደድ የተገባ ነበር።

የማይወሰነው አምላክ ተወሰነ። ይህ ሕፃን በአንድ እጅ እንደ ማንም ሕፃን እንደ ነበር፣ ደግሞም በሌላ እጅ ‘ልዩ ሕፃን’ ይህም “መለኮታዊ” መሆኑን ማቴዎስ ሲያሳየን፣ “የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነው … እርሱ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋል” ይላል። ይህ ሕፃን ሰው ብቻ ሳይሆን፣ “አዳኝም” ጭምር ነው።

ሉቃስ ደግሞ ይህንን ውጥረት፣ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” በማለት ሕፃኑን “የእግዚአብሔር ልጅ” ይለዋል (ከመሲሓዊ ስያሜው ባለፈ)። እንዴት ሁለቱ በአንድ ጊዜ እውነት ሆኑ? “ምሥጢር! ምሥጢር!” ብለን ከመጮህ የዘለለ እውቀት የለንም።

ሥጋ ሆነ (γίνομαι)

“ቃልም ሥጋ ሆነ…”። የዮሐንስ ወንጌል፣ እንደ ማቴዎስ፣ አሊያም እንደ ሉቃስ በውስጡ “የልደት” ትረካን አያካትትም። በዮሐንስ ሕፃን ሲወልድ አናይም። የምናገኘው “ቃል” ከተሰኘና ቅድመ ሕላዌ ካለው አካል ጀምሮ፣ ወደ ነገረ ትሥጉቱ የሚሄድ እንቅስቃሴ ነው። ይህ ከላይ ወደታች የሚሄድ የአተራረክ ዘዬ፣ ዮሐንስን ከሌሎቹ ወንጌላውያን ይለየዋል። በቅድመ ትሥጉት ማንነቱ፣ ቃል “ነበረ” ይለናል። የሚጠቀመው “ሆነ” የሚለውን የመሆን ግሥ ሲሆን፣ ይህም ‘በመጀመሪያ ቃል የሆነ፤ እግዚአብሔር የሆነ…’፣ ሳይሆን “ነበር” የሚለውን የመሆን ግሥ በመጠቀም ነው። ይኸውም፣ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ … ቃልም ከእግዚአብሔርም ጋር ነበረ … ቃልም እግዚአብሔርም ነበረ።” “ነበር”፣ “ነበር”፣ “ነበር”! ሆኖም ግን ቁጥር 14 ላይ ሲደርስ፣ ዮሐንስ የመሆን ግሡን ከ“ነበረ” ወደ “ሆነ” ይለውጠዋል፤ ‘ቃልም ሥጋ ነበረ’ ከማለት ይልቅ፣ “ቃልም ሥጋ ሆነ” በማለት። “ሆነ … ዐደረ”።

ይህ ገለጻ አስረግጦ የሚያመለክተን ቁም ነገር፣ “ቃል” በሁለት መደብ በአንድ ጊዜ የሚመደብ መሆኑን ነው። በአንድ በኩል ቃል በመለኮት መደብ ይኖራል። እርሱ አማክሎተ ፍጥረት ነው (Agent of Creation)፤ አማክሎተ ድነት ነው (Agent of Redemption)፤ ቃል አማክሎተ አስተርዮ ነው (Agent of Revelation)። በሌላ በኩል ደግሞ ቃል ከዚህ ቀደም “ያልነበረውን” ነገር ወሰደ፤ “ሥጋ ሆነ”።

በቁጥር 1 ላይ፣ “እግዚአብሔር” የሚለውን ቃል ዮሐንስ በሁለት ዐይነት መንገድ ይጠቀመዋል። አንድኛው አብን የሚወክል የመለኮት አካል ስም ሆኖ ጥቅም ላይ ሲውል፣ “ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበር” እርሱም አብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ “እግዚአብሔር” የሚለው ቃል የመለኮት ባሕርይን ገላጭ ሆኖ ጥቅም ላይ ውሏል፤ “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ”። ስለዚህ ይህ መለኮታዊ ባሕርይ ገንዘቡ ሆኖ ይኖር የነበረው፣ እንዲሁም መለኮታዊ ከሆነው ከሌላኛው አካል ፊት ለፊት ሕልው ሆኖ ይኖር የነበረው ቃል፣ መለኮታዊ ባሕርይውን ሳይለቅቅ፣ ከዚህ ቀደም ያልነበረውን “ሰብዓዊ ባሕርይ” ገንዘቡ አደረገ።

እንቅስቃሴው ከላይ ከምጡቅ ሕልውናው ይጀምርና ወደ ምድር ሰብዓዊ ማንነቱ ይዘልቃል። ቃል “ሥጋ” አልመሰለም፤ ቃል ሥጋ ሆነ እንጂ!

ይህ አቅጣጫ በዮሐንስ ትረካ ኋላ እየዳበረ ይመጣል። ይህ ሕይወትና ብርሃን የሆነው ቃል (ዮሐ 1፥4-5)፣ ሥጋ ሆኖ ተገልጦ (1፥14)፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር በተለይ በመስቀል ሞቱ ተርኮልን (3፥16) ወደ ነበረበት በክብር ይመለሳል።

እግዚአብሔር ሕይወት፣ ብርሃን፣ ፍቅር ነው። የፍቅሩ፣ የሕይወቱና የብርሃኑ መገለጫ ሞገድ፣ የክብሩም መንጸባረቂያ ሥፍራ ‘ትሥጉቱ’ ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው። ዮሐንስ የክርስቶን ልደት “ተወለደ” በሚለው ቃል ሳይሆን፣ “ሆነ” በሚለው ስለተረከልን፣ ነገረ ትሥጉቱን ከሌላና ከምጡቅ ገጽታው አንጻር እንድናይ ረድቶናል።

መልካም በዓል!

Share this article:

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ስለምትቀበል፥ በውስጡ የሚገኙትን መልእክቶችም ትቀበላለች። ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ (የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች) በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገቡና ለቤተ ክርስቲያን ጥቅምና መታነጽ የተሰጡ ናቸው (ሮሜ ፲፪፥፮- ፰፤ ፩ቆሮ. ፲፪፥፬-፲፩)። ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብታተ መንፈስ ቅዱስን የምትረዳበት፥ የምትተረጕምበት፥ የምታስተምርበትና የምትለማመድበት መንገድ የተለየ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

ፍቅር፣ ፍትሕ እና ሰላም የኢየሱስ መንገድ

በዚህ ልዩ ዕትም፣ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው እስክንድር ነጋ የሕንጸት ዕንግዳ ሆኖ ቀርቧል። አገራችን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችና ዴሞክራሲ የሚከበሩባት አገር እንድትሆን መሥዋዕትነትን የጠየቀ ትግል አድርገዋል ከሚባሉት ግለ ሰቦች መካከል አንዱ እስክንድር ነው። በዚህም፥ ከዘጠኝ ጊዜያት በላይ ደጋግሞ ለእስር የተዳረገው እስክንድር፣ በአጠቃላይ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ በእስር አሳልፏል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.