[the_ad_group id=”107″]

ነውር የሌለው አምልኮ

በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን ከሚያዚያ 2–3፣2006 ዓ.ም.“ጉባኤ ስለ ወላጅ አጥ ልጆች በኢትዮጵያ፡- ሀገራዊ ጥሪ ለሀገራዊ መፍትሔ” በሚል መሪ ቃል ጉባኤ ተካሄዶ ነበር። ጉባኤውን ያዘጋጁት “ቤታኒ ክርስቲያን ሰርቪስስ”፣ “ሜክ ዩር ማርክ”፣ “ቅድሚያ ፋውንዴሽን”፣ “የልጆች ዕድገት ሥልጠናና ምርምር ማዕከል” እንዲሁም “አባት ለሌላቸው ብሩኅ ተስፋ” ሲሆኑ፣ ድርጅቶቹም በልጆች አገልግሎት ዙሪያ የተለያየ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው። በዝግጅቱ ላይ 470 የሚደርሱ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ የተለያዩ ቤተ ሰቦች እና ለልጆች ልዩ ሸክም ያላቸው ወገኖች እንደታደሙ ከአዘጋጆቹ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

ከፕሮግራሙ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆነው የ“ቤታኒ ክርስቲያን ሰርቪስስ አፍሪካ” ኦፕሬሽን ዳሬክተር እና በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተጠሪ የሆኑት አቶ ሲቢሉ ቦጃ ፕሮግራሙ ሁለት ዓላማ ይዞ እንደተዘጋጀ ለሕንጸት ገልጸዋል። “አንደኛው፤ ወላጆቻቸውን ያጡ እና ለችግር የተጋለጡ ሕጻናት ያሉባቸውን መጠነ ሰፊ ችግሮች በማሳየት ተግባራዊ ምላሻችን ምን መሆን እንዳለበት የሚጠቁም ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በሀገራችን ውስጥ ስላሉ በጎ ጅማሬዎች እና መልካም ተሞክሮዎች ግንዛቤ በመፍጠር ለሀገራዊ ጥሪ ሀገራዊ መፍትሔ ለመስጠት ማነሣሣት ነው” ብለዋል።

አቶ ሲቢሉ እንደሚሉት ከሆነ፣ ሕጻናትና ልጆች ከሚያስፈልጋቸው ልዩ ትኩረት በመነሣት የእምነት ተቋማት፣ በማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ተሳታፊ የሆኑ ድርጅቶች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የኅብረሰተ ሰብ አካላት በጉባኤው አማካይነት ስለ ወላጅ አጥ ልጆች እንክብካቤ ጠቃሚ መረጃ ለማግኘትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመጀመርም ሆነ፣ የተጀመረውን ለማጠናከር ከሚያስችሉ ተሞክሮዎች ጋር የመተዋወቅ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

“ሀገራዊ ጥሪ ለሀገራዊ መፍትሔ” ሲባል?

በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ከአንድ መቶ ስድሳ ሦስት ሚሊዮን ወላጅ ዐጥ ሕጻናት በላይ እንደሚኖሩ፣ ከእነዚህም አምስት ሚሊዮን ያህሉ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ለጉባኤው የተዘጋጀው መጽሔት ይገልጻል። የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ፣ ሌሎች በሽታዎች፣ ድኽነት፣ ረኻብ፣ ግጭት፣ የቤተ ሰብ መፍረስ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና ያልታቀደ እርግዝና ለችግሩ መባባስ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ነው ጥናቶች የሚያሳዩት። በርግጥም ጉዳዩ ወቅታዊ እና አንገብጋቢ መሆኑን በተለያየ ጊዜ የተለያዩ መረጃዎች አሳይተዋል። የችግሩ ስፋት እና ጥልቀት በየመንገድ ዳር፣ በየቆሻሻ መጣያ ገንዳው እና በየትራፊክ መብራቱ ረዳት አጥተው ከሚንከራተቱት ሕጻናት ገጽታ ላይ ማንበብ ይቻላል። ሕጻናቱ ለረኻብ እና ለእርዛት፣ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለወሲባዊ ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጡ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለአካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ጉዳት ተጋልጠው ያለ ምንም ተስፋ የሚመሽ የሚነጋውን ቀን ያስተናግዳሉ። ለመሆኑ እነዚህ ልጆች የማን ናቸው?

አቶ ንጉሤ ቡልቻ “መስታየት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ለዚህ መልስ ያሉትን አቅርበዋል። እንደ እሳቸው እምነት ከሆነ ልጆቹ “የእኛ ናቸው”። ይህንንም ሲያብራሩ፣ “ወላጅነት፣ አባትነት፣ እናትነት፣ ወንድምነትና እኅትነትን የደምና የሥጋ ጉዳይ ብቻ ነው ያለው ማን ነው? በፈቃደ ሥጋ ተገናኝቶ ልጅ መውለድ፣ ቤት መመሥረት አንዱና ዋናው ʻወላጅነትʼ ወይም ʻባለቤትነትʼ ነው ብለን ብንስማማም፣ ዐይነታቸው የተለያየ ሌሎች ʻወላጅነቶችʼም መኖራቸውን ገሽሽ ማድረግ አይገባም።” በማለት ይገልጻሉ። እንደ ማኅበረ ሰብ፣ እንደ ዜጋ፣ እንደ ሰብአዊ ቤተ ሰብ አባላት በየሜዳው ላይ ያለው ልጅ ቢርበው፣ ቢጠማው፣ ቢታረዝ፣ ቢሞቀው፣ ቢበርደው፣ ቢጨምት፣ ቢያብድ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም፤ ምክንያቱ ደግሞ ለዚህ ችግር ኅብረተ ሰቡ የራሱን ደርሻ መወጣቱ ስለማይቀር ነው። ለዚህም አቶ ንጉሤ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት፣ “ልጆቹን የወለደ ብቻ ሳይሆን አሁን ያሉበትን ቅርፅና ወዘና፣ መልክና ገፅታ የሰጣቸው፣ ያሳደጋቸው፣ ወይም ያሟሻቸውም ጭምር መታሰብ አለበት” የሚለውን ነው፤ ያንን ቅርፅ የሚሰጠው ደግሞ ኅብረተ ሰቡ ራሱ ነው።

ለዚህ ሥር የሰደደ ችግር በተለያየ መልኩ ለመፍትሔነት በሚል ሥራ ላይ የዋሉ ተለያዩ ማኅበራዊ ግልጋሎቶች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል፡- ሕፃናቱ ለችግር ከመጋለጣቸው በፊት ጠንካራ የቤተ ሰብ ትሥሥር እንዲኖር እና ቤተ ሰብ እንዳይፈርስ ቅድመ መከላከል ማድረግ፣ ሕፃናቱ ለችግር ከተጋለጡና በቅርብ የሚረዳቸው ከሌለ ቤተ ሰባዊ እንክብካቤ በሚያደርጉ አካላት (Foster care) ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻል፣ ከዚያም ሲያልፍ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ሀገር ጉዲፈቻ እንዲሰጡ ማድረግ ናቸው።

ጉዲፈቻ?

“ጉዲፈቻ” ለሚለው የኦሮሚኛ ቃል አቻ የአማርኛ ስያሜ፣ “የጡት ልጅ” ወይም “የማር ልጅ” የሚል ነው። ከሌላ ሰው አብራክ የተገኘን ልጅ እንደ ወላጅ በመሆን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቱን ጠብቆ እንደ ገዛ ልጅ ማሳደግ የጉዲፈቻ አድራጊ ኀላፊነት ነው። መቼ እንደ ተጀመረ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ባይቻልም፣ በሀገራችን ባህል መሠረት ለረጅም ጊዜ ሲፈጸም የኖረ ሥርዐት ሲሆን፣ ለጉዲፈቻ የሚሰጡ ልጆች በአብዛኛው ወላጅና አሳዳጊ ያጡ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ አሳዳጊዎቹ ደግሞ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውና በተለያየ ምክንያት መውለድ ያልቻሉ እንደ ነበር ታሪካዊ ዳራውን እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣል።

አንድ ልጅ ለውጪ ሀገር ዜጋ በጉዲፈቻ የሚሰጠው በሀገር ውስጥ ሊረዳ የሚችልባቸው መንገዶች ሁሉ ከጠፉ ነው። ይህም የውጭ ሀገር ጉዲፈቻ የመጨረሻ አማራጭ መሆኑን ያሳያል። ምንም እንኳን በፌደራል ደረጃ የተሻሻለው የቤተ ሰብ ሕግ ስለ ጉዲፈቻ በዝርዝር የሚደነግግ ቢሆንም፣ ይህንን ጉዳይ በሚያሰፈጽሙ ባለድርሻ አካላት ምክንያት ብዙ ሕፃናት እንደሚጉላሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች መገንዘብ ተችሏል።

ታኅሣሥ 18 ቀን፣ 2006 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ተዘጋጅቶ የተላለፈው “ጉዲፈቻ” የተሰኘው ዘጋቢ (ዶክመንተሪ) ፊልም ችግሩ የሚገኝበትን አሳሳቢ ደረጃ የሚዳስስ ነበር። በተለይ ራሳቸውን መጠበቅ እና መንከባከብ የማይችሉ ሕፃናት በማያውቁት ሀገር፣ በማያውቋቸው ግለ ሰቦች እጅ እንዲያድጉ የሚያደርገው የውጪ ሀገር ጉዲፈቻ ለከፋ የማንነት ጥያቄና የሥነ ልቦና ቀውስ ሊዳርጋቸው እንደሚችል ብዙ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሌሎች መረጃዎችም እንደሚያሳዩት ሕፃናቱ ወደ ውጪ ሀገር ከሄዱ በኋላ የተለያዩ ጥቃቶችና ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይደርሱባቸዋል። ለዚህም እንደ ምሳሌ በአንድ ሰሞን በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች ከፍተኛ ሽፋን አግኝቶ የነበረውን የሃና ዊሊያምስ ታሪክ መጥቀስ ይቻላል። ይህች የ13 ዓመት ታዳጊ በጉዲፈቻ አሳዳጊዎቿ በደረሰባት ጥቃት ለሞት ተዳርጋለች። ሃሪ እና ካሪ ዊሊያምስ የተባሉ እነዚህ አሜሪካውያን ባልና ሚስቶች ʻሕጻኗን ደብደበው፣ አስርበው እና አሰቃይተው ገድለዋልʼ በሚል በተመሠረተባቸው ክስ ጥፋተኛ ተብለው የ37 እና 29 ዓመት እስር ቢበየንባቸውም ከትውልድ ሀገሯ፣ ከባህሏ እና ከተገኘችበት ማኅበረ ሰብ ርቃ ትኖር ለነበረችው ምስኪን ሕፃን የሕይወት ምትክ አልሆነም።

ሕጉ ምን ይላል?

በኢትዮጵያ በነበረው የዳበረ ልማድ የጉዲፈቻ ሥርዐት ትኩረት የጉዲፈቻ አድራጊውን ጥቅም እንጂ የጉዲፈቻ ልጁ ጥቅም ባለመሆኑ ሕጉን ማሻሻልና የሕፃኑን መሠረታዊ ጥቅም ማስከበር አስፈላጊ ሆኗል። ይህም በፊደራል ደረጃ በተሻሻለው የቤተ ሰብ ሕግ በዝርዝር ተደንግጓል። የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ናታን ጥበቡ እንደሚናገሩት ከሆነ፣ በአዲሱ የቤተ ሰብ ሕግ ላይ ስለ ጉዲፈቻ ከተደነገጉ አንቀጾች መካከል አንቀጽ 180 የጉዲፈቻ ስምምነት አድራጊዎችና የተፈጥሮ ወላጆች መብት፣ አንቀጽ 184 የጉዲፈቻ አድራጊዎች የዕድሜ ገደብ ሁኔታ በተመለከተ፣ አንቀጽ 191 (3) የሕፃኑን ፈቃደኝነት በተመለከተ እንዲሁም ሞግዚትነትና ቀለብን በተመለከተ እንዲሁም አንቀጽ 197 ለዚህ ማሳያ ናቸው።

ይሁን እንጂ፣ በተሳሳተ መረጃና የግል ጥቅማቸው ላይ ባተኮሩ ግለ ሰቦችና አንዳንድ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ለሕፃናቱ ጥቅምና መብት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ በሕፃናቱ ስም ለመነገድ ያስቻለቸው ሕጉ ላይ ያለው ውስን ክፍተት መሆኑን አቶ ናታን ጨምረው ይናገራሉ። “ሕፃናት ትዳር ለሌላቸው ጉዲፈቻ አድራጊዎች እንዲሰጡ ሕጉ መፍቀዱ፣ አንዱን የጉዲፈቻ ወላጅ ቢያጡ ወይም ተገቢውን እንክብካቤ ሊያደርግላቸው ባይችል ሌላኛው ወላጅ ኀላፊነቱን የሚወጣበትን ሁኔታ ከማሳጣቱም በላይ በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ ለመጣው የተመሳሳይ ጾታ ጥቃትም ሕፃናቱ ሊጋለጡ ይችላሉ” ይላሉ የሕግ ባለሙያው። አክለውም፣ “በሕጋችን ጉዲፈቻ አድራጊው ከጉዲፈቻ ተደራጊው በተጨማሪ ስለሚኖሩት ልጆች ቁጥር አለመገደቡ ለጉዲፈቻ ተደራጊው ሕፃን የሚሰጠው እንክብካቤ የተሟላ እንዳይሆን ያደርገዋል” ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ጉዲፈቻ አድራጊው በአካል መቅረብ ይኖርበታል የሚል አስገዳጅ ሕግ ስለሌለ በወኪል ስምምነቱን መፈጸሙ ሕፃኑ የሚገኝበትን ማኅበረ ሰብ፣ ባህል፣ ቋንቋና አኗኗር አሳዳጊው እንዳያውቅ ክፍተት እንደ ፈጠረ ያብራራሉ።

“ያልወለድኩት ልጅ አባባ ቢለኝ …?”

ታዲያ የወንጌል አማኞች ኀላፊነት እዚህ ላይ ምን መሆን አለበት? የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ለእነዚህ በራሳቸው መቆም፣ ለራሳቸው መናገር እና ራሳቸውን መርዳት ለማይችሉ ሕፃናት ምን አጥጋቢ ሥራ እየሠራች ነው? የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተፈላጊነቱና ትክክለኛነቱ እየተረጋገጠ ባለበት በዚህ ጊዜ አቅሙ ያላቸው የቤተ ሰብ ኀላፊዎች፣ በተለያየ ምክንያት መውለድ ያልቻሉ እና ሌሎችም ምን ያህል በጉዲፈቻ ልጅ ወስዶ የማሳደግ ተነሣሽነት አላቸው? ይህ ተደጋግሞ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው ለማለት ያስደፍራል።
ወ/ት ድንስሪ ብርሃኑ ወላጆቻቸውን ላጡና ለአደጋ የተጋለጡ ልጆች የተሻለ ሕይወት እንዲያገኙ በሁሉም ደረጃ ግንዛቤ የመፍጠር፣ ኅብረተ ሰብን የመቀስቀስ እና የማስተማር እንዲሁም የማስተባበር ሥራዎች ላይ በበጎ ፈቃደኛነት ላይ ተሰማርተው ያገለግላሉ። ʻምን እናድርግ?ʼ ለሚለው ጥያቄ ምላሻውን ለሕንጸት የሰጡት ወ/ት ድንስሪ፣ ምንም እንኳን “ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ከሰጠው ተልእኮ አንዱ ለሕፃናት በተለይም ደግሞ ወላጆቻቸውን ላጡና ለአደጋ የተጋለጡትን እንድናስብ፣ በተለያየ መንገዶች እንድንደግፋቸው እና እንድንንከባከባቸው” ቢሆንም፣ እንደ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ በበቂና በዘላቂ መንገድ ኀላፊነታችንን እየተወጣን ነው ለማለት ግን እንደማያስደፍር ያሠምሩበታል።

ይህንን ሐሳብ አቶ ሲቢሉ ቦጃም ይጋሩታል፤ “ልዩ ትኩረት የሚስፈልጋቸውን እነዚህ ሕፃናት ሕይወት ለመቀየር እኛ ቀዳሚ ተሰላፊ መሆን ይኖርብናል። በእኔ ዕይታ ይህን አንገብጋቢ ጉዳይ በባለቤትነት መውሰድ ያስፈልጋል። እንደ ዜጋ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ እንደ ክርስቲያን ʻችግሩ የእኛ ነውʼ የሚል ጠንካራ ዕሳቤ መፈጠር አለበት” ይላሉ። በተለይም ሕፃናቱን ለመርዳት ካሉት በርካታ አማራጮች መካከል ጉዲፈቻ የሚበረታታ እንደሆነና ከዚህም ባለፈ ጠንካራ ሥነ መለኮታዊ ንጽረት ሊሰጠው እንደሚችል ይገልጻሉ።

በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን በተካሄደው ጉባኤ ላይ ጽሑፍ አቅራቢ ከሆኑት መካከል አቶ ማሙሻ ፈንታ አንዱ የነበሩ ሲሆን፣ ስለ ሥነ መለኮታዊ ፋይዳው ሲጠቅሱ፣ “ወደ ላይ ለአምልኮ የሚዘረጉት እጆቻችን ወደ ጎንም መዘርጋት ይኖርባቸዋል። ልጆችን መርዳት እና ችግረኞችን መጠየቅ ምርጫችን እና የትርፍ ጊዜ ጉዳያችን ነው ማለት አይቻልም። ይህ እውነተኛ እና ነውር የሌለው አምልኮ እንደ ሆነ መጸሐፍ ቅዱስ ነግሮናል።” ብለዋል። በሌላኛው የሙግት ነጥባቸው ደግሞ ይህን ማድረግ ይዞት የሚመጣውን ዕድል በውል ሊጤን እንደሚገባውና የጌታን ፍቅር ለመናገር፣ ወንጌልን ለመመስከር ምቹ መንገድ እንደ ሆነ አስረድተዋል።

ወ/ት ቤተልሔም ፈላስፋ “በሰባተኛ እና መርካቶ ሕጻናት መርጃ ፕሮጀክት” ውስጥ የማኅበራዊ ሠራተኛ ሆና የምትሠራ ስትሆን፣ በሥራው ላይ ያለውን ስሜት ስትገልጽ፣ “ቀደም ብዬ ስለ ሕፃናት የነበረኝ ስሜት እዚህ አገልግሎት ውስጥ ከገባሁ በኋላ ሙሉ በሙሉ ተለውጧል። እንኳን ኖሮን፣ ከጉድለታችን እንኳን ብናደርገው መንፈሳዊ እርካታው በቃላት የሚገለጽ አይደለም። ʻአይዞህʼ ባይ ሲያገኙ ተስፋ የሚፈነጥቁትን ትንንሽ ዐይኖቻቸውን ማየት ታላቅ ፍሥሐ ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ይህንን ማድረግ የምስኪኖች ወዳጅ የሆነውን ኢየሱስን ማሳየት ነው” በማለት ነበር። አክላም፡- “የተገፉትን ማዳን፣ ለደኻ አደጉ መፍረድ፣ ስለ መበለቲቱም መሟገት ይህ ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተግባር ነውና ቅዱሳን ይህን ለማድረግ ቢፈቅዱ በረከቱን በሕይወታቸው እንደሚያዩት እኔ ሕያው ምስክር ነኝ” ብላለች።

ያልወለዱትን ልጅ እንደ ራስ አድርጎ ማሳደግ በብዙዎች ዘንድ የሚደፈር አይደለም፤ ምናልባት የዘመድ ወይም የሩቅ ቤተ ሰብ ልጅ ተብሎ ካልታሰበ በቀር። ሆኖም እነዚህን ንጹሓን፣ ግን ደግሞ ምንም መድረሻ የሌላቸውን ልጆች ማሰብ ይገባል። በተለይም፣ በችግር ውስጥ ያሉ ሕፃናት በአገር ውስጥ የሚረዳቸው በማጣታቸው ምክንያት በማያውቁት ባህልና ማኅበረ ሰብ ለመኖር ሲገደዱ ማየት ስሜት የሚነካ ነው። እነሱን በማይመስሉ ሰዎች መኻል ከመኖር፣ ራሳቸውን ፈልጎ ከማጣትና ከማንነት ቀውስ ለመታደግ በኢትዮጵያውን የሚፈጸም ጉዲፈቻ ትልቅ ሚና ሊኖረው ይችላል። ያልወለዱትን ልጅ የራስ አድርጎ፣ አሳድጎና አስተምሮ ለቁም ነገር ማብቃት፣ “መወለድ ቋንቋ ነው” የሚለውን ብሒል እውን ማድረግ ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ የወንጌል አማኙ ማኅበረ ሰብ ትልቅ ኀላፊነት አለበት።
ሀብታሙ ማርክ እና ጁሊያ የተሰኙ ባልና ሚስት ከ 8 ዓመታት በፊት ሀብታሙን ከታናሽ ወንድሙ ጋር በጉዲፈቻ ወደ ጣሊያን ሲወስዱት የ6 ዓመት ሕፃን ነበር። ሀብታሙ ከአሳዳጊ ወላጆቹ ፍቅርና እንክብካቤ ባይጎድልበትም ሀገር ቤት ትቷቸው በመጣው ወንድሞቹ ፍቅር እና ናፍቆት በእጅጉ ይሠቃይ ነበር። ፓዴርኖ በምትባለው የሚላን ከተማ ኗሪ የነበረው ሀብታሙ፣ ወደ ሀገሩ መመለስ እንደሚፈልግ እና በጉባኤው ተናጋሪ ከነበሩ ሕፃናት መካከል ወንድሞቹ እንደ ናፈቁት ለሚቀርባቸው አንድ ቄስ ይናገር ነበር። በአሳዳጊ ቤተ ሰቦቹ ስም ሀብታሙ ስካቺያ ተብሎ የሚጠራው ታዳጊ፣ ጣሊያኖቹ እንደሚሉት “የአፍሪካ ሕመም” (The pain of Africa) በሚሉት የሀገርና የወንዙ፣ የአፈሩና የአየሩ ናፍቆት ይሠቃይ ነበር። እ.አ.አ በ2012 የመጀመሪያ ወራት ከቤት በመጥፋት ወደ ሀገሩ ለመመለስ የእግር ጉዞ ጀመረ። አሳዳጊዎቹና የአካባቢው ኅብረተ ሰብ እንዲሁም የፖሊስ ኀይል ለቀናት ሲፈልጉት ከረሙ። ሞንዛ ቱዴይ የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው የሀብታሙ የናፍቆት ስቃይ ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ነበር። ግማሽ ጣሊያንን በእግሩ ካካለለ በኋላ በስተ መጨረሻ ʻወደ ሀገሬ በባቡር እሳፈራለሁʼ ብሎ ካሰበበት ናፖሊ ደረሰ።

የባቡር ጣቢያው የጥበቃ አባላት በፍርሃት የሚናጠውን የ13 ዓመት ልጅ ካገኙት በኋላ በሚላን፣ ፓዴርኖ ዱጋኖን ወደሚገኙት ወላጆቹ በመደወል የልጃቸውን መገኘት ተናገሩ። በወቅቱ ሀብታሙ ከቤት በመጥፋቱ መጸጸቱንና የሚያስጠጋው በማጣቱ መንገድ ላይ እያደረ ከመንገደኞች በሚጣልለት ሳንቲም ቀናቱን መግፋቱን ገልጾ እንደ ነበር ላ ሪፐብሊካ ዘግቦ ነበር። የሀብታሙ አሳዳጊ ወላጆች እሱ እንደሚፈልገው ወደ ሀገሩ ይዘውት በመሄድ የሀገሩንና የወንድሞቹን ፍቅር እንዲወጣ ስላላደረጉት በድጋሚ ከዓመት በኋላ በ2013 ከቤቱ ጠፋ። ይህ ወቅት ግን ሀብታሙ ዳግም የተመለሰበት አልነበረም። ተስፋ ያስቆረጠው የሀገርና የወገን ፍቅር ከቁጥጥሩ ውጪ የሆነበት የ14 ዓመቱ ታዳጊ፣ ከአሳዳጊዎቹ ቤት ብዙም ከማይርቅ ስፍራ ካለ ዛፍ ላይ ራሱን ሰቅሎ ተገኘ።

የሀብታሙ ፍጻሜ በታላላቅ የጣሊያን ጋዜጦች ሽፋን አግኝቶ የአንድ ሰሞን መነጋጋሪያ ሆኖ ከርሟል። ሀገሩ መግባት እንዳማረውና እንደናፈቀው ሳይሳካለት በጣሊያን ግብዓተ መሬቱ መፈጸሙን አዲስ ጉዳይ መጽሔት በነሐሴ 25፣ 2005 ዓ.ም. ዕትሙ አስነብቦ ነበር። አሳዳጊ ወላጆቹን “ለምን እኔን መረጣችሁኝ? ለምን እኔን አመጣችሁኝ? እኔ ከወንድሞቼ ጋር መኖር ነው የምፈልገው” እያለ ይጠይቅ የነበረው ሀብታሙ መልስ ሳያገኝ አልፏል፡፡

” ‘መንፈስ ቅዱስ ካልተናገረ እኔ የምነግራችሁ አንዳች የለም’ ብሎ ጉባኤውን ማሰናበት ጤናማነት ነው”

መጋቢ መስፍን ሙሉጌታ በኮልፌ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በመጋቢነት ያገለግላሉ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ዘወትር ዓርብ ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታዘጋጀው “የፈውስና ነጻ የማውጣት” መርሓ ግብር ላይ ላለፉት በርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። በዚህ ዘመን በፈውስ ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን ያገልግላሉ ከሚባሉት አገልጋዮች መካከል የመጋቢ መስፍን ስም ቀድሞ ይነሣል። ሕንጸት ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ ስለ ስጦታዎቹ እና አጠቃቀሙ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዘው ስለሚነሡ ጉዳዮች ከመጋቢ መስፍን ሙሉጌታ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ሥራ፦ የተዘነጋው መፍትሔ

“አረጋዊያንን፣ ሕፃናትንና ሕሙማን የሚረዱ ሰዎችን አደንቃለሁ፤ የእኔ ምርጫ ግን ይህ አይደለም። የድርጅታችን ራእይም መሥራት የሚችሉ፣ ነገር ግን ተገቢውን ሥልጠና እና የሥራ ዕድል ላላገኙ ሰዎች ዕድሉን በመስጠት ሠራተኞችና ወደፊት ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ማስቻል ነው”

ተጨማሪ ያንብቡ

የፍትሕ ጩኸት እና የዝምታ ኀጢአት

በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚመለከት በታሪክ ሁለት ጽንፎች መንጸባረቃቸውን የሚያስታውሰው ዶ/ር ግርማ በቀለ፣ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የሚታየውን እኩይ ምግባር በአደባባይ ለመኮነን አቅም ሊያንሳት አይገባም ይላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.