የመጽሐፉ ርእስ፦ “የመለኪያ ያለህ፦የሐሰት አሠራርንና የእውነት አሠራርን በምን እንለይ?”
ጸሐፊ፦ ጆንሰን እጅጉ
የኅትመት ዘመን፦ 2015 ዓ.ም.
የኅትመት ቦታ፦ አዲስ አበባ
አታሚ፦ ማንኩሳ ማተሚያ ቤት
የገጽ ብዛት፦ 183
ዋጋ፦ 260 ብር
መግቢያ
እውቁ ሰባኪ ቻርለስ ስፐርጀን፣ ቤተ ክርስትያን በዘመኗ ሁሉ የተነሡባት የስሕተት ትምህርቶች ምንጭ ከውስጥ ቢሆንም፣ ዐላማቸው ክቡሩን አምላካችንን ማራኮትና ፍጡሩን ሰው ባለተገባው ማማ ላይ ማንሳፈፍ ነው ይላል።
የስሕተት ወይም የሐሰት ትምህርቶች እንደ ዐሸነ በፈለቡት በዚህ ዘመን፣ እውነትና ሐሰትን ለመለየት የብዙዎቻችን ጥያቄ የሚሆነው፣ ‘ለመሆኑ እውነቱ የቱ ነው? ሐሰቱንስ በምን እንለይ?’ የሚል ነው።
ቤተ ክርስቲያና ባሳለፈቸው ዓመታት ሁሉ በስሕተት ወይም በሐሰት አስተምህሮዎች ምክንያት ታላቅ መናወጽና ፈተና ላይ ወድቃለች። ይሁንና በእነዚህ ፈተናዎች ሁሉ ግን፣ ለተነሡባት የውስጥም ሆነ የውጭ የስሕተት ወይም ሐሰት ትምህርቶች፣ በአምላኳ በመደገፍ ብርቱ ምላሾችን በማንበር ቀኖናዋን መከላከል ችላለች። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የአምላካችንን ክብር በሰው ለመቀየር የተደረገውን ትምህርት፣ የማሳጣትና እውነቱን ለአማንያን አጽንታ የማስተማር ተግባሯንም ተወጥታለች።
ወንድማችን ጆንሰን እጅጉም፣ “የመለኪያ ያለህ! ሐሰተኛን አሠራርና የጸጋ አሠራር በምን እንለይ?” ሲል በሰየመው መጽሐፉ፣ ይህን እውነት ሐዋርያዊ ዕቅብተ እምነት አተገባበርን በመፈተሽ ለአንባቢዎች እንካችሁ ብሏል።
በመጽሐፉ ገጽ 10-12 ላይ “ቅኝት አንድና ሁለት” ብሎ ባቀረበው እጣሬ፣ የመጽሐፉን መግፍኤ፦ “እኛ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አማኞች በዐበይት ትምህርቶች ላይ ያለን ስምምነት፣ ‘የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስትያኖች ኅብረት’ የተባለውን ተቋም ለመፍጠር አስችሎናል። ይሁን እንጂ፣ በአንድ ተቋም ጥላ ሥር ብንሰበሰብም በርካታ ስምምነት ያጣንባቸው ውዝግቦች አሉብን” በማለት ዐበይትና አንኳር ጕዳዮች ዙሪያ፣ አሉ የሚላቸውን የትርጓሜ መዛነፎች መሆኑን ያመለክታል። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህን መዛነፎች በማረቅና ሐሰተኛ አሠራሮችን በመለየት፣ እውነተኛና ርቱዕ ትምህርትና ልምምዶችን የማንበር ተልእኮ በማንገብ መጽሐፉን ማሰናዳቱን ያስረዳል።
በቅኝት ሁለት ላይ፣ “መለኪያ በሌለበተ ሐሰተኛን ከእውነተኛ መለየት፣ ማረምና ፍጹምነትን ማሳካት ወይም ክርስትናን ማስቀጠል አይቻልም” በማለት፣ መለኪያ አልቦ የመሰሉ ትምህርቶችና ልምምዶችን መለኪያዊ ብያኔ ሊኖርባቸው ይገባል የሚለውን ጩኸት ለማጋራት ይጥራል።
የመጽሐፉ ቅርጽና የተነሡ አንኳር ጭብጦቸ
መጽሐፉ ሦስት ምእራፎችን የያዘ ሲሆን፣ ቀዳሚውን ምእራፍ ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ ጸሐፊው አንዳንድ ወሳኝ ናቸው እንዲሁም ለትርጕም አሻሚነት በር ይከፍታሉ ብሎ ያመነባቸውን ቃላት፣ መዝገበ ቃላዊና ታሪካዊ ብያኔዎቻቸውን በሁለት ገጾች አስፍሯል። በመፍቻው ውስጥ ቅኝት የተደረገባቸው ቃላትና ጽንሰ ዐሳባዊ ሐረጎች የሚከተሉት ናቸው፦ ዓመፅ፣ ዐልቦተ መንፈሳዊ ስጦታ አማኞች (Ceassationist)፣ የዲብ አካል ሃይማኖት፣ ኑፋቄ፣ ሥርው፣ አመክንዮ፣ ወልካፋ፣ ዐቃቢ ሲሆኑ፣ የቃላቱን ሙያዊ ፍታቴም የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን መዝገበ ቃላት በመጠቀም አስፍሯል።
ቀዳሚው ምእራፍ “ድምሰሳ ፍረጃ” በሚል ርእሰ የሚጀምር ሲሆን፣ ደምሳሳ ፍረጃ ተከስቷል የሚለውም የጴንጤቆስጤ ጎራው የሚያስተናግዳቸው ሁሉም የጸጋ ስጦታዎች ቀጥሏል ባይነቱ፣ አእምሮ አልባ፣ ከፍ ሲልም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ኑፋቄያዊ ተግባር ነው በማለት፣ በበርካቶች ዘንድ ያለ ብርቱ ንባብና ትንተና በደምሳሳው መወገዙ አግባብ አለመሆኑን ያገልጻል። ሙግቱንም ሲያሰናዳ ከመንፈሳዊ ጨለምተኝነት ወጣ ብሎ፣ አስቀድሞ የተሰነዱ የጴንጤቆስጤ አማንያኑን አንጡራ ትምህርቶችና ልምምዶች ላይ አነጣጥረው የተሠሩ ሒሳዊ መጻሕፍት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊና አመክኗዊ ነው ባላው መንገድ ይሞግታል፤ ደምሳሳዊ ፍረጃንም ለማረቅ ዐሳቡን ያደራጃል። በገጽ 17 ላይ፣
ዛሬ ላይ ደምሳሳዊያን የኹለቱን ንቅናቄዎች መልክ መለየትና መስመር ከማስመር ይልቅ የእምነት እንቅስቃሴን ከጴንጤቆስጤ ጋራ ደምረው በማብጠልጠላቸው ምክንያት እውነተኛ የሆኑ ልምምዶችን ፊት እንድንነሳቸው እየሆንን ነው። እነኚህ ያላዋቂ ዐዋቂዎች ታሪክን ቆፍረው በቅጡ ሳይገነዘቡ እንዲህ በማመሳሰል፤ የተዛባ ትርጉም በመስጠትና ሕጸጾችን በማጉላት ስለሚያስደነግጡን ልባችን ይከፈልብናል።
በማለት በጴንጤቆስጣውያን ትምህርትና ልምምዶች ላይ ያለ ምንም በቂ ንባብና ትንተና፣ ልማዳዊ ፍረጃ መደረጉን ይኰንናል። ይህንም ኵነና ብቻ በማድረግ የሚያቆም ሳይሆን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ ማስረጃዎችንም በማቅረብ ሚዛናዊ እንሁን የሚል ጥሪ ያቀርባል።
ከገጽ 20-42 ባሉት ገጾች፣ ስጦታዎች “በጥንቷ ቤተ ክርስቲያንና አሁን” በሚለው ንዑስ ርእስ ሥር፣ ታሪካዊ ማስረጃዎችን በየፈረጁ እንዲሁም የሥነ አፈታት ችግር ታይቶባቸዋል ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በዐውዳዊ ልካቸውና አፈታታቸው በማንበር፣ የጸጋ ስጦታዎችን ቀጣይነትና የጴንጤቆስጤ ልምምዶችን መጽሐፍ ቅዱሳዊነትን ያስረዳል። በሂደቱም ከአገር ውስጥ ቀደምት ጸሐፊያን እስከ ውጪ አገር እስካሉ የፈረንጅ አፍ መጻሕፍትን በመዳሰስ ሙግታዊ ዐሳቦችን ያሰፍራል።
በምእራፍ ሁለት ላይ፣ የዕቅብት እምነት አስፈላጊነትና አተገባበሩን በሚመለከት ታሪካዊ የሆኑ የዕቅብተ እምነት ሥራዎችን በመፈተሸና በመዳሰስ፣ አሁን ላይ እየተዘወተረ ያለው የዕቅብተ እምነት አገልግሎት ቤተ ክርስትያንን ሊጠቅምና አንጡራ ትምህርቶችን ማዕከል አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባው ይሞግታል።
በሂደቱም የተለያዩ የዕቅብተ እምነት ዐይነቶችን፣ በታሪካዊዋ ቤተ ክርስትያን መታየቱን በማውሳት፣ የዕቅብተ እምነት አገልግሎታችን ለማቀብ ካለን አፍላ ፍላጎት ብቻ የሚመነጭ መሆን እንደሌለበትና፣ እውቀትና ክኂሎትንም ያየዘ ሊሆን እንደሚገባው ከማስረጃዎች ጋር ያቀርባል።
ገጽ 76 ላይ እንዲህ ይላል፦ “በተለይ የክርስትና ዕውነት የሚያዳፍኑ የውስጥና የውጪ ተግዳሮቶች በተበራከቱበት በዚህ ዘመን ዕቅብተ እምነት እጅግ አስፈላጊና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሁሉም አገልጋይ ሊረባረብበት የሚገባ አገልግሎት” ነው ይላል። በተመሳሳይ፣ በዚሁ ገጽ ላይ “ጥምር ግንባር” በሚለው ንዑስ ርእስ ሥር፣ የዕቅብተ እምነት ሥራ የሐዋርያቱ የቤት ሥራ ብቻ ያልነበረና የሁሉም አማኝ ሥራ መሆኑን በማስረገጥ የማንቂያ ግሣጼ ያኖራል። የዕቅብተ እምነት አቀራረባችንም ምን መምሰል እንዳለበት ለማሳየት፣ በገጽ 101 ላይ “ዕቅብተ እምነትና ሐዋርያቱ” በሚል ንዑስ ርእስ ሥር፣ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ይሁዳ ድረስ ያሉትን መልእክታት፣ ያላቸውን ዐቃቤያዊ አንድምታዎችን በማሰስ ግንዛቤ ያስጨብጣል (ከገጽ 101-108)።
ምእራፍ ሦስት ላይ፣ “…መለኪያዎች ከጅምላ ፍረጃ፤ ከውዝግብና ከጭቅጭቅ የጸዳ የጋራ ስምምነት መፍጠራቸውንና ሥራን ማቀላጠፍ ማስቻላቸውን ነው። በአንጻሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተመለከትን እንደሆነ ከመስማማት ይልቅ መለኪያ እንደሌለው ሕዝብ የምንወዛገብባቸው ነገሮች ዕለት ዕለት እየጨመሩ መሄዳቸው አሳሳቢ ሆኗል። እከሌ መናፍቅ ነው! ወይም ሐሰተኛ ነው! ለማለት የምንስማማበት መለኪያ በውል ማወቅ እየተሳነን ነው።” (ገጽ 110) በማለት የመለኪያ ያለህ የሚለውን ሐቲት ያቀርባል።
በዚህ ምእራፍ ውስጥ አሁን ላይ ለገባንበት ዥንጉርጉርነትና ወጣ ገባ መልክ መንሥኤው፣ መለኪያ አልቦነታችን ነው በማለት የምናደርጋቸው ማናቸውም ልምምዶችና ትምህርቶች፣ መነሻቸው መጽሐፍ ቅዱሳች ብቻ ሊሆን እንደሚገባው በማተት፣ በሥነ አፈታት ላይ መለኪያ አለቦነት እዚህም እዚያም እየተስተዋለ ነው፤ የትክክለኛውና ርቱዕ ትምህርት መገንቢያው መንገድ ጤነኛ ሥነ አፈታት ነው ሲል ዐሳብ ይሰጣል። የምንከተለው የዘፈቀደ የትርጓሜ መንገድ ከሆነ፣ በውጤቱ የኑፋቄ ማዕከል መሆናችን አይቀርምና ደርዝ ያለው ሥነ አፈታት መለኪያችን ይሁን ይለናል። በዚሁ ከፍል ውስጥ ታሪካዊ ነገረ ጕዳዮችንም እንደ መለኪያነት ከዋናው መጽሐፍ ቅዱሳችን ለጥቆ ሊያገለግል ይገባል በማለት ሐቲት ቀርቧል።
በመጨረሻም፣ “መደምድማት” ተብሎ በቀረበው የመጽሐፉ ከፍል፣ ዕቅብተ እምነትና ፍትሐዊነት እንዲሁም የእምነት እንቅስቃሴ ኑፋቄ ነውን? በሚል ተጠይቃዊ ርእሰ ነገር፣ ወሳኝ ሐተታዎችን በማቅረብ፣ የዕቅብተ እምነት ሥራችን ሐሰተኛ ትምህርቶችን አንጥሮ በማውጣትና ርቱዕ ትምህርትና ልምምድን በማንበር ሊሠራ ይገባል የሚለው አንኳር ጭብጥ በተማጽኖ መልክ ቀርቧል።
ለምን እናንብበው?፦ እንደመውጫ
ይህ፣ ‘“የመለኪያ ያለህ!” የተሰኘው መጽሐፍ፣ በእያንዳንዳችን እጅ ገብቶ ቢነበብ ያለው ጠቀሜታ ምንድር ነው?’ ብሎ ለሚጠይቅ፦ ዕቅበተ እምነታዊ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ሲሰናዱ፣ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ዳሩ ግን አንዳንድ ጕዳዮችን በማኅበራዊ ድረ ገጾቻችችን ላይ ብቻ የምንፋተግባቸው ሳይሆኑ፣ በመጽሐፍ መልክ ሰንድን በማውጣት ሙያዊና ነገረ መለኮታዊ ይዘትን በተላበሰ መልኩ ምላሾችና ሙግቶችን ማቅረብ ግድ ይለናል። መጽሐፉ ምንም እንኳ እስከ አሁን ያልተነሡ አዳዲስ የሚባሉ ነገረ ጕዳዮችን የያዘ ባይሆንም፣ ከዚህ በፊት ተነሥተው፣ ዐሳብ የተሰጠባቸውን ከላይ የተጠቀሱትን ነገረ ጕዳዮችን በወጉ መጽሐፍ ቅዱሳዊና አመክንዮአዊ በሆነ መንገድ፣ ደርዝ ያለው ክርክር ወይም ሙግት ይዞ የቀረበ ነው። ለምሳሌ፣ የጸጋ ስጦታዎች በሙሉ መቀጠል አለመቀጠልን በሚመለከት የታሪክ ማስረጃ ትንታኔን በማቅረብ ለሚሟገቱ የአለቦ ጸጋ ስጦታ አቀንቃኞች፣ “አማኞች እስኪ እንደገና እንሟገት” በማለት፣ አሉ የተባሉ ማስረጃዎችን በአግበቡ በማሔስ የእንደገና እንወያይ ጥሪውን ያቀርባል።
መጽሐፉ በአቀራረቡ ከዚህ ቀደም የተሰናዱ መሰለ ሥራዎችን ዐውዳቸውን በጠበቀ መልኩ፣ ተገቢውን የንቅለ ተከላ ማለትም ተቃውሟዊ ዐሳቦቹን ሲያደራጅ፣ በሌላ ጎኑ የሰፈሩ ዐሳቦችን ከሰፈሩበት ዐውድና ትርጓሜ ጋራ ሳያዛንፍ ርቱዐዊ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የተደረገው ጥረት የመጽሐፉን የተነባቢነት ፍላጎት ከፍ ያደርገዋል።
“የመለኪያ ያለህ!” ይዞት በተነሣው ርእሰ ነገር ዙሪያ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጸሐፍት የተነሡ ተቃውሟዊም ሆነ ድጋፋዊ ትንታኔዎችን በአግባቡ ያቀርባል። በአቀራረቡም፣ ነገረ መለኮታዊና አመክኗዊነትን ዋጋ በመስጥት፣ ተገቢ መረጃዎችን ያቀርባል። ለምሳሌ፣ ገጽ 111 ላይ፣ “ቤተክርስቲያንከፍጹምነትጉዞዋእንዳትደናቀፉለዐበይትትምህርቶችምይሁንለርቱዕትምህርቶችትኩረትመስጠትያስፈልጋል።ኑፋቄበዐበይትወይምበርቱዕክርስትናትምህርትወይምነገረመለኮትተፈትሾመወገዝአለበት፤እንዲሁምሁሉሐሰተኛአሠራርምከእውነተኛውተለይቶበጽኑናበግልጽሊወገዝይገባል።”
መለኪያ አልቦ ብያኔና ንግግር ፍጻሜው ድምሰሳዊነት ነውና፣ ነገሮችን በጅምላ እየገረደፉ ማለፉ መጽሐፍ ቅዱሳዊም ሆነ ታሪካዊ ስላልሆነ፣ ሸማን በየፈርጁ በማለት፣ መረጃ አልቦና ስሜትን ብቻ መሠረት ያደረጉ ጡዘቶችን መሬት ይዘን እንድንሟገት ጥሪ ቀርቧል። የዕቅብተ እምነት አካሄዳችንም መሥመር ካልተበጀለትና እውቀትን ያማከለ ካልሆነ፣ የሚፈጥረው ችግር የጀብደኝነት ስለሚሆን፣ ከወዲሁ ሳይቃጠል በቅጠል የሚል ምክር መስጠቱ፣ ለመነበብ ተገቢ እንዲሆን ያደርገዋል።
Add comment