[the_ad_group id=”107″]

የመጽሐፍ ቅኝት

ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ

ርእስ :- ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ (3ኛ መጽሐፍ) ጸሐፊ፡- (ቄስ) ኮሊን ማንሰል
የታተመበት ዓመት፡- 1999 ዓ.ም
አሳታሚ፡- አቶ ፍትሐ አምላክ እንየው
የገጽ መጠን፡- 234

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ የሆኑት ቄስ ማንስል ከባለቤታቸው ከሄዘል ማንሰል ጋር ከዐርባ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚስዮናዊነት አገልግለዋል። ቄስ ኮሊን ማንሰል የተወለዱት እ.ኤአ. በ1933 እንግሊዝ አገር ውስጥ በምትገኝ ባዝ በተባለች ከተማ ውስጥ ነው። ቅስናን ከአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን የተቀበሉ ሲሆን፣ በሰራዊተ ክርስቶስ ማኅበር አስተዳዳሪነት እ.ኤ.አ. በ1961 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የነበራቸው አገልግሎት በተለዩ የአገሪቱ ክፍሎች መስበክን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማሰተማርን፣ የተለያዩ ሥነ ጽሑፎችን ጽፎ ማሳተምን ያካትታል።

ቄስ ማንሰል ዋነኛ የአገልግሎታቸው አካሄድ አድርገው ይንቀሳቀሱ የነበረው፣ የራሳቸውን አብያተ ክርስቲያናትን ማቋቋም ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የበለጠ እንዲረዱ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ መንፈሳዊ መነቃቃትን እና ለውጥን ማምጣት ነው። ቄስ ማንሰል ከባለቤታቸው ጋር በመተባበር “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መግቢያ”፣ “በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ጋር”፣ “እግዚአብሔር ወልድ”፣ “ከባቢሎን ምርኮ መልስ”፣ “የእግዚአብሔር ጸጋ አሠራር”፣ “አስደናቂ ልውውጥ” የሚሉ መጻሕፍትን ጽፈዋል።

ይህ “ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ” የተሰኘው መጽሐፍ ከዚህ በፊት በደራሲው ታትመው ለንባብ የበቁት የ“ትምህርተ እግዚአብሔር” (1995 ዓ.ም.) እና “ትምህርተ ክርስቶስ” (1998 ዓ.ም.) ተከታይ ሦስተኛ መጽሐፍ ነው። ሦስተኛው መጽሐፍ ከዚህ በፊት የወጡት የሁለቱ መጻሕፍት ቀጣይ ስለሆነ በምዕራፍ 78 ይጀምራል። እነዚህ ሦስት መጻሕፍት አጠቃላይ ነገረ መለኮትን ለኢትዮጵያውያን በሚስማማ መልኩ ለማቅረብ ታስቦ የተጻፉ ናቸው። ጸሐፊው ይህን ሦስተኛ መጽሐፋቸውን በመጻፍ ላይ እያሉ ነው ያረፉት። መጽሐፉም ወደ ኅትመት እንዲመጣ የባለቤታቸው እና የአቶ ፍትሐ አምላክ እንየው ሚና በእጅጉ የጎላ ነው። አቶ ፍትሐ አምላክ መጽሐፉን በማረምና በማስተካከል ላቅ ያለን ድርሻን አበርክተዋል።

መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? የመንፈስ ቅዱስ ግብሩስ ምንድን ነው? ከአማኞች ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ይመስላል? ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎች ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሁል ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው። መንፈስ ቅዱስ ኀይል ነው ከሚለው አስተምህሮ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አንድ አካል ነው እስከሚለው ምላሽ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከላይ ለተነሡ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾች ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ለመንፈስ ቅዱስ ማንነት ተገቢ የሆነን ሥፍራ አለመስጠት ይስተዋላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን በተለየ መልኩ መረዳት እንዲሁ የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው። ይህ መጽሐፍ እነዚህን ችግሮች በማጉላት መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ አንባቢው ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው።

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቄስ ማንስል በሳል በሆነ መልኩ ትምህርተ መንፈስ ቅዱስን ከሥልታዊ ነገረ መለኮት አንጻር ያስቃኙናል። መጽሐፉ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ክፍል 6 ምዕራፎችን፣ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ 10 ምዕራፎች የያዘ ነው። በመጀመሪያው ክፍል የመንፈስ ቅዱስ ግብር የተተነተነበት ሲሆን፣ በሁለተኛው ክፍል መንፈስ ቅዱስና የሰው ልጆችን ደኅንነት የተመለከቱ ርእሰ ጉዳዮች ሰፊ የሆነ ትንታኔ አግኝተውበታል።

በመጽሐፉ የመጀመሪያው ክፍል የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ተዳሰዋል። በዋነኝነት ትኩረት የተሰጣቸው መንፈስ ቅዱስ በድኅነት ዐውድ ውስጥ ያለው ሚና፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንዴት እንደ ተገለጠ፣ መንፈስ ቅዱስና የጋርዮሽ ጸጋ፣ መንፈስ ቅዱስና ኢየሱስ ክርስቶስ፣ መንፈስ ቅዱስ በቅስድት ሥላሴ እና መንፈስ ቅዱስና የደኅነት ጸጋ ናቸው። በእነዚህ ርእሰ ጉዳዮች በቂ የሆነ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። ጸሐፊው ትምህርት መንፈስ ቅዱስ ድንገት በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተፈጠረ ትምህርት ሳይሆን በብሉይ ኪዳንም መንፈስ ቅዱስን የተመለከቱ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እንደምናገኝ ይጠቁማሉ። በተለይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስ ፅንሰት፣ ልደት፣ ዕድገት፣ ጥምቀት፣ መፈተን፣ አገልግሎት፣ ሞት እና ትንሣኤ ውስጥ ትልቅ የሆነን ሚና መጫወቱ ተተንትኗል።

በዚህ ክፍል ሥር ጸሐፊው አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በህላዌ፣ በባሕርይ፣ በመለኮትነት፣ በፈቃድ አንድ እንደ ሆኑ፣ በግብር (በሥራ) አንድ ዐላማ እንዳላቸው ተገልጻል።“የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ሁሉ ወደ ፍጻሜ ማድረስ” (ገጽ 23) መሆኑ የተብራራ ሲሆን፣ ይህ መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን እንደ እግዚአብሔር እስትንፋስ በአዲስ ኪዳን ደግሞ እንደ ክርስቶስ እንደ ራሴ ሆኖ እንደ ተገለጠ ያብራራል።

በሁለተኛው ክፍል ትኩረት የተሰጣቸው ርእሰ ጉዳዮች የሰው ድነት፣ ግብረ መንፈስ ቅዱስ፣ የእግዚአብሔር ጥሪና የሰው ዳግም ልደት፣ ንሰሓ፣ ጽድቅና ቅድስና፣ ልጅነት፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እና ዋስትና የመሳሰሉት ጉዳዮች ናቸው። ይህ ክፍል ሰዎችን ወደ ድነት የሚመራው ከድነትም በኋላ ጸንተው በቅድስና እንዲኖሩና ክርስቲያናዊ ኑሯቸውን እንዲወጡ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ ትኩረት ተሰጥቶበታል።

ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያናዊ አስተምህሮ ውስጥ ወሳኝ ስፍራ ያለው ነው። የክርስቲያኖች የእምነት አንቀጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ታሪካዊ ገጽታ እንዳለው መጽሐፉ ያስገነዝበናል። ለዚህም በሁለት ክፍሎች መጽሐፉ ሰፊ የሆነን ትኩረት ሰጥተዋል። ጸሐፊው ከታሪካዊ የክርስትና አስተምህሮ ያፈነገጡና ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ አንጻር የሚጣረሱ መንፈሳዊ ልምምዶችንም በማንሣት ይተቻሉ።

መጽሐፍ ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት ጥሩ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንታኔ የቀረበበት ነው። በህላዌ፣ በባሕርይ፣ በባሕርይ መገለጫዎች፣ በመለኮት ፈቃድ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አይበላለጡም (ገጽ 62)። መጽሐፉ መንፈስ ቅዱስ ባሕርዩ ረቂቅ ቢሆንም አካል እንደ ሆነ ያብራራል። ይህም አካላዊነት መንፈስ ቅዱስ በሥላሴ ግብር ውስጥ ባለው ተሳትፎ፣ ከዓለም እና ከምእመናን ጋር ባለው ግንኙነት የተገለጸ ነው። እንደ አርዮስና ሰባልዮስ ያሉ አስተማሪዎችና ተከታዮቻቸው በመንፈስ ቅዱስ አካላዊነት (Personhood) አያምኑም። በአንጻሩ “መንፈስ ቅዱስ ኀይል ነው” ወይም “ነገር” ነው ብለው ያስተምራሉ። ይህ ዐይነት አመለካከት አሁንም በዘመናችን በተለያዩ ብድኖች የሚንጸባረቅ የእምነት አቋም ነው። መጽሐፉ እነዚህ አመለካከቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር በእጅጉ የሚቃረኑ መሆናቸውን አጽንኦት በመስጠት አብራርተዋል።

እንዲሁም መጽሐፉ ሰለ መንፈስ ቅዱስ አሠራር ሰፋ ያለን ትንታኔ ይሰጣል። መንፈስ ቅዱስ በአማኞች መካከል በሥራ ላይ በሚሆንበት ጊዜ ክርስቶስን ከፍ ከፍ እንደሚያደርግ (1ዮሐ. 4፥2)፣ የዓለምን ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሆነ ነገርን እንደሚናገር (1ዮሐ. 4፥4-5)፣ ሰዎች የበለጠ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ እንደሚያደርግ (1ዮሐ. 4፥6)፣ መንፈስ ቅዱስ የእውነት መንፈስ ስለሆነ ሰዎችን ሁሉ ወደ እውነት እንደሚመራ (1ዮሐ. 2፥27)፣ መንፈስ ቅዱስ ፍቅር ስለሆነ “በሰው ዘንድ ያለው መንፈስ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው በፍቅር ሲሠራ ሥራው ከመንፈስ ቅዱስ መሆኑን ያሳያል።” (ገጽ 29) እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የምናረጋግጥባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መለኪያዎች ተደርገው ተቀምጠዋል። ይህ በተለይ በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ከመንፈስ ቅዱስ አሠራር ጋር ተያይዘው ለሚነሡ ችግርች እንደ መፍትሔ ሊያገለግሉ የሚችል መርሖዎችን የሚጠቁመን እና መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲንቀሳቀስ በአማኞች እና በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ምን ምን ነገሮች እንደሚከሰቱ ቆም ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርገን ነው።

በመጽሐፉ የመጨረሻ ክፍሎች ላይ የእንግሊዝኛና የሌሎች ቋንቋዎች ቃላት፣ የሰዎች ስምና የአርእስት ማውጫ እንዲሁም ማብራሪያ የተሰጠባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተካተዋል። ይህ አንባቢው አስቸጋሪ የሆኑ ሙያዊ ቃላትን በቀላሉ እንዲረዳ እና በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እና ወሳኝ ርእሰ ጉዳዮች የት እንደሚገኙ በመጠቆም አንባቢውን ከድካም የሚጠብቁ ናቸው።

መጽሐፉ የተጻፈበት ቋንቋ ለአንዳንድ አንባቢያን ጠጠር የሚል ቢሆንም፣ ጥሩ የአጻጻፍ ዘዴን የተከተለ እና በቂ የሆነ የአርትኦት ሥራ የተደረገበት በመሆኑ ለሌሎች ጸሐፊዎች በጥሩ ምሳሌነት ሊነሣ የሚችል ነው። መጽሐፉ ዐውዳዊ ነገረ መለኮት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲስፋፋ የራሱን አስተዋጽኦ የሚጫወት ነው። ከዘህም በተጨማሪ ጥልቅ ከሆነው

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮታዊ ቃላትን በመዋስ ጸሐፊው ሊያስተላልፉ የፈለጉትን መልእክት ተገቢ በሆነ መልኩ አስተላልፈዋል። ይህም ጸሐፊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያላቸውን ጥልቅ እውቀት አመላካች ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአማሪኛ ቋንቋን በማጥናት ብዙ መጻሕፍን መጻፋቸው ጸሐፊው ለዐውዳዊ ነገረ መለኮት የሰጡትን ዋጋ እና የሚያገለግሉትን ሕዝብ አክባሪ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው።

ማጠቃለያ

ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያ የክርስትና ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ደራሲው የወንጌላውያንንም ሆነ የኦርቶዶክስ አማኞችን ያማከለ ጥሩ መጽሐፍ አበርክተውልናል። መጽሐፉ መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እና በታሪክ ውስጥ በተለያዩ ቤተ እምነቶች እና የነገረ መለኮት መምህራን መካከል ያሉትን አመለካከቶች በማሳየት አንባቢው ርእሰ ጉዳዩን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ያደርገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፉ በተለያዩ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደ መርጃ መጽሐፍ ሆኖ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ነው። ነገረ መለኮት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰባኪያን እና መምህራን የሆኑ ሁሉ ቢያነቡት እምነታቸውን በተመለከተ ጠንቅቀው እንዲያውቁ እና ይህንንም ለሌሎች እንዲያስተላልፉ ያግዛቸዋል። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ መሠረታዊ እውቀት እንዲኖረው የሚፈልግ ሁሉ መጽሐፉን እንዲያነበው እመክራለሁ። ቄስ ማንስል ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላበረከቱት አስተዋጽኦ በእጅጉ በማመስገን ምልከታዬን እቋጫለሁ።

Nebeyou Alemu (PhD)

ነቢዩ ዓለሙ፣ በትምህርት ዝግጅቱ በጥንታዊ መዛግብት ጥናት (Philology) የፒ.ኤች.ዲ ጥናቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያደረገ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ሥነ መለኮት ት/ቤት ማስተርስ ኦፍ ዲቪኒቲ ሠርቷል። በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (UNISA) በሥነ መለኮት ሁለተኛ የፒ.ኤቺ.ዲ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል። በተለያዩ የሥነ መለኮት ት/ቤቶች የሚያስተምረው ዶ/ር ነቢዩ ዓለሙ፣ በዊክሊፍ ኢትዮጵያ የትርጉም ሥራ አማካሪ ነው። ታሪክ፣ ሃይማኖት እና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥናቶችን ማድረግ ያስደስተዋል።

Share this article:

የራቢ ሃሮልድ ኩሽነር ጥያቄና መልስ

“የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ፣ የክፋትን ኀይል በሙላት መቆጣጠር እንደማይችል እና ክፋት/መከራ ከእርሱ ፈቃድ ውጭ ሊሆኑ እና ሊከሰቱ እንደሚችል በድፍረት ደመደሙ። ለእዚህ ዐይነት መልሶቻቸው ብዙ እጆች አጨበጨቡላቸው፤ የብዙዎችንም ልብ ‘አሳረፉ’።”

ተጨማሪ ያንብቡ

‘ምን ላስብ? ምንስ ላድርግ?’ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ

የወንጌል አማኝ ነኝ። የወንጌል አማኝ በመሆኔ ከክፉ ዳንኩ እንጂ ከዓለም አልወጣሁም። ከዓለም ወጥቼም ከሆነ፣ የወጣሁት ዓለማዊነት ከውስጤ ወጥቶ የወንጌል መልእክተኛ ሆኜ ወደ ዓለም እንድላክ እንጂ፣ የራሴን እና የብጤዎቼን ደሴት ሠርቼ፣ ተነጥዬ እንድኖር አይደለም። ጥበብ እንደ ጎደላት ሰጎን ጭንቅላቴን አሸዋ ውስጥ ቀብሬ ‘የለሁም’ ካላልኩ በስተቀር የአገሬ፣ የምድሬ ነገር ያገባኛል። ጥሪዬ ለምድር ጨውነት፣ ለዓለም ብርሃንነት እስከ ሆነ ድረስ ምድሩና ዓለሙ የሥራ መስኬ፣ የተግባር መከወኛዬ እንጂ ጥዬ የምሸሸው ጣጣ አይደለም። ያመንኩት የዓለምን መድኃኒት ነው፤ መድኃኒቱን ተቀብዬ መዳን ብቻ ሳይሆን መድኃኒት እንድሆን ተጠርቻለሁ። ስለዚህ ጥል ባለበት ፍቅርን፣ መለያየት ባለበት አንድነትን፣ ጥፋት ባለበት ልማትን፣ ኹከት ባለበት ሰላምን ለማወጅ ተጠርቻለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Leave a Reply to Melkamu Alemayehu Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • እወድሃለሁ ሀብታም ነህ ቅን ልቦና አለህ አሁን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ነኝ; በምቀጥሉት ዘመናት ጌታ እድል ከሰጠኝና ምህረቱን ካበዛልኝ ፈቃዱም ከሆነ ጥሩ አንባብና የተረጋጋ ሰው መሆን እፈልጋለው እባክህ ካላስቸገርኩህ። ተለግራም አካውንትህ ላይ ወይም በምትጠቀማቸው ማህበራዊ ምድያዎች ላይ ትምህርቶችህንና መጽሐፎችህን በpdf ማግኘት ብንችልና ለሌሎችም በስጦታ ለመስጠት በቀላሉ ለመጠቀም; ትምህርቶችን ለማዘጋጀት ና ለመሳሰሉት እጅግ በጣም ፈልገው ነበር ።
    ስለ ድፍረቴ ይቅርታ ;ከምስጋና ጋር።
    መልካሙ ዓለማየሁ ; ከዲላ ።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.