[the_ad_group id=”107″]

የ“ሪቫይቫል ኢትዮጵያና የመለከት በዓል” መጽሐፍ ዕጥርጥር

“ሪቫይቫል ኢትዮጵያና የመለከት በዓል” የተሰኘው የመጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን መጽሐፍ ከዚህ ቀደም “ሪቫይቫል ኢትዮጵያ እና የመጨረሻው መጨረሻ” በሚል ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት ለንባብ ቀርቦ የነበረው መጽሐፍ ርማትና ማሻሻያ ተደርጎበት የቀረበ አዲስ ሥራ ነው፡፡ “ለኢትዮጵያው ጴንጤቆስጤአዊ ሪቫይቫል ኀምሳኛ ዓመት መታሰቢያ የተዘጋጀ ልዩ የኢዮቤልዩ ዕትም (1958-2008)” መሆኑ የተነገረለት ይኸው መጽሐፍ ባለፉት ኀምሳ ዓመታት በኢትዮጵያ የተነሣውን ጴንጤቆስጤአዊ መነቃቃት በማስታወስ ከፊት እየመጣ ነው ለሚለው “ታላቅ መንፈሳዊ ሪቫይቫል” ያዘጋጃል፡፡

ይህ ሁለተኛ ዕትም እንዲጻፍ ያደረጉ ሦስት ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ጸሐፊው በመጀመሪያው ዕትም ያላነሧቸው ወይም በበቂ ያልዳሰሷቸው ጉዳዮች በመኖራቸው እነሱኑ ለማካተት መፈለጋቸው ነው፡፡ “በመጀመሪያው ዕትም ውስጥ እየመጣ ነው ያልኩት ሪቫይቫል እኔ ካሰብኩትም ጊዜ ይልቅ ፈጥኖ ሊደርስ ያለ፣ በአንጻሩ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን በኩል መሰናዶው ገና የሌለ ስለ መሰለኝና ስለ ፈራሁ ነው፡፡” የሚለው የጸሐፊው ሁለተኛ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡ እንደ ሦስተኛ ሰበብ ሆኖ የተጠቀሰው ምክንያት፣ የመጀመሪያው ዕትም በ1994 ዓ.ም. ከታተመ በኋላ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ያስመዘገቡት አሓዛዊ ዕድገት ብዙ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን እንዲገኙ ማድረጉ ሲሆን፣ ይኸው ወጣት ደግሞ ከቀደሙት ሊረከበው የሚገባው ታሪክ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን ሩጫ የሚያሳየው ሠነድ አስፈልጎታል፤ ስለሆነም መጋቢው እንደ ስጦታ ሊያበረክቱለት መፈለጋቸው ለመጽሐፉ “ዳግም ልደት” ሰበብ ሆነ፡፡

ይህ መጽሐፍ ዳግም ኅትመት (Reprint) አይደለም፤ ቅፅ ሁለትም አይደለም፡፡ መጽሐፉ መሠረታዊ ጭብጡን ሳይለቅቅ፣ ከመጀመሪያው የተሻሻሉ፣ የታረሙና የዳበሩ እንዲሁም ነባራዊውን ሁኔታዎች አገናዝበው በአዲስ መልክ የገቡ ዐሳቦች የተስተናገዱበት ሥራ ነው፡፡ ጸሐፊው ይህንኑ ባስረዱበት ክፍል “ሁለተኛው ዕትም የቅርጽም የይዘትም ለውጥ ተደርጎበታል፡፡” ሲሉ የምእራፎች አሰዳደር ወዲህና ወዲያ ማለታቸውን አስቀድመው እወቁልኝ ይላሉ፡፡ በ1994ቱ መጽሐፍ “የመጨረሻው መጨረሻ” በሚል ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የነበረው አቀራረብ ወደ “ግሎባዊው ሪቫይቫል” ማደጉ በይዘት ላይ ለውጥ መደረጉን ከሚያሳዩ አስረጆች መካከል አንደኛው ነው፡፡ በዚህ “ግሎባዊው” በተባለው ሪቫይቫል ላይ ወንጌላውያን ብቻ ሳይሆኑ የምሥራቋም ሆነች የምእራቧ ቤተ ክርስቲያን – ማለትም ኦርቶዶክሳውያኑ እና ካቶሊካውያኑ የሚካተቱ መሆናቸውን ያስገነዝባል፡፡

የመጽሐፉ ቅርጽ

“ሪቫይቫል ኢትዮጵያና የመለከት በዓል” የተሰኘው የመጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን መጽሐፍ በአጠቃላይ ሦስት መቶ ዘጠና ሁለት ገጾች ያሉት፣ በሦስት ክፍሎች የተከፈለ እና በዐሥር ምእራፎች የተሰናዳ መጽሐፍ ነው፡፡ በዐሥሩ ምእራፎች ውስጥ ቁጥራቸው ሰማኒያ ዘጠኝ የሚደርስ ንዑሳን ርእሶች ዐሳብ አጎልባች፣ ዐሳብ አደራጅ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ይህ አዲሱ መጽሐፍ ከመጀመሪያው ዕትም የአንድ መቶ ዐሥራ አምስት ገጾች ጭማሪ ይዞ መጥቷል፡፡

በክፍል አንድ ውስጥ ስለ ሪቫይቫል ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ ስለ ሪቫይቫል ብያኔ ሰጥቶ ከመጀመር ይልቅ ሁለት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተከሰቱ የተባሉ ሪቫይቫሎችን፣ አንድ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ በአውሮጳ የሆነ ታሪክ በማቅረብ አንባቢያን ተጨባጭ ግንዛቤ እንዲይዙ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል፡፡ በዚሁ ክፍል ውስጥ የሚነሣው ሌላኛው ጉዳይ፣ ሪቫይቫል ሲመጣ ስለሚሆኑ ወይም ስለሚታዩ ክስተቶች ማብራሪያ የቀረበበት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የሪቫይቫል ባሕርያት የተብራሩበት ነው፡፡

በአጠቃላይ ይህ የመጀመሪያው ክፍል የያዛቸው አራት ምእራፎች ሲሆኑ፣ እነሱም፡- “ሪቫይቫል”፣ “ሪቫይቫል እና መለያዎቹ”፣ “ሪቫይቫል እና መንደርደሪያዎቹ” እንዲሁም “ሪቫይቫል እና መሰናክሎቹ” የተሰኙ ናቸው፡፡ በእነዚህም አራት ምእራፎች ውስጥ መጽሐፉ ስለ ሪቫይቫል ምንነት፣ ስለ ባሕርያቱ፣ በታሪክ ስለታየባቸው አጋጣሚዎች፣ ምን እንደሚፈልግ እና ምን ሊያሰናክሉት እንደሚችሉ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡

ክፍል ሁለት “ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ በዚህ ክፍል ውስጥ አምስት ምእራፎችና አርባ አምስት ንዑሳን ርእሶች ቀርበውበታል፡፡ ይህ ክፍል ከሌሎቹ ሁለት ክፍሎች ሰፊውን የገጽ ሽፋን የሚይዘው ሲሆን፣ በዋናነት ስለ አገራችን ኢትዮጵያ እና “ስለተገባው ተስፋ”፣ ባለፉት ዘመናት በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ተቀጣጠለው የወንጌል እሣት፣ የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ በምድራችን እንዴት እንደተነሣና እንደተስፋፋ፣ ወዘተ. ሰፊ ትንታኔ ቀርቦበታል፡፡ “ኢትዮጵያ”፣ “እግዚአብሔር በመንፈሱ ማሳወቅ የጀመረው መቼ ነው?”፣ “ቅዱስ መንፈሱ እና ኢትዮጵያ”፣ “ትንቢት አትናቁ!”፣ እና “ከንውጥውጥታው ውጤቶች ውስጥ” የተሰኙት የአምስቱ ምእራፎች ስያሜ ናቸው፡፡

“የመለከት በዓል” ስያሜ የተሰጠው ክፍል ሦስት “የእግዚአብሔር በዓላት” የተሰኘ አንድ ምእራፍ ይዟል፡፡ ይህ ክፍል በዋናነት በእስራኤላውያን ይከበሩ የነበሩትን/የሚከበሩትን ሰባት በዓላት በማንሣት እነዚሁ በዓላት ከሞላ ጎደል በአዲስ ኪዳን ፍጻሜ ማግኘታቸውን ያወሳል፡፡ በተለይ ግን ለመጽሐፉ ርእስ ለመሆን የበቃውና “የመለከት በዓል” የተሰኘው በዘመን መጨረሻ ላይ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለምድራዊቷ እስራኤልም ያለውን ፋይዳ አጽንኦት ሰጥቶ ያቀርባል፡፡ ይህን በማድረግም ወደ መጽሐፉ ድምዳሜ ይፈጥናል፡፡

አንዳንድ ዐሳቦች ከመጽሐፉ

ይህ የመጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን መጽሐፍ አንድ ገዢ ዐሳብ አለው፡፡ ይኸውም፣ በኢትዮጵያ “በቅርቡ” ሊነሣ ያለ ሪቫይቫል መኖሩንና ይኸው ሪቫይቫልም መላ ዓለሙን ሊያጥለቀልቅ እንዳለ አንባቢያንን እያሳሰበ ያዘጋጃል፡፡ “የዚህች መጽሐፍ ዓላማ እንዲያው በደፈናው ስለ ሪቫይቫል ማውራት አይደለም፡፡ የዚህች መጽሐፍ ዓላማ በተለይ በኢትዮጵያ፣ ደግሞም በቅርቡ ሊከሠት ስላለ ታላቅ እና ምናልባትም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመጨረሻው ስለሚሆን ሪቫይቫል ማውራት ነው፡፡” ይላል በገጽ 165 ላይ፡፡

ጸሐፊው ለዚህ እምነታቸው ጽኑ አቋም እንዳላቸው ማወቅ አይከብድም፡፡ “ታላቅ ሪቫይቫል በቅርቡ በኢትዮጵያ” ይነሣል የተባለው “ቅዠት” እንዳልሆነ ወይም በእሳቸው አባባል “ከኪሳቸው አውጥተው” የተናገሩት አለመሆኑን በታቻላቸው ሁሉ ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት በመጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ ስለ ተባለላት” ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ስለተባሉት ሕዝቦች “ብዙ ሳይሆን በቂ” ያሏቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ታሪካዊ መረጃዎቻቸውን በማቅረብ ነው፡፡

ይህንን ሲያደርጉ ግን፣ ስለ ሪቫይቫል ምንነት እና ባሕርያቱ ከማስረዳት አልቦዘኑም፡፡ ሪቫይቫል ሰዎችን ወደ ልዩ መታደስ፣ መለወጥ፣ ዳግም ሕይወት ወደ ማግኘት የሚያመጣ ዘላቂ ተጽእኖ ያለው የሚያመጣ ጊዜያዊ ክስተት መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሪቫይቫል የሚከሰተው በእግዚአብሔር እና በሰው ምክንያት መሆኑን (ገጽ 33-35)፣ ሪቫይቫል ሊጨነግፍ የሚችል መሆኑን፣ ተጠያቂው ግን ሰይጣን እና ሰው ስለመሆናቸው፤ በሰው በኩል ሲጨነግፍ “በአብዛኛው ባለማወቅ፣ ደግሞም ባለመጠንቀቅ” እንደሚሆን ያስረዱልኛል ያሏቸውን ታሪኮች ከነማስረጃቸው በማቅረብ ነው፡፡ “ለሪቫይቫል መቀስቀስ ምክንያት የሆኑ ሰዎች ተመልሰው ለዚያው ሪቫይቫል መክሰምም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ … ለዚህ ነው ሪቫይቫልን የሚጠሙ ሰዎች ሁሉ ስለ ቀደሙት ሪቫይቫሎች፣ ሪቫይቫሉን ይመሩት ስለ ነበሩት ሰዎች፣ ስለ ብርቱና ስለ ደካማ ጎናቸው ሊያጠኑ የሚገባቸው፡፡” ሲሉ ምክር ይሰጣሉ (ገጽ 91)፡፡

ጸሐፊው ሪቫይቫል ዕድሜው አጭር መሆኑን ይነግሩንና፣ ጥቂቷንም ዕድሜ እኛ ሰዎች ይበልጡኑ እንዳናሳጥረው ያሳስባሉ፡፡ “… ሪቫይቫልን ብዙ ሰዎች፣ ለብዙ ጊዜ አርግዘውታል፡፡ እርግዝና በሚያስከትለው የጤና መጓደል፣ በሰላም ለመገላገል ባለው ናፍቆትና ሥጋት ውስጥ አልፈዋል፡፡ ብዙ ሰዎች፣ ለአያሌ ዓመታት ያለ ዕረፍት አምጠውታል፡፡ ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ ስለ እነርሱም ሲባል ሪቫይቫል መጨንገፍ የለበትም፡፡ በአጭር መቀጨት የለበትም፡፡ ይልቁኑ ማድግ እና መመንደግ ነው ያለበት፡፡” (ገጽ 90)፡፡

ጸሐፊው በክፍል አንድ፣ “ጽርኀ አርያማዊ እና አጥቢያዊ” በሚለው ንዑስ ርእስ ሥር ሪቫይቫል በሚሆንበት ጊዜ አጥቢያዊው የቤተ ክርስቲያን መልክ በጣም እንደሚደበዝዝ፣ ለብዙዎችም አስፈላጊነቱ እንደማይታያቸው ይገልጻሉ፡፡ አያይዘው ግን፣ አማኞችን ደቀ መዛሙርት የማድረግ የዕድሜ ልክ ጉዞውን የምትወጣው አጥቢያዊቷ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ያሠምሩበታል፡፡ “በምእመናን ሕይወት ውስጥ ይህንን ሂደት [አማኞችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ] የመፈጸም አገልግሎት ለሪቫይቫል አልተሰጠውም፡፡ … ሪቫይቫል በባሕርዩም ሆነ በዕድሜው ይህንን ማድረግ አይችልም፡፡ ይህንን የማድረግ አደራ የተሰጠው ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አማኞች እና አገልጋዮች ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ጽርኀ አርያማዊ [Universal] መልክ ያለ ልክ ተስበው ከአጥቢያዊው መልኳ እንዳይቆራረጡ፣ በአጥቢያዊው መልኳም ያለ ቅጥ ተወጥረው ለጽርኀ አርያማዊው መልኳ ቁብ እንዳያጡ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፡፡” ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

“የወይን ጠጅ እና አቁማዳ” በተሰኘው ንዑስ ርእስ ሊመጣ ያለው ሪቫይቫል “በአሮጌ” አሠራር (አቁማዳ) ማስተናገድ ሊያስቸግር እንደሚችል ምክር ተሰጥቶበታል፡፡ ይህን መሰሉ ችግርም ከዚህ ቀደም በተነሡ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መስተዋሉንም ጭምር ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ፣ “በጀርመን እና በሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ʻሊተራዊነትʼ የተባለ የወይን ጠጅ በተጣለ ጊዜ፣ ʻየሮማ ካቶሊካዊትʼ የተባለው አቁማዳ ፈንድቷል፡፡ በስዊትዘርላንድ እና በሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ʻመጥምቃዊነትʼ (Anabaptist) የተባለ የወይን ጠጅ በተጣለ ጊዜ ʻሉተራዊነትʼ የተባለው አቁማዳ በተራው ፈንድቷል፡፡ በእንግሊዝ አገር ʻሜቶዲዝምʼ የተባለ የወይን ጠጅ በተጣለ ጊዜ ʻአንግሊካንʼ የተባለው አቁማዳ ፈንድቷል፡፡” (ገጽ 103) ይሉና በእኛም አገር “ተሐድሶ” የተባለ የወይን ጠጅ በየቦታው እየተጣለ እንደ ሆነ ይጠቁማሉ፡፡

“ማስተዋወቂያውን” እንደ መውጫ

በቀለ ወልደ ኪዳን “ሪቫይቫል ኢትዮጵያና የመለከት በዓል” በተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው ገጽ 20 ላይ “ማስተዋወቂያ” ሲሉ የሰየሙት አጭር መግቢያ ቢጤ ገጽ አለ፡፡ በዚህ ገጽ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፡- “ኢትዮጵያ ችግረኛ አገር መሆኗን ብዙ ሰዎች ያውቃሉ፤ ችግሯ መንፈሳዊ መሆኑን የሚያውቁ ግን ብዙ ሰዎች አይደሉም፡፡ ችግሮቻችን የሚመሳሰሉ አይመስሉም እንጂ፣ እስራኤልም ችግረና አገር ናት፡፡ ችግሯ ለዓለሙ ሁሉ የተረፈረና ገናም ሊተርፍ ያለ ነው፡፡ የእስራኤል ችግር መንፈሳዊ መሆኑን ግን ብዙ ሰዎች አያውቁም፡፡ እንደ እስራኤል ሁሉ፣ የኢትዮጵያም ችግር ከመሪዎቿና ከተመሪዎቿ ብዙዎቹ አገራቸው የእግዚአብሔር ዓላማ ያለባት መሆኗን አለማወቃቸው ነው፡፡ ይህች መጠነኛ መጽሐፍ የተዘጋጀው በመጠኑም ቢሆን ይህንን ዕውቀት እንድትሰጥ ታስቦ ነው፡፡”

Share this article:

መሪነት:- ወሳኙ ጉዳይ

ʻመሪዎች ለሁሉም ዐይነት ተቋማዊ ችግር ፍቱን መድኃኒቶች ናቸውን?ʼ በርግጥ በአመራር ላይ ጥናት ያደረጉ ጥቂት የማይባሉ ምሁራን መሪዎችን እንዲህ ባለ መልክ አያቀርቧቸውም። እጅግ የተደነቁቱ የአመራር ዘይቤዎችም ሳይቀሩ (ለምሳሌ፡- ሎሌያዊ አመራር – “Servant Leadership” እና ተሃድሷዊ አመራር – “Transformational Leadership”) ላለንበት ተቋማዊም ሆነ አገራዊ ችግር ብቸኛ መፍትሔ እንዳይደሉ እነዚሁ ምሁራን ይስማማሉ። ይህን አቋማቸውን “Leadership is not a panacea to all our problems” በማለት ነው የሚገልጡት – መሪነት ለችግሮቻችን ሁሉ ፍቱን መድኃኒት አይደለም እንደማለት ነው። ይህ ሲባል ግን የመሪዎች ሚና እንደዋዛ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ ሊታሰብበት ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ

እምነታችን ሲፈተሽ

የእምነትን አመለካከት በሁለት አቅጣጫ ዐጠር ባለ ሁኔታ እንመልከት። ይህም አንደኛ፤ እምነትን ለግል ኑሮ የምንጠቀምበት አግባብና፣ ሁለተኛ እምነትን ለመንግሥቱ የምንጠቀምበት አግባብ ነው።  እምነት ለግል ኑሮ በግል

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.