ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ እናውቃቸው የነበሩ አንዳንድ አፍሪካውያን “አገልጋዮች” በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ መታየት ጀምረዋል። በቅርቡ የተከሰቱ ሁለት ኩነቶችን እንኳ ብንመለከት “ሜጀር ሼፐርድ ፕሮፌት” ቡሽር ከማላዊ፣ “ነቢይ” ኮቦስ ቫን ሬንስበርግ ከደቡብ አፍርካ ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ልብ ይሏል። እነዚህ ሁለት ግለ ሰቦች የሚያመሳስላቸው ዋና ነገር አዋዛጋቢ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ልምምድ እና አስተምህሮ ያላቸው መሆኑ ነው።
ከዚህ በፊት “ሜጀር ሼፐርድ ፕሮፌት” ቡሽሪ በኢትዮጵያ ያካሄዱት “አገልግሎት” የተሳሳተ መሆኑ በሕንጸት መጽሔት ቁጥር ሁለት ዕትም ላይ መቅረቡ ይታወሳል። ይሁን እንጂ፣ የ“ነቢይ” ቡሽሪ ጦስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አሁንም የለቀቃት አይመስልም። ብዙዎች የእርሳቸውን ፈለግ ተከትለው በየመድረኩ ምእመናንን በማወናበድ ላይ ይገኛሉ። ለዚህ እማኝ የሚሆነው በቅርቡ አንድ ‘ነቢይ ነኝ’ የሚሉ ግለ ሰብ በአካሄዱት ኮንፍራንስ ላይ የተካሄደው የውሃ ሽያጭ ነው።
ጥር 2 እና 3፣ 2007 ዓ.ም. “የክርስቶስ ኢየሱስ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ከCJ TV ጋር በመተባበር” በሚሌኒየም አዳራሽ በአዘጋጁት ስብሰባ ላይ “ነቢይ” ኮቦስ ቫን ሬንስበርግ የተባሉ ግለ ሰብ ከደቡብ አፍሪካ በመምጣት ጉባኤ ሊደርጉ እንደ ነበር የሚታወስ ነው። ሆኖም ግን የታሰበው ስብሰባ በተጠቀሰው ቦታ ሳይካሄድ መቅረቱ በወቅቱ ሲነገር ነበር። የዚህም ምክንያቱ ከደቡብ አፍሪካ መጡ በተባሉት ግለ ሰብ የአስተምህሮ ችግሮች ያሉባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የክርስቲያኖች ኅብረት እንዲሁም ሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር ባሰሙት ተቃውሞ ነበር።
ተቃውሟቸውን ያሰሙ ወገኖች ምክንያት “ነቢይ” ኮቡስ ቫን ሬንስበርግ የመጡበት ወርልድ ኦፍ ስፒሪት ሚኒስትሪ የአስተምህሮ ሕጸጽ ያለበት በመሆኑ ነበር። ይህ ተቋም በኮቡስ ቫን ሬንስበርግ የተጀመረ አገልግሎት ሲሆን፣ ኮቡስ ቫን ሬንስበርግ ታኅሳስ ወር 2006 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ልጃቸው ኮቡስ ቫን ሬንስበርግ አገልግሎቱን ተክተው መምራት ጀመሩ። ወደ አገራችንም ተጋብዘው መጥተው የነበሩትም እኚሁ ሰው ናቸው።
ይህ ጽሑፍ፣ ወርልድ ኦፍ ስፒሪት ሚኒስትሪ ካሉበት የአስተምህሮ ስሕተቶች መካከል ሁለቱን ብቻ ነቅሶ የሚያወጣ ይሆናል። በዚህም የኮቡስ ኑፋቄ ናቸው የተባሉትን ሁለት ጉልሕ አስተምህሮዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከሆነው አስተምህሮ ጋር ይነጻጸራል። በመጨረሻም፣ “‘የክርስቶስ ኢየሱስ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን” የተሳሳተ አስተምህሮ ያላቸውን ሰዎች እና ቤተ እምነቶች የአገልግሎት አጋር ማድረጓ ለምን አስፈለገ?’ በሚል የሚያጠይቅ ነው።
ኑፋቄ ፩፡- “አካላዊ ሞት ምርጫ ነው፤ ክርስቲያኖች ሳይሞቱ ለዘላለም ሊኖሩ ይችላሉ!”
የስፒሪት ወርልድ ሚኒስትሪ መሥራች የሆኑት “ነቢይ” ኮቡስ ቫን ሬንስበርግ “የማይሞት/የማይጠፋ ዘላለማዊ ሕይወት” በተሰኘው ስብከታቸው ክርስቲያኖች ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ከሠራው ሥራ የተነሣ በምድር ላይ ሳይሞቱ ለዘላለም መኖር እንደሚችሉ አስተምረዋል። እንደ እርሳቸው እምነት ከሆነ የኢየሱስ ክርሰቶስ የመስቀል ላይ ሞት፣ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ እንዳይጠፉ/እንዳይሞቱ ነው። ለዚህ ማስረገጫ እንዲሆናቸው ዮሐ. 3፥14-15፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በዋናነት ያነሣሉ። በመቀጠልም፣ “ዛሬ ብትሞቱ አካላችሁ ምን ይሆናል?” በማለት እየጠየቁ ራሳቸው መልስ ሲሰጡ፣ “አካላችን ይጠፋል፤ ነገር ግን ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች ሞተው ‘እንዳይጠፉ’፣ ለዘላለም በምድር ላይ ሞትን ሳይቀምሱ እንዲኖሩ ነው።” ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር የመጣው ሞትን ለማሸነፍ እንደ ሆነ፣ ሞትንም እንዳሸነፈ እንዲሁም በሞት የሚሸነፍ አካል እንዳልነበረው የሚገልጹት እኚሁ ነቢይ፣ ይሁን እንጂ ኢየሱስ በገዛ ፈቃዱ ራሱን አሳልፎ ስለ ሰጠ እንጂ ማንም (ሞትም እንኳ ቢሆን) ሕይወቱን ከእርሱ ሊነጥቅ እንደማይችል ያብራራሉ። በድምዳሜያቸውም፣ “ክርስቶስ ስለ እኛ ሞትን ከቀመሰ እኛ ሞትን መቅመስ የለብንም። የአማኞች የቀብር ሥነ ሥርዐት ሲካሄድ ‘ዛሬ ወንድማችን/እኅታችን በሞት ቢለየንም በመጨረሻ ሞትን አሸንፎ ይነሣል’ የሚለው አባባልም ትክክል አይደለም” በማለት ይሞግታሉ። ለዚህም የሚያቀርቡት አስረጅ አካላዊ ሞትን የሞተ ሰው በሞት ኀይል መሸነፉ ነው ባይ ናቸው። ስለዚህም፣ ክርስቶስ ሞትን ስላሸነፈ እኛ መሞት የለብንም፤ እንደ እርሳቸው አስተምህሮ።
በዚሁ ላይ ሲያክሉም፣ ሞት ኢየሱስን ፈጽሞ ሊያሸንፈው ያልቻለው መንፈስ ቅዱስ ያለገደብ ስለ ተሰጠው ወይም በመንፈስ ቅዱስ ስለ ታተመ ነው ይላሉ። እንደ ኮቡስ አስተምህሮ የኢየሱስ ክርስቶስ በሞት ያለመሸነፍ ምሥጢር መንፈስ ቅዱስን ያለ ገደብ መሞላቱ ነበር። በመሆኑም፣ ክርስቲያኖችም ሞትን እንዳይቀምሱ ከፈለጉ የዘላለም ሕይወት የሚሰጠውንና ለዘላለም በምድር ላይ ሳይሞቱ እንዲኖሩ የሚያደርገውን፣ የሕይወት መንፈስ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ያለገደብ መሞላት አለባቸው። “ኢየሱስ በተቀበለው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ የታተማችሁ ከሆነ ሞት ሕይወታችሁን ሊቆም አይችልም። ልትሞቱ አትችሉም። ይልቁኑም የሕይወት ውሃ ምንጭ ከሕይወታችሁ ይፈልቃል፤ ሞትን የምታሸንፉ ትሆናላችሁ እንጂ በሞት የምትሸነፉ አትሆኑም። ሞትንም አሸንፋችሁ ለዘላለም በዚህች ምድር ላይ መኖር ትችላላችሁ!” ይላሉ።
እውን መጽሐፍ ቅዱስ ‘ክርስቲያኖች ሳይሞቱ ለዘላለም በዚህች ምድር ይኖራሉ’ የሚል ተስፋ ይሰጣል? በፍጹም አይሰጥም! በርግጥ የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት የሰው ልጆችን የኀጢአት ዕዳ ለመክፈል የሆነ ነው። በመሆኑም፣ ሞት በክርስቶስ ትንሣኤ ተሸንፏል። ሆኖም ግን አሁን የምንኖረው “በአሁን እና በወደ ፊት የመጨረሻው ዘመን ውጥረት” (already but not yet eschatological tension) በተሰኘ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ነው። ይህም ማለት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የድነት ሥራ እና ትንሣኤ አማካኝነት የኀጢአት ውጤት የሆነው ሞት ተሸነፏል፤ ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች አሁንም ይሞታሉ፣ ይታመማሉ፣ በዓለም ውስጥ ያለው መከራ ሁሉ ይደርስባቸዋል። ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ግን ይህ ሁሉ ይሻራል። የሞቱ አማኞች ዳግመኛ የማይሞት የትንሣኤ አካልን ይለብሳሉ። በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩ አማኞች በቅጽበት በመለወጥ የማይሞት እና የማይበሰብስ የትንሣኤ አካልን ይለብሳሉ፤ ምድርም ትታደሳለች። የፍጥረት ሁሉ ናፍቆት እና ተስፋ ፍጻሜውን ያገኛል።
የኮቡስ ቫን ሬንስበርግ ስሕተት ‘ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ስላሸነፈ፣ እኛም በመስቀል ላይ የተከፈለውን ዋጋ ሁሉ አሁን፣ እዚሁ እናገኛለን’ የሚል መሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ሞቱ እና በትንሣኤው ሁሉን እንደፈጸመልን ቢናገርም፣ የተባለው ሁሉ በእጃችን የሚገባው በመጨረሻው ዘመን፣ በእርሱ ዳግም መምጣት ጊዜ ነው። “ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ” (ዮሐ. 6፥40)፤ “ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ” (ዮሐ. 6፥53-54)፤ ይህ የአማኝ ሁሉ ናፍቆት እና ተስፋ ነው። በመጨረሻው ዘመን ኢየሱስ በመላእክት ታጅቦ ሲመጣ ለዘላለም ከእርሱ ጋር የትንሣኤን አካል ለብሰን እንኖራለን፤ የተባረከው ተስፋችን ይህ ነው። ማራናታ!
ነፉቄ ፪፡- “ሞትን የማይቀምሱ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ ሰዓት አሁን ነው”
“‘ታዲያ በተለያዩ ዘመናት የኖሩ ክርስቲያኖች ለምን ሞቱ?’ የሚል ጥያቄ ልትጠይቁኝ ትችላላችሁ” ይላሉ “ነቢይ” ኮቡስ። ሲመልሱም፡- “የተወሰነለት/ የተቀጠረለት ጊዜ ስላልደረሰ” የሚል ነው። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ ምንም እንኳ ይህንን የተስፋ ቃል እንደማያገኝ ቢያውቅም በዚህ ወንጌል ግን እንደማያፍር ተናግሯል። ያላገኘው ደግሞ “የተወሰነው ጊዜ ስላልደረሰ ነው”። “አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል። ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።” 2ጢሞ. 1፥10-12።
ጳውሎስ በዚህ ሥፍራ ላይ የዘላለም ሕይወትንና አለመጥፋትን፣ በዚህ ምድር ለዘላለም የመኖር ተስፋን እንደሚሰብክ፣ ነገር ግን ይህ በእርሱ ሕይወት ውስጥ እንደማይከናወን ተናግሯል። በእርሱ ሕይወት ባይፈጸምም እንኳ እርሱ ግን በዚህ ወንጌል እንዳላፈረ ኮቡስ ይገልጻሉ። ይኸው ጉዳይ በሐዋርያው ጳውሎስ እንዲሁም ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ በሆነው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አንድም ጊዜ ያልተፈጸመበትን ምክንያት ሲናገሩ፣ “እግዚአብሔር የወሰነው ጊዜ አልደረሰም ነበርና” ይላሉ። ማለትም ከዚህ በፊት በነበሩት ዘመናት “ክርስቲያኖች መሞት የለባቸውም” የሚለውን ትምህርት ማንም አስተምሮት አያውቅም ነበር፤ “ሰዎች ዘላለማዊ ሕይወትን አላመኑም ምክንያቱ ደግሞ ስለ ዘላለማዊ ሕይወት አልሰሙም፣ ማንም ስለ ዘላለማዊ ሕይወት [ሥጋዊ ሞትን ስለ አለመቅመስ] አልሰበከላቸውም፤ ያልተሰበከላቸው ደግሞ ይህን እንዲሰብኩ ሰዎች አልተላኩላቸውም ነበር።” ብዙ ሰዎች የዘላለም ሕይወትን በሰበኩ ቁጥር ብዙ ሰዎች ይሰሙታል፣ ብዙ ሰዎች በሰሙት ቁጥር ብዙ ሰዎች ያምኑታል፣ ብዙ ሰዎች ባመኑ ቁጥር ብዙ ሰዎች ይናገሩታል፣ ብዙ ሰዎች አምነው በተናገሩት ቁጥር አካላዊ ሞት የማይሞቱ “የእግዚአብሔር ልጆች” በምድር ላይ በብዛት ይገለጣሉ። ምድር ስትጠባበቀው የነበረው ሞትን የማይቀምሱ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ ጊዜው አሁን ደርሷል። እኛም ይህንን ትምህርት ብናስተምር፣ ብዙ ሰዎች ይህንን አስተምህሮ ቢቀበሉ፣ ቢያምኑት ዘመናችን ሞትን የማይቀምሱ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ ይሆናል። ምክንያቱም ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆችን መገለጥ በጭንቀት ውስጥ ሆኖ ይጠባበቃል፣ ሞትን የማይቀምሱ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ ሰዓት አሁን ስለሆነ ይላሉ “ነቢይ” ኮቡስ።
በዚህ አስተምህሮው ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉ። አንደኛው፣ ሞትን የማይቀምሱ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ ሰዓት አሁን መሆኑን እንዴት ለእርሳቸው ብቻ ተገለጠላቸው? ክርስትና ከሁለት ሺህ ዘመናት በላይ ዕድሜን ያስቆጠረ ሃይማኖት ሆኖ ሳለ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ “ነቢይ” ኮቡስ “እግዚአብሔር ለእኔ ገልጦልኛል፣ ዘመኑ ሞትን የማይቀምሱ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ ነው” ማለታቸው እግዚአብሔር ለ“ነቢዩ” አዳዲስ መገለጦችን እንደሚሰጥ ማመናቸው ነው። ትክክለኛ የወንጌላውያን ክርስትና አስተምህሮ ግን የእግዚአብሔር የድነት ሥራ ዕቅድ አንድ ጊዜ በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠ በመሆኑ አዲስ መገለጥ ከእንግዲህ አይኖርም የሚለው ነው። በርግጥ በቀደምት ክርስቲያኖች ዘንድ ይደረግ እንደነበረው እግዚአብሔር ዛሬም በዘመናችን አብርሆትን ይሰጠናል፣ ያልተረዳነውን ነገር ይገልጥልናል፣ ያስረዳናል፤ ነገር ግን የድነት ዕቅዱን በተመለከተ አዲስ መገለጥን አይሰጥም። ይህ “አዲስ ነገር ተገለጠልኝ” የሚል ብሂል የኑፋቄ መምህራን ዐይነተኛ መለያ ባሕርይ ነው።
ሞትን የማይቀምሱ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ ሰዓት አሁን ነው በሚለው የኮቡስ አስተምህሮ ላይ ያለው ሁለተኛው ስሕተት፣ የእግዚአብሔርን የድነት ዕቅድ በትክክል ካለመረዳት የተፈጠረ ኑፋቄ ነው። ሮሜ 8፥19-22 “የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነጻነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት እንዲደርስ ነው። ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የሚያመለክተው በመጨረሻው ዘመን ክርስቶስ ዳግም እስኪመጣ ድረስ፣ ክርስቲያኖች የማይበሰብስ የትንሣኤ አካል እስኪለብሱ ድረስ፣ ምድርና ሞላዋ እንደገና እስክትታደስ ድረስ ሁሉም በናፍቆት እና በተስፋ መጠባበቃቸውን የሚያሳይ እንጂ ከክርስቶስ ዳግም ምፅዓት በፊት የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑት ክርስቲያኖች ሳይሞቱ የሚኖሩበትን ዘመን ፍጥረት በናፍቆት እየተጠባበቀ ነው ማለት ግን አይደለም።
መደምደሚያ
በዚህ ጽሑፍ ሁለት የኮቡስ ቫን ሬንስበርግን የአስተምህሮ ስሕተቶች መርጦ ለማሳየት ተሞክሯል። እነዚህ “ክርስቲያኖች ሳይሞቱ ለዘላለም በዚህ ምድር መኖር ይችላሉ” እና “የማይሞቱ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ ሰዓት አሁን ነው” የሚሉት አስተምህሮዎች ኮቡስ የኑፋቄ አስተማሪ ለመሆናቸው አስረጅዎች ናቸው ብለን እናምናለን። ምንም እንኳ ግለ ሰቡ ይህንን ይበሉ እንጂ ሞትን ከመቅመስ አላመለጡም። ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር በበሽታ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። እርሳቸው ይመሯት የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገለገሉ የነበሩ ምእመናን፣ አገልጋዮች እና የቅርብ ወዳጆቻቸው ሞታቸውን መቀበል ተስኗቸው ለስድስት ተከታታይ ቀናት ከሞት እንዲነሡ ቢጸልዩም ጸሎታቸው አልተሰማም።
የአባታቸውን አገልግሎት የተረከቡትና ወደ እኛ አገርም መጥተው የነበሩት “ነቢይ” ኮቡስ ቫን ሬንስበርግ (ልጅየው) የአባታቸውን አስተምህሮ እስካሁን አላስተባበሉም። ቤተ ክርስቲያናቸውም፣ “ክርስቲያኖች በምድር ላይ ለዘላለም ሳይሞቱ መኖር ይችላሉ” የሚለውን አስተምህሮ መቀየሯን የሚያሳይ የአቋም መግለጫ እስከ አሁን ድረስ አላወጣችም። ስለዚህ የስፒሪት ወርልድ ሚኒስትሪ “ክርስቲያኖች በምድር ላይ ለዘላለም ሳይሞቱ መኖር ይችላሉ” በሚለው አቋሙ ላይ ምንም ለውጥ አላደረገም ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ “የክርስቶስ ኢየሱስ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን” ይህ አስተምህሮ ያለውን ግለ ሰብ ሳትመረምር እንዴት ልትጋብዘው ቻለች? የአስተምህሮው ተጋሪ ሆና ወይስ ካለማወቅ በመነጨ ስሕተት? መልስ የሚያሻው ጥያቄ ይመስለናል!
Add comment