ልጆች ሳለን በሚነገሩን ጣፋጭ ተረቶች በኩል አጮልቀን የምናያቸው የሕልም ዓለማት ነበሩን። (ርግጥ፣ በነ “አያ ጅቦ” ታሪክ ብቻ ላደገ ልጅ ይህ አባባል አይሠራም።) እኒያ ተረቶች የሚያነጫንጩ የልጅነት ችግሮቻችንን በማስረሳት በሐሳብ ሰመመን ውስጥ አስገብተው እንደሚያፍነከንኩን ትዝ ይለናል። ነገር ሁሉ “አልጋ በአልጋ” በኾነበት የተረት ዓለም፣ የፈጠራ ታሪኮቹ፣ ከደስታ ባሕር ላይ ያንሳፍፉን ነበር። በዕድሜያችን ከፍ ብለን ከእውነታው ጋር መገናኘት ስንጀምር ግን፣ በልጅነት ልቡናችን የገነባናቸው ረቂቅ የሐሳብ ዓለማት መናድ ይጀምራሉ። የእውናዊውና የገሓዱ ዓለም “ጣጣ ፈንጣጣ” ይቀበለናል። እኛም ከእናቶቻችን ጀርባና ከአባቶቻችን ዕቅፍ እንወርድና በግላችን ወደምንውተረተርበት ስፍራችን “ዝቅ” እንላለን።
የአጽናፈ ዓለሙ ማእከል እንደ ኾንን ያህል እንዲሰማን የሚያደርጉን እኒያ የተረት ዓለም ጣፋጭ ነገሮች እየተነኑ ይለዩናል። ከብዙዎች እንደ አንዱ የመኾናችን ሐቅ ፊታችን ይገሸራል። ከሕይወት ጋር ፊት ለፊት እንጋፈጣለን። ዓለማችንን ከነቡጉሯ ጭምር እናያለን። የእሳት ዳር ትራኬዎች ቀስ በቀስ ትርጕማቸው ይወይብና፣ ከሕይወት ጋር የሚኖረን ተራክቦ አስተውሎት ተጨምሮበት፣ አካባቢያችንን ከውጣ ውረዱ፣ ከደስታና ኀዘኑ፣ ከጥያቄው፣ ከሩጫው … ጋር እንረከባለን። እየወደቅንና እየተነሣን የምናዘግምበት ወይም የምንክተፈተፍበት መንገድ ይኖረናል። ሩጫ በተሞላው የኑሮ ጎዳና ላይ ማዝገሙ አይቀሬው ዕጣ ፈንታችን ይኾናል።
እናም፣ ሕይወት እንደ መንገድ፣ ሕይወት እንደ ጕዞ፣ ሕይወት እንደ አቀበት፣ ሕይወት እንደ ሩጫ … ትመጣብናለች። አንድ ነገር ግልጽ ይኾንልናል፦ በተሰጠን ዘመን “ሯጮች” ነን።
በሕይወት መንገድ ላይ ሁላችን ሯጮች ነን
ቀዝፈን የምንዋኝ በዕድሜ ጅረት ሰፍረን
የዚህ ምድር ሩጫና ግብግብ ብርቱ ሰልፍ የተሞላ ነው (ኢዮ. 7፥1)። ለእኛ ለክርስቲያኖችም የዚህ ዓለም ኑሮ መከራና ተግዳሮት የሞላው መኾኑ ተነግሮናል። ሐዋርያቱ፣ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” (ሐዋ. 14፥22) በማለት እንደ ተናገሩት ያለ ነው። ዳገት እንወጣለን፤ ቍልቍለት እንወርዳለን፤ ሸለቆም እንሻገራለን ።
የልባችን ዐይኖች ሲከፈቱልን፣ ለከበረ እውነትና ለዘላቂ ዓለማ መሰለፍ አለ። አለዚያ ይህ “እንጀራ” ይሉት ነገር ወዛችንን እየመጠጠና ሐሳባችንን እየሰነከለ ያንከላውሰናል። ዘመናችንን የምንደኛ ወራት ሊያደርግብን ይዳዳዋል። ደረጀ በላይነህ በየዕድሜ መንገድ ውስጥ ባሰፈራት “ሯጮች” በተሰኘችው ግጥሙ እንዳለው እናንጐራጕራለን፤
ሁላችን ሯጮች ነን፥ ሁሌ እንሮጣለን ከእንጀራችን ኋላ፥
ምንም አሸንፈን ዋንጫውን ባንበላ።
ብታንስም ብታድግም የየራሳችን ሩጫ አለችን። የልደታችን ፀሓይ ከሠረቀችበት ቅጽበት ፊትም ኾነ ኋላ ሩጫውና ትግሉ እንዳለ ነው። “ከልደታችን በፊት” ያልኩት ባይታወቀን እንጂ፣ በማሕፀንም ውስጥ እያለን ስንትና ስንት “ሩጫ” ማሳለፋችን አልቀረምና ነው። በዚች ምድርም ላይ የተሰጠንን ዘመን ያህል መፏተቱ ይኖራል። ቀን ሳይል ሌሊት መብከንከኑ ይቀጥላል። የባሰበት ተኝቶስ መች ያርፋል? በስሜት እየዋተተ ጣራ ሲቈጥር፣ ሲያስርና ሲፈታ፣ ሲወጣና ሲወርድ ሌሊቱን ማጋመሱና ሲብስም ማንጋቱ አለ። እንዲህ ዐይነቱ መማሰን ከብዙዎች አንደበት ሲነገር የምንሰማው ሕማም ነውና እናውቀዋለን።
ይህ ሩጫ ታዲያ “ዐልጋ በዐልጋ” ዐይነት የምቾትና የተድላ መንገድ ብቻ አይከተልም። አድካሚና “የዳገት ላይ ጕዞ” የሚኾንበት ወቅት አለ። በግልም ኾነ በጋራ ዳገቱን መቧጠጥ ይኖራል። ያንዳንዱ ጥረት እንደ ሸረሪት ነው፤ ድሩን እያደራ እያውተበተበ። የሌላው እንደ በረሮ ነው፤ በዘፈቀደ የመርመስመስ። የገብረ ጕንዳን ዐይነት ጥሮ አደርም አለ። በጥምዝምዙ ሳይበገር በኅብረት እየተረዳዳና እየተጋገዘ የሥልጣኔ “ኵይሳውን” የሚገነባ።
ቤተ ሰብ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ማኅበረ ሰብና ሀገር ማለት እንደ ኵይሳው ይመስለኛል። “እኔው የሠራሁት” እና “የእኔው ነው” አይባልምና። “የእኔ፣ በእኔ፣ ለእኔ” ብቻ የማለት መደገግ ከመጣ፣ አፈር ድቤ የምታስግጠውን የናቡከደነፆርን ጽዋ መጨለጥን ያስከትላል (ዳን. 4፥30- 33)።
ግርማ ተስፋው የተባለ ገጣሚ፣ የጠፋችውን ከተማ ኀሠሣ በምትል መድበሉ መግቢያ ላይ፣ “ሁላችንም የየራሳችንን ዳገት በየቀኑ እንወጣለን” ይላል። እውነት ነው። በግልም በኅብረትም የሚወጣ አቀበት አለ።
የአንድ ትውልድ ጕዞ፣ የአንድ ማኅበረ ሰብ የዕድገትና ለውጥ ተስፋ የሚጠይቀው ጥረት ታላቅ ነው። ዛሬ ጠዋት ተጀምሮ ምሽት ላይ የሚጠናቀቅ ስኬት የለም፤ በአንዲት ጀንበር የተጠናቀቀ ሥልጣኔም አይታወቅም። በውጣ ውረድ የተሞላ ትጋት ይሻል።
እኛማ፣ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጧ ጭምር በተራራና በዳገት የተሞላች ሀገር ውስጥ የምንኖርም አይደለን? The Ethiopian Highlands ማለትን ማን ያጣዋል? በአጠቃላዩ ማኅበራዊ ጥምዝምዛችን ውስጥ እንደ ሕዝብም እንደ ሀገርም የራሳችን ዳገት ያለን መስሎ ይታየኛል። ልንወጣው የምንፍጨረጨርበት አቀበት ይሣልብኛል። ከሀገሪቱ ጐምቱ ባለሥልጣናት፣ ምሁራን፣ ጸሓፍትና ከያኒያን አንደበትና ብርዕም ይህንን ሐቅ መልቀም ይቻላል።
ለምሳሌ፣ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ በረከት ስምዖን የሁለት ምርጫዎች ወግ በተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ ሐሳባቸውን የሸበለሉት “ናዳን የገታ ሀገራዊ ሩጫ” በሚል ሐረግ ነው። ናዳ ከዳገትና ገደል በቀር ወደየት አለ? ያለ ዳገት ናዳ የለም።
ዘመን መጽሔት በኅዳር 2005 ዓ.ም. በድጋሜ ታትሞ ለንባብ በበቃው ልዩ ዕትሙ ላይ ክቡር ጠ/ሚ ኀይለማርያም ደሳለኝ በቀድሞው ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ የቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ ያደረጉትን ንግግር አስፈሯል። ከዚያ ውስጥ የሚከተለውን እንቀንጭብ። አቶ ኀይለ ማርያም፣ “በእሳቸው መሪነት የዳገቱን ጕዞ አጋምሰናል። … ዳገቱ መኻል ላይ መቀመጥ ወይም ማረፍ አይፈቀድልንም። ካረፍን ይደክመንና ዳገቱን መውጣት ይሳነናል” ይላሉ። ልብ በሉ፤ ሀገራዊው ጕዞና ጥረት የተመሰለው በዚያው በዳገት ነው።
ለማለት የፈለግሁት፣ ማኀበረ ሰባዊና ሀገራዊ “የዳገት ላይ ጕዞ” የመኖሩ ነገር ሰፋ ያለ ቅቡልነት አለው ነው። ዳገቱ የግል ሕይወት ጕዳይም ነው። በርግጥ፣ አንድ ሰው በሰሎሞን ደሬሳ የአሰላስሎ ንጽረት ላይ ተመሥርቶ “የዳገቱ ነገር” እንደ አተያዩ ነው ብሎ ሊከራከር ይችላል።
“ዳገት ሽቅብ የታየ ቍልቍለት ቍልቍለት
ወደ ታች የታየ ዳገት” እያለ።
የኾነ ኾኖ፣ “ዳገት” አለ፤ በግልም በጋራም የምንወጣው “አቀበት” አለ። አቀበቱን ለመውጣት የሚከፈል ውድ ወዝ ከየዜጋው ተመጥጦ መፍሰሱ አልቀረም። በየዘመኑ ዳገት መቧጠጡ እንደ ነበረና እንዳለ እናውቃለን። በየሥርዐቱ ልዩ ልዩ የዳገት ላይ መንገዶችን ተጋፍጠናል። በየልማዱ ውስጥ የተመደበልንን አቀበት ለመውጣት ተውተርትረናል። በየአግባቡ ያጋጠሙንን ፈፋዎች ለመሻገር ሞክረናል። የተሳካልን ያለውን ያህል፣ ያልተሳካም ይኖራል። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአንድ ግጥማቸው ውስጥ ያኖሩት ሐረግ “ዳገት ላይ ሰው ጠፋ” ይላል። በዳገት ላይ ሩጫው የተከሠተን “ጥፋት” የገለጹበት ቍጭት ይመስላል።
እንደ ማንኛውም ሕዝብ፣ የእኛም ጥረትና መፍገምገም ያለና የነበረ ነው። ከስሕተታችን ተምረን፣ በስኬታችንም ተበረታትተን ከመቀጠል ሌላ ምን አማራጭ ይኖራል?
በዚህ መፍገምገም ውስጥ እንደ ወጣ የቀረ እልፍ አእላፍ ዜጋ አለ። ገሚሱ ታሪክ ሠርቶ፣ ለተከታዩ የመሸጋገሪያ መደላድል አበጅቶና “መሰላሉን” ኾኖ ተተኪው ትውልድ ወደ ደርቡ ይወጣ ዘንድ ዐግዟል። መሪው፣ ተመሪው፣ ገበሬው፣ ነጋዴው፣ ወታደሩ፣ ምሁሩ፣ የእጅ ባለሞያው፣ ካህኑ፣ ወዘተ… ሀገራዊ ዋጋውን ታሪክ ይሰጠዋል ብለን ተስፋ እናድርግ። ወሮታውን የሚያኪያኪስ ትውልድ ካልተነሣበት ዐላፊው ወገን የቈፈረው ምንጭ ላይ አሸዋ አይሞጀርበትም፤ ጕድፍ አይጣልበትም።
በርግጥ፣ አንዳንዴ ሁሉን ነገር የዛሬው ትውልድ የጀመረው የምናስመስልበት ጊዜ አለ። ቀድሞ የነበረውን በጅምላ የሚያጣጥል አይጠፋም። ብርሃኑ ድንቄ አልቦ ዘመድ ውስጥ የሳሉት ፀሓዩ የተባለ ገጸ ባሕርይ ሲጸጸት፣ “[ትውልዱ] ባህሉን፣ ወጉን፣ ሥርዓቱን፣ ሥነ ጽሑፉንና ታሪኩን ጭምር ነቅፎ ከባዶ ቤት የሸፈተ ስለ ነበረ” ዐብሮ ተደምሮ ሲያጨበጭብ መኖሩን በቍጭት ይተርካል። “ለካስ አባቶቻችንን አድኃሪያን እያልን የምንሰድበው የኛን ድንቍርና ለመሸፈን [ኖሯል]” እያለ ይተክዛል። መተከዝ ሲያንሰው ነው?! መደበኛ ትምህርት ቤት ካልሄዱት አባቴና እናቴ ስንቱን ክቡር ነገር ሸምቻለሁ እኮ!
ለማንኛውም ዳገቱን የመውጣት መፍጨርጨሩ አለ። በእነዚህ ሁሉ ትግሎቻችን ምን ያህል ተሳካልን? ወይም ምን ያህል ጊዜ ተንሸራትተን ወደ ታች ተመለስን? ትልቅ ጥያቄ ነው። በዚህ የዳገት ላይ ጕዞ ተሸንፈው ወደ አዘቅቱ የሰረጉ እንደ ነበሩ ስንሰማ ኖረናል፤ አንብበንማል። ሌሎች ደግሞ በአቀበቱ መኻል ሲፍገመገሙ ሳሉ በሌሎች ተጓዦች ተገፍትረው ተሰውረዋል። ይህ በዓለማዊውም በቤተ እግዚአብሔርም ታይቷል። ጥቂቶች በጽናት ተጕዘው ከአፋፉ ላይ ደምቀው እንደሚያበሩ ግልጽ ነው።
ዋናው ነገር፣ የዳገት ላይ ሩጫው ምሬትና ሥቃይ እንዳይበረታበት ምን ማድረግ አለብን? በጥርጣሬና በመካሰስ የምናተርፈው ነገር ያለ አይመስለኝም። አቀበቱን በእሾኽ መሙላትስ ምን ይጠቅመናል? ለበደሉን የምንበትነው ጠጠር እኛኑ መልሶ እንዳያውከን ማሰብ ይኖርብናል። የዳገቱን ጕዞ በመያያዝ እንጂ በመጓተት አንዘልቀውም። ወንድሞቻችንና ጎረቤቶቻችን ከፈፋው ጥልቅ ሰርገው ከቀሩ በኋላ ብቻችንን ከተራራው አናት ብንደርስስ ሐሴት ይሞላናልን? የአጥቢያችን ስኬት ብቻ ያስፈነድቀናል? “በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ” (1ጴጥ. 5፥9) ስታውቁ ዐብሮ በጸሎት ከመትጋት ጋር አጋርነትን ማሳየት እንዳለ መጽሐፍ አስተምሯል።
የአቀበቱ ጕዞ መተማመን ይሻል። ገጣሚ አበባው መላኩ “ዳገት የከፈላቸው” ወንድሞችን በአቤልና ቃየል የውረድ እንውረድ ሽመቃና ነፍስ ነጠቃ ምሳሌነት በሣለበት “እሰከ ማዕዜኑ” ስንኞች ውስጥ የመጠራጠርን ፍዳና የመተማመንን ፋይዳ ልብ በሚነዝር ቋንቋ ያወሳል።
“ከዚህ የቀን ጐደሎ ነው ከዚህ ክሕደት በኋላ፣ በተራራው አናትና ከግርጌ በቆመው መኻል መተማመኑ የላላ።”
ታዲያ ተስፋው ምንድነው? ተስፋው ተስፋ ነው። እንደ ተራራ የተገተረውን አቀበት በጽናት መውጣት እንደሚኖርብን ይሰማኛል። ወገባችንን በፍቅርና ተስፋ ጠበቅ ካደረግን በማሸንፈጥ እንወጣዋለን። ሀገረኛው ብኂል “ሆድን በጎመን ቢደልሉት፣ ጕልበት በዳገት ይለግማል” ይላል። በቍጭትና ቍዘማ ብቻ የትም አይደረስም። “ቍጭትና መረቅ ለጊዜው ይጣፍጣል”፤ ነገር ግን ተስፋ ከሌለበት አጥንት ያነቅዛል።
ተስፋ ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ ነው። አንዳንዶች የተስፋን አስፈላጊነት ኦክስጂን ለሳንባችን ከሚያስፈልግበት ውድነት ጋር ያመሳስሉታል። ያለ ኦክስጅን ታፍኖ መሞት እንደሚከሠት ሁሉ፣ ያለ ተስፋ ደግሞ የሰው ሕይወት በተስፋ መቍረጥ አዘቅት ውስጥ ይዘፈቃል፤ በዓላማ ቢስነትና ትርጕም የለሽነት መቅሠፍት ይመታል። የሰውን ልጅ አእምሯዊም ኾነ መንፈሳዊ ጥረት የሚያንቀሳቅስ የኀይል ምንጭ ተስፋ ነው። ተስፋ ለግለ ሰብ የሚያስፈልገውን ያህል ለማኅበረ ሰብም ያሻዋል። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የእምነት፣ የፍቅርና የተስፋ ማኅበረ ሰብ ናት።
ከማኅበራዊ መነፅር ከተመለከትነው፣ ተስፋ የአንድ ማኅበረ ሰብ ሕዝባዊ ንቃተ ኅሊና (civic consciousness) መጐልበት ምንጭ ይኾናል። ምክንያቱም ተስፋ የመጪውን ጊዜ ኅብረተ ሰብ፣ ከተማ ይሁን ሀገር መድረሻ ብሩኅና አጓጊ ያደርጋልና። ያለ ተስፋ ሰው ወደየራሱ የብቸኝነት ጥግ ተስፈንጥሮ በመስረግ ከማኅበራዊ ተግባቦቱ ይነጠላል። በሌላ በኩል፣ ተስፋ መቍረጥ የመታው ሰው ምናኔያዊ ሽሽትን እንደ ብቸኛ አማራጭ ስለሚወስድ የኅብረት ክብር ይወድቃል። እንዲህ ዐይነት ሰው ከፊቱ ያለውን ዕንቅፋት ሁሉ ለማንሣት በሚያደርገው የሞት ሽረት መንፈራገጥ በጭካኔና ደመ ነፍሳዊ መወራጨት ሊሞላ ይችላል።
ተስፋ ትዕግሥትን ያስተምራል፤ በሐሳብ ከማይስማማን ሰው ጋር እንኳን በፍቅር እንድንደማመጥና በማስተዋል እንድንመላለስ አቅም ይሰጠናል። ሮናልድ ቼይ እንዳለው፣ “ተስፋ ቢስነት የሞት ዐይነት ነው። ምክንያቱም የፍርሃትን በር ይከፍታልና፤ ፍርሃት ደግሞ ያደክማል፤ ያሽመደምዳልም።”
ተስፋ የመቍረጥ ደመና ቢከበንም እንኳ ተስፋ ብርታትን ይሰጠናል። የተስፋን ባሕርይ አስመልክቶ፣ ከግማሽ ምእት ዓመት በፊት ታዋቂው ፈላስፋ ጋብርየል ማርሰል እነዚህን ቃላት ጻፈ። “እውነቱ ይህ ነው። የተስፋ መቍረጥ ፈተና በሌለበት ጊዜ ተስፋ ሊኖር አይችልም፤ ተስፋ እኮ ይህን ፈተና በንቃት፣ በቅልጥፍና፣ ያለዳተኝነትና በድል አድራጊነት የምንቋቋምበት ክዋኔ (ተግባር) ነው።” አሜሪካዊቱ ክርስቲያን ኖቭሊስት አኔ ላሞትም ለዚህ አተያይ የቀረበ ሐሳብ አላት። “ተስፋ የሚጀምረው በጨለማ ውስጥ ነው፤ ትክክለኛውን ነገር በማድረግ የምትቆምበት ጽኑ ተስፋ ካለህ የማለዳው ንጋት ይመጣል። በንቃት ትጠብቃለህ፤ መሥራትህንም አታቆምም፤ ተስፋም አትቆርጥም” ትላለች።
አንድ ነገር ግን ግልጽ መኾን አለበት። የክርስቲያን ተስፋ ከልማዳዊው ተስፈኛነት (Optimism) የተለየ ነው። “ነገ ይህ መኾኑን አላውቅም፣ ምናልባት ሊኾን እንደሚችል ግን ተስፋ አደርጋለሁ” ማለት ፍጥረታዊ ነው። ክርስቲያናዊ ተስፋ እግዚአብሔር አምላክ ከሰጠው አስተማማኝ የተስፋ ቃል የተነሣ አንድ ነገር እንደሚኾን በጌታ ላይ መተማመን ነው።
ነጋችን በእግዚአብሔር ዋስትና ያልተጠበቀና ርካታ የሌለው ከኾነ፣ ከልክ በላይ በመጨነቅ ሕይወታችንን እናባክናለን። ይህ ዐይነቱ መፋዘዝ በበኩሉ አደንዛዥ ሥጋትና ፍርሃት ይለቅብናል፤ አለዚያም በስግብግብነት መንፈስ ይሞላናል። በመጨረሻም ንፉግነት ይጠናወተንና “ስለራሴ ብቻ፣ ስለእኔ መጪ ጊዜ ብቻ፣ ስለእኔው ችግር ብቻና ስለእኔው ብርታት ብቻ” በሚብከነከን የስስት ዐጥር ውስጥ ይቀይደናል። ያ ደግሞ ሌሎችን ከማፍቀርና ከተቈርቋሪነት ይመልሰናል።
በሌላ አባባል ተስፋ ራስን መስጠት የተሞላው የክርስቲያናዊ ፍቅር መገለጫ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲጠብቀን በመፍቀድ በራሳችን ምኞትና ብርታት ከመተማመን ጣዖት ይጠብቀናል። ርካታችን በግል ገበታችን ላይ በቀረበው ማዕድ ልክ መኾኑ ያበቃለታል። ስለ ሌሎች ግድ ይለናል፤ ሕመማቸው ይሰማናል። በዚህም አኗኗራችን ውስጥ እግዚአብሔር የበለጠ ይታያልና ለክብሩ ምስጋና ይኾናል። ምክንያቱም የክርስቲያን ተስፋ የሚጀምረው በመስቀሉና በትንሣኤው ኀይል ነው። ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተነሣ ከዓለም በተለየ መንገድ መኖር እንችላለን።
ሀገራዊ አበርክቶዎቻችን ከዜግነት ኀላፊነታችን እንደሚመነጩ ግልጽ ነው። ግን ደግሞ ክርስቲያናዊ ምግባራችንም ይህን ያስገድደናል። ለሰላም ለዕርቅና ለመግባባት መሠረት የኾነውን የክርስቶስ ወንጌል ተስፋ ላጣ ትውልድ ማቅረብ የተልእኳችን ማእከል ነው። የተሰበረው ዓለም የፍቅር አስታማሚና ፈዋሽ ይሻል። የወንጌል መልእክተኞች አስለቃሾች ሳንኾን ዕንባ አባሾች ነን። ዐመፅን መሸሽ ብቻ ሳይኾን ማውገዝም አለብን። ሰይፍ የሚያነሡ በሰይፍ ይወድቃሉ ያለው የጌታ ትምህርት ብርሃን በእኛ ሕይወት በኩል ማብራት አለበት። አለበለዚያ የዳገቱን መንገድ የበለጠ እናከብደዋለን። “በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ” (ማቴ. 6፥23)!
ጌታ ኢየሱስ ዓለምን ስለመለወጥ አስተምሮናል። ግን ዓለምን የምንለውጥበት መንገድ ከፍ በማለት ሳይኾን፣ በዝቅታ ነው፤ ጥቅማችንን በማሳደድ ሳይኾን መብታችንን ጭምር በመተው ነው። በባልንጀሮቻችን ላይ ጕልበትን በመፈተሽ ሳይኾን፣ እግራቸውን በማጠብ ነው። የሚያሳዝነው ግን፣ “ከፍ ለማለት” የሚደረግ ግብ ግብ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከመስፋፋቱ የተነሣ የጌታ ማኅበር እየተከፋፈለች ይታያል። ይህ ከንቱ ምኞትና ትንንቅ የዳገት ላይ ጕዞውን ያሰናክለዋል። ነገር ግን፣ “የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም በአምላኩ በእግዚአብሔር የሆነ ሰው ምስጉን ነው” (መዝ. 146፥5)።
የማይገኘውን ከመፈለግና ከእኔነትን ርኵሰት ራሳችንን ካልገታን የሕይወት ጕዞ በባዶነት ይመታል። ታላቁ እስክንድር ፈላስፋው ፕሉታርክ አንዳች ነገር እንደሚፈልግ ሰው፣ የዐፅም ክምር ላይ አፍጥጦ ያየዋል። ምን እየፈለገ እንደ ኾነም ይጠይቀዋል። ፈላስፋውም ሲመልስ፣ “ፈጽሞ ላገኘው የማልችለውን ነገር እየፈለግሁ ነው። ያም ምን መሰለህ? በአባትህ (ዳግማዊ ፊሊጶስ) ዐጥንትና በባሪያዎቹ ዐጥንቶች መካከል ያለውን አንዳች ልዩነት እየፈለግሁ ነው” አለው። የማይገኘውን የመፈለግ ከንቱ ልክፍትን ያሳየበት ነው።
በምድር ላይ ሕይወታችን መጨረሻ ላይ በጣም ልዩት (unique) ወይም በጣም አስፈላጊ የኾነው ነገር ከአካላዊ ቅሪታችን ጋር የተዛመደ አይደለም። ከኋላችን ትተን የምንሄደው ምልክት ወይም የውርስ አሻራችን በክርስቶስ የኖርነው ሕይወት ነጸብራቅ ነው። በተለይም በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ የተውነው ቋሚና ምግባራዊ ሀብት ነው ዋጋ ያለው። ይህን እንጠይቅ፡ – ʻሕይወቴ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ከሠራው ነገር የተነሣ በተቀበልኩት ፍቅር የሚታወቅ ነውን? ከዚህ ፍቅር በሚመነጭ ተስፋ የተሞላና የዳገት ላይ ጕዞውን የሚያግዝ ነውን?ʼ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት እንደሚያደርግ ደግሞ እናውቃለን (2ቆሮ. 4፥17)። አኔ ግርሃም ሎዝ እንዳለችው፣ “እግዚአብሔር በመከራ ከተቆረሰው የኢየሱስ አካል በረከት ማውጣት ከቻለ፣ መስቀልን ከመሰለ ዘግናኝ የሥቃይ ቦታም ክብርን ማውጣት ከቻለ፣ ከእኔም ችግር፣ ሕማምና ያልተመለሰ ጸሎት ውስጥ ባርኮት ሊያወጣ ይችላል። እኔ እሱን መታመን ብቻ ነው ያለብኝ።” አዎ፤ በስብራታችን ውስጥ የሚሠራ አለ።
ፍቅርን የምንማረውና የምናስተምረው ለራሳችን ፈቃድና ምኞት በመሞት ነው። በዚህ ፍቅር የተሞላ ተስፋ ያለው ሰው የሕይወትን ዳገት በአግባቡ ይወጣዋል። የዳገት ላይ ጕዞ ያለ ተስፋ ቢሞክሩት የመፍገምገም እዥ ያጠምቀዋል። ተስፋም ያለፍቅር ባዶ ምኞት ኾኖ ይቀራል። አንድ ዐቢይ ጕዳይ ግን አለ። ተስፋችን ዘላለማዊ እንጂ እዚሁ ተጀምሮ እዚሁ የሚያልቅ ልቅላቂ አይደለም። ምክንያቱም፣ እኛ ምእመናን “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” (2ጴጥ. 3፥13)።
Add comment