[the_ad_group id=”107″]

ቤተ ክርስቲያንና የገንዘብ አስተዳደር

አሜሪካ – October 8, 1985 እ.አ.አ

ለስምንት አመታት የወጣቶች ፓስተር በመሆን ሲያገለግል የቆየው የ42 አመቱ ፓስተር ኑዛዜ አስደንጋጭ ነበር፡፡ መጋቢው በቤተክርስቲያኒቱ አመታዊ ስብሰባ ላይ በጉባኤ ፊት ቆሞ “በእግዚአብሔር፣ በባለቤቴ፣ በልጆቼ፣ በቤተሰቦቼና የክርስቶ አካል በሆነችው ኮሎራዶ የምትገኘው የኢውዛ ባይብል ቸርች ፊት ኃጢአትን አድርጌያለሁ” በማለት ተናገረ፡፡ ላለፉት ስድስት አመታት ከቤተክርሰቲያኒቱ የመባ መሰብሰቢያ እቃ ውስጥና እርሱ ከሚመራው አገልግሎት ከወጣቶች አካውንት ወደ 42,000 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብን በስድስት አመት ጊዜ ውስጥ በመውሰድ ለራሱ ጥቅም ያውል አንደነበርና ይህንን ወንጀሉን ከሚስቱም ሰውሮ ያደርግ አንደነበር በመግለጽ እራሱን በቤተክርሰቲያኒቱ መሪዎች አና በአገሪቱ ህግ ተጠያቂ ለማድርግ አንደወሰነ ተናገረ፡፡ በዚህም ምክንያት በማጭበርበርና በስርቆት ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡

ኢትዮጵያ – 1990ዎቹና 2000ዎቹ እ.ኢ.አ

“በግለሰብ የተመሰረቱ” የሚባሉት ቤተ ክርስቲያናት ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት እንዳለ ይነገራል፡፡ ቤተክርስቲያን የገንዘብ ምንጯ ከምዕመኖቿ የሚሰጥ አስራት፣ መባና ስጦታ ናቸው ምእመኑ ለእግዚአብሔር አንጂ ለሰው አንደሚሰጥ አያስብም፡፡ ቤተክርስቲያን አንደ ተቋም ለመቀጠል ገንዘብ አጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ገንዘብ ቤ/ክ እንዴት እየተጠቀመችበት ነው? ለታለመለት አላማ እየዋለ ነው? ወይንስ የግለሰቦች ኪሰ ማደለቢያ ሆኗል? የሚለው ጥያቄ መልስ ያሻዋል፡፡ የቤተክርስቲያን ገንዘብ መንግስት አንኳ የሚቆጣጠረው አንደመሆኑ (የስራና የፋይናንስ ሪፖርት በየአመቱ አንዲቀርብ ሕጉ ያስገድዳል) ለታለመለት አላማ በትክክለኛው ሁኔታ እየዋለ ነው? ቤ/ክ ውስጥ ትክክለኛውን የሂሳብ ህግ ተከትሎ እየተሰራ ነው ወይ የሚለው አጠያያቂ ጉዳይ ሆኗል ?

ገንዘብን በተመለከተ አደገኛ ሊባሉ የሚችሉ አካሄዶች እየታዩ ነው፡፡ በችግረኛ ስም ስጦታ ከጉባኤ ሰብስቦ ለግለሰቡ ያልሰጠ ፓስተር ፣ ቤ/ክ የማታውቀው ደረሰኝ በግሉ አሳትሞ ገንዘብ ሲሰበስብ ተደርሶበት የተባረረ አገልጋይ ፣ ለተጋባዥ አገልጋዮች የሚከፈለው የትራንሰፖርት ገንዘብ ለአገልገዩ ተቀናንሶ ወይንም ጭራሹኑ አለመድረስ ፣ “የመሰረታት” ቤ/ክ ገንዘብ በፐርሰንት ይከፈለኝ ያለ አገልጋይ ፣ ከአገር ውስጥና ከውጪ አገር የፈንድ ሬይዝ የሚያደርጉትን ገንዘብ በፐርሰንት የሚወስዱ፣ ገቢያቸው እጅግ በተጋነነ ሁኔታ ጣራ ነክቶ ሳለ በዚያው ቤ/ክ ከነቤተሰባቸው የሚራቡ አገልጋዮች እና ምዕመናን መኖር፣ የተጋነነ የደመወዝ ልዩነት 500 ብር እና 70 ሺህ ብር የምትከፍል ቤ/ክ፣ 90 ሺህ እና 200፣ 124 ሺህ እና 3000 ሚከፈልበት አገልግሎት (ሚኒስትሪ)፣ ከሚገባው በላይ ስለመስጠት የሚሰብኩና እና ስጡ ብሎ ለማስተማር የሚሸማቀቁ አገልጋዮች ፣ አገልግሎት ሲጠሩ ስንት ትከፍሉናላቹህ ብለው ክፍያ የሚደራደሩ ፣ ገንዘብ ያለ እቅድ ይወጣል   ሲተርፍ የማይመለስበት ሁኔታ ፣ ጊዜ በማጣት አስራት፣ ማባና ስጦታ ገቢ አንዲያደርጉ የተሰጣቸውን ገንዘብ በአግባቡ የማያደርሱ አገልጋዮች ፣ ፈትቶ ሲያገባ ከሚሰጠው ጠቀም ያለ ገንዘብ የተነሳ ዝም የተባለ ሐብታም ፣ የደለበ አስራት ስለሚከፍሉ ለባለጸጎች በጉባኤ የተለየ ስፍራ መስጠት፣ “እስታቴር ያለውን አሳ ማጥመድ” በሚል ብሂል ሃብታሞችን ማሳደድ. . . ይህ ሁሉ “የአዳዲሶቹ” አልፎ አልፎም የነባሮቹ ቤተክርስቲያናት ችግር አንደሆነ ይነገራል፡፡ ችግሩ ከምን ይመነጫል?

የአስተምህሮና የመዋቅር ችግር

አገልጋዮች ገንዘብን ባለመውደድ ነውረኛውን ረብ ሳይሹ መንጋውን ሊጎበኙና ሊያገልግሉ አንደሚገባ ቅዱስ ቃሉ ይናገራል፡፡ 1ኛ ጢሞ 6፡10 “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ስር ነው” አንደሚል በበርካታ ቤ/ክ የሚፈጠር ግጭት ሽፋኑ ሌላ ቢሆንም እውነተኛው ምክንያት ግን በገንዘብና በጥቅም መነሾነት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡: በሜክሲኮ አማኤል ሕብረት ቤ/ክ መጋቢነት የሚያገለግለው ኤርምያስ ይርጉ “ለአገልጋዮች ትልቁ ነገር ከገንዘብ ፍቅር መራቅ ነው” በማለት “በገንዘብ ያልታመነ አገልጋይ በሌላ ነገር መታመን እንደሚቸግረው” ይናገራል፡፡ አክሎም “የገንዘብ ፍቅር ከሐይማኖት አስቶ እራስን በስቃይ እስከመውጋት የሚያደርስ አንደሆነ” ቅዱስ ቃሉን ዋቢ ያደርጋል፡፡ የሕግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አቶ ጂማ ዲልቦም “አገልጋዮች ለሚያገለግሉት አምላክ ለሕዝቡና ለህሊናቸው ሲሉ ታማኝ መሆን ይገባቸዋል” ይላሉ፡፡ አለማውያን ባለስልጣናት እና የስራ ሐላፊዎች አንኳ የሐብታቸውን ምንጭና መጠን እያሳወቁ ባለበት በዚህ ወቅት አገልገዮች ከህዝቡ ያልተሰወረ የገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም ሊኖራቸው ይግባል፡፡ የህግ ባለሙያው አቶ ጂማ “ በህገ መንግስት በተደነገገው ያኃይማኖት ነጻነት መንግስት ቤተክርስቲያንን የሚያውቃት በህጋዊ ፈቃድ የምትንቀሳቀስ ተቋም አድርጎ ነው፡፡ ስለዚህ አመታዊ የስራና የፋይናንስ ሪፖርት የሚጠበቅ አንደመሆኑ የገባውና የወጣው ገንዘብ በአግባቡ በሕጋዊ ሰነዶች ተደግፈው ሊቀርቡ ይገባል” በማለት የገንዘብ ብክነትና ጉድለት ሲከሰት ገንዘብ ያጎደለው ግለሰብ በፍትሃ ብሄርና በወንጀል ሕጎች ሊጠየቅ የሚችልበት የህግ አግባብ መኖሩን ይናገራሉ፡፡ በአብዛኛው አዲስ የሚከፈቱ አብያተክርስቲየናት ላይ በርካቶች ጥያቄ ያነሳሉ “የከፋቾቹ አላማ ከአፍቅሮተ ነዋይና እና ከዕልቅና ጥማት ውጪ ቢሆን ለምን ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ሔደው አይሰሩም?” በማለት ይጠይቃሉ፡፡

ለገንዘብ ብክነት መነሾ የሚሆነው ሌላው ምክያት የመዋቅር ችግር ሲሆን ይህም በዘመድና በትውውቅ የሚደረግ የጠቅላላ ጉባኤና የቦርድ ስብስብ የገንዘብ ብክነትና የተጋነነ ክፍያ ሲፈጠር ለምን ብሎ ጠያቂ አንዳይኖር የሚያደርግ አሰራር ነው፡፡ ቤ/ክ ተቋማዊ ልትሆን የሥፈልጋል ሲባል በእቅድ የምትመራ ፣ የፋይናንስ ስርአቷም ግልጽ ሊሆን ይገባል ማለት ነው፡፡ “መንግስት ባስቀመጠው ሕግና ስርአት የተደራጀ ቤ/ክ በህጉ መሰረት አሰራሩን፣ መተዳደሪያ ደንቡን፣ የአገልጋዩን ስልጣንና ሐላፊነት፣ በግልጽ ማቀመጥ ይገባዋል ይህ ደግሞ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ከማስፈን አንጻር ድርሻው ጉልህ በመሆኑ ቼክ ኤንድ ባላንስ በመስፈን ግልጽነት አንዲሰፍር ያችላል” የሚሉት አቶ ጂማ ዲልቦ ናቸው፡፡

በርካታ ሰዎች በግላቸው ተነሳስተው ለአገልጋዮች ገንዘብ መስጠታቸውን በአዎንታዊም በአሉታዊም መልኩ የሚተረጉሙት ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንድ አገልጋዮች “አስራት የአገልጋይ ቀለብ አንጂ የቤ/ክ አስተዳደራዊ ወጪዎች ስራ ማስፈጸሚያ አይደለም” ሲሉ ይደመጣሉ ወንጌላዊ ደሉ ጸጋዬ ግን በዚህ አይስማማም “ቤተክርስቲያን አንደ ተቋም የአገልጋዮችና የሰራተኞን ደመወዝ ከመክፈል በተጨማሪ በርካታ አስተዳደራዊ ወጪዎች አሉባት ስለዚህ አንዚህን ሁሉ ግምት ውስጥ ማስገባት ነገንም በማሰብ ገንዘቧን ማስተዳደር አንጂ ሁሉም ለአገልጋይ ይሁን ማለት አንደማይቻል” ይናገራል፡፡

መስጠትን የተመለከተ ሁለት አይነት ጽንፎች በቤ/ክ አሉ፡፡ የመጀመሪው ምዕመኖች አንዲሰጡ በከፍተኛ ግፊት የሚሰብኩ በስብከታቸውም ምዕመናን እስኪሰላቹና “የት አንድረስ” አስኪሉ አብዝተው አንዲሰጡ የሚሰብኩና የሚያስተምሩ ከዚያም አልፎ የሚገፋፉ(የሚነዘንዙ) የመኖራቸውን ያክል በአንጻሩ ደግሞ በይሉኝታ ታስረው ስለ ገንዘብ ማስተማር ነውር መስሎ የሚታያቸው አገልጋዮች አሉ፡፡

አስተምህሮን በተመለከተ “ሚዛናዊ አስተምህሮ ሊኖር ይገባል” የሚለው ኤርምያስ ይርጉ (መጋቢ) ነው፡፡ ኤርምያስ አክሎም “ከገንዘብ ሌላ ስብከትና ትምህርት የሌለ አስኪመስል ድረስ መስጠት የአንዳንድ አገልጋዮች መታወቂያቸው ሆኗል” ይላል፡፡ መሪዎች የሚመሩት ምዕመኑን ብቻ ሳይሆን አገልጋዮንም አንደመሆኑ አገልጋዮች ለችግር ወይንም ለቅንጦት ህይወት ሲዳረጉና ከወንጌል ተቃራኒ ሕይወት ሲኖሩ ሀይ ባይ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በእጃቸው ያለውን ገንዘብ በአግባቡ ካላስተዳደሩ በእግዚአብሔርም፣ በህዝቡም፣ በህግም፣ በህሊናቸውም ተጠያቂዎች አንደሆኑ ሊያውቁ ይገባል፡፡ ወንጌላዊ ደሉ ይህንን አስመልክቶ ሲናር “አንዳንድ መጋቢዎች የሚያዋቅሩት አመራር (ጠቅላላ ጉባኤና ቦርድ) የግል ተውውቅ ያላቸውና ስህተት ሲፈጠር ለመጠየቅ አቅም የሌላቸውን ሰዎች በመሆኑ መጋቢው አንደፈለገው አንዲሆን በር ይከፍታል ይላል” ይህ ማለት ግን አገልጋዮች የመሪዎችና የምዕመን መጋቢያን አንጂ ደጅ ጠኚ አይደሉም፤ ይህንን እውነት ያልተረዱ “አገልጋዮች” ግን የሐብታም ደጅ ጠኚ ሲሆኑ ይታያል፡፡ አንደ ምሳሌ ለመጥቀስም በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ቤ/ክ በአንዱ የሚያገለግሉ አገልጋዮች የቤተክርስቲያኒቱን ባለጸጎችን ገንዘብ በመጠየቅ ያሰለቹ ከመሆናው የተነሳ ባለጸጎቹ “ሶፍት አንኳ ለማውጣት እጃችንን ወደ ኪሳችን ለመክተት ተሳቀቅን” እስኪሉ ድረስ አገልጋዮቹ ገንዘብ ወዳድ ሆነዋል እየተባሉ ይታማሉ፡፡ የሚያገለግሉት ሕዝብ በከፋ ድህነት ሲማቅቅ የአንዳንድ መጋቢያን ደመወዝ ከአገር ፕሬዘዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ደሞዝ የበለጠበት ሁኔታ አንዳለ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አብዛኞቹ አገልጋዮች የሚያገለግሉት ማንን እንደሆነ አንኳ ግልጽ አይደለም፡፡ አላማቸው መክበር ከሆነ የስራ እድል በተመቻቸበት ሁኔታ ወጣ ብለው ቢነግዱና ድርጅት ቢከፍቱ እጅግ ስኬታማ አንደሚሆኑ አያጠራርጥርም፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን አይነት ትውልድ እየቀረጹና ለሌሎች ምሳሌነታቸው ምን አንደሆነ ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ ለትውልድ የሚያወርሱት ፍቅርን፣ ታማኝነትንና ስለ ወንጌል መከራ መቀበልን ነው? ወይንስ በወንጌል መክበርን የሚለው ጥያቄ አግባብነት ይኖረዋል፡፡

የቤ/ክ ወጪና ገቢ ሕጋዊ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ሳይንስን የተከተለ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ማለት የሚገባው በህጋዊ ደረሰኝ፣ ለሚወጣውም ሕጋዊ ደረሰኝ ሊቀርብ ይገባል፡፡ አገልጋይ ተጋብዞ ካገለገለ በህዋላ የሚሰጠው የትራንስፖርት ገንዘብ በህጋዊ መንገድ የሚወጣ አለመሆኑ ሌላው ለሙስና ያጋልጣ ተብሎ የሚታማ አሰራር ነው፡፡ በአንድ ቤ/ክ አገልግሎ በፖስታ የተሰጠው ገንዘብ በቤ/ክርስቲኒቱ ከተመደበው አንድ ሶስተኛ በታች ብቻ አንደነበር የሚናገረው ስሙ እዳይቀስ ፈለገ ወንድም ከቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮችጋ ባደረገው ውይይትም ገንዘቡ ጎድሎ የተሰጠው መሆኑን አንደተረዳ ይናገራል፡፡ ከፖስታ ገንዘብ ከመቀነስ በከፋ ጭራሹኑ ባዶ ፖስታ የተሰጣቸው አገልጋዮች እንዳሉም ይወራል፡፡ በዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ ጂማ ዲልቦ “አንዲህ አይት ሰው በወንጀል ሕግ መሰረት በማታለል ወይንም በእምነት ማጉደል ሊጠየቅ አንደሚችል” ይናገራሉ፡፡ የተጠቀሰውን አይነት ችግር ለመከላከል በአንዳንድ ቤተክርስቲያናት ከጉባኤ በኋላ መሪዎች ያገለገለውን ሰው ቢሮ ጠርተው ከጸልዩና ከባረኩ በኋላ የትራንስፖርት ገንዘቡ በግልጽ ተሰጥቶት በተዘጋጀው ሰነድ ላይ አንዲፈርም ይደረጋል፡፡ ኤርምያ ይርጉ (መጋቢ) ግን በዚህ አይስማማም “ቤ/ክ ተቋማዊ ብትሆንም የእምነት ስፍራ አንደመሆኗ መጠን ሁሉም ነገር በህግ ይመራ ማለት አስቸጋሪ” ሊሆን አንደሚችል ያሰምርበታል አንደ ምሳሌም “አንዳንድ በዕድሜና በልምድ ትልቅ የሆኑ ሰዎን ቢሮ ጠርቶ እዚህ ላይ ፈርሙና ገንዘብ ውሰዱ” ማለት ከሞራል አንጸር አንደሚከብድ ይናገራለ፡፡ አክሎም “ገንዘብ የሚያጎድሉ አገልጋዮች ካሉ ሌብነታቸው አንደ ይሁዳ አስኪገልጣቸው መተው አንጂ በስንቱ ተቆጣጥሮ ይዘለቃል?” በማለት ይጠይቃል፡፡ አስተያየቱንም ሲቀጥል በአፍቅሮተ ነዋይ የተጠመዱ አገልጋዮች መጨረሻቸው አንደማያምርና መጨረሻቸው ውድቀት አንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህ ሁሉ ሲባል ግን ነገር ሁሉ ወደ አንድ አቅጣጫ መጉረፍ የለበትም፡፡ በገንዘብ ጉዳይ ስማቸው በአሉታዊ የሚነሱ የመኖራቸውን ያክል ለጠራቸው ጌታና ለሚያገለግሉት ሕዝብ እጅጉን ታማኝ የሆኑ አገልጋዮች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ እነዚህ አገልጋዮች ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ ልጆቻቸውን የሚመግቡት አጥተው የሚራቡ ሲሆኑ በእውነትና በታማኝት ያገለገሉት ጌታ ዋጋቸውን በዚህ ምድር ደግሞም በዘላለም ሕይወት “አንተ ልባም ታማኝ ጌታ ወደ ጌታህ በደስታ ግባ” ብሎ አንደሚከፍላቸው ቅዱስ ቃሉ ይናገራል፡፡ “የአገልጋይ ክፍያ ምን ያክል መሆን አለበት የሚለው አከራካሪ ጉዳይ መሆን የለበትም ቤተክርስቲያኒቱ እንደ አቅሟና አንደ ሁኔታው ልትከፍል ይገባል” የሚለው ደሉ ጸጋዬ ነው፡፡ አንደ መንግስት መዋቅር ይህንን ያክል መሆን አለበት ማለት አንደሚከብድ የአገልጋዮች ክፍያ ደሞዝ አንደ አካባቢው ሁኔታ ፣ አንደ ቤተክርስቲኒቱ ገቢ እና አንደ አገልጋዩ ሐላፊነት አንዲሁም የአገልግሎት ዘመን ቆይታ ሊሆን ይገባል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “እጥፍ ክብር ይገባቸዋል የተባሉት ሌሎች ሳይሆኑ አገልጋዮች ናቸው” የሚለው መጋቢ ኤርምያስ ነው፡፡ “አገልጋዮችን ቤ/ክ ከምታከብርባቸው መንገዶች አንዱ ለኑሯቸው የሚገባውን በማድረግ የሚባቸውንም በመክፈል ነው” ይላል ኤርምያስ፡፡ በእርግጥ እነርሱ ስለ ነፍሳችን ይተጋሉና ቤትከርስቲያን ስለ እነርሱ ልትተጋ ይገባል፡፡ ወንጌላዊ ደሉም “አገልጋዮች ተቸግረው የሰው እጅ አንስኪያዩና ለልመና ወይንም ለማጭበርበር አስኪጋለጡ መድረስ ለባቸውም” ይላል፡፡ ይህንን ሁኔታም ለማስወገድ በኩሉን አድርሻ ለመወጣት “ቤተር ላይፍ ሚኒስትሪ” የተሰኘ ተቋም መስርቶ ለችግር የተጋለጡ አገልጋዮችንና ቤተሰባቸውን በገንዘብ ለመደገፍ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እያገለገለ ይገኛል፡፡

አገልጋዮች የሚያገለግሉትን ሕዝብ ኑሮ፣ ችግር፣ ሀዘን፣ ደስታ ሊካፈሉ ይገባል አንጂ ከሕዘቡ ኑሮ እጅግ ሩቅ ሆነው በሕዝቡ ላይ የሚሰለጥኑ ሊሆኑ አይገባም የሚለው ያስማማል፡፡

ቅጥ ያጣ ቅንጦት

አገልገዮች አንደማንኛውም ሰው ፍላጎት ያላቸው አንጂ ልዩ ፍጥረት ተደርገው መታየት አይገባቸውም፡፡ ይህ አሉታዊ አስተሳሰብ ለበርካታ አመታት አያሌዎችን ከነቤተሰባቸው የጉስቁልና ቋት አድርጎ ከርሟል፡፡ የበርካታ አገልጋዮች ቤት የሰቆቃና የመከራ ቤት፣ ልጀቻቸውንም ደሀ አደጎች ያደረገ አመለካከት መሰበር አለበት፡፡ በተቃራኒው ከጥቂት አመታት በፊት ምንም ያልነበራቸው አገልጋዮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊየነር ሲሆኑ እየታየ ቤተክርስቲያን መክፈት እጅግ አትራፊና በአቋራጭ መክበሪያ እንደሆነ በመታሰብ “ሐይማታዊ ስራ” ፈጠራ እየተባለ ነው፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ሽንኩርትና በቆሎ ይዘው ወደቤታቸው በሚሄዱበት ሳምሶናይት ገንአዘብ ይዘው የሚሄዱ አገልጋዮች፣ ከጥቂት አመታት በፊት ቤተሰባቸውን የሚመግቡት አንኳ ያልነበራቸው ዛሬ በግል አካውንታቸው በርካታ ሚሊየን ብር አንዳላቸው ይነገራል፡፡ ከሚያገለግሉት ሕዝብ መካከል በቀን አንዴ አንኳ የሚበላው አጥቶ ሳለ እነርሱ ግን በሚሊዮን ብሮች የተገዙ መኪኖች ባለቤት ሆነዋል፡፡ የአንዲህ አይነት አገልጋዮች ሕይወትና አገልግሎት ከቃሉ ርቆ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆኖ ከቃሉ በተቃራኒ በሚያገለግሉት ሕዝብ ላይ እየሰለጠኑ ነው፡፡ በእርግጥ አገልጋዮች “ከሚያገለግሉት መሰዊያ ተጠቃሚ” ሊሆኑ አንደሚገባ ቃሉ ሲናገር “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” ይላል፡፡ ይህ ማለት ግን ቅጠል ሽጦ አስራት፣መባና ስጦታ የሚያመጣው ህዝብ በከፋ ድህነት ሲማቅቅ አገልጋዮች ከቤተሰባቸውጋ ከከተማ ወጣ ብለው የእረፍት ጊዜያቸውን ስለሚያሳልፉበት የቅንጦት መዝናኛ፣ ስለሚሰሩት ቪላ፣ ስለገዟቸው ሚኪኖች፣ በቀን ውስጥ ለበርካታ ጊዜ ስሚቀያይሩት ውድ ልብሶች የሚጨነቁ ከሆነ የሚያገለግሉት ማንን ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ “አገልገዮች ከሚያገለግሉት ሕዝብ የራቀ ሕይወት ሊኖራቸው አይገባም” ሚለው ኤርምያስ ይርጉ (መጋቢ) “ሐዋርያት ያላቸውንና ሕዝቡ ያመጣውን ለእያንዳንዱ አንደሚያስፈልገው መጠን ያካፍሉ አንደነበር” ቃሉንና የቤተክርስቲያንን ታሪክ ዋቢ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ይላል መጋቢው “አገልጋይ ቃሉን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱንም ገንዘቡንም ማካፈል ይገባዋል” ይላል፡፡ አገልጋዮች ለተጠሩለት ወንጌል በመጠን እየኖሩ ሊያገለግሉ ይገባል፡፡ መጽኸፍ ቅዱስ የሚለው “በመጠን ኑሩ ንቁም ባላጋራችሁ ዲያቢሊስ የሚውጠውን ፈልጎ አንደሚያገሳ አንበዛ ዙሪያችሁን ይዞራል” ነው፡፡ የኑሮና የገንዘብ ጽንፎቹ ሃይ ባይ እስካልመጣ ድረስ የሚቀጥሉ ይመስላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ይሁዳ ከደቀ መዛሙርትአንዱ ሆኖ ይኖራል፡፡

“ከመደነጋገር መነጋገር”

መስከረም አበባ አበረ፣ “ከመደነጋገር መነጋገር” በሚል ርእስ ለንባብ በበቃውና ለወቅታዊው የአገራችን የትርምስ ገጽታ ሁነኛ ምክር አለው በተባለው መጽሐፍ ላይ ያቀረቡትን የአንባቢ ዕይታ እንደሚከተለው አቅርበዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ስለ ዘፈን

ዘሪቱ ከበደ በሕንጸት ድረ ገጽ ላይ ለንባብ ባቀረበችው በዚህ ጽሑፍ፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ እስከ አሁን በዘለቀው የዘፈን ጕዳይ ላይ ብያኔዋን ትሰጣለች። “ይህን ጕዳይ ሳነሣ ለዘፈን ጥብቅና ልቈም ፈልጌ አይደለም። ይሁን እንጂ፣ እውነትን መናገርም ሆነ መነጋገር አስፈላጊ እንደ ሆነ ደግሞ አምናለሁ።” የምትለው ዘሪቱ፣ ወደ ጌታ የመጣችበትን ሂደትና የተለማመደችውን መንፈሳዊ ሕይወት እያስቃኘች፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ በርእሰ ጕዳዩ ላይ ሊኖረው ስለሚገባ ግንዛቤ ዐሳቧን ታካፍላለች፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው ያለቻቸው ማስረጃዎቿንም ታቀርባለች። በዚህ ብቻ አታበቃም፤ በሙዚቃ ጥበብ ውስጥ መዝለቅ የሚሹ ክርስቲያን ወገኖች ሊኖራቸው ስለሚገባ መንፈሳዊ አመለካከትና መውሰድ ስለሚጠበቅባቸው ጥንቃቄ የምክር ቃል ታካፍላለች።

ተጨማሪ ያንብቡ

ዊክሊፍ:- የታላቁ ለውጥ አጥቢያ ኮከብ

የፕሮቴስታንት ተሓድሶ በሚታወስበት በዚህ ሰሞን፣ ለማርቲን ሉተርና ለሌሎቹ ተሓድሷውያን ነገረ መለኮታዊ መደላድል አስቀድሞ ሠርቶ አልፏል ስለሚባልለት ጆን ዊክሊፍ እንድናስታውስ፣ ፍቅረየሱስ ሁንዴሳ ይህን ዝክር እንደሚከተለው ያስነብበናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.