በብርታቱ ኀያልነት ያስገበራቸውን አገራት በግሪክ ፍልስፍናና ባህል ማጥመቅን እንደ ዐቢይ ተግባሩ አድርጎ ይዞታል፡፡ እናም የመከከለኛው ምሥራቅ፣ የአውሮፓና የሰሜን አፍሪካ ግዛቶችን በእጁ ባስወደቀ ጊዜ በጽርዕ ባህልና ፍልስፍና ከመንከር ወደ ኋላ አላለም፡፡ ጦረኛው ልዑል ፊቱን ወደ ሰሜን አፍሪካ ባቀና ጊዜ የሜዲትራኒያንን ባህር ተግና የተዘረጋችው ግዛትም ብርቱ ክንዱን ልትቋቋመው አልተቻላትም፤ ፈጥና በክርኑ ሥር ወደቀች፣ እናም ይህቺን ጠረፋማ የግብጽ ግዛት ለስሙ መጠሪያና ለክብሩ መታያ ትሆን ዘንድ እስክንድርያ ሲል ሰየማት፡፡ ታላቁ ጦረኛና ገናናው የግሪክ ንጉሥ እስክንድር፡፡
እስክንድርያ የሄለናዊያን ባህልና ፍልስፍና ማዕከል፣ የግሪክና የሮማዊያን ጠበብት መናኸርያ፣ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት አለኝታ፣ የስመ ጥር ጳጳሳትና የቤተ ክርስቲያን ምሁራን መፍለቂያ፡፡
እስክንድርያ በሮም ግዛት ከሚገኙ ከተሞች በተሻለ ሁኔታ የነጻነት አየር የነፈሰባትና ልዩ ልዩ አስተሳሰቦችም ያለገደብ የተንሸራሸሩባት በመሆንዋ የምሥራቃውያን ፈላስፎች፣ የግሪክና የሮም አውጠንጣኞች እንዲሁም የዐዲስ አፍላጦናዊያን መፍለቂያ ለመሆን በቅታለች፡፡ በዚያም አይሁዳዊው ፊሎ ሥርወ እምነቱን በግሪካውያን ፍልስፍናና አስተሳሰብ ቀንብቦባታል፤ ግኖስቲሲዝም ወደ ምልዐቱ ተሸጋግሮበታል፡፡ ክርስቲያን አሳቢዎችም የቀደምት ግሪካዊያንን ነገረ ፍልስፍና አዋዝተው እምነትን ከአመክንዮ አናበውበታል፡፡
ከሁለተኛው ምዕተ ዓመት መባቻ አንሥቶ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስማቸው ገናን ከነበረው የነገረ መለኮት ተቋማት መካከል አንጋፋው የትርጓሜ ማዕከል በዚህች ከተማ ይገኛል፡፡ ማዕከሉ ነገረ መለኮትን ከአፍላጦን ፍልስፍና እያዛነቀ የተነተነን ካህን ያፈራ ሲሆን፣ ካህኑም ክርስትናን ከግሪካዊያኑ ፈላስፎች ይልቁን ከአፍላጦን ዕሳቤ ከማቃየዱ የተነሣ ስሙ በተነሣበት ዘመናት ሁሉ ውዳሴና ነቀፌታን፣ ተቃውሞና ድጋፍን፣ ክብረትና ውርደትን ተቀብሏል፡፡ የነገረ መለኮት ተቋሙ ርእሰ መምህር፣ ታላቅ ምሁርና ሥልጣነ ክህነትን ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ዲሜጥሮስ የተቀበለ ካህን፤ ቀሌምንጦስ፤ የባዕድ ልሳናት የአሌክሳንድርያው ክሌመንት አሰኝተው እንዲጠሩት፡፡
እቅጫዊ የሆነ ትውልደ ዘመኑና፣ ትውልደ ሥፍራው አይታወቅም፤ ያም ሁኖ አንዳንድ የታሪክ መጻሕፍት አቴንስን የውልደቱ ስፍራ ያደርጉታል፡፡ ከኢ-አማንያን ቤተ ሰብ መወለዱ፣ በሄለናዊያን ባህልና አስተሳሰብ ውስጥ ማለፉ ግን ክርክር የለበትም፡፡ ልቡ ለፍልስፍና የቃተተው ቀሌምንጦስ በግሪክና በሮም የአስተሳሰብ ዓለም ውስጥ መንፈሱ መጥቆ የሄደና በልዩ ልዩ የፍልስፍና ፈለጎች ውስጥ የቀዘፈ ቢሆንም እንደ ግሪኩ ተወላጅ አፍላጦን ልቡንና ልቦናውን የማረከ ፈላስፋ ግን አልነበረም፡፡
ልቦናው በእውቀት ጥማት የተንተከተከው ቀሌምንጦስ፣ በወቅቱ የሮም ምሥራቃዊ ግዛት ወደነበረችው እስክንድርያ በማቅናት የሐዋርያቱን ፈለገ እምነት ለማወቅና ለመረዳት ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡ በመሥመሩ ላይ የእስክንድርያውን መምህር ፓንዴኖስን ባገኘ ጊዜ ግን ልብ አልቀረለትም፤ ለፓንዴኖስ ነገረ እውቀት እጅ ሰጠና በመዲናይቱ ከተመ፡፡ በነገረ መለኮት ትምህርት እውቀትም ሽቅብ ይወጣ ጀመር፡፡
የአዲስ ኪዳን ዕውቀቱን ካበለጸገ በኋላ ግሪካዊው ፍልስፍና፣ የወንጌልን እውነት ለማፍጠን እንደ ሁነኛ መሣሪያ ሊያገለግል እንደሚችል ማውጠንጠን ጀመረ፡፡ የመልካም ኩነቶች መገኛ የሆነው እግዚአብሔርም ለፍልስፍና አቅጣጫ እንደተለመለት አስረዳ፡፡ እርሱ እንዳጤነው፣ የእስክንድርያ ከተማ የፈላስፎች መናኸርያ እንደመሆንዋ የመስቀሉን ሥራ ወደ እነዚህ ተጠባቢያን ለማድረስ ከፍልስፍና የተሻለ መሥመር አልታየውም፡፡
በተለያዩ ዘመናት፣ አጥብቆ በዘለቀበት በዚህ አስተሳሰብ አማካይነት ወንጌልን ወደ ሰርጥ ገፍትሯል የሚሉ አባቶች የተነሡ ቢሆንም፣ የተከተለው መሥመር ግን አያሌ ፈላስፎችን ወደ ክርስቶስ በመምራትና ለክርስትና እምነት እንዲያድሩ በማድረግ ከፍ ያለውን አገልግሎት ማበርከቱን ሊያስተባብል የቻለ ግን አልነበረም፡፡
በእስክንድርያው የነገረ መለኮት ተቋም የመሠረት መጣያ ዘመንም ሆነ ከዚያ መለስ ባለው ጊዜ ባለጉዳያችን ቀሌምንጦስና ደቀ መዝሙሩ አርጌኔስ ስማቸው ከፍ ብሎ መጮኹን መካድ አይቻልም፡፡ በተለይም የክርስትናን እምነት ከማወቁ ቀደም ብሎ የስቶይኮች ፈላስፋ እንደ ነበረ የሚነገርለት የቀሌምንጦስ አስተማሪና ርእሰ መምህር ፓንዴኖስ ሁለንተናዊ ቀልቡ በባለጉዳያችን ከመያዙ የተነሣ፣ “ቀለም ዘለቅ” በማለት ሲያወድሰውና ሲያሞካሸው እንደ ነበረ ታሪካዊ ሠነዶች ይነግሩናል፡፡
ኋላ ላይ ቀሌምንጦስ ፓንዴኖስን ተክቶ የትምህርት ቤቱ የበላይ ጠባቂና ርእሰ መምህር በሆነ ጊዜ ʻማዕከሉን በአፍላጦን ዕሳቤ አጥምቋልʼ የሚሉ የታሪክ ምንጮች አሉ፡፡ እንደ እርሱ አመለካከት፣ ፍልስፍና ዐቢይ የሆነ የሳይንስ ጥበብ ሲሆን፣ ሙዚቃ፣ ጂኦሜትሪ፣ ሰዋ ሰውና የአነጋገር ክኅሎት ደግሞ ወደ ፍልስፍና የሚያደርሱ ሁነኛ መንገዶች ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሣት ነገረ መለኮትንም ለመገንዘብ ፍልስፍናን ማወቅ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ይመክራል፡፡ እርግጥ የማናቸውም እውቀት ቁንጮ ፍልስፍና እንደ ሆነ ቢያስገነዝብም ከቶም የነገረ መለኮት ራስ ሊሆን እንደማይችል ግን በተደጋጋሚ ከማውሳት አልተገታም፡፡
በተለያዩ ጽሑፎቹ የግሪካዊያኑን ፍልስፍና አስመልክቶ ሲጽፍ፣ ቀደም ባለው ዘመን በመላው ዓለም የተበተኑ አይሁድ በቶራ አማካይነት የጠለቀ እውቀት ላይ ከመድረሳቸው የተነሣ ቀደምት ግሪካዊያን ፈላስፎች ፍልስፍናቸውን ከዚህ ብሔረ ኦሪት አናበው ግሪካዊ መደላደል ፈጠሩለት እንጂ የተለየና አዲስ አስተሳሰብ ይዘው አልመጡም ይለናል፡፡ እንደ እርሱ አባባል፣ አፍላጦን ከሙሴ የጠለቀ እውቀት ባለቤት አይደለም፡፡
እንዲህ ዐይነቱ የቀሌምንጦስ አካሄድ የተዛበጠ የመሰላቸው አበው፣ ሰውዬው ከሙሴ ይልቅ ለአፍላጦን ያደረ መሆኑን ከራሱ ድርሳን በመጥቀስ ይሞግቱታል፡፡ እንዲያም ይበሉ እንጂ የሄደበትን የነገረ መለኮት አጠቃላይ ይዘት ከእርሱ አንጻር ስናጤነው ትምህርተ ክርስትናን ፈር በማስያዝ በኩል ያከናወነውን ዐቢይ ተግባር ሜዳ ላይ የምንበትነው አይደለም፡፡
በመሠረቱ እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ አበው ሥላሴን አስመልክቶ የሚሰነዝሩት አስተያየትና ትንታኔ ከኋለኞቹ ጉባዔያት አስተሳሰቦች ጋር አልፎ አልፎ ይተላለፉ እንደ ነበር የሚካድ አይደለም፡፡ ከዚያ ወዲህ በቤተ ክርስቲያን ገጽ ላይ ብቅ ያለና የኋለኞቹን ታዋቂ ጉበዔያት ያጠኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መለስ ብለው የቀሌምንጦስን አካሄድ መጎንተላቸው አልቀረም፡፡ እርግጥ ወልድን አካላዊ አስብሎ የተረጎመበትን መሥመር ʻይበልʼ እያሉ ቢያወድሱም፣ ዝርው ቃል አሰኝቶ የገለጸበትን አንቀጽ ግን አብጠልጥለውታል፡፡ ያም ብቻ አይደለም፤ አለማወቅ የክፋት ምንጭ እንደ ሆነ በመጥቀስ የተናገረበትን ክፍል ከአርስጣጣሊስ ዕሳቤ ጋር በማገናኘት ኢ – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያሰኙትም አልጠፉም፡፡
አሳቢው ቀሌምንጦስ ይሁነኝ ብሎ በመረጠው መንገድ አቴንስን ከኢየሩሳሌም ለማወዳጀት ወይም አቴንስን የኢየሩሳሌም አገልጋይ ለማድረግ ብርቱ ምርምር አድርጓል፡፡ በተለይ የክርስትና ሥርወ ትምህርት ከግሪኩ ፍልስፍና የሚጣረስበትን መሥመር ፈር ለማስያዝ አያሌ ትንታኔዎችን አቅርቧል፡፡ በልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮችም ላይ በርካታ መጻሕፍትን ጽፏል፡፡ በአንጻሩ በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን አዕማዳት የነበሩት ጳጳሳት አትናቴዎስና ቄርሎስ፣ አቴንስና ኢየሩሳሌም ግጣማቸውም ሆነ ጠበላቸው ለየቅል መሆኑን በመግለጥ፣ በእስክንድርያ የትርጓሜ ትምህርት ቤት የሠረገውን ፍልስፍና ከታበተበት ጠፍር ለመለየት ብርቱ ትግል ማድረጋቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡
በሁለተኛ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ሮምን ይገዛ የነበረው ቄሳር ሳዊሮስ (ስቮረስ) በንጉሣዊ ግዛቱ ባሉ ክርስቲያኖች ላይ መከራን ባዘነበ ጊዜ ቀሌምንጦስ እስክንድርያን ለቆ በመጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም ኋላም ወደ አንፆኪያ ተሰደደ፡፡ ስደት ባደረባቸው ሁለት ከተሞችም፣ “የተባረከ አገልጋይ” የሚል ስያሜ ሲያገኝ፣ በተለይ ደግሞ የኢየሩሳሌሙ ጳጳስ፣ “ስለ ቤተ ክርስቲያን መታነጽ የደከመና መጽናናት እንዲመጣለት አብዝቶ የተጋ” ሲሉ አወድሰውታል፡፡ በ210 ዓ.ም. በአንፆኪያ ያረፈው ቀሌምንጦስን አፈሩ ይቅለለው፡፡
Add comment