[the_ad_group id=”107″]

“ኑ፡- ʻአምላክʼን እንፍጠር”

“ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ያለው እግዚአብሔር ነው። የዚህ ፍጥረት ዋነኛ ተግባር ለፈጣሪው ሙሉ ዕውቅና መስጠት፣ በእርሱ እና ለእርሱ እንዲኖር፣ በዘለዓለምም መንፈስ በእግዚአብሔር ደስ እንዲለው ነው። ይኸው ፍጡር ሳት ካለው ደግሞ የማያደርገው የለም፤ በአምላኩ ላይ ማመፅ ይችላል። ይህንንም ደግሞ ደጋግሞ አድርጎታል። ተስፋውንም አምላክ ባልሆኑ አማልክት ላይ በማድረግም የመሳቱን ልክ አሳይቷል። ባስ ሲልበትም ራሱ በገዛ እጁ የቀረጸውን፣ አንደቧሎ እና ጠፍጥፎ የሠራውን ምስልም ʻአምላኬʼ ይለዋል፤ ድሮም ዘንድሮም። የሚከፋው ግን፣ ውሉን ለመለየት ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ የሚሆነው እውነተኛውንና ራሱን በቅዱስ ቃሉ የገለጠውን አምላክ አስታክከው ሰዎች ለራሳቸው የሚፈጥሩት “አምላክ” ጉዳይ ነው።
የመጣጥፌ ዋናው ዓላማ ከፈጣሪያችን ድንጋጌ ውጪ የሆነና የሰዎች አእምሮ አበጃጅቶ ከሠራው፣ ከሚሰበክለትም “አምላክ” መንፈሳችን እንዲርቅ፣ ልባችንንም ለእውነተኛው አምላክ ዕለት ዕለት እንድናቀና ነው። ትኩረቴም የሚሆነው ራሳቸውን ለጌታ ኢየሱስ ከሰጡ ከወንጌላውያን ክርስቲያኖች መካከል ሊወገድ ስለሚገባውና በፍጡራን ከተፈጠረ “አምላክ” አስተዋዋቂ እና አደላዳይ ትምህርትና አመለካከት ላይ ነው።

የፍጡራኑ “አምላክ” አፈጣጠርም እንዲህ ነበር

ሰዎች ቅዱስ ቃሉን አስታክከው የሚፈጥሩት “አምላክ” አለ፤ ነበርም። የዚህ ዐይነት “አምላክ” አፈጣጠር በዋናነት ፍጥረት (ሰው) እግዚአብሔርን በራሱ (በሰው) መንገድ እንዲጓዝ ሲጎትተው፣ እየሄደለትም ያለ ሲመስለው፣ ʻየእርሱ ቃል ነውʼ ብሎ ያሻውን እና በልቡ ያለውን “በአምላኩ” አንደበት ላይ ሲያስቀምጠው መልሶም “ከእርሱ ቃል” የሰማ ሲመስለው፣ ለዘመኑ እና ባለበት ሁኔታ እግዚአብሔርን ለምኞቱ እና ለምቾቱ ሲያበጃጀው (customize ሲያደርገው) ያኔ ነው አምላክ ያልሆነው “አምላክ” ተፈጠረ የምንለው፤ ይኼኔ ፍጡራኑ ሰዎች የአምላካቸው ፈጣሪ ይሆናሉ። ይህም “አምላክ” በመልኩ እና በምሳሌውም ቁጭ የፍጡራኑን የአእምሮ እና የልብ ፍላጎት ይመስላል፤ የፈጠሩትንም ሰዎች ቃል ያትማል፣ ያጸድቃል።
ፍጡራን “ፈጣሪያቸውን” ሲፈጥሩ፣ ሲሰግዱለትም ዓለም ደጋግማ ማየቱን የጠገበች አትመስልም። ሕዝቡም ደግሞ አሁንም ሆነ ድሮ ለጠቢባኑ “ልንል የምንፈልገውን የሚልልንን፣ ልናደርግ የከጀልነውን የሚፈጽምልንን ፍጠሩልን” ይላል። እነርሱም ከቃሉ ንባብ በስሕተት መንገድ ተጉዘውም ይሁን፣ ከየዘመናት ልምድ እና ባህል ጋር አዳቅለው ወይም ከእርኩስ መንፈስ ግፊትም ይሁን ከልባቸው ክፋት፣ አለያም ከእነዚህ ሁሉ ድምር ምክንያት ይሁን፣ ብቻ ግን ከክርስቶስ ጋር የማይተዋወቅ “ሌላ ክርስቶስ” ፈጠር፣ ፈጠርጠር አድርገው ʻእነሆ!ʼ ይሉታል።

እንደ ምሳሌ ይሆነን ዘንድ የሆነውን እንመልከት። ለአንዳንድ የላቲን አሜሪካ ካቶሊኮች የባህላዊ ሃይማኖታቸው ዋነኛ ኀይል እና አጋዥ ʻኢየሱስʼ ነው ብለው አመኑ። በጭሳ ጭስ በሚታፈነው አምልኳቸው ውስጥ ተገኝቶ ያንዘፈዝፋቸዋል፣ ያስጓራቸዋል፣ ትንቢት ያናግራቸዋል፣ ፈውስን ይሰጣቸዋል። ʻይኼ ነገር እንዴት ነው?ʼ ብሎ ለሚጠይቃቸው መልሳቸው ʻሌላ አምላክ እያመለክን ነውʼ የሚል እንደማይሆን ልብ በሉ። ሲጀምሩም ሲያሳርጉም የመጽሐፍ ቅዱሱን የኢየሱስን ስም ጠርተው ነው፤ የማርያምን ልጅ ዋቢ አድርገው ነው። ʻነህʼ አሉት፤ በሚወዱትና በሚፈልጉት መንገድ “ሆኖ” አገኙት። ፈጠሩት።

ደቡብ ኮሪያ ስትሄዱ የአንዳንድ ሰው ክርስትና ከሻማኒዝም (Shamanism) ጋር ተደባልቆ ላለመቅረቡ ርግጠኛ መሆን ቀላል አይደለም።

ጥንታዊያን አክሱማውያን ትተውልን ካለፉት ቅርሶች አንዱ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ናቸው። እንደ ታሪክ ማጣቀሻም፣ እንደ መረጃም የመጀመሪያው ከ“ጣዖት” አምልኮ ወደ ክርስትና የመጣው ንጉሥ ስሙ ኢዛና መሆኑን ያስረግጡልናል። ቀድሞ ማኅረም የሚባል አምላክ ያመልክ ነበር። ይህን አምላኩን ሲያወድስ “ለጦርነት የማይሸነፍ” (invincible) ይለዋል። ኋላ ላይ ክርስትናን ተቀበለ። ከዚያም በጽሑፉ ውስጥ ከአንዳንድ ለውጦች ጋር ኢየሱስ የማኅረምን ቦታ ተክቷል። አምላኩ ረዳውና ጦርነት አደረገ፣ አሸነፈም። ስለዚህም “ኢየሱስ በጦርነት የማይሸነፍ” (invincible) እንደ ሆነ አመነ፣ ሆነለትም። ጦሩ ሲገድል፣ ምርኮውን ሲዘርፍ፣ ጭብጥ እርግጥ አድርጎ ሲገዛ “እሱ” እየረዳው ነበር፤ ቢያንስ እንደዚያ አስቧል። “ኢየሱስ እዚያ ጦርነት ውስጥ ነበር ወይ?” ብሎ መጠየቅ ሌላ ጥያቄ ነው። ይሁን እንጂ ንጉሥ ኢዛና ʻነበርʼ ብሏልና “ነበር”።

ሌላውም ከወደ ዐረቢያ ስለ ኢየሱስ “እውነቱን” ተናገረ ወይም “ገብርኤል” ተገልጦ ነገረው። መልአኩም አለው፡ – ʻኢየሱስ ፍጡር ነው!ʼ። ወዲያውኑ የእግዚአብሔር ልጅ፣ ሰው አምላክ የሆነው ጌታ ኢየሱስ፣ የሁሉ ፈጣሪና አስገኚ የሆነው እርሱ ፍጡር ነቢይ “ሆነ”። የመጽሐፍ ቅዱሱን ኢየሱስን ሳያማክሩት በቅጽበት ፍጡር ኢየሱስ “ተፈጠረ”። ዓለም ብዙ ሌላ ዐይነት ሐሳባዊ ፈጠራ ያስገኘውን “ኢየሱስን” አይታለች። እነዚህ ፈጣሪዎች የሚሥሉትና የሚቀቡት፣ የሚሰብኩት እና/ወይም የሚሰግዱለት እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ይሁን አይሁን ግድ የሚሰጣቸውም አይመስልም። ሲያሻቸው እንዲህ፣ ሲያሻቸው ደግሞ እንዲያ ያደርጉታል።

አሜሪካ፤ የፈጣሪነት ቁንጮ

ከሁሉም ከሁሉም ግን ሰሜን አሜሪካ በ“አምላክ” ፈጠራ ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይዛለች። ቀደም ባሉት ዘመናት “የሞርሞኖች ኢየሱስ”ን ብቅ አደረገች። እርሱም ተከታዮች አገኘ። ይኸው በየሁሉም ክፍላተ አህጉር ያሉት አማኞቹ በየብስም በአየርም ለሌሎች ሊያስተዋውቁት ነጭ ሸሚዝ ታጥቀው ጎንበስ ቀና ይላሉ። እሱም ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ የሚወዱለትን “የሞርሞን መጽሐፍ ቅዱስን” ሰጥቷቸዋልና ደስተኛ ናቸው።

ይህቺው አገረ አሜሪካ የይሖዋ ምስክሮችን ፍጡር ኢየሱስንም ፈጥራ በደጃችን አድርሳለች። ይዘመርለታል፣ ይሰበክለታል። እነርሱም ፈጠራው የተሳካላቸው ደስተኞች ናቸው። ለእኛ ግን አንደኛውኑ ቆፍጠን ብለው ስለ “ልዩ” ማንነቱ በኅትመት ውጤቶቻቸው ግልጽ ማድረጋቸው ስለ እሱ ከመደናገር ያድነን ይሆናል።

ያቺው አሜሪካ በ20ኛው ክፍለ ዘመንም ይህንን የ“አምላክ” መፍጠር ሥራ ገፍታበት ነበር። የዚህኛው አፈጣጠር ታሪክ ሌላ “ቅዱሳት” መጻሕፍት በማዘጋጀት ተጨማሪ ድጋፍ አላስፈለገውም፤ ያው አንዱን መጽሐፍ ቅዱስ እያስታከኩ፣ እየፈለጡና እየቆረጡ መፍጠርም አንድ “ጥበብ” ነውና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተገለጠው ኢየሱስ ለየት ያለ የፈጣሪያኑ አእምሮና ልብ ልክ የተዘጋጀ “ኢየሱስ” ከአንዴም ሁለቴ እና ሦስቴ ብቅ አድርገዋል። የ“ኢየሱስ ብቻ” (Jesus Only) ጅማሬ ሐሳዊ መምህራን አብን ከወልድ ደብልቀውና ቀላቅለው ʻይኸውና አምላካችንʼ ብለውናል።
ዘመን እና ሁኔታ በተለየ መንገድ “የአምላክ” ፈጠራን ያበረታታሉ። የ1950ዎቹ “ሌላ ኢየሱስ” አፈጣጠር ደግሞ ከ1945 እስከ 1975 (እ.ኤ.አ.) የታየውን የሀብት ፍሰት ተከትሎ የመጣ ነው። ዓለም በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ያየችውን የሀብት እና የገንዘብ መጠን በሌላው ዘመን እና ታሪኳ አይታው አታውቅም ሲባል ሰምተን ይሆናል። የብዙ ጊዜያት የተጠራቀመ የኢንደስትሪያላይዜሽን ውጤት መሆኑ ነው። ይህ ወቅት ሀብት እና ፌሽታ “ለብዙዎች” መቋደስ የሆነበት፣ የምዕራባዊያን አኗኗር በብዙ ሁኔታ የተቃኘበት ጊዜ ነው። የሀብት ቅርብ መሆን አብዛኛውን ምዕራባዊ (በተለይ ሰሜን አሜሪካዊ) ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲያነጣጥር አድርጎታል። ይሠራል፣ ገንዘብ ያገኛል፣ የተሻለ ደግሞ ይፈልጋል። የአሜሪካ ሕልም (the American Dream) ቅርብ ነው፤ የሚፈጸም፣ የሚጨበጥ። ታዲያማ “ቤተ ክርስቲያንም” ይኼንን ለሀብት ታጥቆ የተነሣውንና “የነቃውን” ሕዝብ የሚመጥን “ኢየሱስ” ፈጠን ብላ ማዘጋጀት ነበረባት።

በመሆኑም ሰው በማዕከላዊነት የሚያሽከረክረው “ኢየሱስ” መገኘት ነበረበት። ለዚህም ደግሞ እሱ ድኽነትን፣ ማጣትን፣ መከራን እንዲጠላ እና እንዲፀየፍ ተነገረው። እሱም ʻእሺʼ አለ። እነ ማጣትም የርኩስ መንፈስ አካል ተደረጉ፤ ሆኑም። ዘመኑም 1950ዎቹ ነበር። (ይህ በጥንቱ ዘመን ከዚህ በተቃራኒ ድኽነትን ʻቤቴ ጎረቤቴʼ ይሉ የነበሩና “ክርስትናን” በዚያው መልኩ ሊቀርጹ ከወደዱ መነኮሳትና ባሕታዊያን በተቃራኒ ፅንፍ የተፈጠረ ነው።)

ይህ ሁለንተናው ወርቅ እና ብር የሆነ “አምላክ” አስተዋዋቂ “ልዩ ወንጌል” ፈጠራ ላይ ሸሚዛቸውን ሰብሰብ አድርገው አትሮንሱ ፊት የቆሙት ደግሞ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ላይ “ወንጌል” ሰባኪዎች ነበሩ። ሲጀምር የነገረ መለኮት ጥያቄ እንጂ ከገንዘብ ጋር ንክኪ አልነበረውም የሚባልለትን “የእምነት እንቅስቃሴ” ጠልፈው ለዚህ የልባቸው ምኞት “አምላክ” ግብር አደረጉት። ብር ትልቅ፣ ትልቅም አድራጊ መሆኑ ተበሰረ። ሆድ አምላክ ሲሆን በተግባር ታየ። እናማ ብልጣ ብልጦቹ አገልጋዮች በሚፈልጉትና በሚያስፈልጋቸው የልባቸው ምኞት ልክ የተሰፋውን “አምላክ” ለተጠማው እና ለጎመጀው ሕዝብ ʻእነሆ!ʼ አሉት። ፈጣሪዎቹንና ጋሻ ጃግሬዎቻቸውን ከበፊት እና ከአሁን የስብከት የቲቪ ጣቢያዎች ላይ መቁጠር ትችላላችሁ። ስለዚህ እነ ኬኔት ሃገን፣ ኦራል ሮበርትስ፣ ጆኤል ኦስቲን፣ ክሬፍሎ ዶላር፣ ወዘተ. ያደረጉትና የሚያደርጉት ከጥቂት አዲስ ኪዳን እና ከብዙ ብሉይ ኪዳን ተቀነጣጥቦ ለሙከራ የተፈጠረውንና ሆድ ማዕከል ያደረገ “አምላክ” ለሽያጭ ማቅረብ ነው። ገዢው ደግሞ በመጎምጀት መንፈስ የተጠቃው ነው። ገበያውም ደራ።

በክርስቶስ ውስጥ ያለው የሕይወት መንፈስ ከፍታ ሳይሆን በሚታየው ቁሳቁስ ክርስትናን አበጁት። ከማግኘትም ከማጣትም በላይ የሆነውን ወንጌል ወደ ክብራቸው አወረዱት። “እንግዲያውስ በክርስቶስ ልታምኑ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር መከራን ልትቀበሉ ተጠርታችኋል” የሚል ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸው ውስጥ ስፍራ አሳጡት፤ ቢሰብኩም የይስሙላ ነው። ʻበመከራ ተመኩ፤ ጽናትን እና ትዕግሥትን ያደርግላችኋልʼ ባይ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስንማ ማን ሊያነበው?! ʻበውርደትም በክብርም የእርሱ ነን’፤ ደግሞም ‘በብዙ መከራ ወደ መንግሥቱ ልንገባ ይገባናልʼ የሚሉ ጥቅሶችን ʻየድሮʼ ብለው ለመፈረጅ የሆድ አምላክ ሰባኪዎች በጥቂትም ቅምም አላላቸው።

ይህ “አምላክ” በሥራ ላይ፡- ዋናው ውጤቱ ነው

የዚህ የ1950ዎቹ “አምላክ” ሥራና ተጽእኖ የትየለሌ ነው። ከጥቅሶች ውግርግር የተሠራው “ጌታ” እነሱ የሚሉትን ሁሉ የሚያደርግ ታዛዥ፣ የሚጠይቁትንም ሁሉ የሚፈጽም እንደ ሆነ በተግባር ለማሳየትም ለጠቢባኑ ፈጣሪዎች ቀላል ሆኖላቸዋል። ማሠሪያ ገመዱም “በመስጠት የመቀበል ሕግ” ዘርን በተገቢው ስፍራ የመዝራት ጥበብ ተበጅቶለታል። ለመቀበል የጎመጀው ሕዝብ ይሰጣል፤ ለ“አምላኩ”፣ ማለትም ያው ለፈጣሪዎቹ። የ“ጌታ” ኪስ እና የሰዎቹ ኪስ በአስደናቂ፣ ብልጣ ብልጣዊ፣ ሥውራዊ መንገድ የተሣሠረ መሆኑን ርግጠኛ መሆንም የጥበባቸው አካል ነው። ስለዚህም የሚሊዮኖች ጌታ ʻይኸው፤ ይህን አደረገ!ʼ ይባልለታል። በአገልጋዮቹ ነበልባላዊ አንደበቶች ላይ ይህ “ውጤት” በተግባር ሲታይ የነፍስን ለገንዘብ የመጎምጀት ጉልበት በተከታዮች ውስጥ እስከ መጨረሻው ይቀሰቅሳል። ይህ “ጌታ” ለቅቡዓኑ አገልጋዮች ፈቅዷልና ሕዝቡ ይሰጣል፤ ተቀባዩ ይከብራል፤ ጌታም እንዳከበረው ይናገራል፤ ሕዝቡም ይህን በብር እና በወርቅ የሚሞላውን ጌታ አብዝቶ ይማጠናል፤ እንዲደረግለትም ገንዘቡን ይሰጣል። “ለጌታ” ገንዘብ አምራች አዙሪታዊ ማሽን ይሏል ይህ ነው።
ስለዚህ “ፈጣሪ ጌቶች” የግል አውሮፕላን ቢገዙና ቢጨማምሩ፣ በሚሊዮኖች ሀብት ቢያጠራቅሙ እና የቅንጣት መኪኖችን ቢደረድሩ፣ በቡጥቦጣ ባገኙት ገንዘብ በልተው ቢያጋሱና በዕብሪት ቢሞሉ፣ ያው “ጌታ” ነው ያደረገው። እናም እነዚህ ጋሻ ጃግሬዎችን ʻአንተስ ለምን አትሰጥም?ʼ ብሎ ጠያቂ የዚህ “ጌታ” ጸር ነው። ʻለአንተ ከምሰጥ ለተቸገረና ለደኻ ብሰጥ የመስጠት -መቀበሉ ሕግ ይሠራል?ʼ ባይ ጠያቂ “በተገቢው ቦታ የመዝራት ሕግ” እንደሚጣረስ ይነገረዋል። “ጉባኤ ውስጥ ʻሆነልን!ʼ የሚሉ 20 እና 30 ናቸው፤ የቀሩት ብዙ ሺህዎች መቼ ነው የሚሆንላቸው?” ብሎ መጠየቅ የዚህን “አምላክ” ትዕግሥት መፈታተን ነው፤ ማለትም እነሱኑ መፈታትን ነው።

ከዚህ ፈጠራ ጀርባ የሥነ አእምሮ (psychology) ጥበቦች እና የእርኩስ መንፈስ የኋላ ግፊት መኖር ያለ መኖሩን መወያየት የአሁኑ ትኩረቴ አይደለም። ነገር ግን የኢኮኖሚ ዕድገትን እና ምቹ ዘመንን ተንተርሶ የሕዝቡን ፍላጎት ታሳቢ አድርጎ ለንግድ፣ ለገቢ እና ትርፍ ማስፈጸሚያ የተፈጠረውን ባለ “ልዩ ወንጌል ኢየሱስ” ለይቶ ያለ ማወቅ ግን ጥልቅ የጨለማ እና የብዝበዛ ጉዞ ነው። እውነቱን በግልጽ ለማየት ደግሞ በቅንነት ለሚጠጉት እና በእውነት መንፈስ ደጁን ለሚጠኑ ጌታ እግዚአብሔር በቃሉ እና በመንፈሱ አማካይነት ብርሃንን ሰጥቷል።

የዚህ “አምላክ” ጉዞ ወደ አፍሪካ፤ ኢትዮጵያ

እስከ አሁን የተባለው ስለ አሜሪካውያኑ የዚያ “አምላክ” ፈጠራ እና ጋሻ ጃግሬዎቹ ነው። በርግጥ አፍሪካ የዚህ “አምላክ” ጉብኝት እና ትምህርት ደጋግሞ ደርሷታል። ከሁሉም ጫን ባለ ሁኔታ አገራችንን ጨምሮ በምዕራብ እና ደቡብ አፍሪካ መሠረቱን ጥሏልና የተመሳሰለ ነገር አስተውላችሁ ከሆነ፣ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የዚያ “አምላክ” ትምህርት ጥሙቃን ወይም በገዛ ፍላጎታቸው የእሱን የመንፈስ ልጅነት እየተቀበሉ እየበዙ ስለሆነ ነው።

ለኢትዮጵያም የተለያዩ ሰዎች (ከአሜሪካ፣ ከካናዳ ሆነ ከዚሁ የአፍሪካ ክፍል) የፍጡራኑን የእጅ ሥራ “አምላክ” አድርሰዋታልና ለዚህ ገንዘብ እና ስኬትን መሠረት አድርጎ የተበጃጀውና የልብ ምኞትን ሊያገለግል የተፈጠረው “ጌታ” ለምድራችን ባዕድ አይደለም። ትምህርቱ ቀድሞውኑ መሠረት የተበጀለት፣ ቅኝት የተቃኘለት ነው። ዋነኛ ማስተላለፊያ አሸንዳዎቹ የድል አጥቢያ ዐርበኞች ሆነው ከወደ ምዕራብ ዓለም የ(ሚ)መጡ አገልጋዮችና ፓስተሮች ሲሆኑ፣ ከ“የስማ በለው” የዘለቀ እውቀት የሌላቸውም አገር በቀል አገልጋዮቹ አሉለት። ሁሉም በአንድነት የሚፈረጁ አይሆኑም። አንዳንዱ እንደ ኀይሉ ዮሐንስ እና “ሐዋርያ” ዘላለም ጌታቸው ያለው አውቆ እና ፈቅዶ ከዚህ አምላክ ጎራ የተሰለፈ፣ “አምላክ” ፈጣሪ ʻአምላክ ነኝʼ ባይ አለ፤ አንዳንዱ ከንግግርና ሰበካ ባለፈ መልኩ የዚሁ “አምላክ” ተጠቃሚ አለ፤ አንዳንዱ የትምህርቱን የት መጣነት ሳያውቅ ጥቅሙን አይቶ የገባበት አለ፤ አንዳንዱ የዚህ “አምላክ” አፈ ቀላጤዎችን የተከበሩ እና የታፈሩ ሰዎች አድርጎ በመቀበሉ ተታልሎ አጋፋሪ የሆነ አለ፤ አንዳንዱ ደግሞ ከመጎምጀት ብዛት እዚሁ ሰፈር ሆኖ ለዚያኛው ሰፈር ወገብ ሰባቂ አለ፤ ከማግኘትና ማጣት በላይ በሆነ መንፈስ ለተያዘው አማኝ የእግዚአብሔር ለሰው ልጆች በጎ የማድረግንም የመግቦተ ትምህርት ከዚህ ሰው ተኮር ትምህርት ጋር የተደበላለቀበትም አይጠፋም።

ልባችን እና ቤታችን ከፈጠራው ጥልፍልፍ አሠራር ይርቅ ዘንድ

እንግዲያውስ ወደ ቅርባችን ይበልጥ ስንመለከት በግብሩም በሥሪቱም የዘራፊዎች አጋር ተደርጎ የተሠራው ይህ ወንጌል ተብዬ እግር ሥር ስንቱ እንደወደቀ መቁጠር አስፈላጊ አይሆን ይሆናል። በአጉል ተስፋ ለሚንጥ ትረካ ስንቶች ልባቸውን እንደከፈቱና ለዚህ የጋሻ ጃግሬነት ተግባርም ታጥቀው ከዓመት ዓመት ጎንበስ ቀና የሚሉ “የተወዳጆቻቸውን” ትርፍና ኪሣራቸውን መተንተንም አስፈላጊ አይደለም። ʻየትኞቹ የዚህን አምላክ ተረፈ ትምህርት ተቀባብለው ዘመሩ፣ ተነበዩበት፣ ሰበኩበት?ʼ አይደለም ዋናው ትኩረቴ። ጽኑ እምነቴ የልብን እና የመንፈስን ንፅሕና የመጠበቅ አስፈላጊነት ላይ ነው። ምክሬም ለማንም “ከውስጥ መጣን”፣ “ከውጪ ብቅ አልን” ለሚሉት ነጣቂዎች እራት ያለመሆንን ነው። “ኑ እንፍጠረው” ተብሎ የተሠራውም ከእውነት ሕዝቡን እንዳይነቅል ነው። ሕዝቡን ወደ አትራፊ ንግድ ቤትነት ከቀየሩ ጮሌዎች ስለ መራቅ ነው። የተፈጠረውን እና/ ወይም በምናብ የሣሉትን ይህንን ጌታ ሳይሆን ʻጌታʼ ከሚሉ እና በልተው ከማይጠረቁ ስለመራቅ ነው። አገራችንም ራሱን ከጥንቆላ እና መተት ጋር በማዛመድ እየተንሠራፋ ካለ እንግዳ የትምህርት ዘር ራስን ስለ መለየት ነው። ለተቀበልነው የእውነት መንፈስ ታማኝ ስለ መሆን፣ በከፍታም በዝቅታም የእርሱ ሆኖ ስለመሞት፣ ገንዘብ ተኮር ከሆነው ከ1950ዎቹ የፈጠራ ሥራ ከሆነው “አምላክ” ተብዬ እና እንደ ቡሽሪ መሰል ጋሻ ጃግሬዎቹ (የመንፈስ ትብብርና ትሥሥር) ጥልፍልፍ አሠራሮች በመዳን ሌላውን ስለ ማዳን ነው።

ብዙ የተባለለት እና ጥንቆላን ከፈጠራው “ወንጌል” አዳቃዩ ቡሽሪ ጉዳይም እርሱ ወደሚሄድበት ከሄደ በኋላ የተወንና በቀላሉ የምንገላገለውና የተገላገልነው ጉዳይ አይደለም፤ ስታዲዮም ከተደረገው የአዲስ ዓመት ስብሰባ ጋር ተያይዞም የሚነሣ ሆኗል። በዚያን ቀን ጥዋት ስብሰባ ላይ የሚሆነውን ሁሉ በኤልሻዳይ ቲቪ ስመለከት ከቄስ ቶሎሳ ስብከት እና ቡራኬ ቀጥሎ አንድ ሰው ለሕዝቡ ይጸልይና ሕዝቡን ይባርክ ነበር። ቄሱ የዚህ የፈጠራ ወንጌል አራማጅ መሆናቸውን ዐውቃለሁ፤ ግን ይህን ሰው ስለማላውቀው “ማን ነው?” ብዬ ስጠይቅ “በምድሪቱ ላይ የተነሣ ታላቅ ነቢይ ነው” አለኝ አንዱ። ቀጥሎም “ቡሽሪ ‘ወራሼ ነህ፤ ፎቶዬን ቢሮህ ውስጥ ሰቅለሃልና ውርሱ ይገባሃል’ ብሎታል” ሲልም አከለ። እንዲህ እና ይህን መሳይ ነገር በዚህ ሰው እና በቡሽሪ መኻል ሆኖ ከሆነ “ውስጡ የውጪ” የመሆኑ ነገር መደበቅ የማይቻል የአደባባይ ሆኗል ማለት ነው። በስታዲየሙ ስብሰባ ላይ የዚህ ሰው ጋባዥ አስጋባዦች ይህንን “የመንፈስ ውርርስ” ውል ሳያውቁት ቀርተው ነው? ወይስ ‘ምን ታደርጉናላችሁ? ምንስ ትሆኑ?ʼ ባይ ድፍረት ነው? በርግጥ ግን ሕዝባቸውን እየደጋገሙ ለዚህ ዐይነት ንግርት እና ድርጊት አሳልፈው የሚሰጡ መሪዎች ʻምን ዐይነት ብርቱ ድንዛዜ ቢወርድባቸው ነው?ʼ ብዬ ጠይቄአለሁ። መንቃት ቢሆንላቸውማ ኖሮ ከዚህ ለብዝበዛ ከተፈጠረ የ“ወንጌል” ባለአደራዎች “ሕዝባቸውን”፣ ራሳቸውን እና ቤታቸውን መጠበቅና ማጽዳቱ የቀረላቸው አስቸኳይ የቤት ሥራ ነበር።

‘ቢያይ የሰው ኪስ፣ ቢስቅ በወርቅ ጥርስ’ የሆነ ዝግንትል “አምላክ” አስተዋዋቂዎችንና “ወንጌላቸውን”ም ከሰው ልብና አንደበት የሚያርቅ፣ ሊያርቅም የሚችል የመንፈስ ቅዱስ ብርቱ ጉብኝት እና የቃሉ እውነት ዳግም ምሥረታ ብቻ እንደ ሆነ አላጣሁትም። እግዚአብሔርም ይህን የሰውን ምኞት በመከተል ተዘርቶ የበቀለ እና “ተደላደልኩ” ያለውን፣ “በአምላክ” የፈጠራ ሙከራ የተበጃጀውን የ1950ዎቹ ሥሪተ ትምህርት የልኩን ቦታ እንዲሰጠው፣ የቃሉን እውነት እንዲያበራ እና ጌታ ኢየሱስም ስሙን እና መልእክቱን ዳግመኛ እንዲያከብር ለእውነት እንቁም።

Afework Hailu (Ph.D.)

Afework Hailu serves EGST as lecturer in Church History and Dean of Students. He holds a Ph.D. from the School of Oriental and African Studies at the University of London. His doctoral dissertation was titled The Shaping of Judaic Identity of the Ethiopian Orthodox Täwaḥədo Church: Historical and Literary Evidence, which discussed the origin and development of the so-called Jewish cultural elements such as circumcision, and Sabbath in the Ethiopian Church. The study analysed pertinent historical, archaeological, and literary evidence available from the Aksumite, Zagwe, and ‘Solomonic’ dynasties. The study will be published as ‘Jewish’ Elements in the Ethiopian Church (Gorgias Press, USA). Before his doctoral study at SOAS, Dr. Afework earned Masters degrees from Addis Ababa University in Cultural Studies, the Free University Amsterdam in Church History, and a Master of Theology from EGST. He has taught theological and historical courses in theological colleges in Ethiopia. His general academic interest is in the field of history, but specifically history of Christianity, African and Ethiopian church history, Eastern Christianity, Jewish-Christian relations, Muslim-Christian relations, culture and culture formation, religion and Development/Environment. He has a growing passion for the study of practical aspects of church reform. ዶ/ር አፈወርቅ ኀይሉ በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት (ኤገስት) የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መምህር ሲሆን፣ የት/ቤቱ የተማሪዎች ዲን በመሆን ያገለግላል። ዶ/ር አፈወርቅ የፒኤችዲ ጥናቱን ለንደን በሚገኘው School of Oriental and African Studies (SOAS) ያደረገ ሲሆን፣ የጥናቱ ትኩረትም የአይሁድ ማንነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ የሚመለከተ ነው። አፈወርቅ የፒኤችዲ ጥናቱን ከማድረጉ በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባህል ጥናት፣ አምስተርዳም ከሚገኘው Free University በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት በነገረ መለኮት ጥናት የማስተርስ ዲግሪዎች አሉት። ዶ/ር አፈወርቅ በጠቅላላው በታሪክ መስክ ላይ ምርምር ማድረግ የሚወድድ ሲሆን፣ በክርስትና ታሪክ፣ በተለይም ደግሞ የአፍሪካ እና የኢትዮጵያ ክርስትና ታሪክ፣ የምሥራቅ ክርስትና ታሪክ፣ የአይሁድ ክርስትና ግንኙነት፣ የሙስሊም ክርስቲያን ግንኙነት፣ ባህል እና የባህል ለውጦች እንድሁም ሃይማኖትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረግ ጥናት ያካሂዳል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ተሓድሶና ተግባራዊነቱ ላይ ልዩ ትኩረት አለው። ዶ/ር አፈወርቅ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ነው።

Share this article:

የቃላት ጡጫ እና ጉዳቱ

የብእር ሐሳብ ከማይነጥፍባቸው ነገሮች አንዱ የፍቅር ጉዳይ ነውና ዛሬም ስለ ፍቅር እናውጋ። የፍቅር ታሪኮችን ስናደምጥ ደግሞ ተያያዥ ስሜት መውረሩ አይቀርም። አንዳንዱ ታሪክ ልባችንን ጮቤ የሚያስረግጥ ነው፤ የተከፈለው መሥዋዕትነት ‘ብዙ ውኾች’ ፍቅርን ለማጥፋት የፈረጠመ ጡጫ እንደሌላቸው ምስክር ነው (መኀ. 8፥7)። ሌላው ደግሞ ውስጣችን በቁጭት እንዲብሰከሰክ ምክንያት የሚሆን ነው (2 ሳሙ. 13፥1-20)። በስመ ፍቅር አንዳንዶች የተጎነጩትን ጭቆና እና ግፍን ተመልክቶ አለመቆጣት በርግጥም የተባባሪ ያህል ያስቆጥራል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ለማነጽ እንሠራለን!

ሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ ወንጌሉ እውነት እንዲሁም እርሱ ስለ መሠረታት ቤተ ክርስቲያን ግድ የሚላቸው ሰዎች ተሰባስበው ያቋቋሙት መንፈሳዊ ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ በምድራችን ላይ ያለችው ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቶስን መስላ እንድታድግ በሚደረገው የማነጽ ሂደት ውስጥ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ያለመ ነው፡፡ ስያሜውም ይህንኑ የሚገልጽ ነው፤ “ሕንጸት” የግዕዝ ቃል ሲሆን፣ “ማነጽ” ወይም “መገንባት” የሚለውን ፍቺ ይይዛል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.