
የእግዚአብሔር ሕዝብ፦ ሕዝብን ፍለጋ
“የእግዚአብሔር ሕዝብ” በሚል መሪ ዐሳብ፣ ዘሪቱ ከበደ የምታስነብበው ጽሑፍ ሁለተኛ ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።
[the_ad_group id=”107″]
በዓለማችን ላይ የፀሓይ መውጣትና መግባት ግልጽ የሆነውን ያህል፣ ግልጽ ያልሆኑ፣ ለጕዳዩ መሪ ተሳታፊዎች ካልሆነ በስተቀር ለተመልካች ግራጫ የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። አንዳንድ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ግልጽ አይደሉም፤ አንዳንድ ነገሮች ደግሞ ጥቂት ፍንጭ አላቸው፤ ሌሎች ነገሮች ደግሞ በግማሽ ታውቀው በግማሽ አይታወቁም፤ አንዳንድ ነገሮች ደግሞ ሊታወቁ የሚገባቸውን ያህል ይታወቃሉ።
ሰው በግልጽ ከሚያውቀው አጥቂ ነገር ይልቅ፣ በስውር ያለ የማያውቀው ነገር ያስፈራዋል፤ እንዲህ ዐይነቱ ነገር በአንዳንድ ሕዝብ ላይ ጎልቶ ቢታይም ችግሩ ግን የሰው ልጆች ሁሉ ጠባይ ነው።
አሳሳቢው ጕዳይ ግን ከዚህ በመነሣት ነባራዊውን ዓለም ለመኖር በሚደረገው የየዕለት ትግል የማይታወቅውን ክፍተት ለመሙላት የሚደረገው የፈጠራ ትርክት ነው። እንዲህ ዐይነቱ ትርክት ሰዎች ሳያውቁ የሚፈሩትን “አውቀው” እንዲፈሩት ስለሚያደርጋቸው ከአላውቀውም ሥጋት የማያውቁትን፣ ነገር ግን ያወቁ የመሰላቸውን ፈጥረው ይኖራሉ።
እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች የተበጣጠሱ ጭብጦች ስላሏቸው ስሞችን፣ ኹነቶችን፣ የታሪክ እንቡጥን ሳይሆን ጠርዞችን፣ የሃይማኖትና የርእዮተ ዓለማትም ኅዳጋዊ (Peripheral) እውቀቶችን በውዘው የያዙ ስለሆኑ፣ ነጥሎ እዚህ ጋ ነው የተሳሳታችሁት ለማለት እንኳ አስቸጋሪ ናቸው። እነርሱ የሠሩት ምናባዊ ዓለም ዳስሰን፣ ጨብጠን ከምናውቀው የገሃዱ ዓለም ይልቅ፣ የጠነከረ ስለ ሆነ ሐሳባቸውን ማስቀየር አይቻልም። እንደውም ከቻሉ ያሳምናሉ፤ ካልቻሉ ቢያንስ የምንኖረው የገሃዱ ዓለም ቅዥት ነው ብለን እንድንጠረጥር ያደርጉናል፤ ጠንክሮ የሚሞግታቸውንም እንደ አስፈላጊነቱም የሴራው ጎራ አድርገው ይመድቡታል። ይሁን እንጂ፣ ከእነርሱ ይልቅ በእነርሱ ውስብስብ ዓለም የተምታታበት ሰለባቸው ያሳዝናል።
አብዛኛዎቹ ተበድለናል ብለው የሚያስቡና ዓለም እንቅስቃሴዋ ሁሉ በሴራ ዙሪያ እንዳለ የሚያምኑ ናቻው። በዙሪያችን በበዙ መጠን በምናባዊው ዓለም እና በእውነታው ዓለም መካከል ያለው ልዩነት ሊምታታብን ይችላል።
ለምሳሌ፣ የኒውዮርክ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ በአሸባሪዎች መጠቃት የአሜሪካን መንግሥት እጅ ያለበትና ከጦርነት የሚገኝ ጥቅም ተፈልጎና ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው የሚል ሴራዊ ሐሳብ። ዓለም የምትመራው በኢሉሚናቲ ነው። የሮማው ጳጳስ የ666 አራማጅ ናቸው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ከኦነግ ጋር በጫካ ስምምነት አድርገዋል። በአደጋ ጊዜ የውስጥ አካል ብልት ለጋሽ (organ donor) መሆን በሚድን በሽታም ቢሆን ታመህ ሐኪም ቤት ብትገባ የአካልህን ብልት ፈልገው ይገድሉሃል። የንግሥት ዳያና የመኪና አደጋው የተቀነባበረ ነው፤ ከነገሥታቱ ቤተ ሰብ አንዱ እንድትሞት ስለፈለገ ነው እና ሌላም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው ሴራዊ ሐሳብ ፍሪ ሜሶነሪ እና ኢሉሚናቴ የተባለው ጃንሆይም ነበሩበት የሚባለው ድርጅት ሲሆን፣ በየአገሩና በየመንደሩ ደግሞ አእላፋት ሴራዊ አስተሳሰቦች አሉ። ዙሪያችንን ብቻ ሳይሆን ራሳችንን እንኳ እንዳናምን የሚያደርጉ፣ አካላቸው የት እንዳለ የማናውቃቸው ጥላቸው ግን ሲያስበረግገን የሚኖር የሴራ አስተሳሰቦች አገሩን ሞልተውታል።
የዓለም ከባቢ አየር ግለት (global warming) የሚባል የለም፤ ባለ ሀብቶች ለራሳቸው ጥቅም የፈጠሩት ወሬ ነው። እገሌና እገሊት በቅርብ ጊዜ ወዳጅነት የጀመሩት እንትናን ለማጥቃት ነው እስከሚለው ግላዊ የሴራ ወሬ ግንኙነት ድረስ፣ በላእላይ መዋቅር ላይ ያሉ ጉዳዮችንም ሆነ በግለ ሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በሴራ የሚያይ በመሆኑ ወደ አስተሳሰብ ደንብነት የተቀየረውን ይህንን ታዋቂውን ሴራዊ ዕይታ በዐይነቱም ሆነ በዓለም ላይ በብዛቱ በአጭሩ መዘርዘር በጣም አስቸጋሪ ነው።
የአንድ ነገር የእውነታ ክልል የትኛው ድረስ እንደሚዘልቅ እንዳናውቅ፣ ባልተጠመዱ ቦምቦች ስንሰጋ እንድንኖር የሚያደርገን፣ እንዳንክደው የሰው ክፋት ልኩን አናውቅ (ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን)፣ እንዳናምነው የገሃዱን ያህል ተጨባጭነት የለው (ማስረጃው ጉንጭ አልፋ ይሆንብናል)፣ እንዳናስጥለው ከሃይማኖት ሁሉ የጠነከረ እጅግ ውስብስብ ማኅበራዊ ችግር ነው (እየናኘ ያለና ብዙው ሰው የተቀበለው ነው)። በውጤቱ ግን ከማጀት እስከ አደባባይ እንደ ሙጫ አጣብቆ የሚያኖረንን መተማመን የተባለውን ንጥረ ነገር እንደ ብል በልቶ፣ እንደ አይጠመጎጥ ገዝግዞ፣ እንደ ወራጅ ወንዝ ሸርሽሮ የሚጥል በሽታ ነው።
ይሁን እንጂ ይህንን የፍርሀት ብርገጋ እና የሥጋት ጥፍነጋ በሞራላችንና በእርስ በርስ ግንኙነታችን ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተጽእኖ ማወቅና ማብራራት ምንም እንኳ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ራሳችንን እና አካባቢያችንን መጠበቅ ይኖርብናል።
በውሸት ላይ ወይም በጥቃቅን እውነት መሰል መረጃዎች ላይ፣ ተመሥርተው በሚጋነኑ ወሬዎች ስንት ትዳር፣ ጓደኝነት፣ ቤተ እምነት፣ ማኅበራት ፈረሱ? ወገን እባካችን እንትረፍ!
ስንቶች በማያውቁት ተወጕ? ስንቶችንስ ባልዋሉበት አስዋልናቸው? ግማሽ እውነትና ግማሽ ውሸት የጭብጥ ሙሉ አካል ላይሆን በማይገጥሙ የወሬ ስብስቦች ስንት ጊዜ የሚታቀፈውን ገፍተን የሚገፋውን አቀፍን?
መንግሥት በጨቋኝ ሥርዐት ሲበድለን ስለኖረ፣ የዜና ማሰራጫዎች ደግሞ የማታለያ መሣሪያዎቹ ስለሆኑ አናምናቸውም፤ ግን በአሁን ሰዓት አጭር ጥናት አድርገን በምንደርስበት የመረጃ ዘመን ማን ማንን ያታልላል?
የምናያቸው ፊልሞች፣ ቤተ ሰብን፣ ንግድን፣ ፍቅርን፣ ፖለቲካን ይሁን ብቻ አብዛኛው ማለት በሚቻል ደረጃ ሴራና ማታለሎች አሉበት፤ ዓለም ሁሉ ግን እነዚህ ፊልሞች ብቻ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኛው ዓለም ልትቀጥል የቻለችው በፊልሙ ውስጥ እንዳሉት ማታለሎች ስለሆነ አይደለም፤ ሰው ስለሚተማመን ነው እንጂ።
ሁላችንም እውነቱን ከውሸት የመለየት የግልም የቡድንም ኀላፊነት አለብን። ይሄኛው ትክክል ነው፤ ይኼኛው ደግሞ ትክክል አይደለም ብለን መለየት፣ ያልሰማሁት መረጃ ሁሉ የተደበቀኝ ላይሆን ይችላል፣ ማወቅ እየፈለግሁ ያለሁት የሚገባኝን ነው ወይስ ከ“ክልሌ” ውጪ ሆኜ ነው? የሚለውን መጠየቅ አለብን።
‘እውነቱ አሁን የምናየው ሳይሆን በስተጀርባው ያለነው እያልን’ የሚታየው መልካም ነገር ሁሉ የማይታየው ዓለም ማታለያ ነው እያልን ለመኖር እንዴት እንወስናለን ጎበዝ? ከወሰንን እኛ ራሳችን የምናታልል ሳንሆን አንቀርም ማለት ነው። ኑሮ እንዴት እንደዚህ ይዘለቃል? መቀየር አለበት!!!
እያንዳንዳችን ገጽታዎችን ከሚያባዙ የመስታወት ግድግዳዎች ውስጥ መውጣት አለብን። እውነታውን ማንም አይደለም የሚቀርጽልን፤ ራሳችን ነን፤ ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱን ተግባር በተናጠል ማየት ይጠቅማል፤ የፖለቲካውን ተዋንያን ሁሉ የአንድ ድርሰት ባለቤት ማድረግም አይገባም።
ጥልቅ አሳቢያን በነፋስ የመጣን ወሬን እና ተራምዶ የመጣን ጭብጥ የሚለዩ ናቸው። በተለይ ወጣቱ ፈልጎ የሚያገኛቸው ማታለሎች ካሉ በማስረጃ፣ ከ “ይሆን ይሆናል” እና “ሳይሆን አይቀርም” ሴራዊ አስተሳሰብ ተርፎ የማንም መጠቀሚያ እንዳይሆን ሊያስተውል ይገባል።
Share this article:
“የእግዚአብሔር ሕዝብ” በሚል መሪ ዐሳብ፣ ዘሪቱ ከበደ የምታስነብበው ጽሑፍ ሁለተኛ ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።
The pre-eminent scholar Robert Alter has finally finished his own translation.
ሰሎሞን ጥላሁን፣ ሰሞኑን በአገሪቱ የተፈጠረውን አሳዛኝ ክስተት መነሻ በማድረግ፣ የመብት ትግልን በማካሄድና በፍጻሜ ግቡ መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ልዩነት ከግምት ማስገባት እንደሚበጅ በዚህ ጽሑፉ ያሳስባል።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment