[the_ad_group id=”107″]

ሙስና እና አማኝ ማኅበረ ሰቡ

ዐጭር የዳሰሳ መጠይቅ ዘገባ

ይህ የዳሰሳ መጠይቅ የተዘጋጀው፣ ሙስና በአማኝ ማኅበረ ሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽዕኖ ለመቃኘት በሚል ነው። መጠይቁ ከጷጕሜ 2014 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 2015 ዓ.ም. ድረስ፣ በበይነ መረብ (online) አማካኝነት በተሳታፊዎች ምላሽ ሲሰጥበት ቈይቷል። በዚህም 194 (አንድ መቶ ዘጠና አራት) ተሳታፊዎች ለመጠይቁ ምላሽ ሰጥተዋል። የዳሰሳ ጥናቱ በሕንጸት የምርምርና ጥናት አገልግሎት ክፍል ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው።

ከዚህ መጠይቅ የተገኙ ምላሾች ዐጭር ዘገባ ቀጥሎ ቀርቧል።

1. የሥነሕዝብ (ዲሞግራፊ) መለያዎች

ከጾታ አኳያ፣ መጠይቁን ከሞሉት ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ናቸው። እንዲሁም ከ93 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቋሚ የመኖሪያ አድራሻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ የተቀሩት ከአገር ውጪ የሚኖሩ ናቸው።


ቻርት 1 እና 2፦ የመላሾች ጾታ ተዋጽዖ እና ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ

ከዕድሜ አንጻር፣ ግማሽ ያህል የሚሆኑት (49.1 ከመቶ) ከ18 እስከ 34 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሲሆኑ፣ ከ35 እስከ 44 የዕድሜ

ክልል ውስጥ የሚገኙት ደግሞ 30.9 ከመቶ ናቸው።

ግማሽ ያህሉ (49.5 ከመቶ) መልስ ሰጪዎች፣ የወንጌላውያን ክርስትና አማኝ የሆኑት ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ 26.3 ከመቶ የሚሆኑት ከ20 ዓመት በላይ፣ 17 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ10 ዓመት በላይ በአማኝነት እንደቈዩ ገልጸዋል።


ቻርት 3 እና 4፦ የመላሾች ዕድሜ እና በወንጌል አማኝነት ያስቈጠሩት ዘመን

2. አጠቃላይግምገማ

“ ‘ሙሰኛ’ ማለት ጕቦ የሚቀበል፣ የሚሰጥ ወይስ የሚቀበልም የሚሰጥ?” ለሚለው ጥያቄ 5.2 ከመቶዎቹ “ጕቦ የሚቀበል ነው” ብለው ሲመልሱ፣ 94.8 ከመቶዎቹ ደግሞ ሁለቱም መሆናቸውን በመልሳቸው አመላክተዋል። “ሙሰኛ ማለት ጕቦ የሚሰጥ ብቻ ነው” የሚል መላሽ ግን አልተገኘም።

አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን የሙስና ደረጃ በተመለከተ አብላጫዎቹ መላሾች (91.2 ከመቶ) “እየባሰበት ነው” ብለው ሲመልሱ፣ 8.8 ከመቶ የሚሆኑት ከበፊቱ እምብዛም ለውጥ የለውም ብለዋል። “እየቀነሰ ነው” የሚል መላሽ ግን አልተገኘም።


ቻርት 5 እና 6ሙሰኛማነው? እና የኢትዮጵያ የሙስና ደረጃ የግል ምዘና

2.1 ለሙስናመስፋፋትአስተዋጽዖያደረጉነገሮች

በአገራችን ሙስና ለመስፋፋቱ አስተዋጽዖ አድርገው ሊሆን ይችላሉ የተባሉ ስድስት ሰበቦች ተዘርዝረው፣ መላሾች እያንዳንዳቸው ምን ያህል ለሙስና መስፋፋት አስተዋጽዖ አላቸው ብለው የሚያስቡትን እንዲገልጹ ተጠይቀዋል። እነዚህ ስድስት ለሙስና መስፋፋት አስተዋጽዖ አድርገው ሊሆን ይችላል ተብለው የተዘረዘሩ ሰበቦች የሚከተሉት ናቸው፦

  1. ድኽነት
  2. ሙስናን የሚያበረታታ ባሕል መኖር
  3. አማራጭ ማጣት
  4. መብትና ግዴታን በውል አለማወቅ
  5. የሞራል ውድቀት
  6. ሕግ የማስከበር ሥርዐቱ በቂ አለመሆን

እነዚህን ስድስቱ እያንዳንዳቸው ለሙስና መስፋፋት ምን ያህል አስተዋጽዖ አላቸው ብለው እንደሚያምኑ ከ1 እስከ 5 (1 = እጅግ አነስተኛ፣ 5 = እጅግ ከፍተኛ) እንዲገልጹ መላሾች ተጠይቀው፣ በሚከተለው መጠን ምላሽ ሰጥተዋል።


ሠንጠረዥ 1፦ ለሙስና መስፋፋት አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ነገሮች

የሞራል ውድቀት (86 ከመቶ)፣ ሕግ የማስከበር ሥርዐቱ በቂ አለመሆን (76.2 ከመቶ)፣ እንዲሁም ሙስናን የሚያበረታታ ባሕል መኖር (72.5 ከመቶ) መለሾች ለሙስና መስፋፋት እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል ብለው የገለጿቸው ናቸው።

በአንጻሩ ድኽነት፣ አማራጭ ማጣት እና መብትና ግዴታን በውል አለማወቅ ለሙስና መስፋፋት አስተዋጽዖ ቢኖራቸውም፣ የተቀሩት የሦስቱን ያህል ሁኔታው የከፋ አድርገዋል ብለው እንደማያምኑ መላሾች አመልክተዋል።

3. የሙስናተጋላጭነትደረጃበየተቋማቱ

በመቀጠል፣ መላሾች እንደየተቋሙ ዐይነት ሙስና የት ድረስ የከፋ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተጠይቀው ነበር። ለዚህም፣

ዐምስት ዐይነት ተቋማት ተዘርዝረዋል፦

  1. መንግሥታዊ ተቋማት
  2. የፋይናንስ ተቋማት (ባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ ብድርና ቁጠባ ተቋማትና የመሳሰሉት)
  3. የግል ተቋማት
  4. የሃይማኖት ተቋማት
  5. መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች

በእነዚህን ዐምስቱ ተቋማት ዐይነቶች ሙስና ምን ያህል ሥር ሰድዷል ብለው እንደሚያምኑ ከ1 እስከ 5 (1 = እጅግ አነስተኛ፣ 5 = እጅግ ከፍተኛ) እንዲገልጹ መላሾች ተጠይቀው፣ በሚከተለው መጠን ምላሽ ሰጥተዋል።


ሠንጠረዥ 2፦ ሙስና በየተቋማቱ የሚገኝበት የአሳሳቢነት ደረጃ

85.6 ከመቶ መላሾች በመንግሥታዊ ተቋማት ያለውን የሙስና አሳሳቢነት ደረጃ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

የፋይናንስ ተቋማት (61.5 ከመቶ) እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (67.5 ከመቶ) ውስጥ የሚገኘው የሙስና ደረጃን አሳሳቢነት አብላጫዎቹ መላሾች ከዐምስት፣ “4” እና “5” ሲሉ ገልጸውታል። በአንጻሩ የግል ተቋማት እና የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚገኘው የሙስና ደረጃ የተሻለ ነው ተብሎ እንደሚገመት ምላሾች ቢያሳዩም፣ እነዚህም ውስጥ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑ መላሾች የሙስና ደረጃቸውን ከዐምስት “4” እና “5” ላይ አስቀምጠውታል።

4 ለሙስና የሚሰጥ የግል ምላሽ

ቀጣዩ የመጠይቁ ክፍል የተዘጋጀው መላሾች ለሙስና ያላቸውን የግል ምላሽ ለመመዘን በማለም ነበር።


ቻርት 7፦ ሙስና የደረሰባቸው መላሾች

ሙስና ወይም የአስተዳደር ብልሹነት ገጥሟቸው ያውቅ እንደሁ የተጠየቁ ከመጠይቁ መላሾ መካከል፣ 87.1 ከመቶ የሚሆኑት፣ “አዎ፤ ደርሶብኛል” ሲሉ መልሰዋል። ከእነዚህም ውስጥ 95 ከመቶ በላይ የሚሆኑት እንዲህ ያለው ሁኔታ የገጠማቸው በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ መሆኑን አመልክተዋል።


ቻርት 8፦ ሙስና ያጋጠሟቸው ተቋማት

ከመንግሥት ተቋማት ሌላ፣ ከፍተኛ ሙስና ወይም የአስተዳደር ብልሹነት እንዳለባቸው የተጠቀሱት የፋይናንስ ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የግል/የንግድ ተቋማት (በቅደም ተከተል) ናቸው። ይህም መላሾች ለተቋማት ከሰጡት የሙስና ተጋላጭነት ደረጃ ጋር ስምም የሆነ መልስ ነው (የላይኛውን ክፍል ይመልከቱ)።


ቻርት 9፦ ጒቦ ሊሰጡ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች

የመጠይቁ መላሾች ጒቦ እንዲሰጡ ቢገደዱ፣ እንዴት ባለ ሁኔታ ጒቦ ሊሰጡ እንደሚችሉ ሲጠየቁ፣ ግማሽ ያህል የሚሆኑት (51.5 ከመቶ) በምንም ዐይነት ሁኔታ ጒቦ እንደማይሰጡ ሲገልጹ፣ የተቀሩት (48.5 ከመቶ) በምንም ሁኔታ ውስጥ ጒቦ ሊሰጡ እንደሚችሉ አመላክተዋል።

የግድ ቢሆንባቸው ጒቦ ሊሰጡ እንደሚችሉ የጠቆሙት ውስጥ 73.4 ከመቶ የሚሆኑት (ከአጠቃላዩ 35.6 ከመቶ) ናቸው። እነዚህም፣ “አጣብቂኝ ውስጥ የሚከትት አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥም” ብቻ ሊሰጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል። 57.4 ከመቶዎቹ (ከአጠቃላዩ 27.8 ከመቶ)፣ “ከእንግልትና መጉላላት ለመዳን”፣ 30.1 ከመቶዎቹ (ከአጠቃላዩ 14.9 ከመቶ) “የዜግነት መብት የሆኑ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት”፣ 6.4 ከመቶዎቹ ደግሞ (ከአጠቃላዩ 3.1 ከመቶ)፣ “ተጨማሪ ጥቅም ወይም ትርፍ ለማግኘት” ጒቦ ሊሰጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

“አጣብቂኝ ውስጥ የሚከትት አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥም” ጕቦ ሊሰጡ እንደሚችሉ ምላሽ የሰጡ ከመጠይቁ ተሳታፊዎች መካከል 92.8 ከመቶ የሚሆኑት ከ10 ዓመት በላይ በወንጌላውያን ክርስትና እምነት ውስጥ የቈዩ ናቸው።


ቻርት 9፦ ጒቦ የማይሰጡበት ምክንያት

በምንም መልኩ ጒቦ እንደማይሰጡ ምላሽ የሰጡ የመጠይቁ ተሳታፊዎች ጕቦ የማይሰጡበትን ምክንያት (አንድም ይሁን ከዚያ በላይ) ሲገልጹ፣ 84.5 ከመቶ መላሾች፣ “በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ኀጢአት ስለ ሆነ” ነው ሲሉ፣ 51 ከመቶዎቹ ደግሞ፣ “ኅሊናዬ ስለማይፈቅድልኝ” ብለዋል። ከመላሾቹ ሢሶ የሚሆኑት ደግሞ፣ የሕግ ተጠያቂነት ስላለበት፣ ሌሎችን ስለሚጎዳ እንዲሁም አርዓያነት ስለሚጎድለው ጒቦ እንደማይሰጡ አመልክተዋል።

5 የተሰጡ ተጨማሪ አስተያየቶች

በመጠይቁ ማገባደጃ፣ መላሾች ማንኛውም ተጨማሪ አስተያየት ወይም ዐሳብ ካላቸው እንዲያሰፍሩ ተጠይቀው ነበር። በዚህም

34 መላሾች (17.5 ከመቶ) ተጨማሪ ዐሳብ ሰጥተዋል።

እነዚህ ምላሾች የተገኙ አስተያየቶች ከሞላ ጎደል፣ አንዳች ርምጃ ካልተወሰደ የኢትዮጵያ የሙስና እና የአሰተዳደር ብልሹነት ችግር ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሄድ የሚያስጠነቅቁና “ወዮልን” የሚሉ ማሳሰቢያዎች የታከሉባቸው ናቸው። የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ እንደሚሠሩ የጠቀሱ መላሾችም፣ በዕለት ተዕለት ተግባራቸው የችግሩን አስከፊነት እየታዘቡ እንደሚኖሩ ተናግረዋል። ከችግሩ ስፋት አንጻር ሕንጸት እንዲህ ያለውን መጠይቅ በማዘጋጀት ጥናት ለማድረግ መነሣቱን የሚያመሰግኑ ቢኖሩም፣ ተጨማሪና ስፋት ያላቸው ሥራዎች መሥራት እንደሚያስፈልግ ዐሳብ ያካፈሉ መላሾች አሉ።

አብዛኞቹ አስተያየቶች የሃይማኖት ተቋማት (በተለይም ቤተ ክርስቲያን) ተጠያቂነት የሚሰማው፣ ግብረ ገብነት ያለው ትውልድ በማፍራት፣ እንዲሁም በጸሎት ፊተኛ ሆና መምራት እንዳለባት የሚወተውቱ ናቸው።

ስለ ዘፈን

ዘሪቱ ከበደ በሕንጸት ድረ ገጽ ላይ ለንባብ ባቀረበችው በዚህ ጽሑፍ፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ እስከ አሁን በዘለቀው የዘፈን ጕዳይ ላይ ብያኔዋን ትሰጣለች። “ይህን ጕዳይ ሳነሣ ለዘፈን ጥብቅና ልቈም ፈልጌ አይደለም። ይሁን እንጂ፣ እውነትን መናገርም ሆነ መነጋገር አስፈላጊ እንደ ሆነ ደግሞ አምናለሁ።” የምትለው ዘሪቱ፣ ወደ ጌታ የመጣችበትን ሂደትና የተለማመደችውን መንፈሳዊ ሕይወት እያስቃኘች፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ በርእሰ ጕዳዩ ላይ ሊኖረው ስለሚገባ ግንዛቤ ዐሳቧን ታካፍላለች፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው ያለቻቸው ማስረጃዎቿንም ታቀርባለች። በዚህ ብቻ አታበቃም፤ በሙዚቃ ጥበብ ውስጥ መዝለቅ የሚሹ ክርስቲያን ወገኖች ሊኖራቸው ስለሚገባ መንፈሳዊ አመለካከትና መውሰድ ስለሚጠበቅባቸው ጥንቃቄ የምክር ቃል ታካፍላለች።

ተጨማሪ ያንብቡ

መሪነትም እንደ ውበት

ለመሆኑ፣ የየቤተ ክርስቲያኑ መሪዎች አንድን የአመራር ዘይቤ በሚመሯት ቤተ ክርስቲያን በሥራ ላይ እንዲውል ካደረጉ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች እንዳሰቡት የአመራር ዘይቤውን ውጤታማነት ማየት ቢቸግራቸው ምን ማድረግ ይችላሉ?

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.