[the_ad_group id=”107″]

ለዋጭ ለውጦች!

ሁላችንም ባለ ታሪኮች ነን። ታሪኮችንን የተገነቡት ደግሞ በእለት ተእለት ገጠመኞቻችን እና ለእነዚህ ገጠመኞቻችን በምንሰጠው ምላሽ (response) እና ትርጉም (meaning) ላይ ተመሥርተው ነው። የሕይወት ገጠመኞቻችን ደግሞ መልካቸው ብዙ ነው፤ በአንዳንዶቹ ፈንድቀናል፤ በሌሎቹ ተከፍተናል። ፍንደቃዎቻችን እና መከፋቶቻችን ትተው በሚሄዱት አሻራ ልክም ይለያያሉ። የአንዳንዶቹ ትውስታ ከቀናት አይዘልምና ከትውስታ ማኅደር እንዲወጡ “ትዝ ይልሃል” የሚል አስታዋሽ የግድ ይፈልጋሉ። ሌሎቹን ለመርሳት ጥረን እንኳ አይሳካም፤ ሁሌ ትኩስ ናቸው፤ አብረናቸው እንተኛለን፤ አብረናቸውም እንነቃለን።

ለዋጭ ለውጦች በስሜታችን፣ በአስተሳሰባችን እንዲሁም በማኅበራዊ ግንኙነታችን ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ መሠረታዊ (fundamental) የሚባል ነው። የተጽእኖዋቸው ጥልቀት፣ ሕይወታችንን ከእነዚህ ክስተቶች በፊት (ቅድመ) እና በኋላ (ድኅረ) ብለን እስክንከፍለው ያደርሰናል። እኚህ ለውጦች ለሁሌው ለውጠውን ያልፋሉና ሕይወት ለዋጭ ክስተቶቹን (transformative events) እና ተጽእኖዎቻቸውን ሳያውቁ እኛን እናውቃለን ማለት በርግጥም ዘበት ነው። ከሌሎች ጋር ያለን የመተማመን የሚለካው እኚሁን ክስተቶች ለማካፈል ውስጣዊ ድፍረትን በመጎናጸፋችን ልክ ይሆናል።

ማን ይለካው?


በዚህ መጣጥፍ የትኩረት አቅጣጫችን እስክንጠየቅ ሳንጠብቅ ለመናገር የምንሽቀዳደማቸውን የስኬት ክስተቶችን አይደለም። ስኬት እንደ ተጣለ ግዳይ በወዳጅም ሆነ በጠላት ፊት የምንኩራራበት እንጂ ማንም እንዳያይብኝ ብለን የምንሸፋፍነው ጉዳይ አይደለም። ትኩረታችን ሳንናገራቸው በብቸኝነት ስለምንብሰለሰልባቸው የእጦት ክስተቶች (events of loss) ላይ ይሆናል። የእጦት ክስተቶች ስሜታችንን ያለ ልክ የናጡና የረበሹ (traumatic)፣ ውስጣችንን እጅጉን የወጠሩ (stressful) እና አንዳንዴ ደግሞ መልሰን የማንነሣ እስኪመስለን ያንኮታኮቱንን (crises) ክስተቶችን ያካትታል።

የእጦታችን ጥልቀት ሚዛኖች በአብዛኛው የራሳችን ግላዊ ፍርድ (subjective) ሲሆን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌሎቹም ሁሉ ጉዳታችን የሚስማሙበት (objective) ይሆናል። ለግለኛ ፍረጃ፣ የማይታረቅ ቅራኔ ተከትሎ የተከወነ ፍቺን ማንሣት እንችላለን። ፍቺው በተፋቺዎቹ ላይ የፈጠረውን ጠባሳ እና እስከ ዛሬ ድረስ የሚጠዘጥዘንን የልብ ቁስል ሌሎች አቃልለው ሊያዩት ይችላሉ። ለተፋቺዎቹ ግን ገና ያልጠገገ ቁስል መሆኑን መካድ አይቻልም። ሌላው የእጦትን ስሜት ጥልቀት አልተሰማውም ማለት ተጎጂዎቹ አጋነናል ተብሎ መወሰድ የለበትም! መጋቢት 1፥ 211 ዓ.ም. ላይ የመከስከስ አደጋ የደረሰበት ቦይንግ 737-8 የፈጠረውን እጦት ታላቅነት አስመልክቶ ባለ ኅሊና ሁሉ እንደ መስማማቱ የሚዛን ልዩነት ላይኖር ይችላል።

የአንዳንድ እጦቶቻችን ጥልቀቶች ማንም ሰው ሊያጽናናን እስካይችል ድረስ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑን ሰዎች ከቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ማስታወስ እንችላለን። የልጁን የተበጫጨቀ እና በደም የተነከረ ልብስ ተመልክቶ ያዘነው ያዕቆብ ስላጣው ልጁ ያለው፣ “ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እውርዳለሁ” ነበር (ዘፍ 37፥32-35)። ለያዕቆብ የልጁን ማጣት ዜና የጥቂት ቀናት ሳይሆን፣ እስከ ሞቱ ድረስ የሚከተለው ክስተት መሆኑን ተገንዝቧል። በራማ ልጆቹዋን ያጣችው ራሄልም የተባለላት “ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች” (ኤር 31፥15) ተብሎላታል። መጽናናትን እንቢ ብሎ ከሦስቱ ወዳጆቹ ጋር የተከራከረው ጻድቁ ኢዮብ አንዳንድ እጦቶች በቀላሉ የማንጽናናባቸው እና ሕይወታችንን ለሁሌው ለውጠውት የሚያልፉ መሆናቸውን የሚያመለክት ዋቢ ምስክር ነው።

ገሚስን ማጣት

እጦቶች ሁሉ እኩል አይደሉም። የእጦታችን ጥልቀት የሚለካው ካጣነው ሰው ወይም ከነገረ ጉዳዩ ጋር የተጣመርንበት ቀደምት የስሜት ተጋምዶ (emotional investment) ጋር ተያይዞ ነው። የስሜት ትሥሥራችን ለነገሩ ወይም ለሰው ያለንን መሰጠት ያመለክታል። ስሜታዊ ትሥሥር ሲኖረን ነፍሳችን ከሌላው ሰው እና ከምንከውነው ነገር ጋር ይተሳሰራል፤ ሳናውቀው ከሁለትነት ወደ አንድነት እናድጋለን። መጋመዳችን ጥልቀቱ፣ እኛን ሳይነኩ፣ የተሣሠርነው መንካት የማይቻል ያደርገዋል። ከዚህም የተነሣ እጦታችን ከእኛ ውጭ የሆነ በቸልተኝነት የምንመለከተው ድርጊት አይደለም፤ ከማንነታችን ላይ ሳንወድድ የተገመሰ ክፋያችን ይሆናል። እንዲህ ዐይነቱን እጦት፣ ከአሰላስሎዋችን ሆነ ከትውስታችን ብንፈልግ እንኳ በቀላሉ የሚባረር አይሆንም። አንዳንዴ እንደውም ሆን ብለን እጦታችንን ትውስታችን ውስጥ ልናቆየው እና በሕይወታችን ያለውን ዋጋ ልናሰላስልም እንፈልጋለን። የሚወዷትን ሚስታቸውን ድንገት የተነጠቁ ባሎች፣ አባቶቻቸውን ያጡ ልጆችን እናስብ። ማናቸውም ሚስቶቻቸውን ሆነ አባታቸውን ከትውስታ ማኅደራቸው ማስወገድ አይፈልጉም፤ ይልቁኑ ከዚሁ ከሚያመው እጦታቸው ጋር የሕይወት ትርጉማቸው አስተካክለው መኖርን ይፈልጋሉ።

ምን ሊረባን?


የእጦት ታሪኮቻችንን እናካፍል የሚል ሐሳብ ጥያቄ ማስነሣቱ አይቀርም። ከእነዚህ ጥያቄዎች ዋንኛው “ምን ሊረባን?” የሚል ነው። የሥነ ልቦና ባለሙያዎች የእጦት ታሪኮቻችንን ለሌሎች ማካፈል እንዳለብን ሲነግሩን ምክንያት አላቸው። የመጀመሪያው ምክንያት፣ ሰዎች ታሪኮቻችንን እንዲሸፋፈኑ ሳይሆን እንዲነገሩ እንፈልጋለን። እጦታችንን ያመጡትን ክስተቶች መግለጽ መፈለግ፣ የምንችለውን ያህልም ምክንያቱን ለማብራራት መጣር፣ ተያያዥነት ያላቸው ስሜቶች እና የማንረዳቸው ውስብስብነቶችን መተንፈስ መፈለግ የሰውነታችን አካል ነው። አሊያ ደግሞ ውስጣችን ውጥር ብሎ ልንፈነዳ የደረስን ይመስለናል፤ ጭንቀታችንንም መሸከም ሲያቅተንም ለሥነ ልቦናዊ እና ለአካላዊ ሕመሞች መጋለጣችን አይቀርም።

ከውድቀቶቻችን ጋር ተያያዥነት ያላቸው ክስተቶች ዝርዝራቸው ሳይነገር፣ ሳይብራሩ፣ ውስብስብነታቸውን ሳናስረዳ ከቀረን የስሜት ጉዳታችንን ሳይታወቅ ውስጣችን እየተብሰለሰለ በሐሳብ እናነክሳለን። ነገራችን ወይ አይቋጭ አሊያም አዎንታዊ በሆነ መልኩ ተርጉመነው ወደ ፊት ለመጓዝ አይረዳንም። ታሪካችንን ሳንናገረው በቀረን ቁጥር፣ ከሰውነታችን ጋር ግጭት ውስጥ መውደቃችን አይቀርም። የዚህ ምክንያት ደግሞ ሰው መሆን የሚነገር ታሪክ ባለቤት መሆንና ያንኑ ታሪክ ከመናገር ጋር የተያያዘ ከመሆኑ የተነሣ ነው። እጦትን መናገር ውድቀትን ማሞገስ ሳይሆን እውነት መሆኑን መቀበል ነው። የሚያመው ታሪካችን ሲነገር፣ በአብሮነት የምንጎናጸፈው ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ አለ፤ ውስጣችን እንደ ገና ሊታደስ እና ለሥራ ይነሣሣ ይጀምራል። የድካም እና የማጣት ታሪካችንን የምንናገረው ተናግረን እንዲቀለን ብቻ ግን አይደለም፤ ሌሎችም ምክንያቶች አሉን።

በእኛ ጫማ ሆኖ ያለ ፍርድ የሚሰማ እና ምሥጢርን የሚጠብቅ ሰው ከተገኘ መናገር ሌሎች ጥቅሞችም አሉ። ርግጥ ነው፤ የእጦት ስሜቶቻችንን ለመግለጽ ሁሌ የሚሰማን ሰው አያስፈልግም፤ ምናልባትም በጽሑፍ ልንከትባቸውም እንችላለን። ለመተንፈስ ብቸኛው አማራጭ ሰው ብቻ ባይሆንም፣ የሚያምኑት ሰውን የሚተካ አለመኖሩ ርግጥ ነው! እኚህን ታሪኮቻችንን በተነፈስናቸው ቁጥር፣ የሆነብንን ነገር አስመልክቶ የዕይታ አድማሳችን ለመስፋት ዕድል ይኖረዋል። የእጦት ታሪኮችን ስናካፍል ስለ ራሳችን ያለንን ምልከታ፣ አሁን እያሳሰቡን ስላሉ ጉዳዩች፣ ስለ ወደፊት የሕይወታችን እጣ ፈንታ አስመልክቶ አዳዲስ ዕይታዎችን የምናገኝበት ዕድል እናገኛለን። እኚህ አዲስ ምልከታዎችን የምንቀናጀው የሚሰማን ሰው ስለምናስበው እና ስለሚሰማን ነገር በሚጠይቀን ጥያቄዎች በኩል እንጂ፣ ንግግራችንን ተከትሎ በሚያዥጎደጉዳቸው ምክሮች አይደለም። የእጦት ታሪኩን የሚናገር ሰው ከምንም በፊት የሚፈልገው አድማጭ ጆሮ መሆኑን ማወቅ እንረዳለን ብለን የምናስበውን ሰውን እንዳንጎዳ ይግዘናል።

ከእጦቶቻችን ጋር ተያይዘው የሚንጡን አሉታዊ ስሜቶቻችን በንግግሮቻችን ውስጥ ሲገለጡ፣ የስሜቶቻችንን ጥልቀት አብልጠን እንድንረዳው ይሆናል። በሂደቱም እጦቱን ከመካድ ወደ ማመን እና አሉታዊ ተጽእኖውንም ለመቀነስ አቅም እናጎለብታለን። ያጣውን ነገር ስንተነፍስ፣ ለእጦታችን እውቅና እየሰጠን ነው። እጦታችንን እውቅና ስንሰጥ ክስተቶቹ ያደረሱብንን አሉታዊ እና አዎንታዊ ውጤቶችንም እንገነዘባለን፤ እንዴትም ማለፍ እንዳለብን እናውቃለን።

የእጦት ታሪኮቻችንን መናገር ሌላም ጥቅም አለው። እነዚህ ታሪኮቻችን ሲተረኩ አዋዋይ (company) አግኝተናል ማለት ነው። የሚያወሩት እና የሚያደምጥ ሰውን ማግኘት በራሱ የሚፈጥረው የአብሮነት ስሜት አለ። በሕይወት ጎዳና ለብቻችን ተለይተን እንዳልተጠቃን፣ ዛሬም በአብሮነት ሊጓዝ የሚፈልግ ሰው መኖሩን እንገነዘባለን። ታሪካችንን ስናካፍል መጽናናት (solace) የምንችልበት ዕድልና አብሮነት የሚፈጥረውን ጥንካሬም (solidarity) እንጎናጸፋለን። ሐሳባችንን እና ስሜታችንን ስናካፍልም፣ በምላሹ እነዚህን ክፉ እና ከባድ ቀናት ለማለፍ የሚያስችሉ መንገዶችንም የምናገኝበት ዕድልም ይፈጠራል። ተመሳሳይ ክስተቶችን ካስተናገዱ ሰዎች ጋር እነኝህን ታሪኮቻችንን ከተለዋወጥን ደግሞ ጠንካራ ልባዊ ትሥሥር የምናደርግበት ዕድልም ይፈጠርልናል። ሰዎች የእጦት ታሪኮቻችንን በአክብሮት ሲያደምጡን ስንመለከት፣ በምንም ውስጥ ብናልፍ እኛውኑ የሚገነዘቡ እና የሚቀበሉን ሰዎች መኖራቸውን እንረዳለን።

ያጣነው ጆሮ


ጥሩ አድማጭ ይጠይቃል። ጥያዌዎችን የሚጠይቅበት ምክንያት፣ የእጦት ታሪኮቻችን ንግርት፣ ለተራኪው እረፍት እንዲሰጥ ከተፈለገ ሁለት ነገሮችን እንዲያካትቱ ያስፈልጋል። አንደኛው፣ ክስተቱ በዝርዝር እንዲብራራ ስለሚያስፈለግ ነው። ስለዚህም በታሪኮቻችን ውስጥ የሆኑ ክስተቶች እና ደርጊቶች በዝርዝር እንዲነገሩ ማበረታታት የሻል። እኚህን ጥያቄዎች ስንጠይቅ ታዲያ መርማሪ (interrogator) እንዳንመስል መጠንቀቅ ይኖርብናል። ስለዚህም ከክስተቱ ጋር ተያይዞ ማን፣ እንዴት፣ የት፣ መቼ እና ምን የሚሉት ጥያቄዎችን በጥንቃቄ ማንሣት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ታሪክ የራሱ ዐውድ ያለው እንደ መሆኑም መጠን፣ ትርክቶቹ የክስተቱን ሂደት፣ ቀደምት ጉዳዮች እና ተከታይ ነገሮችን ማወቅም ለሰፊ ግንዛቤ ይረዳል።

የሚተረከው ታሪክ፣ ክስተቶችን ዘርዝሮ ማብቃት የለበት። ትርክቱ ክስተቱ በተራኪው ላይ ያደረሰውን ውስጣዊ ተጽእኖ ማካተት ያስፈልገዋል። እኚህ ውጫዊ ክስተቶች ከእኛነታችን ጋር በብርቱ የተጋመዱ እንደ መሆናቸው መጠን በውስጣችን ላይ የሚጥሉት የራሳቸው ጠባሳ አለ። ስለዚህም፣ ታሪኮቻችን ሐሳባችን፣ ስሜቶቻችንን እና ትርጉማችንን በምን መልኩ እንደለወጡት ጭምር ባለ ታሪኮቹ እንዲናገሩ ማበረታታት ያስፈልጋል። ጥያቄን ማንሣት ደግሞ በውስጣችንን የሆነውን ነገር ለመረዳት የተዋጣለት መንገድ ነው።

ታሪካችንን የሚያደምጥ ሰው በዋነኛነት ሰሚ ነው ማለት ለንግግሮቻችን ግድ አይኑረው እና ቸልተኛ ያሳይ ማለታችን አይደለም። በንግግሮቻችን ውስጥ በተደጋጋሚ የሚታዩትን ዋንኛ ጭብጦች (key teams) እንደ ንቁ አድማጭ (Active listener) ለመረዳት ይጥራል። እንደ እድማጭ ተራኪውን ሊጎዱ የሚችሉ አደገኛ አስተሳሰቦች እና አመለካከቶችን (problematic thoughts and beliefs) ከትርክት ውስጥ ማድመጥም አንዲሁ የሰሚው ኀላፊነት ነው። እኚህን የእጦት ውጤቶች ስንሰማ፣ አሰማማችን ለባለታሪኩ ያለንን አክብሮት የሚያንጸባርቅ ሊሆን ይገባዋል። በየመሀሉ እየገባ የራሱን አስተያየት መስጠት የሚፈልግ ውስጣዊ ጉትጎታችንን መግዛት ትኩረታችንን በተራኪው ላይ ማድረግ እጅጉን ያስፈልገናል። አሰማማችን የታይታ ሳይሆን ከልባዊ መሰጠት መንጭቶ፣ የባለ ታሪኩ የሚሰማውን ስሜት እንዲሰማን ብሎም እንድንረዳ ሊረዳን ያስፈልጋል።

የእጦት ታሪኮችን ደፍሮ ለሌላ ሰው ከውስጥ ስሜት ጭምር መናገር ትልቅ ወኔ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን አድማጭ መገንዘብ ይኖርበታል። የዚህ አንድምታ በታሪኩ ማጠቃለያ ላይ ይህንኑ ድፍረት ማወደስ (praise) እጅጉን ይጠቅማል። ከነገሩ ጋር ተያይዞ እኛም የተሰማንን ስሜት እና ከታሪኩ የተማርነውን ነገር በጥንቃቄ ማካፈልም እንዲሁ አስፈላጊ ነው። ምናልባትም ተመሳሳይ ክስተቶች ውስጥ አልፈን ከሆነ፣ የእኛውኑ ታሪክ ወዲያውኑ ለመናገር መቻኮል አያስፈልገንም። የእኛውኑ ታሪክ ስንናገር ጥንቃቄ የንግግር ልውውጣችን የትኩረት አቅጣጫ ከተራኪው ወደ ሰሚው ታሪክ እንዳያዘነብል መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሁል ጊዜ ራሳችንን ማስለመድ ያለብን ነገር ዋንኛው የትኩረት አቅጣጫ ተራኪው እንጂ እኛ ሰሚዎቹ አለመሆናችንን ነው። ሰሚ ያጡ ክስተቶችን መስማት የሚችል ባልንጀራ እንድንሆን አምላክ ጸጋውን ያብዛልን!

Share this article:

ኢትዮጵያ የ“አረማዊ ደሴት”?


የእሬቻ በዓል በክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ መካከል መነጋገሪያ ሆኖ እንደ ሰነበተ ተከብሮ ዐልፏል። በዓሉ ተከብሮ ይለፍ እንጂ፣ መነጋገሪያነቱ አልቆመም፤ ምናልባትም ለመጭዎቹ ዘመናት እንዲሁ መነጋገሪያ እንደ ሆነ ይቀጥል ይሆናል። ባንቱ ገብረ ማርያም፣ “ኢትዮጵያ የ ‘አረማዊ ደሴት’?” ሲሉ የሰየሙት ይህ ጽሑፍ፣ በሮም ግዛት ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች፣ እንዲህ ላለው የአደባባይ በዓል የሰጡትን ምላሽ በታሪክ መነፅር እያስቃኙ፣ ለዛሬ ክርስቲያኖች መልእክት ያቀብላሉ። የባንቱ ገብረ ማርያም ጽሑፍ፣ የእሬቻ በዓልን በሚመለከት ለሚካሄደው ውይይት መፋፋት የራሱ ፋይዳ አለው በሚል እንደሚከተለው ለንባብ በቅቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ

“የሁላችን ድርሻ ተጠራቅሞ ነው ውጤት ያመጣነው”

ዘላላም አበበ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስትያን ተማሪዎችና ምሩቃን ማኅበር (ኢቫሱ) ውስጥ ለረጅም ዓመታት አገልግሏል፡፡ ለአራት ዓመታት በደቡብ አካባቢ የኢቫሱ ቢሮ በሙሉ ጊዜ አገልጋይነትና የአካባቢው ቢሮ አስተባባሪ በመሆንና ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ለዘጠኝ ዓመታት ደግሞ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ በመሆን አገልግሎ በቅርቡ በራሱ ፈቃድ የዋና ጸሐፊነት ሥራውን አስረክቧል። ወንድም ዘላለም በትምህርት ዝግጅቱ ከአዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ እርሻ ኮሌጅ በእርሻ ሥራ እንዲሁም ከኢቫንጄሊካል ቲዮሎጅካል ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪውን በነገረ መለኮት ያግኝቷል። ዘላለም በአሁኑ ሰዓት አሜርካን አገር በሚገኘው Gorden Conwell Theological Seminary በሥነ አመራር የድኅረ ምረቃ ትምህርት በመመላለስ እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በኢቫሱ ውስጥ በነበረው አገልግሎቱና በተያያዙ ጉዳዮች አስናቀ እንድርያስ ከዘላለም አበበ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

ለግብ መብቃት

“መጽሐፍ ቅዱስ ከነገር ጅማሬ ይልቅ ለነገር ፍጻሜ ከፍተኛ አጽኖት ይሰጣል። ለፍጻሜ ትኵረት የመስጠቱም ምክንያት ብዙዎች ከጠራቸው ከእግዚአብሔር ጋር ጕዞ እንደሚጀምሩ፣ ነገር ግን በጀመሩበት ፍጥነትም ሆነ ቅናት እንደማይቀጥሉ፣ ከዚያም ዐልፎ ከመሥመር እንደሚወጡ ለማሳየት ነው።” ይልቃል ዳንኤል

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.