[the_ad_group id=”107″]

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ መንግሥትና ሕዝብ ልብ ልንል የሚገባቸው ነጥቦች

በታሪኳ ዕርዳ

ሰላም! ስሜ ታሪኳ ሲሆን፣ በአሜሪካ ውስጥ በኒውዮርክ ከተማ የዶክትሬት ተማሪ ነኝ። በአሁኑ ሰዓት ከተማው የኮሮና ቫይረስን መተላለፍ ለመግታት ከቤት እንዳትወጡ ብሎ ባስተላለፈው ምክር መሠረት ከቤት የማልወጣ ቢሆንም፣ ቀን ከሌት ሐሳብ የሆኑብኝ የበሽታው ኢትዮጵያ መግባት እናም “ከዚህ በኋላ ቤተ ሰቦቼን አገኛቸው ይሆን? መቼ?” የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው። በርግጥ ከመንግሥት አልፎ በቴሌግራም፣ ዋትስአፕ፣ ትዊተር በመሳሰሉት ብዙ ሰዎች ሲንቀሳቀሱ በማየቴ ተስፋ ሰጥቶኛል። ሆኖም ግን ከቤተ ሰቦቼ እና ከጓደኞቼ ጋር በማደርጋቸው የስልክ ግንኙነቶች እንዲሁም ከምከታተለው ዜና ለወረርሽኙ ሰፊው ኅብረተ ሰብ በቂ ትኩረት እንዳልሰጠው ስለሚሰማኝ ነው፤ በተለይ በተለይ ማኅበራዊ መራራቅን አስመልክቶ።

ጣልያን እና አሜሪካ፣ ሌሎችም የበለጸጉ አገራት የሳይንቲስቶችን ማስጠንቀቂያ ችላ ከማለት አልፎ ምርመራዎችን በቶሎ እና በብዛት ባለማድረጋቸው ብዙ ሕይወት ተቀጥፏል። ወረርሽኙ ኢትዮጵያ እንደ ገባ በምርመራ የተረጋገጠው ከሳምንት በፊት ቢሆንም የዛሬ ሁለት ሦስት ሳምንት እነዚህ የበለጸጉ አገራትም እንደኛ በጣት የሚቆጠሩ ሕመምተኞች ብቻ ነበሯቸው። ቫይረሱ ድንበር ሳይለይ በየአገሩ በተመሳሳይ መልኩ ነው የሚራባው። ስለዚህ ከእነሱ ልምድ በመውሰድ ኢትዮጵያ የእነዚህ አገራት ዕጣ ፈንታ እንዳይደርሳት ምን ማድረግ እንደምንችል ለመጠቆም ይህንን በጥናት በተረጋገጠ መረጃ የተደገፈ ጽሑፍ ላጋራችሁ ወድጃለሁ። ማንንም ለማስፈራራት ወይንም ለማስጨነቅ አይደለም፤ መረጃ ለማስታጠቅና ፈጥነን ካልተንቀሳቀስን ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሌሎችን ልምድ ለማካፈል እንጂ። ወረርሽኙ የሁሉንም ሰው ትብብር ስለሚጠይቅ ለእኔ አንድ ሰው ብቻ እንኳን አይቶት ትምህርት ቢወስድ እና ባሕርይውን ቢቀይር፣ ብሎም ሌሎችን አስተባብሮ በኅብረተ ሰቡ/መንግሥት ደረጃ እንቅስቃሴ ቢያደርግ ታላቅ ደስታዬ ነው። ሳይቃጠል በቅጠል አይደል የሚባል?!

ወጣቶች ቫይረሱን ከጉንፋን መጠን ቆጥረው ወይንም በወጣትነታቸው ተመክተው መናቅ የለባቸውም

አንዳንድ ወጣቶች በወጣትነታቸው ተመክተው ወይም ቫይረሱን እንደ ቀላል ጉንፋን አይተው ይንቁታል። በእውነቱ ቫይረሱ ወጣቶችና በተለይ ሕፃናት ላይ የሚያስከትለው ሕመም አዛውንትና እንደ አስም፣ ካንሰር የመሳሰሉት ሌላ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ላይ ከሚያስከትለው ሕመም አንጻር ቀለል ያለ ነው። ሆኖም አንዴ ቫይረሱ ከያዛቸው በኋላ እነሱ ምንም ምልክት ሳያሳዩ ቫይረሱ የበለጠ ለሚያጠቃቸው አዛውንትና ሌላ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ሊያጋቡ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች የእኔና የእናንተ፣ የሁላችንም ወላጆች ወይም አያቶች፣ አክስትና አጎቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ቸልተኝነቱ ኋላ ወደ ቁጭት እንዳይቀየር መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ወጣቶች በቫይረሱ ምክንያት በጣም በኀይለኛው ሊታመሙ እንደሚችሉ ብሎም ከዳኑ በኋላ የሳንባቸው አየር የመያዝ አቅም እስከ ሠላሳ በመቶ ድረስ ልቅንስ እንደሚችል ጠቅሰዋል፤ ይህም ማለት እንደ ቀድሞው ጥልቅ ትንፋሽ መተንፈስ፣ ስፖርት መሥራት አይችሉም ማለት ነው። ስለዚህ ያልጠረጠረ ተመነጠረ እንዳይሆን በማንኛውም ዕድሜ ያለ ሰው መጠንቀቅ አለበት።

በስብሰባዎች ላይ የተደረገውን እገዳ አጠንክረን እንዲሁም የማኅበራዊ አኗኗር ባህላችንን ለዚህ ጊዜም ቢሆን ከማኅበራዊ መራራቅ መርሖዎች ጋር ማቻቻል አለብን

አንዲት እድሜዋ የገፋ አክስቴን ከቤት እንዳትወጣ ስመክራት “እንዴ ልቅሶና ክርስትና እንዴት ብዬ እቀራለሁ? ይሉኝታውስ??” አለችኝ። ትላልቅ ስብሰባዎች ቢከለከሉም ይህ ውሳኔ የኅብረተ ሰቡ ማኅበራዊ ኑሮ ድርና ማግ የሆኑ ስብሰባዎችን (ለምሳሌ ልቅሶ፣ ሠርግ፣ ክርስትና የመሳሰሉት) እንደሚያጠቃልል ግልጽ አልተረደገም። ሆኖም ጣልያናውያን በቶሎ ወረርሽኙን ባለመግታታቸው አሁን ሁሉም ሰው ከቤት እንዳይወጣ በመንግሥት ታዞ እንኳን ልቅሶ ሊሄዱ ቀርቶ፣ ሟች ቤተ ሰቦቻቸውን ለመቅበርም አልቻሉም። ከዚህም ብሶ ሆስፒታሎቻቸው ከመጠን በላይ በቫይረሱ ታማሚዎች ስለተሞሉ በጠና የታመሙ ዘመዶቻቸውን ወደ ሆስፒታል መውሰድ ሳይችሉ እዛው በመኖሪያ ቤታቸው ሬሳ ሸሽገው የተቀመጡም አሉ። አዎ፤ አያድርስ ነው! ከዚህ ሁሉ መከራ አንዳቸውም እንዳይከሰቱብን ከአሁኑ ስብሰባዎችን (ልቅሶና ሌሎች ማኅበራዊ ስብሰባዎችን ጨምሮ) በጥብቅ ማገድና ለሕዝብ ማሳወቅ ከመንግሥት ይጠበቃል።

በዓለም ዙሪያ ብዙ ሙሽሮች ሠርጋቸውን በወረርሽኙ ምክንያት ሰርዘዋል። በኢትዮጵያ ያሉ ከትንሣኤ በዓል በኋላ ጋብቻቸውን ለመፈጸም የሚያስቡ ጥንዶችም የእንግዶችን ቁጥር በደንብ ለመቀንስ፣ ካስፈለገም ለመግፋት ከአሁኑ ቢያስቡበት ያዋጣል።

ስለዚህ ማኅበራዊ መራራቅን በሰፊው ለመተግበር መንግሥት ግልጽ እና ጠንካራ መልእክት ማስተላለፍ አለበት። በተጨማሪም የግለ ሰቦች፣ ዕድሮች፣ ዕቁቦች እና የሃይማኖት ተቋማት ትብብር ያስፈልጋል። እባካችሁ ሁሉንም ደጋሾች ከለቀስተኞች እስከ ሠርገኞች ታዳሚዎቻቸውን (በተለይ ከቅርብ ቤተ ሰብ ውጭ ያሉትን) ጤናቸውን እንዲያስቀድሙና እንዳይመጡ እንዲያበረታቱ ንቃተ ኅሊና እንፍጠር። ለዚህ ዐጭር ጊዜ ይሉኝታን ሳይሆን መተሳሰብን እና መተባበርን አስቀድመን ወረርሽኑን እንግታ፤ ሕይወት እናትርፍ።

ማኅበራዊ መራራቅ ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እጅ ወደ አፍ ኑሮ ጋር አይጣጣምም የሚል ስጋት አለ

እስከ አሁን በተነገረው መሠረት 9 ሰዎች “ብቻ” ናቸው በቫይረሱ የተያዙት። ከእነዚህም አብዛኞቹ እያገገሙ መሆኑ ተያይዞ ተገልጿል። ሆኖም ግን በዚህ ዘገባ መዘናጋት አይገባንም። ጣልያንና አሜሪካ አንድም ለዚህ ከባድ ደረጃ የተዳረጉት በቶሎ እና በሰፊው ለሰዎች ሁሉ ምርመራ ባለማድረጋቸው ነው። በተቃራኒው ደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን ለብዙ ሰዎች በጊዜ ምርመራ በማድረጋቸው ወረርሽኙን በተሻለ ሁኔታ ተቆጣጥረውታል። ስለዚህ እኛም ከመዘናጋት ይልቅ በቶሎ ምርመራን ለማስፋፋት እና ውጤቱ ሲመጣ ደግሞ በአንድ ጊዜ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር አሻቅቦ ከተገኘ እንዴት የሚቀጥለውን ምዕራፍ እንደምንወጣ ማሰብ አለብን። በዚህም ረገድ ሁሉም ሰው ቤቱ ይቀመጥ እስከ ማለት የምንደርስ ከሆነ የተለያዩ እንቅፋቶችን ከነመፍትሔዎቻቸው ከግምት ማስገባት አለብን።

ዋናው እንቅፋት የሚሆነው አብዛኛው የአዲስ አበባ ብሎም የኢትዮጵያ ነዋሪ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ያለው መሆኑ ነው። ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ሥራን ከቤት ሆኖ ስለ መሥራት እያወራን በነበረበት ሁኔታ ነው ይሄ ጉዳይ የተነሣው። ጓደኛዬ ከፍተኛ ማኅበራዊ መራራቅን መተግበር (ለምሳሌ ሁሉም ሰው ከቤት እንዳይወጣ ብሎ ማዘዝ) በእኛ ኅብረተ ሰብ ውስጥ የማይቻል ነው ብሎ ያስባል። ከዚህም ዐልፎ ከቤት አትውጡ ዐይነት ትእዛዝ ይህን ከእጅ ወደ አፍ የሚኖር ሕዝብ የገቢ ምንጭ ማሳጣት እና ለራብ/ሞት መዳረግ ነው የሚሉ ሥጋቶችም እንዳሉት ነገረኝ። ርግጥ ነው፤ የዚህ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ መስፋፋት እንደ ሌሎች ምእራባውያን አገሮች የሰሞኑ ጠንካራ ማኅበራዊ መራራቅ ሕጎች መተግበርን እጅግ ያከብደዋል። ሆኖም እነዚህ ሥጋቶች መንግሥትና ሕዝብ ቀድሞ ቢያስቡበት እና ቢተባበሩ ሊያስወግዳቸው የሚችላቸው ናቸው።

ቪዲዮ ስለ ማኅበራዊ መራራቅ፦

ከግለ ሰብ አንጻር የቤቱ ሁኔታ እና የሥራ መስኩ የሚፈቅድለት ሰው በተቻለው መጠን ሥራውን ከቤቱ ሆኖ ቢሠራ የራሱን ብቻ ሳይሆን የአዛወንቶችን ጨምሮ የብዙኃንን ሕይወት ያተርፋል። ከላይ ያለው ስለ ማኅበራዊ መራራቅን የሚተነትን ቪዲዮ እንደሚያሳየው የእያንዳንዱ ሰው እንቅስቃሴ መቀነስ፣ ሀብት መጠን፣ ጾታ ሳይለይ ሆስፒታሎችና የጤና ባለሙያዎቻችን ላይ የሚከሰተውን ሽክም ይቀንሳል። ይህም ማለት የጤና ማዕከሎቻችን፣ ባለሞያዎቻችንና ግብዓቶቻቸው (ለምሳሌ፦ አይ.ሲ.ዩ. ክፍሎች፣ የመተንፈሻ መርጃ ማሽኖች/ventilator ወዘተ) እጅግ ርዳታ ለሚፈልጉ አዛውንት፣ የሌላ በሽታ ተጠቂዎች እና በሥራቸው ዘርፍ ምክንያት ራሳቸውን እንደ ሌላው ቤታቸው ሊያገልሉ ያልቻሉ ሰዎች እንዲሁም ጎዳና ተዳዳሪዎችን ሊያገለግሉ ይችላሉ ማለት ነው። በዚህም የብዙዎችን ሕይወት መታደግ ይችላል፤ ሁሉም ሰው እንዳሻው በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ግን ተቃራኒው ይሆናል። ለምሳሌ ጣልያን ውስጥ ይህ ማኅበራዊ መራራቅ በቶሎ እና በአግባቡ ባለመተግበሩ ብዙ ዶክተሮችና ነርሶች የመሣሪያ እጥረት አጋጥሟቸው ከታማሚ ታማሚ እየመረጡ እንዲያክሙ ተገድደዋል (ለምሳሌ አንድ መሣርያ ብቻ ሁለት የ80 ዓመት ሰዎች እና አንድ የ40 ዓመት የኮሮና ቫይረስ ሕመምተኞች ካሉ፣ ከአዛውንቶቹ ይልቅ የበለጠ ሕይወቱ የመትረፍ እና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የመጥቀም ዕድል ያለውን የ40 ዓመት ሰው ለመርዳት መወሰን እንደማለት ነው፤ ይህም የሚሆነው ከከባድ የኅሊና ወቀሳ ጋር መሆኑን ልብ ይሏል)። ስለዚህ ሆስፒታሎቻችንን እና የጤና ባለሙያዎቻችንን ከዚህ ለመታደግ የሥራ ዘርፋችን፣ የኑሮ ሁኔታ የሚፈቅድልን ሰዎች ሁሉ ሥራችንን ከቤት ብንሠራ ይመረጣል። በተለይም አሜሪካ (ካሊፎርኒያ ውስጥ) እንደታወጀው አዛውንቶችንም በተቻለ መጠን ውጭ እንዳይወጡ እና ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ማረግ ይበጃል።

ይህን ሁሉ ስንል በሥራ ዘርፋቸው ምክንያት ቤት መዋል የማይችሉ ወይም ከዋሉ ደግሞ የገቢ ምንጫቸው የሚናጋ ወገኖቻችንን ደግሞ (ለምሳሌ የሱቅ ሠራተኞች፣ አስተናጋጆችና ሆቴል አገልግሎት ላይ የተሰማሩት፣ ሹፌሮች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ እና ጉልት ነጋዴዎች የመሳሰሉትን) መንግሥትና ሕዝብ በመተባበር ሊደጉሙ ይችላሉ። ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮም ርዳታ ለማድረግ እንዲቻል የስልክ መሥመር ሊከፍት ይችላል።

በተጨማሪም የሕዝቡ የምግብ አቅርቦት እንዳይቋረጥ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ለወራት አስቤዛ ገዝተው መዘጋጀት ለማይችሉ ወገኖች የሸማቾች ማኅበራትና ቀበሌዎች የማኅበራዊ መራራቅን መመሪያ በጠበቀ መልኩ (ለምሳሌ አሰላለፍን በማስተካከል እና በአንድ ጊዜ ሱቅ ወስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ሰዎችን ቁጥር በመገደብ) ማቅረብ ይቻላል። ብዙ ሰዎች አስቤዛ በሚገዙባቸው ቦታዎች፣ ከሰፈር ሱቆች እስከ ትላልቅ ሱፐር ማርኬቶች መንግሥት ዋጋ በመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን የንጽሕና መጠበቂያ (እንደ ፀረ ተዋስሕያን ያሉ) በማቅረብ፣ ለሕዝቡ የተራርቆ መሰለፍን ሥነ ሥርዐት በማስተማር አቅርቦቱ ሲቀጥል የሸማቶችንም የሻጮችንም ጤና በጠበቀ መልኩ የምግብ አቅርቦቱን ማስቀጠል ይችላል።

“ጥቁር አፍሪካውያን በቫይረሱ አይጠቁም” የሚል ሐሰተኛ ወሬ

አንዲት አክስቴ አብረዋት ከሚሠሩት ወጣቶች የተወሰኑት “እኛ ጥቁር ሰዎች በቫይረሱ አንያዝም/አንጠቃም” ሲሉ እንደ ሰማች ጠቅሳ ብዙም እንደማትጨነቅ፣ እኔም ብሆን ብዙ መጨነቅ እንደሌለብኝ ነገረችኝ። ይህ ወሬ በሳይንስ ደጋፍ የሌለው ውሸት እንደ ሆነ ሮይተርስን ጨምሮ ብዙ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ከጥቂት ቀናት በፊት ቢቢሲ እንደዘገበው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሁለት ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ውስጥ ሕይወታቸው አልፏል። ይህም ‘ጥቁር አፍሪካውያን በቫይረሱ አይጠቁም’ የሚለውን ወሬ ሐሰተኛነት አጉልቶ ያሳያል።
እባካችሁ ሁላችንም የመረጃ ምንጫችንን እያጣራን ይሆኑ፤ በተለይ እድሜያቸው ለገፋ እና የቴክኖሎጂ/ኢንተርኔት አጠቃቀም እውቀታቸው ሰፊ ላልሆነ ወገኖች መረጃ ስናካፍል እንጠንቀቅ፤ ሌሎችም ሲሳሳቱ እናስተካክል።

“እግዚአብሔር ይጠብቀናል”

እባካችሁ፤ ‘እግዚአብሔር ይጠብቀን’ ስንል ፈጣሪ የሚረዳንና የሚያድነን እንደ ሆነ ብናምንም፣ በቅድሚያ እንደ ሰው ኀላፊነታችንን በመወጣትና እርሱ በሰጠን ጥበብ ተጠቅመን ራሳችንን ከጉዳት መጠበቅ ፈቃዱ መሆኑን አንዘንጋ። የእኛን ኀላፊነትና ተግባር ገሸሽ አድርገን ሁሉን ለፈጣሪ ከመጣላችን በፊት፣ ከዓለም የጤና ድርጅትና ከመንግሥት መረጃ ምንጮች የተሰጡ መመሪያዎችን መተግበራችንን፣ ተአማኒነት ያለው መረጃ ለመቀበልና ለሌሎች በበጎ ፈቃድ ለማስተላለፍ ዝግጁነታችንን፣ ለጎረቤቶቻችንም ሆነ ለማናወቃችው የሰው ዘር በሙሉ ቸር ልቦና ይዘን መገኘታችንን አንርሳ። እንደውም ያለንን እውቀት፣ መረጃ፣ ገንዝብም ሆነ ንብረት ተጠቅመን ራሳችንንና ሌሎችን ለማዳን ስንሞክር እግዚአብሔር የበለጠ የሚደሰተው ያኔ ነው።


Tarikua Erda is a PhD student in Sustainable Development at Columbia University. I am passionate about human capital, health & development economics. Twitter: @TarikuaErda

Share this article:

ከታሪክ አልማር ብለን ይሆን?

“በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በወንጌላውያን አማኞች መካከል ያለውን ታሪካዊ የአግላይነት ውጥረት ይበልጡን የሚያከርሩ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሚዛንና ብስለት ያጡ አስተምህሮቶች እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የጐደላቸው ሥነ ምግባራዊ ቀውሶች መታየት ከጀመሩ ሰንብተዋል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በእነዚሁ ሁለት ታላላቅ ቤተ እምነቶች ውስጥ ያለው የእርስ በእርስ መከፋፈል፣ ጐሣዊና ፖለቲካዊ ጽንፈኝነትን የተላበሰ በመሆኑ፣ የአገሪቱን ፈርጀ ብዙ መከራ የበለጠ አክብዶታል።” ግርማ በቀለ (ዶ/ር)

ተጨማሪ ያንብቡ

የበዓለ ጥምቀት አከባበር በግብጽና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረገው ነገር ኹሉ የመታሰቢያ በዓል አዘጋጅቶ አምላክ የኾነው እርሱ ሰው በመኾን ያሳየውን ድንቅና በትሕትና የተሞላ ሥራውን በመዘከር እርሱን በእውነተኛ ልብ ማምለክና ማክበር መቻል መልካም ነገር ነው። ትልቁ ጥያቄ ግን በዚህ ውስጥ የበዓሉን ባለቤት ስንቱ ሰው አስታውሶት ይኾን?

ተጨማሪ ያንብቡ

የትንሣኤው ዐዋጅ

ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱ የሚታሰብበት የትንሣኤ በዓል በክርስቲያኖች ኹሉ ዘንድ በምስጋናና በዝማሬ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በኢኦተቤ ትውፊት መሠረት ከዘጠኙ የጌታ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱና ታላቁ በዓል የትንሣኤ በዓል ነው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ዘንድ በዓሉ አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመውን ጾም በማሰብና በመጾም፥ በመጨረሻም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም በአይሁድ እጅ የተቀበለውን መከራና ሥቃይ የሚያስታውሰውን ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሳምንት) በማስቀደም፥ በመጨረሻም ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውን ጌታ በዝማሬዎች በመወደስና ትንሣኤ ክርስቶስን በማወጅ ይከበራል። ልዩ ልዩ ሃይማኖታውያንና ባህላውያን ሥነ ሥርዐቶችም የበዓሉ አካላት ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.