[the_ad_group id=”107″]

ዴክሳሜታሶን እና ኮቪድ-19

የእግዚአብሔር ሰላም ለእናንተ ይሁን!

ጽሑፉን ከተረዳን በኋላ ስለ ዴክሳሜታሶን የተዛነፈ ግንዛቤያችንን እናርማለን፣ ከኮቪድ-19 መጠንቀቁን እንተጋበታለን፣ በሐኪም ያልታዘዘልንን ዴክሳሜታሶን ከመውሰድ እንታቀባለን፣ ለሌላ ሕመም የታዘዘላቸው በአቅርቦትና በዋጋ ጭማሪ እንዳይቸገሩ እንጠንቀቅላቸዋለን።

እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው የጽሑፉ ዐላማዎች መሆናቸው ነው።

ዴክሳሜታሶን በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ከሚታወቀውና የአስም ሕመምተኞች ከሚታከሙበት ከ“ፕሬዲኒሶሎን” (ሮዟ ኪኒን) ጋር ኮርቲኮስትሮይድ በሚባለው የመድኃኒት ቤተ ሰብ ውስጥ የሚገኝ ፀረ ብግነትና (Anti inflammatory) መድኅን አማቂ (Immunosuppressant) መድኃኒት ነው። በዚህ የመድኃኒት ቤተ ሰብ ሌሎችም በርካታ መድኃኒቶች ይገኛሉ። በዋናነት እንደሚያከናውኑት ሥራ በሁለት ንዑስ ቤተ ሰብ ይመደባሉም፤ ግሉኮኮርቲኮይድ እና ሚነራሎኮርቲኮይድ። ዴክሳሜታሶን አቅመኛና ከሞላ ጎደል ንጹሕ ግሉኮኮርቲኮይድ ሲሆን፣ አንድ ጊዜ ተወስዶ ለሰዓታት በሰውነት ውስጥ የሚቆይ ዐይነት ነው። ይህ ማለት በትንሽ ልክ ውጤታማ ይሆናል፤ በቀን ውስጥ ደጋግሞ መውሰድን አይጠይቅም፤ ሲያቋርጡት ቀስ በቀስ እየቀነሱ ባይሆንም እንኳ ብግነቱ ይመለስበታል ተብሎ አይፈራም፤ በዝቅተኛ ልክ ከተወሰደ በአካላችን ውኃንና አሸቦን የማቆር ጉዳት አያደርስም፤ ግሉኮስ (ስኳር) መጠንን በደም የመጨመር ዕድል ግን አለው1 ማለት ነው። ወደ አንጎል ጥሩ አድርጎ ይዘልቃል። በዚህ ቤተ ሰብ እንደሚገኙት እንደተቀሩት መድኃኒቶች ሁሉ በርካታ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፣ በተለየያየ መልክ ተዘጋጅቶ (እንክብል፣ በመርፌ፣ ወዘተርፈ.) ይገኛል።

ይህ መድኃኒት ጽኑ የኮቪድ-19ን ታማሚዎች ለማከም ሚና ሊኖረው እንደሚችል የሚያሳይ መረጃ ከሰሞኑ ወጥቷል2። የታማሚው ሰውነት ቫይረሱን የሚዋጋባቸውን (ከቫይረሱ መድኅን የሚያገኝባቸውን) ንጥረ ነገሮች (ሳይቶካይኖች) በተጋነነነ መጠን (የሳይቶካይኖች ማዕበል) እንዳይኖር በማሰናከል የታማሚውን ሳንባና ልብ እንዳይበግን ያደርጋል። በኮቪድ-19 ታማሚዎች ሳንባንና ልብን አበግነው አደገኛ የመተንፈስ ችግርን በማስከተል የእነዚሁ ንጥረ ነገሮች ማዕበል ተከሳሽ ነው3። ሳይቶካይኖች በቫይረስ የተጠቃውን ሴል ሕዋስ ለማስወገድ ሲጠቅሙ ማዕበል ደረጃ ሲደርሱ ግን ጤናማውንም ሕዋስ የማይምሩ ይሆናሉ ማለት ነው።

ከኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የተሰጠው መግለጫ እንደሚያመለክተው በሆስፒታል ከገቡ የኮቪድ-19 ታካሚዎች መካከል በቬንቲሌተር (በመተንፈሻ መሣሪያ) ኦክስጅን በተሰጣቸው በአንድ ሦስተኛ ያህል፣ በሌላ መንገድ የኦክስጂን ድጋፍ በተሰጣችው ደግሞ በአንድ አምስተኛ ያህል የመሞት ዕድል ቀንሶ ተገኝቷል። የመተንፈስ ድጋፍ ባልተሰጣቸው (ባላስፈለጋቸው) ግን ጠቅሞ አልተገኘም። ዩኒቨርስቲውም በድምዳሜው በመተንፈሻ መሣሪያ ኦክስጅን እየተሰጣቸው ያሉ ስምንት ያህሉን ወይም የኦክስጅን ድጋፍ ብቻ እየተሰጣቸው ያሉ ሃያ አምስት ያህሉን በዴክሳሜታሶን በማከም አንድ ሰው ከሞት ማትረፍ ይቻላል ይላል4

ተመራማሪዎቹ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱት በሆስፒታል መደበኛው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ከሚገኙ የኮቪድ-19 ሕመምተኞች መካከል “ዴክሳሜታሶን”ን ለ2 ሺህ ያህሎቹ ሰጥተው፣ ለ4 ሺህ ያህሎቹ ባለመስጠት በሁሉቱ መካከል በ28 ቀናት ውስጥ የሞቱትን ቁጥር በመቶኛ በማነጻጸር ነው። የባለመተንፈሻ መሣሪያዎቹ ሞት ዴክሳሜታሶን የተሰጣቸው 29.0% መደበኛ እንክብካቤ ብቻ የተሰጣቸው 40.7% የባለኦክስጅኖቹ ሞት ዴክሳሜታሶን የተሰጣቸው 21.5% መደበኛ እንክብካቤ ብቻ የተደረገላቸው 25% ነበር። ድጋፍ ያላስፈለጋቸው ዴክሳሜታሶን የተሰጣቸው ሞት 17.0% መደበኛ እንክብካቤ ብቻ የተደረገላቸው ሞት 13% ነበር5

ይህን መሠረት በማድረግ በብሪታንያ አግባብነት ያላቸው ከፍተኛ የህክምና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች በጋራ መግለጫቸው ኦክስጅን ድጋፍ ለሚሰጣቸው ወይም በመተንፈሻ መሣሪያ ለሚተነፍሱ የኮቪድ-19 ታካሚዎች ሙሉውን መረጃ መታተም ሳይጠበቅ በሆስፒታል ጥቅም ላይ እንዲውል ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል። ሲያስረዱም የሟች ቁጥር መቀነሱ በግልጽ ይታያል። ዴክሳሜታሶን በተሰጣቸውና ባልተሰጣቸው መካከል የውጤት ልዩነቱ በጣም ጉልሕ ነው። በሚገባ የሚታወቅም መድኃኒት ነው። የጎንዮሽ ጉዳቱም ለእነዚህ ዐይነት ታካሚዎች ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ ክብደት የሚሰጠው አይደለም6።አከበሽታው አንገብጋቢነት አኳያ ታይቶ ጊዜ መፍጀት አያሻም ነው ምክሩ። የጎንዮሽ ጉዳቶቹ ሲደርሱም በጽኑ ሕሙማን እንክብካቤ ክፍል ሁኔታ እስከተሆነ ድረስ መቆጣጠር ይቻላል7። የዓለም ጤና ጥበቃም ውጤቱን በመቀበል ስለአጠቃቀሙ መመሪያ (መቼና እንዴት) ለማውጣትና በነበረው የኮቪድ-19 ሕክምና ፕሮቶኮል ለማካተት እየሠራ ይገኛል። በሌላ በኩል የሳውዝ ኮሪያ የጤና ኀላፊዎች ሊያደርስ በሚችለው ጠንቅ ምክንያት ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳስባሉ8

ከአሜሪካ ሆስፒታሎች ውስጥ የተጠቀሱትን ሕመምተኞች ለማከም ሥራ ላይ እንዲውል ያበረታቱ አሉ። ከእነዚህ መካከል የኦክስፎርድ አጥኚዋች መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ ራሳቸውም ቢሆኑ ሕመምተኞቻቸውን ሲያክሙበት የቆዩ ይገኙባቸዋል። ፈራ ተባ የሚሉም አሉ። ምክንያታቸውም ጥናቱ አልተጠናቀቅም፣ (የጥናት ፕሮቶኮሉን መመልከት ይቻላል) 9። ተጠናቆና የእኩያ ሳይንቲንስቶች ግምገማን አልፎ፣ ብቃት ያለው ሥራ መሆኑ ተረጋግጦ በታወቁ ሙያዊ መጽሔቶች አልወጣም። የጥናቱ ዝርዝር መረጃ ወጥቶ ግምገማ ሲደረግ ያደርሰናል ነው የሚሉት። ከዚህ ቀደም በዴክሳሜታሶን ቤተ ሰብ የሚገኙ መድኃኒቶች በቀደምትነት በሚታወቁት በሌሎቹ ዐይነቶች የኮሮና ቫይረሶች የተለከፉ ሕመሞችን (SARS እና MERS) መርዳታቸው አከራካሪ ሆኖ ቆይቷል። እንዲያውም ቫይረሶቹ በደም ውስጥ የሚገኙበትን ጊዜ ከማርዘም ጋር ጉድኝት አሳይተዋል። ይህ ማለት ቫይረሶቹ ለተጨማሪ ጊዜ ከታማሚው ወደ አካባቢው የመለቀቅ ዕድል አላቸው ማለት ነው። በዚህኛው ኮሮና ቫይረስም ዴክሳሜታሶን በተመሳሳይ ሁኔታ ጉድኝት እንዳይኖረው ሥጋታቸው ነው። ክሎሮኩዊን እና ሐይድሮ ክሎሮኩዊን ተስፋ ተጥሎባቸው መክሸፋቸው የዴክሳሜታሶን ወሬም እንደዛው ሆኖ እንዳያርፈው ሥጋት ያላቸውም አሉበት1011። አሁን ግን የአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋም ጥናቱን በመከተል ልብ ሊባሉ የሚገባቸውን አሳቦች በማከል ስለ አጠቃቀሙ መምሪያ አውጥቷል። በተጠቀሰው አንድ ጥናት ብቻ ተመሥርቶ በመተንፈሻ መሣሪያ ለሚጠቀሙ “ይሰጥ”ን በብርቱ፣ በሌላ ዘዴ የኦክስጅን ድጋፍ ለሚያገኙ “ይሰጥ”ን በልኩ፣ የኦክስጅን ድጋፍ ለማያስፈልጋቸው “አይሰጥ”ን በብርቱ ደግፏል12። መምሪያው ፈራ ተባ የሚሉትን እንዲያክሙበት ሊያበረታታ ይችላል።

ከአፍሪካ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ይኸንኑ ተከትለው በሆስፒታሎቻቸው በድንገተኛ አገልግሎት እንዲውል በመወሰን ቅድሚያውን ይዘዋል13

የምሥራቹ ወሬ ከተሰማ ጀምሮ የዴክሳሜታሶን የግዢ ጥያቄ ወደ ላይ ተተኩሷል። የሚወጋው (የመርፌው) ዴክሳሜታሶን በአሜሪካ ሆስፒታሎች ብቻ ከሰኔ 16 እስከ 19 2020 ባሉት ቀናት በ610% ጨምሯል። አከፋፋዮቹም ለጭነት አዘጋጅቶ በየሆስፒታሉ የማድረስ መጨናነቅ ገጥሟቸዋል14። በአዲስ አበባም ወገኖቼ ‘ዴክሳሜታሶንን እየተሻሙ ገዝተዋል፣ ዋጋውም ንሯል15። ዜናው ተሻምተው የገዙት የጤና ድርጅቶች ይሁኑ ወይም ግለ ሰቦች፣ የተቸበቸበውም እንክብሉ ወይም የሚወጋው ይሁን ለይቶ አላመለከተም። ከስሜቱ በመነሣት የገዙት ግለ ሰቦች እንደሆኑና የተቸበቸበውም እንክብሉ እንደ ሆነ መገመት ግን ስሕተት አይሆንም። ይህም ለመከላከያነት ለመጠቀም እንደ ሆነ ያሳብቃል ማለት ነው። በጥናቱ እንደተመለከተው ሳንባቸው ደኅና ለሚሠራ ታካሚዎች ዴክሳሜታሶን ፋይዳ አላሳየም።
በቤታቸው ቆይተው ሊያገግሙና ሊድኑ ለሚችሉት ቀድሞ እየወሰዱ ባለበት ሕመም ምክንያት ካልሆነ በስተቀር አይታዘዝላቸውም። የዓለም ጤና ጥበቃም የሚመክረው በጥናቱ ለጠቀማቸው ዐይነት ሕሙማን በ “ጽኑ ሕመም እንክብካቤ ክፍል” ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ውሳኔም ከዚህ የወጣ አይደለም16። እንደ አንዳንድ ባለሙያዎች አስተያየት ለተመላላሽ ሕሙማን (የኦክስጅን ድጋፍ ለማያስፈልጋቸው ማለት ነው) የኮቪድ-19ን ሊያባብስ ይችላል17፤ ለመከላከልም አይረዳም። ዴክሳሜታሶን ኮሮና ቫይረስን የሚገል አይደለም ወይም እንዳይባዛ የሚያሰናክለውም አይደለም። ቫይረሱን ምንም አያደርገውም። ዴክሳሜታሶን የሚያተርፋቸው ቢኖሩም አሁንም 28% ያህል የመሞት ዕድል እንዳለ ልብ ማለት የአደጋውን አለመወገድ ያሳያል። ስለዚህ በጥናቱ ባልተሰጠ መተማመኛ ‘ብውጠው/ብወጋው’ ይከላከልልኛል በማለት በኮቪድ-19 ላለመያዝ ከመጠንቀቅ መዘናጋት ብልህነት አይደለም።

ዴክሳሜታሶን ላይጠቅም በተለይም ለበርካታ ቀናት (ከሁለት ሳምንት በላይ) ከተወሰደ የወሳጆቹ የተለያዩ የአካል አባላት (ዓይን፣ ልብ [ደም ግፊት]፣ አጥንት [መሳሳት]፣ የስኳር ብዛት፣ ወዘተርፈ.) የጎንዮሽ ጉዳት ያገኛቸዋል። ከዚህም በላይ ዴክሳሜታሶን አንዳንድ ዐይነት ሕመም ላለባቸው ፈጽሞ ይከለከላል። የተዳፈኑ ልክፈቶችን (ለምሳሌ ሳንባ ነቀርሳ) ሊቀሰቅስ ይችላል። አብሯቸው ከተወሰደ ፍቱንነታቸውን የሚቀንስባቸው መድኃኒቶችም አሉ። በቂ ክትትል እየተደረገበት ብቻ ሊሰጥ የሚችልባቸው ሁኔታዎችም እንዲሁ18። እነዚህን ሁሉ አጣርቶና አስማምቶ ጉዳት በማያደርስበት ወይም ጉዳቱ የከፋ በማይሆንበት መንገድ እንዲጠቀሙበት ሊያዝ የሚችለው ሐኪም ነው። የጤና ሚኒስቴር ያለ ሐኪም ትዕዛዝ እንዳይሸጥ መመሪያ19 ማውጣቱ ተገቢ ነው። ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግም ለራስ ጥቅም ነው።

መድኃኒቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው ኩባንያ ብቸኛ ባለመብትነት ጊዜው ካለፈ ብዙ ዓመታት አልፈዋልና በርካታ ኩባንያዎች መደበኛ ስሙን እየሰጡ የሚያመርቱት መድኃኒት ነው። እነዚሁ ኩባንያዎች የምርት መጠናቸውን እንዳስፈላጊነቱ ሊያሳድጉት ይችላሉ። የጥሬ ዕቃውን የሚያቀርቡ የተፈተኑ ኩባንያዎች አሉ። በርግጥ የሚወጋው ሲዘጋጅ ጥራቱን የማረጋገጥ ሂደቱና ቁጥጥሩ ብርቱ ስለሆነ የመጓተት ዕድል አለ። የዓለም ጤና ጥበቃም በሚፈለገው ሥፍራ አቅርቦቱ እንዳይጓደል ይመክራል20። ስለዚህ በአቅርቦት በኩል ችግር ቢኖር እንኳ ለዐጭር ጊዜ ስለሆነ ተሻምቶ ማከማቸቱ ስሜቱን መረዳት ቢቻልም ምክንያታዊ ግን አይደለም። መረጋጋት ያስፈልጋል። ለሌላ ሕመም በሚጠቀሙበት ሕሙማን ላይ የዐጭር ጊዜም ቢሆን የዋጋና በመፈለግ የመንከራተት ሸክም መጨመር አይገባም። መረጋጋቱ መድኃኒት ቤቶችንም ዋጋውን ለመስበር ያበረታታቸዋል። የሐሰት ዴክሳሜታሶንን ለሚያቀርቡ ሲሳይ ከመሆንም መትረፍ ነው።

ይህን አንብበው እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ዴክሳሜታሶን የኮቪድ-19 መከላከያ እንዳማይሆናቸው የተረዱ ወይም ከኮቪድ-19 በመጠንቀቁ ትጋታቸውን ያደሱ ወይም በሐኪም ያልታዘዘላቸውን ዴክሳሜታሶን ከመውሰድ የታቀቡ ወይም ለሌላ ሕመም የታዘዘላቸውን በአቅርቦትና በዋጋ ጭማሪ እንዳይቸገሩ የተጠነቀቁ ጥቂት ሰዎች ከተገኙ ጽሑፉ ሰምሮለታል ማለት ይቻላል። ስላነበባችሁ ምስጋና ይግባችሁ።

 1. PulmCrit – Dexamethasone & COVID – a study in immunopathology, evidence-based medicine, and ourselves [ተነበበ ሰኔ 26 ቀን፥ 2020]
 2. Oxford university news release. low-cost dexamethasone reduces death by up to one third in hospitalized patients with severe respiratory complications of COVID 19 [ተነበበ ሰኔ 18 ቀን፥ 2020]
 3. Dexamethasone: what is the breakthrough treatment for COVID-19? [ተነበበ ሰኔ 20 ቀን፥ 2010]
 4. ከላይ 2 ይመልከቱ
 5. https://www.medrxiv.org/content/10.1101/2020.06.22.20137273v1 [ተነበበ ሰኔ 23 ቀን፥ 2020]
 6. https://www.rpharms.com/Portals/0/RPS%20document%20library/Support%20alert/CMO%20-dexa%20letter.pdf?ver=2020-06-17-092605-187 [ተነበበ ሰኔ 18 ቀን፥ 2020]
 7. ከላይ 3 ይመልከቱ
 8. WHO Moves to Update COVID-19 Guidance After ‘Great News’ in Drug Study – Medscape [ተነበበ ሰኔ 19 ቀን፥ 2020]
 9. Randomised evaluation of COVID-19 therapy (RECOVERY) NCT04381936 [ተነበበ ሰኔ 20 ቀን፥ 2020]
 10. The effect of corticosteroid treatment on patients with coronavirus infection: a systematic review and meta analysishttps://pubmed.ncbi.nlm.nih.gov/32283144/  ይገኛል።[ ተነበበ ሰኔ 27 ቀን፥ 2020]
 11. Dexamethasone for COVID-19: Some US Hospitals Wait to Change Practice – Medscape – [ሰኔ 19 ቀን፥ 2020]
 12. COVID-19 Treatment Guidelines Panel. Coronavirus Disease 2019 (COVID-19) Treatment Guidelines. National Institutes of Health. [ተነበበ ሰኔ 27 ቀን፥ 2020]
 13. https://lancasteronline.com/business/nation/thelatest-south-africa-ethiopia-to-usedexamethasone/article_667d9b4a-7c3b-5903-83eae7a88c4b72e3.html ይገኛል።[ተነበበ ሰኔ 28 ቀን፥ 2020]
 14. Hospitals see shortages of a cheap steroid thatone study says helps Covid-19 patients [ተነበበ ሰኔ 29 ቀን፥ 2020]
 15. በአዲስ አበባ የዴክሳሚታሶን ዋጋው መናሩንና ብዙ ሰዎችም መድሃኒቱን እየተሻሙ እየገዙ ይገኛሉ ተባለ [ተነበበ ሰኔ 20 ቀን፥ 2020]
 16. https://www.africanews.com/2020/06/19/coronavirus-ethiopia-the-federal-ministry-of-health-fmohrecommends-the-emergency-use-of-low-dosedexamethasone-for-covid-19-patients/ [ተነበበ ሰኔ 29 ቀን፥ 2020]
 17. Breakthrough Drug for Covid-19 May Be Risky for Mild Cases [ተነበበ ሰኔ 28 ቀን፥ 2020]
 18. Micromedex® (electronic version). IBM Watson Health, Greenwood Village, Colorado,USA. [ተነበበ ሰኔ 24 ቀን፥ 2020]
 19. ዴክሳሜታዞን ካለሐኪም ትዕዛዝ አትውሰዱየጤና ሚኒስቴር ማሳሰቢያ [ተነበበ ሰኔ 22ቀን፥ 2020]
 20. https://www.who.int/dg/speeches/detail/whodirector-general-s-opening-remarks-at-the-mediabriefing-on-covid-19—22-june-2020 [ተነበበ ሰኔ 29 ቀን፥ 2020]

Bantu Gebremariam

ባንቲ ገብረ ማርያም በፋርማሲ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በፋርማኮሎጂ የማስተርስ ዲግሪ እንዲሁም በቢብሊካል ካውንስሊንግ ማስተርስ ዲፕሎማ የሠሩ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም “Comparative Theology” - “የነገረ መለኮት ንጽጽር” በሚል እንዲሁም “Forgiveness to Let Go” - “ይቅር ማለት- ለመተው ነጻነት” የተሰኙ መጻሕፍትን ወደ አማርኛ መልሰዋል። E-mail: bantge@yahoo.com

Share this article:

“እግዚአብሔር፣ ያልተቀደሰች ቤተ ክርስቲያንን ፈጽሞውኑ መኖርያው አያደርግም” – ቻርልስ ሀደን ስፐርጀን

ግርማ በቀለ (ዶ/ር)፣ የታዋቂውን እንግሊዛዊ የወንጌል ሰባኪና አስተማሪ ቻርልስ ሀደን ስፐርጀንን ግለ ታሪክ መነሻ አድርገው ባቀረቡት በዚህ ጽሑፍ፣ ስፐርጅን ያለፈበትን አስቸጋሪ የሕይወት ትግል፣ ስለ ወንጌል ንጽሕና ሲል የተጋፈጣቸውን ዕቡያን እንዲሁም፣ በጽናት የተደመደመውን የድል ሕይወት ያስቃኙናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

መልካም ጅምሩ እንዳይደናቀፍ

የሥነ መለኮት ጥናት በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን አጭር ዕድሜ ያለው ነው፡፡ የዕድሜው ዕጥረት ከወንጌላውያን ክርስትና አጀማመር ጋር የራሱ ቁርኝት አለው፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ የቆይታ ዘመን በአንጻራዊነት ከታየ አጭር የሚባል ነውና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ቤተ ክርስቲያናት፣ አጋር ቤተ ክርስቲያናትና ግለ ሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶችን መክፈት ጀምረዋል፡፡ በመሠረቱ ይህን መሰሉ ጥረት ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጥረቱን ማበረታታት እንዳለ ሆኖ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዋናነት ከትምህርት ጥራት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.