[the_ad_group id=”107″]

ቀዳሚው ፍቱን መድኃኒት

(ደወል 2 ዘኢትዮጵያ)

በ“ደወል 1 ዘኢትዮጵያ”፣ ኢትዮጵያ በሚድን በሽታ ተይዛ ግን በሽታው እየገደላት እንደ ሆነ ተመለከትን። አሁን ደግሞ ይህን በሽታ ተመልክተን እንነቃበት ዘንድ “ደወል 2 ዘኢትዮጵያን” እንመለከታለን። በሽታውን ስናውቅ መድኃኒቱ ይታየናል።  ይህን ለማድረግ በኢትዮጵያ ያሉትን ሦስት ገጸ ባሕርያት ለምሳሌነት እንውሰድ። አንደኛ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብን ተጠያቂ የሚያደርግ ሰሚ ያጣ ፈጣሪ አለ። ሁለተኛ፤ የኢትዮጵያ ልኂቃንን ተጠያቂ የሚያደርግ ሰሚ ያጣ ሕዝብ አለ። ሦስተኛ፤ ብዙ ሰሚዎችን ያገኙ የጠብ ገበሬዎች አሉ።

ሰሚ ያጣ ፈጣሪ፦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠየቅ

 የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኑሮ ጋር እየታገለ፣ ቀን ያልፍልኛል በማለት ተስፋ የሚያደርግና ተስፋ ባለመቁረጥ የሚታወቅ ነው። ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው፣ ሰውን በሰውነቱ በማየት ከተለያዩ ብሔር ተወላጆች ጋር በጋብቻ የተገመደ ነው። አስቸጋሪ የሆነውን ኑሮ በዐብሮነት እየተረዳዳና እየተደጋገፈ፣ ሃይማኖትና ዘር ሳይለየው ለዘመናት በፍቅር የኖረ ነው። ተረኛ ባለሥልጣናት እየነገሡ ቢፈራረቁበትም፣ ሕዝብ ሁሉም ያለ ልዩነት የመከራን ገፈት እየተጋፈጠና ለአገሩ ደሙን እያፈሰሰ ኢትዮጵያን እስካሁን ያቆየ ነው። ሲቸግረው ዐመፅ አድርጎ መንግሥት ቢቀየር፣ ቤተ መንግሥት አይገባ ነገር ወደ ቤቱ ዐደራ ሰጥቶ ይመለሳል። ይሁን እንጂ፣ ባለ ዐደራው መንግሥት ዐደራውን ቀርጥፎ እየበላ ሕዝብን ባዶ እጁን ያስቀረዋል። ይህም ሳያንስ፣ መንግሥት ሕዝብን ምረጥ እያለ ያታልለዋል። ሕዝብ ሥልጣን ተሰጠኝ ብሎ ቢመርጥም፣ ወይ ምርጫው ይሰረቃል፣ አለበለዚያም በሐቅም ተመረጠ ቢባል እንኳ ዐደራው ይበላል። ኢትዮጵያ በመልካም ሕዝብ፣ በለምለም ምድር፣ በውብ የአየር ፀባይ ብትታደልም፣ እጣ ፈንታዋ ድኽነት፣ ሰቆቃና ሞት ሆነ። ሕዝብ መውጫ ቀዳዳ አጥቶ፣ አገሩ እስር ቤት ሆኖበት የቻለው ለመኮብለል ይናፍቃል። እንባውን ለፈጣሪ እያፈሰሰ ለዘመናት ኖረ።

በሌላ በኩል ሰማይ ጥሪ ያቀርብልናል። ፈጣሪ እኛን እንዲሰማን እንደምንፈልግ ሁሉ፣ ፈጣሪም እርሱን እንድንሰማው ይፈልጋል። የሕዝብ ሀብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን የሚዘረፈው፣ የተስፋ ቃሉ እንኳን ሳይቀር በባለተረኞች ይሰረቃል። ኢትዮጵያን በከፍታ ስፍራ የሚያስቀምጣት ፈጣሪ ራሱ ነው። ነገር ግን፣ በኢትዮጵያና በፈጣሪ መካከል እየገባ ቦታውን የሚወስድ ባለጊዜ ባለሥልጣን ነው። ያንን ደግሞ ሳያውቅ የሚያደርገው ሕዝብ ራሱ ነው። የቀድሞ መሪን የይሁዳ አንበሳ ብለን ማስተጋባት ስናበቃ፣ የአሁኑን መሪ ደግሞ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ሙሴ ብለን ዐረፍን። 

ኢትዮጵያን የሚያሻግር የሰው ሙሴ እንደሌለ ሁሉ፣ ኢትዮጵያን የሚበታትን የሰው ሰይጣንም የለም።

የእስራኤልን ዐላማ ኢትዮጵያ መኮረጅ አትችልም። የእስራኤል ሕዝብ ጥሪ በአንድ ሰው፣ ያውም በአብርሃም ላይ የተመሠረተ ነው። ስለሆነም ያዕቆብ እስራኤል በመሆን የቃል ኪዳኑን ሕዝብ መሠረተ። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች[1] ማለት፣ ጥሪው የቀረበው ለሕዝብ እንደ ሆነ ያሳያል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ጥሪ በሕዝብ ላይ የተመሠረተና ከእርሱ ጋርም የተያያዘ ነው። ለኢትዮጵያ ሙሴ ትላንት አልነበረም፤ ዛሬም የለም፤ ወደ ፊትም አይመጣም። ፈጣሪ ኢትዮጵያን በግለ ሰብ እጅ ሳይሆን በሕዝብ እጅ ያሻግራታል። ለዚያ ጥሪው የቀረበለት ደግሞ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያን የሚያሻግር የሰው ሙሴ እንደሌለ ሁሉ፣ ኢትዮጵያን የሚበታትን የሰው ሰይጣንም የለም። ለደጉም ለክፉም ግለ ሰብ ላይ መንጠልጠላችን ይቅር። ይልቁንስ የኢትዮጵያ ሕዝበ ቤተ ሰብ መለኮታዊ ጥሪውን ለመቀበል ይነሣ። ያኔ ፈጣሪም ይነሣል። ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይናገራል፦ “ስለ ድሆች መከራ፣ ስለ ችግረኞች ጩኸት እግዚአብሔር፦ ‘አሁን እነሣለሁ’ ይላል፤ ‘መድኃኒትን አደርጋለሁ፣ በላዩም እገልጣለሁ’ ”[2]

ሰሚ ያጣ ሕዝብ፦ የኢትዮጵያ ልኂቃን ይጠየቁ

የኢትዮጵያ ልኂቃን ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጡና እሴቱን የሚያንፀባርቁ ናቸው። ራሳቸውን መሥዋዕት በማድረግ ይህ ሕዝብ ያልፍለት ዘንድ እንደ ሻማ እያለቁ የሚያበሩ ናቸው። በጥበብና በዕውቀት የተካኑ ትልቅ ሰዎች ናቸው።  ያም ቢሆን እስካሁን አልተሳካላቸውም። ብርሃኑ እንዳያበራ ንፋሱ ሻማውን ያጨልመዋልና። ሁሉ ከንቱ ሆኖባቸዋል።  ራሳቸውንና ቤተ ሰባቸውን ትርፍ ለሌለው ነገር ማንከራተት ሆኖባቸዋል። ምንም ያህል ሐቀኛና ታታሪ ቢሆኑ፣ የሚያመክናቸው ነገር መኖሩ ነው። ልፋት ብቻ። ሁሉ ነገር የአንድ ሰሞን ጕዳይ ሆነ።

ብርታታቸው ራሳቸውን መሥዋዕት ማድረጋቸው ነው። ድክመታቸው ደግሞ የራሳቸውን ግላዊ ራእይ መሠዋት አለመቻላቸው ነው።  ሰው ብዙ ዋጋ እየከፈለ ግን መነሻ ዐሳቡ ስሕተት ከሆነ ዒላማውን አይመታም። ሰው ሊሞት ይችላል፤ ብዙ መከራ ሊቀበል ይችላል። ያም ሆኖ የግልን ራእይ ጥሎ፣ በአንድነት ለኢትዮጵያ ባለመነሣቱ ብኩን ሆኖ ሊቀር ይችላል። ዋናው ቍም ነገር ከጀርባው የሚገፋው ኀይል ከእኔነት መፅዳቱ ነው። በእኔነት ከተነዳን አንድ ሆነን መቆም አንችልም። አንድነት እንዲመጣ ራስን ክዶ፣ ከሌላው ጋር በትሑት ልብ ሆኖ፣ ለሕዝብ ጥቅም ሙሉ በሙሉ መሰጠት አለብን። ፍሬያማ የመሆን ምስጢር ያለው ለእኔነት ሞቶ፣ ከሌላው ጋር በአንድ ልብ መያያዝ በመቻል ነው። በልብ እልከኝነት ያለ ፍሬ እንዴት ዕድሜያችንን እንጨርሳለን? አንቆ የያዘን ከእኛ ውጭ ያለው ሳይሆን፣ በእኛ ውስጥ የተደበቀው እኔነታችን ነው።

ፍሬያማ የመሆን ምስጢር ያለው ለእኔነት ሞቶ፣ ከሌላው ጋር በአንድ ልብ መያያዝ በመቻል ነው።

አስተሳሰባቸውና አመለካከታቸው የተለያየ መሆኑ ችግር አይደለም። ይህ የዐሳብ ልዩነት ጸጋ ነው። የዐሳብ ብዝኃነት ጸጋ የሚገለጠው ግን መነጋገር ሲኖር ነው። መነጋገር ደግሞ ወደ መግባባት አምጥቶ ራሳቸውን የሠዉለትን ለውጥ ማምጣት ያስችላል። ደግሞ መግባባት ችግር አይሆንም ነበር፤ ምክንያቱም በልባቸው ያለው ራእይ ለሕዝብ ስለ ሆነ፣ ያ የጋራ ጥቅም ለማግባባት አቅም ያለው በመሆኑ። ውይይት ቢኖር ልዩነቱ ተጋጭቶና ተፋጭቶ መድኃኒት ይወጣው ነበር። አሁን የተያዘው መጮኽ ነው፤ እንደ ገደል ማሚቶ። ጩኸቱን ሌላው አይሰማም። የሚጮኽ ራሱ የራሱን ጩኸት ይሰማል።

ነገር ግን፣ ይህ ሁሉ ታሪክ የሚቀየርበት ጊዜ አለ። ያም የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈጣሪን ሰምቶ ለተሰጠው መለኮታዊ ጥሪ ራሱን መልስ አድርጎ ሲቆም፣ ልኂቃንም እንደዚሁ ሕዝብን ሰምተው በአንድ ልብ ለመገለጥ ግድ ይላቸዋል።

ብዙ ሰሚዎችን ያገኙ የጠብ ገበሬዎች

ፈጣሪና ሕዝብ ባልተሰማበት ሁኔታ እነዚህ ግን ብዙ ሰሚዎችን አገኙ። እነዚህ ሰርጎገብ ናቸው፤ የኢትዮጵያ አይደሉም። የግላቸው ናቸው። ሁሉም ውስጥ ተደብቀው አገር እንዲታመስ ምክንያት የሚሆኑ ናቸው። የትም ከለላ ውስጥ ቢሆኑ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ነው። ያም ለግል ጥቅም የሚኖሩ ናቸው። የፖለቲካ ሽፋን ውስጥ ሲገኙ ራሳቸውን ለማኖር እንጂ ለሕዝብ ሊኖሩ አይደለም። ሃይማኖት ውስጥ ሲሸሸጉ ለፈጣሪ ክብር ሊያመጡ ሳይሆን፣ ለራሳቸው ክብር ለማምጣት ነው። ሕዝብ ውስጥ ሲደበቁ ለሕዝብ ተቆርቁረው ሳይሆን፣ ብሔራቸውን መነገጃ ለማድረግ ነው። እነዚህ ኢትዮጵያን ለማቃጠል እሳት የሚጭሩ ክብሪት የሆኑ ናቸው። 

ፈጣሪ ከኀጢአት ሁሉ ይበልጥ ነፍሱ አጥብቃ የምትጸየፈው በወንድማማች መካከል ጠብ የሚዘራ መሆኑን ልብ እንበል።

ሥራቸው የጠብ ግብርና ነው። የሚዘሩት ዘር ደግሞ ጠብ ይባላል። ቃሉ ስለነዚህ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፤ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዓይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፣ ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፣ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፣ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ”[3]። ፈጣሪ ከኀጢአት ሁሉ ይበልጥ ነፍሱ አጥብቃ የምትጸየፈው በወንድማማች መካከል ጠብ የሚዘራ መሆኑን ልብ እንበል። በወንድማማች መካከል የሚዘሩት ጠብ የሚያበቅለው ሁለት ዐይነት ፍሬ ይታጨዳል። በአንድ በኵል ሕዝብ አለመደማመጥና አለመግባባትን እያጨደ እርስ በርስ ይበላላል። በሌላ በኩል በሕዝብ ሰቆቃ ላይ የጠብ ገበሬዎች ሀብት ዝናና ሥልጣን እያጨዱ ለራሳቸው ጥቅም ትርፋቸውን ይበላሉ።

የነገሩ ፍጻሜ ምንድን ነው?

ሲጀመር የሚሰማ ጆሮ ይኑረን። መሰማት ያለበትን አስቀድመን እንስማ።  የሕዝብ ጆሮ ሰሚ ያጣውን ፈጣሪ ለመስማት ይከፈት። የልኂቃን ጆሮ ሰሚ ያጣውን ሕዝብ ለመስማት ይከፈት። ያንን ከሰማን ወደ እርስ በርስ መደማመጥ እንመጣለን።  ስንደማመጥ ደግሞ ወደ መግባባት እንደርሳለን።  ስንግባባ ዐብረን እንደ አንድ ሆነን እንቆማለን። አንድ ላይ አንድ ሆነን ስንቆም፣ ያኔ ከመድኃኒታችን ጋር እንገናኛለን። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።


1 መዝሙረ ዳዊት 68፥31

2 መዝሙረ ዳዊት 12፥5

[3] መጽሐፈ ምሳሌ 6፥16-19

Share this article:

በዓለ ጰራቅሊጦስ

በኢትዮጵያ ከ1555-1585 ዓ.ም. የነገሠው የዐፄ ሠርጸ ድንግል ዜና መዋዕል ጸሐፍት ዜና መዋዕሉን መጻፍ የጀመሩት የሚከተለውን ጸሎት በማቅረብ ነበር። “ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አስተብቍዖ ወሰአሎ ለእግዚአብሔር አቡከ ከመ ይፈኑ ላዕሌነ ጰራቅሊጦስሃ መንፈሰ ጽድቅ ዘኢይክል ዓለም ነሢኦቶ። ወመጺኦ ውእቱ ይመርሐነ ኀበ ኵሉ ጽድቀ ነገር። እስመ አይነግር እም ኀቤሁ ፈጠራ ወሐሰት አምሳለ ካልኣን መናፍስት እለ አልቦ ጽድቀ[ቅ] ውስተ አፉሆሙ። – ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ዓለም ሊቀበለው የማይችለውን የእውነት መንፈስ የኾነውን ጰራቅሊጦስን ይልክን ዘንድ የባሕርይ አባትኽን እግዚአብሔርን ማልደው፤ ለምነውም። መጥቶም ወደ እውነት ነገር ኹሉ ይመራናልና፤ በአፋቸው ውስጥ እውነት እንደሌላቸው እንደ ሌሎች መናፍስት የሐሰትን ነገር ከራሱ አንቅቶ አይናገርምና” (የዐፄ ሠርጸ ድንግል ዜና መዋዕል 1999፣ 3)።

ተጨማሪ ያንብቡ

እግዜር እንግዳ ሆኖ ሲመጣ

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በምናስብበት በዚህ ሰሞን፣ “እግዜር እንግዳ ሆኖ ሲመጣ” ሊኖረን ስለሚችልና ስለሚገባ ምላሽ የሚከተለውን ጽሑፍ ሰሎሞን ጥላሁን ያስነብበናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

“ማን ኦፍ ጋድ” መባል ያማራት ነፍስ

” ‘ማን ኦፍ ጋድ መባል አማረኝ’ አለ … ቲቪ ላይ ማፍጠጥ፣ ኮት በሰደሪያ መልበስ፣ ጸጉሩን እንደ አክሱም ሐውልት ማቆም፣ ድምፁን ማጎርነንና መንጎራደድ አብዝቶ ነበረና፡፡” አስናቀ እንድሪያስ ይህን የምኞት ጉዞ እንዲህ ያስቃኘናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

4 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • በጎ ምክር ይመስላል። ከእውነታው ጋር ግን አልተገናዘበም። ሕዝቡ መልካም፣ መሪና ሊኂቃኑ ነው ችግሩ ማለት ጨርሶ ስህተት ነው። የሚሰማ ጆሮ ሲኖረን ሁሉ ይቃለላል ማለት ውስብስቡን ማቅለል ነው።

    • ጸሐፊው ያለውን ሰጠን። ታዲያ እንደርስዎ ምን ይሻለናል?
      – ችግሩ ሕዝብ ነው ባይ ነዎት?
      – ውስብስቡ ተቃለለ ያሉት ችግርና መፍትሔው ምንድነው? … ይሉናል? (መልስዎን በአክብሮት እጠብቃለሁ)

  • አሜን ጆሮ ያለው ይስማ። ጸጋውን ያብዛልህ ውድ ወንድሜ።
    _________ እኔም ከአንተ ጋር

    “ሲጀመር የሚሰማ ጆሮ ይኑረን። መሰማት ያለበትን አስቀድመን እንስማ። የሕዝብ ጆሮ ሰሚ ያጣውን ፈጣሪ ለመስማት ይከፈት። የልኂቃን ጆሮ ሰሚ ያጣውን ሕዝብ ለመስማት ይከፈት። ያንን ከሰማን ወደ እርስ በርስ መደማመጥ እንመጣለን። ስንደማመጥ ደግሞ ወደ መግባባት እንደርሳለን። ስንግባባ ዐብረን እንደ አንድ ሆነን እንቆማለን። አንድ ላይ አንድ ሆነን ስንቆም፣ ያኔ ከመድኃኒታችን ጋር እንገናኛለን። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”

    እላለሁ።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.