[the_ad_group id=”107″]

ለሚድን በሽታ የሚገድል መድኃኒት መውሰድ ይብቃ!

ደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ

ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ሕዝበ ቤተ ሰብ። በደወል 1 ዘ ኢትዮጵያ፣ በሚድን በሽታ ተይዛ ግን በሽታው እየገደላት ያለች ሀገር ኢትዮጵያን አየን። በደወል 2 ዘ ኢትዮጵያ፣ ለዚህ በሽታ ያልተጠቀምንበትን ቀዳሚው ፍቱን መድኃኒት ምን እንደ ሆነ ተመለከትን። አሁን በደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ መድኃኒት መስሎን የምንወስደው ዘረኝነት ገዳይ መርዝ እንደ ሆነ እናያለን።

 ሰው የሚድን በሽታውን ለማሻል የሚያድን መድኃኒት ይወስዳል እንጂ፣ ጭራሽ ለሞት የሚያጋልጠውን መርዝ በመድኃኒት ስም አይወስድም። ኢትዮጵያ ግን የብሔር ብሔረሰብን እኵልነት ለማምጣት ዘረኝነትን እንደ መድኃኒት እየወሰደች፣ የማያቆም የስቃይ ድራማና ምስቅልቅል ባለ ጎዳና ላይ እየተጋዘች አለች። የኢትዮጵያ ሕልውናም ቦግ ድርግም እያለ፣ በቁልቁለት ጉዞ ፀሓይ እስክትጠልቅባት ድረስ የሚሄደው ለዚህ ነው። መፍትሔው አንድ ነገር ነው። የዐሳብ ልዕልና መውጫ መንገዳችን ነው። የዐሳብ ልዕልና ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ሲያሸንፍ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ ጭምር ሰጥቶ ነው።

ዘረኝነት ግን ዐብሮነታችንን እየገዘገዘ ብትንትናችን እንዲወጣ መንገድ ይጠርጋል። 

ለመግባባት አንድ መሠረት መኖሩ ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ በብዝኀነት የበለፀገች ናት። የሁሉም ውበት ደምቆ እንዲወጣ፣ የሁሉም ሰብእና እና ዕሴቶች በሙሉ በእኵልነት እንዲታዩ፣ ከዚህ ዐልፎ ልዩነቶቹ እርስ በእርስ እየተመጋገቡ እንዲጎለብቱና በዘለቄታ እንዲዘልቁ ከተፈለገ፣ ሁላችንም አንድ መሠረት ሊኖረን ያስፈልጋል። ያም መሠረት ዐብሮነት ይባላል። ዘረኝነት ግን ዐብሮነታችንን እየገዘገዘ ብትንትናችን እንዲወጣ መንገድ ይጠርጋል። ያኔ ባለጊዜና ያሸነፈ የሚመስለው ተረኛ፣ ራሱን መሠረት ለማድረግ ይሞክራል። በዚህ ሂደት ሁሉም ይከስራል። ይህ እንዳይሆን ያልታሰበውን ማሰብ መጀመር አለብን።

ያልታሰበውን ማስብ፦ የዐሳብ ልዕልና 

ያልታሰበውን ለማሰብና የዐሳብ ልዕልናን ለመጨበጥ፣ እኛ ራሳችንን የምናይበትን ዕይታና ሌሎችን የምናይበትን ዕይታ መቀየር አለብን።  ምክንያቱም በተለመደው ዕይታ ዘረኛው ሁልጊዜ ሌላኛው ነው እንጂ እኛ አይደለንም። ለዐብሮነት መሠረት ደግሞ እንቅፋት የሆነው ዘረኝነት ነው። ቋንቋችን የሚደባለቀው እዚህ ላይ ነው። አንዱ ከሳሽ፣ ሌላኛው ተከሳሽ እየሆንን ስለ ቁምነገር መነጋገር አንችልም። ነጻ የሚያወጣን ሁላችንም ወርደን ታች ዝቅ ብለን እግዚአብሔር እኛን የሚያይበትን ዕይታ ማየት ነው። ያኔ ሁላችንም ዘረኛ እንደሆንን ይታየናል። ዘረኝነት በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው። ከዘረኝነት የምንወጣው በፍቃዳችን ነው። ያንንም በአሸናፊነት የምንወጣው፣ ሁላችንም ዐብረን ዘረኞች እንደሆንን ሁሉ፣ ሁላችንም ከዚያ ተላቅቀን ሰው መሆንን ስንፈቅድ ነው። 

አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፣ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል። አንዱ ብሔሩን ሲያስቀድም፣ ሌላኛው ዜግነቱን ያስቀድማል። አንዱ የብሔር ዘረኛ የራሱን ብሔር ለብቻው ሊያገንን ሲፈልግ፣ ለኢትዮጵያ ዐብሮነት መሠረት ውጋት ይሆናል። እንደዚሁም የዜግነት ዘረኛ ኢትዮጵያን ለብቻዋ እንድትገን ሲፈልግ፣ በጨለማ ላለ ጥቁር አፍሪካ ሕዝብ አንድነት ውጋት ይሆናል። አንድ ብሔር እንዲሠለጥን የሚፈልግ ዘረኛና፣ አንድ ኢትዮጵያን ለማግነን የሚፈልግ ዘረኛ አንድ አፍሪካን ሕልም አድርጎ የሚያስቀር ነው። ይህን በማድረግ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ያጨልማል። 

አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፣ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል። አንዱ ብሔሩን ሲያስቀድም፣ ሌላኛው ዜግነቱን ያስቀድማል። አንዱ የብሔር ዘረኛ የራሱን ብሔር ለብቻው ሊያገንን ሲፈልግ፣ ለኢትዮጵያ ዐብሮነት መሠረት ውጋት ይሆናል። እንደዚሁም የዜግነት ዘረኛ ኢትዮጵያን ለብቻዋ እንድትገን ሲፈልግ፣ በጨለማ ላለ ጥቁር አፍሪካ ሕዝብ አንድነት ውጋት ይሆናል።

በኢትዮጵያ ዘረኝነት እንደ መድኃኒት መወሰድ የተጀመረው በጭቆና ተሳብቦ ነው። ጨቋኝ ሁልጊዜ ሕዝብ ሳይሆን የተረኛ መንግሥት ውጤት ነው። የጨቋኝ እናት ደግሞ በጥቁር ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ጭቆና ነው። ኢትዮጵያ በአድዋ የነጻነት ምልክት የሆነችውና ለፓን አፍሪካ መነሻ ያደረጋት፣ እንድትመጻደቅበት ሳይሆን፣ ለእውነተኛው ጭቆና መልስ እንድትሰጥ ነው። ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦችን ጭቆና ለመፍታት እስካልተነሣች ድረስ፣ ራሷን በራሷ ተጠላልፋ የብዙዎች እንቆቅልሽ መሆን ይሆናል ዕድል ፈንታዋ። 

ያለን ዘረኝነት የብሔር ዘረኝነት እና የዜግነት ዘረኝነት ነው። እዚህ ላይ መኻል ሰፋሪ የለም። መኻል ነኝ ብሎ የብሔር ዘረኝነትን “ጠባብ” የሚልና፣ የዜግነት ዘረኝነትን “አሕዳዊ” የሚል ፖለቲካዊ ብልጣብልጥነት ነው። አሁን ሁላችንም ብንፋቅ ወይ የብሔር ዘረኛ ነን፣ አለበለዚያ ደግሞ የዜግነት ዘረኛ ነን። እውነተኛይቷ ኢትዮጵያ የምትገለጠው ልጆቿ የተፈጥሮ ዘረኝነትን በፍቃዳቸው ለመላቀቅ የሚያስችላቸውን ኀይል እንዲላበሱ የኢትዮጵያን ተልእኮ ሲያውቁ ነው።  

 በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ልጆች ከዘረኝነት ወጥተን ሰው በመሆናችን፣ ለጥቁር ሕዝብ ጭቆና መልስ መሆን ተልእኳችን መሆኑን እንወቅ። ችግራችን የሚፈታው ከራሳችን በላይ ማሰብ ስንጀምር ነው። በዓለም እስካሁን ካልታዩት የተሻለ ሥርዐት ሊያመጡ የሚችሉ አቅም ያላቸው ልጆች እናታችን ኢትዮጵያ አላት። ከዘረኝነት የምንወጣው በፍቃዳችን እንጂ በተፈጥሯችን አይደለም። 

የራስን ባሕል ቋንቋ ዕሴት ማዳበር ሰውዋዊነትና ኢትዮጵያዊነት ነው። ነገር ግን፣ የብሔር ዘረኝነት ራስን መንከባከብ ላይ ብቻ አያቆምም። ራስን በሌላው ላይ ጭኖ መግነን ነው የሚፈልገው። ጨቋኝነት ከባለጕልበታምነት (ተረኛ ባለጊዜነት) የሚመነጭ ነው። ራስን በትዕቢት ከሁሉ የበላይ ነኝ የሚል መንፈስ የእኵልነት ጠላት ነው። የብሔር ዘረኝነት የብሔርን ክብር የሚያዋርድ ነው። ብሔር ክብሩና ውበቱ የሚገለጠው በእውነተኛ ኢትዮጵያዊ ዐብሮነት ውስጥ ነው። 

ከዘረኝነት የምንወጣው በፍቃዳችን እንጂ በተፈጥሯችን አይደለም። 

የአድዋ ታሪካችን ፈጣሪ ለጥቁር ሕዝብ ፋና ወጊ እንድንሆን ዕድል የሰጠን መሆኑን የሚያሳይ ነው። ለራስ ብቻ ከመኖር ለሌሎች ለመኖር እንድንፈልግ ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ እንጀራ እንዲወጣላት ከፈለግን ማወቅ ያለብን ነገር አለ። ያም ለአፍሪካ እንጀራ እንዲወጣላት ኢትዮጵያ እርሾ እንደ ሆነች ነው። ኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ትልቅ ካልሆነች፣ በእኛው ልክ ብቻ ከሰፋናት፣ ዕሺ ብላ አትሰፋልንም። ይልቁንም ትበጣጠስብናለች። 

ሰው መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ሰው ሰውን ገዥና ለሰው ተገዥ ሆኖ እንዲኖር በፈጣሪ አልተፈጠረም፤ ሰው ተፈጥሮን እንዲገዛ እንጂ። ሰው ግን ተባብሮና ተዋድዶ ምድርን እየገዛ፣ የምድርን በረከት ከመብላት ይልቅ፣ አንዱ ሌላውን ለመግዛት እየሮጠ እርስ በርስ መበላላትን መረጠ። 

ሰው መሆን ሲመነዘር በዜግነት የሚወሰን ሳይሆን በአህጉራችን ጥቁር ሕዝብነት ነው የሚታየው። ያኔ ነጭ ጥቁር ሳንል ለሰው ፍጡር ሁሉ ፈውስ ምክንያት እንሆናለን። አፍሪካ ስትድን ያኔ ሁላችንም እንድናለን። ይህን መንገድ ካልመረጥን ግን በተናጥል እያንዳንዳችን በጠላት እንመታለን። ዐብረን ካልቆምን ለየብቻችን የዓለምን ተፅዕኖ አሸንፈን ከጨለማ አህጉርነት ወደ ብርሃን አህጉርነት አንሻገርም። ኢትዮጵያ ደግሞ ለዚህ በመሪነት እንድትቀደም በታሪክ አጋጣሚ ይሁን በፈጣሪ ፍቃድ ብቻ እሙን ነው። 

ዘረኝነት ራሱን አንደኛ ያደርጋል፤ የዐብሮነትን ድምፅ ያጠፋል። ዘረኝነት በመጨረሻ ሄዶ ሄዶ ከራሱ ጋር ይጣላል።  

ዘረኝነት ራሱን አንደኛ ያደርጋል፤ የዐብሮነትን ድምፅ ያጠፋል። ዘረኝነት በመጨረሻ ሄዶ ሄዶ ከራሱ ጋር ይጣላል።  ዛሬ ብሔሩን አስቀድሞ ከሌላው ብሔር ጋር የሚጋጭ፣ ትንሽ ቆይቶ ወደ ጎሣው ዝቅ ብሎ በብሔሩ ካሉት ከሌሎች ጎሣዎች ጋር ይጋጫል። ከዚያ እየወረደ ወደ ቤተ ሰብ ወርዶ ከቤተ ሰቡ ጋር ይጋጫል። በመጨረሻ ከራሱ ጋር ይጣላል። የዘረኝነት ሩጫ ወደ ውስጥ ነውና ሄዶ ሄዶ ከራሱ ጋር ይላተማል።

የነገሩ ፍጻሜ ምንድን ነው?

ምርጫችን የትኛው ነው? ለዘመናት “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ስንባል ቆየን። ይህ አጠራር የዜግነት ዘረኝነታችንን ያሳብቃል። ዘመን አመጣሹ “ብሔር ብሔረሰብ፣ ሕዝቦች” ብሎ ይጠራን ጀመር። ይህ አጠራር የብሔር ዘረኝነታችንን ያሳብቃል። ያልታሰበው ዐሳብ ደግሞ፣ “የኢትዮጵያ ቤተ ሰብ” ሊለን ይፈልጋል። ክፋቱ ፖለቲካችን ለራሱ ፍላጎት የሚጠቅመውን እንዲጭንብን ያደርጋል እንጂ፣ ለሕዝብ የሚጠቅመውን አያደርግም። ኢትዮጵያ ራሳችን እንደሆንን በዚያ ማንነታችን እንታወቅ ዘንድ አልቻልንም (Ethiopia: To Be Known As We Truly Are)። ዘረኝነት ካመጣብን ከዚህ የማንነት ጭንብል ማን ይገላግለናል? “እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ፤ ኃይል የእግዚአብሔር ነው” (መዝሙረ ዳዊት  62፥11)።

Share this article:

ተኣምረ ማርያም፣ ገድላትና ድርሳናት ምን ይኹኑ?

መምህር አግዛቸው ተፈራ፣ ሰሞኑን መነጋገሪያ በሆኑት ድርሳናትና ገድላት ጕዳይ ላይ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት፣ በሊቃውንት ጕባኤ በኩል ተገቢው ማስተካከያ እንደሚሰጥ መናገራቸውን ተከትሎ የሚከተለውን ዐሳብ አጋርቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ

የእግዚአብሔር ሕዝብ፦ ኢየሱስ ለሁሉ

“ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎች ሁሉ ጥልቅ የነፍስ ፍለጋ ነው። ሰው ከእርሱ ጋር ኅብረት ያደርግ ዘንድ ፈጥሮታልና፣ ሰው ያንን ማድረግ በቻለ ጊዜ ብቻ ያርፋል። ሰውም ያንን እስኪያደርግ ድረስ ጥልቅ የሆነውን ክፍተቱን እየሸነገለና ያንንም ለመሙላት የተለያየ ነገርን በማሳደድ በብዙ ይደክማል።” ይህ፣ ዘሪቱ ከበደ “የእግዚአብሔር ሕዝብ” በሚል እያስነበበች ካለችው ጽሑፍ፣ ሦስተኛና የመጨረሻ ከሆነው ክፍል የተወሰደ ነው። ተጨማሪ ያንብቡ፦

ተጨማሪ ያንብቡ

ዓለም በ2007 እንዴት አለፈች?

የተለያዩ ክስተቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማያያዝ፣ “በዚህ ጊዜ ጌታ ሊመጣ ነው፤ የዓለም መጨረሻ ሊሆን ነው” የሚሉ ግምቶች ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለመኖራቸው ታሪክ እማኝ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • “አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፣ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል።” ዜግነት ብሎ ብሔር አልገባኝም። የብሔር ፖለቲካ ቢቆም ሰዎች ወይም የአገሪቱ ዜጎች በአንድ አላማ ተሰባስበው በግለሰብና የማሕብረሰብ ዲሞክራሲ እንዲኖር ይፎካከራሉ እንጅ እንዴት ነው የዜጋ ዘረኝነት የሚኖረው ? አሁን መጀመርያ ስለ ሃገራችን እንጅ ስለ አፍሪካ እንዴት ነው ምናስበው? እኛ እንደ ሃገር መቆም ቸግሮን ስለ አፍሪካ ማሰብ ይቻላል? ነው አሕዳዊ ብለው የሚያስቡትን ለመሳብ የገባ እሳቤ? በቆንቆ እና በዘር ሳይሆን በጆግራፊ ወይም ሌሎችን እሳቤ ውስጥ ያስገባ ያልተማከለ አስተዳደር መገንባት ይቻላል። ችግሩ መንግስት ስለሚፈልገው እና ተረኞቹ እንጠቀማለን ብለው ስለሚስቡ ነው። ግናስ ከቀደመው መማር አለመቻላቸው ውድቀታቸው የከፋ እንዳይሆን እፈራለሁ።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.