[the_ad_group id=”107″]

ምእመናንን ስለ መድረክ አገልግሎት ያላቸውን አመለካከት የሚመዝን የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት

ምስጋና

ምእመናን ስለ መድረክ አገልግሎቶች ያላቸውን አመለካከት ለመመዘን በተዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት ላይ ተሳታፊ ለሆኑት የሕንጸት ጥናት እና ምርምር ቡድን አባላት፣ እንዲሁም ለጥናቱ መከናወን ፈቃደኞች ለሆኑት የተመረጡ ዐሥራ ዘጠኝ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አጥቢያ መሪዎች እና የዳሰሳ ጥናቱን መጠይቆች ለሞሉ ምእመናን ሕንጸት ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።

1. መግቢያ

እንደ ሌላው ዓለም ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትም የመድረክ አገልግሎት የክርስትና አምልኮ አንድ ቍልፍ አካል ነው። የመድረክ አገልግሎት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ፣ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለጕባዔ አባላት የምታደርስበት ዋና መንገድ ሆኖ ቈይቷል።

ይሁን እንጂ፣ የመድረክ አገልግሎት በባሕርይው የሁለት ወገን መስተጋብርን የሚፈቅድ አይደለም። ከዚህ የተነሣ፣ መድረክ ላይ ሆነው የሚያገለግሉ አገልጋዮች ጕባዔው ከምስባኩ የሚተላለፈውን መልእክት በምን መልኩ ተረድቶታል የሚለውን ለመገንዘብ የሚችሉበት ዕድል እምብዛም የለም።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወንጌላውያን ቤተ እምነቶችና አብያተ ክርስቲያናት ቍጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ባለፉት ሁለትና ሦስት ዐሥርት ዓመታት፣ የወንጌላውያን አማኞች ቍጥርም የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። ዳሩ ግን ከዚህ ቍጥር ጭማሬ ጋር ተያይዞ የመድረክ አገልግሎት በወንጌላውያን ጕባዔ ተሳታፊዎች ዘንድ እንዴት ይታያል የሚለውን ለመገንዘብ የተደረገ ይህ ነው የሚባል ጥረት አይገኝም። ከጕባዔ ተሳታፊዎች ቍጥር፣ በሰው በሰው ከሚነገሩ አንዳንድ ነገሮች፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚዘዋወሩ ልውውጦች ከሚያስገኟቸው ያልጠሩ ምልከታዎች ባለፈ፣ አብያተ ክርስቲያናትና ቤተ እምነቶች የመድረክ አገልግሎት በጕባዔው ዘንድ እንዴት ይታያል የሚለውን በውል ለመረዳት ምንም ዐይነት ሁሉ ዐቀፍ ዘዴ ሲጠቀሙ አልታየም።

ሌሎች ጥረቶች ማስፈለጋቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ የመድረክ አገልግሎት ውጤታማነት ላይ ብርሃን ለመፈንጠቅ የጕባዔ ተሳታፊዎች እንዴት ያዩታል የሚለውን መገንዘብ ወሳኝ ነው። የጕባዔ ተሳታፊዎች ከመድረክ ስለሚተላለፈው አገልግሎት ያላቸው አመለካከት፣ ከአገልግሎቱ የሚያገኙትን መልእክት ምን ያህል ተቀብለው ከሕይወታቸው ጋር በማዋሓድ፣ እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት ለመኖር ይጠቀሙት እንደሆን ይወስናል።

ይህን ዐውድ ይዞ፣ ይህ የዳሰሳ ጥናት ኢትዮጵያውያን ወንጌላውያን አማኞች አገልግሎት በሚካፈሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት ስላለው የመድረክ አገልግሎት ያላቸውን አመለካከት ለመዳሰስ ያለመ ነው።

የዳሰሳ ጥናቱ በተለይ ሦስት የመድረክ አገልግሎት ቅርጾች ላይ ያተኰረ ሲሆን፣ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፦

 • የትምህርት/ስብከት አገልግሎት፣
 • የዝማሬ አምልኮ አገልግሎት፣ እንዲሁም
 • የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት።

ይህ የዳሰሳ ጥናት የተካሄደው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተመረጡ ጥቂት ቤተ እምነቶች እና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ነው። በርግጥ የዳሰሳ ጥናቱ የሚያመለክተው ውጤት አጠቃላዩ ሁኔታ እንዲህ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር አያስደፍር ይሆናል። ይሁን እንጂ፣ ከዳሰሳ ጥናቱ የተገኘው ውጤት እንዲሁም በውጤቱ ላይ ተመርኩዞ የተሠራው ትንታኔ፣ የዳሰሳ ጥናቱ በተካሄደባቸው አብያተ ክርስቲያናትና ቤተ እምነቶች፣ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአዲስ አበባ በአጠቃላይ፣ የወንጌላውያን ጕባዔ ተሳታፊዎች የመድረክ አገልግሎትን አስመልክቶ ስላላቸው ዕይታ በቀላሉ የማይገመት መረጃ ሊገኝበት የሚችል መሆኑ እሙን ነው።

2. ዐላማ

ይህ የዳሰሳ ጥናት የተካሄደው አንድ ዐላማ አንግቦ ሲሆን፣ ይኸውም፦

የመድረክ አገልግሎትን (ማለትም ስብከት/ትምህርት፣ የዝማሬ አምልኮ፣ እንዲሁም ጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ዘርፎችን) በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ያላቸውን ዕይታ ወይም እንዴት ይመዝኑታል የሚለውን መቃኘት ነው።

3. ጥናቱ የተጠቀመው ዘዴ

ከላይ የተገለጸውን ዐላማ ለማሳካት፣ የሚከተለው የጥናት ዘዴ ጥቅም ላይ ውሏል፦

 1. የዳሰሳ መጠይቅ ዝግጅት፦ ከመድረክ አገልግሎት ጋር ተያይዘው የሚነሡ ጕዳዮችን ሁሉ የሚዳስስ መጠይቅ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ውሏል። መጠይቁ አማኞች የመድረክ አገልግሎትን ውጤታማነት፣ ፋይዳና የሕይወት ተዛምቶ፣ አሳታፊነት፣ እንዲሁም በግል ስላሳደረባቸው ተጽዕኖ ምዘናቸውን እንዲያካፍሉ ተጠይቀዋል።
 2. የናሙና ምርጫ፦ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትና ቤተ እምነቶች መካከል ሆነ ተብሎ የሚደረግ ወካይ የናሙና ምርጫ (purposive sampling) ጥቅም ላይ ውሏል። ውጤቱን በተቻለ መጠን ሁሉንም የሚወክል እንዲሆን፣ የናሙና ምርጫው የተደረገው ቀደም ሲል በተወሰኑ አካባቢያዊ እና የቤተ እምነት ወሰኖች ውስጥ ነው።
 3. መረጃ አሰባሰብ፦ መጠይቁ የተሞላው የጥናት ቡድኑ አባላት በተመረጡት አብያተ ክርስቲያናትና ቤተ እምነቶች በአካል ተገኝተው፣ የመላሾችን ማንነት ምስጢራዊነት በጠበቀ መልኩ ነው።
 4. የመረጃ ትንታኔ፦ ከዳሰሳ መጠይቁ የተሰበሰበውን ጥሬ መረጃ ለማደራጀትና ለመተንተን፣ የስታትስቲክ ዘዴዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። በመሆኑም፣ አማኞች የመድረክ አገልግሎትን አስመልክቶ ያላቸውን ምዘናና ዕይታ በማብራራት ሂደት ውስጥ፣ ገላጭ የስታትስቲክ ዘዴ (descriptive statistics) እንዲሁም የተዛምዶ ትንታኔ (inferential analysis) ልዩ ልዩ አዝማሚያዎችን እና ተዛምዶዎችን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውለዋል።
 5. የሥነ ምግባር ጥንቃቄ፦ ለዳሰሳ መጠይቁ መልስ የሰጡ መላሾች ሁሉ የጥናቱ ዐላማና ይዘት ተገልጾላቸው፣ ፈቃደኝነታቸው ተጠይቆ፣ በጥናት ውስጥ የማንኛቸውም ማንነት ምስጢራዊነቱ እንደሚጠበቅ ተነግሯቸው ሂደቱ ተከናውኗል።


4. ዘገባ እና ትንታኔ

በሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር ከሰኔ – ሐምሌ 2015 ዓ.ም. አማኞች የመድረክ አገልግሎት ላይ ያላቸውን አመለካከት የሚመዝን ዳሰሳ በዐሥራ ዘጠኝ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተላከ፣ የግል መረጃን አጠቃልሎ አርባ ጥያቄዎች ያሉት መጠይቅ ተበትኖ ነበር። የተደረገው ዳሰሳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄደው የመድረክ ላይ አገልግሎት የሚያጠቃልለውን የትምህርት እና ስብከት፣ የዝማሬ አምልኮ እንዲሁም የጸሎት እና ነጻ የማውጣት አገልግሎትን በተመለከተ የአገልግሎት ተደራሽ የሆነው የቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ዕሳቤ ለመቃኘት የተሠራ ነው።

ይህን መጠይቅ የሞሉት መላሾች በዕድሜ፣ ጾታ እንዲሁም በአማኝነት የቈዩበት ዘመን ብዝኃነቱን የጠበቀ ነው። ይህም ልዩነት ከተለያየ ቤተ እምነት የመጡ ተደራሾች ከመሆናቸው ጋር ሲደመር፣ የተሰበሰበው ምላሽ ከወጥ ወይም ተመሳሳይነት ካለው የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ብቻ የተገኘ እንዳልሆነና ምላሹም በሚገባ ቤተ ክርስቲያንን መወከል የሚችል መሆኑን የሚጠቁም ነው። የተሰበሰበው መረጃ፣ ከዳሰሳ ጥናቱ የተገኘው በጎ ጐንም ሆነ ችግር፣ ሁሉንም የሚነካ መሆኑን ያሳያል።

ምስል 1 እና 2፦ የመላሾች የዕድሜና የጾታ ተዋጽዖ

በምስሉ ላይ መመልከት እንደሚቻለው፣ የመጠይቁ ተሳታፊዎች የዕድሜ ክልል ተገቢ ስብጥርን የያዘ ሲሆን፣ በተለይ ዕድሜያቸው ከ24 – 54 የሆኑት ከመቶ 72.1 ድርሻ የሚይዙ ናቸው። ይህ የዕድሜ ክልል በአብዛኛው፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አዋቂ በሚባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚታቀፍ ሲሆን፣ በተለይም በመድረክ አገልግሎትና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች የሚሳተፍ፣ በተለያየ የሕይወት መንገዶች ላይ በመሪነት (በቤተ ሰብ፣ በሥራ፣ በማኅበረ ሰብ፣ ወዘተ.) ላይ ያለ የዕድሜ ክልል ነው። ይህም በማኅበረ ሰቡ ውስጥ በዕድሜ ከፍ ባለው እና በታዳጊዎች መካከል ያለውን ክፍተት የሚሸፍን ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ድልድይ በመሆን የሚያገለግል ጭምር ነው። ከዚህም የተነሣ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለው የመጠይቁ ተሳታፊ የሚሰጠው ምላሽ ተጽዕኖ ከፍተኛነት ከግምት ውስጥ የሚገባ ይሆናል (Roberto, 2015, Seasons of Faith)።

የመጠይቁ ተሳታፊዎች በክርስትና እምነት ለብዙ ዘመናት የቈዩ ሲሆን፣ በምስሉ ላይ መመልከት እንደሚቻለው 80.8 ከመቶ የሚሆኑት በክርስትና ከ10 – 40 ዓመታት ያስቈጠሩ ናቸው። ይህም ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚኖራቸው አመለካከት በብዙ ዘመን ልምድ እና አገልግሎት ጭምር የተደራጀ መሆኑን ያመላክታል። ምላሽ ከሰጠው የዳሰሳው ተሳታፊ መካከል 68.3 ከመቶው በሳምንት ሁለት ጊዜ እና ከዚያ በላይ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሚከናወን የመድረክ አገልግሎት ላይ በተገልጋይነት የሚሳተፍ ሲሆን፣ 97.1 ከመቶ የሚሆነው ደግሞ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚሳተፍ ነው። ይህም መጠይቁ የያዘውን ጭብጥ በተገቢው መንገድ ተረድተው ምላሽ ሰጥተዋል ለማለት ያስደፍራል።

ምስል 3 እና 4 መላሾች በአካል የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን የማዘውተራቸው ልክ እና በአማኝነት ያስቈጠሩት ጊዜ

ቀጣዩ ምስል መላሾች ባሉበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚሳተፉባቸውን ሳምንታዊ መርሓ ግብሮች የሚያመለክት ነው። ከውጤቱ መመልከት እንደሚቻለው፣ አብላጫዎቹ መላሾች በእሑድ አምልኮ እና በትምህርት ጊዜ መርሓ ግብሮች የሚሳተፉ ሲሆን፣ በወጣት፣ ታዳጊ እና ሴቶች የአገልግሎት መርሓ ግብሮች ላይ መሳተፋቸውን የገለጹ አነስተኛ ቍጥር ያላቸው መላሾች አሉ። የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት የሚካፈሉ ሰዎች ከመላሾች መካከል 29.1 ከመቶ ሲሆኑ፣ ይህም ቍጥር አነስተኛ ተሳትፎ በመሆኑ በመጠይቁ ክፍል ሦስት ሥር የተመለሱትን ጥያቄዎች ላይ የሚሳድረው ተጽዕኖ ታሳቢ ይሆናል።

ምስል 5፦ መላሾች አዘውትረው የሚካፈሉት መርሓ ግብር


4.1     ክፍል አንድ፦ የስብከት/ትምህርት የመድረክ አገልግሎት ዕይታ

የስብከት/ትምህርት የመድረክ አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ፊተኛ ከሚባሉት አንዱ ሲሆን፣ መጠይቁ በተሞላባቸው ቤተ ክርስቲያናት አገልግሎቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና በተጋባዥ አገልጋዮች አማካይነት ይሰጣል። በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት ተገባዥ ሰብኪዎችና አስተማሪዎች የሚበዙባቸው አጋጣሚዎች አሉ። የስብከት እና ትምህርት አቀራረቡም በገላጭ ስብከት፣ ርእሳዊ ስብከት፣ በአንድ ዐሳብ ላይ ተከታታይነት ባለው መልኩ የሚቀርብ ስብከት/ትምህርት የሚሰጥባቸው ናቸው። ይሁን እንጂ፣ ተጋባዥ ሰባኪዎች/አስተማሪዎች በሚያይሉባቸው መድረኮች፣ ወጥነት ያለው መልእክት ለመጨበጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን ዐሳባቸውን ያካፈሉ የመጠይቁ መላሾች አሉ። አንድ ምላሽ ሰጪ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል፦ 

አንድ እሑድ፣ ለአንድ ወንድሜ በመንፈስ የክርስቶስን የመስቀል ሥራ፣ በእግዚአብሔር ብርቱ በሆነው ፍቅር እንዴት እንደተወደድን፣ ከዚያም የተነሣ በክርስቶስ የሆነውን ማንነታችን ሲገለጥ ተደንቄ፣ የተሰማኝን ስገልጽለት፣ ምን ዋጋ አለው፤ [በቀጣዩ] ሳምንት አንዱ መጥቶ እንክርዳድ ይዘራበታል አለኝ። ይህ አባባሉ እውነት ሆኖ አገኘሁት።

ይህ እና መሰል አስተያየቶች፣ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ወጥነት የጎደለው፣ የመርሓ ግብር መካሄድ ላይ ብቻ ትኵረት ያደረገ የአገልጋይ ምድብ እና ስብጥር፣ ሥርዐት ያልተበጀለት የስብከት/ትምህርት አገልግሎት እንዳለ የሚጠቁሙ ናቸው።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የመድረክ ላይ ትምህርት/ስብከት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን በከፍተኛ ደረጃ የጠበቀ እንደ ሆነ 67.7 ከመቶ የሆኑ መላሾች እንደሚያስቡ ሲናገሩ፣ 21.4 ከመቶ የሚሆኑት መላሾች ግን አነስተኛ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አጠባበቅ በዚህ አገልግሎት ላይ እንደሚመለከቱ ተናግረዋል። 89.6 ከመቶ የሚሆኑት መላሾች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ለትምህርት/ስብከት አገልግሎት አስፈላጊ መሆኑን የሚያምኑ ናቸው።

ይህ ውጤት በመድረክ ላይ ያለው የትምህርት/ስብከት አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱስን ዋና ይዘት እና የትምህርት መሠረት ማድረጉ ላይ ጉድለት ያለበት ተደርጎ እንደ ሆነ በጥቂቱ ማሳያ ነው። የሚከተሉት ወካይ ምላሾች በምእመኑ ዘንድ ያለውን በልምዳቸው ላይ የተመሠረተ ዕሳቤ አመላካች ናቸው፦

      . እኔ ባለሁበት ቤተ ክርስቲያን በአንጻሩ ትምህርት የሚበዛ መሆኑ መልካም ሲሆን ሌሎችም ምእመናን ለማነጽ የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማር ላይ ትኵረት ቢሰጡ

      . በአንድ አጋጣሚ የሄድኩበት ጕባዔ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍቶ ሳያነብብ፣ ሳይጸልይ፣ የመሰለውን ነገር ከዐሳቡ አውጥቶ በመናገሩ ምክንያት፣ ብዙ ሰው ውዥንብር ውስጥ ገብቶ ከጩኸትና ከግርግር ያለፈ ቁም ነገር ሳላይ ወጥቻለሁ።

      . ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደን ጥቅስ/ክፍል ከዐውዱ ውጪ በሆነ መልኩ አጠቃላይ የሆነውን የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዐሳብ እና የመጽሐፍ ቅዱሳን ጠቅላላ ዐሳብ ያላማከሉ ስብከቶች/ትንቢቶች ይዘወራሉ

. መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ሳያጠኑ የሚመጡ ሰዎች ስብከት አጋጥሞኛል


የመጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊነት እና ማእከላዊነት በመጠይቁ መላሾች ዋና ቦታ የተሰጠው ሲሆን፣ በአድማጩ ሕይወት ውስጥ መልእከቱ እንዲሠርጽ እና የተማሩትን በሚገባ በሕይወታቸው ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የሚቀርብ መሆኑ ከመላሾች ዘንድ በአብዛኛው አዎንታዊነቱ የሚያመዝን ምላሽ ተሰጥቶታል። ከመድረክ የሚሰጡ ትምህርቶች ተግባራዊ ፋይዳቸው ላይ 73 ከመቶ የሚሆነው መላሽ ከፍተኛ ነው ያለ ሲሆን፣ እንዲሁም የሕይወት ተዛምዶው ከፍ ያለ መሆኑን 63 ከመቶ መላሾች ገልጸዋል። ይሁን እንጂ፣ የሚቀርበው ስብከትም ሆነ ትምህርት በምእመናን ሕይወት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን የሚያሰርጹ ስለ መሆናቸው በተነሣው ጥያቄ ላይ 55.8 ከመቶ የሚሆነው መላሽ ከፍተኛ እና በጣም ከፍተኛ ነው የሚል መልስ የሰጠ ሲሆን፣ 25.9 ከመቶው አላውቅም የሚል፣ 18.9 ከመቶው የሚሆነው ደግሞ አነስተኛ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይህም በመጀመሪያ ከተነሣው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን የጠበቀ እና የሕይወት ተዛምዶ ያለው ስብከት እና ትምህርት ይቀርባል ከሚለው አብላጫ ዐሳብ ጋር አብሮ መታየት አለበት።

የዳሰሳ ጥናቱ ተሳታፊ መልስ ሰጪዎች በትምህርት እና ስብከት የመድረክ አገልግሎት ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት በመቀጠል በአገልግሎቱ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው የትምህርቱ/ስብከቱ ለሕይወት ያለው አስፈላጊነት ወይም ፋይዳ፣ እንዲሁም የአስተማሪው/ሰባኪው ዝግጅት መሆኑን እንደሚያምኑ ገልጸዋል። ቀጣዩ ምስል መላሾች ለትምህርት/ስብከት አገልግሎት አስፈላጊ ነው ያሉት የቱ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ምስል 6፦ ይበልጥ አስፈላጊ የተባሉት የስብከት/ትምህርት መገለጫዎች

የተገኙት አብላጫዎቹ ምላሾች መድረክ ላይ የሚቀርበው ስብከት/ትምህርት ከአገልጋዮቹ ሕይወት ጋር በሚገባ የተዋሓደ እንዳልሆነ እንደሚያምኑ የሚጠቁሙ ናቸው። አድማጮች መልእክቱን ከመስማት ባሻገር፣ የሚቀርብበትን መንገድም ልብ ይላሉ፤ አገልጋዩ ምን ያህል ተዘጋጅቶበታል የሚለውን ያጤናሉ፤ እንዲሁም ለዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ያለውን ፋይዳ ይመዝናሉ። አብላጫዎቹ መላሾች አገልጋዮቹ በሚያገለግሉበት ርእሰ ጕዳይ ላይ በቂ እውቀት አላቸው ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል፤ እንዲሁም በቂ ዝግጅት እንደሚያደርጉ፣ እንዲሁም ለጕባዔው በሚስማማ መልኩ ያቀርባሉ ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከፍተኛ ቍጥር ያላቸው መላሾች ሰባኪው ወይም አስተማሪው በሚናገርበት ርእሰ ጕዳይ በቂ እውቀት ይኖረው እንደሁ አሊያም በቂ ዝግጅት አድርጎ እንደሁ ለመናገር እንደሚቸግራቸው ገልጸዋል። ቀጣዮቹ ወካይ ተጨማሪ ምላሾች፣ ከዚህ አኳያ ያለውን መደበላለቅ የሚጠቁሙ ናቸው፦

      . በአብዛኛው የተካፈልኩት የቃል ጊዜ እጅጉን ደስ ይላል። ነገር ግን አንድ አንድ ብዙም የመንፈሳዊ ሕይወት ብስለት የሌላቸው አገልጋ አልፎ አልፎ ያጋጥማሉ። ብዙም ብስለት ከሌላቸው ሰዎች ቃል መካፈል ብዙ ጊዜ ይረብሸኛል ምክንያቱም የአገልግሎቱ ሳብ ፍሰት የሚዘበራረቅ ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።

      . አብዛኛውን መልካም ቢሆንም አንዳንድ ስብቶች [ከተነሡበት] እና ጥቅስ ውጪ የሆነ ምስክርነት፣ ሳብ እና ሌላ ጥቅስ ውስጥ ይገባሉ ይህም አንድ ረታዊ የሆነ ሳብ አያስይዝም።

      . ከር ጋር የማይሄድ የተንዛዛ ምስክርነት [ያጋጥማል]

      . ብዙ ጊዜ በሚገባ ተዘጋጅተው የሚመጡ ሰባኪዎች ናቸው የሚገጥሙኝ። ነገር ግን በቂ ዝግጅት ያላደረጉ ገጥመውኛል

      . ከስብከት ጋር በተገ በቂ የመልእክት ፍሰት የላቸውም ጊዜ አጠቃቀም ደካማ ነው

አድማጩ ምእመን ከመድረክ ላይ የሚሰጠውን መልእክት እንደ ወረደ ዐሳቡን ብቻ ሳይሆን፣ የሚያገለግለው ሰው መልካም ምስክርነት፣ ዝግጅቱ እና አቀራረቡ ጭምር ለመማሩ ምክንያት እንደሚሆን መመልከት እንችላለን። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የማስተማር እና የስብከት የመድረክ አገልግሎት፣ በምስባኩ የቈመውን የአቅራቢውን ማንነት ጭምር በሚገባ የሚዳስስ፣ የሰባኪውና አስተማሪው የሕይወት አርአያነት፣ እንዲሁም ትምህርቱ ወይም ስብከቱ ላይ ለመወያየት፣ ለመነጋገርና ለመተራረም ያለው ልብ እንዲሁ በምእመኑ ዘንድ ቦታ አለው። መጠይቁን ከሞሉ ሰዎች መካከል 27.9 ከመቶ የሚሆኑት የአስተማሪው/ሰባኪው የሕይወት አርአያነት መሻሻል የሚያስፈልገው መሆኑን ሲገልጹ፣ 14.9 ከመቶ የሚሆኑት ምንም አይልም፣ 32.3 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ መልካም አርአያነት ያለው ሕይወትን እንደሚመለከቱ አስፍረዋል። በቀጥታ ከሰባኪው ወይም አስተማሪው ጋር ተገናኝቶ የመጠየቅም ሆነ የመነጋገር ዕድልን ከማግኘት አንጻር 41.5 ከመቶ የሚሆኑት ዕድሉ ስለመኖሩ እንደማያውቁ የገለጹ ሲሆን፣ 33.8 ከመቶ የሚሆኑት “ምንም አይልም” የሚል ምላሽ አስቀምጠዋል፤ ይህም በአጠቃላይ ከዚህ አኳያ አሉታዊ ዕሳቤን መኖሩን የሚያመላክት ነው።

መደምደሚያ

መድረክ ላይ የሚቀርበው የትምህርትና ስብከት አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን መጠበቅ ያለበት፣ የሚነገረው መልእክትም በምእመናን ሕይወት ውስጥ ያለውን ፋይዳ እና ተግባራዊነት ማመላከት የሚገባው ነው። ከመልእክቱ ይዘት በተጨማሪ፣ የአገልጋዩ የሕይወት ምስክርነት፣ ዝግጅት እና አቀራረብ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በምእመናን ዘንድ ይታመናል። መላሾች በስብከትና ትምህርት ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል ማዕከላዊነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ። በተጨማሪም፣ የትምህርትና ስብከት አገልግሎት ለዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ተግባራዊ ፋይዳ ያላቸው መርሖዎችን የሚያገኙበት አገልግሎት ነው ብለው ያስባሉ።

4.2     ክፍል ሁለት፦ የዝማሬ አምልኮ የመድረክ አገልግሎት ዕይታ

ይህ የዳሰሳ ጥናት በበርካታ የተመረጡ አብያተ ክርስቲያናት ጕባዔዎች ውስጥ ተካፋይ የሆኑ ሰዎች ስለ ዝማሬ አገልግሎት ያላቸውን ዕይታ አጢኗል። የተገኘው ውጤት ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት መላሾች የዝማሬ አምልኮ አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው ብለው የሚያምኑ መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን፣ 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አገልግሎቱ ራሱን ችሎ እንደ አገልግሎት ዘርፍ ለመታየት በቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ይኖረው እንደሁ እንደማያውቁ አሊያም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትነት አለው ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል። ዳሩ ግን፣ ከመላሾች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መድረክ ላይ የሚቀርበው የዝማሬ አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን በጕባዔ ተካፋዮች ሕይወት ውስጥ ለማስረጽ ይረዳል ብለው የሚያምኑ ናቸው። 25.5 ከመቶ የሚሆኑት መላሾች መድረክ ላይ የሚቀርቡት ዝማሬዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን በጕባዔ ተካፋዮች ሕይወት ውስጥ ለማስረጽ አያግዙም ያሉ ሲሆን፣ 24.5 ከመቶዎቹ ደግሞ በዚህ ጕዳይ ላይ እንዲህ ነው ብለው ለመናገር እንደሚቸግራቸው አመልክተዋል። ይሁን እንጂ እነዚሁ መላሾች፣ የዝማሬ የመድረክ አገልግሎት በአማኞች ሕይወት ውስጥ ቍልፍ ሚና ይጫወታል ብለው እንደሚያምኑና ፋይዳውም የጎላ ነው ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል።

በዝማሬ አምልኮ አገልግሎት ውስጥ፣ መላሾች ይበልጥ አስፈላጊ ነው የሚሉት ምን እንደ ሆነ ለመረዳት፣ ቀጣዩን ምስል ይመልከቱ።

ምስል 7፦ ይበልጥ አስፈላጊ የተባሉት የዝማሬ አምልኮ አገልግሎት መገለጫዎች

የዝማሬ አገልግሎት ላይ ከመዝሙሩ ይዘት ባለፈ የዘማሪዎች ዝግጅት እና በዕለቱ ከሌሎች የመድረክ አገልግሎቶች በተለይም ከስብከት ወይም ትምህርት ጋር የተገናኘ ስለ መሆኑ ከምላሽ ሰጪዎች የተገኘው ምልከታ አዎንታዊነቱ ያመዝናል። በተለይም ከዝግጅት አንጻር ሲሦ የሚሆነው ምላሽ ሰጪ (32 ከመቶ) “አላውቅም” የሚል መልስ የሰጠ ሲሆን፣ 25 ከመቶ የሚሆነው ደግሞ አነስተኛ ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል። እንዲሁም በዕለቱ ከሚሰበከው ስብከት ወይም ከሚሰጠው ትምህርት ጋር የዝማሬ አገልግሎት ያለው ግንኙነት አነስተኛ ነው ብሎ የሚያምነው ምላሽ ሰጭ 36 ከመቶ ሲሆን፣ 32.5 ከመቶ የሚሆነው መላሽ “አላውቅም” በማለት ምልከታውን አስቀምጧል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፣ ዝማሬዎች ከዕለቱ መልእክት ጋር የበለጠ ተያያዥነት ቢኖራቸው እንደሚበጅ ዐሳባቸውን አካፍለዋል።

የዝማሬ አምልኮ አገልግሎት፣ በዝማሬ ጊዜ ጕባዔውን የሚያሳትፍና ዐብሮ ለማምለክ ዕድልን የሚፈጥር መሆኑን በሚመለከት ለተጠየቁት ጥያቄ፣ መላሾች አሉታዊነቱ የሚያመዝን ምላሽ ሰጥተዋል። 32.2 ከመቶዎቹ አሳታፊነቱ ላይ ርግጠኛ እንዳልሆኑ፣ 20.9 ከመቶዎቹ ደግሞ አሳታፊነቱ አነስተኛ መሆኑን በመግለጽ፣ በድምሩ 53.1 ከመቶ መላሾች አሳታፊ ነው ብለው እንደማያምኑ አሳይተዋል። ተከታዩ ተጨማሪ አስተያየት ይህን ያስረዳል፦

      በአንድ የአምልኮ ክፍል ጊዜ ቡድን/ኳየር አገልግሎትና የአምልኮ መሪዎች ተብሎ ሁለ ለዚህ ፕሮግራ ጊዜ መሰጠቱ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ጊዜውን ከመሻማቱ ባሻገር ድካምና መሰላቸት ያስከትላል ሌላው የአምልኮ መሪዎች ሕዝቡ [ዐብሮ] እንዲያመልክ [የሚያስችል] የሚታወቅ መዝሙር ስለማይዘምሩ ብዙ አስቀድሰን እንደምንመጣ ይነት ስሜት ነው የሚሰጠው

በተመሳሳይ መልኩ ዘማሪያን፣ እንደ አገልጋይ ያላቸው የሕይወት አርአያነት ላይ የምላሽ ሰጪዎች ምልከታ አሉታዊነቱ እንደሚያመዝን መመልከት ይቻላል። 35.7 ከመቶ የሚሆነው ምላሽ ሰጪ የዘማሪያኑ ሕይወት አርአያነት የሚጎድለውና መሻሻል የሚያስፈልገው እንደ ሆነ የሚያስብ ሲሆን፣ ተቀራራቢ በሆነ መጠን 33.7 ከመቶ የሚሆነው ደግሞ ስለ ዘማሪያኑ ሕይወት አርአያነት እንደማያውቅ ገልጿል። የዘማሪያንን የሕይወት አርአያነት በተመለከተ፣ የሚከተሉትን ዐሳቦች መሰብሰብ ተችሏል፦

. የአገልግሎት ዝግጅት አገልግሎት ሲሰጣቸው ብቻ ሳይሆን ሁሌም እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖሩ ይገል። ቅድስና የሁልጊዜ ኑሮ ስለ ሆነ ሁሌም በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ማንነት መኖር ነው ያለባቸው።

. የዘማሪዎቻችን ሕይወት መንፈሳዊ ሆነው ቤተ ክርስቲያን መጡ ወይም መድረክ ላይ ቆሙ ብቻ መሆን የለበትም። በሄዱበት ሁሉ ጌታን መሽተት አለባቸው እላለ በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያ አገልጋዮች ምክርና ክትትል ያስፈልጋቸዋል።

. ለታይታ የሆነ እና የተገላለጠ አለባበስ መኖር የለበትም

. የዘማሪዎች በተለይም የመሪያ ተጫዋቾች አለባበስና ፀጕ አቆራረጥ (ወንዶ) ሥርዐ የጠበቀ ቢሆን ጥሩ ነው ዘማሪዎች በአብዛኛው የዝማሬ ልብስ ስለሚለብሱ በዚሁ ቢቀጥል

እነዚህና መሰል አስተያየቶች፣ የዝማሬ አምልኮ አገልጋዮች ለአለባበሳቸውና አጠቃላይ አቀራረባቸው የበለጠ ትኵረት ሊሰጡ እንደሚገባ የሚያመለክቱ ናቸው።

መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የዝማሬ አምልኮ አካላዊ እንቅስቃሴን የሚቀሰቅስ መሆኑ የተለመደ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ 55 ከመቶ ያህሉ መላሾች በቤተ ክርስቲያን ከዝማሬ አምልኮ ጋር የሚታየው አካላዊ እንቅስቃሴ ጤናማ ነው ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል። 23.7 ከመቶ መላሾች ያለው አካላዊ እንቅስቃሴ ጤናማነት የጐደለው ነው ብለው እንደሚያምኑ የገለጹ ሲሆን፣ 21.1 ከመቶ የሚሆኑት ስለዚህ ጕዳይ የሚያውቁት ወይም የሚሉት ነገር አለመኖሩን አመልክተዋል። ቀጣዩ ምስል የዚህን ምላሽ ስብጥር የሚያሳይ ነው።

ምስል 8፦ በዝማሬ አምልኮ ጊዜ የሚደረገው አካላዊ እንቅስቃሴን በተመለከተ

ይህ ምላሽ ከሚከተሉት ወካይ አስተያየቶች ጋር ተያይዞ ሊታይ የሚገባው ነው፦

. ከቤተ ክርስቲያን ያሉ አገልጋዮች ዐልፎ ዐልፎ ወጣ ያለ እንቅስቃሴ ንዲያዩ ምእመኑን መጋበዝ የተለያዩ ልምምዶችን ማምጣት አስተውያለሁ

. በተለይ ከሙዚቃ ጋር የሚደረገው እንቅስቃሴ ቃሉን መስማታችን ነው መዝሙር መሆኑ የሚታወቀው እንጂ አንድ መስማት የተሳነው ሰው ዘፈንና መዝሙርን ለይ ቢባል መለየት የማይችልበት ወቅት ላይ ነን።


መደምደሚያ

የዝማሬ አምልኮ አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ እውነትን በጕባዔ ተካፋዮች ሕይወት ውስጥ እንዲያሠርጽ ከተፈለገ፣ ብዙ ሥራ መሠራት እንደሚያስፈልገው የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት ያመለክታል። ይህ እንዲሆን፣ መዝሙሮች ይበልጥ ቃለ እግዚአብሔር ላይ የተመረኮዙ መሆን ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም የዳሰሳ ጥናቱ ተሳታፊዎች መድረክ ላይ የሚዘመሩት መዝሙሮች ከምስባክ ከሚሰማው ስብከት ወይም ትምህርት እንዲሁም ከሌሎች የመድረክ አገልግሎቶች ጋር ያላቸው ተያያዥነት አነስተኛ ነው ብለው ያምናሉ። መዝሙሩ የሚቀርብለትና ዐብሮ እንዲዘምር የሚጠበቀው ምላሽ ሰጪ፣ በቤተ ክርስቲያን ያለው ዝማሬ ከዕለታዊ ኑሮ ጋር ያለው ፋይዳና ከዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር ያለው ተያያዥነት ላይ ርግጠኛ አይደለም፤ በሕይወት ላይ የሚጨምረው ይህ ነው የሚባል ዋና ነገር ምን እንደሆነም አያውቅም። የዘማሪያን ሕይወት ላይ የአርአያነት ጕድለት አለ የሚለው ምልከታ፣ እንዲሁም የአገልግሎት ዝግጅት ማነስ ይታይባቸዋል የሚለው ዐሳብ ተጨማሪ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል።

4.3     ክፍል ሦስት፦ የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ዕይታ

የዚህ ዳሰሳ ጥናት መጠይቅ እንዲሞላ የተበተነባቸው 19 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ መጠይቁን የሞሉት ምእመናንም በሁለት ተከታታይ እሑዶች ከነበሩ የጕባዔ ተሳታፊዎች መካከል በዘፈቀደ የተመረጡ ናቸው። ይህ የተደረገውም መጠይቁን የሞሉት ሰዎች ምላሽ የሚሳተፉበት መርሐ ግብር ላይ ባላቸው ልምምድና እውቀት ላይ ብቻ የተመሠረት እንዲሆንና በተቻለ መጠን ትክክለኛ ወካይ መረጃ መሰብሰብ እንዲቻል ነው።

ከዳሰሳ ጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል 61.9 ከመቶ የሚሆኑት የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎትን የሚካፈሉት ዐልፎ ዐልፎ እንደ ሆነ የገለጡ ሲሆን፣ 29.6 ከመቶ የሆኑት ደግሞ በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ እንካፈላለን ብለዋል። ይህም የሚያሳየው አብዛኛው መላሽ የአገልግሎቱ ዘወትር ተካፋይ መሆኑን ነው። በተጨማሪም፣ 64 ከመቶ ያህሉ መላሾች የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት በቤተ ክርስቲያን እንደ አንድ መርሐ ግብር መካሄዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ብለው ያምናሉ። እንዲሁም፣ የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት በግል ሕይወት ላለ መንፈሳዊ ውጊያ አስፈላጊነቱ ላይ 36.8 ከመቶ የሚሆኑት በጣም ከፍተኛ እንደ ሆነ ሲያምኑ፣ 44.2 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ለምእመናን ሕይወት መታነጽ አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

ምስል 9፦ የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ለምእመናን ሕይወት መታነጽ ያለው ጠቀሜታን በተመለከተ

የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትና ለግል ሕይወት ያለውን አስፈላጊነት አስመልክቶ ምላሽ ሰጭዎች በከፍተኛ መጠን አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ያም ሆኖ መላሾቹ የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት አስፈላጊነትና መጽሐፍ ቅዱሳዊነት ላይ እምነት ቢኖራቸውም፣ በመርሐ ግብሩ ላይ ያላቸው ተሳታፊነት በአንጻራዊነት ሲታይ አነስተኛ እንደ ሆነ ገልጸዋል። የሚከተሉት ወካይ አስተያየቶች እንዲህ ያለውን ልዩነት የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ናቸው፦

. ቃሉ ቢሰበክ፣ በቃሉ ረት ጸሎት ሲደረግ መንፈስ ቅዱስ እንደወደደ ሰዎችን ነጻ ያወጣል ብዬ አምናለሁ፤ ነጻ የማውጣት ጊዜ ብሎ መወሰን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ብዬ አላስብም።

. ንደዚህ ያለ ፕሮግራም መካፈል አልወድም በተለየ አጋጣሚ ሲገጥመኝ ግን ፕሮግራሙን ለመካፈል እጥራለሁ

. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጸሎት/ነጻ የማውጣት አገልግሎት የተለየ ፕሮግራም [መኖሩ] በግሌ ባይመቸኝም፣ አገልግሎቱ ግን ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። በዚህ አገልግሎት በጣም የተጠቀምሁ ሰው ነኝ።

የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለሆነ ክርስቲያናዊ ሕይወት ላይ ያለው ፋይዳ ላይ ጥያቄ ባይኖርም፣ በምላሽ ሰጭዎች ዘንድ አገልግሎቱ ውስጥ ስላለው የመንፈስ ቅዱስ ምሪትም ሆነ ስለሚመጣው መልእክት ተዓማኒነት ርግጠኝነት ማጣታቸው ያመዝናል። 26.7 ከመቶ የሚሆነው ምላሽ ሰጪ አገልግሎቱ ለመንፈስ ቅዱስ ምሪት መገዛቱ ላይ ርግጠኛ አይደለም፤ 32.6 ከመቶ የሚሆነው ምላሽ ሰጪም የሚመጣው መልእክት ወይም ትንቢት ተዓማኒነት ላይ ጥርጣሬ አለው። ከአገልግሎቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትን መጠበቅ (89.6 ከመቶ) ቀጥሎ፣ 60.6 ከመቶ መላሾች ለአገልግሎቱ ዋና አስፈላጊ ነገር ያሉት የመልእክቱን ተዓማኒነት መሆኑን ልብ ይሏል።

አንድ አስተያየት ሰጭ እንዲህ ይላሉ፦

አንዳንድ የሚታዩ ነጻ መውጣት ላይ፣ አጋንንት ከወጣ በኋላ በተደጋጋሚ አጋንንት የመጮኽ ጕዳይ፣ ይህም ጊዜ ሰጥተው አጋንንት ለያዘው ሰው አላመጸለይ በተደጋጋሚ እንዲጮኽ ማድረግ [ችግሮች ይስተዋላሉ።]


ከዚህ አስተያየት ጋር የሚመሳሰሉ የትንቢት ግልጽ አለመሆን፣ የሰው ምስጢር አለመጠበቅ፣ አጋንንት ከማስወጣት ሂደት አግባብነት መጓደል እና የመሳሰሉ ጕዳዮች ከአገልግሎቱ ጋር በተያያዘ ደጋግመው የሚነሡ አሉታዊ ምልከታዎች ናቸው።

ምስል 10፦ የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት የሰዎችን ግላዊና ሰብአዊ ክብር ምን ያህል ይጠብቃል የሚለውን በተመለከተ

42 ከመቶ መላሾች የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት የሰዎችን ግላዊ እና ሰብዓዊ ክብር በአግባቡ አይጠብቅም ብለው ያምናሉ። ይህም ለሰዎች የሚደረግ ጸሎትን፣ መልእክት ወይም ትንቢት ማምጣት፣ እንዲሁም አጠቃላይ መስተጋብርን የሚያጠቃልል ነው።

የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልጋዮች የሕይወት ምስክርነት እና አርአያነትን አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ የተሰጠውን መልስ ስንቃኝ፣ ይህን በተመለከተ ያለው ዕሳቤ የሰባኪያን/አስተማሪዎች እና የዘማሪያን ሕይወት ላይ ከታየው በአንጻራዊነት እጅግ የከፋ ሆኖ ይገኛል። 25.3 ከመቶ መላሾች የአገልጋዮቹ ሕይወት ምስክርነት መሻሻል የሚያስፈልገው ነው ያለ ሲሆን፣ 7.7 የሚሆነው ደግሞ ፍጹም አርኣያነት ይጐድለዋል ብለው እንደሚያምኑ አመላክተዋል። 49.2 ከመቶ የሚሆነው መላሽ፣ ለጸሎትና ነጻ ማውጣት አገልጋዮች የሕይወት ምስክርነት የአገልገሎታቸው እጅግ አስፈላጊ አካል እንደ ሆነ እንደሚያምኑ አመላክተዋል።


መደምደሚያ

የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ላይም ሆነ ለክርስትና ሕይወት ያለው አስፈላጊነት ላይ እምብዛም ጥያቄ ያነሣ መላሽ ባይኖርም፣ ነገር ግን ውጤታማነቱ፣ የአገልጋዮቹ የሕይወት ምስክርነት እንዲሁም የአገልግሎቱ እውነተኝነት ወይም ሐቀኝነት ላይ ዐሳሳቢ ጥያቄዎች ይነሣሉ።

5. የተዛምዶ መረጃ ትንተና

የመድረክ ላይ አገልግሎት ዕይታ ጥናት የተዛምዶ መረጃ ትንተና፣ በዳሰሳ ጥናቱ የተገኘውን መረጃ እርስ በርስ በመመሳከር የተገኘውን ትንተና በሦስት ክፍል የሚያቀርብ ነው። እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ፣ የመጀመሪያው ክፍል የስብከት/ትምህርት የመድረክ አገልግሎት ዕይታን፣ ሁለተኛው ክፍል የዝማሬ አምልኮ የመድረክ አገልግሎት ዕይታን፣ ሦስተኛው ክፍል ደግሞ የጸሎትና ነጻ የማውጣት የመድረክ አገልግሎት ዕይታን የሚያብራሩ ናቸው። የተገኙት ውጤቶች በእያንዳንዱ የትኵረት አቅጣጫ ሚና ያላቸው ልዩ ልዩ ጕዳዮች ከስታቲስቲክ አንጻር ዋጋ የሚሰጠው ተዛምዶ መኖሩን የሚያመለክቱ ናቸው። ይህ የመረጃ ትንተና በዋናነት የሚያተኵረው ጉልህ በሆኑ አዎንታዊ እና አሉታዊ ተዛምዶዎች ላይ ነው። የዚህ የጥናቱ ዘገባ ክፍል ዐላማ በተጠቀሱት የመድረክ አገልግሎት ዘርፎች ላይ ሚና ያላቸው ጕዳዮች ቍልፍ ተዛምዶ ማጤን ነው።


5.1. ክፍል አንድ፦ የስብከት/ትምህርት የመድረክ አገልግሎት ዕይታ

የስብከት/ትምህርት የመድረክ አገልግሎት ዕይታ በስምንት የመለኪያ መስፈርቶች ተመዝኗል። የመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከላዊነት፣ የአገልጋዩ እውቀት፣ የአገልጋዩ ዝግጅት፣ የአገልጋዩ የሕይወት ምስክርነት፣ የመልእክቱ አቀራረብ፣ መልእክቱን ለመረዳት በሚመችና ተስማሚ በሆነ መልኩ መቅረቡ፣ መልእክቱ በምእመናን ሕይወት ውስጥ ለማሥረጽ በሚያመች መልኩ መቅረቡ፣ የሕይወት ተዛምዶ፣ እንዲሁም ተግባራዊ ፋይዳ የሚሉት መስፈርቶች ጥቅም ላይ ውለዋል። ቀደም ሲል በቀረበው የዘገባና ትንታኔ ክፍል የዳሰሳ ጥናቱ የሰበሰባቸው ምላሾች ይዘት የቀረበ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በእነዚህ መስፈርቶችና ምላሽ ባገኙባቸው ዕይታዎች መካከል ተዛምዶ ይኖር እንደ ሆነ እናያለን።

በአገልጋዩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትና መልእክቱን በምእመናን ሕይወት ውስጥ የሚሠርጽ በመሆኑ መካከል ያሉት ዕይታዎች ጠንካራ አዎንታዊ ተዛምዶ ታይቶባቸዋል (r(204)=0.705, p<0.001, r2=0.497))። ከዚህ ውጤት ጋር ተያይዞ፣ የመልእክቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊነት ካለው የሕይወት ተዛምዶና ተግባራዊ ፋይዳ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው መላሾች እንደሚያስቡ ተንጸባርቋል ((r(204)=0.773, p<0.001, r2=0.759 እና r(204)=0.773, p<0.001, r2=0.759)። እነዚህ የስታትስቲክ ውጤቶች፣ ከመድረክ የሚተላለፉ መልእክቶች የሕይወት ተዛምዶና ተግባራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው፣ በቂ ዝግጅት፣ ተስማሚ አቀራረብ እንዲሁም በርእሰ ጕዳዩ እውቀት ባለው አገልጋይ የሚቀርቡ መሆን አለባቸው ተብለው እንደሚታሰቡ ግልጽ ጠቋሚዎች ናቸው።

ከላይ የተገለጹት ተያያዥነትን የሚጠቁሙ ውጤቶች፣ ከተመዘኑት መስፈርቶች መካከል ከሁሉ ጠንካራ ተዛምዶ የታየባቸው ናቸው፤ አንድምታቸውም የስብከት/ትምህርት የመድረክ አገልግሎት ግቡ መልእክቱን በአድማጩ ሕይወት ውስጥ ማሥረጽ ነው የሚል ነው። የአገልጋዩ እውቀትና ዝግጁነት ከዚህ ጋር ጠንካራ ትስስር እንዳለው መላሾች ያስባሉ። በመሆኑም የሰባኪው ወይም አስተማሪው በቂ ትምህርትና ሥልጠና ማግኘት፣ እንዲሁም በሚሰብከው ወይም በሚያስተምረው ርእሰ ጕዳይ በቂ ዝግጅት የማድረጉ ጕዳይ ትኵረት ተሰጥቶ ሊጤን የሚገባው ነው።

የመልእክቱ አቀራረብ ተስማሚነት ወይም ተገቢነትም መልእክቱን ለማቅረብ ምን ያህል ዝግጅት ተደርጓል ከሚለው ዕሳቤ ወይም ግምት ጋር ጥብቅ ቁርኝት የሚታይበት ነው (( r(207) = .638, p = <0.001, r2 = .407)፤ የአገልጋዩ እውቀት ( r(206) = .697, p = <0.001, r2 = .485)፣ ተግባራዊ ፋይዳ ( r(204) = 0.626, p = <0.001, r2 = .391)፣ የሕይወት ተዛምዶ ( r(204) = 0.626, p = <0.001, r2 = .391)። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው አንድ ጕዳይ፣ የአገልጋዩ እውቀትና ዝግጅት ከሚቀርበው ስብከት ወይም ትምህርት ይዘት ጋር አዎንታዊ ግንኙነት እንዳለው ቢታሰብም፣ መልእክቱን በአድማጩ ሕይወት ውስጥ ለማሥረጽ መላሾች ይበልጥ ቍልፍ ነው ብለው ያሰቡት የመልእክቱን አቀራረብ መሆኑ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከላዊነትና በአገልጋዩ የሕይወት ምስክርነት ወይም ዝግጅት መካከል ያለው ግንኙነት እምብዛም መሆኑን ምላሾች ያሳያሉ (r(204) = 0.773, p = <0.001, r2 = 0.759)። አብላጫዎቹ መላሾች በስብከት/ትምህርት አገልግሎት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረትነት ዋና ነገር አድርገው ቢቈጥሩም፣ የመልእክቱ ውጤታማነት ከአገልጋዩ ሕይወት ጋር ያለው ተዛምዶ ጠንካራ ተደርጎ አይታይም። እንዲህ መሆኑ፣ የዳሰሳ ጥናቱ ተሳታፊዎች የአገልጋዩን የግል ሕይወት፣ የስብከት ወይም ማስተማሪያ ዘዴ፣ ወይም ለአገልግሎት የሚያደርገውን ዝግጅት የግድ ከአገልግሎቱ አቀራረብ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከላዊነት ጋር እንደማያይዙት የሚጠቁም ነው። በመላሾች አተያይ፣ የአገልጋዩ የሕይወት ምስክርነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከላዊነት ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት አለው ተብሎ የማይታሰብ መሆኑን የተዛምዶ ምዘናው ይጠቁማል (r(204) = 0.057, p = .419)። በመጽሐፍ ቅዱስ መልእክትና በአማኝ ሕይወት መካከል ያለው ቁርኝት አስፈላጊነት ላይ የሚነሣ ምንም ዐይነት ነገረ መለኮታዊ ጥያቄ ባይኖርም፣ ወደ መድረክ አገልግሎት ስንመጣ ግን በሰባኪው ወይም በአስተማሪው ሕይወት እና በአገልግሎቱ መካከል ያለው ትስስር የተፋታ ወይም ዐብሮ የማይታይ ይመስላል።


5.2. ክፍል ሁለት፦ የዝማሬ አምልኮ የመድረክ አገልግሎት ዕይታ

የዝማሬ አምልኮ የመድረክ አገልግሎትን በተመለከተ፣ የአገልጋዮች የሕይወት ምስክርነት ወይም አርአያነትና የአገልግሎት ዝግጅት፣ እንዲሁም አቀራረባቸውና ሁኔታቸው፣ እንዲሁም የዝማሬ አገልግሎቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትን መጠበቅ፣ ከሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ጋር ያለው ስምረት፣ ብሎም ለአማኞች ሕይወት ያለው ተግባራዊ ፋይዳና ተዛማጅነት እና በምእመኑ ሕይወት ውስጥ ምን ያህል መልእክቱን ያሠርጻል የሚሉት ጕዳዮች ታይተዋል። የዝማሬ አገልግሎት አንድ የቤተ ክርስቲያን ዋና አገልግሎት መሆኑ የማይካድ ነው። ይሁን እንጂ፣ የዝማሬ አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን የጠበቀ ዐላማ፣ ወደ አምልኮ የሚመራ አቀራረብ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን የሚያንጽ ሊሆን ይገባል። የዳሰሳ ጥናቱ መልስ ሰጭዎች ያላቸው ምልከታ እንዲሁም በልዩ ልዩ ጕዳዮች ያሏቸው ምልከታዎች ተዛምዶ፣ ዛሬ የሚገኘውን የዝማሬ በሚገባ ማጤን እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙ ናቸው።

ለዝማሬ አገልግሎት የሚደረገው ዝግጅትና አቀራረቡ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክትን በአማኞች ሕይወት ውስጥ ከማሥረጽ አኳያ ጥብቅ ተዛምዶ አለው ተብሎ እንደሚታሰብ የዳሰሳ ጥናቱ ያስገኛቸው ምላሾች ያሳያሉ (r(204) = 0.523, p = <.001)። የያዙትን መልእክት በአማኞች ሕይወት ውስጥ ያሠርጻል ብሎ መታሰቡ፣ ዝማሬው በስብከት ወይም በትምህርት ከቀረብው መልእክት ጋር የተጣጣመ ሲሆን ከፍ ያለ ሆኖ ይገኛል (r(204) = 0.615, p = <.001)።

በታሪክ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መስተጋብር አንድ ቍልፍ አካል የሆነው የዝማሬ አገልግሎት፣ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን መምሰልን እንዲያመጣ ከተፈለገ ብርቱ ዝግጅት እንደሚያስፈልገው የተገኘው ውጤት ያመለክታል። የዝማሬ አገልግሎት ከሚዘመርበት ድምፅ ቅላጼና ከሙዚቃው ማማር ይልቅ፣ ከተቀረው የመድረክ አገልግሎት ጋር የሠመረ መሆኑ ይበልጥ አስፈላጊ ነው ብለውን እንደሚያምኑ መላሾች ገልጸዋል።

የሚዘመሩት መዝሙሮች መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውም፣ መልእክቱ ለአድማጩ ሕይወት ካለው ተግባራዊ ፋይዳ ጋር አዎንታዊ ግንኙነት አለው ተብሎ ይታሰባል (r(204) = 0.627, p = <.001)። በአጠቃላይ፣ የመድረክ የዝማሬ አገልግሎት ተጽዕኖው ከፍ ያለ የሚሆነው በቂ ዝግጅት ሲደረግበትና ከተቀረው የመድረክ አገልግሎት ጋር በአግባቡ የሚሄድ ሲሆን፣ እንዲሁም መዝሙሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መልእክት የያዘ ሲሆን እንደ ሆነ ይታመናል።

የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት፣ የዝማሬው አቀራረብ ለአድማጩ ተስማሚ ሆኖ መገኘቱ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን ከመጠበቁ ጋር ተያያዥ ተደርጎ የመታየቱ ሁኔታ አነስተኛ መሆኑን ያሳያል (r(204) = 0.216, p = .002)፤ እንዲሁም ከአገልጋዩ ወይም አገልጋዮቹ ዝግጁነት (r(204) = 0.140, p = .45) እና በመድረክ ከሚቀርበው አገልግሎት ጋር ካለው ስምምነት ጋርም (r(204) = 0.242, p = <.001) ተያያዥ ተደርጎ አይታይም።

የመዝሙሩ አቀራረብ እና የዘማሪዎች ሕይወት አርአያነትና አኳኋን በመዝሙሩም ሆነ በስብከት/ትምህርት ከመድረክ ከሚተላለፈው መልእክት ጋር አዎንታዊ ተዛማጅነት አለው ብለው እንደሚያምኑ መላሾች ቢያመለክቱም፣ አዎንታዊነቱ ግን ያን ያህል ብርቱ አይደለም። የዝማሬ አገልግሎቱ ምን ያህል ዝግጅት ተደርጎበት ይቀርባል የሚለው ከዝማሬው የሕይወት ተዛምዶ ጋር ያለው ግንኙነትም እንደዚያው አዎንታዊ፣ ግን ደካማ ሆኖ ተገኝቷል (r(204) = 0.123, p = .078)፤ አሳታፊነቱም እንደዚሁ ከሌሎቹ መገለጫዎች ጋር አዎንታዊ ግን ደካማ ግንኙነት እንዳለው ታይቷል (r(204) = 0.153, p = .028)። እንዲህ ያለው አዎንታዊ ግን ደካማ የሆነ ተዛምዶ፣ የመዝሙሩ አቀራረብ በአማኞች ሕይወት ውስጥ እምብዛም ተጽዕኖ ያመጣል ተብሎ የሚታሰብ አለመሆኑን የሚጠቁም ነው።

መረጃው እንደሚያሳየው፣ የጕባዔ ተካፋዮች በመድረክ የሚቀርቡ ዝማሬዎች ለሕይወታቸው ያላቸውን ተዛምዶ መጠነኛ አድርገው ይመለከቱታል (r(204) = 0.615, p = <.001)። የዝማሬ አገልግሎት በጕባዔ ተካፋዮች ሕይወት ያለው ተግባራዊ ፋይዳ የሚጨምረው መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ሲያደርግ (r(207) = 0.627, p = <.001)፣ እንዲሁም በቂ ዝግጅት ሲደረግበት (r(207) = 0.594, p = <.001) ነው ተብሎ ይታመናል።

በመድረክ ላይ ከዝማሬ ጋር ተያይዞ የሚታየው የአካል እንቅስቃሴ አንዱ የቤተ ክርስቲያን ልማድ እየሆነ የመጣ ነው። በዚህ ዳሰሳ ጥናት የተሰበሰበው መረጃ እንደሚጠቁመው ከዝማሬ ጋር ዐብሮ የሚስተዋለው አካላዊ እንቅስቃሴ፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ማድረግ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክትን በአማኞች ሕይወት ውስጥ ማሥረጽ እና የዝማሬ አገልግሎት ለአማኞች ሕይወት ያለው ፋይዳና ተግባራዊ ተዛምዶ ከመሳሰሉ የዝማሬ አገልግሎት መገለጫ መስፈርቶች ጋር ያላቸው ተዛምዶ አናሳ ሆኖ ታይቷል። በዝማሬ አገልግሎት ጊዜ የሚታየው አካላዊ እንቅስቃሴ አግባብነት፣ ከመንፈሳዊነት ጋር ያለው ተዛምዶም በመልስ ሰጪዎቹ አተያይ አናሳ ሆኖ ተገኝቷል።

5.3. ክፍል ሦስት፦ የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ዕይታ

የዳሰሳ ጥናቱ ሦስተኛው ክፍል በቤተ ክርስቲያን የሚታየው የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት እንዴት ይታያል የሚለውን የተመለከተ ነበር። 64 ከመቶ የሚሆኑት መላሾች አገልግሎቱ የራሱ መርሓ ግብር ኖሮት መካሄዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ብለው ቢያምኑም፣ አዘውትረው የሚካፈሉት ቁጥራቸው አነስተኛ ነው። መላሾቹ መርሓ ግብሩን አዘውትረው የሚካፈሉ አለመሆናቸው፣ አገልግሎቱ ለዕለት ተዕለት መንፈሳዊ ሕይወታቸው ያለው ፋይዳ አነስተኛ ነው ብለው የሚያስቡ መሆናቸውን የሚጠቁም ነው (r(190) = .280, p = <0.001, r2 = 0.427)፤ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ ያለው ፋይዳም የበረታ ነው ብለው እንደማያስቡ ያሳያል  (r(204) = 0., p = <0.001, r2 = 0.427)። እንዲህ ካለው የተዛምዶ ጉድለት የተነሣ፣ ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው ብለው ቢያምኑም፣ አገልግሎቱ በመላሾች ሕይወት ላይ ያለው ተጽዕኖ ሊታይ አልቻለም።

የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ያለው ፋይዳ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱን ከመጠበቁ፣ እንዲሁም በአገልግሎቱና ከሚመጡት መልእክቶች እውነተኝነትና ተፈጻሚነት ጋር ቀጥተኛና ጠንካራ ግንኙነት ያለው ተደርጎ ይቈጠራል። ሌሎቹ በዳሰሳ ጥናቱ የተመዘኑት መለኪያ መስፈርቶች ይህ ነው የሚባል ተያያዥነት አያሳዩም። የዕለት ተዕለት መታነጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትን ባለመልቀቅና በመልእክቱ እውነተኝነት ይወሰናል። አገልግሎቱ ለመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተገዛ እንደ ሆነ ሲታመን፣ ይዘቱ ለአማኙ ሕይወት ፋይዳ ያለው ተደርጎ ይቈጠራል። በመሆኑም፣ የተገኘው ውጤት አገልግሎቱ ላይ እውነተኝነትና የመንፈስ ቅዱስ ምሪት አስፈላጊ የመሆናቸውን እውነት የሚያስረግጥ ነው።

ከዳሰሳ ጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል፣ የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ግላዊና ሰብአዊ ክብርን በአግባቡ እንደሚጠብቅ የሚያምኑት 33.2 ያህሉ ብቻ ናቸው። ይኸውም አብላጫዎቹ መላሾች አዘውትረው የቤተ ክርስቲያን መርሓ ግብሮች የሚካፈሉ ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ ሲታሰብ፣ ጒዳዩ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

በጸሎትና ነጻ ማውጣት አገልግሎትና ተያያዥ መልእክቶቹ ያላቸው እውነተኝነትና ተፈጻሚነት ላይ ከፍ ያለ መተማመን ያላቸው (ከ5 ሲመዘን 4 እና 5 ቊጥር የሰጡት)፣ ከመላሾች 37.7 ከመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው። ይኸውም የአገልግሎቱን መሠረታዊ ተዓማኒነት የሚንድና አስደንጋጭ አዝማሚያ መኖሩን ጠቋሚ ነው።

6. ማጠቃለያ

የዳሰሳ ጥናቱ በአጠቃላይ በአገልግሎት በልዩ ልዩ መልኩ (በስብከት/ትምህርት፣ በዝማሬ አምልኮ እንዲሁም በጸሎትና ነጻ ማውጣት) በሚተላለፈው መልእክት እውነተኝነት እና አግባብ ባለው ምግባርና አኳኋን መካከል ብርቱ እና አዎንታዊ ግንኙነት የመኖሩን የማይካድ ሐቅ ያሳያል። በሦስቱም በጥናቱ በተካተቱት የመድረክ አገልግሎቶች መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት የማድረግ አስፈላጊነት ማዕከላዊ ስፍራ ይዟል። የተገኘው ውጤት የአገልጋዩ ወይም የአገልጋዮቹ እውቀትና ዝግጁነት እንዲሁም መልእክቱ የቀረበበት መንገድ ለጕባዔ ተካፋዮች ሕይወት አለው ተብሎ ከሚታሰበው ፋይዳ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ያመለክታል። በተጨማሪም ጥናቱ፣ መላሾች ከመድረክ የሚነገሩትን ቃላት ብቻ ሳይሆን፣ ለአገልግሎት የተደረገውን ዝግጅት፣ አቀራረብና ጥንቃቄ ዋጋ እንደሚሰጡ ያሳያል።

በተጨማሪም የጥናቱ ውጤት ሰባኪዎች/አስተማሪዎች፣ ዘማሪዎች እንዲሁም የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልጋዮች ከጕባዔ ተካፋዮች ጋር ተገናኝቶ ለመነጋገር የመገኘት ዕድላቸው የጠበበ መሆኑን ያሳያል። የመድረክ አገልግሎትን ውጤታማነት የተመለከቱ በርካታ ጥናቶች፣ የመድረክ አገልግሎት ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ከአገልጋዩ ጋር ተቀራርቦ የመነጋገር ዕድል ሲኖር እና የአገልጋዩ ሕይወት ከፍ ያለ አርአያነት ያለው ሲሆን እንደ ሆነ ይጠቁማሉ። ከዚህ የዳሰሳ ጥናት የተገኘው ውጤት ግን አብላጫው መላሽ ስለ አገልጋዩ ሕይወት ምስክርነት ወይም አርአያነት የሚያውቀው ነገር የለም፤ እንዲሁም ተቀራርቦ የመነጋገር ዕድሉም የለውም። በገቢር በሚኖር የዕለት ተዕለት ሕይወት፣ የመድረክ አገልጋዮች ከጕባዔ ተካፋዮች ርቀው የሚገኙ ተደርገው ይታያሉ፤ ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ የተነሣውም መድረክ ላይ የሚቈሙት ሰባኪዎች/አስተማሪዎች፣ ዘማሪዎች እና የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልጋዮች ያለማቋረጥ ስለሚለዋወጡ የግል መስተጋብር ለመፍጠር የማያመች ስለሚያደርገው ነው። እምነት ሊያድግና ሊጠነክር የሚችለው በግል መስተጋብርና ግንኙነት መዳበር ውስጥ መሆኑን ያሳያሉ፤ ይህ ሳይሆን ሲቀርም የእምነት መሠረት ሊናጋ ወይም ሊጣመም ይችላል ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ ኪዳን የቃሉ አገልጋዮች ሕይወታቸውን ከአገልግሎታቸው ጋር የገመዱ እንደነበሩ ያስተምረናል፤ የመረጃ ፍሰቱ ከተራ የመረጃ ፍሰት የዘለለ ፍሬያማ የሆነበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስና ለቲቶ የጻፋቸው፣ የልቡን በሚናገርባቸው ደብዳቤዎች፣ በቃልም በድርጊትም በቅርብ የሚገኝ ሰው መሆኑን ይጠቁማሉ። ከመድረክ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ምንም ግላዊ መስተጋብርና ግንኙነት የሚከተል ተደርጎ አለመታሰቡ፣ ከመድረክ የሚተላለፈውን መልእክት ውጤታማነት የሚጎዳ ነው።

የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው፣ 40 ከመቶ መላሾች በመድረክ አገልግሎት ላይ አንድም ሆነ ሌላ ቅሬታ አላቸው። ይህ ቅሬታ ከሕይወት ጋር ተዛማጅነትና ተግባራዊ ፋይዳ ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብከት/ትምህርት፣ ዝማሬ እንዲሁም የጸሎትና ነጻ የማውጣት አገልግሎት ከመጓደሉ ጋር የተያያዘ ነው። ዳሩ ግን ይህን መሰሉ ቅሬታ፣ መልስ ሰጭዎችን አዘውትረው የቤተ ክርስቲያን መርሓ ግብሮችን ከመካፈል አልገታቸውም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸውን መቀጠላቸው፣ እምብዛም ጥቅም አገኝበታለሁ ተብሎ ባይታሰብም እንኳ፣ ክርስቲያናዊ ማኅበር ያለውን አስፈላጊነት የሚጠቁም ነው። አብያተ ክርስቲያናት ይህን የጕባዔ ተካፋዮችን መሰጠት በአግባቡ ሊይዙና ሊጠቀሙበት ይገባል። የመድረክ አገልግሎቶች ይበልጥ ለዕለት ተዕለት ሕይወት ፋይዳ ያላቸው ቢሆኑ፣ አጠቃላዩን ክርስቲያናዊ ሕይወት ለማነጽ ብርቱ መሣሪያ መሆን  ይችላሉ። አብያተ ክርስቲያናት የመድረክ አገልግሎት ላይ ያላቸው ዕይታ የነቃ ቢሆን፣ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለኅብረተ ሰቡም ጭምር በጎ ለውጥ መነሻ የመሆን አቅም አለው።

የመድረክ አገልግሎት ለሕይወት ተግባራዊ ፋይዳ ሊኖረው ይገባል ተብሎ በጽኑ እንደሚታመን በዚህ የዳሰሳ ጥናት የተገኘው ውጤት በአጽንዖት ያሳያል። አሁን በሚገኙበት ይዞታ የመድረክ አገልግሎቶች ለጕባዔ ተካፋዮች “መደበኛ የድንገቴ ክስተቶች” ናቸው፤ ከሳምንት ሳምንት በሚካፈሉት ጕባዔ ምን ሊከናወን እንደሚችል ይህ ነው ብለው የሚጠብቁት ተጨባጭ ነገር የለም። ታስቦባቸው በተነደፉ፣ በሚገባ በተደራጁ፣ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ባደረጉና ለሰዎች መስተጋብር ዋጋ በሚሰጡ የመድረክ አገልግሎቶች መሣሪያነት፣ ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመርኩዛ አማኞችን ሁሉ ለማነጽ ያለባትን ኀላፊነት ለመወጣት ያስችሏታል።

የመድረክ አገልግሎት ያለው ፋይዳ እና በአማኞች ሕይወት ውስጥ ያለው ተግባራዊ ዋጋ ማዕከላዊ ስፍራ ሊይዝ የሚገባው ነው። የተዛምዶ መረጃ ትንተናው እንዳሳየው፣ የመድረክ አገልግሎት የሚመዘነው በመርሓ ግብሩ ክንዋኔ ስኬት እንጂ፣ በአማኞች ሕይወት ባመጣው ተጽዕኖ አይደለም።

ይህ ዳሰሳ ጥናት በተመረጡት አብያተ ክርስቲያናት ላይ ስለሚገኘው የመድረክ አገልግሎት ዕይታ ብርሃን የሚፈነጥቅ ነው። የዳሰሳ ጥናቱ ተሳታፊዎች ከመጽሐፍ ቅዱስና ከክርስቲያናዊ መታነጽ አኳያ፣ የመድረክ አገልግሎት በሚገባ ሊጤንና ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል ብለው እንደሚያምኑ ያሳየ ነው። በኢትዮጵያ ስላለው የመድረክ አገልግሎት አንድምታ፣ ዕድገት፣ እንዲሁም የሕጸጾቹ መንሥኤ ተጨማሪ ጥናቶች የሚያስፈልጉ መሆኑ አያጠያይቅም።

7. ምክረ ዐሳቦች

 1. የመድረክ አገልጋዮችን ሁሉ በእውቀትም ሆነ በክኂሎት ብቁ ለማድረግ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። አብያተ ክርስቲያናት ተጋባዥ ሰባኪና አስተማሪዎችን እንዲሁም ዘማሪዎችን ከማፈራረቅ ባለፈ፣ ያሏቸውን አገልጋዮች በእግዚአብሔር እውቀት ለማስታጠቅ ትኵረት ቢሰጡ፣ ይበልጥ ያተርፉበታል።

 2. በአገልጋዩና በሕዝቡ መካከል ጥሩ ተግባቦት ያለበት፣ እንዲሁም ሕዝቡ፣ “ስለ እኛ ግድ የሚለው እረኛ አለን” የሚል ስሜት ያለበት ልማድ ወደ አብያተ ክርስቲያኖቻችን መመለስ አለበት። አብዛኛውን ሕዝብ መድረሻ አንዱ ሁነኛ መንገድ መድረካችን ወይም ምስባካችን ነው፤ ይህን በውል በመረዳት፣ አብያተ ክርስቲያናት ሕዝቡ ፊት መድረክ ላይ ቈሞ የሚያገለግለው አገልጋይ ማን ነው፣ ሕዝቡንስ ምን ይመግባል የሚለውን በሚገባ ማጤን አለባቸው።

 3. የዚህ ዳሰሳ ጥናት አብዛኞቹ መላሾች በወጣትነት ወይም ጐልማሳነት ዕድሜ ላይ የሚገኙ (ከ24-44 ዓመት ዕድሜ ያላቸው) ናቸው፤ ይህም ከአገሪቱ አብላጫ የወጣት ሕዝብ ቍጥር ጋር የሚስማማ ነው። ተያይዞም፣ በመቶኛ ንጽጽር ሲታይ በቤተ ክርስቲያን የመድረክ አገልግሎት አለመርካታቸውንና ቤተ ክርስቲያን ተሓድሶ እንደሚያስፈልጋት አብልጠው የገለጹትም በዚህ የዕድሜ ክልል የሚገኙ መላሾች ናቸው። ይህም ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ላይ ይበልጥ መሥራት እንደሚገባት ይጠቁማል። ይህ በራሱ ከተጠቀምንበት ትልቅ ዕድል የሚያስገኝ (ወጣቱ ብዙ የመሥራት አቅምና ተነሣሽነት ስላለው)፣ ካልሆነም ትልቅ ኪሳራ ሊያስከትል የሚችል ነው።

 4. የመድረክ አገልግሎቶች ሆነ ተብለውና ታስቦባቸው የሚቀረጹ፣ በወጉ የተደራሹ፣ ቃለ እግዚአብሔርን ማጠንጠኛ ያደረጉና ከሕዝቡ ጋር መልካም ተግባቦት ያላቸው የመድረክ አገልጋዮችን የሚጠቀሙ ሊሆኑ ይገባል። የስብከት/ትምህርት፣ የዝማሬ እንዲሁም የጸሎትና ነጻ የመውጣት አገልግሎቶች፣ በጋራ በአንድ ሠምረው የሚጓዙ ሊሆኑ፣ በዚህም በቤተ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት ማፍራት ላይ ያነጣጠሩ ሊሆኑ ይገባል።

 5. በመድረክ አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ወይም ችግሮች በጥናቱ በተካተቱት ልዩ ልዩ ቤተ እምነቶች ሁሉ ይነስም ይብዛ ተመሳሳይ መልክ ያላቸው ናቸው፤ የትኛውም ቤተ እምነት ወይም ቤተ ክርስቲያን አይመለከተኝም ሊለው የሚችል አያደለም። ይህም ችግሩ የጋራ መሆኑን ተገንዝቦ ለመፍትሔው የአብያተ ክርስቲያናት የጋራ ጥረት የሚፈልግ መሆኑን የሚያሳይ ነው።


8. አባሪዎች

አባሪ I – የዳሰሳ ጥናቱ መጠይቅ


 • አባሪ II የጥናት ቡድኑ አባላት የሰበሰቡትን ምላሽ ገቢ ያደረጉበት ማረጋገጫ ቅጽ

Download the research in PDF

Hintset

ፖለቲካችን ክርስቲያናዊ ዕሴቶችን ይሻል!

አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ እንዳለች በብዙዎች ዘንድ መግባባት አለ። የተጀመረው ለውጥ የሚፈለገው ቦታ ላይ እንዲደርስ ሁሉንም የኅበረተ ሰብ ክፍል ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ አሁንም በብዙዎች ዘንድ እምነት አለ። የወንጌላውያን አማኞች የኅብረተ ሰቡ አካል እንደመሆናችን ለአገራችን ሰላም፣ ፍትሕ እንዲሁም ብልጽግና የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እስከ አሁን በነበረን አገራዊ ተሳትፎ ‘ብዙ ትኩረት አልሰጣችሁም’ ተብለን የምንወቀሰው እኛ ወንጌላውያን፣ ለዚህ ወቀሳ አዎንታዊ ምላሽ የምንሰጥበት ጊዜ ላይ እንዳለን ይሰማናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

የጌታ የሆኑትን ማሳደድ ራሱን ጌታን ማሳደድ ነው

የማኅበረ አኀው የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የአርባ ምንጭ አጥቢያ፣ ከየካቲት 8-10 የሥልጠናና የአምልኮ ጊዜ አዘጋጅታ ነበር። በዚህ የሦስት ቀናት መርሓ ግብር የመጨረሻው የአምልኮ ጊዜ ላይ፣ ‘ስለ ወንጌል ቀንተናል’ ያሉ ወገኖች ወደ ጉባኤው ገብተው፣ ድብደባና ዘረፋ መፈጸማቸው ተነግሯል። ይህ የዲያቆን አግዛቸው ተፈራ ዐጭር ጽሑፍ፣ የጌታ የሆኑትን ማሳደድ ክርስቶስ ራሱን ማሳደድ መሆኑን ያመለክታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

የተመለሱና ያልተመለሱ ጥያቄዎች፡- ስለ እግዚአብሔር፣ ስለሰው፣ ስለክርስቶስ

ትምህርተ ክርስቶስ እጅግ መሠረታዊ ከሆኑ የክርስትና አስተምህሮዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ አነጋጋሪ ከሆኑ ሰዎች መካከል ኢየሱስ ዋነኛው ነው፡፡ ገና ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጊዜ ጀምሮ የኢየሱስ ማንነት አከራካሪ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ክርስቶስን በተመለከተ በያዙት የተለየ አቋሞች የተለያዩ ቤተ እምነቶች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

2 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

 • ሕንጸቶች፣
  በኢትዮጵያ ሕዝብ እና ቤተ ክርስቲያን ስም ገንዘብ ሰብስበው የሚጠቀሙት/የሚሰርቁትን ተከታትሎ መመዝገብ እና ለሕዝብ ማስታወቅ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ወይስ ብዙ ድካም ስላለበት ወይም ከሰዎች ጋር ስለሚያነካካ ችላ ብላችሁታል? 1ሺህ ቤተ ክርስቲያን ተከልን ይላሉ፤ 50ሺህ ፓስተሮችን አሠለጠን፤ 2ሺህ ተማሪዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ አስመረቅን፤ እህል ልብስ መድኃኒት አደልን ወዘተ። በፎቶ እና በቪዲዮ ቀርጸው ለጥፈዋል። አንዳንዱ ፎቶ የቆየ ነው፤ ሌላው ፎቶ እጃቸው የሌለበት ሌሎች ያቋቋሙት ድርጅት ነው! ለዚህ ዓይነቱ ጋዜጠኝነት ትጋቱ ቁርጠኝነቱ አላችሁ? ወንጌላውያን መሪዎች ኃላፊነታቸውን ችላ ብለው ከፖለቲከኞች ጋር የተመሣጠሩበትንስ?

 • ይህንን እያደረጉ ያሉት ኢትዮጵያውያን በግል ሚኒስትሪ ስም፤ ደግሞ ከፈረንጆቹ ጋር ተመሳጥረው። ረብሻ ሲከሠት፣ የረሃብ ወሬ ይመቻቸዋል፤ የአክራሪ እስላማውያን ወሬ። ይህን ያክል ሺህ መጽሐፍ ቅዱስ አደልን ይላሉ። ከቦታው ሲኬድ ግን ወይም ምንም የለም ወይም ለወሬ ብቻ ያህል ነው።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.