[the_ad_group id=”107″]

መለኮታዊ ፈውስና የእምነት ምስክርነት ፈተናዎች

በማርች 23 ቀን 2008 ዓ. እ. በአንድ የአሜሪካ ቤተ ሰብ ውስጥ አስደንጋጭ ኀዘን ተከሠተ። በማርች 26 ዜናውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሠራጨውን አሶሼትድ ፕሬስን ጨምሮ ዋነኛዎቹ የዜና ተቋማት ወሬውን ተቀባበሉት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ የዊስኮንሲን ነዋሪ ስለ ነበረችው የ11 ዓመቷ እምቦቃቅላ ማድሊን ካራ ኑማን (Madeline Kara Neumann) በተከታታይ መነገርና መጻፍ ተጀመረ። ክርክሩም ተጧጧፈ።

ማድሊን በቀላል የሕክምና ክትትል ሊያዝ ይችል የነበረ የስኳር ሕመም (diabetes) ነበረባት። አባትና እናቷ ሌላኒ እና ዴል ኑማን እንደ አብዛኞቻችን አጥባቂ የጰንጤቈስጣዊ ክርስትና ተከታይ ነበሩ። ስለሆነም ፈውሷን በመጠባበቅ በጸሎት ሲተጉ ሰነበቱ። ማድሊን ግና ሊሻላት አልቻለም። የሕመሟ ሁኔታ እየተባባሰ ቢሄድም እንኳ፣ ወላጆቿ ወደ ሕክምና ሥፍራ ሊወስዷት አልፈቀዱም። በጸሎት ትጋታቸው ብቻ ገፉበት፤ ግን አልሆነም። የልጃቸው ሕይወት በእጃቸው ላይ ዐለፈ። ዐንገታቸው በድንጋጤ፣ አንጀታቸውም በኀዘን ታጠፈ።

ኀዘናቸው ከውስጣቸው ሳይወጣ የልጃቸው ኅልፈት ሌላ መዘዝ ይዞ መጣ፤ ተከሰሱ። እኒህ ኀዘን የሰበራቸው ወላጆች በሁለተኛ ደረጃ የቸልተኝነት (ኀላፊነት የጐደለው) ነፍስ ማጥፋት (second-degree reckless homicide) ተግባር ተወንጅለው 25 ዓመት ተፈረደባቸው። በዚህም ምክንያት በየዓመቱ ለ30 ቀናት እስር ቤት ያሳልፋሉ። የተቀሩትን ጊዜያት በሕግ ጥበቃ ሥር ሆነው ቀሪዎቹን ልጆቻቸውን ይንከባከባሉ። 

በርካታ ይህን መሳይ አስደንጋጭ ታሪኮችን መጥቀስ ይቻላል። ይህ ዐይነቱ አሳዛኝ አሟሟት በሚወድዱት ሰው ላይ እንዲደርስ እንኳን እናትና አባት ማንኛውም ሰው ሊፈቅድ አይችልም። እኒህ ወላጆች በእግዚአብሔር ልዕልናና በቀጣይ ተአምራዊ አሠራሩ እንደማመናቸው በጸሎት መትጋታቸው የሚጠበቅ ነው። መለኮታዊ ፈውስን ከጌታ መፈለጋቸው ስሕተት አልነበረም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታን የተጻረረና ሚዛን የሳተ አጕል “መንፈሳዊነት”ለእንዲህ ያለው አሳዛኝ ፍጻሜ ሊዳርግ እንደሚችል ታሪካቸው ፍንትው አድርጎ ያስተምረናል። በአንጻሩ የእነርሱ በዚህ ዐይነት ችግር ውስጥ ማለፍ የመለኮታዊ ፈውስን ዕውናዊነት ሊደመስስ አይችልም።

የመለኮታዊ ፈውስ እውነታ ተጨባጭም ምሥጢራዊም እንደ ሆነ አለ። ባለፉት ሁለት ሺህ የክርስትና ታሪክ ዘመናት መለኮታዊ ፈውስን አስመልክቶ ብዙ ውጣ ውረዶችና የሐሳብ ውርክቦች ሲካሄዱ ነው የኖሩት። በአንዳንዶቹ ዘማናትማ፣ መለኮታዊ ፈውስ ጨርሶ እንዳከተመ ክሥተት ተደርጎ ተወስዶ ያውቃል። እግዚአብሔር ፈዋሻችን በሥራ ላይ ለመሆኑ ምስክሮቹ ብዙ ነን። መለኮታዊ ፈውስን በሚመለከት የንድፈ ሐሳባዊ ግምቶችና ነባቤ ቃላትን በሚደረድሩ ሰዎች ዘንድ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር እንደ ፈቀደ ተአምራዊ ፈውሶች ሲካሄዱ በተመለከቱና በተለማመዱ ምስክሮች መካከል ርእሰ ጕዳዩን ለመነጋገር በመቻላችን እግዚአብሔርን ማመስገን ይኖርብናል። እግዚአብሔር ለእኛ ተረት አይደለም። 

እግዚአብሔር በመካከላቸው በኀይል እንደሚሠራ በሚያምኑና በሚለማመዱ የእግዚአብሔር ሕዝቦች መካከል ለመካተት በክርስቶስ ሥራ ተዋጅተናል። የእውነት ዐምድና መሠረት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የሕያው አምላክ ማደሪያ ቤት ናት (1ጢሞ 3፥15)፤ የእውነተኛው አምላክ የማያቋርጥ ሕያው መገኘት ተካፋይ እንጂ ተረት ተናጋሪ አይደለችም። ታሪኳ በእግዚአብሔር የማዳን እንቅስቃሴዎች የደመቀ ነው። ባለፉት ጥቂት ምእተ ዓመታት የሆነውን እንኳ ብንመለከት የስብከተ ወንጌል ንቅናቄዎች፣ ተአምራትና የፈውስ ድንቆች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አካል ሆነው ታይተዋል። ይህ እውነት የሚከናወነው በእግዚአብሔር መንፈስ ኀይል አማካኝነት የክርስቶስ መንግሥት በመያቋርጥ የትድግና ሥራዋ ላይ ስለ ሆነች ነው። እነሁ፣ ቤተ ክርስቲያን በበጎ ስጦታዎች ተትረፍርፋ ኖራለች። 

ይሁን እንጂ የምንኖርበት የሕይወት ገጽታ ከመልካም ስጦታዎች በሚገኝ ደስታ የታጀበ ብቻ ሳይሆን፣ “የአሁኑን ዘመን ሥቃይ” (ሮሜ 8፥18) በመካፈል ጭምር የተዥጐረጐረ ሆኗል። እኛ ክርስቲያኖች የሰው ልጆች ስለሚያልፉበት መከራ ቸልተኞች ልንሆን አንችልም። ለሕሙማን እንጸልያለንም፤ በምንችለው ሁሉ እንደግፋለንም። እግዚአብሔር ሰዎችን ከመከራቸው በመገላገል፣ ለአካላቸው ፈውስ ለልባቸው ደግሞ የእርሱን የመገኘት ብርሃን ሲሰጣቸው ደስ ይለናል። ገና ከመጀመሪያው፣ ክርስቲያኖች የሚታወቁት ለሕመምተኞች በሚያደርጉት ጸሎት፣ እንክብካቤና ጥበቃ መሆኑ የታወቀ ነው። ማድረግ ያለባቸውን የሚያደርጉትም፣ በዚህ ዓለም ስላለው የሕይወት ገጽታዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው የእይታ አድማስ ላይ አሻግረው በመመልከት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ፈዋሽ አምላክ መሆኑን ሲያስተዋውቅ (ዘጸ 15፥26፤ 2ነገ 5፥7)፣ ጌታ ኢየሱስን የመለኮታዊ ማዳንና ፈውስ ወኪል አድርጎ ያሳየናል። ለምናምንም፣ ከክፉ የሚጠብቀንና በመከራችን የሚራራልን አምላክ መሆኑን ያስተዋውቃል። ፈውስ የቸርነቱ መገለጫ መሆኑን ያበሥረናል። በዚያው ልክ ደግሞ፣ ክብሩን ለመካፈል የመከራው ተካፋዮች የመሆናችንን እውነታ ያስተምራል (ሮሜ 8፥17፤ 1ጴጥ 5፥1፤ 2ቆሮ 4፥17-18)። ለክብር አክሊል የተጠሩቱ ምርጦች የመስቀል ኑሮ ተካፋይ የእምነት መናኒያን ተደርገዋል። ስለሆነም፣ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ሥራ አማካይነት ፈውስን መቀበላቸው ርግጠኛ ሲሆን፣ በአካላዊ ሕማም ውስጥ ሊያልፉ የመቻላቸውም ገጽታ እንደ ተጠበቀ አለ።

በዚህ እውነት ላይ ተመሥርተን፣ ስለ መለኮታዊ ፈውስና ክርስቲያናዊ የእምነት ምስክርነት የተወሰኑ ሐሳቦችን  ቀጥሎ እንመለከታለን። ሆኖም፣ ለመወያያነት እንዲፈይድ ብቻ ሐሳቡን በመጠኑ ከማንሣት ባለፈ፣ በዚህ ዐይነቱ ዐጭር ጽሑፍ መለኮታዊ ፈውስን አስመልክቶ ሁሉንም ጥያቄዎች ለመመለስ ማሰብ እንደማይሞከር እንገነዘባለን። በዚሁ አንጻር፣ አስቀድመን ስለ መለኮታዊ ፈውስ ምንነት በማየት እንጀምር።

መለኮታዊ ፈውስ ምንድር ነው?

ፈውስ ምን እንደ ሆነ ለመናገር፣ ፈውስ ሊያስገኘው ስለሚችለው ጤና (ጤንነት) ማንሣት ጠቃሚ ነው። ጤና (ጤንነት) ምንድር ነው? በመጠነ ሰፊው የትርጓሜ ሕብረ-ቀለም (spectrum) ላይ ጤንነትን በሦስት የተለያዩ ዐይነት ገጽታዎቹ መበየን ይቻላል።

የመጀመሪያው፤ የሕብረ ቀለሙ ደብዛዛ ጫፍ (minimal end) ላይ የተመሠረተ ብያኔ ሲሆን፣ ሐሳቡን ከመታመም ወይም በሽታ ጋር አያይዞ የሚተረጕም ነው። ስለዚህ በዚህ አተያይ መሠረት፣ ጤንነት የአካላዊ ሕመም ወይም በሽታ አለመኖር ተደርጎ ይወሰዳል።

ሁለተኛውና የሕብረ ቀለሙ መካከለኛ ሥፍራ (centre of the spectrum) ላይ የሚውለው እይታ በፈንታው፣ ከአካላዊ ሁኔታ ይልቅ በአብዛኛው ጕዳዩን ከአጠቃላይ የጤና መቃወስ አኳያ የሚመለከት ነው። (ማለትም፣ ከማኅበራዊ ወግ-ልማድና ደኅንነት መጕደል ወይም ማፈንገጥ፤ ለምሳሌ፣ በሆነ ዐይነት ፍርኀትና ጭንቀት ጭልጥ ብሎ መወሰድ ሊሆን ይችላል።) ስለዚህ፣ ጤና ማለት በዚያ ማኅበራዊ ደኅንነትና ወግ ውስጥ እንከን ሳያገኘው ደኅነኛ ሆኖ መገኘትና ከዚያ ማኅበራዊ ደኅንነትና ወግ-ልማድ ጋር ተስማምቶና ተጣጥሞ መመላለስ ነው። ሲግመንድ ፍሮይድ የሚሰጠው ብያኔ ከዚህ ጋር የተቀራረበ ነው። ለፍሮይድ ጤና ማለት ለመሥራትና ለደስተኝነት ብቃት ማግኘት ነው። በዚህ መሠረት፣  አንድ ሰው ለሥራ ያለው ዐቅም ከተጓደለ እና ለመደሰት ያለው ብቃቱ ከተቃወሰ ታምሟል።

ሦስተኛውና የሕብረ-ቀለሙ ደማቅ ጫፍ (maximal end of the spectrum) ስለ ጤንነት ያለው እይታ የዓለም ጤና ድርጅት ስለ ጤንነት በሚሰጠው ብያኔ ሊጠቃለል የሚችል ዐይነት ነው። “ጤና ማለት የሕመም ወይም የበሽታ አለመኖር ማለት ብቻ ሳይሆን የአካላዊ፣ አእምሯዊና ማኅበራዊ ደኅንነት (well-being)” ማለት ነው።

የጤንነት ክርስቲያናዊ እይታ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ-ሰብእ አኳያ የተቃኘ መሆን ይገባዋል፤ ይኸውም የሰው ማንነትን ከመገንዘብ የሚመነጭ ነው። ሰው በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረና ከአምላኩ ጋር በኅብረት እንዲኖር ተሠርቷል (ዘፍ 1፥26-28)። የፍጥረት ኀላፊነታችን የእግዚአብሔርን መልክ ማንጸባረቅ ነው። ጤናማ ሰብአዊ ማንነት የሰው ልጅ በገዛ ራሱ ላይ በሚያኖረው አፈንጋጭ ባለመብትነት ላይ የተደላደለ ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ከተመሠረተ የማይናወጥ ኅብረትና በእርሱ ላይ ብቻ ከሚኖረው መደገፍ የሚመነጭ የተሟላ ሕይወት ነው።

የሰው ሕይወት የተለያዩ ገጽታዎች አሉት። በመሆኑም ጤንነት የሰውን ሁለንተናዊ ደኅንነት ግቡ ያደረገ ነው። ለመጽሐፍ ቅዱስ ባዕድ የሆነው ምንታዌነት (unbiblical dualism) በአፍላጦናዊ (platonic) ንጽረት የሚታመን የግሪክ ዲበ አካላዊ የአስተሳሰብ ውቅር እንጂ የክርስትና አተያይ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አስተሞህሮ የአሁኑ ሕይወት የማይታየው ዓለም የቅዠት ነጸብራቅ ተደርጎ አልቀረበም። ጌታ ኢየሱስ ሥጋችን (አካላችን) ለነፍሳችን እንዲገብር በሚል ስሌት ልናስጨንቀው የሚገባ ዕኵይ ክፍል አድርጎ አልተመለከተውም። በአይሁዳዊ-ክርስትና ትምህርትና ትውፊት ሥጋ የነፍስ ወሕኒ ቤት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አተያይ አካል ተገቢ ቦታ ተሰጥቶት ነው የምናገኘው። የክርስቶስ አካል ክፍልና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መቅደስ መደረጉን ነው የምናነበው (1ቆሮ 3፥16፤ 6፥15፡ 19-20)። ስለሆነም፣ የሰውነት ክፍሎች (anatomy)፣ የሰውነት አሠራር (physiology)፣ እና ሥርዐተ-በራሄ ጅን (genetic make-up) በሙሉ የእግዚአብሔር ሥነ ፍጥረት መልካምነት ክፍል እንደ መሆናቸው የሰው አካል በጥንቃቄና በአግባቡ መያዝ ይኖርበታል።

ጤናማነት መጽሐፍ ቅዱስ ሻሎም ብሎ የሚጠራው ሁለንተናዊ ዕረፍትና ደኅንነት አካል ነው። ሁለንተናዊ ደኅና መሆን ሻሎም ይባላል። ይህ ሰላም፣ የጦርነት አለመኖር ማለት ብቻ አይደለም። ሻሎም ግጭት የሌለበትን ሁኔታ ከማመልከት ያልፋል፤ ይሰፋል፤ ይጠልቃልም። በእግዚአብሔር ክብርና በመገኘቱ ግርማ በሰው ልጆችና በአጠቃላይ ፍጥረቱ ሁሉ ላይ የሚመሠረተው የእግዚአብሔር መልካምነትና በጎነት በጥልቀት መሥፈን ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳዊው አረዳድ መሠረት፣ የሰው ምሉዕነት እና ማኅበራዊ ፍትሕ እርስ በርስ የተጣመሩ ሆነዋል። ሻሎም በሰው ልጅ ዙሪያ-መለስ የሕይወት ገጽታዎች ላይ የሚገለጥ የተሟላ ደኅንነት፣ ከፍተኛ ጥንካሬና ብርታት ተካትቶበታል። ይህን የእግዚአብሔር ሻሎም የሚያመጣው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑ ታውጇል።

ስለዚህ መለኮታዊ ፈውስ ማለት የእግዚአብሔር ሻሎም አካል እንደ መሆኑ በሉዓላዊ ፈቃዱ መሠረት፣ ልዕለ ተፈጥሯዊ በሆነ፣ ተአምራዊና መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ምክንያት በእምነት በኩል ሰዎች ከእግዚአብሔር እጅ የሚቀበሉት ጤንነትና ደኅንነት ነው።

እግዚአብሔር በዚህ ዓለም የሠራውና የሚሠራው በሥነ ፍጥረት፣ በመግቦቱና በአድኅኖት (መቤዠት) ሥርዐት ነው፤ ሁሉን ምሉዕ የሚያደርገው መታደስ የመንግሥቱ አሸናፊነት (ድል ነሺነት) ይሆናል። እግዚአብሔር ዓለሙን ያስገኘ ነውና በራሱ ዓለም ውስጥ እንደ ፈቃዱ ምክር የወደደውን ለማድረግ በማይገሠሥ የልዕልና ሥልጣኑ ይሠራል። እግዚአብሔር ፈጥሮት ሲያበቃ እንዳሻው እንዲተራመስ የጣለው ዓለም የለውም። እርሱ የሚሠራው “ክፍት በሆነ” መንገድና በሉዐላዊ ፈቃዱ መርሕ ነው። ደግሞም የፈጠረውን ዓለም በማያቋርጥ መግቦቱ አጽንቶና ደግፎ ይዞታል።

ዓለሙ በኀጢአት በመበላሸቱ ምክንያት ፍጹም የሆነ ዘላለማዊ ትድግናውን የሚቀዳጀው በክርስቶስ በኩል በተገለጠው ቤዝዎታዊ ሥራ ብቻ ይሆናል። ይህ ከሚከወንባቸው መንገዶች አንዱ በሆነው መለኮታዊ የፈውስ አሠራሩ የእግዚአብሔር ቸርነት የአድኅኖቱ አካል ሆኖ ይገለጣል። እግዚአብሔር ተአምራት የሚያደርገው ከዓለሙ ተነጥሎ ከከረመበት ድንገት ብቅ እያለ አይደለም። ዘወትር በመግቦቱ በገዛ ዓለሙ ውስጥ በሥራ ላይ ያለው አምላክ በተለየና ባልተጠበቀ መንገድ ይሠራል። የሆነ ሆኖ፣ መለኮታዊ ፈውስ በእግዚአብሔር ልዕልናና ቸርነት የሚከናወን ቢሆንም፣ አሁን ባለንበት ዓለምና ዘመን ምክንያት ሐሳቡ የሚታይበት የውጥረት ደርዝ ተበጅቶለት እናገኘዋለን።

መለኮታዊ ፈውስና የሁለቱ “ዓለማት” ውጥረት

ዓለማችን የታመመና የተፈወሰ ነው። ፈውስ ያስፈለገው ምን ችግር አጋጥሞት ነው ያልን እንደ ሆነም፣ የችግሩ መሠረታዊ ምክንያት ኀጢአት የወለደው ውድቀት ሆኖ እናገኘዋለን። የምንኖረው በወደቀና በተሰበረ ዓለም ውስጥ ነው፤ ኀጢአት ጥሎታል። የወደቀው ከእግዚአብሔር ተለይቶ በመሆኑ ክፉኛ የተንኰታኰተ ዓለም ነው። ዐመፃ አዳሽቆታል። እነሆ፤ ሕሙሙ ዓለም ለጥፋት ባርነት በተስፋ ተገዝቶና ምጡን ተሸክሞ በመቃተት ይኖራል (ሮሜ 8፥19-22)። ዓለሙ ሁለንተናዊ ሕመም መታቀፉን መዘንጋት አንችልም፤ ክፉኛ ታምሟል።

የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ሕመም ምክንያት ኀጢአት ሲሆን፣ መፍትሔው ደግሞ የእግዚአብሔር ትድግና ነው። ይህ በጽኑ ሕመም የተሰባበረ ዓለም ዝም ብሎ የተተወ አይደለም፤ ጌታ አለው። በርግጥ ሕመሙ መሪር ስብራቱም ታላቅ ነው። ይሁን እንጂ፣ ስብራቱ ክፉ ሕመም አስታቅፎት ቢገኝም እንኳ፣ ይህ ዓለም ፈጣሪው የራራለትና የወደደው ዓለም ነው። እግዚአብሔር ለገዛ ራሱ ዓለም ራሱን ያለመሠሠት ሰጥቶቷል፤ ንጹሕ ሕይወት ከፍሎለታል። በኤን. ቲ. ራይት አባባል ለመግለጽ፣ እግዚአብሔር “ራሱን መሥዋዕት ባደረገበት ጥልቅ ፍቅሩ ብዛት፣ በተትረፈረፈ ደግነቱ ስፋትና ገደብ ባልታየበት ለጋስነቱ ራሱን እየቈረሰ በገዛ ፍጥረቱ ላይ ክቡር ሕይወቱን አሟጥጦ አፍስሶለታል።” ይሁን እንጂ ይህ አስደናቂ መለኮታዊ በጎነት “በተከወነ እውናዊ ተካፍሎት” እና “ሊሆን በሚጠበቅ ተስፋ” ቢጋር ውስጥ ተቀንብቦ ነው የምናገኘው። ለምን?

ኀጢአት የወለደው ውድቀት ዓለሙን አበላሽቶታል። ስለዚህ ጭንቀት፣ ሽብር አካላዊ ድካሞች፣ ሕመምና መናጋት ሁሉ በዓለም ተገኙ። እግዚአብሔር በመቤዠት ሥራው ሁሉን ፍጹም እስከሚያደርግ ድረስ ችግሮች በዓለማችን ነበሩ፤ ይኖራሉም። በኀጢአት መግባት ምክንያት ክፉ የሆነው የአሁኑ ዓለም ሥርዐት ተንሠራፍቶ ይገኛል (ገላ 1፥4)። “የአሁኑ ዓለም”፣ ወይም “ይህ ዓለም”፣ ወይም “የአሁኑ ዘመን”  ተብሎ በተጠራው ሥርዐት ላይ አዳም የወደቀው የሰው ዘር ሁሉ አባት ሆኗልና መላው የሰው ዘር በዐመፃ ኀይል ከኀጢአት ባርነት ሥር ተንበርክኳል። በሙሴ በኩል የተሰጠው አሮጌው ወይም ሲናዊው ኪዳን እንኳ ሊታደገው አልተቻለውም። በዚህ ሥርዐት ፍጥረት ሁሉ ለጥፋት፣ ለመበስበስና ለሞት ተገዝቷል። ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደ መባሉ፣ ምድርን እንደ መንግሥቱ መቀመጫ ይጠቀምባታል። የሰው ልጆችን፣ ማለትም የዳግም ልደት ብርሃን ያላገኙትንና ከእግዚአብሔር ተለይተው ከእርሱ ጋር በጠላትነት ያሉትን ሁሉ “ሥጋ” ይቈጣጠራቸዋል። የእግዚአብሔር ሕዝቦች በአሕዛብ (አረማውያን) ግዛት ሥር እየተገፉ ይኖሩበታል። ይህ ነው ክፉ የሆነው የአሁኑ ዓለም የሚባለው።

ነገር ግን፥ “ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኀጢአታችን ራሱን” (ገላ 1፥4) በሰጠው መሲሕ ኢየሱስ መምጣት ምክንያት፣ ይመጣ ዘንድ ያለው የአዲሱ ዓለም ሥርዐት ተመርቆ ተከፍቷል። የሚመጣው ዘመን (ዓለም) ተብሎ የተጠራው ይህ የመታደስ ሙላት የአዲስ ፍጥረት ምልሰት ሥርዐት ተደርጓል።

“ስለ እርሱ የምንናገርበት የሚመጣው  ዓለም” (ዕብ2፥5) በተስፋ ሲጠበቅ የኖረ ነበር። ይህ ዘመን በመሲሑ ኢየሱስ መምጣት፣ በተለይም በመስቀል ሞቱና በትንሣኤው እንዲሁም፣ በመንፈስ መውረድ የተነሣ ተመርቆ የተከፈተ ዘመን (ዓለም) ነው። ክርስቶስ ኢየሱስ “የኋለኛው አዳም” ነውና፣ የአዲሱ ሰው ዘር ራስ ሆኗል። በክርስቶስ የተመሠረተው አዲሱ ማኅበረ ሰብ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ለጽድቅ “ባሪያ” በመደረግ የአዲሱ መታዘዝ አገልጋይ የሆነበት ነው። ይህ ዘመን የአዲስ ኪዳን ዘመን ነው። ከጥፋት፣ ሞትና ድቀት የተለየው አዲሱ ፍጥረት ሕይወትን በሚሰጠው የዘላለም መንፈስ አማካይነት የእግዚአብሔርን ክብር ያንጸባርቃል። አሐዱ-ሥሉስ የሆነው አምላክ ዘላለማዊ ንጉሥ ሆኖ ይገዛበታል፤ ምድርም የእርሱ መንግሥት ግዛት አካል ተደርጋለች። በመስቀሉ ሥራ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቁ በመንፈስ ኀይል የተሞላው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የመሠረተውና ዳግም የተወለደው አዲሱ ሰው የሚመራው “በመንፈስ ቅዱስ” ሲሆን፣ እርሱም የእግዚአብሔር ሕዝብ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ለመግዛት እንዲቻላቸው የተስፋ ዐረቦን አስይዟቸዋል።

እንግዲህ የተነሣንበት ጕዳይ የሚያርፈው እዚህ ጋ ነው። እነዚህ ሁለት ዘመናት (ዓለማት) ከመደራረባቸው የተነሣ ውጥረት ተፈጥሯል። ይህም ማለት፣ በብሉይ ኪዳን በተሰጠው ተስፋ መሠረት ይመጣ ዘንድ ያለው የእግዚአብሔር መንግሥትና መለኮታዊ አገዛዙ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ መምጣት አስቀድሞ እውን ሆኗል። ነገር ግን ምልዓታዊ ትፍጽምቱን አግኝቶ አልተጠናቀቀም፤ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ነው። እስከዚያ ድረስ ልናመልጠው በማንችለው ውጥረት ውስጥ ገብተናል። ስለዚህ ተፈውሰናል፤ ግን ደግሞ ገና እንፈወሳለን። “ወዳጆች ሆይ፤ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፣ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም ” (1ዮሐ 3፥2) ተብሎ እንደ ተጻፈ።

ከዚህ የተነሣ፣ ቤተ ክርስቲያን የዘመነ-ፍጻሜ የእምነት ማኅበረ ሰብ (eschatological faith community) ተብላ ትጠራለች። ይህ የመጨረሻው ዘመን ነው (2ጢሞ 3፥1፡5፤ ሐሥ.  2፥17፤ 1ቆሮ 10፥11፤ ዕብ 1፥2፤ 9፥26፤ ያዕ 5፥3፤ 1ጴጥ 1፥19-21፤ 1ዮሐ 2፥18)። ጥንት አማኞች የዘመን መጨረሻ ተስፋ ፍጻሜውን እንደ አገኘና እነርሱ በሚኖሩበት ዘመን የመጨረሻው ቀን እንደ ደረሰባቸው ያምኑ ነበር (1ቆሮ 10፥11)። እግዚአብሔር በአቀደውና በተገበረው የታሪከ ደኅነት ቢጋር ምክንያት፣ የቅዱሳት መጻሕፍት አጥኚዎች ቤተ ክርስቲያን አሁን ያለችበትን ሥፍረ ዘመን፣ “አስቀድሞ የሆነና ሊሆን ባለ እውነታ የታጠረች የቤተ ክርስቲያን ዘመን” (the Already-Not-Yet Church Age) ብለው ይጠሩታል። የአዲስ ኪዳን ጸሓፍያን ከነበራቸው የትርጓሜና የንጽረተ ዓለም ቅድመ ልባዌ መካከል አንደኛው የአዲስ ኪዳንናዊ ቀዳሚ ሁነትና ገና ያልተፈጸሙ የተስፋ ሁነቶች መካከል ያለ ውጥረትን ይመለከታል፤ ቀደምት-ግን-መች ገና/ አስቀድሞ-ነገር ግን-ገና (Already-Not-Yet)። የአዲስ ኪዳን ተማሪዎች ይህንን ውጥረት ተመርቆ የተከፈተው የዘመን ፍጻሜ ወይም “አስቀድሞ የሆነው-ነገር፣ ግን-ገና የሚጠበቀው” የፍጻሜ ዘመን ብለው ይጠሩታል።

እነሆ፤ የመጨረሻው ዘመን ተመርቆ ተከፍቷል። ይህም ማለት፣ በብሉይ ኪዳን በተሰጠው ተስፋ መሠረት ይመጣ ዘንድ ያለው የእግዚአብሔር መንግሥትና መለኮታዊ አገዛዙ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ምጽአት አስቀድሞ እውን ሆኗል። በኢየሱስ ክርስቶስ ትሥጉት፣ ሞትና ትንሣኤ (ወይም በማንነቱና በሥራዎቹ) የእግዚአብሔር ተስፋዎች ተፈጸሙ (ዮሐ 19፥30፤ 2ቆሮ 1፥20)። ክፉ ከሆነው ከአሁኑ ዓለም ድነናል (ገላ 1፥2-3)። የመንፈስ ቅዱስ ካሪዝማዊ ኀይል በክርስቶስ በተገኘው መላለማዊ የእምነት ማኅበረ ሰብ ውስጥና መካከል ይሠራል። ይመጣ ዘንድ ያለው ዓለም ወይም ዘላለማዊ መጪ ዘመን (ሉቃ 20፥35፤ ዕብ 2፥5)፣ የዘላለም ሕይወት፣ የልጅነት ክብር፣ የመንግሥቱ ድል ነሺነት ወዘተ. ተመርቆ ተከፍቷል (inaugurated eschatology)። ነገር ግን ምልዓታዊ ትፍጽምቱን አግኝቶ አልተጠናቀቀምና የዚህ ዓለም መከራ አማኞችን ሊያገኛቸው ይችላል። ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይሆናልና በተስፋ ይጠበቃል። ስለዚህ ገና የሆነውን ተፍጻሜትን (the not yet eschatological consummation) እንጠባበቃለን ማለት ነው።

መለኮታዊ ፈውስም የሚታይበት ጠገግ የተዋቀረው በዚህ የማይለወጥ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ቢጋር ዐውድ ውስጥ ነው፤ ይኸውም በመጣችውና ገና በምትመጣው የመንግሥቱ ሥርዐት። የእግዚአብሔር መንግሥት መጥታለች (ማቴ 12፥22-28፤ ሮሜ 14፥17)፤ ነገር ግን፣ በምልዐት በዚህ አይደለችምና ገና ትመጣለች (ማር 14፥25፤ ሉቃ 14፥12-15፤ 2ጢሞ 4፥18)። እነሆ፤ ተፈውሰናል፤ ግን ገና እንፈወሳለን።

ፈውስና የእግዚአብሔር መንግሥት

መለኮታዊ ፈውስን ከእግዚአብሔር መንግሥት የመገለጥ ኀይል ጋር ማየት ይገባል ብለናል። የእግዚአብሔር መንግሥት ስንል የእግዚአብሔር አምላክ አገዛዝ፣ አምላካዊ ሥልጣነ-መንግሥት ወይም ሥፋኔ-መንግሥት ማለታችን ነው። ቀደም ብለን እንዳልነው፣ በክርስቶስ ማንነትና በሥራዎቹ አማካይነት የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥጢር ሥርዐት ተመርቆ ተከፍቷል። ስለዚህም፣ መለኮታዊ ፈውስ ከእግዚአብሔር መንግሥት መገለጥ ጋር የተቈራኘ ነው።

የኢየሱስ አገልግሎት የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጥ ዐዋጅ ምስክር ስለ ነበር መለኮታዊ ፈውስ የዚያ አንዱ ማሳያ ተደርጓል። ጌታ ኢየሱስ፣ “እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፣ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች” (ማቴ 12፥28) ያለው ለዚህ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ምድር የመጣው የሰው ልጆች መድኅንና ፈዋሽ ጌታ ሆኖ ነው። የናዝሬቱ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በተገለጠበት ግብሩ የመንግሥቱን ወንጌል ለመስበክና ሁሉን ደኅና ሊያደርግ በመካከላችን ተገኘ። ቃሉ ለድሆች፣ ለታሰሩና ለመከረኞች መልካም ብሥራት ያመጣ ሲሆን፣ የታመሙትንም ፈውሷቸዋል። “ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፣ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፣ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር” (ማቴ 9፥35 እና 4፥25)። ፈውስ የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት ማረጋገጫዎች አንዱ ሆኖ ተገልጧል። ስለ ሆነም የጌታችን አገልግሎት በፈውስ ተአምራት የተንቈጠቈጠ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ፈውስ የመንግሥቱ ተልእኮ አካልም ነበር፤ ኢየሱስ “ዐሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው … በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው ” (ሉቃ 9፥1-2፡ 10) አላቸው። ስለዚህ፣ ፈውስ ለመንግሥቱ ወንጌል ዐዋጅ ምሥክር ሆኖ ቀርቧል (የሐዋ. 14፥3)። ይህም ማለት የእግዚአብሔር መንግሥት ከሰይጣን ኀይል በአሸናፊነት ልቃ በድል ነሺነት እየታየች የመምጣቷ መገለጥና መታየት መሆኑ ነው። ይህ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል የሚሠራው የመንግሥቱ ባርኮት ምልክቶች የመጀመሪያዋን የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ሞገሳም እንዳደረጋት ጥቂት የአዲስ ኪዳን ምንባባት ያስረዳሉ (ሐዋ. 3፥1-11፤ 4፥21-22፤ 4፥32-37፤ 5፥1-16፤ 9፥33-34፤ 14፥8-10 ወዘተ.)። የእኛስ ዘመን እንዴት ነው? እኛም መለኮታዊ ፈውስን ጨምሮ ለተአምራትና ድንቅ ምልክቶች መጸለይ ይገባናል ወይ?

ዛሬም ለፈውስ መጸለይ እንችላለን

መለኮታዊ ፈውስ ዘለቄታዊ የቤተ ክርስቲያን ልምምድ ስለ መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የተለያዩ አቋሞች ተይዘዋል። በዚህ ሰበብ ዛሬም ለሕሙማን ፈውስ መጸለይ እንችላለን ወይ? የፈውስ ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን ይሠራሉን? … የሚሉና ተመሳሳይ ጥያቄዎችን የሚያነሡ ወገኖች አሉ። መልሱ አዎን ነው። እግዚአብሔር ሕያው ነው። የአዲስ ኪዳን ዘመነ መግቦት በመንፈስ መውረድ የታደሰ እንደ መሆኑ የጸጋ ሥልጣን የተጐናጸፈችው የክርስቶስ ማኅበር የማይቋረጥ ጸጋና ኀይል ከመንፈስ ቅዱስ ትቀበላለች።

የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ አሠራር በአንድ ወቅት ብልጭ ብሎ የተዳፈነ ነበልባል አይደለም። እንደርሱ ለማየት መጽሐፍ ቅዱስ አይፈቅድልንም። ባጋጠመው መንፈሳዊና ነገረ መለኮታዊ የአቋም ለውጥ ምክንያት ዳላስ ሴሚናሪን ለቅቆ እስከ መሄድ የተገደደው ጃክ ዲር፣ “ማንም ሰው፣ መጽሐፍ ቅዱሱን አንሥቶ ማንበብ ከጀመረ በኋላ፣ እግዚአብሔር ምልክቶችንና ድንቆችን ከዚህ በኋላ አያደርግም፤ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታም ዐልፎበታል ለማለት ፈጽሞ አይችልም። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በዘመናችን መሥራት አቁመዋል የሚለው አቋም (cessationism) የመነጨው መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ከማንበብ ሳይሆን ከተሞክሯዊ ልማድ ነው” ያለው ለዚህ ነው። መንፈስ በአማኝ ሕይወት ውስጥ ውስጣዊ የቅድስና ለውጥ ከማስገኘቱ በተጨማሪ ምእመናንን በሚያለብሳቸው የኀይል ስጦታዎቹ አማካይነት ለማነጽ መሥራቱን ቀጥሏል። ስለሆነም፣ ለሕሙማን መጸለይ እንችላለን።

አዶልፍ ቮን ሐርናክ የተባለ ጀርመናዊ የነገረ መለኮት ሰው፣ የኒቼን በሚመስል ድምፀት፣ በአንድ ወቅት እንዳለው፣ “ክርስትና ለሕሙማን የተሰጠ ሃይማኖት ነው።” ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ስለ ሕሙማን መጸለይ አለባት። ይህ ለምን ይሆናል? ነገሮችን ማቻቻል ስላለብን ነውን? አይደለም። ይልቅስ፥ መንፈስ ቅዱስ ይህንና ሌሎችን መንፈሳዊ ስጦታዎች ለቤተ ክርስቲያን መስጠቱን አዲስ ኪዳን ስለሚያስተምረን (1ቆሮ 12፥8-11) ነው። ማስተማር ብቻ ሳይሆን እንድንለማመደው ስለሚያዘንም ጭምር ነው (1ቆሮ 14፥1)። እግዚአብሔር ከሉዓላዊ ፈቃዱ ጋር በተጣጣመ መንገድ (ዕብ 2፥4) ሰዎችን በተአምራዊ መንገድ ዛሬም ይፈውሳልና።

የእግዚአብሔር መንግሥት የሕያው እግዚአብሔር አገዛዝ ናትና በምሥጢራዊ ሥርዐቷ እየሰፈነች በገሀዳዊ የመገለጥ ብርሃኗ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ታበራለች። አሁን በክርስቶስ አካል በቤተ ክርስቲያን በኩል እግዚአብሔር በሥራ ላይ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ኀይል በምእመናን ሕይወት መታየት የሕያው ቤተ ክርስቲያን አንዱ መገለጫ ሆኗል።

በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በማንኛውም ጊዜና ቦታ አንዳች ነገር ያደርጋል በማለት ይጠባበቃሉ። በተለይም በጴንጠቈስጣዊ-ካሪዝማዊ የክርስትና ዘርፍ ባሉ አማኞች ዘንድ “የመንግሥቱ የአሁንነት ገጽታ” በትምህርታቸውና በልምምዳቸው አጽንዖት ይሰጠዋል። ጄ. አይ. ፓከር “ካሪዝማውያን [ክርስቲያኖች]፣ ‘ቤተ ክርስቲያን ገና ታላላቅ የእግዚአብሔር ጕብኝቶች ይጠብቋታል’ ብለው በፍል ጕጕትና ጥበቃ በአውራ ጣታቸው ቆመዋል” ማለቱ ከዚህ የመነጨ ነው። እናከብረውና በእርሱ ብቻ ደስ ይለን ዘንድ እግዚአብሔር ፈዋሻችን ምሕረቱን ያደርጋል። በዚህ እውነት ተደግፈንና በትሕትና ተሞልተን ስለ መለኮታዊ ፈውስ መገኘት መጸለይ እንቀጥላለን።

ሆኖም ፈውሱ ዐላማ አለው። እግዚአብሔር የፈውስ ስጦታን የሚሰጠው ለተደረገለት ሰው ከሚያመጣው እፎይታ በላይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማክበርና ሰዎችን ወደ ወንጌሉ ለማምራት ነው። ለዚህ ነው ጳውሎስ እንደማንኛው ስጦታ ሁሉ፣ የፈውስ ስጦታም ለማኅበሩ ጥቅም መሆኑን የሚናገረው (1ቆሮ 12፥7)። ከፈጣሪ አምላክ በቀር ማናችንም ሰዎችን ለመፈወስ ኀይል የለንም (ሐሥ 3፥12-13)፤ ሁልጊዜም በኢየሱስ ስም መጸለይ የተገባንም ለዚህ ነው። እግዚአብሔር አንድን ሰው በፈወሰ ጊዜ፣ ለታማሚው ከሚያደርግለት ምሕረትና ርኅራኄ እንዲሁም የእምነት ማበረታታት በላቀ ሁኔታ፣ ለስሙ ክብርን ይወስዳል (ማቴ. 4፥23)። ወንጌልን ለማካፈል ልዩ ዕድል በመፍጠር ለቤተ ክርስቲያን ጥቅምና ለዓለም ምስክር እንዲሆንም ይፈልጋል።

መለኮታዊ ፈውስና የሕክምና መድኀኒት

መለኮታዊ ፈውስ ለማግኘት የመጸለያችንን አግባብ ተመልክተን ስናበቃ በመግቢያችን ላይ ያየነውን ዐይነት ታሪክ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ስለሚያልፉ ወገኖች ምን እናድርግ? ስለ መለኮታዊ ፈውስ ጸሎትና አገልግሎት ያለው እውነታ ክርስቲያኖች በታመሙ ጊዜ ዘመናዊ የሕክምና ዕገዛ እንዳያገኙ ይከለክላቸዋል ወይ? የተጸለየላቸው ሰዎች ሁሉስ ይፈወሳሉ ወይ? እነዚህና ተመሳሳይ ጥያቄዎች በዙሪያችንና በመካከላችን ይገኛሉ።

ይህ ርእሰ ጕዳይ በኢትዮጵያ ክርስቲያን ሐኪሞች ማኅበር ተዘጋጅቶ በተበተነውና በዚሁ የሕንጸት ዕትም ላይ በታተመው መግለጫ የቀረበ ስለ ሆነ ሰፋ ባለ ሁኔታ አልገባበትም። ሆኖም ከላይ እያየነው ከመጣነው ሐሳብ ጋር በሚገናኝ መልኩ አንዱን ገጽታውን ብቻ ማንሣት የሚገባ ይመስለኛል። ይኸውም፣ ክርስቲያኖች የሕክምና መድኀኒት መውሰዳቸው በመለኮታዊ ፈውስ ማመናቸውን የሚቃረን አለመሆኑን መጠቈም ይመለከታል።

በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜያት እንደ ታየው፣ መድኀኒት መውሰድ የእምነት መጕደል ምልክት የሚመስላቸው አማኞች አሉ። እንዲያውም ኢየሱስ ማንንም ወደ መድኀኒተኛ አልሰደደም በማለት የሚሟገቱ ይኖራሉ።

በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የሕክምና አገልግሎት ለረጅም ዘመናት የቈየ ሙያ እንደ ሆነ ይታወቃል። በጥንታዊው ዓለም የሕክምና ሙያና ምርምር ይካሄድ ነበር። ሆኖም በእስራኤላውያን ዘንድ የሕክምና ሙያ የነበረ ቢሆንም የዳበረ አይመስልም። በጥቅሉ፣ በዘመኑ የሕክምና ባለሙያዎች መኖራቸው ቢታወቅም ያልዳበረ እንደ ነበረ ግልጽ ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከተወሰኑ ፍንጥቅታዎች ውጭ ስለ ሕክምና ሙያና ሐኪሞች የሚሰጠው ዝርዝር ነገር የለውም። ዐልፎ፣ ዐልፎ የተጠቀሱ ፍንጮችን ብቻ ነው በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የምናገኘው (ምሳ. 17፥22)፤ አንድ ተደብድቦ በአልጋ ላይ የዋለ ሰው ተሽሎት እስቲያገግም ድረስ ጕዳት አድራሹ ሊንከባከበው እንደሚገባ በሚናገርበት ክፍል “ያስፈውሰው” የሚል ሐሳብ ተጠቅሷል (ዘጸ. 21፥19)። እንዲሁም ተምሳሌታዊ አገላለጥ ጥቅም ላይ በዋለባቸው አንዳንድ ምንባባት ውስጥ ባለ መድኀኒቶች (ሐኪሞች) ተጠቅሰዋል። ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ መንፈሳዊ ፈውስ መታጣት በጮኸበት ክፍል “በገለዓድ የሚቀባ መድኀኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? የወገኔ ሴት ልጅ ፈውስ ስለ ምን አልሆነም?” (ኤር. 8፥22) በማለት ሲጽፍ ሐኪሞችን ጠቅሷል። ገለዓድ በጊዜው ቅመማ ቅመምና ለመድኀኒት የሚሆኑ ዕፀዋት የሚገኝበት ምድር ነበር (ዘፍ. 37፥25 ይመ.)።

የይሁዳ ንጉሥ አሳ ከእግዚአብሔር ይልቅ ባለ መድኀኒተኞችን በመፈለጉ መነቀፉ ተዘግቧል፤ “አሳ እግሩን ታመመ፤ ደዌውም ጸናበት፤ ነገር ግን በታመመ ጊዜ ባለ መድኀኒቶችን እንጂ እግዚአብሔርን አልፈለገም” (2ዜና. 16፥12) ይላል። በርግጥ ችግሩ መድኀኒት መጠቀሙ አይመስልም፤ “እኔ ፈዋሽህ ነኝ” ያለውን አምላኩን ያህዌን አለመፈለጉ እንጂ። ምናልባትም፣ ኀጢአት፣ ርኵሰትና ጥንቈላ ወደ ማይጠፋበት የአረማውያን ልማዳዊ ሕክምና ሳይሆን አይቀርም የሄደው።

በኢሳይያስ 38፥1 ላይ እንደምናነብበው ሕዝቅያስ ታሞ በሞት አፋፍ ላይ ደርሶ ነበር፤ እንደሚሞትም ሰማ። አምርሮ ካለቀሰ በኋላ ግን በነቢዩ በኩል እንደሚፈወስ ተነገረው። ኢሳይያስ በሰጠው መመሪያ መሠረት የሕዝቅያስ ዕባጭ ላይ “የበለስ ጥፍጥፍ” ወስደው ማድረግ ነበረባቸው። በጥንቱ ዓለም፣ በተለይም በኡጋሪት፣ በለስን በመድኀኒትነት የመጠቀም ልማድ ነበር። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐታቲያን በለሱን በዕባጩ ላይ እንዲያደርጉ መታዘዛቸውን የሚገልጠው ግስ ብዙ ቍጥር መሆኑን ከግምት በማስገባት፣ “የቤተ መንግሥቱን ሐኪሞች የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም” ይላሉ (አመት የግርጌ ማብራሪያ ገጽ 1066 ይመ.)። በቀጥታ የቀረበ ባይሆንም፣ ይህ ምንባብ ልዕለ ተፈጥሯዊ የሆነ ተአምራዊ ፈውስ በጊዜው ይታወቅ በነበረ የሕክምና መድኀኒት በኩል ተፈጽሟል ሊያሰኝ ይችላል።

በኤርምያስ 30፥12-13 ላይ ስናነብብ ይሁዳ ላይ ስለ ደረሰው መንፈሳዊ ስብራትና ቍስል ይናገራል። “ስብራትህ የማይፈወስ ቍስልህም ክፉ ነው። … ቍስልህንም የሚፈውስ መድኀኒት የለህም።” በዚህ ተምሳሌታዊ ንግግር ውስጥ የይሁዳን ውርደት የሚፈውስ መድኀኒት አለመገኘቱ ተጠቅሷል። እንግዲህ፣ ተምሳሌቱ የተዋቀረው በዘመኑ በሥጋዊ ቍስል ላይ መድኀኒት ይደረግበት ከነበረው የሕክምና ልማድ ተወስዶ መሆኑ ነው፤ ተጠየቃዊ አካሄዱም የቈሰለ ሰው መድኀኒት ይሰጠዋል የሚል ነው። ተመሳሳይ ተምሳሌታዊ አገላለጽ በኤርምያስ 51፥8 እና ሕዝቅኤል 30፥21 ላይ መመልከት ይቻላል።

የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና ቍጥር ውስጥ በማይካተተውና ሲራክ በሚባለው አንድ የአይሁድ አዋልድ መጽሐፍ ውስጥ ሐኪሞችን በሚመለከት በማዕከለ ኪዳናት (በሁለቱ ኪዳናት መካከል) የነበረውን ግንዛቤ የሚያሳይ ምዕራፍ አለ (ሲራክ 38)። ሲራክ የቀኖና መጽሐፍ አይደለም። በእስትንፋሰ እግዚአብሔር አልተጻፈም። በዘመኑ የነበረ አይሁድ ድርሰት ነው። ስለሆነም ሲራክ የሚለውን እንደ ቃለ እግዚአብሔር መመሪያ እንወስዳለን ማለት አይደለም። ነገር ግን መጽሐፉ የተጻፈው በማዕከለ-ኪዳናት ዘመን በነበሩ አይሁድ በመሆኑ ምክንያት የአይሁድ ማኅበረ ሰብ ዘንድ በዘመኑ የነበረውን ግንዛቤ በታሪክ ማስረጃነት ሊያሳየን ይችላል። ስለዚህ፣ የተወሰነ ክፍሉ እንዲህ ይላል። “ባለ መድኀኒትን አክብረው…እርሱንም እግዚአብሔር ፈጥሮታልና። ማዳን ከእግዚአብሔር የሚገኝ ነው። …እግዚአብሔር መድኀኒትን ከምድር ፈጠረ፤  …እግዚአብሔር ለሰዎች ጥበብን ሰጣቸው፤ … ልጄ ሆይ በሽታህን ቸል አትበል፤ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፤ እርሱም ይፈውስሃል። እግዚአብሔር እርሱን ፈጥሮታልና ለባለመድኀኒት መንገድ አብጅለት” (ቍ. 1-9)።

እንግዲህ የሕክምና እርዳታ መኖሩን የሚያሳዩ ፍንጮችን ተመልክተናል። በአዲስ ኪዳንም ሉቃስ ሐኪም እንደ ነበር ተገልጿል (ቆላ. 4፥4)። ኢየሱስ በተምሳሌቶቹ ውስጥ ስለ ባለ መድኀኒተኞች ጠቅሷል። (ማር. 2፥17፤ ሉቃ. 4፥23፤ በተጨማሪ ሉቃ. 8፥43 ይመ.)።

ከእነዚህ ጥቂት ክፍሎች የምንረዳው የሕክምና አገልግሎት በአሉታዊነት አለመጠቀሱን ነው። እግዚአብሔር በጥንቱ ዘመን በእስራኤል የነበሩትን ሐኪሞች የነቀፈበት ግልጽ ማስረጃ የለም። ዛሬም ቢኾን፣ ክርስቲያኖች የሕክምና ዕገዛ እንዳያገኙ ለመከልከል የሚያበቃ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አናገኝም። ሲሆን ሲሆን በሕክምና ጥበብ አማካይነት ሰዎች ስለሚያገኙት ዕገዛና እርዳታ እግዚአብሔርን ማመስገንና ስለ እነርሱ መጸለይ የተገባ ነው። ዐልፎ ዐልፎ የምናየውና የምንሰማው ግን በተቃራኒው ሆኗል። ማስተዋል በጐደለው መልኩ በግልጽና በተዘዋዋሪ መንገድ የሚሠነዘሩ የማጣጣልና የማንጓጠጥ ተግባራት ከክርስቲያናዊ አስተሳሰብና ምግባር በሩቁ የቆሙ ናቸው።

በጥቅሉ፣ እግዚአብሔር በመለኮታዊ የፈውስ ኀይል ሰዎችን ከሕመም ሥቃያቸው ያሳርፋል። ሐኪሞች በሚሰጡት ሙያዊ ዕገዛ በኩልም ሕሙማን እንዲድኑ እንደሚያደርግ ግልጽ ነው፤ ክርስቲያኖች እንዲፈወሱ መጸለይም ይገባል። ይህ ሁሉ ሆኖ ክርስቲያኖች ላይፈወሱ የሚችሉበት ሁኔታ አለ? 

ባንፈወስስ?

እግዚአብሔር እንደሚፈውሰን እናምናለን። በክርስቶስ ማኅበር መካከል በመንፈሱ የጸጋ ኀይል ሕሙማንን ይፈውሳል። ይህ ማለት ክርስቲያኖች ጨርሶውኑ ሊታመሙ አይችሉም ማለት አይደለም፤ ወይም የታመሙ ሁሉ ይፈወሳሉ ማለትም አይሆንም። ይህ ለምን ይሆናል? ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱ ሁሉንም ፈውሶ የለምን?

ጌታችን ኢየሱስ ወደ እርሱ የመጡትን ሰዎች ሁሉ ፈውሷል (ማቴ. 8፥6-13፤ 12፥15፤ 19፥2፤ 21፥14)። ሌሎች ሰዎች ተሸክመው ወደ እርሱ ያመጧቸውንም እንደ ፈወሳቸው መጽሐፍ ይመሰክራል (ማቴ. 4፥24፤ 9፥32-33)። ሰዎች አምጥተው ከእግሩ ሥር የጣሏቸውንም (ማቴ. 15፥30) ፈውስ ሰጥቷቸዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ ራሱ ወዳሉበት ቦታ ሄዶ ያገኛቸውን ሕመምተኞች ፈውሷቸዋል (ማቴ. 8፥14-15)። ሆኖም በሁሉም ቦታ፣ ሁልጊዜምና ሁሉንም ሰዎች ፈውሷል የሚል ቀኖና ለማግኘት አንችልም። ለምሳሌ፣ እኛ በማናውቀው ምክንያት ከብዙ ሕሙማን መካከል አንዱን ብቻ ፈውሶ የሄደበትን ታሪክ እናገኛለን። በተለያዩ ሕመሞች ተይዘው ካሁን አሁን ወደ ውሃው በገባን እያሉ በቤተ ሳይዳ ከተኙ ከብዙ ታማሚ “ሕዝብ” መካከል ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በአልጋ ቍራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ የኖረውን ሰው ብቻ ፈውሶ ሄደ (ዮሐ. 5፥1-0)። ሌሎቹን ሁሉ በመደዳ ለምን አልፈወሰም? እኔ አላውቅም።

በሐዋርያቱ አገልግሎትስ? በመጀመሪያው ምእት ዓመት ቤተ ክርስቲያንስ? በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን የፈውስ አገልግሎት በቀጣይነት ቢታይም እንኳ፣ ሁሉም ሕመምተኞች ቀጥተኛ የፈውስ ኀይል በመደዳ ሲቀበሉ አይታዩም። ይህን የሚያረጋግጡ የተወሰኑ ምንባባት በአዲስ ኪዳን ይገኛሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ወንድም ጥሮፊሞስን ታሞ እያለ በሚሊጢን ትቶት ሄደ (2ጢሞ 4፥20)። ጢሞቴዎስ “ስለ ሆዱ ሕመምና ስለ በሽታው ብዛት” ወይንን በመድኀኒት መልክ እንዲወስድ ተመከረ (1ጢሞ 5፥23)። የጳውሎስ የአገልግሎት አጋር የነበረው አፍሮዲጡ ከሞት አፋፍ እስኪመለስ ድረስ በጠና ታምሞ ተኝቶ ነበር (ፊል 2፥25-28)። በጳውሎስ ላይ ኀዘን እንዳይበረታ ጌታ ማረለት እንጂ። የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ በድንቅና በተአምራት የታጀበ የነበረው ጳውሎስ ለእነዚህ ወገኖች ሊያውም የአገልግሎት አጋሮቹ ለነበሩ ዐርበኞች ጸልዮ ፈውስን ሲያመጣ አለመታየቱ አስገራሚ ይመስላል።

ከሁሉም ትኵረታችንን የሚስበው፣ ጳውሎስ በመገለጥ ታላቅነት እንዳይታበይ “የሥጋው መውጊያ እንዲሆን የተሰጠውን ጐሳሚ የሰይጣን መልእክተኛ” አስመልክቶ ጌታ እንዲያነሣለት ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት ወደ ጌታ ቢጸልይም ያገኘው ምላሽ ነው። “በጸጋው ብቃት” ከችግሩ ጋር ዐብሮ እንዲቈይ እንደ ተተወ እናነብባለንና (1ቆሮ 9፥2-10)። ሆኖም፣ እነዚህ ሁሉ ጳውሎስን በመለኮታዊ ፈውስ ከማመን አላገዱትም። ጳውሎስ ለሕሙማን በመጸለይና ብዙዎች ፈውሳቸውን ሲቀበሉ ለማየትና ለመመስከር በቅቷል (ለምሳሌ፣ በሐዋርያት ሥራ 14፥8-18፤ 16፥16-18፤ 19፥11-12፤ 20፥7-12፤ 28፥1-9 ይመ.)።

እግዚአብሔር የሚፈውሰን እንደ ፈቃዱ ነው (ዕብ 2፥4)። እንደ ሰው ልንዘናጋ ስለምንችል ማስተዋል አለብን፤ ያዕቆብ “አትለምኑምና አትቀበሉም” (ያዕ 4፥2) ይላልና ጌታን መጠየቅ ይገባናል። ነገር ግን፣ በምንኖርበት የፍጻሜ ዘመን እውነታ ምክንያት ሁሉንም የመንግሥቱን ባርኮቶች በዚች ሕይወት ሳለን አልሰበሰብናቸውም። የመንግሥቱን መከር የፊተኛ በኵራት ፍሬዎችን መቅመሳችን እውነት ነው። ነገር ግን፣ የመዋጀታችን የፍጻሜ መጠቅለያ የሆነውን የሙታን ትንሣኤ እንጠባበቃለን። እንዲያውም፣ የመጀመሪያውን የመንፈስ ፍሬ የተቀበልንና “በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን” (2ቆሮ. 5፥4) በተባለበት ልክ በተጋድሎ ላይ እንገኛለን። የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት (የእግዚአብሔር ልጅነት ውርሳችንን በምልዐት የምንጨብጥበት ድምዳሜ) በናፍቆት እየተጠባበቅን በመቃተት የመኖራችን እውነታ በጕልህ የተጻፈ እኮ ነው (ሮሜ 8፥23)! ስለዚህ ስለ ሕመማችን ጸልየን ሳንፈወስ ብንቀር ብርቱ የሆነውን የማስቻል ጸጋውን እንዲሰጠን እንጸልያለን እንጂ እምነታችንን መጣል አይኖርብንም (2ቆሮ 12፥7-10)። ልንዘነጋው የማይገባ እውነት አለ። ብንኖርም የጌታ፣ ብንሞትም የእርሱ ነን (ፊል 1፥21)። ሞት ለክርስቲያን ሽንፈት አይደለም።

በሌላ በኩል፣ ፈውስ ያላገኘነው ከእምነታችን ማነስ ወይም ሰይጣን በሚነዛው ፍርሀትና ጥርጣሬ ተዋክበን ከሆነ እምነታችን እንዲያሳድግልን ጌታን መማጸን እንችላለን (ማር 6፥5-6፤ ማቴ 9፥22፡ 29፤ ሉቃ 17፥19)። ይሁን እንጂ፣ ማስተዋልና ርኅራኄ የጐደላቸው አንዳንዶች እንደሚያደርጉት፣ የእምነት ማነስ ወይም የእምነት ማጣት የተባለው ሰበባ ሰበብ ሕሙማንን በጭካኔ የምንቀጠቅጥበት ከንተሮ አይደለም። ጌታ ኢየሱስ እርሱን ለማያውቁ ሰዎች ሁሉ ፈውስ መስጠቱን አንዘነጋም።

ሌላው በጣም ግልጽ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ለሕሙማን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዲጸልዩ የማድረግን መርሕ ችላ አለማለት ነው፤ ሕሙማንን የሚፈውሰው የእምነት ጸሎት መሆኑ በግልጽ ተጽፏል (ያዕ 5፥14-15)። ይህ ሲባል ሌሎች ክርስቲያኖች እንዳይጸልዩ መከልከሉ ባይሆንም፣ የአንዲት አጥቢያ ማኅበረ ምእመናን ጠባቂና ባለ ዐደራ እረኞች ኀላፊነት እንዲወስዱ ያበረታታል። የእግዚአብሔርን መንጋ በእረኝነት የመጠበቅ አገልግሎት ከምእመናን መካከል የታመሙትን መንከባከብና ስለ እነርሱ መማለድን ያካትታል። ይህ በአግባቡ በተግባር ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ በዘመናችን የሚታየው ፋታ ያጣ ከቦታ ቦታ የመንከራተት ልማድ ጋብ ሊል በቻለ ነበር።

በአጠቃላይ፣ ዛሬ በየቦታው የሚታየው መሥመር የለቀቀ ትርምስ ሊታረም የሚችለው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ነው። “ክርስቲያኖች ሊታመሙ አይችሉም ወይም መታመም የለባቸውም” የሚሰኘው ዘመን አመጣሽ ሽለላ መጽሐፍ ቅዱሳዊም ሆነ ታሪካዊ መሠረት የለውም። የፈውስ ጸሎት ድራማዊ አይደለም። ኢየሱስ የፈውስን ትዕይንታዊ ገጽታ በትንሹ ነው የተጠቀመው። ሰዎች በተአምራት ዛፎች ላይ አፍጥጠው የወንጌልን ደን እንዳይዘነጉ ልብ ማለት ያስፈልጋል። የፈውስ አገልግሎትንና ሕሙማንን ወደ አደባባይ አውጥቶ ለታይታና ለዝና ፍጆታ ማዋል መታረም ያለበት ጥፋት ነው። ለአጸፋ ሐሰት (counterfeit) በር እንዳይከፍትም መጠንቀቅ ይጠይቃል። በገንዘብ ማግኛነት መጠቀምማ ከጸያፍነት የባሰ አጓጕል ድፍረት ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር የሚጥልም ነው። ጸሎት የሚደረግላቸው ታማሚዎች ፈቃድ ባልታከለበት አግባብ ስማቸውን፣ ታሪካቸውንና ምስሎቻቸውን በየመገናኛ ብዙኀኑ ላይ መጣድም ትኵረት ሊሰጠውና ሊታሰብበት ይገባል። መለኮታዊ ፈውስ ለጌታ ኢየሱስ ስም መክበርና ለሰዎች ጥቅምና በጎነት እንጂ የግለ ሰቦችንና ተቋማትን ዝና ለማውለብለብ ከዋለ አምልኮተ ጣዖት ይሆናል፤ እግዚብሔርንም ያሳዝናል።

ታማሚዎች ወደ ሕክምና ደጃፍ እንዳይደርሱ መከልከል፣ ሄደውም ቢገኙ የተቀበሏቸውን መድኀኒቶች እንዲጥሉ ማዘዝና ተፈውሳችኋል ለተባሉት ፈውሳቸውን በሕክምና እንዲያረጋግጡ አለማድረግ ወይም ችላ ማለት በየቦታው የሚሰማና በርካታ ችግር እያስከተለ መሆኑን የክርስቲያን ሐኪሞች ማኅበር ይፋ አድርጓል። ይህን መሳዩን የጭካኔ ተግባር የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች በቸልታ ሊያዩት አይገባም። ተፈውሳችኋል ተብለው የተላኩ ሰዎች በተለያዩ ችግሮች ውስጥ መግባታቸውና የአንዳንዶቹም ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ ማለፉ ፀሓይ የሞቀው፣ አገር ያወቀው ጕዳይ ነው። በተለያዩ ቦታዎች የተከሠቱትን አሳዛኝ ድርጊቶች አንባብያን ምስክር ይሆኑበታል የሚል እምነት አለ።

መደምደሚያ

በታወቀም ሆነ ባልታወቀ ምክንያት ሰዎች ሕመም ባጋጠማቸው ጊዜ ፈውስን ፍለጋ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልዩ ማበረታታት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። ፍጥረትን ያበጀው ዘላለማዊና ፈጣሪ የሆነው የአምላክ መንፈስ ፍጥረትን ሁሉ አጽንቶ ይጠብቃል። እንደ ፈቃዱና ገደብ በሌለው ነጻነት በቤተ ክርስቲያን እየሠራ ይኖራል። በሚመጣው የአዲስ ፍጥረት ትፍጽምትም ሁሉን አዲስ አድርጎ ከጥፋት ባርነት ነጻ በማውጣት ያሳርፈዋል። ክርስቲያኖች የመጀመሪያውን የመንግሥቱን ፍሬዎች ቀማሾች እንደ መሆናቸው የሕይወትን ጣዕምና ፈውስን በዚህ ሕይወት እርሱ እንደ ፈቀደ ሊሰጣቸው ይችላል። በቤዛነቱ ለመዋጀታችንም ሆነ ከአካላዊ ሕመም ለመፈወሳችን መሠረቱ የክርስቶስ ሕማምና የመስቀል መከራው ብቻ ነው፤ እርሱ ድካማችን ተቀብሎ ሕማማችንን ተሸክሟልና (ኢሳ 53፥4-5፤ ማቴ 8፥16-17፤ 1ጴጥ 2፥24)። ነገር ግን በመንፈስ፣ በአካል በማኅበራዊና በግለ ሰብ ደረጃ እርሱ እንደ ወደደ የሚቀበሉት ፈውስ የመኖሩ እውነታ ባያከራክርም፣ ሁሉንም እዚሁና ዛሬ ብቻ እንደምናገኝ መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምርም። የክርስቲያን ሕይወት ወደ ዘላለም ቤት የሚደረግ ግሥጋሤ ነው፤ የመጻተኝነት ገጽታ አለው።

ከጠፊው ዓለም የተጠሩት ምእመናን የእምነት ተጓዦችና እግዚአብሔር የመረጣቸው የማሰማሪያው በጎች ናቸው። ወደ ቤታችን በመሄድ ላይ ያለን የእምነት ተጓዦች ነን። “ዘላን ቤት የለውም፤ ሽፍታ ከቤቱ የሸሸ ነው፤ እንግዳ ከቤቱ የራቀ ሲሆን፣ የእምነት ተጓዥ ግን ወደ ቤቱ የሚሄድ ነው።” እንግዲህ በእምነት በምንጓዝበት ጊዜ ብቻችንን አይደለንም፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው። የዚህ ማረጋገጫው ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ማደሩ ነው። አዎ፤ ጌታ እንደ ተስፋ ቃሉ “ያን መንፈስም፣ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፣ በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው” (ቲቶ 3፥6-7)።

ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እግዚአብሔርን ለማገልገል ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን የመንፈስ ኀይልና እውነተኛ ኑሮን መለማመድ አለባት። ለሕሙማን የሚደረግ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አስፈላጊ ቢሆንም፣ ዋነኛው የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ማእከል ግን አይደለም። መደረግም ያለበት በመንፈስ ቅዱስ ምሪትና በእግዚአብሔር ቃል መመሪያነት ነው።

ፈውስ እግዚአብሔር በሰይጣን ሥልጣን ሥር ያለውን የጨለማ ግዛት ድል በመንሣት ማንበርከኩን ለዓለም የሚያሳይበት ምልክት መሆኑን አዲስ ኪዳን ግልጽ ያደርጋል። የሞት ሥልጣንና አገዛዝ ክፉ የሆነው የአሁኑ ዓለም ከንቱነት ወደ ፍጻሜ ዘምን አድኅኖታዊ ትፍጽምት እያመጣ መሆኑን ይመሰክራል (ሮሜ 5፥17፤ 8፥20)። የእግዚአብሔር ፍጹማዊ መንግሥት አገዛዝ የመምጣት ዐዋጅ አካልም ሆኗል። ደግሞም፣ ለሕሙማን መጸለያችን የሚያመለክተው የእግዚአብሔር መንግሥት አሸናፊነት መናፈቃችንን ነው። “መንግሥትህ ትምጣ” (ማቴ 6፥10) የማለታችን ነጸብራቅ ነው።

Solomon Abebe G. Medihin

መልካም ጅምሩ እንዳይደናቀፍ

የሥነ መለኮት ጥናት በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን አጭር ዕድሜ ያለው ነው፡፡ የዕድሜው ዕጥረት ከወንጌላውያን ክርስትና አጀማመር ጋር የራሱ ቁርኝት አለው፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ የቆይታ ዘመን በአንጻራዊነት ከታየ አጭር የሚባል ነውና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ቤተ ክርስቲያናት፣ አጋር ቤተ ክርስቲያናትና ግለ ሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶችን መክፈት ጀምረዋል፡፡ በመሠረቱ ይህን መሰሉ ጥረት ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጥረቱን ማበረታታት እንዳለ ሆኖ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዋናነት ከትምህርት ጥራት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

የፍትሕ ጩኸት እና የዝምታ ኀጢአት

በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚመለከት በታሪክ ሁለት ጽንፎች መንጸባረቃቸውን የሚያስታውሰው ዶ/ር ግርማ በቀለ፣ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የሚታየውን እኩይ ምግባር በአደባባይ ለመኮነን አቅም ሊያንሳት አይገባም ይላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.