[the_ad_group id=”107″]

ከፍቺ በኋላ፣ ኃፍረት ሲሰነብት!

ቬኔታ ሬንደር ሪዝነር
ትርጕም፦ በእምነትአብ አየለ

አንድም ቀን ይህ በእኔ ሕይወት ይሆናል የሚል ግምት አልነበረኝም። [በእኔ የቀደመ አስተሳሰብ] ፍቺ በሌሎች የሚሆን ነው፤ ክርስቲያን ባልሆኑ እና ቁም ነገር በማያውቁ ሰዎች ሕይወት። ነገር ግን፣ የመጨረሻውን የመለያያ ፊርማውን ሳኖር፣ ድሮ ምን ያህል እንደተሳሳትሁ ገባኝ። ያልታሰበው ሆነብኝ! ስለዚህም፣ አሁን ልከኛ ባልሆነ ዳኝነት አየተወቀስኩ፣ እየተገፋሁና ብቻዬን እንድሆን እየተገደድሁ በምኖርበት ዓለም፣ የራሴን መንገድ መፈለግ ይገባኛል አልሁ።

ከቀደመው ባለቤቴ ጋር ግንኙነት ያቆምሁበት የመጀመሪያዎቹ ወቅቶች እጅግ ከባድ ነበሩ። እዚያ መካከል ለእኔ የሚሆን ቦታ እንደማይኖር ሳስብ፣ ከክርስቲያን ማኅበረ ሰቡ መካከል ሸሽቶ መጥፋት ያምረኛል። ሰዎች በእኔ ትዳር መፍረስ ጕዳይ ሊያወሩ የሚችሉትን ሳስብና ግምታቸውን ስጠረጥር፣ ብቻዬን መሸማቀቅ እጀምራለኹ። ፍቺ እንደፈጸምኩ ለሚያውቁ ሰዎች ሁሉ፣ ራሴን ብዙ ማብራራትና ልክ እንደሆንሁ እንዲያውቁልኝ መድከም እፈልግ ነበረ።

ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ፍቺ ሊፈጽሙ ይችላሉ። አንዳንዶች ክፉዎችና ራስ ወዳዶች ስለ ሆኑ ሲሆን፣ አንዳንዶች ደግሞ ታማኝነት የጎደላቸውና የትዳር አጋሮቻቸውን የሚያሰቃዩ በመሆናቸው ምክንያት ነው። በርግጥ ለማብራራት በሚከብዱና አስቸጋሪ በሆኑ ምክንያቶችም ጭምር ፍቺ ሊፈጸም ይችላል።

ምክንያቱ ምንም ይኹን ምን፣ እኛ በክርስቶስ ያለን፣ ጸጋንና ምሕረትን ወደምናገኝበት ጌታ በድፍረት መሄድ እንችላለን (ዕብ 4፥12)። ጌታ ልባችንን ያውቃል፤ በኅጢያት ሲወቅሰን፣ መናዘዝ እንችላለን። እርሱም ኀጢያታችንን ይቅር ይለናል፤ ከበደል ኹሉም ያነጻናል (1ዮሐ 1፥9)።

ኀፍረት ሲሰነብትስ?

ልባችን ንጹሕ ከሆነ በኋላ እንኳን፣ ኀፍረት ከፍቺ ታሪካችን ጋር ተጋምዶ የቀረ ይመስላል። ሐሜት፣ ቤተኛ ሆነን ከኖርንበት ማኅበረ ሰብ ለያይቶ የሚያስቀር ነው። “ማን ምን ብሎ ሊጠይቀኝ ይችል ይሆን?”፣ “ምን ዐይነት የሚረብሹ ጥያቄዎች ይነሡ ይሆን?” የሚለው ውጥረት በራሱ ከማኅበራዊ ግንኙነቶቻችን ራሳችን እንድናርቅ አስገዳጆች ናቸው።

በዮሐንስ ወንጌል 4 ላይ የተጠቀሰችው ሳምራዊቷ ሴት ይህንኑ ስሜት ያስተናገደች ትመስላለች። በውሃ ምንጩ አጠገብ ኢየሱስን ስታገኘው እኩለ ቀን ነበረ። ከነበረው ሙቀት የተነሣ፣ በዚያ ሰዓት ውሃ ለመቅዳት ከቤቷ የምትወጣ ሴት ማግኘት እምብዛም ነው።

የሴቲቱን ሙሉ ታሪክ አናውቅም። የምናውቀው፣ ዐምስት ባሎች እንደነበሯትና አሁንም ካላገባችው ሰው ጋር ዐብራ እንደምትኖር ብቻ ነው (ዮሐ 4፥18)። በዚያ ዘመን ባሕል መሠረት፣ ወንዶች ኀያላን ስለ ነበሩ፣ ያለ ምንም ምክንያት ሚስቶቻቸውን ማንም በሌለበት ጥለዋቸው ሊሄዱ ይችላሉ። በዚህ ዐይነት ባሕል ውስጥ፣ ሳምራዊቷ ሴት ታማኝነቷን በማጉደል ቢሆን ትዳሯን ያጣችው፣ አይደለም ደጋግሞ ለማግባት ይቅርና በድንጋይ ተወግሮ ከመሞት መዳን እንኳን አትችልም ነበረ።  ምንአልባት ባሎቿ ታማኝነት የጎደላቸው ወይም ዐብረዋት ሲቆዩ የምትሰለቻቸው ይሆናል።

በተደጋጋሚ ለማግባቷ የነበራት ምክንያት ምንም ይኹን፣ በዚያን ዕለት በዚያ የውሃ ምንጭ ዳር ግን ትልቅ የኀፍረት ሸክም ዐዝላ እንደ መጣች ግን ግልጽ ነው። ነገር ግን፣ ይህቺ ሴት ኢየሱስን ካገኘችው በኋላ፣ የሕይወቷ መዘውር ተቀየረ። ወደ ማኅበረ ሰቧ ተመለሰች፤ ድብቅ የነበረው ሕይወቷ ቀርቶ፣ በታላቅ ስሜት ስለ ኢየሱስ ማውራትን ጀመረች። የዚህች ሴት ሕይወት፣ በሕይወታችን ከገጠመን ስብራት በኋላ እንዴት ወደ ፊት መራመድ እንደምንችል፣ ብዙ ታላላቅ እውነቶችን እያሳየ ያስተምረናል።

፩. ኀፍረት ከቤተ ክርስቲያን እንዲያስቀራቹ አለመፍቀድ

ከሰዎች ጋ አለመገናኘትንና ማውራት አለመቻልን እረዳለኹ። የእኔን የፍቺ ታሪክ ከማያውቁ የቤተ ክርስቲያን ጓደኞቼ ጋ መገናኘት ለእኔ በጣም ከባድ ነገር ነበረ። በሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ ለረጅም ዓመታት ያህል አስተምሬአለኹ፤ ነገር ግን ድንገት አገልግሎቴ የማይጠቅም እና ምስክርነቴም የማይጠቅም እንደ ሆነ ተሰማኝ።

ኀፍረት፣ ፋይዳ ቢሶች እንደ ሆንን እየነገረን ከግንኙነቶች ሁሉ ይለየናል። ከሌሎች ሸሽቶ አዲስ ሕይወት መጀመር ቀላል ነገር ነው። ቢንም ግን፣ በኅብረት ውስጥ ቆይቶ እግዚአብሔርን መታመን ትልቅ ፈውስ ነው። ‘ሌሎች በእኔ ጕዳይ ምን ያስቡ ይሆን?’ እያልኩ መጨነቄን ትቼ በክርስቶስ ያለኝን ማንነት መሠረቱን ማጠንከር ነበረብኝ። ከዚያም፣ ፍርሀቴን እንድጋፈጠው፣ ኀፍረቴን እንድጥልና ቀድሞ የነበሩኝን ልክ ያልሆኑ አስተሳሰቦቼን እንዳውቅ ጌታ እኔን ወደ ቃሉ በማቅረብ ረዳኝ።

በኢሳይያስ 54፥4-6 በግዞት ለነበረችው ለእስራኤል አስቀድሞ የተባለው ቃል፣ ለእኔ እንደ አዲስ ትርጕም ሰጠኝ፤ “አታፍሪምና አትፍሪ … ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፤ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር እንደ ተተወችና እንደ ተበሳጨች፣ በልጅነትዋም እንደ ተጣለች ሚስት ጠርቶሻል ይላል አምላክሽ።” እግዚአብሔር ጠራኝ፤ ሥቃዬን ተረዳኝ። ኀፍሬትን ከላዬ ላይ ገፈፈልኝ።

፪. የሕይወትን ውሃ ወደሚሰጣች አምላክ ሂዱ

ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት ውሃ ሊሰጣት እንደሚችልና፣ ደግማ እንደማትጠማ ይነግራት ነበረ። ያ ሕያው ውሃ ክርስቶስ ራሱ ነው። ቢሆንም ብዙውን ጊዜ እርሱን እየገፋን እኛው ለመቅዳት እናስባለን። በሕይወታችን ሳይታወቀን ከምናደርጋቸው አጥፊ ከሆኑ ድርጊቶች አንዱ፣ በጌታ ያለን መታመን በእኛው ጥበብ ላይ ካለን ድጋፍ በጣሙን እያነሰ ሲመጣ ነው። አዳዲስ ወዳጆችን ልናገኝ እንችላለን፤ አዳዲስ ልማዶችም ልናሳድግ ከክርስቶስ ውጪ ባለ ሕይወት ለመርካትም ልንሞክር እንችላለን፤ ዳሩ ግን፣ እንደ ተሰበረ የውሃ ጋን ነን። በጥቂቱ ጭል ጭል እያለ የሚፈስሰው ውሃ ሲያልቅ፣ ደርቀንና ተጠምተን እንቀራለን።

ከፍቺ በኋላ በተፈጠረብኝ ተስፋ ቢስ ስሜት፣ ሕይወት ዳግም ተመልሶ እንዴት መልካም ሊሆን ይችላል ብዬ ዐስብ ነበረ። ባዶ እና የደረቅሁኝ ነበርሁ። በታላቅ ጕጕት፣ በየማለዳ እየነቃሁ መጽሐፍ ቅዱሴን ማንበብና ወደ እግዚአብሔር መጮኼን ቀጠልሁ። በየዕለቱ መዝሙር 119፥25፣ “ነፍሴ ወደ ምድር ተጠጋች፤ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።” የሚለውን አነብባለሁ። ከዚያም፣ በታምራዊ መልኩ እግዚአብሔር በሕያው ውሃው ሞላኝ። ሊያፈራርሰኝ የጀመረው የሕይወቴ መንገድ አሁንም በመደነቅ በማስታውሰው መልኩ፣ መሠረቴን አጠንክሮት ዐለፈ።

፫. እግዚአብሔር ታሪካቹን ለሌሎች ትምርት ሊጠቀምበት እንደሚችል ስቡ

ብዙ ሳምራዊያን በዚያች ሴት ምስክርነት ምክንያት በኢየሱስ አመኑ (ዮሐ 4፥39)። የቀደመ ታሪኳ ያሳፍራት ይሆናል፤ የራሷን ታሪክ መስማቷ ግን ሌሎችን ወደ ክርስቶስ ለመጥራት አድርጓታል። እግዚአብሔር በሕይወታችን ያሉ ከባድ ታሪኮችን፣ እርሱ ማን መሆኑን ማሳየት ሲወድድ ለራሱ ይጠቀማል፤ ፍቺንም ጨምሮ። ፍቺን መፈጸም ማለት አገልግሎትን ማቆም ማለት አይደለም። የእኔ አገልግሎት የበለጠ ፍሬአማ የሆነው ከዚያ በኋላ ነው። ብዙ የሚደግፉኝንም ሰዎች ደግሞ ከጠበቅኩት የበለጠ አግኝቼአለሁ።

ጥንቅቅ ያለ የቤተ ሰብ ሥርዐት ያላቸውን ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስናይ፣ የእርነሱን ሕይወት እንመኛለን። እግዚአብሔርን አጥብቆ የሚታመን የተሰበረ ቤተ ሰብ ስናይ ግን አምላካቸውን ነው የምንፈልገው። ስለዚህ፣ በከሸፉ ሕልሞቻችን መካከል ያለውን የእግዚአብሔርን ታማኝነት የሚያሳየው ታሪካችን፣ ለሌሎች የምንሰጠው ትልቁ ምስክርነታችን ነው።


[1] ቬኔታ አር. ሬዝነር በስቃይ ውስጥ ስላለ ተስፋ በመጻፍና በመናገር የምትታወቅ ክርስቲያን አሜሪካዊት ጸሐፊ ናት። በተያያዥ ጕዳዮች፣ Desiring God and The Gospel Coalition በሚባሉ ክርስቲያናዊ የጽሑፍ መድረኮች ላይ ብዙ መጣጥፎችን በማቅረብ ትታወቃለች። በቅርብ የታተሙትን “Walking through fire: a memoir of loss and redemption” እና “The scars that have shaped me” የሚሉትን መጻሕፍት ጨምሮ በርካታ የጽሑፍ ሥራዎች አሏት። ይህ ጽሑፍ (When shame remains after divorce) በፈረንጆቹ መጋቢት 24፥ 2022 በጎስፕል ኮአሊሽን ላይ የቀረበ ነው።

Share this article:

አስታራቂ መሪዎች ይፈለጋሉ!

በየዕለቱ በመገናኛ ብዙኀን የምንሰማው የጦርነት እና የግጭት ወሬ የምንኖርባትን ዓለም በሰቆቃ የተሞላች አድርጓታል፡፡ ጥላቻውና በቀለኝነቱም ከቀን ወደ ቀን እያየለ የሚመጣ እንጂ የሚበርድ አይመስልም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

በሚድን በሽታ ተይዛ በሽታው እየገደላት ያለች አገር፦ኢትዮጵያ

“የሁሉንም ጆሮ ቀልብ ይዞ አንድን ዐሳብ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ማድረስ ካልተቻለ፣ እየተነጋገርን አይደለም ማለት ነው። እስካልተነጋገርን ድረስ ደግሞ መግባባት ፈጽሞ አንችልም። ካልተግባባን ደግሞ የሚድን በሽታችንን ማከም ስለማንችል፣ በሽታችን የምንኖር እስኪመስለን እያታለለን ወደ ሞት ይወስደናል። ታዲያ ምን ይሻላል?” ዘላለም እሸቴ (ዶ/ር)

ተጨማሪ ያንብቡ

4 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.