[the_ad_group id=”107″]

“መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ”

አገልጋዩ ከኢትዮጵያ ውጪ ራቅ ብሎ እንዲያገለግል ተጋብዟል። ቀኑም ደርሶ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መጋቢ ጋር ወደ አገልግሎቱ ስፍራ ሲጓዙ ድንገት ጥያቄ አነሣ፣ “ፓስተርዬ፣ የዚህቺን አገር ወይን ሳልቀምስ?” አገሪቷ ጥንታዊ ስለሆነች ወይኗ ከሚያቀርበው መልእክት በላይ አጓጉቶታል። መኪናው ቆመ፤ ወይኑ በጠርሙስ ተገዝቶ ተሰጠው፤ አላስችል ያለው አገልጋይም ለመቅዳት ሲሞክር (ከመኪናውም እንቅስቃሴ) ልብሱ ላይ ተደፋበት። ተመልሰው ወደ ማረፊያው በማቅናት ልብስ ቀይረው ጉባዔውን ተቀላቀሉ። ወይንም ለካ ከምስባክ ይዘገያል!

አንዳንዱ መድረክ የሚጠበው፣ ግርታን የሚፈጥረውና “መድረኩ ተመልካች የለውም እንዴ?” የሚያስብለው በዚህ ነው ግን አላልኩም። ገጠመኙ ግን ከመንፈስ ለማቆራኘት ለከበደን እንግዳ እንቅስቃሴና ባሕርይ ጥሩ የመላምት አማራጭ ያስቀምጣል።

እንደ ርእስ የወሰድኩት ቃል ያለው የኤፌሶን መልእክት ውስጥ ነው (5፥18)። ከፍ ብሎ ማስተዋልንና ሞኝነትን በመጥቀስ፣ ፊተኛውን እንዲሆኑ፣ ከኋለኛው ግን እንዲታቀቡ ይመክራል። በማስተዋል ላይ ደግሞ የከበረውን መንፈስ ቅዱስን እንዲጨምሩ። የዚህ ተነጻጻሪው (ተጻጻሪው) ደግሞ በሞኝነት ላይ የሚታከል የወይን ጠጅ ነው፤ በቡሃ (ገላጣ) ላይ ቆረቆር እንዲሉ።

መንፈስ (ቅዱስ) በንጽጽር ትምህርት እንዲሆን ከወይን ጠጅ ጋር ቀረበ እንጂ ሁለቱ እርስ በርስ በባሕርይ ተወራራሽ አይደሉም። ሕላዌ-እኔ ያለው የመለኮት አካልና በሰው ብልሃት የተጠመቀ መጠጥ ምንና ምን። አንዳንድ ሰዎች ግን ጉባዔ ፊት ቆመው፣ የቆሙ መስለው፣ “በመንፈስ ስከሩ” ሲሉ ይሰማሉ። በወይን ጠጅ እንጂ በመንፈስ ግን አይሰከርም፣ እንደ መጠጥ ራስ ላይ ስለማይወጣ። መጠጥ አንዴ ወደ ውስጥ ከገባ በደም ውስጥ ያለ ቁጥጥር ነው የሚሰራጨው። ይፈቅዱለታል እንጂ አያስፈቅድም። ከዚያማ ሰውየውን ስናይ፣ ʻኧረ እርሱን አይደለምʼ እንላለን። የምናውቀው ሰው የማናውቀው ማንነት ሲያሳየን መሆኑ ነው።

መንፈስ ግን እንዲህ አይደለም፤ ሲገባ ፈቅደን፣ ሲወርሰን ወድደን፣ ሲመራና ሲያስታጥቅም ልብ እያልን ነው። “መንፈስ ይሙላባችሁ” የሚለው ፈቃድ ጠያቂ ትእዛዝ የማያቋርጥ ምላሽ የሚፈልግ ነው፤ የግሱ አገባብ ቀጣይነት ያለው ስለሆነ። ክርስቲያን ለመሞላት ሊጓጓ፣ ካለ መንፈስ አብሮነትና አጋዠነትም አቅም እንደሌለው ሊያስብ ይገባዋል። ወይን መንፈስን ሊሆን ቀርቶ ከወይን አልባነት እንኳ የተሻለ አይደለም። በሰውነቱ የተረጋጋና አንዳች ሞቅታ ውስጥ ያሉ ለየቅል ናቸውና።

ወይን ልብን ለተወሰነ ጊዜ ያስደስት ይሆናል፤ ይህ ደስታ ግን ቅጽበታዊና ተለዋጭ ነው፤ ቆይቶ ወደ ድባቴና ቁጭት የሚለወጥ። የማይነቁት እንቅልፍ እንደሌለ ሁሉ የማይወጡበትም ደስታ የለም፤ ችግሩ ደግሞ ሲወጡ ከገቡበት ሁኔታ በላይ የስሜት መውረድ ወይም መበረዝ መከሰቱ ነው። ወይን ወይም ሌላ ብርቱ መጠጥ ከውስጥ ሲጎድል ስሜትን ይዞ መጉደሉ አይቀርም።

የኤፌሶኑን ያደረሰን ጳውሎስ በሌላ ስፍራ “መንፈስን አታጥፉ” (1ተሰ. 5፥19) ብሏል። ሰው የሚሞላበትን ሊያጎድል፣ አልፎም ሊያከስም ይችላል ማለት ነው። የማይጎድለው ወይም የማይተካው መንፈስ ቅዱስ የሚጠፋ ማንነት የለውም። ሰው ግን አሁንም በፈቃዱ ከመንፈስ ገለል ሊል ይችላል፤ እንዲህ ሲባል ከመንፈስ ዕይታ ይወጣል ሳይሆን (“ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ?” መዝ. 139፥7) ከሕልውናው (ከጥቅሙ) ይነጠቃል ወይም ውጭ ይሆናል ማለት ነው።

በመነሻ ሐሳባችን መሠረት ጎዶሎው እንዳለ የሚተው ወይም ባዶነቱ በተገኘው ሁሉ የሚሞላ አይደለም። አንድ ብርቱ ጉዳይ ግን ሊያሳስብ ይችላል፤ በወይን ለመሞላት ቅድመ ሁኔታ የለም። ፈሳሽን በተገኘው ውስጥ እንደሚጨምሩ ሁሉ ወይንም በተከፈተው ጉሮሮ ሁሉ ይንቆረቆራል፤ በመጀመሪያ ተፈቅዶለት፣ ቀጥሎ ቀድሞ በገባው ፈቃድ። መንፈስ ግን እንደ ማንነቱ ነው የሚንቀሳቀሰው፤ ቅዱስ ስለሆነ ንፁሕ ነገር ይወዳል። የጎደፈ ቤት አይመቸውም፤ ጥዩፍ (ተጠያፊ) ግን አይደለም፤ ገብቶ የሚያጠራና የሚቀድስ እንጂ!

መምረጥ እንግዲህ የክርስቲያን ፈንታ ነው፤ ቀላሉን ሞልቶ የሚያቀለውን ወይም ብርቱውን ገብቶም የሚያበረታውን። መንፈስ ቅዱስ በገባበት ሁሉ ፍሬ ይከተላል፤ የመንፈስ ፍሬ። ከእነዚህ ዘጠኝ እንደሆኑ ከተገለጹት መካከልም አንዱ ራስን መግዛት ነው፤ ራስን በመግዛት ውስጥ ደግሞ ስሜት በዓላማ ሥር ሲገባ ንግግርም ሆነ እንቅስቃሴ የተመጠነ፣ የተለካና የተቀመመ ይሆናል።

ራስን መግዛትን ያህል ቅርብ፣ ደግሞም ከባድ ነገር የለም። ሌላ ኀይል ያስፈለገንም ለዚሁ ነው። እንግዲህ ለስክነት፣ እርጋታና ከፍተኛ ውጤታማነት በመጣ መንፈስ እንዴት ተደርጎ ነው “የሚሰከረው”? የሰከረ ኀፍረት የለውም፤ የተሞላ ግን ዙሪያ ገባውን ልብ ይላል፤ የሰከረ ጸንቶ አይቆምም፣ ተወዛዋዠ ነው፤ የተሞላ ግን መሬት ይይዛል፣ ጽኑ ነው። የሰከረ አይበረክትም፤ የተሞላ ግን ያበረክታል። የሰከረ በፈቃዱ ላይ ገዢ አይደለም፤ የተሞላ ግን በፈቃዱ ላይ አዛዠ ነው። የሰከረ ኀይል የከዳው ነው፤ የተሞላ ግን ጉልበታም።

አንዱን ልቀቁ ሌላውን ያዙ፤ የያዛችሁትን ደግሞ ከልብ ያዙ፤ በልብ ያዙ። መንፈሱን የሰጠን አምላክ ከመንፈሱ ጋር ሌላውንም ሰጥቶናል፤ በመንፈሱ የሚጠበቅ ስጦታ። ደስታ ሩቅ፣ ብርቅም ነው። በመንፈስ ለሚሞሉ ግን ደስታ ከውስጥ ይፈልቃል። እነዚህም ደስታ ፍለጋ ሲማስኑ፣ ተቅበዝብዘው በዚያው የሚጠፉ አይደሉም። የረሰረሱ፣ በሐሴት የተሞሉ፣ ሁልጊዜም የሚያመሰግኑ እንጂ! 

ልቤን መንፈስ ሞላው አእምሮዬ በራ
ሩጥ ሩጥ አለኝ በከፍታው ስፍራ።

በሚድን በሽታ ተይዛ በሽታው እየገደላት ያለች አገር፦ኢትዮጵያ

“የሁሉንም ጆሮ ቀልብ ይዞ አንድን ዐሳብ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ማድረስ ካልተቻለ፣ እየተነጋገርን አይደለም ማለት ነው። እስካልተነጋገርን ድረስ ደግሞ መግባባት ፈጽሞ አንችልም። ካልተግባባን ደግሞ የሚድን በሽታችንን ማከም ስለማንችል፣ በሽታችን የምንኖር እስኪመስለን እያታለለን ወደ ሞት ይወስደናል። ታዲያ ምን ይሻላል?” ዘላለም እሸቴ (ዶ/ር)

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.