
ኢየሱስ? ወይስ ሞት?
“በኢየሱስ የሆንን እኛ በሕይወት ነን፤ ማንም እርሱን በሕይወትነቱ ቢያውቀው በሕይወት ይኖራል። ሊያውቀው ባይወድድ ግን በሞት ይቀራል፤ መጨረሻውም ለዘላለም ከእግዚአብሔር የመለየት ቅጣት ይሆናል።” ዘሪቱ ከበደ
[the_ad_group id=”107″]
ፍሬውን በቃሉ አርቆ ሲያሳያት
ሔዋን ተጠንቅቃ “አትንኩት” ብላ አለች፤
ቆይቶ ባሳቹ ደምቆ ሲገዝፍባት
በምኞት አንሥታ በጉጉት ወደቀች።
በዔድን የነበረው ሕይወት “መልካም” እጅግ ያማረም ነበር። ከምድር ዐፈር የተበጀው ሰው በዚህ ውብ ስፍራ ተቀመጠ፤ እንዲኖር፣ እንዲያለማ፣ እንዲንከባከብም። በዚያ የነበረው ዛፍ ሁሉ “የሚያስደስት ለመብልም መልካም” ነበር (ዘፍ 2፥9)። ሕይወት አካላዊ (ውጪአዊ) ብቻ ስላይደለ ከመኖርና ከመደሰት ያለፈ ደርዝ አለው፤ ነፍሳዊ፣ መንፈሳዊ ገጽታ። ይህም ደግሞ የተሟላ እንዲሆን በሚታየውና በሚበላው መካከል ምጡቅና ረቂቅ የሆነው አምላክ እንዲታሰብ፣ እንዲከበርም ታሰበ።
በዚህ ውብና ዐዲስ ጅማሬ መካከል የአምላክና የሰውን ግንኙነት የሚጠብቅ፣ የሚያስቀጥልም ሚዛን ተቀመጠ፤ “በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ።” እነዚህ ሁለት ዛፎች ሕይወት ከሚታየውና ከሚስበው፣ ከሚዳሰሰውና ከሚቀመሰው በላይ የከበረና የገዘፈ ለመሆኑ ማስረጃ ናቸው። ነገሩ ሁሉ ከመብቀል ስለ ነበር፣ ሰውም ከዐፈር እንደ በቀለ ልብ ይሏል፤ የእግዚአብሔርንና የሰውን ግንኙነት የሚያንጸባርቁ አላባውያንም (ነገሮች) መሬት ላይ ያረፉ ወይም የተተከሉ ነበሩ። አዳም ከሌላው እየበላ፣ ሔዋንም እንዲሁ እየረካች፣ የተከለከለው ዛፍ ጋር ሲደርሱ ደግሞ ይበልጥ ቀና ይላሉ፤ ከፍሬው በላይ እግዚአብሔርን እያሰቡ።
“ያንን ዛፍ ግን እግዚአብሔር ለምን አስቀመጠ?” የሚለው ጥያቄ በአማኙም ሆነ በተጠራጣሪው አእምሮ ሲያስተጋባ አልፎም ጆሮ ሲደርስ ኖሯል፤ ዛሬም ይህ ጥያቄ እየተጠየቀ ነው። “እውነት ለምን?” ብትሉም ይህንን በጥበብ አትጠይቁም አትባሉም።
ʻዛፉ ባይኖር ዐመፅ አይመጣም ነበርʼ ብሎ ማለት ግን ነገሩን ከጥልቁ አለማንሣት ይሆናል። ሰይጣን ቀድሞ መልአክ ወይም የሚጋርድ ኪሩብ ነበር። በተገኘበት ዐመፃ ግን ወደቀ። ምኞቱ በውስጡ ሲጠነሰስና ዙፋኑን “ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ አደርጋለሁ” እንዲሁም “ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ” ሲል ፍሬ በልቶ ወይም ሌላ ትእዛዝ ተላልፎ አይደለም (ኢሳ 14፥13- 14)። ክፋት እስኪገኝበት ድረስ ያለ ነቀፌታ ነበር (ሕዝ 28፥15)። ውሸትን ለማመንጨት የመጀመሪያ እንደ ሆነ ዐመፅንም ለማመንጨት የመጀመሪያ ሆነ። እንግዲህ ለማመፅ የዛፍ መኖር አስገዳጅ አይደለም።
ወደ ሔዋን ፈተና መለስ ስንል፣ ችግሩ ከዛፉ ሳይሆን ከምኞቱና እንደ እግዚአብሔር ለመሆን ከመከጀሉ ላይ ነበር። ሰይጣን በተፈተነበት ፈተና (እንደ እግዚአብሔር መሆን) ሰውን ፈተነ፤ እርሱ በክፉ ስለሚፈተን ሌላውንም እንዲሁ ይፈትናል (ከያዕ 1፥13 ጋር ያነ.)። በመልካምና ደስ በሚያሰኝ ዛፍ መካከል እየኖሩና ሁሉንም መብላት እየቻሉ፣ አንዱን ብቻ መከልከል የሰጪውን ደግነት እንጂ ንፉግነት ጨርሶ አያሳይም። ሁሉን ሰጥቶ፣ አንዱን ከልክሎ ቢሉ፣ ለሁሉ አመስግኖ፣ ለአንዱ ተጠንቅቆ ነው ምላሹ።
ብቻውን የበላ፣ ብቻውን ይሞታል እንዲሉ፣ ሔዋን “ከእርሷ ጋር ለነበረው” ባሏ ሰጠችው፤ “እርሱም በላ”። ዓይናቸው ቢከፈትም፣ ዕይታቸው ከፍ አላለም፤ የተመኙትም አልሆነም፤ “ዕራቁታቸውን መሆናቸውን” አወቁ እንጂ። ርግጥ ነው እግዚአብሔር ያወቀውን አውቀዋል፤ ግን ኀፍረት ባጠላበት ድባብ ዕራቁትነትን መገንዘብ፣ ከዚያም እግዚአብሔርን ፈርቶ ወይም አፍሮ መሸሸግ።
እግዚአብሔርን ታዝዘው፣ ዛፉን ገሸሽ አድርገው ቢሆን ኖሮ፣ ስንቱን ጥቅም በተጋሩት። የማይበላውን ሲበሉ የሚበላውን ተከለከሉ፤ ከዔድን ተባርረዋልና። ሰው የተከለከለውን ሲፈቅድ፣ የተፈቀደለትን ይከለከላል፤ መለኮታዊው ስሌት እንደዚሁ ነው። ያለማ ልጅ ጎሽ ተብሎ እንደሚዳበስ፣ ያጠፋውም በዚያው እጅ እንደሚቀጣ፣ እሺ ብሎ ያረፈ አተረፈ፤ ʻካልነካሁ፣ ካልቀመስኩʼ ያለ ደግሞ ከሰረ፤ ያውም ውድ ኪሳራ።
የገነቱ ዛፍ በራሱ መርዝ አይደለም፤ ዐላማ ይዞ ስለ ተተከለ ግን ገዳይ ሆነ። የሞቱት በፍሬው መዘዝ ሳይሆን፣ ባለመታዘዝ ጠንቅ ነው። ለመብል የሆነ ፍሬ ዓይን አይከፍትም ወይም አይዘጋም። በልተውም በአካል አልወደቁም፤ እንደውም ድምፅ ሰምተው እስኪሸሸጉ ድረስ በአካላቸው እንደ ወትሮው ብርቱ ሆኑ እንጂ። ስለዚህ የሞቱት በውስጡ ማንነታቸው ነበር።
የ“አትብሉ-ብሉ” እውነታ ዛሬም አለ። አንዱ ፍሬ ብዙ ሆኖ፣ የተከለከሉና ገዳይ የሆኑ ነገሮች በዝተዋል። ለአዳም አንድ ትእዛዝ የሰጠ ለሙሴ 10፣ ለእስራኤልም 613 ሰጠ። በዐዲስ ኪዳን ላለን ደግሞ ትእዛዛቱ ጸጋ ለተሰጠው ማንነት በሚመጥን ሁኔታ ጠብቀዋል፤ እንዲህ “እንደ ተባለ ሰምታችኋል … እኔ ግን እላችኋለሁ …” እየተባለ። እንደውም “በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኀጢአት ነው” ተብሎ ተጽፏልም (ሮሜ 14፥23)።
ትእዛዝ በዛ የሚል ይኖር ይሆን? ጸጋስ የተትረፈረፈው፣ መንፈሱስ፣ የእግዚአብሔርስ ኀልዎት (መገኘት)፣ የእርሱ ቤተ መቅደስ መሆን፣ የአማኞች ሁሉ ክህነት፣ የመንግሥቱ ዜግነት፣ በሰማይ የተጠበቀው ተስፋ፣ ሌላም፤ እነዚህ ሁሉ ከምሕረቱና ከበጎነቱ የተቀዱና የተቸሩን ናቸው።
እንግዲህ “ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ” ኑሩ። “አትብላ” ያለ እርሱ የሕይወት እንጀራ ሆኖልናል!
Share this article:
“በኢየሱስ የሆንን እኛ በሕይወት ነን፤ ማንም እርሱን በሕይወትነቱ ቢያውቀው በሕይወት ይኖራል። ሊያውቀው ባይወድድ ግን በሞት ይቀራል፤ መጨረሻውም ለዘላለም ከእግዚአብሔር የመለየት ቅጣት ይሆናል።” ዘሪቱ ከበደ
ንጉሤ ቡልቻ በዚህ ጽሑፋቸው፣ ምስቅልቅል ለበዛበት የአማኞች አምልኳዊ ገቢር መፍትሔ እንዲመጣ፣ “የልየታ መንፈስ” ይፈስስ ዘንድ ለአምላክ ተማጽኖ፣ ለምእመናንም ምክሮች ይለግሳሉ።
“በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርስ አንተን ካገኘሁ ምን እሻለሁ?” (መዝ. 73፥25)
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment