[the_ad_group id=”107″]

“በዚያ ያለውን እንድታደራጅ ተውሁህ!”

ይህ ጽሑፍ እንደ ግል ምስክርነት ወይም የግል ገጠመኝን እንደማካፈል ሊወሰድ ይቻላል። ከቅምጥ የሚያስነሣ ታሪክ ወይም ታምር የታጨቀበት ወይም የነገረ መለኮት ብስለት የጐበኘው ባለመሆኑ ከማንበብ አትከልከሉብኝ።

እኔና ቤቴ ከአገራችን ኢትዮጵያ ወጥተን ስለ መኖራችን አስቀድመን ያሰብንበት ጕዳይ አልነበረም። ከብዙ የዐሳብ መዋለልና ማመንታት በኋላ፣ በኢትዮጵያ ለዓመታት ስናበጃጅ የነበርነውን ኑሮ ሁሉ ርግፍ አድርገን ትተን፣ በምድረ አሜሪካ መኖርን ቆረጥን። በአሜሪካ አገር ቀርተን ለመኖር የተወሳሰበ ጕዳይ ሆኖብን ነበር። እግዚአብሔር ባይረዳን ኖሮ አይከናወንልንም ነበር ብለን አምነናል። በርግጥ ነገሮችን በማገጣጠሙ/በማሰካካቱ ወደር የማይገኝለትን የባለቤቴን ትጋትና ጥንካሬ፣ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የተስማሙ በርካታ ነጭ ክርስቲያኖችን ሳላደንቅ ማለፍ አልችልም።

የእነርሱን ጕዳይ እዚህ ላይ መሸንቀሬ ስለ አርካንሳ[1] ነጭ ክርስቲያኖች ቀድሞ የሰማሁት ዘረኝነት በእኛ ላይ ያልደረሰብን[2] መሆኑን ጠቅሼ ለማለፍ ነው። የረዱን ዝርዝራቸው በርካታ ስለ ሆነ፣ ፈቃዳቸውንም ስላልጠየቅሁ ስማቸውን ለመጥቀስ አይመቸኝም። ስለተወሳሰበው ጕዳያችንም አልጽፍም። በጥቅሉ ግን በዚህ አጋጣሚ ከአገር ቤት ከመነሣታችን አንሥቶ በአሜሪካን አገር፣ አርካንሳ ግዛት እስከተደላደልነበት ጊዜ ድረስ፣ በእኛ ጕዳይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያደረጉትን (ኢትዮጵያውያንንም ሆኑ፣ አማሪካውያንን) ሁሉ ሆድ ይመርቅ ብዬአለሁ። አሁን ይህን ሳስታውስ እንባ ተናንቆኛል።

በኋላ ላይ ጥቂት ከማይባሉ ጥቁር አሜሪካውያንም ጋር በሥራ ምክንያት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሴት ልጆችን ያገቡትን ተዋውቄአለሁ፤ ዐብሬ ከሠራኋቸው አለቆቼ የነበሩም አሉባቸው። ሁሉም ጥሩ ሰዎች ሆነው ነው ያገኘኋቸው።


ወደ ተነሣሁበት ነገር ልመለስና፣ በአሜሪካ ኑሯችን በአራተኛው ዓመት ላይ፣ “የቀረውን እንድታደራጅ በዚያ ተውሁህ” የሚል ዐሳብ በድንገት በአእምሮዬ ታሰበ። ከዚያን ጊዜ አንሥቶ፣ ለሁለት ዓመታት ያህል የሚለቅቀኝ ዐሳብ አልሆነም። ዐሳቡ እንዲህ ሲጠናብኝ ከእግዚአብሔር የመጣ መልእክት አድርጌ ወሰድሁት። ይሁን እንጂ፣ ‘እነማንን? ለምን ዐላማ? እንዴት?’ ለሚለው ምንም ፍንጭ አልነበረኝም።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ “በዚያ” የሚለው ቃል ግራ የሚያጋባኝ ሆነ። በምንኖርበት ከተማ ወይም ክፍለ አገር ነው እንዳልል፣ በዚያ ኢትዮጵያውያን አሉ ማለት አይቻልም ነበር። እንደ ሰማሁት በተራራቁ ከተሞች ተበታትነው የሚገኙ ስምንት ብቻ ነበሩ። ከእነዚህ አራቱን በተለያዩ ጊዜያት በአካል አግኝቼአቸዋለሁ። የተቀሩትን ግን፣ በስልክም እንኳ የማገኛቸው አልሆኑም። ይህ ሊሆን ባለመቻሉ በቅርብ ርቀት በሚገኝ የአጎራባች ክፍለ አገር ከተማ ያሉትን ወንጌላውያንን ማደራጀት መሆን አለበት ብዬ አመንኩ። ይህን የሚያሟላው ደግሞ የቴነሲው ሜምፊስ[3] ነበር። ይሁን እንጂ፣ በዚያ ከተማ ወንጌላውያን አማኞች መኖራቸውንም ሆነ፣ መደራጀት የሚያስፈልጋቸው መሆኑንም አላውቅም ነበር። በአሜሪካ ገጠር ከተማ እንደሚኖር ሰው ትልቅ በሆነው በሜምፊስ ከተማ ያለ እገዛ ካርታ እያነበብኩ ተንቀሳቅሶ ማፈላለጉ ቀላል አልሆነልኝም። ያን ጊዜ፣ ከMapquest ካርታ አትመን፣ በዚያ አቅጣጫችንን እያወቅን ነበር የምንነዳው። የጉግል አሰሳም አልተስፋፋም ነበር፤ ቶም ቶም (GPS)ም ለዚያን ጊዜ አልደረሰልንም። ዐብሮኝ የሚነዳ ባገኘሁ ቍጥር ከከሸፉብኝ ጥቂት የማፈላለግ ሙከራዎች በኋላ፣ የሰብሳቢያቸውን ሰው ስልክ ቍጥር ካልጠብቅኩት ሰው አገኘሁ። ጊዜም አላጠፋሁ! በቀጠሯችን ዕለት ከእኔና ቤቴ ጋር ይኖር ከነበረ የወንድሜ ልጅ ጋር ከአርካንሳ ተነሥተን በዚያ በተመቸ ጎዳና ላይ ፈጥነን ከቀጠሮ ሰዓታችን በፊት ደረስን። ከተማው በአሜሪካ አነዳድ በመኪና ከሁለት ሰዓት ተክሉ የማይበልጥ ጕዞ ርቀት ላይ ነበረ። ከተለያየ ቤተ እምነት የተገኙ፣ የተለያየ ዳራ የነበራቸው፣ ለመደራጀት በሂደት ላይ የነበሩ ሆነው አገኘናቸው።

ኢንተር ዲኖሚኔሺናል ቤተ ክርስቲያን

ቀጥተኛ አደራጁ ባልሆንም፣ ከሜምፊሶቹ ጋር ስለመደራጀታቸው ዐብሬአቸው መከርሁ፤ ዘከርሁ። ቤተ ክርስቲያኒቷን ኢንተርዲኖሚኔሺናል አድርገው ስለሚያደራጁበት ምክረ ዐሳብ አቀረብሁ። ከተለያየ ቤተ እምነት የመጡትን ኅብረታቸውን የሚያሳምርና ክርስቶስን በአንድ ድምፅ ለመመስከር የሚያስችል አርአያ (ሞዴል) አደረጃጀት ነበር። እርስ በእርስ ከመጋጨት ይጠብቃል፣ ሰሚዎችንም በተለያየ ድምፅ ከማደናገር ያተርፋል። ይህን አደረጃጀት ያወቅሁት ቀደም ሲል በክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት አገልግሎት[4] በመሳተፌ ነበር። ቈይቶም የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በሰሜን አሜሪካ (EECF) ጋር እንዲገናኙ አስተዋወቅኋቸው። ከዚያ በኋላ የደረሱበትን መተረኩን ለእነርሱ እተዋለሁ። ይህን በማድረጌ  ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ያመንኩትን ያንን ድምፅ እንደታዘዝኩ ተሰማኝ። ለስድስት ዓመታት ያህል በየሁለት ሳምንቱ እሑድ መመላለሴ ቀርቶ አሁን ሜምፊስን የምጎበኘው ዐልፎ ዐልፎ ሆኗል። መንዳቱ ደከመኛ።

ለመደጋገፍ ማደራጀት (ኦርቶዶክሳውያንና ወንጌላውያንን)

ከሜምፊስ ወገኖቼ ጋር ቤተ ክርስቲያንን ስለማደራጀቱ እየመከርሁና እየሠራሁ ሳለ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስታውሱኝ ሁለት ነገሮች አጋጠሙኝ። አዎ፤ የሜምፊሶቹ ወንድሞችና እኅቶች በአንድነት ተቀመጡ፤ የሚያስተባብራቸውም የሚመራቸውም ሰው አለ። ነገር ግን፣ ለመሪዎችና ለተቀሩት አገልጋዮች ማን ሹመትን ይስጥ? ማን ይቀባቸው? መንፈሳዊ ሥልጣን ያለውን ቀቢ ለማመልከት ተቸገርሁ። ቀድሞ እንደማውቀው፣ ሚሲዮናውያንን (ወንጌላውያንን) ያሰማራች ቤተ ክርስቲያን ስትኖር፣ ያቺው ቤተ ክርስቲያን ትሾማለች፣ ትቀባለች። እነዚህን ማኅበርተኞች ግን ማንም አልተከላቸውም። ከተለያየ ቤተ እምነት በየራሳቸው የተለያየ ሁኔታ ዐልፈው የተገናኙ ናቸው። ስለዚህ ማነው ሊሾምላቸው የሚችለው? በዚህ በኩል ፈራ ተባ አልኩ። አሁን እንዴት እንደ ሆነ በማላስታውሰው ሁኔታ እንዳውም ዐሳቤ ነጉዶ፣ ወደ ኋላ የፕሮቴስታንቶች ታሪክ ላይ ወሰደኝ።

ሉተር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከተወገዘና ከተለየ በኋላ ክህነቱ የጸና ኖሯል ወይ? የክህነት ሥልጣኑ የተሻረ ከነበረስ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን በምን ቤተ ክርስቲያናዊ ሥልጣን ቀጠለች? ካልቪን ጭራሽኑ ክህነትን ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዳላገኘ ይነገራል[5]። ክህነትን ያላገኘ ከነበረስ፣ የፕሬስቤቲሪያን ቤተ ክርስቲያን አገልጋዩች በምን ቤተ ክርስቲያናዊ ሥልጣን ተሾሙ? የሚል ጥያቄ ተጫረብኝ። መልሱ አላስጨነቀኝም፤ መልስ ፍለጋም አልሞከርኩም። መልስ አይኖረውም ብዬም አላሰብኩም። ነገር ግን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበራትን ግንኙነት ፊቴ ላይ ደቀነብኝ። የራሷን ፓትረያርክ መሾም እንድትችል ትፈልግ ነበርና ለዚህ ውጣ ውረድን አሳልፋለች። ምን ደጅ አስጠናት? ኮሚቴ ወይም ኮሚሺን አቋቁማ ያ አካል ሊሾምላት አይችልም ኖሯል? በተለይም በጊዜው በአገር ውስጥ ጠንካራ የፖለቲካ ድጋፍ እየነበራት፣ ያ ሁሉ ድርድርና ጊዜ ማባከን ለምን አስፈለጋት? ንጉሠ ነገሥቱም በቀጥታ ራሳቸው ስለ ምን አልሰየሙም? ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የቤተ ክርስቲያን ሥልጣንን የማውረስ ሥርዐትን ላለመስበር ነው ወይስ ቢደረግም መንፈሳዊ ሥልጣኑ የማይዝ ይሆናል ብሎ (null and void እንዲሉ) በመሥጋት? ኦርቶዶክስን ያስታወሰኝ የመጀመሪያው ገጠመኝ ይህ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ በዚያው በሜምፊስ ኅብረት ከወገኖች ጋር ለማምለክ እየተመላለስኩ ሳለሁ በጅማ ስደት መነሣቱ ነው። “ከአሰንዳቦ/ጅማ ዞን በርካታ የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያኖች ተቃጠሉ፣ በሺሕዎች ተሰደዱ። አንድ የኦርቶዶክስ ክርስቲያንም ተገደለ”[6]። ይህ በወቅቱ ያነበብሁት መረጃ ነበር። ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ስደት በግል እንዳጠና ያደረገኝ ከመሆኑም በላይ፣ ስለ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዳስብ ሌላ ምክንያት ሆነኝ።

ነገሩ እንደዚህ ነው፦ ለተሰደዱት ዕርዳታ እንድናደርግ ተጠየቅን። ይሁን እንጂ፣ እኔ በሰማሁት የዕርዳታ ጥያቄ ማስታወቂያ ስለ ተሠዋው ኦርቶዶክስ ያነሣ፣ የተነፈሰ አልነበረም። የሚመለከተው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያንን ነው ተብሎ ወይም የአንድ ሰው ጕዳይ ክብደት ሳይሰጠው ቀርቶ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም፣ ጨርሶ አለመነሣቱ ለምን ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። የኦርቶዶክሱ ምዕመን ለመሞቱ ምክንያቱ ከወንጌላውያኑ ጋር መገኘቱ ስለ መሰለኝ፣ ኀላፊነት የነበረብን አድርጌ ዐስቤአለሁና። እነዚህ ሁለት መነሻዎች የኢትዮጵያ ወንጌላውያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን የሚቀራረቡበት ግንኙነት ወይም አደረጃጀት ሊያበጁ አይገባም ወይ ወደሚል ዐሳብ አሻገረኝ።

ይህን እያሰብኩ ባለሁበት ወቅት አንዱን ቀን፣ “Comparative Theology by H.H Pope Shenouda III” መጽሐፍ አደናቀፈኝ። ለተመኘሁት ግንኙነት መንገድ ጠራጊ ይሆናል በማለት መጽሐፉን ወደ አማርኛ መለስኩት[7]። ከዚያም በኋላ መደጋገፍን የሚያበረታቱ ሌሎች ጽሑፎችንም እንደ አቅሜ በየጊዜው ሞነጫጭሪአለሁ። አሁን ላይ፣ መከራው በኦርቶዶክስ እንደበዛባት፣ አንዳንዱንም መከራ በጋራ የተቀበልነው መሆኑን ሳስተውል፣ እንዲሁም እነርሱም እኛን የሚያሳድዱበት አጋጣሚ መኖሩን ስመለከት ለመደጋገፍ ዐብሮ መደራጀቱ ሊገፋበት እንደሚገባ ታይቶኛል። ይህን ከሁለቱም ወገን ያሉቱ ዋነኞቻችን ያስቡበታል፤ ሊያንጹትም ይነሣሣሉ ብዬ ተስፋ በማድረግ ወደሚቀጥለው ዐሳቤ ልሻገር።

በባሕል ማደራጀት

በዚያው በሜምፊስ ቤተ ክርስቲያን አንዱን ሰንበት በተሰጠኝ ዕድል በሆነ ርእስ ላይ የተማርኩትን አካፈልኩኝ። በኋላ ላይ፣ ባሰፋው የማደራጃ ዐሳብ ሊወጣው እንደሚችል ታየኝ። ከአዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያና ከበርካታ የገጠር አካባቢዎች ለሥልጣን የማይፎካከረው የአገሬ ሰው (ከብዙ ብሔር ብሔረሰቦች) መፈናቀሉን እሰማም፣ ያሳስበኝም ነበርና ከዚያ ጋር ተያይዞ ነበር የታየኝ። ለዚህ መድረክ የሚስማማ መስሎ ስላልታየኝ እዚህ ላይ አላስተዋውቀውም። አደራጁ እኔ ልሆን ባልችልም፣ ጥቅም ላይ መዋል እንዲችል በሌላ መድረክ ላስተዋውቀው እጣጣራለሁ።

በጽዋ ማኅበር አርአያነት ማደራጀት

ሜምፊስ ለዐምስት ዓመታት ያህል እንደተመላለስኩ፣ እንደ እግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ውድ ባለቤቴን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን በየሙያቸው ሥራ እያገኙ በአርካንሳ ብቅ ብቅ ማለት  ጀመሩ። ከነገድና ከቋንቋ የተዋጀን ወንጌላውያንን በተመለከተ በድምሩ ወደ ዐሥራ ሁለት ያህል ቤተ ሰብ ደረስን። ሁላችንም በዋና ከተማውና በአቅራቢያው በሚገኙ ከተሞች  የምንኖር ሆንን። ኅብረት የመጀመሩን ዐሳብ ያፈለቅሁት እኔ ባልሆንም፣ ቀደም ባለው ዘመን ከአብዛኛዎቹ ጋር የምንተዋወቅ ስለ ነበርን በማገናኘቱ ተሳትፌአለሁ። ሁለቱ ከእኛ ጋር ኅብረትን ለማድረግ አልተመቻቸውም።  የተቀረነው ግን፦ በየሦስት ወሩ ተራ በደረሰለት ሰው ቤት ልንሰበሰብ፣ ተረኛ ቤተ ሰቡም ፕሮግራሙን ሙሉ ለሙሉ በኀላፊነቱ ሊያካሂድ፣ እንዲሁም ለመስተንግዶ ከሻይና ዳቦ ያለፈ ነገር እንዳይቀርብ ተስማማን።

ሦስት ወሩ ሲቃረብ፣ ከሥራ ስምሪት ጋር መሳከር ቢያጋጥም ማንም እንዳይቀር የጊዜ ሰሌዳ ማስተካከያ የሚያደርግ፣ ፕሮግራምን እየከፈተ መድረኩን ለባለ ተረኛው የሚለቅቅ፣ ተራን የሚያስጠብቅ (የሚያስታውስ) እንዲሁም ተራ መቀያየር ሲያስፈልግ ያንን የሚያሰማምር ከመኻላችን ሰው ሰየምን።

ይህን ኀላፊነት የሚወስድ ሰው በየወቅቱ የሚቀየር ነበር። ሁሉም እንደተናገሩት እጅግ የወደድነው፣ እየተነፋፈቅን የምንጠብቀውና የምንገናኝበት ፕሮግራም ሆነ። አንዳንድ በመደበኛው የቤተ ክርስቲያን አምልኮ ወይም ትምህርት የማናገኛቸውን ዐይነት ዝግጅቶች የማግኘት ዕድልም አግኝተን ነበር[8]። ሻይና ዳቦ ብቻ እንዲቀርብ የተስማማን የነበረ ቢሆንም፣ የፍቅር ብዛት ስምምነቱን ያጐበጠበት ወይም የሰበረበት አጋጣሚዎች ነበሩ።

ይህ ኅብረታችን በኦርቶዶክሳውያኑ መኻል ፍቅር በአንደበትም በሥራም የሚገለጥባቸውን የልጅነቴን የሰንበቴና የመድኃኒዓለም ጽዋ ማኅበርን አስታወሰኝ፤ ኅብረታችን ከእነርሱ ጋር ተመሳሰለብኝ። በርግጥ ልዩነቱ ግልጽ ነው። መጥቀስ ቢያስፈልግ፦

  • እኛ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ዙሪያ የተሰበሰብን ነበርን።
  • በመኻላችንም መንፈስ ቅዱስ ነበረ (በወቅቱ በጽዋ ማኅበሩ ወይም በሰንበቴው ሲጠጡ መንፈስ ቅዱስ በመኻላችን አለ ሲሉ አልሰማሁም። ለዚህ ነው በልዩነት ያሰፈረኩት። በርግጥ ጽዋውና የመሶብ ወርቁ አለ። ምን ይወከል? ምን መልእክት ያስተላልፍ? በእኛ ቋንቋ ምን ይመስክር ወይም ያውጅ አላጤንኩትም)፠
  • ጽዋ ማኅበሩ በየወሩ በየቤቱ የሚደረግ ሲሆን፣ የእኛ በየቤቱ የሚደረግ፣ በየሦስት ወሩ ሊያውም ወደ ፊትም ወደ ኋላም ሊሸጋሸግ የሚችል ነው። የሰንበቴው በየሳምንቱ ሆኖ ቆሎው፣ ዳቦውና ጠላው ቤት ተዘጋጅቶ የሚሄድ ሲሆን፣ የሚመገቡትና የሚሰበሰቡሱት ግን በቤተ ክርስቲያን ነው።
  • በተገናኘን ጊዜ ከምንጠጣው መኻል ጠላ አይገኝም[9]
  • ሌላው ልዩነት በሰንበቴውና በማኅበር ቤቱ ምጽዋት ፈላጊ ቢያንስ ለዕለቱ የሚሆነውን የሚበላና የሚጠጣ ማግኘቱ ነው። በምድረ አሜሪካ መቼም እንዲህ ዐይነት ነገር አይታሰብም። የቸርነት ሥራ የሚሠራበት የራሱ ሥርዐት ስላለው በየደጃችን የሚኮለኮል ምጽዋተኛ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። ታዲያ ምን አንድ አደረጋችሁ የተባለ እንደ ሆነ፦ ፍቅር በአንደበትና በሥራ የሚገለጥባቸው መሆኑ ነው። ሰንበቴ  ወይም ማኅበር ዐብሮ የጠጣ ሰው ሰላምተኛውን፣ የሚጨዋወተውን ሰው ያገኛል፤ በፍቅር ይተሳሰራል፤ በሥራ ይተጋገዛል፤ በኀዘን፣ በደስታ ይደራረሳል። ችግር ቢደርስ ይወያያል፤ ድጋፍ ከማኅበርተኛው ያገኛል።
  • የእኛው ፕሮግራሙን የሚቃኘው ሰው እንደ ሰንበቴውና ጽዋ ማኅበሩ “ሙሴ” ነበር ልበል?


ለማንኛውም ይህ ከመደበኛው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጎን ያለ፣ በፈቃደኝነት በሚሰበሰቡ መኻል ፍቅርን በአንደበትና በሥራ የሚገልጡበት ኅብረት ነው። የማኅበርተኞቹ ቍጥር ሲበዛ ወይም በአንድ አካባቢ በማይኖሩ ወይም እጅግም በማይተዋወቁ ሰዎች መኻል የሠመረ ላይሆን ይችላል። እጅግ ግፋ ቢል ለዐሥራ ሁለት ሰው ይሠራ ይሆናል። የሚበላው የሚጠጣውም ከሻይ ዳቦ ሲያልፍ ውሎ ዐድሮ በሀብት ልዩነት ላይ ተመሥርቶ ማሰብም ሊከተል ይችላል። በሀብታቸው ብዛት ተለይተው ማኅበርን የሚመሠርቱ ሲኖሩ፣ ከሥራቸው ዋንኛው “ከድኽነት ወለል በታች ያሉትን ስለማሳደግ” ማሰብ ሊሆን የሚገባው ይመስለኛል።

በዐሥራ ስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እነማንን? ለምን ዐላማ? እንዴት ላደራጅ ለሚለው እንቆቅልሼ መልስ ያገኘሁ እንደ ሆነ ተሰምቶኛል። ታዲያ የሚገርመው እነዚያ በአርካንሳ ኅብረት እኔና ቤቴን እየባረኩን የነበሩ ቅዱሳን ሁሉም ከጥቂት ዓመታት በኋላ በተከታታይ የተሻለ ሥራ ወዳገኙበት፣ ወደመረጡበት ከተማና አገር መሄዳቸው ነው። እኔና ቤቴ ብቻ በዚያው በአርካንሳ ቀረን። ድንገት በቅላ ጥላ እንደሆነችለትና ወዲያው ደግሞ እንደደረቀችበትና ለፀሓይ እንዳጋለጠችው የዮናሱ የቅል ቅጠል ሆነው ታዩኝ። ደግነቱ እነርሱ በመድረቅ ሳይሆን በመለምለም ነበር።ሲመጡልን ድንገት ተከታትለው ነበር። ሲለዩንም ድንገት ተከታትለው ሆነ። ዐብረውን የቈዩበት ጊዜ ዐጭር ሆኖ ተሰማኝ። ስለሆነም እኔም እንደ ዮናስ በእግዚአብሔር ላይ እስከ ሞት ድረስ መቆጣት አማረኝ፤ አዘንኩኝ።

ይሁን እንጂ፣ “አብርሃም ለልጁ ለይስሓቅ ከአገሩ ሚስትን እንዳገኘለት፣ ያንተም ሦስቱም ልጆችህ በኅብረቱ ምክንያት ከአገር ቤት ከተገኙ ቆነጃጅት ጋር ትዳር ያዙልህ። በመጨረሻም፣ በኅበረታቸው ደስ ያሰኙህን እነርሱን ለበለጠ በረከት አወጣኋቸው። ደግሞም፣ በሜምፊሱ ቤተ ክርስቲያን ምክንያት አንተንና ቤተ ሰብህን ብሎ የመጣው የወንድምህ ልጅም ከአገርህ ቆንጆ ልጅ ጋር ትዳር መያዙን አትዘንጋ! ስለ ሁሉም ይገደኛል።” ብሎ የእግዚአብሔር መንፈስ ወቀሰኝ። ይህን ያለኝ የወንድሜ ልጅ ያገባው በሜምፊስ ቤተ ክርስቲያን የተዋወቃትን ልጅ በመሆኑና  ልጆቼ  ደግሞ ያገቡት በአርካንሳው ኅበረት በነበሩ ወንድሞችና እኅቶች ዐይንና መንገድ ከፋችነት ስለ ነበር ነው።

እግዚአብሔር ተናግሮኝ ይሆን? ዳኝነቱን ለእናንተ እተዋለሁ።

ቸር ሰንብቱልኝ!


[1] ከአርካንሳ መሆኔን ስነግራቸው ሰዎች የት እንደሆነ ይጠይቁኛል።የሚያውቁልኝ የክሊንተን ስቴት ስላቸው ነው።አርካንሳ ከአሜሪካ ስቴቶች ውስጥ በከፍተኛ የሩዝ እርሻ ይታወቃል። የዋልማርት (Walmart) ዋና መሥሪያ ቤትም የሚገኘው በዚያ ነው።

[2]  ዛሬም ድረስ ጥቁሮቹ ጥቁሮች ብቻ ወደሚያመልኩበት፣ ነጮቹም ነጮች ብቻ ወደሚያመልኩበት ቤተ ክርስቲያን መሄድ ምርጫቸው ይመስላል። እንዳይደባለቁ የሚከለክላቸው ግን የለም።ዛሬ ላይ በየቀለማቸው የመሰብሰባቸው  ዋንኛው ምክንያት የሚስማማቸው ልማድ መለያየት (ሙዚቃው፣ የስብከቱ ዘይቤ  ወዘተርፈ) ሳይሆን አይቀርም። ዐልፎ ዐልፎ በአንድነት ኮንፈረንስ ያደርጋሉ። የነጮቹ ቤተ ክርስቲያን የጥቁሮቹን ቤተ ክርስቲያን መዘምራን ጨምሮ ሰባኪዎችን የሚጋብዙበት ጊዜ አለ። እኔና ቤቴ የምናመልከው በብዛት ነጮች ሆነው በሚያመልኩበት ቤተ ክርስቲያን ነው። ለእኛ ተስማምተውናል፤ እኛም ለእነርሱ ክፉ አይደለንም።

[3]  ሜምፊስ በቴነሲ ክፍለ አገር የሚገኝ፣ ለአርካንሳ ቅርብና ብዙ ሕዝብ የሚኖርበት ከተማ ነው። የጥቁሮች መብት ተሟጋች ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ የተገደለው በዚያ ነበር። ስሙ ከዓለማየሁ እሸቴ ጋር ተያይዞ የሚነሣው የዘፋኙ የኤልቪስ ፕሪስሊ ሙዚየሙም በዚያ ይገኛል። የፌዴክስ (FEDEX) ዕቃ ማመላለሽ አይሮፕላን ማዕከሉም እዚያ ነው።

[4]  ማን ምን ስለ እኔ አስረድቶ ለምርጫ እንደቀረብኩ ባላውቅም፣ የፋርማሲ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለሁ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ክርስቲያን ኅብረት (EUSCF) ለብሔራዊ ኮሚቴ ከሌሎች ሁለት ወገኖቼ ጋር ተመርጬ ነበር። በዚያ የማስተባበር አገልግሎት ላይ በመገኘቴ በመንፈሳዊ ጕዞዬ በብዙ ተጠቅሜአለሁ። እግዚብሔር በእጅጉ የተመሰገነ ይሁን! ያን ጊዜ የተዋወቅኋቸው ወንድሞችና እኅቶች በየሄድኩበት ሳገኛቸው ዛሬም ድረስ እጽናናባቸዋለሁ። ተመርቄ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በፍቅር ያገባኋት ሚስቴ፣ የዚያን ጊዜዋ ገንዘብ ያዥ ነበረች። ታዲያ የሚያዝ ገንዘብ የነበረ እንዳይመስላችሁ። ሊቀ መንበራችንን አውራ ሚዚአችን አደረግነው።

[5]https://www.newadvent.org/cathen/03195b.htm?fbclid=IwAR1fKAlRA_dqEP8y47SuD7BM8YvmHsRt6Eodi2WHSKcTUUSUMarO9VOLhj8 Calvin never was ordained in the Catholic Church; his training was chiefly in law and the humanities; he took no vows.

[6] https://www.opendoorsusa.org/take-action/pray/one-dead-as-islamist-mobs-in-ethiopia-destroy-church-buildings/ March 7, 2011

[7] ተርጓሚው እኔ ከወንጌላዊ ወገን በመሆኔ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ ምንም እንኳ መጽሐፉ የሚያስተምረው የራሳቸውን ትምህርት ቢሆንም፣   ያማከርኳቸው ኦርቶዶክሳውያን (በእርማት የረዱኝ እንዳሉ ሆኖ) በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በስፋት እንዲነበብ ድጋፍ ሊያደርጉልኝ አልመረጡም። ከእኛ ጋር እንደሚሠሩ ከሚጠረጥሯቸው ተሐድሶዎች ጋር ተደምረው እንዳይታዩ ጥንቃቄ ወይም “በጎችን አስኮብላዮች” ወይም “ዘራፊዎች” ከሚሏቸው አንዱ አድርገው ጠርጥረውኝ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱን በውል አልተረደሁትም። ጥቂት ወንጌላውያን ወዳጆቼ በአካባቢያቸው ባሉ እንዲነበብ የተቻላቸውን አድርገዋል። ከዚያ በስተቀር ጕዳዩ የእኛ አይደለም በማለት በየአቅራቢያቸው ላሉ ወንጌላውያን እንዲያዳርሱ ያስቸገርኳቸው ወዳጆቼ (ጥቂት አይደሉም) ወይ ፍላጎት አላሳዩኝም ወይም አልተሳካላቸውም። በምተረጐምበት ወቅት መንፈሳዊ በረከት አገኝበታለሁ ማለቱ ቢቀር እንኳ፣ ለዕውቀት አነብባለሁ ማለትን ድንበርን የማስከበር ፍላጎት እንቅፋት ይሆነዋል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ምንኛ ገራገር ኖሬአለሁ! ያም ቢሆን ድካሜ ከንቱ ቀረ አላልኩም።

[8] ተራው የደረሰው ቤተ ሰብ እንግዳ ሊጋብዝ ይችል ነበርና፣ በአንደኛው ቤተሰብ ተጋብዞ አንድ ወንድማችን ከሜኔሶታ በመምጣት ስለ ትዳር አስተምሮን ተመልሷል። ወንድማችን ብዙ ሊሠራና ሊያገለግል በሚችልበት የጎልማሳነት ዕድሜው ወደ ሚወደውና ወደ አገለገለው ጌታ ሄዷል። እኔና ቤቴ በመልካም ስብዕናው፣ ለቅዱሳን በነበረው ፍቅርና ርኅራሄ እንዲሁም በአገልግሎት ትጋቱ አብዝተን እናስታውሰዋለን። ያ ወንድማችን ዶ/ር ታመነ መልካሙ ( PhD) ነው።

[9] “መጠጥን በተመለከተ ኦርቶዶክሳውያኑም ቢሆኑ በዱሮ ዘመን የሚያገኙት ያልተጣራ ወይም ድፍርስ ውሃ ብቻ ቢሆንባቸው፣ በሽታ አምጪ ህዋሳት ለማስወገድ ጠላ መጠጣት ለምደው ይሆን? የፍቅራችን ጽናት በሻይና በዳቦ መወሰንን እንዳከሸፈው ሁሉ፣ የኦርቶዶክሳውያንን የጽዋ ማኅበር ድግስ መስፋቱን ከጊዜ በኋላ የፍቅራቸው ብዛት ያስከተለው ይሆን?” ብዬ ጠይቄአለሁ (ለጥያቄዬ መልስ ጥናት ያሻዋል ወይም የሚገድደው ኦርቶዶክሳዊ ያስረዳን ይሆናል)።

Bantu Gebremariam

ባንቲ ገብረ ማርያም በፋርማሲ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በፋርማኮሎጂ የማስተርስ ዲግሪ እንዲሁም በቢብሊካል ካውንስሊንግ ማስተርስ ዲፕሎማ የሠሩ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም “Comparative Theology” - “የነገረ መለኮት ንጽጽር” በሚል እንዲሁም “Forgiveness to Let Go” - “ይቅር ማለት- ለመተው ነጻነት” የተሰኙ መጻሕፍትን ወደ አማርኛ መልሰዋል። E-mail: bantge@yahoo.com

Share this article:

ዊክሊፍ:- የታላቁ ለውጥ አጥቢያ ኮከብ

የፕሮቴስታንት ተሓድሶ በሚታወስበት በዚህ ሰሞን፣ ለማርቲን ሉተርና ለሌሎቹ ተሓድሷውያን ነገረ መለኮታዊ መደላድል አስቀድሞ ሠርቶ አልፏል ስለሚባልለት ጆን ዊክሊፍ እንድናስታውስ፣ ፍቅረየሱስ ሁንዴሳ ይህን ዝክር እንደሚከተለው ያስነብበናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ኢየሱስ ይልቃል

“ኢየሱስ ይልቃል” የተሰኘው ይህ ጽሑፍ በዕብራውያን መልእክት ላይ መሠረቱን ያደረገ ሲሆን፣ የመልእክቱ ማጠንጠኛ “በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” በሚለው ሐሳብ ላይ የሚመሠረት መሆኑን ጸሐፊው ሳምሶን ጥላሁን በሚከተለው ፍታቴው ያስቃኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Pluralism: The Culture of Democracy

In this article, Andrew DeCort (Dr.) argues that pluralism is vital if democracy should take the floor, in societies such as ours. He even says: “Advocating democracy without pluralism is like advocating fish without water. The one cannot live without the other.”

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.