[the_ad_group id=”107″]

የበዓለ ጥምቀት አከባበር በግብጽና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት

ይህ ዐምድ በተቻለ መጠን ሆሄያትን (ፊደላትን) እንደ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላትና የግእዝ ቍጥሮችን ይጠቀማል።


መነሻ

በዓለ ጥምቀትን የተመለከተ ጽሑፍ ለማዘጋጀት በማሰብ ላይ ነበርኹ። ከጕዳዩ ጋር በተያያዘ ሳይኾን በአጋጣሚ እጄን ወደ መጻሕፍት መደርደሪያዬ ሰደድኹና ከጥንታውያን መጻሕፍት መካከል አንዱን ስቤ አወጣኹ። መጽሐፉ በ፲፱፻፵፫ ዓ.ም. የታተመና “ሢመተ ሊቀ ጳጳሳት ኢትዮጵያዊ በመዋዕሊሁ ለቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” የሚል ነው። ለጊዜው መጽሐፉን ለምን እንዳወጣኹት ግልጥ ባይኾንልኝም፥ ገለጥ ሳደርገው ገጽ ፳፪ “በዓለ ጥምቀት” በሚለው ርእስ ላይ ዐይኖቼ ዐረፉ። ወዲያው በዚህ ርእስ ሥር የተጻፉትን ፯ መሥመሮች አነበብኹ። ከዚህ ቀደም ነገሩ እንዲህ መኾኑን ሰምቼም አንብቤም ስለማላውቅ ጽሑፉ አስገረመኝ። እጽፍበት ዘንድም ግድ አለኝ። (በቅድሚያ ግን ይህ አጋጣሚ እውነተኛ እንጂ ልቦለድ አለመኾኑን ለአንባቢው ሳስገነዝብ በምሪት የተጻፈ ጽሑፍ ነው ለማለት ዳድቶኝ አለመኾኑን ግን በትሕትና ለመግለጥ እወዳለኹ)።

ጽሑፉ እንዲህ ይላል፦ “የጥምቀት በዓል በግብጽውያን ልማድ እንዴት እንደሚከበር ለማየት በጣም ጓግተንለት ነበር፤ ዳሩ ግን እንዳሰብነው ያኽል ሊኾን አልቻለም። ቅዳሴው በሌሊት ከመኾኑ በቀር ከዘወትሩ የእሑድ ዕለት የተለወጠ ሥነ በዓል የለበትም። ኀሙስ ማታ ደወል ተደውሎ ካህናቱ ተሰበሰቡ፤ ከሕዝቡም ለጸሎት የመጣ ነበር። ከማታው እስከ ፪ ሰዓት ድረስ የበዓሉ ጸሎት በውሃው ላይ በዜማና በንባብ ተደርጎ ውሃውን በሕዝቡ ላይ ረጩት፤ ከዚያም በኋላ ቅዳሴ ገቡና ከሌሊቱ በ፭ ሰዓት ተኩል ከቅዳሴ ወጡ። ቀጥሎም ሠርሖተ ሕዝብ ኾኖ በዓሉ ተፈጸመ።”

መጽሐፉ በግብጽ ውስጥ በወርኀ ጥር ፲፱፻፵፫ ዓ.ም. የተከናወነውን የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ በዓለ ሢመት ክንውንንና ከዚያ ጋር የተያያዙ ጕዳዮችን ዘግቦ የያዘ አነስተኛ ግን እጅግ ጠቃሚ መጽሐፍ ነው። በዚያ የሚከናወነውን የጥምቀትን በዓል ሥርዐትም ለመመልከትና ከኢትዮጵያዊው ሥርዐተ በዓል ጋር ለማነጻጸር የተቻለውም ልኡካኑ በጊዜው በዚያ ስለ ተገኙ ነው። ከኢትዮጵያ ብፁዕ አቡነ ባስልዮስን ተከትለው ወደ ግብጽ የኼዱት ልኡካን ብፁዕ ቴዎፍሎስና ክቡር ብላታ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ መኾናቸው በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቅሷል (ገጽ ፲፪)። 

ይህን በበዓለ ጥምቀት አከባበር ሥርዐት ላይ የቀረበውን አስተያየት ያነበበ ሰው የተለያዩ ስሜቶች ሊሰሙት እንደሚችሉ እሙን ነው። በአንድ ወገን የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ እናት የምትቈጠር ቤተ ክርስቲያን እንደ መኾኗ፥ በግብጽ የሌለው የጥምቀት በዓል አከባበር ሥርዐት ከየት መጣ? የሚል ጥያቄን ሲያጭር፥ በሌላ ወገን ደግሞ የአገራችን የጥምቀት በዓል አከባበር ልዩ በመኾኑ ላይ ያተኰረ አስተያየት ሊሰጥ ይችላል።

 

የተጓጓለት የግብጻውያን የጥምቀት ሥርዐተ በዓል

“የጥምቀት በዓል በግብጽውያን ልማድ እንዴት እንደሚከበር ለማየት በጣም ጓግተንለት ነበር፤ ዳሩ ግን እንዳሰብነው ያኽል ሊኾን አልቻለም።” ነው ያሉት በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታደሙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልኡካን። ልኡካኑ ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ በጣም የጓጕት ለምን ይኾን? በኹለቱ እኅት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የበዓሉን አከባበር ተመሳስሎና ተለያይቶ ለማገናዘብ ይኾናል። ምናልባትም የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ እናት የምትቈጠር በመኾኗ (ማርቆስ አባቴ እስክንድርያ እናቴ ይባልም አልነበር?!)፥ እንዴት የበዓሉ ሥርዐትና ድባብ ሊመሳሰል አልቻለም የሚለው ሳያስገርማቸው አልቀረም ይኾናል። በሌላም በኩል የሃይማኖታችን ትምህርትና ሥርዐት የተቀዳው ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከኾነ፥ የእኛው የጥምቀት በዓል አከባበር ሥርዐት ከእነርሱ እንዴት ልዩ ሊኾን ቻለ? በሚልም ሊኾን ይችላል። በዚህም ተባለ በዚያ በግብጽና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የጥምቀት አከባበር ሥርዐተ በዓል ከተመሳስሎው ይልቅ ተለያይቶው ስላየለባቸው “ዳሩ ግን እንዳሰብነው ያኽል ሊኾን አልቻለም” የሚል ትዝብታቸውን ሊያሰፍሩ ቻሉ ማለት ነው።

 

ልዩነቱ ምን ያኽል ነው?

በልኡካኑ ትዝብት መሠረት በግብጽ የተደረገው የጥምቀት በዓል አከባበር ሥርዐት ብዙም የተለየ ክሥተት አልተስተዋለበትም። እንዲያውም ቅዳሴው የተከናወነው በሌሊት ከመኾኑ በቀር ከዘወትራዊው የእሑድ ሥርዐተ ቅዳሴ የተለየ ሥነ በዓል አልታይቶበትም። በርግጥም በኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው የጥምቀት በዓል አከባበር ልዩነቱ እጅግ ሰፊ ነው። በግብጽ ሥርዐተ በዓሉ የሚከናወነው ጥር ፱ ማታ ላይ ሲኾን በኢትዮጵያ ግን ጥር ፲ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ነው።

በግብጽ በዕለቱ ማታ ላይ ደወል ተደውሎ ካህናቱ ይሰበሰባሉ። ከሕዝቡ መካከል በበዓሉ ላይ የሚታደም ይኖራል። ማታ ሲኾን እስከ ምሽቱ ፪ ሰዓት ድረስ የበዓሉ ጸሎት በውሃው ላይ በዜማና በንባብ ይጸለይና ውሃው በሕዝቡ ላይ ይረጫል። ከዚያ ቅዳሴ ይቀደስና ከሌሊቱ ፭ ሰዓት ከ፴ ሲኾን ሥርዐተ ቅዳሴው ተፈጽሞ ሠርሖተ ሕዝብ (ሕዝቡን ወደየቤቱ ማሰናበት) ኾኖ በዓሉ ፍጻሜ ያገኛል። በአጠቃላይ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የበዓለ ጥምቀት አከባበር ሥርዐት የሚወስደው ከ፭ ሰዓት ተኩል ያልበለጠ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ግን በዓለ ጥምቀት በርካታ ሰዓታትን የሚወስድና የተለያዩ ክንውኖች የሚካሄዱበት ነው። ከዋዜማው ዕለት አጋማሽ ጀምሮ ለዋዜማ የተዘጋጀው ያሬዳዊ ዝማሬ በመዘምራን ይቀርባል። ከዚያ ታቦታት ከየደብራቸው ወጥተው፥ በመዘምራንና በሰንበት ተማሪዎች ዝማሬዎች፥ በሕዝቡ ሆታና እልልታ ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር ጕዞ ይቀጥላል። በስፍራው እንደ ተደረሰም ለዕለቱ የተዘጋጀው ሥርዐተ ጸሎት ይካኼዳል። ሌሊቱንም ሥርዐተ ማሕሌትና ሥርዐተ ቅዳሴ ይከናወናሉ። በማግሥቱ ማለዳ ላይ በተዘጋጀው ውሃ ላይ ጸሎት ከተደረገ በኋላ ሕዝቡ ይረጫል። ሌሎች መርሐ ግብሮችም ከተከናወኑ በኋላ ረፋዱ ላይ ታቦታቱ በወጡበት አኳኋን ወደየደብራቸው ይመለሳሉ። ይህ ኹሉ ሥርዐት ከ24 ሰዓት ያላነሰ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። የኢትዮጵያው ሰፊ ጊዜ የሚወስድ ብዙ ክንውኖችን የያዘ በመኾኑ ከግብጾቹ የ፭ ሰዓት ተኩል የበዓል አከባበር ሥርዐት ጋር ሲነጻጸር በርግጥም እንደ ተጠበቀው የታሰበውን ያኽል አይኾንም።

ሌላው ልዩነት በዓሉ የሚከበርበት ስፍራ ሳይኾን አይቀርም። ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ላይ ይህ ጕዳይ በውል ባይጠቀስም፥ ግብጾች በዓሉን የሚያከብሩት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኾኑ በግልጥ የሚታይ ይመስላል። ደወል ተደውሎ ካህናቱና ሕዝቡ መሰብሰባቸው ሲጠቀስ፥ የተሰበሰቡበት ቦታ ግን አልተጠቀሰም። አለመጠቀሱ ቦታው የተለየ ባለመኾኑ ወይም ቤተ ክርስቲያን ወስጥ መኾኑን የሚያሳይ ነው። የኢትዮጵያው ጥምቀት በዓል አከባበር ግን ከቤተ ክርስቲያን ተጀምሮ ወደ አደባባይ የሚወጣ፥ ከዚያ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመመለስ ፍጻሜን የሚያገኝ ቢኾንም፥ በዓልነቱ ግን የአደባባይ ነው። ልኡካኑ ይህን በአገራቸው የሚታወቀውንና ብሔራዊ በዓል ኾኖ የታወጀውን የአደባባይ በዓል፥ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተወስኖ ከዘወትራዊ ሥርዐተ ቅዳሴ ባልተለየ መልኩ ከሚከበር በዓል ጋር ሲያነጻጽሩ የታሰበውን ያኽል አለመኾኑ ቢያስገርማቸው አይደንቅም።

በጥምቀት የበዓል አከባበር ሥርዐት ላይ በኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚታየው ተመሳስሎ፣ የበዓሉ ጸሎት በውሃው ላይ በዜማና በንባብ ከደረሰ በኋላ ውሃው በሕዝቡ ላይ መረጨቱና ቅዳሴ መቀደሱ ናቸው። ይኹን እንጂ በእነዚህ ክንውኖች መኖር ተመሳስሎ ቢኖርም ቅደም ተከተሉ ግን አልተጠብቆም። በግብጽ የተጸለየበት ውሃ በሕዝቡ ላይ የሚረጨው አስቀድሞ ሲኾን፥ ቅዳሴው ይከተላል፤ በኢትዮጵያ ግን ቅዳሴው ይቀድምና በኋላ ውሃው ይረጫል።

ብዙ ልዩነቶች እንዴት ሊፈጠሩ ቻሉ? የሚለውን ጥያቄ መጽሐፉ አይመልስም። ካለው ተጨባጭ ኹኔታ በመነሣት ግን ምላሽ መስጠት የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው። ልዩነቱ ሊፈጠር የቻለበት ዋናው ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓሉን አከባበር በራሷ መንገድ ስለ ቀረጸችው ነው ቢባል ያስኼዳል። ይህን አፍ ሞልቶ ለመናገር ድፍረት የሚሰጠውም፥ የጥምቀት በዓል አከባበር ሥርዐት በሌላው የክርስቲያን ዓለም የማይታይና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ መኾኑ ነው።

 

ኢትዮጵያዊው የጥምቀት በዓል አከባበር ሥርዐት መቼ ተጀመረ?

በ፪ ሺሕ ፮ ወይም በ፳፻፮ ዓ.ም. ለበዓለ ጥምቀት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በተዘጋጀው ልዩ ዕትም መጽሔት ላይ፥ “የጥምቀተ ባሕር በዓል ታሪካዊ አመጣጥ” በሚል ርእስ ጽሑፍ ያቀረቡት መጋቤ ብርሃናት አባ ተክለ ያሬድ ጎርጎርዮስ፥ “የጥምቀተ ባሕር በዓል በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት በ፭፻፴ ዓ.ም. በሀገር ዐቀፍ ደረጃ በሜዳና በወንዝ ዳር መከበር ተጀመረ” ይላሉ (ገጽ ፴፱)። በዚህ ጊዜ አከባበሩ የእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በአጥቢያቸው በሚገኝ ሜዳና ወንዝ ተሰባስበው ለብቻቸው ማክበር እንደ ነበር መረዳት ይቻላል። ምክንያቱም ጸሓፊው አክለው ከወጥ ዐለት የተፈለፈሉ አብያተ ክርስቲያናትን ያነጸው ንጉሥ “ቅዱስ ላሊበላ በ፲፩፻፵ ዓ.ም. በየአካባቢው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በተናጠል ሳይኾን በአንድ ላይ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው በማደር፥ በዓለ ጥምቀቱን እንዲያከብሩ ዐዋጅ በማወጅ የጥምቀተ ባሕሩን ሥርዐት ይበልጥ አጠናክሮታል” ይላሉና።

በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች ታክለው አከባበሩ የሚከተለውን መልክ ይዟል። “ታቦታት ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ በጥምቀት ዋዜማ ጥር ፲ ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀት ወርደው እንዲያድሩና ሀገርን በኪደተ እግር [በእግር በመኼድ] እንዲባርኩ፣ በኼዱበት መንገድ እንዳይመለሱ ሥርዐት ሠርተዋል” (ገጽ ፵፩)። “ታቦትና ሙሽራ በኼደበት መንገድ አይመለስም” የሚባል አነጋገር አለ። አነጋገሩ ከዚህ ሥርዐት የተወሰደ ሊኾን ይችላል።

ቀጥሎም በ፲፬፻፹፮ ዓ.ም. ዐፄ ናዖድ “ምእመናን ከየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚወጡትን ታቦታት አጅበው በማውረድ አጅበው እንዲመለሱ ይህንኑ ሥርዐት ደግመው ዐውጀዋል።” (ዝኒ ከማሁ)። እንዲህ እንዲህ እያለ በዓሉ በዘመናችን ወደሚከበርበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው። በዚህ ኹሉ ውስጥ የቀደሙት ነገሥት በየዘመናቸው የቤተ መንግሥታቸውን ሥርዐት ብቻ ሳይኾን የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዐት በመወሰኑና በማወጁ ተግባር ውስጥ ትልቅ ሚና እንደ ነበራቸው እንረዳለን። ዛሬ በዓሉ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን “በአገሪቱ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ከእምነታቸው ጋር ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን በጋራ የሚያንጸባርቁበት” አገር ጐብኚዎችም ከውጭ በመምጣት የሚታደሙበት ብሔራዊ በዓል ኾኗል (ገጽ ፵፭)።

በአገራችን በዓለ ጥምቀት በሜዳና በወንዝ የሚከበርበት ታሪካዊ አመጣጡ ከላይ የተጠቀሰው ሲኾን፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመነሻ ሐሳብ እንዲኖረው የተደረገበት ኹኔታ ግን አለ። በዚሁ መሠረት የታቦታቱ ከየአብያተ ክርቲያኑ ወደ ሜዳና ወንዝ መውረዳቸው የክርስቶስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱን አመልካች ነው ተብሏል።

 

ጌታ ለምን ተጠመቀ?

ጌታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ (በዮርዳኖስ ወንዝ፥ በዮሐንስ እጅ) መጠመቁና ከውሃው ሲወጣ ሰማያት ተከፍተው መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲመጣ መጥምቅ ዮሐንስ አይቷል። ድምፅም ከሰማያት መጥቶ “በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው” ብሏል (ማቴ. ፫፥፲፮-፲፯)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  የመጠመቁ ታሪክ በወንጌላት ከመመዝገቡ በቀር ለምን ዐላማ እንደ ተጠመቀ ምክንያቱን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ አይናገርም። በዚህ ጒዳይ ላይ ሐዋርያት የሰጡት ግልጥ ማብራሪያም የለም።

ጌታችን በውሃ ከተጠመቀ በኋላ ሌላ የሚጠመቀው ጥምቀት እንዳለው ተናግሯል፤ ይህም ከሞቱ ጋር የተያያዘ እንደ ኾነ እንረዳለን (ማቴ. ፳፥፳፪፤ ሉቃ. ፲፪፥፶)። ሐዋርያው ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር አንድ ለመኾን የተጠመቀ አማኝ ከሞቱ ጋር አንድ ለመኾን መጠመቁንና ከእርሱ ጋር በጥምቀት መቀበሩን አብራርቷል (ሮሜ ፮፥፫-፬፤ ቈላ. ፪፥፲፪)።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጌታ የተጠመቀበትን ምክንያት ስታስረዳ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነቢያት የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም፥ ውሃን ለመቀደስ፥ ለጥምቀት ኀይልን ለመስጠትና ለእኛ አርኣያና ምሳሌ ለመኾን መጠመቁን ትናገራለች። በየዓመቱ በዓለ ጥምቀትን የምታከብረውም ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች በመፈጸም ጌታ ያሳየውን ትሕትና ለመመስከርና ለማስተማር ነው። ቤተ ክርስቲያኗ አክላም በበዓሉ ዕለት ማለዳ ላይ የተጸለየበት ውሃ በሕዝቡ ላይ የሚረጨውም ጥምቀትን ለመድገም ሳይኾን የጌታችንን ጥምቀት ለማስታወስና በረከትን ለመቀበል ነው ትላለች (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፥ ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት ፲፱፻፹፰፣ ገጽ ፹፰)።

በዚህም ብቻ ሳትወሰን ጌታ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ የተጠመቀው ጠላት ዲያብሎስ በዮርዳኖስ ወንዝ በድንጋይ ላይ ጽፎ የቀበረውን የዕዳ ደብዳቤ ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ ረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ ለማጥፋት ነው የሚል ትውፊታዊ ትረካም አላት። ይህም ትረካ ለቈላ ፪፥፲፬ ላይ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው” ለሚለው ንባብ በተሰጠው ትርጓሜ ላይ ተብራርቷል (የቅዱስ ጳውሎስ መጽሐፍ ንባቡና ከነትርጓሜው ፲፱፹፰፣ ገጽ ፫፻፳)።

 

ማሳረጊያ

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላደረገው ነገር ኹሉ የመታሰቢያ በዓል አዘጋጅቶ አምላክ የኾነው እርሱ ሰው በመኾን ያሳየውን ድንቅና በትሕትና የተሞላ ሥራውን በመዘከር እርሱን በእውነተኛ ልብ ማምለክና ማክበር መቻል መልካም ነገር ነው። ትልቁ ጥያቄ ግን በዚህ ውስጥ የበዓሉን ባለቤት ስንቱ ሰው አስታውሶት ይኾን? ካላስታወሰው ግን፥ ለእርሱ መታሰቢያ የተሠራው በዓል መልኩን ቀይሮ ለሌላ ዐላማ ውሏል ማለት ነው። በመንፈስ ጀምሮ በሥጋ መጨረስ ይሏል ይህ ነው።

ይህን ሽሽት፥ ኹሉን እርግፍ አድርገው የተዉ የመሰሉትና ጌታን ማምለክ በእውነትና በመንፈስ ነው የሚለውን ዐቋም የያዙት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አማኞችስ፥ ጌታችን በምድር ሲመላለስ የሠራቸውን ታላላቅ ሥራዎች በምን መልክ እያሰቧቸው ይኾን? በእነርሱ ምክንያት ጌታን ምን ያኽል እያመለኩትና ክብርን እየሰጡት ይኾን?

Yimrhane Kirstos

ድምፃዊ ተፈራ ነጋሽ:- “ታንክ ቢመጣ ወደኋላ አልመለስም”

5 አልበሞች ለአድማጭ አድርሷል፤ ከእነ አረጋኸኝ ወራሽና ሌሎች ድምፃውያን ጋር የሠራቸው ስብስብ ሥራዎችም አሉት። “ደህና ሁኝ ልበልሽ በእንባ እየታጠብኩኝ”፣ “ምነው ቀዘቀዘ ፍቅራችን”፣ ከሥራዎቹ መካከል ጎልተው የሚጠቀሱት ናቸው። ሰሞኑን በታክሲ ሾፌርነት መታየቱ ተሰምቶ አነጋግረነዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ኢየሱስ እና የመከራ ሕይወት

በእግዚአብሔር ሕልውና የማያምኑ ሰዎች “እግዚአብሔር የለም” ለማለት በየዘመናቱ ከሚያነሧቸው ጥያቄዎች አንዱ በምድር ላይ የመከራ መኖር ነው፡፡ ʻእግዚአብሔር ቢኖር ይህ ሁሉ ጥፋት በሰዎች ላይ ለምን ይደርሳል?ʼ ይላሉ፤ እግዚአብሔርን የሚያምኑ ሰዎችም ጥያቄውን ደጋግመው ያነሡታል፡፡ ሰዎች መከራን በተለያየ መልኩ ሲጋፈጡ በእግዚአብሔር ሕልውና፣ በእግዚአብሔር መልካምነት ወይም በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ላይ ጥያቄ ይፈጠርባቸዋል፡፡ የመከራ ሕይወትና የእግዚአብሔር ሕልውና የተጋመዱ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ አውግስጢኖስ፣ “እግዚአብሔር ከሌለ ይህ ሁሉ መልካም ነገር እንዴት ይኖራል? እግዚአብሔር ካለስ እንዴት ይህ ሁሉ ክፋት ይኖራል?” ሲል የጠየቀው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.