
የነቢያቱ “መደመር” እና የፈጠረው ስሜት
ኅብረቱ ከአራት ነቢያት “የአጋር አባልነት” ስምምነት ማድረጉን ተከትሎ፣ በርካታ አስተያየቶች በመሰጠት ላይ ናቸው። የስምምነቱ ይዘት፣ ነቢያቱ የተረዱበት መንገድ፣ የሂደቱን አጀማመር እና ስምምነቱ አለበት የተባሉትን ክፍተቶች ሚክያስ በላይ የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሮ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
[the_ad_group id=”107″]
የኢትዮጵያ ወንጌላዊው ክርስትና በአገሪቱ ከመቶ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈው ይህ ሃይማኖታዊ ማኅበረ ሰብ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ መስተጋብር ውስጥ የራሱን አሻራ እየተወ የመጣ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ይልቁኑም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ እንደ ከዚህ ቀደሙ የተናቀ ማኅበረ ሰብ ሆኖ ላለመቀጠል በሚያደርገው ትግል እየተፈጠረ ያለው ለውጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት የተከሰተው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያ ለውጥ በአገሪቱ ሃይማኖታዊ መስጋብር ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ በዚህ ለውጥ ውስጥ ተጠቃሚም ተጎጂም መኖሩ አይቀርም፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ ይህ ለውጥ ለወንጌላውያኑ ማኅበረ ሰብ የድል ብሥራት ይዞ እንደመጣ ሊታሰብ ይችላል፡፡ በርግጥ ይህ አስተሳሰብ እውነት የሚሆንባቸው ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላል፤ በአንጻሩም ያልተጠበቀ ውጤት አስከትሎ እንደ ሆነ ማሰቡ ተገቢ ነው፡፡
ይህ ጽሑፍ በመሠረቱ በሁለት አንጓ የተከፈለ ነው፡፡ የመጀመሪያው አንጓ ወንጌላዊው ክርስትና ለአገሪቱ ያበረከተው በጎ አስተዋጽዖና አማኝ ማኅበረ ሰቡ ይዟቸው የመጣው ኅብረተ ሰባዊ ለውጦች በወፍ በረር የሚቀኙበት ይሆናል፡፡ ሁለተኛው አንጓ፣ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታና የጉዞ አቅጣጫ ምን እንደሚመስል በትዝብት ዐይን የሚገረምም ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በተራድዖ ተግባራትና ልማታዊ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወቱ መክረማቸው ይታወቃል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ የወንጌል ትምህርት የሰውን ሁለንተናዊ ፍላጎት ማርካት አለበት የሚለው አመለካከታቸውን መሠረት አድርገው በርካታ የበጎ አድራጎትና መሰል ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ቀደምት የሆኑት፣ የወንጌል ተልእኳቸው ይህን መሰል ከሆነው ተግባር ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው፡፡ በርግጥ ይህንኑ ተግባር ወንጌል የማስፋፊያ ዘዴ አድርገው የሚጠቀሙ እንደ ነበሩ እሙን ነው፡፡
አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊያን እንደታዘቡት ከሆነ፣ ወንጌልን ከተራድዖና ከልማት ሥራዎች ጋር አሰናስሎ ማስኬድ የተጀመረው ሚሲዮናዊያኑ ወደ ኢትዮጵያ ወንጌልን ይዘው በሚመጡበት ጊዜ መንግሥታቱ የሃይማኖት ሰባኪን ብቻ ካለመፈለጋቸው የተነሣ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የጄስዊት ሚሲዮናዊያን ከኢትዮጵያ ከተባረሩ በኋላ የመጡት የፕሮቴስታንት ሚሲዮናዊያን ከሃይማኖት ትምህርታቸው በተጨማሪ ሙያ ያላቸው እንዲሆኑ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ፈቃዱ ጉርሜሣ “የወንጌል እምነት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ለዚህ ምሳሌ የሚሆን ታሪክ የሚጠቅሱ ሲሆን፣ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ፒተር ሄይልንግ በነገሥታቱ ለመወደዱ ምክንያቱ ሙያተኛ መሆኑ እንደ ነበር ጽፈዋል፤ “ሄይልንግ በሕክምና ሙያ በሕግ ትምህርትም የሠለጠነ በመሆኑ በቀላሉ በአበሾቹ ዘንድ … ከፍተኛ ከበሬታን አግኝቶ የንጉሥ ፋሲለደስን እኅት በማግባት ለ[ዐ]ሥራ ዘጠኝ ዓመታት” ቆይቷል፡፡
የወንጌል እንቅስቃሴን በኢትዮጵያ በማስፋፋት በመጀመሪያ ረድፍ ላይ ካሉት ቤተ ክርስቲያናት መካከል እንደነ መካነ ኢየሱስ፣ ቃለ ሕይወት፣ ሉተራን፣ መሠረተ ክርስቶስ፣ ገነት፣ እና የመሳሰሉት አብያተ ክርስቲያን በሁለንተናዊ አገልግሎት ዘመን የዘለቀ አበርክቶ አላቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ እጅግ ብዙ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የብዙ ዜጎችን ሕይወት የሚቀይር ተግባራት ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ በተጠቀሱት አብያተ ክርስቲያን መካከል ሁለንተናዊ አገልግሎትን በተመለከተ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ አቋም ያለ ይመስላል፡፡ በጤና፣ በትምህርት፣ በምግብ ዋስትና፣ በተፈጥሮ ሀብት አስተዳደርና በአካባቢ ጥበቃ፣ በጾታ ጉዳዮች እና በመሳሰሉት ሰፊ ሥራም ሠርተዋል፡፡
በማኅበራዊ አገልግሎቶች ረገድ ቤተ ክርስቲያናቱ ብቻ ሳይሆኑ፣ እምነት ተኮር የሆኑት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያዶች) እና አጋር ቤተ ክርስቲያናት የሆኑ ተቋማትም እጅግ ትልቅ ሊሰኝ የሚችል አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡ የዐሥራ ዘጠኝ ሰባ ሰባቱን ድርቅ ተከትሎ ወደ አገር ውስጥ ከገባው ዎርልድ ቪዥን ጀምሮ፣ እንደ ኮምፓሽን ኢትዮጵያ፣ ኤስ አይ ኤል ኢትዮጵያ፣ ፉድ ፎር ዘ ሀንገር፣ ሆፕ ኢንተርናሽናልና ሌሎቹም ለዚህ ተጠቃሾች ናቸው (እነዚህ ተቋማት በፕሮቴስታንት ክርስትና ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ መሆናቸውን ልብ ይሏል)፡፡
በቀረበ ዕይታ ለማነፀር የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስን ምሳሌ አድርገን ብንወስድ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የወንጌል ተልእኮዋን መወጣት የምትችለው ሁሉንተናዊ አገልግሎት በመስጠት ብቻ እንደ ሆነ ታምናለነች፤ ከጥንት ጀምሮ ትሠራቸው የነበሩ ሁሉን አቀፍ/ማኅብራዊ አገልግሎቶችም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ተመስገን ሽብሩ The Mission Thinking of Ethiopian Evangelical Church Mekane Yesus በተሰኘው የድኅረ ምረቃ ማሟያ ጥናቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ አገልግሎትን በተመለከተ የያዘቸውን አቋም ይዳስሳል፡፡
እንደ ተመስገን ከሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ አገልግሎቷን የምትመራው “ማኅበራዊ አገልግሎት” (social service) እና “ማኅበራዊ ተሳትፎ” (social action) በሚል ከፍላ ነው፡፡ “ማኅበራዊ አገልግሎት” የተሰኘው የድቁና እና የልማት አገልግሎቶችን በመስጠት ሲሆን፣ “ማኅበራዊ ተሳትፎ” ደግሞ የፍትሕና ፖለቲካዊ ተሳትፎን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የምታስተናግድበት ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባለፉት ዓመታት የሁለንተናዊ አገልግሎትን በመስጠት በወንጌላውያን አማኞች ዘንድ ጉልሕ ድርሻ እንዲኖራት አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርሰቲያንም በተመሳሳይ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የልማትና የተራድዖ ተግባራትን ስትፈጽም ቆይታለች፡፡ በሃይማኖት ቤቶች ድጋፍ ከሚደረጉና ትልቁን በጀመት ከሚይዙ የልማት ሥራዎች መካከል የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነች፡፡
በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያንናት ተዘጋጅቶ በሚሊኒየሙ መባቻ ላይ በቀረበው አነስተኛ ጽሑፍ፣ የወንጌላውያኑ ማኅበረ ሰብ ለአገሪቱ ያበረከተው በጎ አስተዋጽዖ በመጠኑም ቢሆን ተዘርዝሮ ተጠቅሷል፡፡ በትምህርት በኩል ወንጌላውያኑ ሁነኛ ተግባር እንዳከናወኑ የሚያወሳው ይህ አነስተኛ ወረቀት፣ በተለይም ሥራዎቹ የተከናወኑበትን የአገሪቱ አካባቢዎች ይዘረዝራል፡፡ “በአዲስ አበባ፣ በደብረ ዘይት፣ በናዝሬት፣ በደምቢ ዶሎ፣ በባሌ፣ በአጋሮ፣ በአላባ፣ በአለማጣ፣ በአሶሳ፣ በባሕር ዳር፣ በቦንጋ፣ በጨንቻ፣ በሐረርጌ፣ በዳንግላ፣ በድባጤ፣ በደብረ ብርሃን፣ በቦሩ ሜዳ፣ በዲላ በድሬዳዋ፣ በዱራሜ፣ በገለምሶ፣ በጎባ፣ በሐመር፣ በሆሳዕና፣ በጅጅጋ፣ በጅማ፣ በቀላፎ፣ በማይጨው፣ በሳጃ (ከፋ)፣ በሻሸመኔ፣ በስልጤ፣ በስሬ፣ በዋካ፣ በአለታ ወንዶ፣ በወሊሶ፣ በይርጋ ጨፌ፣ በዚንዚቾና በሌሎችም ከተሞች” የትምህርት ተቋማት ተገንብተዋል፡፡
በተለይ ደግሞ አገሪቱ ከሁለት የማይበልጡ ማተሚያ ቤቶች ባልነበራት በጥንት ጊዜ፣ “በ1860 ዓ.ም. አካባቢ የእምኩሉ ጣቢያ ጥራታቸውን የጠበቁ የማስተማሪያና መንፈሳዊ መጻሕፍትን በማተምና በማሳተም፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የትርጉም ሥራዎችን በማከናወን፣ እንዲሁም የቀለምና የሙያ ትምህርቶችን በመስጠት ያበረከተው አስተዋጽዖ የላቀ ግምት የሚሰጠው እንደ ሆነ ይኸው ወረቀት ይጠቅሳል፡፡ በአገሪቱ የመጀመሪያው የሆነው “የምስራች ድምፅ” የተሰኘው የሬዲዮ ጣቢያም ከወንጌላውያኑ የተሰጠ ገጸ በረከት ነበር፡፡
በጤናው ረገድም “የአለርት ሆስፒታልና የፓስተር ኢንስቲትዩትን ከመጀመር ጋር የኃይለማርያም ማሞን (ናዝሬት)፣ የደደርን፣ የሕይወት በርን (አምቦ)፣ የጊምቢ፣ የደንቢ ዶሎ፣ የአይራ፣ የዲላን፣ የግንደ በረትን፣ የበቆጂን፣ የቀላፎን፣ የሌመን፣ የሻሻመኔን ሆስፒታሎችና በመቶዎች የሚቆጠሩ በርካታ ክሊኒኮችን፣ የጤና ረዳት ት/ቤቶች እንዲሁም ጤና ጣቢያዎችን በመክፈት በደርግ እስከሚወረሱበት ጊዜ ድረስ ለአገሬው ሕዝብ ከፍተኛ ግልጋሎቶን” መስጠታቸውን፣ በልማት ሥራዎች በኩልም የእርሻ፣ የሴቶች ባልትና፣ የሙያ፣ የዐይነ ሥውራን ት/ቤትንና ሌሎች ፕሮግራሞችን ያቀፈ ተቋም በባኮ እንደ ነበረ ያስታውሳል፡፡
በሌላ በኩል የወንዶ ጨብቻ የእርሻና የእጅ ሥራ ት/ቤት፣ የውጫሌና የሰለክላካ የእርሻ ት/ቤቶች፣ የዳብና የእጅ ሥራ ት/ቤት፣ የነጆ የእጅ ሥራ ት/ቤት፣ የአርባ ምንጭ ሆስፒታልና የእጅ ሥራ ት/ቤት፣ የደዴሣ ዲምቱና የዲላ ሠፈራ ፕሮግራም ከእነዚህ የልማት ዘርፎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በርግጥ ከላይ የተጠቀሱት አብዛኞቹ ሥራዎች በደርግ ዘመን የተወረሱ ቢሆኑም፣ ከዚያም ወዲህ ባሉት ዓመታት ወንጌላውያኑ የውሃ ልማት፣ የግብርና ዘዴ መሻሻያ፣ የአርብቶ አደሮች ሰፈራ፣ የዛፍ ተከላ፣ የድልድይና የመንገድ ሥራዎችን በስፋት በመሥራት በአገሪቱ የልማት ዕድገት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ በማበርከት ላይ እንዳሉ ከስድስት ዓመት በፊት የተዘጋጀው ይኸው ጽሑፍ ያትታል፡፡
ሬንያ ሳቶ “Remapping Ethiopia: Socialism and After” በተሰኘው መድብል “Evangelical Christianity and Ethnic Consciousness in Majangir” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ የወንጌላውያን ክርስትና በቤኒሻንጉልና በአካባቢው ማኅበረ ሰብ ያመጣውን የብሔር ንቃት ያትታሉ፡፡ እንደ ሳቶ ከሆነ፣ “በመጂንገር ንቃተ ኅሊና ውስጥ ክርስትና ʻየብሔር እኩልነትʼ ምልክት ሆኗል፡፡ … ወጣት የሆኑ የእምነቱ ሰባኪዎች አጽንኦት ሰጥተው እንደሚያስተምሩት የክርስቲያን አምላክ ተከታዮች በሆኑት ብሔሮች መካከል እኩልነት አለ፡፡” ከዚህም የተነሣ በአካባቢው ያሉ ክርስቲያኖች፣ ክርስቲያን ካልሆኑት ይልቅ በተሻለ ደረጃ የብሔር ንቃትን አግኝተዋል፤ በሌላ አባባል ማንነታቸውን መቀበልና በእግዚአብሔር ዓለም ውስጥ ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው የሚለውን እውነታ መለማመድ ጀምረዋል፡፡ ይህም ለወንጌል መስፋፋት የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳበረከተ ነው ሳቶ የሚገልጹት፡፡
የብሔር ንቃትን በተመለከተ ሚሲዮናዊያኑ ጉልሕ ሚና ሳይጫወቱ አልቀሩም፤ በተለይም ደግሞ የወንጌላውያን እንቅስቃሴ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተጠበቀውን ያህል አለመስፋፋቱ፣ በዐሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የአውሮፓ ሚሲዮናዊያን የትኩረት አቅጣጫቸውን “በስተ ደቡብ” ወዳለው የአገሪቱ ክፍል እንዲያዞሩ አድርጓቸዋል (“ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች” የተሰኘው ሐረግ የመልክዓ ምድር አቀማመጥን ሳይሆን፣ በባሕልና በሃይማኖት ከ“ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል” የሚለየውን ሕዝብ ለማመልከት የዋለ ነው)፡፡ ታዲያ በዚህ ሂደት ውስጥ በስተ ደቡብ ያሉ የኢትዮጵያ ዜጎችን በወንጌል ለመድረስ ከሌላ የአገሪቱ ክፍል የመጡ ወንጌል ሰባኪዎችን ከመጠቀም ይልቅ፣ የአካባቢውን ተወላጅ የወንጌል ትምህርት አስተምሮ መልሶ መላክ ለሚሲዮናዊያኑ የተሻለው አማራጭ ሆኖ ታይቷቸዋል፡፡ ለዚህ ኀላፊነት የተለዩ ሰዎች የወንጌል ትምህርትና ሌሎች ተጓዳኝ ሥልጠናዎች በሚወስዱበት ጊዜ፣ ስለ ብሔር ንቃት የተሻለ ግንዛቤ የማግኘት ዕድል ነበራቸው ቢባል ስሕተት ላይሆን ይችላል፡፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን (ኢኦተቤክ) ትጠቀመው የነበረው ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ ለአካባቢያዊ ቋንቋዎች ትኩረት እንዳትሰጥ አደርጓታል የሚል ወቀሳ ይሰነዘርባታል፡፡ ከዚህም የተነሣ፣ የአማርኛ ቋንቋ የማይናገሩ ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች የኦርቶዶክስ ክርስትናን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አልቻሉም፡፡ አንዳንድ ምሁራንም የኢኦተቤክ ሃይማኖትንና ቋንቋን ከማስፋፋት ውጪ ዘመናዊነትን በማስረጽ ረገድ ይኼ ነው የሚባል ሚና እንዳልተጫወተች ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ውስን ሚናዋ የተነሣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል ላይ የባሕል (የቋንቋ) ወረራ ከማድረግ ውጪ ፋይዳ እንዳይኖራት አደርጓል የሚሉ ሰዎችም አልጠፉም፡፡ በአንጻሩ ይህንን ክፍተት በመጠቀም ረገድ ሚሲዮናዊያኑ የተሻለ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ለዚህም ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀሰው በአፍ መፍቻ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጊዜ ሂደት የሰዎችን የብሔር ንቃት ማጎልበቱ አልቀረም፡፡
በርግጥ በሌላ በኩል ያሉ ወገኖች ሚሲዮናዊያኑ በተንቀሳቀሱባቸው የአገሪቱ “ደቡባዊ ክፍሎች” አክራሪ የብሔርተኝነት/የጎሠኝነት ስሜት ሥር እንዲሰድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ብለው ሲከሰሱ ይደመጣሉ፡፡ ይኸው አስተሳሰብ ሥር ሰዶ በደርጉ ዘመን በተለይ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ መሪዎችን ሕይወት ሲያስከፍል፣ ሚሲዮናዊያኑ ደግሞ ከአገር እንዲባረሩ አድርጓል፤ ለአገር አንድነትና ደኅንነት ፀር ናቸው በሚል፡፡ አሁንም እንኳን ʻፕሮቴስታንት ብሔርተኞች ከአገር አንድነት ይልቅ የብሔር ማንነት ላይ ትኩረት ያደርጋሉʼ እየተባሉ ይነቀፋሉ፡፡
በሌላ አንጻር የታየ እንደ ሆነ፣ ክርስትና የሚሰብከው እኩልነት ማለትም በመጀመሪያ ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ፣ ቀጥሎም በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ያለ ልዩነት የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች የመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ እኩልነት ባልሰፈነበት ማኅበረ ሰብ ውስጥ የሚያመጣው የአስተሳሰብ ለውጥ አለ፤ ይህም ሰዎች የእኩልነት ሰብእና እንዲኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ማንነታቸውን እንዲቀበሉና ባሕላዊ ትውፊታቸውን አጥብቀው እንዲይዙ ሊያደርግ ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች በአገሪቱ በነበረው/ባለው ሃይማኖታዊ ተዋስኦ (discourse) ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከቁጥራቸው ጋር ሲነጻጸር የገዘፈ ሆኖ ይታያል፡፡ አሁን እየተገለጸ ካለው ቁጥር እጅግ አናሳ በነበሩበት ጊዜ እንኳ ወደ ኅብረተ ሰቡ ይዘውት የገቡት አዲስ ሃይማኖታዊ ተዋስኦ በቀላሉ እንዲታዩ አላደረጋቸውም፡፡ በተለይም፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን (ኢኦተቤክ) እና ከምእመናኑ ጋር የነበራቸው መስተጋብር ከአዎንታዊነቱ ይልቅ አሉታዊነቱ ጎልቶ የታየበት ነበር፡፡ በምድሪቱ ላይ ከኢኦተቤክ ሌላ ቤተ ክርስቲያን እንዲኖር የማይፈልጉ ወገኖች የመንግሥትንም ሆነ ማኅበራዊ መዋቅሮችን የተቆጣጠሩ በመሆናቸው፣ ወንጌላውያኑ ከፍተኛ የሆነ ስደትና እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ በተለይም፣ አሁን ካለው መንግሥት በፊት የነበሩት መንግሥታት ለወንጌላውያን ክርስትና ፈታኝ እንደ ነበሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡
ይህ አሉታዊ መስተጋብር መልኩን ቀይሮም ቢሆን እንደ ቀጠለ የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት እንደተስተዋለው በሃይማኖት ተቋማት መካከል በርካታ ውይይቶች መደረጋቸውና “መቻቻልን” በተመለከተ በየአደባባዩ ብዙ ቢባልም፣ ውጥረቶች ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡ ይመስላል፡፡ በተለይም፣ ወንጌላውያኑ ʻአገኘነውʼ ባሉት የሃይማኖት ነጻነት እምነታቸውን ከበፊቱ ይልቅ መስበካቸውና የተከታዮቻቸው ቁጥር መጨመሩ፣ ብሎም ራሳቸውን በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ሚና እንዳለው ማኅበረ ሰብ መቁጠር መጀመር እንደ ስጋት እንዲታዩ ሳያደርጋቸው አልቀረም፡፡ ለዚህም ይመስላል አንዳንዶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አማኝ ማኅበረ ሰቡን ማጠልሸትን እንደ ዋና ተልእኳቸው ያደረጉት፡፡ በመጻሕፍት፣ በጋዜጦችና በመጽሔቶች፣ በኤሌክተሮኒክስ ማሰራጫዎችና በመሳሰሉት ሁሉ በኢኦተቤክ ከፍ ሲልም በአገሪቱ ላይ “ፕሮቴስታንታዊ ጂሓድ” እንደተከፈተ ለማሳየት ጥረት ያደርጋሉ፡፡
በሌላ አንጻር፣ የኢኦተቤክ ለውጥ ያስፈልጋታል ብለው የሚያምኑ ሰዎች እንዲነሡ ወንጌላውያኑ ጉልሕ አስተዋጽዖ ሳያበረክቱ አልቀሩም (ይህ ሲባል ከወንጌላውያኑ በፊት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለውጥ እንደሚያስፈልጋት የሚያምኑና የተጉ ኢትዮጵያን አልነበሩም ማለት አይደለም፤ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአባ እስጢፋ እና በተከታዮቻቸው የተነሣውን ንቅናቄ ልብ ይሏል)፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን፣ ሚሲዮናውያኑ የወንጌል እንቅስቃሴን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው ለመግባት ያደረጉት ጥረት የተጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት ካልቻለ በኋላ እንደ ሆነ አንዳንድ የታሪክ ድርሳናት ዘግበዋል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የተወሰኑ ተሓድሶ ናፋቂ ኦርቶዶክሳውያን ከወንጌላውያኑ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደ ነበራቸውና ድጋፍ ይደረግላቸው እንደ ነበር ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩልም ወንጌላውያኑ ይጠቀሙበታል የተባለውን “ስትራቴጂ” በመቅዳት፣ ጥንታውያን የሃይማኖት ተቋማት ʻጉድለቶቻችን ናቸውʼ ባሏቸው ላይ “የማሻሻያ” ርምጃን ወስደዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል የስብከት ዘዴን፣ አዲስ የዝማሬ አገልግሎትን፣ ደቀ መዛሙርትን የመከታተያና የማስተባበሪያ መንገዶችንና ስልቶችን በመከለስ አዲስ ሃይማኖታዊ ተዋስኦ በአገሪቱ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ይህ ዐይነቱ ለውጥ ለወንጌላውያኑ የተሰጠ ምላሽ እንደ ሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ የወንጌላውያን ክርስትና በኢትዮጵያ ባይኖር ወይም ይህ ነው የሚባል ሚና ባይጫወት በሌላኛው የክርስቲያን ቤተ እምነት የሚታየው ሃይማኖታዊ ገጽታ ምን ሊመስል ይችል እንደ ነበር ለመገመት ብዙ አይከብድም፡፡
ከላይ ለመዘርዘር እንደ ተሞከረው የወንጌላውያን ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን ተከትሎ በአገሪቱ ላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች በጉልሕ ተከስተዋል፡፡ የለውጡ ይዘት አዎንታዊ ነው ወይስ አሉታዊ የሚለው እንደ ተመልካቹ ዐይን ሊለያይ ቢችልም፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ይዞት የመጣው አዲስ ተዋስዖ ግን ወደኋላ ሊመለስ የማይችል የኅብረተ ሰብ ቅርፅ ፈጥሯል፡፡ በርግጥ የልማትና የተራድዖ ሥራዎቹ በራሳቸው አዎንታዊና ክርስቲያናዊ ናቸው፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱም ሆኑ የተራድዖና የልማት ድርጅቶቹ ስላደረጉት በጎና ምሳሌያዊ ተግባር እውቅና ብሎም ምስጋና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ወንጌል ባዶ ጩኸትና ዝላይ ሳይሆን፣ በተግባር የሚገለጥ በጎ ምግባር/ተግባር እንደ ሆነ ቤተ ክርስቲያናቱም ሆኑ ድርጅቶቹ ዐሳይተውናል፡፡ ይህ የታሪክ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ዛሬም ቀደምት የሆኑት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ድኾችን በማሰብና ለሌሎች አለኝታ በመሆን ረገድ ብዙ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ እዚህ ለመጥቀስ ቦታውም ሆነ ጊዜው የማይበቃ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፕሮጀክቶች በአብያተ ክርስቲያናቱም ሆነ ክርስቲያናዊ በሆኑት ድርጅቶች እየተተገበሩ ነው፡፡ ከዚህ እውነታ ተነሥተን በዛሬ ውስጥ ትላንትን ማየት እንችላለን፡፡
ይህ ሲባል ግን ትላንት ዛሬን ሆኖ ሙሉ ለሙሉ ቀጥሏል ማለታችን አይደለም፡፡ ትላንት ከዛሬ የሚለይባቸው በርካታ ሁነቶች እዚህም እዚያም እየተከሰቱ እንደ ሆነ እያየንና እየሰማን ነው፡፡ እነዚህ ሁነቶች ደግሞ በፍጹም መልካም የሚባሉ አይደሉም፤ እንደውም ʻአሳሳቢ ናቸውʼ ማለት ተገቢ ይመስለናል፡፡ የለውጥ ነፋስ እየነፈሰ ነው፤ ለበጎ ግን አይመስልም፡፡
በቀድሞ ዘመናት የነበረው የወንጌላውያኑ አዎንታዊ ተጽእኖ በዚህኛው ትውልድ ስለ መቀጠል አለመቀጠሉ ተገቢ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በተጨባጭ መታዘብ እንደሚቻለው ʻክርስትናውʼ መልኩን እየቀየረ እንዳለ የሚያሳዩ በርካታ አስረጆች አሉ፡፡ እንግዳ ትምህርቶች (ኑፋቄ)፣ ቡድንተኝነት፣ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት፣ እውነተኛ ደቀ መዛሙርትን በሚፈለገውና በሚጠበቀው መጠን ማፍራት አለመቻል፣ የአመራር ዕጦትና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች ክርስትናውን እያጠየሙ ያሉ ፈተናዎች ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡
የ1983ቱ የመንግሥት ለውጥ ለወንጌላውያኑ ድልን ብቻ ይዞላቸው አልመጣም፤ ቀድመው ያላሰቡበትንና ያልተዘጋጁበትን አዳዲስ ተጋፍጦዎችንም አምጥቶ እንደዘረገፈባቸው ወደኋላ ዞሮ ማየት ይቻላል፡፡ በድብቅ ትንቀሳቀስ የነበረችው ቤተ ክርሰቲያን ወደ አደባባይ ስትወጣ ልትቆጣጠረው የማትችለው ሕዝብ ደጆቿ ላይ ተኮለኮለ፡፡ የኮሚዩኒዝሙ ርእዮት ያዛላቸውና የፖለቲካው ሁኔታ ተስፋ ያስቆረጣቸው በርካቶችም እጃቸውን ለክርስቶስ እየሰጡ ሲመጡ የአማኝ ማኅበረ ሰቡ ቁጥር እንዲያሻቅብ አደረገው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊነትቷን ጠብቃ፣ ክርስትናውም ንቅናቄ (movement) መሆኑን ሳይለቅ እንዴት አጣጥሞ ማስኬድ እንደሚቻል አስቀድመው ያሰቡበትና ራሳቸውን ያዘጋጁ መሪዎች ስለ መኖራቸው ርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ወደ ተቋማዊነት መምጣት አለባት የሚሉ ወገኖች በንቅናቄ መልክ እንድትቀጥል ከሚፈልጉት ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው አልቀረም፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን የመጡ አንዳንድ አዳዲስ መሪዎችም ሁለቱን ማጣጣም ስላቃታቸው ለተነሡት ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ሳይቻሉ ቀሩ፡፡ በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያናትም የተሰየሙ መሪዎች ከመንፈሳዊው ዓለም ውጪ ያለውን የአመራር ዘይቤ በቀጥታ በቤተ ክርስቲያን ላይ ለመተግበር በመሞከራቸው በአገልጋዮች በኩል ከፍተኛ ቅሬታን ሊፈጥር ቻለ፤ ይህም አገልጋዮች ባሉበት አጥቢያ ተረጋግተው እንዳያገለግሉ ከምክንያቶቹ አንዱ ሆነ፡፡
በርግጥ በንቅናቄ ደረጃ ላይ የነበረ የሚመስለው የወንጌላውያን ክርስትና በድኅረ ደረግ በዚሁ ገጽታው ለተወሰኑ ዓመታት መዝለቅ ችሎ ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ ንቅናቄውን የሚያስጠብቁም ሆነ የሚጠብቁ መሪዎች ባለመኖራቸው መሪ እንደ ሌለው መርከብ ወደየትም ይጓዝ ጀመር፡፡ ይህ ደግሞ ለተኩላዎቹ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ከ1980ቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ 90ዎቹ አጋማሽ ድረስ ለበርካታ ፀጉረ ልውጥ ሰባኪያን መድረኮች ተዘጋጁላቸው፡፡ የትምህርት ማጥለያ አልነበረምና የመጣውን ሁሉ መቀበል የወቅቱ ʻፋሽንʼ ሆነ፡፡ ብዙ እንግዳ ትምህርቶችን የታጨቀው የ“እምነት እንቅስቃሴ” ሥሩን በወንጌላውያኑ አብያተ ክርስቲያን ውስጥ መስደድ የጀመረው ያን ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ዛሬ የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች ራሳቸውን ፈልገው ስለማግኘታቸው ርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ የመጣ የሄደውን ሁሉ ለመምሰል የሚዳክሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያናት አስተምህሯቸውን ተከትለው ለመጓዝ ከባድ ፈተና እየገጠማቸው ያለ ይመስላል፡፡ ከቶ ነገር “ወንጌላውያን” የሚለው ስያሜ አማኝ ማኅበረ ሰቡን ምን ያህል ይወክለዋል የሚለው በራሱ አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡
በኢትዮጵያውያን ዐውድ መሠረት፣ “ወንጌላውያን” የተሰኘው “ፕሮቴስታንት” የሚለውን የወል ስም እንዲተካ ተብሎ የመጣ ነበር፤ “ጴንጤቆስጢያዊውም” ሆነ “ካሪዝማቲካዊው” በወንጌላዊነት ጥላ ሥር መሰባሰብን ብዙም ሳይቆረቁረው ለረጅም ዓመታት ዘልቆበታል፡፡ አሁን ግን በእነዚህ አስተምህሯዊ አቋሞች መካከል ያለው ልዩነት እየደበዘዘ መጥቷል፡፡ ማን ምን እንደ ሆነና ምን እንደሚያምን ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ʻታዲያ ይሄ ምን ችግር አለው፤ እንደውም አንድ ወደ መሆን እየሄድን ነዋ?ʼ የሚል የየዋህ አስተያየት ሊሰጥ ይችላል፡፡ እውነታው ግን እሱ አይደለም፤ “የወንጌላውያኑን” እምነት/አስተምህሮ እና መንፈሳዊ ልምምድ የሚመራው በጴንጤቆስጤያዊውም ሆነ በካሪዝማቲካዊው ክርስትና አይደለም፤ “የእምነት እንቅስቃሴ” እና የዚያ ውላጅ በሆነው “በበልጽግና ወንጌል” ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ ይህ የትምህርት ንፋስ “በአዳዲሶቹ” ብቻ ሳይሆን፣ ʻቀደምትʼ እየተባሉ በሚጠሩት ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ መግባት ጀምሯል፡፡
Share this article:
ኅብረቱ ከአራት ነቢያት “የአጋር አባልነት” ስምምነት ማድረጉን ተከትሎ፣ በርካታ አስተያየቶች በመሰጠት ላይ ናቸው። የስምምነቱ ይዘት፣ ነቢያቱ የተረዱበት መንገድ፣ የሂደቱን አጀማመር እና ስምምነቱ አለበት የተባሉትን ክፍተቶች ሚክያስ በላይ የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሮ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
“ቅዱሳን እና መላእክት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አስታራቂ ተደርገው ይታመናሉ። በሌላ አኳያ፣ በአንዳንድ ቤተ ክርስትያናት ‘የእግዚአብሔር ሰው’ በሚለው ስም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የቈሙ አድርገው ራሳቸውን የሚያቀርቡ ወይም እነዚህን ሰዎች እንደ መካከለኛ አድርገው የሚወስዱ ሰዎች አሉ።” ባትሴባ ሰይፉ
“እግዚአብሔር ለመንግሥትና ለቤተ ክርስቲያን የውክልና ሥልጣን ነው የሰጣቸው። የሥልጣን ውክልናቸው፣ እግዚአብሔር የሚከለክለውን ማድረግን ወይም የሚያዝዘውን መከልከልን አይጨምርም።” ባንቱ ገብረ ማርያም
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment