
Adoniram Judson: The First missionary to Burma
Genaye Eshetu introduces us a missionary who lost everything he has, but endured to tell the good news to the Burma people.
[the_ad_group id=”107″]
በዚህ ጽሑፍ ሁለት ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሙከራ አደርጋለሁ። አንደኛው ዴሞክራሲ ምንድን ነው? መሠረቱና እሴቶቹስ ምንድን ናቸው? የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው እውነተኛ ሰውነት ምንድን ነው? ትርጒሙስ ምንድን ነው? የሚል ነው።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት ሲመኙትና ሲያልሙት የነበረው ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ከሰሜን እስከ ደቡብ እንዲሁም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በመናፈስ ላይ ይገኛል። ሥልጣኔ ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ የሰው ልጆች ብዙ ዐይነት አስተዳደራዊ ሥርዐቶችን ናፍቀው ሞክረዋል። በእኛ አገር አንኳ ሁለት ዐበይት አስተዳደራዊ ሥርዐቶች ተሞክረዋል። አንደኛው ዐፄአዊ አገዛዝ ሲሆን፣ ሁለተኛው ሶሻሊስታዊ አገዛዝ ነው። ሁለቱም አገዛዞች በሕዝብ ዐመፅ ተወግደዋል፤ አትፈለጉም፣ አትናፈቁም ተብለው። በዓለም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ከተሞከሩት አስተዳደራዊ ሥርዐቶች ሁሉ ዴሞክራሲ የተሻለ ሆኖ የተገኘ ይመስላል። ዴሞክራሲ ለአንድ ሕዝብ ብዙ መልካም ተስፋዎችን ይሰጣል። ከዴሞክራሲ ተስፋዎች አንዱና ምናልባትም ትልቁ ነጻነትና እኩልነት ናቸው። ይሁንና ዴሞክራሲ ያለ ሕግ፣ ያለ ፍትሕና ያለ እውነት መሥራት አይችልም። ዴሞክራሲ እንዲያውም ያለ እነዚህ መሠረቶች መቆምም ሆነ መዝለቅ አይችልም።[1]
“ዴሞክራሲ” የሚለው ቃል የመጣው “ዴሞክራቲያ” (“ዴሞስ” = ሕዝብ፤ “ክራቶስ” = አገዛዝ) ከሚል የግሪክ ቃል ሲሆን፣ በቁሙ “ሕዝባዊ አገዛዝ” ማለት ነው። ዴሞክራሲ በሕዝቦች ፍላጎትና ምርጫ ላይ የተመሠረተ አገዛዝ ወይም አስተዳደር ነው። የአገዛዙ ወይም የአስተዳደሩ መሠረተ ሌላ ማንም ሳይሆን ሕዝቦች (ብዙኃኑ ሕዝብ) ናቸው።[2] በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንጂ ሞናርኪያዊና አሪስቶክራሲያዊ አገዛዝ እንዲሰፍን አልመኝም። ዐፄአዊና ሶሻሊስታዊ አገዛዞቹንም ስለሞከርናቸው እነርሱም ተመልሰው እንዲመጡ አልናፍቅም። በዴሞክራሲና በሞናርኪ እንዲሁም በዴሞክራሲና በአሪስቶክራሲ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ዴሞክራሲ በሕዝቦች ፍላጎትና ምርጫ ላይ የተመሠረተ አስተዳደር ሲሆን፣ ሞናርኪ (አንዳዊ ወይም ንጉሣዊ አገዛዝ) በዘር ወይም በውርስ የሚገኛና በአንድ ሰው አገዛዝ ላይ የተመሠረተ አስተዳደር ነው።
በዴሞክራሲ አገዛዝ የሥልጣን ምንጩ ብዙኃኑ ሕዝብ ነው። መሪዎች ወይም ርእሰ ብሔሮች የሚመረጡት በሕዝብ ነው፤ የሥልጣን ዘመናቸውም ውሱን ነው። በዴሞክራሲ ሥርዐተ ማኅበር ውስጥ የብዙኃኑ መብትና ነጻነት ወይም ምኞትና ፍላጎት የሚረጋገጠው በምርጫ ነው። በሞናርኪ አገዛዝ የሥልጣን ምንጩ አንድ ግለ ሰብ ነው። ንጉሡ ወይም ርእሰ ብሔሩ የአገሩ ሕግ ነው። ከእርሱ በላይ ሌላ ማንም ሕግ የለም፤ የሥልጣን ዘመኑም ገደብ የለውም። አሪስቶክራሲ (“አሪስቶስ” = ልህቅና፤ “ክራቶስ” = አገዛዝ) ደግሞ በምርጦች ወይም በልሂቆች ላይ የተመሠረተ አስተዳደር ነው፤ የኅሩያን ምስፍና ወይም የምርጥ ዜጎች አገዛዝ ሊባል ይችላል። መንግሥታዊ አመራር “ምርጥ” ናቸው ለሚባሉ የተለየ ችሎታ፣ ስጦታና ብቃት ላላቸው ሰዎች መሰጠት አለበት የሚል ፍልስፍና ነው። አንዳንድ ጊዜም በሥርወ ትውልድ ሐረግ ላይ የሚመሠረትና በዘር፣ በሀብትና በዕውቀት ከሌሎች ይሻላሉ ወይም ይበልጣሉ የሚባሉ ጥቂት ግለ ሰቦች አገርና ሕዝብ ለመምራት ሥልጣን ይሰጣቸዋል። ግሪካዊው ፈላስፋ አርስጣጣሊስ ለሦስቱ ሥርዐተ አገዛዞች ዕውቅና ቢሰጥም ለሕዝብ የሚበጀው ግን ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ እንደ ሆነ ይገልጻል። ርግጥ አናርኪዝም የሚባል በምዕራብ አውሮፓ የጎለበተና በመላው ዓለም በመስፋፋት ላይ የሚገኝ አስተዳደር አለ። አናርኪዝም እንኳን ለወዳጅ ለጠላትም የሚመኙት አገዛዝ አይደለም። ቃሉ “አናርኮስ” ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን፣ በቁሙ “ሥርዐተ ቢስ፣ ሕገ ቢስ፣ ሥልጣነ ቢስ” ማለት ነው፤ አናርኪዝም ወይም ሥርዐት አልበኛነት የመንግሥትን መጥፋትና መክሰም የሚመኝ ፀረ ሕዝብና ፀረ ፍጥረት ፍልስፍና ነው። በአናርኪዝም አገዛዝ ሕግ፣ ሥርዐትና ሥልጣን ከቶ ስፍራ የላቸውም። ሰው ሁሉ የራሱ ሕግ፣ ሥርዐትና ሥልጣን ነው። ሁሉም ርእሰ ብሔር ነው፤ ሁሉም ንጉሥ ነው፤ ሁሉም ባለሥልጣን ነው።[3] በመጽሐፈ መሳፍንት ላይ “በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር” (መሳ 21፥25) የተባለው እንዲህ ዐይነቱን ሥርዐት ለመግለጽ ሳይሆን አይቀርም።
ዴሞክራሲ ሊያካትታቸው ወይም ሊያንጸባርቃቸው የሚገቡ መሠረታዊ እውነታዎች አሉ። አንዳንድ ምሁራን እነዚህን እውነታዎች እንደ ዐበይት መሥፈርትና ወሳኝ መመዘኛ አድርገው ይወስዷቸዋል። ዴሞክራሲ ሁነኛ መለኪያዎችና መመተሪያዎች አሉት። እነዚህ ነገሮች ካልተሟሉ ዴሞክራሲ አለ ለማለት ያስቸግራል። እነርሱም 1) the right to vote, 2) the right to be elected, 3) the right of political leaders to compete for support and votes, 4) elections that are free and fair, 5) freedom of association, 6) freedom of expression, 7) alternative sources of information, and 8) institutions for making public policies depend on votes and other expressions of preference ናቸው።[4]
በቅድሚያ ስለ ዴሞክራሲ ሲነሣ ሁልጊዜ ስሟ ስለሚጠቀሰው ስለ አሜሪካን ዴሞክራሲ ጥቂት ነገሮችን ልናገር። አሜሪካን በመንግሥታዊ አቋሟ ዴሞክራሲያዊት አገር ስትሆን በኢኮኖሚያዊ አቋሟ ደግሞ ካፒታሊስት ናት። የሁለቱ ዝምድና (ዴሞክራሲ + ካፒታሊዝም) አገሪቱን መጥቀሙ ምንም ባያጠራጥርም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዱ በሌላው ላይ በሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ (በተለይም ካፒታሊዝም በዴሞክራሲ ላይ) የሁለቱንም መሠረት እያናጋው ይገኛል። ሥርዐቱ ሁለት ዋና ዋና ጠንቆች ተጋርጠውበታል ማለት ይቻላል። አንደኛው፤ ካፒታሊስታዊ ሥርዐቱ በጥቂቶች መዳፍ ውስጥ መውደቁ ነው። በአመራር ቦታ ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ሥልጣን የሚጨብጡት ባለጠጎች በሚሰጧቸው ገንዘብ ከሆነ አዲዮስ ዴሞክራሲ ውሃ በላው።[5] በዚህ ዐይነት መንገድ ሥልጣን የሚጨብጡ መሪዎች ደግሞ ለመላው ሕዝብ ሳይሆን ገንዘብ ለሰጣቸው አካል ጥቅምና ጥብቅና ነው የሚቆሙት። ሁለተኛው፤ ዕጩ ተወዳዳሪዎች የሚመረጡት ርእዮታቸው ወይም የሃይማኖት መደባቸው እየተፈተሸ መሆኑ ነው። ዕጩ ተወዳዳሪው የሚያቀርበው ሐሳብ ሳይሆን ርእዮቱና ሃይማኖቱ ወይም ብሔሩ የሚታይ ከሆነ አዲዮስ ዴሞክራሲ ቀለጠ።
ርግጥ ርእዮትና ሃይማኖት ወይም ብሔር የአንድን ሰው አስተሳሰብና አካሄድ የመቅረጽ ጉልበታቸው ብርቱ ነው። ሰዎች የሚሆኑትንና የሚያደርጉትን ነገር የሚሆኑትና የሚያደርጉት ከርእዮታቸውና ከሃይማኖታቸው አንዳንድ ጊዜም ከብሔራቸው የተነሣ ነው። ይሁንና ገንዘብና ሃይማኖት ወይም ብሔር ሥልጣን መጨበጫ መሣሪያ መሆን የለባቸውም፤ ከቶውንም! እንደሚታወቀው የአሜሪካን ዴሞክራሲ እንደ አብነት የሚጠቀስ ዴሞክራሲ ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም። አሜሪካን ዴሞክራሲያዊት አገር መሆኗ ሕገ መንግሥቷ በግልጽ ይመሰክራል። በአገሪቱ ውስጥ ሥልጣን የሚገኘው በዘር ወይም በምርጥ ዜግነት ሳይሆን በምርጫ ነው፤ ሥልጣን የሚተላለፈውም በሰላማዊ መንገድ ነው። መፈንቅለ መንግሥት የሚባል ነገር የለም። የአገሪቱ ፕሬዘዳንት በየአራት ዓመቱ፣ ሲኔተሮች በየስድስት ዓመቱ፣ የሕዝብ ተወካዮች ደግሞ በየሁለት ዓመቱ ይመረጣሉ። ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል አገር አይበጠበጥም። ሚደያዎች ነጻ ናቸው። ሕዝቡም የመናገርና የመጻፍ መብት አለው።
እንዲህ ሲባል ግን ሁሉም ነገር ፍጹም ነው ወይም ሥርዐቱ አንዳች እንከን አይወጣለትም ማለት አይደለም፤ በጭራሽ! በገንዘብ ኀይልና በሃይማኖት ወይም በቆዳ ቀለም አመራርና ሥልጣን የሚጨብጡ ሰዎች አሉ። መራጮች የሰጡት ድምፅ በትክክል አልተቆጠረም በሚል አተካሮ የሚፈጠርበት ጊዜ አለ። ሰዎች ድምፃቸውን እንዳይሰጡ መሰናክል የሚቀመጥበት ጊዜ አለ፤ መታወቂያ ካላወጣችሁ አትመርጡም የሚባልበት ወይም የምርጫ ጣቢያውን ለመራጩ አመቺ ወዳልሆነ ስፍራ የሚወሰድበት ጊዜ አለ። ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ በተለይም ሴኔተሮችና የሕዝብ ምክር ቤት አባሎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዐቱ ለመፈረካከስ አደጋ እስከሚጋለጥ ድረስ የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙበት ጊዜ አለ።
እንግዲህ የአሜሪካን ዴሞክራሲ የሚወደሰውን ያህል ውስጣዊ ችግሮች አሉት ማለት ነው። አንዳንዶች እንዲያውም ሥርዐቱ ከምንጊዜውም በላይ ራሱን ማደስ ያለበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው የሚል ብርቱ ሙግት እያነሡ ናቸው።[6] ሥርዐቱ መዛግና መሻገት ጀምሯል የሚሉ ወገኖች ሥጋታቸውን ከመግለጽ ወደኋላ አላሉም። አንድ ሥርዐት ከዛገና ከሻገተ ደግሞ ወይ መወገድ አለበት አለዚያም በሚቻለው ሁሉ መታደስና መጠገን ወይም መለወጥ አለበት። ለውጡ እንዲያውም ሥር ነቀል ለውጥ መሆን አለበት።[7]
የአሜሪካን ዴሞክራሲ መዛግና መሻገት ጀምሯል ለሚለው አብነት መጥቀስ ካስፈለገ የወቅቱ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥሩ ምሳሌ ነው። በርካታ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ ፕሬዘዳንቱ ለአሜሪካን ዴሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ትልቅ ሥጋት ሆኗል።[8] ምንም እንኳ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ቢመረጥም[9] ለዴሞክራሲያዊ ሥርዐቶች ጨርሶ ባይተዋር መሆኑና ይልቁንም ዴሞክራሲያዊ ሥርዐቶችን በአምባገነናዊ አስተዳደር ለመተካት መከጀሉ ለብዙዎች አስገራሚና አስደንጋጭ፣ ብሎም አሳሳቢ ሆኗል። ገና ዕጩ ተፎካካሪ ከነበረበት ጊዜ አንሥቶ ለአምባገነን መሪዎች ቀኝ እጁን ሰጥቷል። ለምሳሌ በፕሬዘዳንት ዘመኑ አንድም ጊዜ የራሺያውን አምባገነን መሪ ፑቲንን ወይም የሰሜን ኮሪያውን ጨካኝ መሪ ኪምን አውግዞ አያውቅም። ይልቁንም ሁልጊዜ ሲያወድሳቸውና በትልልቅ መድረኮች ላይ ሲደግፋቸው ታይቷል። ይብስ ብሎም የአገሪቱ ጸጥታ/ደኅንነት ተቋማት ከሚሰጡት መረጃ ይልቅ ፑቲን የሚነግረውን መቀበሉ በፑቲን ተገዝቷል (blackmailed ተደርጓል ወይም Russian asset ሆኗል) የሚለውን አባባል ይበልጥ አሳማኝ አድርጓል።[10]
በሌላ በኩል ደግሞ ዘረኛነትና አምባገነንነት የሕይወቱ መርሕ ለመሆኑ በየጊዜው ከሚያደርጋቸው ንግግሮች መመልከት ይቻላል። ነጻ ሚዲያዎች እንዲኖሩ አለመፈለጉ እንዲሁም የእርሱን አካሄድና አመለካከት የሚተቹ ግለ ሰቦችን እንደ ጠላት መመልከቱ ሥርዐቱ አልፈቀደለትም እንጂ እንደ ፑቲን ዘብጥያ ቢከረችማቸው፣ ካስፈለገም እንደ ኪም አኖቆ ቢገድላቸው ምርጫው ነበር። በሕዝብ የተመረጠ መሪ እንዲህ የሚያደርግ ከሆነ የአሜሪካን ዴሞክራሲ ችግር አለበት ማለት ነው?[11] ችግሩስ እምን ላይ ነው? በሕዝብ የተመረጠ መሪ እንዲህ እንዳይዘባነንና ሥልጣኑን አላግባብ እንዳይጠቀም ምን መደረግ አለበት? በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች እንደ ትራምፕ አምባገነን እንዳይሆኑ “ቃታ መጠበቂያው” ምንድን ነው?[12] እነዚህ ጥያቄዎች አሜሪካውያንን ከምንጊዜውም በላይ እያስጨነቁ ናቸው። አገራቸው ትልቅ አደጋ ላይ እንደ ወደቀች በእጅጉ ያሳሰባቸው ግለ ሰቦችና ተቋሞች ዴሞክራሲያቸው የቆመበትን መሠረት ዳግመኛ ለመፈተሽ ተገድደዋል።[13] በዚህ ጽሑፍ አሜሪካን የተደቀነባትን ብርቱ ችግር ለመመልከት ሙከራ አላደርግም፤ “የራሷ እያረረባት” እንዳልባል።
ወደ ጽሑፌ ዐቢይ ትኩረት ልመለስና ከዚህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ላንሣ፤ ዴሞክራሲ ለምን ተመራጭ ሥርዐት ሆነ? ዴሞክራሲ የሚሠራው ምን ሲኖር ነው? ዴሞክራሲ ምን ላይ መቆምና መተከል አለበት? ማለት መሠረቶቹና እሴቶቹ ምንድን ናቸው? የዴሞክራሲ ጠንቆችስ ምንድን ናቸው? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሙከራ ሳደርግ ፓለቲካዊ ገጽታዎችን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ገጽታዎችንም ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ኢትዮጵያ እንደ አገር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አመራሯን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወሰን አለባት። ርግጥ ነው ለሁላችንም የሚበጀን ሥርዐት የትኛው እንደ ሆነ በግልጽ መነጋገርና መከራከር አለብን። ጊዜ ወስደን ከተነጋገርንና ከተከራከርን በኋላ ግን በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመና ራሱን በየጊዜው ማደስ የሚችል ሥርዐት መመሥረት አለብን። ያ ልንመሠርተው የሚገባው ሥርዐት ደግሞ ዴሞክራሲ መሆን አለበት (ወይም ዴሞክራሲ ቢሆን ይመረጣል ከተመክሮ እንዳየነው)።
ከሌሎች አገሮች ተመክሮ እንደምንማረው ዴሞክራሲ በዘር፣ በቀለም፣ በብሔር፣ በሃይማኖትና በመደብ ላይ የተመሠረተ አመራርን ያስቀራል። የሕዝቦችን ነጻነትና እኩልነት ያረጋግጣል። እንደሚታወቀው ከሌሎች ሙሉ በሙሉ የተቀዳ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት በእኛ አገር ላይሠራ ይችላል። ደግሞም የሌሎቹ እንከን ዐልባ ነው ማለት አይቻልም። ወረድ ብዬ በማስረጃ ለማሳየት እንደምሞክረው የአሜሪካን ዴሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዐቶች ብርቱ ችግሮች እየታዩበት ነው። ዴሞክራሲያዊ ሥርዐቱ ደንታ በሌላቸው ሰዎች (ራስ ጠቀሞች፣ ራስ አበልጥጎች) በመገዝገዝ ላይ ነው። ኢኮኖሚያዊ ሥርዐቱ ጥቂቶችን ብቻ የሚያበለጽግ በመሆኑ ቀውስ እየፈጠረ ነው። ከሌሎች የሚወሰድና የሚወረስ ሥርዐት እንዳለ ከተወሰደና ከተወረሰ ከእኛ ጋር ላይጋጠምና ላይዋደድ ይችላል። ስለዚህ ከሌሎቹ የምንወስደውንና የምንወርሰውን ዐውደ ገብ ማድረግ ያስፈልጋል። ይበልጥ መሳልና መጥፎ ጎኖቹን መጥረብ ያስፈልጋል።
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ብዙ ትኩረት የምሰጠው በዴሞክራሲ ምንነት ላይ ይሆናል። ብዙ ሳልሄድ አንድ ፈርጠም ያለ ዐዋጅ ልናገር። ዴሞክራሲ ማለትም እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚሠራው ቢያንስ አምስት ዋና ዋና ነገሮች ሲኖሩ ብቻ ነው። እነዚህ አምስት ነገሮች ከሌሉ ዴሞክራሲ ከቶ አይሠራም፤ ጥሩ ምኞት ብቻ ወይም ይስሙላ ይሆናል። ዴሞክራሲ እንዲሠራና ተግባሩን እንዲፈጽም 1) ነጻነት፣ 2) እኩልነት፣ 3) እውነት 4) ፍትሕ እና 5) ሕግ መኖር አለባቸው። እነዚህ የእውነተኛ ዴሞክራሲ መሠረቶችና እሴቶች ናቸው። ዝምድናቸውን በሚከተለው መንገድ እናጢን፤
ሥዕላዊ መግለጫው እንደሚያሳየው አምስቱ የዴሞክራሲ መሠረቶችና እሴቶች የእርስ በእርስ ዝምድና አላቸው። አንዱ ከሌላው ጋር ከመዛመዱም በላይ አንዱ ያለ ሌላው ትርጒመ ቢስ ነው። ደግሞም አንዱ ያለ መጠን መጉላትና ሌላውን መደምሰስ የለበትም። ሁሉም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መተሳሰር አለባቸው። ነጻነትና እኩልነት እንዲሰፍን የሚጮሁ ሁሉ እውነት፣ ፍትሕና ሕግ እንዲሰፍንም መጮህ አለባቸው። ርግጥ የዴሞክራሲ መሠረቶችና እሴቶች እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። ይሁንና እነዚህ ዐበይት፣ ምናልባትም ወሳኝ ከሚባሉት ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። የዜጎች ነጻነት መከበር እንዳለበት ሁሉ ዜጎች ሁሉ እኩል መሆናቸው መረጋገጥ አለበት። የዜጎች ግንኙነትና ንግግር (ክርክር) በእውነት ላይ መመሥረት አለበት። ፍትሕ በዜጎች መካከል መስፈን አለበት። ዜጎች ሁሉ ማንም ይሁኑ ምን ከሕግ በታች እንደ ሆኑ መታመን አለበት። ይህ ሲሆን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዐቶች መልክ ይይዛሉ፤ አደብ ይገዛሉ። በአንድ አገር ውስጥ ሰላም የሚሰፍነው እነዚህ ነገሮች ሲኖሩና ዜጎች ሁሉ የእነዚህን ነገሮች ወሳኝነት ሲቀበሉና ለእነርሱም ሲገዙ ነው። ከእነዚህ መካከል አንዱ ሲጎድል ሰላም ይጠፋል፤ በምትኩ ፍጅት ይነግሣል። ለዚህ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፤
ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ለእውነት ስፍራ ከሌላቸው ትርጒም ያጣሉ። ሸፍጥ፣ ሐሰትና አባይነት ለቅራኔ አልፎ ተርፎም ለዐመፅ ይዳርጋሉ። በተለይ ሥልጣናቸውን ወይም ሀብታቸውን ተተግነው የሚዋሹ ሰዎች በዜጎች መካከል ትምምን እንዳይኖር ትልቅ ጋሬጣ ይፈጥራሉ። ለምሳሌ የአሜሪካንን ዴሞክራሲ ለብርቱ አደጋ ካጋላጡ ክስተቶች አንዱ የፕሬዘዳንት ትራምፕ ሐሰተኛነት ነው።[14] ቀደም ሲል እንዳመለከትሁት እውነት ከዴሞክራሲ መሠረቶችና እሴቶች አንዱ ነው። እውነት ከሌለ ዴሞክራሲ ስንኩል ይሆናል። እንደሚታወቀው ፖለቲከኞች ይዋሻሉ። ለመመረጥ ሲሉ ደስ ደስ የሚሉ ተስፋዎችን የሚሰጡ መሪዎች አሉ (“ቱሪ ናፋ” “ስጥ በለው” እንዲሉ)። ድክመታቸውን ለመሸፈንና ተቀናቃኖቻቸውን ተቀባይነት ለማሳጣት ብሎም ለማስጣት ሲሉ የሚዋሹ መሪዎች አሉ። ለፖለቲካዊ ፍጆታቸው ሲሉ ነገሮችን አለቅጥ የሚያጋንኑ መሪዎች አሉ። ሥልጣን ለመጨበጥ ሲሉ ወይም ግላዊ ችግራቸውን ለመሸፈን ሲሉ ሆነ ብለው የሚዋሹ መሪዎች ግን የዴሞክራሲ ጠንቅ ናቸው። ፕሬዘዳንት ትራምፕ ሆነ ብለው ከሚዋሹ መሪዎች አንዱ በመሆኑ ለብዙ ዐሠርታት ሲወደስ የቆየውን የአሜሪካንን ዴሞክራሲ አደጋ ላይ ጥሏል። “ፕሬዘዳንቱ የለየለት ዋሾ” መሆኑን ብዙዎች በማስረጃ አረጋግጠዋል።[15] ፍርድ ቤቶችም ሐሰተኛነቱን በመመርመር ላይ ናቸው፤ በአንድ ወቅት የእርሱ ቀኝ እጅ የነበሩና ሸፍጡን ለመሸፈን የተጋደሉ ሁሉ ፍርዳቸውን ተቀብለው መከርቸሚያ ቀናቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ፕሬዘዳንቱን በተመለከተ ሁለት ዐበይት ማስረጃዎችን ልጥቀስ።
አንደኛው፤ በደቡብ የአገሪቱ ድንበር ላይ እሠራለሁ የሚለው ግምብ ነው። ገና ዕጩ ተወዳዳሪ ሳለ ይናገር እንደ ነበረው በደቡብ የአገሪቱ አዋሳኝ ቁመቱ ወደ 7 ሜትር የሚደርስ፣ ርዝመቱ ደግሞ ወደ 3,100 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ግምብ እንደሚሠራና ሙሉ ወጪውንም የሜክሲኮ መንግሥት እንደሚሸፍን በየአደባባዩ ተናግሮ (“ሸልሎ” እንዲሉ) ነበር። ኢላይ ስቶኮልስ የተባለ የMSNBC ጋዜጠኛ እንዳመለከተው ይህን በተግባር የማይተረጓም ሕልም ከ200 ጊዜ በላይ ተናግሯል፤ እንደ ስቶኮልስ አገላለጽ የፕሬዘዳንቱ ሽለላ እስኪቸክና አልፎ ተርፎም የአሜሪካንን ዴሞክራሲ እስኪያጠለሽ ድረስ ጧትና ማታ ለፍፎበታል። ሆኖም January 10, 2019 ከጋዜጠኖች ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው መልስ “እኔ ግምብ እሠራለሁ አልኩ እንጂ ወጪውን የሜክሲኮ መንግሥት ይሸፍናል ብዬ ጨርሶ አልተናገርኩም” ብሏል። ይብስ ብሎም “የገነባነው ውብ ግምብ እነሆ አልቋልና ደስ ይበላችሁ” የሚል ዜና በመናገር ላይ ነው። ያልተጀመረ ነገር እንዴት እንደሚያልቅ ግልጽ ባይሆንም፣ ፕሬዘዳንቱ ግን ያለምንም ኀፍረት “ጅምሩ ይለቅ” በማለት መግለጫ ሰጥቷል። በሁኔታው ግራ የተጋባ አንድ ዘጋቢ ትራምፕ ሐሰት እንጂ እውነት መናገር አይችልም በማለት የፕሬዘዳንቱ ቅጥፈት ምን ያህ አሳሳቢ መሆኑን አስታውቋል።[16] ፕሬዘዳንቱን በግል የሚያውቁት ሰዎች እንደ መሰከሩት ትራምፕ ያልሆነውን እንደ ሆነ አንድርጎ የሚናገር (sick narcissist)፣ ነገሮችን በሚሰቀጥጥ መንገድ የሚያገንና (shameless inflator) ሁልጊዜ የሚዋሽ (notorious liar/pathological liar) ሰው ነው።[17]
ሁለተኛው በየጊዜው የሚያደርጋቸው ንግግሮችና ትዊቶች ምን ያህል ዋሾ ሰው እንደ ሆነ እያጋለጡ ናቸው። ፕሬዘዳንት ከሆነበት ቀን አንሥቶ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ከአፉ የወጡትን ቃሎች በሙሉ ልቅም አድርጎ ያበጠረውና ያንጠረጠረው ጋዜጠኛ ዳንኤል ዴል እንደሚለው ፕሬዘዳንቱ አለቅጥ ዋሾ ነው። በ2017 ብቻ በቀን 2.9 ውሸቶችን ይናገር ነበር፤ በ2018 የውሸት መጠኑ ወደ 5.1 አድጓል። ከዚህም የተናሣ Lord of the Lies የሚል መጠሪያ ለፕሬዘዳንቱ እስከ መስጠት ተደርሷል። የውሸቱ መጠን በየዓመቱ እያደገ መምጣቱንና የእርሱ ውሸት ከኦባማ ውሸት ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል አስደንጋጭ እንደ ሆነም ብዙዎች በማስረጃ ለማሳየት ሞክረዋል።[18] በቅርቡ እንኳ አንድ ጋዜጠኛ የጁሊያን አሳንጅን (የዊኪሊክስ መሥራች) መያዝ በተመለከተ ለፕሬዘዳንቱ ጥያቄ አቅርባ ነበር። ፕሬዘዳንቱም “ስለ ዊኪሊክስ ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ የምፈልገውም ነገር አይደለም” ነበር ያላት። ፕሬዘዳንቱ ግን ዕጩ ተወዳዳሪ በነበረበት ወቅት ዊኪሊክስን በተመለከተ ከ140 ጊዜ በላይ ጠቅሷል፤ ድርጅቱንም በየመድረኩ አወድሷል።[19] በእጅጉ የሚያሳዝነው ግን አማካሪዎቹና ጠበቆቹ ስለ እውነት ያላቸው ግንዛቤ አለቅጥ መዝቀጡ ነው። እንደ አማካሪዎቹና ጠበቆቹ አባባል እውነት መለኪያና መስፈሪያ የለውም፤ እንዲያውም እውነት የሚባል ነገር የለም። ያለው የሰዎች አስተያየት ነው።[20] የፕሬዘዳንቱን ሐሰተኛነት ለመሸፈን ሲባል እንዲህ የሚዋሽ ከሆነ ዴሞክራሲ አደጋ ላይ ይወድቃል።
ከዚህ በመቀጠል አምስቱን የዴሞክራሲ መሠረቶችና እሴቶች አንድ በአንድ እናጤናለን። እነዚህ የዴሞክራሲ መሠረቶችና እሴቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲመጣ የሚታገሉ ወገኖች ሁሉ በቅጡ ሊያስቡባቸውና አቋም ሊወስዱባቸው የሚገቡ ነገሮች እንደ ሆኑ በብርቱ ለማሳሰብ እወዳለሁ። አለዚያ ትግሉ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሳይሆን ለይስሙላ ዴሞክራሲ ይሆናል። ልብ እንበል፤ ሥርዐት የሚቆመውና የሚገነባው ርእዮት ወይም ንጽረተ ዓለም ላይ ነው። ከሥሩ ወይም ከበስተጀርባው ርእዮት ወይም ንጽረተ ዓለም የሌለው ሥርዐት ልክ እንደ ጉም ነው። ወዲያው ታይቶ ወዲያው ይጠፋል። አለ ስንለው ይበንናል፤ ይበተናል። እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ መጮህና ዐደባባይ ወጥቶ መቃወም አንድ ነገር ነው። ቁጭ ብሎ በሰከነ ልቡና እንዲመጣ የምንፈልገውን ለውጥ ማሰብና ትክክለኛ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ሌላ ነገር ነው። ሥርዐት ልክ እንደ ቤት መሠረት ወይም መቆሚያ ያስፈልገዋል የሚባለው ለዚህ ነው። ሥርዐቱ የሚመራበትና የሚገፋበት ርእዮት ከሌለው የአንድ ሰሞን ጩኸት ብቻ ይሆናል። የሚበጅና የሚዘልቅ ሥርዐት እናቁም፤ ከዚያም ሥርዐቱ እንዲጎለብት እንከባከብ። ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ የሚተላለፍበት ሥርዐት መፍጠር ከቻልን መፈንቅለ መንግሥት አያስፈልግም። ግብግብና ጦርነት አያስፈልግም። መሪ/ፓርቲ በተለወጠ ቁጥር ሕገ መንግሥት አናረቅቅም። ይሁንና ቀጣይነቱ አስተማማኝ የሆነ ዴሞክራሲ ለመፍጠር ትልቅ ትጋት፣ ትዕግሥትና ትምምን ይጠይቃል።
ነጻነትንና እኩልነትን የሚያረጋግጠው ዴሞክራሲ እንደ ሆነ ገብቶን ይሆናል። ይሁንና የዴሞክራሲ መሠረቶችና እሴቶች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችን መገራትና መገዛት አለባቸው። ቀጣይነቱ አስተማማኝ በሆነ ዴሞክራሲ መሪው ማንም ሆነ ማን ሥርዐቱ ይቀጥላል። ርግጥ እንደ ትራምፕ ዐይነት አምባገነናዊ መሪዎች ሥልጣን የጨበጡ ዕለት ሥርዐቱ ይፈተናል። ዴሞክራሲ የሚጠቅመውን ያህል ሁልጊዜ ለብርቱ አደጋዎች ተጋልጧል ማለት ይቻላል። ለዴሞክራሲ መሠረቶችና እሴቶች ሳይሆን፣ ለፖለቲካዊ ጥቅም የሚጋደሉ መሪዎች ሲመጡ ሥርዐቱን ያናጋሉ። ትራምፕ ገና ለገና ሪፓብሊካን ነኝ ስላለ (ለፕሬዘዳንትነት ለመወዳደር እስከተነሣበት ጊዜ ድረስ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ዴሞክራት እንጂ ሪፓብሊካን ሆኖ አያውቅም) ሪፓብሊካኖች ዴሞክራሲያዊ ሥርዐቱን እያናጋው ዝም ብለው የሚመለከቱ ከሆነ ለሥርዐቱ ሳይሆን ለፖለቲካ ትርፍና ለግል ጥቅም እየተጋደሉ ነው። አንዳንዶቹ እንዲያውም ትራምፕን የሚደግፉት የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘምና ለማሰንበት ነው። አገር እየተናደና እየተደመሰሰና ዲሞክራሲያዊ ሥርዐቶችም እየተፈረካክሱ ሥልጣንን ለማራዘምና ለማሰንበት መጋደል በእውነተኛው ራስ ወዳድነት ነው። አንድዬ ለአገርና ለመጪው ትውልድ ከማይጨነቁ ባለሥልጣናት ይጠብቀን፤ ለራሳቸው ሳይሆን ለአገር ብልጽግና የሚቆሙ መሪዎች ይስጠን።
እንግዲህ እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምፈልገው ጊዜአዊ ጩኸት የትም አያደርስም። በቅጡ ተውጠንጥኖ ያላለቀ ትግል የትም አይሄድም። ይልቁንም አንድ ጊዜ ቁጭ ብለን በቅጡ እናስብ፤ የሚሠራና የሚዘልቅ ሥርዐት እናቁም። ከሕዝቡ ባህል እንዲሁም ከሕዝቡ አገራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታ ጋር የሚዛመድ አስተዳደር እናብጅ። ሁሉንም ነገር ከሌሎች ልንቀዳ አንችልም። የራሳችን አሻራ ያረፈበት ሥርዐት ያስፈልገናል። ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው እንዳለ ከውጭ የተቀዳ ዴሞክራሲ ሳይሆን ዐውደ ገብ ዴሞክራሲ ነው። ምንም ተባለ ምን የምንገነባው ዴሞክራሲ ከዚህ የሚከተለቱ መሠረቶችና እሴቶች ሊኖሩት ይገባል፤
ነጻነት ምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ነገሩን ከሁለት አቅጣጫ መመልከት አለብን። ቃሉን በጥሬው ትርጒሙ ስንመለከት ነጻነት ማለት ሐሳብን፣ ምኞትን፣ ራእይን ያለ ከልካይ መፈጸም ነው። ርግጥ ሰናይ ሐሳብ፣ ሰናይ ምኞትና ሰናይ ራእይ እንዳለ ሁሉ እኩይ ሐሳብ፣ እኩይ ምኞትና እኩይ ራእይ አለ። ነጻ የሆኑ ሰዎች ሐሳባቸውን በነጻነት ይገልጻሉ። ነጻነት ግን ባሪያ አለመሆን እንጂ መረንነት አይደለም።[21] ነጻ ነኝ የሚሉ ሰዎች ጨዋነት (ጨውነት) ያጡ ሰዎች አይደሉም። ነጻነት “እንደ ልቡ” መሆን አይደለም፤ ነጻነት ሕግ ዐልባ፣ ባህል ዐልባ፣ ኅሊና ዐልባ መሆንም አይደለም። ርግጥ ነጻነት የጨቋኝነት፣ በዝባዥነትና አፋኝነት ተቃራኒ ነው። ቃሉን ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር ስንመለከት ነጻነት ትድግና ማግኘት ነው፤ እኩልነት ነው። ሁለቱ እንዲያውም ከቶ አይነጣጠሉም። ነጻ የሆኑ ሰዎች ትድግና ያገኙና እኩልነት ያገኙ ሰዎች ናቸው። እኔ ነጻነት አለኝ የሚል ሰው ሌሎችም ነጻነት እንዳለቸው ይቀበላል፤ ይገነዘባል። የእርሱ ነጻነት በሌሎች ሲጣስ እንደሚያንገበግበው ሁሉ የሌሎች ሰዎችም ነጻነት መጣስ ያንገበግበዋል። ነጻ የወጣ ሰው ጌታ ልሁን፣ ልብለጥ፣ ልተልቅ፣ ልግነን፣ በሌሎች ላይ ልሠልጥን አይልም። ምክንያቱም በሌሎች ላይ መጌትየት የነጻነት ተቃራኒ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነጻነትን በተመለከተ እንደ ትልቅ አብነት ተደርጎ የቀረበው የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ነው። የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ባርነት ነጻ ከወጣ በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆኗል (ዘሌ 25፥42)። አሁን እስራኤላዊ ነኝ የሚል ሁሉ የአንዱ የእግዚአብሔር ባሪያ እንጂ የሌሎች ባሪያ አይደለም። ይህ የእግዚአብሔር ባርነት ወይም በሌሎች ምንባቦች አጠራር ርስትነት ሁሉንም እኩል አድርጓል። በእስራኤላውያን መካከል ሌሎችን ባሪያ ማድረግ ነውር የሚሆነው ሁሉም ከእግዚአብሔር የተነሣ እኩል በመሆናቸው ነው። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከሰዎች ባርነት ነጻ ካወጣ በኋላ መልሶ የሰዎች ባሪያ ማድረግ እኩልነታቸውን መንሳት ነው። እውነተኛ ነጻ አውጪ እግዚአብሔር ነው፤ እንዲያውም የመጀመሪያው ነጻ አውጭ እርሱ ነው። በእግዚአብሔር ነጻ የወጣ ሕዝብ ሌሎችን ልጨቁን፣ ልበዝብዝ፣ ልደፍጥጥ አይልም። እንዲህ ለማድረግ የሚያስቡ ካሉ በእግዚአብሔር እንዲህ ይባላሉ፤ “በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብጽ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች ታውቃላችሁ” (ዘጸ 23፥9)። በሌላ አባባል በአንድ ወቅት ባሪያ የነበረ ሌሎችን ባሪያ አያደርግም። ነጻነት አጥቶ ሲጮህ የነበረ ሌሎችን ነጻነት አይነፍግም። ባርነትን ያየ ለሌሎች ባርነትን አይመኝም። በዐጭሩ ነጻነት ያገኙ ሰዎች ነጻ ከወጡ በኋላ “አዲስ ጨቋኝ” አይሆኑም።[22] የነጻነት ትርጒሙና እንድምታው ሰፊ ነው። ነጻነት ሌሎችን ጥገኛና ተስፈኛ አያደርግም። ሌሎችን ጥገኛ ማድረግ ተጠቂና ተጎጂ ያደርጋቸዋል። ለተበዝባዥነትም የሚያጋልጣቸው የሌሎች ጥገኛ መሆናቸው ነው።
በእስራኤላውያን ዘንድ ራሳቸውን ለማኖር ሲሉ ራሳቸውን እንዲሸጡ የሚያደርግ ሥርዐት መፍጠር ሁልጊዜ ነውር ነው።[23] በብሉይ ኪዳን በተለይም በነቢያቱ ከተነሡት ጒዳዮች አንዱ ብዝበዛ ነው። ሌሎችን መበዝበዝ ነጻነታቸውን ብሎም እኩልነታቸውን መንሣት ነው። ብዝበዛ እጦተኛ ያደርጋል፤ ማጣት ደግሞ ከሌሎች ያሳንሳል። ሰዎችን ጥገኛ የሚያደርግ ኢኮኖሚያዊ ሥርዐት ውሎ ዐድሮ እጦተኛ ከዚያም ተበዝባዥ ባሪያ ያደርጋቸዋል። ሌሎችን መተናፈሻ አሳጥቶ ራስን ብቻ ማበልጸግና ማሳረግ ምንኛ መጥፎ ተግባር እንደ ሆነ ነቢያቱ አስጠንቅቀዋል፤ “ስፍራ እስከማይቀር ድረስ እናንተም በምድር ላይ ብቻችሁን እስክትቀመጡ ድረስ ቤትን ከቤት ጋር ለሚያያይዙ፣ ዕርሻንም ከዕርሻ ጋር ለሚያቀራርቡ ወዮላቸው” (ኢሳ 5፥8)። እዚህ ላይ ነቢዩ የሚያስጠነቅቀው በራስ አበልጽጎት ወይም በቀጥተኛው አባባል በራስ ወዳድነት አትመጠጡ፤ አትመጥመጡ ነው። ሌሎችን የማይቀበልና ለሌሎች ስፍራ የማይሰጥ ማኅበራዊ ሕይወት ሁልጊዜ አደገኛ ነው።
እዚህ ላይ ነጻነትን ከወቅቱ ሚዲያዎች ጋር አነጻጽረን ብንመለከት ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ። ዘመኑ ሰዎችን ሁሉ በሚያስገርም ፍጥነት አቀራርቧል። በአንድ አገር ወይም ቀዬ የተፈጠረ ክስተት ሳይውል ሳያድር በመላው ዓለም ይናኛል። ዕድሜ ለቴክኖሎጂ! የዜና አውታሮች በሌሉበት ቀዬ እንኳ የግለ ሰቦች እጅ ስልክ ከዜና ማሰራጫ ያልተናነሰ አገልግሎት ይሰጣል። ዛሬ ማንም ሰው ከቤቱ ሆኖ የፈለገውን ነገር ማሰራጨት ይችላል። እንግዲህ የዘመናዊው ኅብረተ ሰብ ትልቁ ፈተና እዚህ ላይ ነው። በተለይ ገንዘብና ጥቅም ከስርጭቱ ጋር ከተዛመደ ሌላ ራሱን የቻለ ብርቱ ፈተና ይሆናል። ሰዎች ገና ለገና ነጻ ነኝ ብለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዐቶችን የሚያናጋ “ሐሳብ፣ ምስል፣ ወሬ” የሚናኙ ከሆነ የራሳቸውንና የልጆቻቸውን ዓለም ለጥፋት አደጋ እየዳረጉ ነው።
በአሜሪካን አገር ሐሰት እየናኙ ሀብትና ጥቅም የሚያገኙ ሰዎች ከምንጊዜውም በላይ መብዛታቸው ምድሪቱን ቀውጧል። በተለይ ሕዝብን የሚያገለግሉ ሚዲያዎች የሐሰት ቋት ከሆኑ ውሎ ዐድሮ የሚጎዳው እነርሱን ብቻ ሳይሆን መላውን ኅብረተ ሰብ ነው። እውነተኛ ጋዜጠኞች እንዲሁም በሕዝብ መገናኛ አውታሮች ላይ የሚናገሩና የሚጽፉ ሰዎች በሙሉ ለእውነት ግድ ሊላቸው ይገባል። ጋዜጠኛነት የራሱ የሆነ ሙያና ሥነ ምግባር እንዳለው ይታወቃል። እኔ ስለ ሙያው መናገር አልችልም። ሆኖም ስለ ሥነ ምግባሩ መናገር ይቻላል። ጋዜጠኛ ወሬኛ አይደለም፤ ማለት በሚገባ ያልታሸና ያልተበጠረ ዘጋቢ አይደለም። ሥራው በሐቅ፣ በእውነትና በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ ትንተናዎችን ለሕዝብ ማቅረብ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጋዜጠኛነትን ከመምህርነት ጋር ማዛመድ ይቻላል። ሁለቱም አስተማሪዎች ናቸው፤ የሚያስተምሩት ግን እውነትን መሠረት አድርገው እንጂ “በሬ ወለድ” ዐይነቶች አይደሉም። ጋዜጠኛ እንደ መምህር ተመራማሪ እንጂ ቀባጣሪ አይደለም። ጋዜጠኛ ከሰዎች አንደበትና ብርዕ የሚወጡ ቃሎች ብርቱ ከዋኝነት እንዳላቸው ይገነዘባል፤ ለሚናገራቸውም ሆነ ለሚጽፋቸው ነገሮች በሙሉ ኀላፊነቱን ይወስዳል። “ቃል ብርቱ ኀይል አለው” የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው፤ ከሰዎች አንደበትና ብርዕ የሚወጡ ቃሎች ወይ ለአዎንታዊ ነገር ያነሣሣሉ፤ አለዚያም ለአሉታዊ ነገር ያነሣሣሉ። ሰላማዊነትን የሚያስተምሩ ሰዎች ሰላማዊ ሰዎችን ያፈራሉ። በአንጻሩም ጠበኛነትን የሚያስተምሩ ሰዎች ጠበኛ ሰዎችን ያፈራሉ።
ምንም ተባለ ምን ነጻነት ሥርዐት ዐልበኛ አይደለም። ነጻነት ያለ ኀላፊነት እንዲሁም መብት ያለ ተጠያቂነት ዋጋ የለውም። የነጻነት ዋጋው ኀላፊነት ነው፤ ምክንያቱም ኀላፊነት ነጻነት መረን እንዳይወጣ እንደ ልጓም ይሆነዋል፤ የመብት ዋጋው ተጠያቂነት ነው፤ ምክንያቱም መብት እንዳሻኝ ልሁን እንዳይል እንደ መግቻ ይሆነዋል። ነጻነት ካልተገራ፣ መብትም ካልተገደበ ለብርቱ ጥፋት ይዳርጋል። ነጻነት ምን እንደ ሆነ በትክክል የተረዱ ሰዎች ለተጠያቂነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጡ ሰዎች ናቸው። ጳውሎስ በነጻነትና በተጠያቂነት መካከል ያለውን ዝምድና በተመለከተ ብርቱ ምክንያት ያቀርባል። ምንም እንኳ የሙግቱ ዐውድ ሃይማኖታዊ ቢሆንም አሁን በዚህ ጽሑፍ ለምንዳስሰው ሐሳብም እንድምታው ወሳኝ ነው።
ጳውሎስ በ1ቆሮ 8-9 ላይ ነጻነትን ከራስ መግዛት ጋር አዛምዶታል። እንደ ጳውሎስ አባባል የነጻነት ትክክለኛው ትርጒም የበራላቸው ሰዎች ራሳቸውን የሚገዙ ሰዎች ናቸው። ራሳቸውን የሚገዙ ሰዎች ያልተገዛና ያልተገራ ነጻነት የሚያደርሰውን ብርቱ ጥፋት ይገነዘባሉ።[24] እንዳሻኝ እንዳፈተተኝ ልኑር ልናገር አይሉም። ትርጒም የማይሰጥና ሰዎችን የማይጠቅም ንግግር ማኅበራዊ ቀውስ እንደሚፈጥር ይረዳሉ። እናም ለእውነትና ለሚልቀው ፋይዳ ሲሉ ሁልጊዜ ራሳቸውን ይቆጥባሉ፤ ይገዛሉ፤ ይገራሉ። ነጻነት ተሳዳቢነትና ተዛላፊነት አይደለም። ነጻነት ጨዋነት ነው፤ ልከኛነት ነው፤ ቁጥብነት ነው፤ ሥልጡንነት ነው። የነጻነት ትርጒሙ የገባቸው ሰዎች ልዩነትን በአግባቡና በሥርዐቱ ያስተናግዳሉ። ማንኛውም ሰው የራሱ ሐሳብና አቋም እንዳለው ይታወቃል። ማለትም ማኅበረ ሰብነት እንዳለ ሁሉ ግለ ሰብነትም አለ። ይሁንና እንደ አንድ ማኅበረ ሰብ መሰባሰብና ለጋራ ዕድገት መጣመርና መጣጣር የምንችለው ነጻነታችን ልዩነታችንን በአግባቡ ሲያስተናግድ ነው። ከራስ ግላዊ ሐሳብና አቋም ይልቅ በኅብረት ለተደመርልነት አቋም ራሳችንን መስጠት ያቀባብላል። ነጻነት “በእኔነት” እና “በእኛነት” መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት ይረዳል። ለኅብረትና ለጋራ ዕድገት ወሳኙም እኔነት ሳይሆን እኛነት እንደ ሆነ ይገነዘባል። ስለዚህ መላውን ኅብረተ ሰብ ለሚጠቅመው ፋይዳ መትጋት ወሳኝ መሆኑን ይቀበላል።
እኩልነት ከሒሳባዊ ትክክልነት ጋር ምንም ዝምድና የለውም። እኩልነት ሲባል ሰው ሁሉ አንድ ዐይነት ቤት፣ አንድ ዐይነት ገቢ፣ አንድ ዐይነት የኑሮ ደረጃ ይኑረው ማለት አይደለም። እኩልነት ሲባል ሰዎች ሁሉ በማንነታቸው እኩል በመሆናቸው ምንም ነገር ሊነፈጋቸው አይገባም ማለት ነው። በአንድ አገር የሚኖሩ ዜጎች ለአገሪቱ ሲሳይ እኩል መብትና ዕድል አላቸው ማለት ነው፤ ሰዎች ሁሉ ለትምህርት፣ ለሥልጣን፣ ለብልጽግና፣ ወዘተ እኩል ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል ማለት ነው። የእኩልነት መሠረቱ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠራቸው ነው። በመሆኑም በሰውነት ደረጃ ማንም ከማንም አይበልጥም፤ ማንም ከማንም አያንስም። ዘርም ሆነ ቀለም እንዲሁም ጾታና ችሎታ የማንነት መለኪያ አይደሉም። እንዲህ ሲባል ልክ በሥላሴ መካከል እንዳለው ዐይነት ማለት ነው።
በሥላሴ መካከል በአምላካዊ ማንነት ላይ የተመሠረተ ማለትም ontological ልዩነት የለም (unity እንጂ)፤ ሆኖም በአምላካዊ ተግባር ላይ የተመሠረተ ማለትም functional ልዩነት አለ (diversity እንጂ)። በሌላ አባባል በአምላክነት እኩል ናቸው፤ በሥራ ወይም በተልእኮ ግን ልዩነት አላቸው። ይህ መበላለጥን ወይም መቀዳደምን አያሳይም። አምላካዊ ምሳሌው ወይም ሞዴሉ ግን በሰዎች ግንኙነት ውስጥ ተንጸባርቋል። ለምሳሌ ወንድና ሴት በሰውነት ማንነታቸው እኩል ናቸው። በተግባርና በተልእኮ ግን ልዩነት አላቸው። አካላዊ ቁመናቸውን ብንመለከት እንኳ ወንድና ሴት አንድ ዐይነት አይደሉም። በጾታቸውም እንዲሁ አንድ ዐይነት አይደሉም። አንድ ዐይነት አለመሆናቸው አያበላልጣቸውም። ይልቁንም ልዩ ልዩ ሥራና ተልእኮ እንዳላቸው ያሳያል። ሰዎች ሁሉ በማንነታቸው እኩል ቢሆኑም በተልእኳቸው ግን ልዩነት አላቸው። እኩልነት ይህን ልዩነት በቅጡ ይረዳል። ተልእኳዊ ልዩነት ማንነታዊ እኩልነትን አይደመስስም። እንደ እውነቱ ከሆነ ማንነታዊ እኩልነት የሚጎላው፣ የሚደምቀውና ውበት የሚኖረው በተልእኳዊ ልዩነት ነው።
በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ውስጥ እኩልነት ትልቅ ስፍራ አለው። በአንድ አገር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው ብለን ካልተነሣን ሁልጊዜ እንደ ተጋጨንና እንደ ተፋጨን እንኖራለን። ጾታ፣ ዘር፣ ብሔር፣ ቀለም፣ ሥልጣን፣ ወዘተ ሰዎችን ሊያበላልጥ አይገባም ካላልን አብረን መኖር አንችልም። ዕጣ ፈንታችን ሁልጊዜ መባላትና መበላላት ይሆናል። ጾታችን ምንም ሊሆን ይችላል፤ ብሔራችን ምንም ሊሆን ይችላል፤ የቆዳችን ቀለም ምንም ሊሆን ይችላል፤ ሥልጣናችንም ምንም ሊሆን ይችላል። በአንድነት አብሮ ለመኖር ወሳኙ በሰውነት ደረጃ ሁላችንም እኩል ሰዎች መሆናችን እንጂ ግላዊ መታወቂያዎች አይደሉም። የዜጎች እኩልነት ሳይረጋገጥ መደመርም ሆነ በአንድነት አገር መገንባትና መበልጸግ አይቻልም። በአንድ አገር ስንኖር ከሁሉ ለሚበልጠው ፋይዳ ራሳችንን ካላስገዛን፣ ማለትም ከዘር ይልቅ እኩልነት ይበልጣል ካላልን ወይም ከብሔር ይልቅ ሰውነት ይበልጣል ካላልን ተስፋ የለንም። መበላለጥ ባለበት ስፍራ ሁሉ ፍጭትና ግጭት አለ።
ለኢትዮጵያ የሚበጀው አያሌ ብሔር ብሔረ ሰቦች የሚኖሩባት አገር በመሆኑ አማራነት፣ ኦሮሞነት፣ ጉራጌነት፣ ትግሬነት፣ ወዘተ ከሰውነትና ከእኩልነት አይበልጥም የሚል አስተሳሰብ ነው። የታሪክ አጋጣሚ ሆነና አንዳችን አማራ ሌላችን ኦሮሞ ወይም አንዳችን ጉራጌ ሌላችን ትግሬ፣ ወዘተ ሆንን እንጂ የሁላችንም መነሻው ሰውነት ነው፤ ሁላችንም “አዳሜ” ነን። ሁልጊዜ መጉላትና መብለጥ ያለበት ሰውነት እንጂ ዘር ወይም ብሔር አይደለም። ዘር ወይም ብሔር ይብለጥ ካልን በአባታቸው አማራ እና በእናታቸው ኦሮሞ የሆኑ ሰዎች ምን ሊሆኑ ነው? የትኛው ዘራቸው በልጦ የትኛው ዘራቸው ሊያንስ ነው? ዘረኛነትና ብሔርተኛነት ለኢትዮጵያ ሥጋት የሆነው በዘርና በብሔር ላይ የተመሠረተ ርእዮት በአገሪቱ ላይ ስለናኘ ነው (የዘር ፖለቲካ ስለተሰበከ ነው)። ይህ እኩይ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ መቼም የማይረሳ ጠባሳ ቢሆንም፣ ፈቃደኞች ከሆንና ከሁሉ ለሚበልጠው ፋይዳ ራሳችንን ካስገዛን እኩይ አስተሳሰቡን መነጋግለን መጣል እንችላለን።
ሩቅ ሳንሄድ ዘረኛነት በሩዋንዳ ያደረሰውን ጥፋት እንመልከት። ዘረኛነት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያደረሰውን ጥፋት እንመልክት። ዘረኛነት ሰዎችን ከሰውነት ተራ ያወጣና ጨካኝ አውሬ ያደርጋቸዋል። ከእነርሱ ዘር ውጭ ያለ ሰው ሁሉ ሰው (የሰው ዘር) አይመስላቸውም። ሰው የሌሎችን አካል መፍለጥና መቁረጥ ከቻለ ከሰውነት ተራ ወጥቷል ማለት ነው።[25] የእኔ ዘር ከአንተ ዘር ይበልጣል ስንል የሌሎችን የመኖር መብት እየተጋፋን ነው። እነርሱም እንደ እኛ ሰው መሆናቸውን እየካድን ነው። የሰዎችን ሰውነት ስንክድ ለራሳችን ሉዓላዊ መብት እየሰጠን ነው። አሁን ያሻንን በሌሎች ላይ ለማድረግ አቅምና ጉልበት እናገኛለን። የሥነ ምግባር ምሁራን እንደሚገልጹት ለራስ “የተለየ ስፍራ መስጠት ይኸውም ራስን አተልቆ ሌሎችን ማተነስ” በሌሎች ላይ ለመሠልጠን ልዩ መብት ይሰጣል። ሰብአዊ መብት መጣስ፣ መጨቆን፣ መበዝበዝና አልፎ ተርፎም መግደል የሚመጣው የሌሎችን ሰውነትና እኩልነት ካለመቀበል ነው። ሰዎች ሁሉ እኩል በመሆናቸው መቀባበል እንጂ መወጋገድ አይጠቅምም ስንል በውስጣችን ሁልጊዜ የሚያደባውን ጨካኝ አውሬ እየተቃወምን ነው። ራሳችንን አተልቀን ሌሎችን ስንወግድ ግን ለማያባራ ወጋጅነት እንዳረጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ የሚመክረን እግዚአብሔር እንደተቀበለን እርስ በእርሳችን እንድንቀባበል ነው (ሮሜ 15፥7)። ዛሬ የዓለማችን ትልቁ ችግር መወጋገድ ነው። ሚሮስላቭ ቮልፍ በትክክል እንዳመለከተው “ወጋጅነት በመቀባበል” (“embrace as a response to the problem of exclusion”) ካልተተካ የችግራችን ዑደት እየባሰ ይቀጥላል።[26]
ሕግ አደብ ያስገዛል፤ ሥርዐት ያስይዛል፤ ወይም ልክ ያስገባል። ሰዎች ከሕግ በላይ ለመሆን እንደሚከጅሉ ወይም ወንጀል እንደሚፈጽሙ እሙን ነው። እናም ፍጹም የሆነ ሰው ወይም ፍጹም የሆነ ማኅበረሰብ የለም። ሰዎች ያጠፋሉ፤ ይቀጥፋሉ፤ የራሳቸውን ጥቅም ያስቀድማሉ። ነገሩን ከክርስትና ንጽረተ ዓለም አንጻር ከተመለከትነው ሰዎች የሚኖሩት በወደቀ ዓለም ነው። ኀጢአት የሰዎችን ማንነት ብቻ ሳይሆን የሰዎችን ግንኙነትም አበላሽቷል። እናም ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ነገር ያደርጋሉ። ጉቦ፣ ስርቆት፣ ግድያ፣ ዝርፊያ፣ ቅሚያ፣ ወዘተ በአንድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ የሚፈጸሙ የዕለት ተዕለት ክስተቶች ናቸው። እነዚህ ተግባሮች ግንኙነቶችን ያበላሻሉ። በተለይ በሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች በእነዚህ ተግባሮች ከተጠመዱ መላውን ማኅበረ ሰብ ያውካሉ። በመሆኑም የአንድ ማኅበረ ሰብ ጤንነቱ የሚጠበቀው የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ ነው። የሕግ የበላይነት ተረጋግጧል በሚባሉ አገሮች እንኳ ሕግ ይጣሳል፤ ባለሥልጣኖችና ባለጠጎች እንዲሁም ዝነኞች ከሕግ በላይ እንደ ሆኑ የሚመስላቸው ጊዜ አለ። ርግጥ የሕግ መጣሻው መንገድ እንደ ማኅበረ ሰቡ ዐይነት ቢለያይም ጉቦ፣ ዝና፣ ዝምድናና ሥልጣን ዐበይት ሕግ መጣሻ መንገዶች ናቸው። ጉቦ፣ ዝና፣ ዝምድናና ሥልጣን ሰዎችን ከሕግ በላይ ሊያደርጋቸው አይገባም። እነዚህ ነገሮች ሰዎችን ከሕግ በላይ የሚያደርጓቸው ከሆነ ድኾችና ምስኪኖች ይጎዳሉ፤ ይበደላሉ። ማኅበራዊ ግንኙነቶችም ይቃወሳሉ፤ ይታወካሉ። በዚህ ዐይነት የሰዎች ነጻነት ይገፈፋል፤ እኩልነት ይረገጣል። ነጻነትና እኩልነት ሲጠፋ ደግሞ ቅራኔ ብቻ ሳይሆን ጥላቻና ሽኩቻ ይነግሣል። ሰዎች ከሕግ በላይ ሲሆኑ ዳኝነት ይዛባል፤ ፍትሕ ይጓደላል።
ኢትዮጵያውያን የሕግ የበላይነት ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ በቅጡ ሊገባን ያስፈልጋል። ርግጥ በእኛ ባህል “በሕግ አምላክ” የሚል አባባል አለ። አባባሉ “ኧረ አምላክን ፍራ” ለማለት ቢሆንም፣ አምላክ ሕግ ካለው በእርሱ አምሳል የተፈጠሩ ሁሉ ሕግ ሊኖራቸው ይገባል የሚል እንድምታ ሳይኖረው አይቀርም። ሕግ አድልዎ/መድልዎ እንዳይኖር ብቻ ሳይሆን ፍትሕ እንዲረጋገጥ ያደርጋል። በዳይ የእጁን እንዲያገኝ ተበዳይም እንዲካስ ያደርጋል። እንደ እውነቱ ከሆነ የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ በዳይና ተበዳይ እንዳይበዙ መግቻ ወይም ልጓም ይሆናል። ይሁንና ቀደም ሲል እንዳመለከትሁት ሰዎች ችግር አለባቸው። በእያንዳንዳቸን ውስጥ ሁልጊዜ የሚያደባ ዐመፅ/ዐመፀኛነት አለ። የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በሁላችንም ውስጥ የጥፋት እሳት አለ። የጥፋቱ እሳቱ ተዳፍኗል እንጂ ጨርሶ አልጠፋም። አንድ ቀን በምክንያት ሲገለጥ ይቀጣጠልና ጉዳት ያደርሳል። ሕግ ካለ ቢያንስ እሳቱ እንደ ተዳፈነ እንዲኖር ያደርጋል።
መቼም የሕግ መኖር በብቻው ዋስትና እንደማይሰጥ ይታወቃል። ዋስትና የሚሰጠው በሕግ የሚያምን ኅብረተ ሰብ ሲኖር ነው። በሕግ የሚያምን ኅብረተ ሰብ ለሕግ ይገዛል። በሕግ የሚያምን ኅብረተ ሰብ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልገው በኀይልና በዐመፅ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ነው። ጥይት ሳይተኩሱና ሰይፍም ሳይመዙ የሚፈልጉትን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል እነ ኔልሰን ማንዴላና እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ አሳይተውናል። በቀልና መወጋገድ ሳይሆን መቀባበልና ይቅር መባባል እንደሚጠቅም አሳስበውናል። እኔ እንደሚመስለኝ በእጅጉ የሚጣፍጠው ድል በሰላማዊ መንገድ የሚገኝ ድል ነው። ማንዴላም ሆነ ሉተር ሁለቱም ሰላማውያን ነበሩ። ዐመፅ፣ በቀልና ሰይፍ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንደማይችሉ ተረድተው ነበር። በበቀል፣ በኀይልና በዐመፅ ጊዜአዊ ለውጥ ማምጣት ይቻል ይሆናል። በዚህ ዐይነት የሚመጣ ለውጥ መሠረቱ በቀል፣ ኀይልና ዐመፅ በመሆኑ ተመልሶ ዑደቱ ያው በቀል፣ ኀይልና ዐመፅ ይሆናል። ሚሮስላቭ ቮልፍ ተመክሮን መሠረት አድርጎ እንዳመለከተው “ዐመፅ ዐመፅን ይወልዳል”፤ ሰይፍም ሰይፍን ይወልዳል (“ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ኢየሱስ በማቴዎስ 26፥52 ላይ እንዳመለከተው)።[27] የሚሻለው በሰላማዊ መንገድ መታገልና መፋለም ነው።[28] እንግዲህ ግለ ሰቦች፣ ፍርድ ቤቶችና ተቋሞች ለሕግ የበላይነት ያላቸውን አስተያየት መፈተሽ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የሕግ የበላይነት ሲሰፍን የሰዎች ግንኙንት ይሰምራል።
ፍትሕ ጥልቅ እሳቤ የሆነውን ያህል እጅግ ወሳኝ መርሕ ነው። በመጀመሪያ ስለ ፍትሕ ስንነጋገር ከሁሉ አስቀድሞ ራሳችንን የምናቆምበት ወይም የምንተክልበት ስፍራ ማለትም መርሕ ያስፈልገናል። ሚሮስላቭ ቮልፍ እንደሚለው “Nobody stands nowhere. Most of us stand in more than one place” (በግርድፉ “ማንኛችንም ያለ መቆሚያ ስፍራ አይደለንም፤ ብዙዎቻችን ግን ከአንድ በላይ መቆሚያ ስፍራ አለን”)።[29] በሌላ አነጋገር ሁላችንም ነገሮችን የምንመለከትበት አንጻር አለን። አንዳንዶች ነገሮችን ከባህል አንጻር ይመለከታሉ፤ ሌሎች ከእምነት አንጻር ይመለከታሉ፤ ሌሎች ከዕውቀትና ከልምድ አንጻር ይመለከታሉ። ብቻ ሁላችንም ነገሮችን መመልከቻ አንጻር/መነጽር አለን። ሁላችንም መቆሚያ ስፍራ አለን። ነገሮችን መመልከቻ አንጻር የሌለው ሰው ለመኖሩ ያጠራጥራል። ለምሳሌ ክርስቲያኖች ነገሮችን የሚመለከቱት ከቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት አንጻር፣ በተለይም እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በዚህ ዓለም ካከናወነው ተግባር አንጻር ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች ስለ ፍትሕ ሲናገሩ የቆሙበት ስፍራ አላቸው ማለት ነው፤ ሌሎችም እንዲሁ። እኔ ክርስቲያን በመሆኔ ነገሮችን የምመለከተው ከክርስቲያናዊ አስተምህሮዎች አንጻር ነው።
በክርስትና ትምህርት ፍትሕ፣ ፍቅርና ይቅርታ ትልቅ ስፍራ አላቸው። ፍትሕን የሚራቡ ፍቅርንና ይቅርታንም መራብ አለባቸው። ፍትሕ በብቻው ወይም ፍቅርና ይቅርታ በብቻቸው መቆም አይችሉም። አንዱ ከሌላ ጋር መጋባትና መጣመር አለበት። ወይም አንዱ ሌላውን መግራት አለበት። ይሁንና ነገሩን ከእግዚአብሔር አንጻር ከተመለከትነው ሁልጊዜ የሚበልጠው ፍቅር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር “በነውነት” ደረጃ የተነገረው “ፍቅር ብቻ ነው”። ማለትም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” (1ዮሐ4፥16) ተብሎ ሲነገር “እግዚአብሔር ፍትሕ ነው” ወይም “እግዚአብሔር ይቅርታ ነው” ተብሎ አልተነገረም። ፍቅር ተበድሎ እንኳ ይቅር ይላል። ፍቅር እንዲያውም በደልን አይቆጥርም። በዳይ የእጁን ካላገኘ አልመለስም አይልም። በኢየሱስ ትምህርት መሠረት የእርሱ ተከታዮች “ጠላቶቻቸውን መውደድ” አለባቸው (ማቴ 5፥44)። ኢየሱስ በዚህ አባባሉ ፍቅርን ከፍትሕ አስበልጧል። ፍትሕ እንዳለ ይታወቃል (“ዐይን በዐይን” ወይም “ጥርስ በጥርስ”)። ሰዎች ያጡት ፍቅር ነው፤ ያውም ጠላትን የሚወድድ ፍቅር። ይህ አዲስ ትምህርት ምናልባትም አብዮት ነው። ኢየሱስ በበቀል ላይ ዐምፁ፣ አብዩ ይለናል። በመሆኑም ፍቅርንና ይቅርታን አክስመው ፍትሕን ብቻ የሚያጎሉ ሰዎች በቀለኛነት እንዳይነግሥባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።[30] ትላንት ተበድያለሁና ዛሬ ልበድል ማለት ወይም ትላንት ተበዝብዤአለሁና ዛሬ ልበዝብዝ ማለት ትልቅ ስሕተት ነው።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ጠላትነት ወይም ባላንጣነትና ባላጋራነት ብሔር ብሔረ ሰቦችን አተራምሷል። በዘርና በመደብ ላይ የተመሠረተ ርእዮትና ፖለቲካ በመናኘቱ በሕዝቦች መካከል መቀባበል ጭንቅ ሆኗል። አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር የሚመለከተው በጥላቻ ዐይን ነው። ግልጡን እንነጋገር ከተባለ “አማራ ሌላውን ብሔር ሲጨቁን ኖሯል” በሚል አማሮች በሙሉ እንዲጠሉ ተደርጓል። ርግጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ነገሥታቱና መኳንንቱ በአብዛኛው አማሮች ነበሩ። ለአገሪቱ ጥሩ የሠሩ እንደ ነበሩ ሁሉ መጥፎም የሠሩ ነበሩ። ነገር ግን ዘረኞች አልነበሩም፤ በዘር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካም አላራመዱም።
ከዚህ በፊት አማራ ገዝቷል፤ ቀጥሎም ትግሬ ገዝቷል፤ አሁን ተራው የኦሮሞ (ወይም የሌላ) መሆን አለበት የምንል ከሆነ ለዘር ፖለቲካ እጃችንን እየሰጠን ነው። የዘር ፖለቲካ አይጠቅምም። በመደብ ላይ የተመሠረተ አገዛዝ ፍትሐዊ አይሆንም። የምንጠላውን መጥፎ ዑደት ለመድገም ካልሆነ በስተቀር ዘረኛነትና ብሔርተኛነት አይበጅም። ፍትሕ ዘረኛነትንና ብሔርተኛነትን የሚያስተናግድ ስፍራ የለውም። ትላንት ተጨቁኜ ስለነበር ዛሬ ልጨቁን የምንል ከሆነ አዲስ የጭቆና ዑደት እንጋብዛለን። የራስን ዘር ማተለቅና ማስበለጥ ኢፍትሐዊነት ነው። ሌሎችን የማንቀበልና ለሌሎች ስፍራ የማንሰጥ ከሆነ ፍትሓውያን ልንሆን አንችልም። ሌሎችን ማግለልና ዕድል ማሳጣት ወደ ጨቋኝነትና በዝባዥነት ይወስዳል።
እንግዲህ እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ ሌሎችን ለመቀበልና ከእኛ እንደ አንዳችን አድርገን ለመቁጠር አቅም አለን ወይ? የሌሎችን መቆሚያና መመልከቻ አንጻር የሚያስተናግድ፣ ካስፈለገም የሚያቻችል ስፍራ አለን ወይ? የሚለው ነው። ሌሎችን አለመቀበልና የሌሎችን መቆሚያና መመልከቻ አንጻር አለመገንዘብ ነገሮችን ለማቻቻልና ከሆነልንም ለማስታረቅ በምናደርገው ጥረት ትልቅ መሰናክል ይሆናል። ወደ አንድ መልካም ደረጃ ለመድረስ የምናደርገው ድርድርና ክርክር ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። የሚጎዳው እኔ ልብለጥ አንተ እነስ/ኮስስ ወይም እኔ መቆሚያ ውስጥ ካልገባህ ወግድ የሚል አስተሳሰብ ነው። በቅን ልቡናና መንፈስ ስንደራደርና ስንከራከር እንሟረዳለን፤ ስንገፋፋና ስንወጋገድ ግን እንጠፋፋለን። ልበ ሰፊነት አንዱ የፍትሕ ገጽታ ነው። ሌሎችን ስፍራ ማሳጣት ሰብእናቸውን ይገፍፋል። ወይም መስተናገድ ያለበት የእኔ ሐሳብ ብቻ ነው ማለት ሌሎችን ነጻነት ይነፍጋል። አለን ብሉም እንደሚለው “በዚህ ዓለም የመጨረሻው ጨቋኝ ሥርዐት ሌሎችን የሚያፍን፣ የሚገድብና አልፎ ተርፎም የሚያስወግድ ሥርዐት ሳይሆን፣ ሌሎች አማራጮች እንዳሉ የሚነፍግ ሥርዐት ነው”።[31] ሌላ አማራጭ የለም፤ ሌላ ሐሳብ የለም፤ ነገሮችን የምንመለከትበት ሌላ አንጻር የለም፤ እኔ ያቀረብሁት ሐሳብ ብቻ ነው መስተናገድ ያለበት ማለት ከትዕቢት አልፎ ኢፍትሐዊነት ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር የቀረበው የፍትሕ አምላክ ሆኖ ነው። ፍትሕ ሌሎችን አይበድልም፤ አይጨቁንም፤ አይበዘብዝም፤ አይወግድም። ይልቁንም ሌሎችን በምሕረት ዐይን ይመለከታል። በሌሎች ውስጥ አንድ የሚጠቅም ነገር እንዳለ ይመለከታል። ለሌሎች ዕድል ይሰጣል፤ ለሌሎች ስፍራ ይሰጣል። ነቢያቱ የእስራኤልን ማኅበር ሲያሳስቡ “ፍርድን/ፍትሕን አጽኑ”፤ (አሞጽ 5፥15)፤ “ፍርድን/ፍትሕን አድርጉ” (ሚክ 6፥8) ይላሉ። በሌላ ስፍራ “ፍርድ/ፍትሕ እንደ ውኃ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ” (5፥24)። “እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፣ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፣ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን?” (ኢሳ 58፥6) ይላሉ። በመሠረቱ እግዚአብሔርን ማወቅ ፍትሕ አድራጊነት ነው። በትንቢተ ኤርሚያስ ውስጥ በግልጽ እንደ ተነገረው እግዚአብሔርን የሚያውቁ ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋሉ፤ የተበደለውንና የተጨነቀውን ያድናሉ፤ መጻተኛውንና ደኻ አደጉን ከጉልበተኞች እጅ ያስጥላሉ (ኤር 22፥3)። ራሱ እግዚአብሔር እንደ መሰከረው “ይህ ነው እርሱን ማወቅ” (ኤር 22፥16)። ፍትሕ ጭቆናና ብዝበዛ እንዳይሰፍን ይከላከላል።
እንደሚታወቀው ብዙ ዐይነት ጭቆናዎችና ብዝበዛዎች አሉ። አሁን ከምንጊዜውም በላይ የተንሰራፋው ኢኮኖሚያዊ ጭቆናና ብዝበዛ ነው። ይህን በጥቅሉ ማኅበራዊ ኢፍትሓዊነት (social injustice) ልንለው እንችላለን። ለሠራተኞች ተመጣጣኝ ክፍያ አይሰጣቸውም። ደመወዛቸውም ቢሆን በጊዜውና በሰዓቱ አይከፈላቸውም። ትርፍ እስካመጡ ድረስ ሰብእናቸው ስፍራ የለውም። የሚታወቁትም በሰብእና ደረጃ ሳይሆን በቁጥር ደረጃ ነው። የሠራተኞችን ሰብእና ከግምት ሳያስገቡ መሥሪያ ቤቱ እንዴት ትርፋማ እንደሚሆን ብቻ ስልት ለሚነድፉ ግለ ሰቦች የሚሰጣቸው ክፍያ ለማመን አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ርግጥ የካፒታሊዝም ግቡ ትርፋማነት ብቻ ነው። ይህ ግን መሰንበት የሚችል አስተሳሰብ አይደለም። አሁን እንኳ በብዙ ካፒታሊስት አገሮች ችግሩ አፍጥጦ እየመጣ ነው። ትርፋማነት የተመሠረተው ሌሎችን በማክሰር ላይ ከሆነ የሥርዐቱ ዕድሜ ዐጭር ነው። ብዙዎችን አክስሮና አደኽይቶ ጥቂቶችን ብቻ የሚያበለጽግ ኢኮኖሚ እንዴት ሊወደስ እንደሚችል ከቶ አይገባኝም። ለእንዲህ ዐይነቱ ሥርዐት የሚሟገቱ ሰዎችም ምክንያታቸው አይገባኝም። ለሐቅና ለእውነት ስፍራ የማይሰጥ ከሁሉ በላይ ግን ለምሕረትና ለቸርነት ግድ የማይሰኝ ሥርዐት እኩይ ወርሶታል ወይም ሰይጥኗል ለማለት ያስደፍራል።
እዚህ ላይ ነገሩን ለማስረዳት ማኅበራዊ ኢፍትሓዊነት እያደረሰ ያለውን አሳዛኝ ክስተት እንመልከት። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ የካፒታሊዝም ዕድሜው ከ500 ዓመታት አይበልጥም። ይህ ሥርዐተ ማኅበር እንደ አሜሪካን በመሳሰሉ አገሮች ለምእተ ዓመታት ቢወደስም ራሱን መለወጥና ወሳኝ ፍትሐዊ ጥያቄዎችን መመለስ ባለመቻሉ መጥፊያውን አርግዟል። ሥርዐቱ በቶሎ ራሱን ማደስ ካልቻለ ራሱን በራሱ የሚያጠፋበት ጊዜ ተዳርሷል። ለዚህ አባባል ከሚሰጡ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ጥቂቶችን ብቻ በሚያበለጽግና በሚያሳርግ ርእዮት ላይ የተመሠረተ ሥርዐት መሰንበት ወይም መጽናት አይችልም የሚለው ነው። ከሁሉ የከፋው ግን ይህ እውነታ ለሥርዐቱ አቀንቃኞች አለመገለጹና ሊያባንናቸው አለመቻሉ ነው።[32]
በቅርቡ ይፋ የሆነውን የኦክስፋም ሪፖርት ብንመለከት የ26 ግለ ሰቦች ሀብት 50% (3.8 ቢሊዮን) ከሚሆነው የዓለም ሕዝብ ሀብት ጋር ተመጣጥኗል። የእነዚህ 26 ግለ ሰቦች ሀብት በዓመት 12 በምቶ እያደገ ሲሄድ የምስኪኖቹ በ11% እያሽቆለቆለ መጥቷል።[33] በዐጭሩ ጥቂቶች እጅግ አለመጠን ሲበለጥጉ ብዙዎች እጅግ አለመጠን አጥተዋል፤ ደኻ ሆነዋል። በዚህም በባለጠጎቹና በምስኪኖቹ መካከል ያለው የሀብት ልዩነት በእጅጉ እየሰፋ መጥቷል። ይህ አለመመጣጠን ማንንም ባለአእምሮ ሊያሳስብ የሚገባ ኢኮኖሚያዊ ኢፍትሐዊነት ነው። የባለጠጎቹ ቁጥር በእጅጉ ትንሽ መሆኑ ባንጻሩም የድኾቹ ቁጥር በእጅጉ ትልቅ መሆኑ ሥርዐቱን ለመፈረካከስ አደጋ አጋልጧል። እንግዲህ ለማንም ግልጽ እንደሚሆነው እንዲህ ዐይነቱ ሥርዐት ዕድሜው ዐጭር ነው፤ መሰንበትም ሆነ መቀጠል ወይም መዝለቅ አይችልም።[34] ሥርዐቱ በቶሎ ራሱን ካላደሰና በፍትሐዊ ኢኮኖሚ ራሱን ካልለወጠ ራሱን በራሱ ለማጥፋት ተዘጋጅቷል ማለት ይቻላል።
የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚሉት እስከዛሬ ድረስ የነበሩ ሥርዐተ ማኅበሮች የተወገዱት ከእነርሱ በኋላ በመጡ ጉልበተኛ ሥርዐተ ማኅበሮች ነው። ካፒታሊዝም ግን በሌላ ሳይሆን በራሱ ይወገዳል፤ ምክንያቱም መጥፊያውን አርግዟል። ለምሳሌ የእነ IMF እና World Bank ሥራ ድኻ አገሮች ከድኽነታቸው እንዳይወጡ ማድረግ ከሆነ የበለጸጉ አገሮችን፣ ማለትም የካፒታሊስት አገሮችን ጥቅም የሚያስከብሩት ለጊዜው ነው። እንደሚባለው ከሆነ የእነዚህ ተቋሞች ትልቁ ሥራ ድኻ አገሮች ከድኽነታቸው እንዳይወጡ፣ ይልቁንም በዚያው በድኽነታቸው ሁልጊዜ ጥገኞች እንዲሆኑ ማድረግ ነው። በእውነተኛው እንዲህ ዐይነቱ ሥርዐት አይሰነብትም፤ ራሱንም ማቆየት አይችልም። ለዚህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንመለከተው ፍልሰት አንዱ ማስረጃ ነው። ከድኻ አገሮች ወደ ብልጹግ አገሮች የሚደረገው ፍልሰት ለምን በየጊዜው ጨመረ ቢባል የድኻ አገሮች ድኽነት ጥልቅ መሆኑ ነው። እዚህ ላይ የዎልተር ብሩግማንን ምክር ብናደምጥ ይጠቅመናል፤[35] በዚህም የካፒታሊስት አገሮች የፈጸሙትን ስሕትተ ከመድገም እንቆጠብ ይሆናል የሚል አስተያየት አለኝ።
ብሩግማን ካፒታሊዝምን የሚያነጻጽረው ከመጣጭነትና ከመጥማጭነት ጋር ነው። እንደ ብሩግማን አባባል ካፒታሊዝም አለቅጥ መጣጭ ነው (ነጣቂ ወይም ዘራፊና ገፋፊ ነው)። ሥርዐቱ ሀብት የሚያጋብሰው ከድኾች እየነጠቀና እየዘረፈ ነው። በባለጠጎች ኪስ የሚገኘው ገንዘብ ከድኾች ኪስ የተዘረፈ ገንዘብ ነው። ብሩግማን ለዚህ አባባሉ የሚጠቅሰው ብዙዎች የሚጠቅሱትን እውነታ ነው። በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካን አገር በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች (middle class) ቊጠር እየጠፋ ነው። ቀደም ሲል የኑሮ ደረጃው 1) ብልጡግ 2) መካከለኛ 3) ደኻ ነበር። አሁን “መካከለኛ” የኑሮ ደረጃ እየጠፋ መጥቷል። ሥርዐቱን ለመፈረካከስ አደጋ እንዲጋለጥ ያደረገው ብዙዎችን አሳጥቶ ጥቂቶችን የሚያናጥጥ ብሎም የሚያሳብጥ ሥርዐት መፈጠሩ ነው። እንዲህ ዐይነቱ ሥርዐት ደግሞ ከቶ አይሰነብትም። ዐመፅና ወንጀል ይፈለፍላል።
እውነት የሽንገላ ተቃራኒ ነው። ሽንገላ ሐሰተኛነትና አታላይነት ነው። አንድ አገር ወይም ትውልድ ለእውነት የሚሰጠው ስፍራ በወረደ ቁጥር ግንኙነቶቹ ሁሉ እየተበላሹ ማለትም እየነቀዙ ይመጣሉ። ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዐቶች በእውነት ካልተቃኙ በጭራሽ መግባባት አይቻልም። በመሠረቱ እውነት ፈላጊዋን ትሻለች። እውነተኞችና እውነት በውስጣቸው የነገሠ ሰዎች ለእውነት ትልቅ አክብሮት ስላላቸው እውነት ወደምትወስዳቸው ስፍራ ለመሄድ አይፈሩም። ምክንያቱም ኢየሱስ እንደ ተናገረው “እውነት አርነት ያወጣል” (ዮሐ 8፥32)። ለእውነት ደንታ ቢሶች መሆን ግን ትልቅ አደጋ አለው። ነቢዩ ሕዝቅኤል ለእውነት ደንታ ቢስ መሆንን ያዛመደው ከዐመፀኛ ቤት ጋር ነው። “የሰው ልጅ ሆይ፤ በዐመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፤ ያዩ ዘንድ አይን አላቸው፤ እነርሱም አያዩም፤ ይሰሙ ዘንድ ጆሮ አላቸው፤ እነርሱም አይሰሙም፤ እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና” (ሕዝ 12፥2-3)። ሕዝቅኤል “ዐመፀኛ ቤት” የሚለውን ኤርምያስ “በሽንገላ መካከል” መቀመጥ ይለዋል (9፥6)።
በሽንገላ መካከል የሚቀመጡ ሰዎች እውነት አይናገሩም፤ ይልቁንም ምላሳቸው የለመደው ሐሰት መናገር ነው (ኤር 9፥4-5)። ሐሰት ዐይንን ያሳውራል፤ ጆሮን ያደነቁራል። ሰዎች ዐይን እያላቸው ካልተመለከቱ፣ ጆሮ እያላቸው ካልሰሙ ትልቅ ችግር አለባቸው ማለት ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሂትለር ቀኝ እጅና በኋላም የጦር ሚኒስትር የነበረ ሰው ለምን ከክፋት ጎን እንደ ቆመ ሲናዘዝ ያን ሁሉ ግፍ እንዳላይ “ዐይኔን ጨፍኜ ነበር” ብሏል።[36] የትራምፕ ጠበቃ የነበረውና ሦስት ዓመት ተፈርዶበት እስሩን በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ማይክል ኮኸን ለትራምፕ ሲል እንዴት ወንጀል እንደ ፈጸመ ሲናገር “ጭፍን ታዛዡ ነበርሁ” ብሏል። ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ “እውነትን በዐመፃ በሚከለክሉ [በሚያፍኑ፣ በሚከድኑ፣ በሚረግጡ]” (1፥18) የሚለው እንደዚህ ዐይነት ሰዎችን ነው። እውነት በሐሰት ከተረገጠ ማለትም ከተከደነ፣ ከተዳፈነ ወይም suppress እና tyrannize ከተደረገ ግንኙነቶች ይመሳቀላሉ። ሐሰተኛነት ትምምንን ያሳጣል። ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ጥርጣሬ እንዲነግሥባቸው ያደርጋል። ሰዎች ካልተማመኑ አንድነት ያጣሉ፤ አብሮ ለመሥራት ይቸገራሉ። አባቶች “የተናገሩት (ቃል) ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” እስከ ማለት የደረሱት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። “ቃል የእምነት ዕዳ ነው” የሚል አባባልም አላቸው። እነዚህ አባባሎች ለእውነተኛነት ያላቸውን ስፍራ ያሳያሉ። በዐጭሩ ሐሰት ያውካል፤ እውነት ግን ያንጻል።
በአንድ አገርና ማኅበረ ሰብ ውስጥ እውነት ካልነገሠ ብዙ ጉዳቶች ይደርሳሉ። ሚሮስላቭ ቮልፍ እውነትንና ሐሰትን ምስል ከሳች በሆነ መንገድ አነጻጽሯቸዋል።[37] እውነትን በተዘረጉ እጆች ሲመስል፣ ሐሰትን ከአፎቱ በወጣ ሰይፍ መስሏል። የተዘረጉ እጆች ያቅፋሉ፤ ያስጠጋሉ፤ ያቀርባሉ። ከአፎቱ የወጣ ሰይፍ ግን ያቃርናል፤ ያወጋግዳል፤ በላውህ እያለ ያስፈራራል። ልብ እንበል፤ እውነት ሲደመሰስ ሥነ ምግባርም ይደመሰሳል፤ ሥነ ምግባር ሲደመሰስ የሐቅና የሐሰት ድንበር ይደመሰሳል፤ የሁለቱ ድንበር ሲደመሰስ የሰዎች ግንኙነት መላቅጡ ይጠፋል። አሁን ልክና ስሕተት የሚባል ነገር አይኖርም፤ ሁሉም ነገር ይፈቀዳል። ሙስና፣ ጉቦና ትዕቢት ነውር አይሆንም፤ ቅሚያ፣ ዝርፊያና ዝልፊያ ነውር አይሆንም፤ ጭቆና፣ ብዝበዛና ውገዳ ነውር አይሆንም። አሁን መንደሩ ሁሉ “ያምላክ ያለህ፣ የፈጣሪ ያለህ” እያሉ በሚጮኹ ምስኪኖች ይሞላል። ሀብት፣ ሥልጣንና ዝምድና ያላቸው ሰዎች ጉዳቱ አይደርስባቸውም፤ ምክንያቱም በዚያም በዚህም ብለው ያመልጣሉ፤ ድኾችና ምስኪኖች ግን ይጠቃሉ።
እንግዲህ ዴሞክራሲ የሚሠራው ንግግራችንና ክርክራችን በሐቅና በእውነት ሲቃኝ ነው። ዜጎች የእውነት ጠበቆች መሆን አለባቸው። ሐሰትንና ሐሰተኛነትን የሚጠላ ትውልድ ካልበዛ መጻኢው ዕድላችን አሳሳቢ ነው። በንግድ ዓለም ትርፍ ይጠበቃል። ይሁንና የነጋዴዎች ሚዛን አባያ መሆን የለበትም። ሌሎችን አክስሮና አራቊቶ ራስን የሚያበለጥግ ንግድ እኩይነቱ መኮነንና መጋለጥ አለበት። ፍርድ ቤቶችና ሕግ አስከባሪዎች ፍትሕ እንዳይጓደልና እነርሱም በሙስና እንዳይበከሉ መጠንቀቅ አለባቸው። ሚዲያዎች አሉባልተኞች፣ ጽንፈኞችና በሬ ወለዶች መሆን የለባቸውም። ሥራቸው በማስረጃ ላይ የተደገፈ ትንተና ለሕዝብ ማቅረብ መሆኑን መቼም መች መርሳት የለባቸውም። የመንግሥት ባለሥልጣኖች ከሕዝብ የተቀበሉት ዐደራ ሕዝብን ማገልገያ እንጂ መዘባነኛና ራስን መጥቀሚያ እንዳልሆነ መገንዘብ አለባቸው። በዴሞክራሲ ሥርዐት ውስጥ ሥልጣን ሕዝብን ማገልገያ እንጂ በሕዝብ መገልገያ አይደለም። በሕዝብ የተመረጡ መሪዎች በመረጣቸው ሕዝብ ላይ ለመጌትየት መከጀል ዴሞክራሲን መቃረን እንደ ሆነ መረዳት አለባቸው። በዴሞክራሲ ሥርዐት ውስጥ እንዲያውም ቋሚ ሥልጣን የለም። ሥልጣን ሁሉ ጊዜአዊ ነው። እናም ባለሥልጣኖች በዐጭሯ የሥልጣን ዘመናቸው ሕዝብን በታማኝነት አገልግሎ ማለፍ ትልቅ ክብር እንደ ሆነ መገንዘብ አለባቸው።[38] ሌባ ከመባል ሐቀኛ ተብሎ መጠላት ይሻላል፤ ሐቀኛን መጥላት ትክክል ባይሆንም።
ይህን ጥያቄ የምመልሰው እንደ አንድ ክርስቲያን ነው። የእኔ ንጽረተ ዓለም ክርስቲያናዊ በመሆኑ የሰውን ሰውነት የምመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ከሚያስተምረው በመጀመር ነው። በክርስቲያናዊው አስተምህሮ መሠረት ሰው የእግዚአብሔር ፍጡር ነው። ሰው የተሠራው ከምድር አፈር ቢሆንም፣ መልከ አምላክና አምሳለ መለኮት ነው። ይህ አምላካዊ ማኅተም በሰው ሁሉ ላይ ታትሟል። ርግጥ በክርስትና “ውድቀት” እና “ጥንተ አብሶ” (Fall and Original Sin) የሚባል አስተምህሮ አለ። ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ቢፈጠርም (ዘፍ 1፥26-27) በኀጢአት ምክንያት ግን ወድቋል፤ ከእግዚአብሔር መንገድ ወጥቷል። የእግዚአብሔርን ሳይሆን የራሱን ሐሳብ አስተናግዷል። ያ የአምላክ መልክና አምሳል ምንድን ነው? ደግሞስ ከውድቀት በኋላ በሰው ላይ የታተመው መልከ አምላክና አምሳለ መለኮት ምን ሆነ? የሚለው ራሱን የቻለ ዝርዝር ትንተና ቢኖረውም እዚህ ላይ ነገሩን በዐጭሩ ለመግለጽ እሞክራለሁ።
ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ተፈጥሯል ሲባል የእግዚአብሔርን ምግባራዊና ኅሊናዊ ባሕርይ ወርሷል ማለት ነው። አሁን ሰው ልክ እንደ እግዚአብሔር ጽድቃዊ ባሕርያት አሉት። ምድርን ለመግዛት ምግባራዊና ኅሊናዊ ብቃት ያስፈልጋል። ሰው ልኩንና ስሑቱን፣ እውነቱንና ሐሰቱን እንዲሁም መልካሙንና እኩዩን ለመለየት አቅም ያገኘው አምላካዊ አምሳል ስለታተመበት ነው። ሰውን ከእንስሳ በእጅጉ የሚለየውም ይህ ብቃቱ ነው። ይህ ብቃት ግን ከውድቀት በኋላ በእጅጉ ተጎድቷል፤ ማለት ብቃቱ ሰንፏል፤ በኀጢአት ምክንያት ሙሱን ሆኗል (“ሙሱናነ ልብ” እንዲሉ)። ጳውሎስ ይህን ሁኔታ ሲገልጽ “እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ፤ የማደርገውን አላውቅምና፤ ዳሩ ግን የምወደውን አርሱን አላደርገውም” ይላል (ሮሜ 7፥14-15)። ይህ በሰው ሁሉ ላይ የተጫነ ብርቱ ሕግ ነው። ለዚህ ነው ሰው ታዳጊ ያስፈለገው። ሰው ወደ ቀደመው ስፍራ መመለስ የሚችለው ከውድቀቱ ሲነሣ ነው። ቸሩ እግዚአብሔር ደግሞ ለሰው መዳኛውንና መፈወሻውን አዘጋጀ፤ በአንድ ልጁ ሞትና ትንሣኤ። ጳውሎስ እንዳለው “በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” (ሮሜ 7፥25)።
ምንም እንኳ በሰው ላይ የታተመው አምላካዊ መልክ በእጅጉ ቢጎዳም ሙሉ በሙሉ ግን አልጠፋም። ሰዎች አሁንም ልኩንና ስሑቱን መለየት ይችላሉ። ዕውቀታቸውን፣ ችሎታቸውንና ገንዘባቸውን ለመልካም ተግባር መጠቀም የሚችሉ ሰዎች አሁንም አሉ። ርግጥ ሰዎች ሁልጊዜ የሚመቻቸው ቁልቁለቱ ነው፤ የመልካሙ መንገድ ሁልጊዜ ዳገት ይሆንባቸዋል። ከቁልቁለቱ ይልቅ ዳገቱን የመረጡ ሰዎች ለሰው ልጆች መልካም ነገር ማድረጋቸው አይቀርም። ለእኔ ትልቅና እውነተኛ ሰው ወይም ሕዝብ ማለት መልካምነታቸውን በሚችሉት ሁሉ የሚያሳዩ ናቸው። ለሰዎች፣ ለፍጥረትና ለማኅበራዊ ሕይወት ስምረት የሚችሉትን ሁሉ የሚያደርጉ ናቸው። በሐሳብ የሚለዩአቸውን ሰዎች እንኳ ሥልጡን በሆነ መንገድ ልዩነታቸውን የሚገልጹ ናቸው። ጠበኛነትንም ሆነ ሰይፈኛነትን የሚጠሉ ሰዎች እነርሱ ትልቅ ሰዎች ናቸው። እውነተኛ ሰዎች ሰይፍ አይመዝዙም፤ ጦር አይሰብቁም። ይልቁንም ልዩነት ቢኖር እንኳ በትዕግሥት ይደራደራሉ፤ ወደ አንድ መልካም ድምዳሜ ለመድረስ ይከራከራሉ። የሚደራደሩትና የሚከራከሩት ወደ ተሻለ ግብ ለመድረስ መሆኑን ስለሚያውቁ ይበልጡኑ ይደራደራሉ፤ ይከራከራሉ። ቁልቁለቱ መንገድ አጥፊ፣ በአንጻሩም ዳገቱ መንገድ አልሚ መሆኑን ስለሚያውቁ ከምንጊዜውም ይልቅ የእውነተኛ ሰውነታቸው ማንነት የሚገለጥበትን መንገድ ይከተላሉ።
እኔ ለኢትዮጵያ የምመኘው ሰይፈኛነትንና ሰልፈኛነትን የሚጠሉ፣ እንደ ኀይሌ ፊዳ በኢትዮጵያ ነጻነትና እኩልነት በጥቅሉ ዴሞክራሲ እንዲመጣ ሕይወታቸውን እስከ መሠዋት የሚደርሱ ሰዎች እንዲበዙ ነው።[39] እንደ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) አገራቸውን ከልብ የሚወዱና ለአገራቸው መልካሙን የሚናፍቁ ሰዎች እንዲበዙ ነው።[40] እንደ ታማኝ በየነ በአገራቸው ነጻነትና እኩልነት እንዲሰፍን በሰላማዊ መንገድ የሚፋለሙ ሰዎች እንዲበዙ ነው። እንደ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ በአገራቸው እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲያብብና በሥልጣን ተተግነው ራሳቸውን የሚያደልቡ ሰዎች (ሌቦች) እንዲጠፉ ጧትና ማታ የሚሠሩ ሰዎች እንዲበዙ ነው።[41]
ኢትዮጵያ ምንም ሲሳይ ያልጎደላት በአየር ንብረትም ሆነ በማዕድን ሀብት የታደለች አገር ናት። ያጣችው ግን አንድነት፣ መቀባበልና በሰላማዊ መንገድ መነጋገር ከሁሉ የሚበልጥ ፋይዳ መሆኑን የተረዱ ሰዎችን ነው። ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሉበት አገር ምንም ዐይነት አንድነት ሊመጣ አይችልም። 100 ፓርቲዎች ያሉበት አገር ይቅርና 2 ፓርቲዎች ባሉበት አገር እንኳ ፖለቲካዊ ትርምሱ አያድርስ ነው። 100 ቦታ ተበጣጥሶ ያደገ አገር የለም።
ኢትዮጵያ ወደ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረ ሰቦች የሚኖሩባት አገር መሆኗ ይታወቃል። ታዲያ እነዚህ ሕዝቦች በአንድነት ተሳስረውና ተከባብረው መኖር የሚችሉት እንዴት ነው? መቼም በዘርና በመደብ ላይ የተመሠረተ ፓርቲ/ፖለቲካ ከቶ ሊበጀን አይችልም። የአንድን ብሔርና መደብ ማንነት ወይም ጥቅም፣ ፍላጎትና ምኞት የሚያጎላ በአንጻሩም ሌሎችን የሚያገልል ሥርዐተ ማኅበር በምንም ዐይነት አይጠቅምም። ለታሪካዊ እውነታዎች ስፍራ የማይሰጥ ሥርዐት ሁልጊዜ እርስ በእርስ እንዳናከሰን ይኖራል። ብዙዎች እንደሚስማሙት እኔም እንደሚመስለኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርተኛነት ነግሧል። የራስን ብሔር ማላቅና ማተለቅ ናኝቷል። ከዚህ እኩይ አስተሳሰብ ተመልሰን ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረ ሰቦች የሚኖሩባት አገር መሆኗን ካልተቀበልን ዕጣችን እንደ ሩዋንዳ ነው የሚሆነው። ብሔርተኛነት ያቃርናል፤ አልፎ ተርፎም ያተላልቃል።
እና እንግዲህ የሚበጀን በዴሞክራሲ እሴቶችና ፋይዳዎች ላይ የተመሠረተ ሥርዐት መገንባት ነው። በዘርና በብሔር ላይ የተመሠረተ ሥርዐት አንድ አያደርገንም፤ ተሞክሮ ታይቷል። ሰዎች ሁሉ፣ ዘራቸውና ብሔራቸው ምንም ሆነ ምን እኩል ናቸው ብለን ካልተነሣን ከፍ አንልም፤ አናድግም፤ በሰላም መኖር አንችልም። ብሔርተኛነት ልክ እንደ ዘረኛነት ነው። ዘረኛነት በቆዳ ቀለም ላይ የተመሠረተ ወጋጅነት ነው። ዘረኛነት እኔ ነጭ በመሆኔ ከአንተ ከጥቁሩ እበልጣለሁ የሚል ገፊነት ነው። በማንኛውም መስፈርት ቢሆን እኔ ከአንተ እበልጣልሁ የሚል አስተሳሰብ በሰዎች መካከል ቅራኔ ከመፍጠር በቀር አያቀባብልም፤ አያቀራርብም። ዘረኛነት በደቡብ አፍሪካ ያደረሰውን ጥፋት ማንኛችንም አንዘነጋውም፤ የቅርብ ጊዜ እውነታ በመሆኑ። ብሔርተኛነትም በኢትዮጵያ ውስጥ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ማንም ነጋሪ አያስፈልገውም። የእኔ ዘር ከአንተ ዘር ይበልጣል ካልን ወይም የእኔ ሃይማኖት ከአንተ ሃይማኖት ይበልጣል ካልን ከቶውን አገር አይኖረንም። ወይም ሀብትንና ሥልጣንን ተተግነን ራሳችንን ከሌሎች ለማስበለጥ የምንከጅል ከሆነ ከቶውን አንድነት አይኖረንም።
ሰዎች ልዩ ልዩ ዘር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሊኖራቸው ይችላል። ሁላችንም አንድ ዐይነት ልንሆን አንችልም። እንደ መልካችን ሁሉ ዝንጉርጉር ነን። ወሳኙ ልዩ ልዩ መሆናችን አይደለም፤ ወሳኙ ልዩ ልዩ ሆነን ሳለ አንድ ለመሆን መጣራችን ነው። ልብ እንበል፤ አንድ ዐይነት እንሁኑ አላልኩም። አንድ መሆንና አንድ ዐይነት መሆን ለየቅል ናቸው። አንድ ዐይነት እንሁን ብንል እንኳ የፍጥረት ሥርዐት አይፈቅድልንም፤ ቢያንስ መልካችን ይመሰክራል። በዘር፣ በመልክ፣ በቀለምና በሃይማኖት ልዩ ልዩ መሆናችን ወደ መበላለጥ ሊወስደን አይገባም። ሰውነታችን ብቻ ሳይሆን ሥልጡንነታችንም የሚለካው ልዩ ልዩ ሆነን ሳለ በአንድነት ለመኖር መቻላችን ነው። አንድነት ከሁሉ በፊትና ከሁሉ በላይ ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው ብሎ መነሣትን ይጠይቃል። እኩልነት ሳይረጋገጥ አንድነት አይኖርም። እኩልነት ደግሞ ክልልንና ድንበርን ያፈርሳል። ይህ መሬት ወይም ይህ ክልል የእኔ ብቻ ነው የሚል ትምክህትን ይደመስሳል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመሰክረው ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር መልክ ተፈጥረዋል፤ በመሆኑም ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ምድር የማንም ሳትሆን የእግዚአብሔር ናት። ራሱ እግዚአብሔር “ምድር ለእኔ ናትና” ይላል (ዘሌ 25፥23)። በመሆኑም ምድር ከአንዱ እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ ተሰጥታለች። በታሪክ አጋጣሚ ክልልና ድንበር ተፈጠረ እንጂ ምድር የፈጣሪ ናት። እናም ማንም ሰው የእኔ ብቻ ነው የሚለው ክልልና ድንበር ሊኖረው አይችልም። ሲፈጠር ጀምሮ የእኛ ያልሆነውን ነገር የእኛ ብቻ ለማድረግ መፈለግ ወንጀል ነው። ምድር የእኛ አይደለችም፤ ኧረ ከቶ!! እናም ሰው ሁሉ በምድር ላይ የመኖር መብት አለው።
ሰዎችን ምድር ለማሳጣት መሞከት በእውነተኛው ዕብደት ነው። ማንም ሰው ምድርን የማልማት መብት አለው። ርግጥ ምድርን ማልማትና ምድርን ማጐሳቆል ትልቅ ልዩነት አላቸው። ሰው ምድርን እንዲገዛ ኀላፊነት ቢሰጠውም ምድርን እንዲያጐሳቊል ግን አልተፈቀደለትም። በዘፍጥረት 1፥28 ላይ “ምድርንም ሙሏት ግዟትም” የሚለው ትእዛዝ በዘፍጥረት 2፥15 ላይ “አብጇት፤ ጠብቋትም” ተብሎ ተገልጿል። “ግዟት” ተብሎ የተረጐመውን ቃል ለመግለጽ የገባው የዕብራይስጡ ቃል እንዲያውም “እንደ እረኛ ተንከባከቧት” የሚል እንድምታ አለው።[42] ቃሉ በጭራሽ አጐስቋይነትን (ምጥጥ ምጥምጥ አድርጊነትን) አያሳይም። ሰው ምድርን እንዲመጠምጥ በዚህም ሥነ ምኅዳራዊ ቀውስ እንዲፈጠር አልተፈቀደለትም። እንደ እውነቱ ከሆነ “ግዟት” የሚለው ቃል ለሰው ልጆች የተሰጠውን ታላቅ ዐደራ ያሳያል። ሰውን ከሌሎች ፍጥረታት የሚለየው አንዱ መሠረታዊ ነገር ለሰው ትልቅ ዐደራ መሰጠቱ ነው። ሰውና ሌሎች ፍጥረታት በአንድ ቀን ቢፈጠሩም (በስድስተኛው ቀን) ሰው ከሌሎች ፍጥረታት በሁለት መሠረታዊ ነገሮች ይለያል። አንደኛው በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምድርን ግዟት መባሉ ነው። ሌሎች ፍጥረታት በእግዚአብሔር መልክ ስለመፈጠራቸውም ሆነ ምድርን ግዟት ስለመባላቸው አልተነገረም። እዚህ ላይ ልብ እንበል። ሰው ምድርን ግዟት ከመባሉ በፊት በእግዚአብሔር መልክ ስለ መፈጠሩ ነው የተነገረው። አሁን መልእክቱ ግልጽ ነው፤ እግዚአብሔር ፍጥረትን አያጐሳቊልም። በፍጥረት ይከብራል እንጂ ፍጥረትን አያከስርም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ስለ መደመር ብዙ ነግረውናል። ግን የምንደመረው ምንን መሠረት አድርገን ነው? መደመር አንድነትን የሚያሳይ ከሆነ አንድ ሕዝብ የምንሆነው እንዴት ነው? በምንድን ነው? ሰዎችን የሚያስተሳስራቸውና የሚያዳምራቸው ጊዜአዊ ስሜትና ጩኸት መሆን የለበትም። ምክንያቱም ጊዜአዊ ስሜት ይበርዳል፤ ጊዜአዊ ጩኸትም ይከስማል። ሰዎች መተሳሰርና መዳመር ያለባቸው ተመካክረው በሚገነቡት ሥርዐትና በሚያበጁት መርሕ ነው። ከቶ የማይበርደውና መቼም የማይከስመው ሥርዐትና መርሕ እንጂ ስሜትና ጩኸት አይደለም።
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርሁት ዴሞክራሲ የተሻለ ሥርዐት ይመስላል። ምን ዐይነት ዴሞክራሲ ከተባለ ደግሞ ነጻነትን፣ እኩልነትን፣ እውነትን፣ ሕግንና ፍትሕን መሠረት ያደረገ ዴሞክራሲ እንደ ሆነ ተመልክቷል። በእንዲህ ዐይነቱ ሥርዐት የምናምን ከሆነ አሁን መደመር እንችላለን፤ አሁን አንድ መሆን እንችላለን። እዚህ ላይ ትልቁ ነገር ሰዎች ለተደመሩለትና አንድ ለሆኑለት ሥርዐት መገዛት መቻላቸው ነው። ደግሞም ሥርዐቱ በራስ ጠቀሞችና በአፈንጋጮች እንዳይበከል ተደማሪዎች ሁሉ ዘብ መቆም አለባቸው (ደርግ ደርግን ሸተትሁ መሰለኝ)። ተደምሬአለሁ ለምንለው ሥርዐት ጥብቅና የማንቆምና የማንጋደል ከሆነ ሥርዐቱ አይሰነብትም። አንድ ቀን አምባ ገነኖች ሥልጣን ሲጨብጡ ያንኮታኩቱታል። ዴሞክራሲ በጥቂት ተሟጋቾች ብቻ አይቆምም። ዴሞክራሲ የሚቆመው በሥርዐቱ ውስጥ የተጠለሉ ሰዎች ሁሉ ለሥርዐቱ መጽናት ሲጋደሉ ነው። የኀይሌ ፊዳ ትግል የአንድ ሰው ትግል ነው። የቴዲ አፍሮ ትግል የአንድ ሰው ትግል ነው። የታማኝ በየነ ትግል የአንድ ሰው ትግል ነው። ጥይት ሳይተኩሱ ወይም ሰይፍ ሳይመዙ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና ዕድገት ጥብቅና የቆሙ ድንቅ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። እኔ እዚህ ላይ እነዚህን ሦስት ሰዎች ጠቀስሁ እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነትና እኩልነት ወይም በጥቅሉ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት እንዲሰፍን ዘመናቸውን የጨረሱ ወይም ሕይወታቸውን የሰዉ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። ለሦስቱ ሰዎች ግን የተለየ አክብሮት አለኝ። ዝናም ሆነ ጥቅም ከቶ ሳያማልላቸው በሚችሉት ሁሉ ለኢትዮጵያ ደክመዋል። አንድዬ ዘራቸውን ይባርክ፤ ውለታቸውን ይክፈል።
በመጨረሻም ሥጋቴን ገልጬ ጽሑፌን ልቋጭ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ለመሪው ያለውን አክብሮትና አድናቆት ያለ ማንም ቆስቋሽና ጎትጓች ሲገልጽ ታይቶ አያውቅም ብል ማጋነን አይሆንም። እነ ዶ/ር ዐቢይ ኢትዮጵያ ወደሚበጃት አቅጣጫ እንድታመራ ትክክለኛውን መንገድ እያመላከቱ ናቸው ማለት ይቻላል። እንደመር፣ ይቅር እንባባል፣ እንዋደድ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን አገራችንን እናሳድግ የሚል ጥሪ እያቀረቡ ናቸው።[43] እነዚህ ከዚህ በፊት ያልተሰሙ አዳዲስ ድምፆች ናቸው። ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ ከተጓዘች ተስፋ ይኖራታል። መንገዱ ግን በአግባቡ መጠረግ አለበት። ቤቱም በትክክለኛው መሠረት ላይ መገንባት አለበት። ዴሞክራሲ ስሜትና ጩኸት አይደለም። ዴሞክራሲ ለሰዎች ደስ ደስ የሚሉ ነገሮችን መናገር አይደለም። ይልቁንም ዴሞክራሲ ሥርዐትና መርሕ አለው። ጥያቄው የዴሞክራሲ ሥርዐቶችና መርሖዎች ወይም መሠረቶችና እሴቶች ምንድን ናቸው? የሚለው ነው። የዴሞክራሲ መንገዱ ካልተጠረገና መሠረቱ ካልተገነባ “ጅምሩ አብዮት” እንዳይከሽፍ ፍርሀት አለኝ። እሰይ አገራችን ልትለወጥ ነው የሚለው ተስፋ እንዳይጨልም ሥጋት አለኝ። አሁን ተገኘ የምንለው “ድል” ገና ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም። ገና ብዙ ሥራ ከፊት ለፊታችን ተደቅኗል። ከሥራዎቹ አንዱና ትልቁ የምንመኘው ዴሞክራሲ የሚቆምበትንና የሚተከልበትን ጥብቅ መሠረት መገንባት ነው። አለዚያ ድሉ “የሰመረና የከሸፈ ድል” ይሆናል። ይህ አባባል ምን ለማለት እንደ ሆነ ሁለት ታሪካዊ አብነቶችን በመጥቀስ ላስረዳ፤
እዚህ ላይ የምጠቅሳቸው ሁለት ታሪካዊ አብነቶች እስከ አሁን ድረስ ቁጭት ፈጥረዋል። አንደኛው የአድዋ ጦርነት ሲሆንም፣ ሁለተኛው የማርቲን ሉተር ኪንግ ትግል ነው። ሁለቱም በተቃውሞ ላይ የተመሠረቱ ትግሎች ነበሩ። የአድዋው ጦርነት የጣሊያንን ቅኝ አገዛዝ የሚቃወም ትግል ሲሆን፣ የማርቲን ሉተር ኪንግ ደግሞ የአሜሪካንን ዘረኛነት የሚቃወም ትግል ነበር። የታሪክና የፖለቲካ ምሁራን እንደሚሉት ሁለቱም ትግሎች በአንድ በኩል ሰምረዋል፣ በሌላ በኩል ከሽፈዋል/ጨንግፈዋል። ሁለቱም ትግሎች ድል አጎናጽፈዋል ቢባልም፣ ድሉ ሙሉ ድል አልነበረም፤ ወይም ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም። የአድዋውን ጦርነት በተመለከተ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደሚለው ኢትዮጵያ በቅኝ አገዛዝ ሥር ባትወድቅም ፍጹም የሆነ ነጻነት ተቀዳችታለች ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ነጻነቷ በልማት አልታጀበም፤ አልተደገፈም።[44] የአድዋ ፖለቲካዊ ድል በኢኮኖሚያዊ ድል ባለመደገፉ እውነተኛ ነጻነት አላመጣም። ኢትዮጵያን በወታደራዊና በፖለቲካዊ ስልት ማሸነፍ ያልቻሉ ቅኝ ገዢዎች አገሪቱን ለማንበርከክ ሌላ አማራጭ ነበራቸው፤ ኢኮኖሚያ ድል። በዚህም ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል። ልክ እንዲሁ የማርቲን ሉተር ኪንግ ትግል ለአገሪቱ ጥቁሮች ጊዜአዊ ድል ቢያመጣም ድሉ ዘላቂ መሆን አልቻለም።[45] ጥቁሮችና ነጮ በአንድ ምግብ ቤት መመገብ ቢችሉም ወይም በአንድ አውቶቡስ መሳፈር ቢችሉም አሁንም በመካከላቸው ያለው ልዩነት እንደ ድሮው ሰፊ ነው። አሁንም ቅልጥጥ ያለ መድልዎ/አድልዎ አለ፤ አሁንም በቆዳ ቀለም መናቅ አለ። ሥልጣኑንና ኢኮኖሚውን የተቆጣጠሩት አሁንም ነጮቹ ናቸው። ምርጥ ምርጡ አሁንም ለነጮቹ ነው። የሥራና የትምህርት ዕድል የሚያገኙት ነጮቹ ናቸው። ጥቁሮቹ ዕጣ ፈንታቸው መታሰርና መገደል ብቻ ይመስላል። ድሮ እየተሰቀሉ ነበር የሚገደሉት፤ አሁን በጥይት ነው የሚገደሉት። በየእስር ቤቱ የታጨቁትን ጥቁሮች ቁጥር ብንመለከት በእጅጉ ኅሊና ይቆጠቁጣል፤ ይሰቀጥጣል። አንድ ጥቁርና አንድ ነጭ በሕግ ፊት ያላቸው ስፍራ እኩል ነው ለማለት የሚያስደፍር ተጨባጭ ማስረጃ የለም። ለዚህ አባባል ትልቁ ማስረጃ የአሜሪካን እስር ቤቶች ናቸው።[46] ከ10 ታሳሪዎች መካከል 7ቱ ጥቁሮች መሆናቸው እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ የታገሉለት አልፎ ተርፎም የተሠዉለት ነጻነት እምብዛም ለውጥ እንዳላመጣ ያሳያል።[47]
አንጻራዊ ነጻነት ማግኘት ትልቅ ነገር ነው። ይሁንና ጥቁሮች በማንኛውም ረገድ ነጮች የሚያገኙትን ዕድል እነርሱም ካላገኙ ነጻነታቸውና እኩልነታቸው አይረጋገጥም፤ ኑሯቸውም አይሻሻልም። በአሜሪካን አገር ጥቁሮችና ነጮች የሚኖሩበት ሰፈር ምን ያህል ትልቅ ልዩነት እንዳለው መመልከት ብቻ በቂ ነው። በአገሪቱ ውስጥ አሁንም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉልበት ያላቸው ነጮቹ ናቸው። ይህ የሚያሳየው ድሉ ፍጹም አለመጠናቀቁን ነው። በጥቅሉ ሲታይ የአድዋም ሆነ የሉተር ትግል ውጤቱ/ድሉ ሰምሯልም ከሽፏልም ማለት ይቻላል። አሁን በኢትዮጵያ የተጀመረው የዴሞክራሲ ጉዞ ዕድሉ መሥመርና መክሸፍ እንዳይሆን ልመናዬን ለአንድዬ አቀርባለሁ፤ አንድዬ ኢትዮጵያን ይመልከት፤ በምሕረቱም ይጎብኘን!!
[1] በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ስለ ዴሞክራሲ እሴቶችና መሠረቶች (values and foundations) እንጂ ስለ ዴሞክራሲ ቅርጾች ወይም ሞዴሎች (models) ለመሞገት አልተነሣሁም። ሦስት ዐበይት የዴሞክራሲ ቅርጾች ወይም ሞዴሎች እንዳሉ ይታወቃል፤ እነርሱም “The representative/republic model of democracy,” “The westminster model of democracy” እና “The consensus model of democracy” ናቸው። የመጀመሪያው በአሜሪካን፣ ሁለተኛው በእንግሊዝ፣ ሦስተኛው በጀርመን አገሮች የሚታወቁ የዴሞክራሲ ሞዴሎች ናቸው። ለኢትዮጵያ የሚበጀው የትኛው ሞዴል እንደ ሆነ መነጋገር ይጠይቃል። እኔ በዚህ ጽሑፍ ይህን ጥያቄ ለመቃኘት አልሞከርሁም። ሌሎች በዚህ ጒዳይ ላይ ብዙ የሠሩ ሰዎች ሐሳቡን እንድናብላላው ቢረዱን መልካም ነው እላላሁ።
[2] የአሜሪካን ሕገ መንግሥት “We the People” በማለት ይጀምራል። ይህም ሥርዐቱ የቆመው በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ላይ መሆኑን ያሳያል። የአሜሪካን ዴሞክራሲ አብርሃም ሊንከን ሁልጊዜ በሚጠቀስለት ንግግሩ እንዳመለከተው “government of the people, by the people, for the people” የሚል እሳቤ አለው። መንግሥታዊው ሥርዐት መመሥረት ያለበት በሕዝብ ነው፤ የሚያገለግለውም ሕዝብን ነው (“በሕዝብ ለሕዝብ” እንደ ማለት ነው)።
[3] የአገዛዝ ሥርዐቶቹ ዐይነት እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚገልጹት ወደ 20 የሚደርሱ የአገዛዝ ዐይነቶች አሉ። አራቱ ዐይነት አገዛዞች ከላይ ተጠቅሰዋል፤ የተቀሩት ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፤ 5) Bureaucracy 6) Capitalism 7) Colonialism 8) Communism 9) Federalism 10) Feudalism 11) Kleptocracy 12) Meritocracy 13) Military Dictatorship 14) Oligarchy 15) Plutarchy 16) Republicanism 17) Socialism 18) Theocracy 19) Totalitarianism 20) Tribalism.
[4] Arend Lijphart, Patterns of Democracy: Government Forms and Performance in Thirty-Six Countries (New Haven: Yale University Press, 2012) 46-47.
[5] “አዲዮስ” የስፓኒሽ ቃል ነው። ጣሊያኖች ቃሉን የወሰዱት ከስፓኒሽ ሳይሆን አይቀርም። ለማንኛውም ትርጒሙ “ደኅና ሰንብት፤ ደኅና ሁን/እግዚአብሔር ይከተልህ” ማለት ነው። በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ አገባቡ “ደኅና ሰንብት ወይም ደኅና ሁን” እንደ ለማለት ቢሆንም፣ “አይ ጉድ ቀለጠ፤ ከሰረ፤ ጠፋ” የሚል እንድምታ ሳይኖረው አይቀርም። አንዳንድ ሰዎች ቃሉን ሲጠቀሙበት እንደ ሰማሁት የአንድን ነገር መክስርና መጥፋት ለመግለጽ ነው። ተስፋ ያደረጉት ነገር እንደ ጉም ሲበንባቸው የሚጠቀሙበት አገላለጽ ይመስለኛል።
[6] Alan Wolfe, Does American Democracy Still Work? (New Haven: Yale University Press, 2006). Richard Wolff, Democracy At Work: A Cure For Capitalism (Chicago, Haymarker Books, 2012).
[7] Emmanuel Wallerstein, Randall Collins, etl., Does Capitalism Have A Future? (New York: Oxford University Press, 2013).
[8] Andrew G. McCabe, The Threat: How the FBI Protects America in the Age of Terror and Trump (New York: St. Martin’s Press, 2019).
[9] ነገሩ ብርቱ አከራካሪ ጒዳይ ሆኗል፤ የሮበርት ሙለር ምርመራ እንደሚያመለክተው ትራምፕ በራሺያ እርዳታ ለመመረጡ ብዙ ሁነኛ ማስረጃዎች ቀርበዋል፤ በርካታ ረዳቶቹም ክስ ተመስርቶባቸው ፍርዳቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፤ እርሱም ቢሆን የራሺያ አሻንጉሊት ሳይሆን አይቀርም በሚል በFBI እየተመረመረ ነው። ምርመራውን ለማጨናገፍና ለማዳፈን የወሰዳቸው እርምጃዎች ግን በሙለር የምርመራ ውጤት በተጨባጭ ተረጋግጧል። አሁን ፕሬዘዳንት ስለሆነ አይከሰስም የሚል የDepartment of Justice (DOJ) መመሪያ ስላለ እንጂ ተራ ዜጋ ቢሆን ኖሮ ያለ ጥርጥር መታሰሩ አይቀርም ነበር (ከ800 በላይ የሚሆኑ የሕግ ባለሙያዎች የሙለርን ሪፖርት በመጥቀስ እንዳመለከቱት ፕሬዘዳንቱ ከመከሰስ የተረፈው ፕሬዘዳንት ስለሆነ ብቻ ነው)። አሁን የሚጠበቀው የሥልጣን ዘመኑን እስኪጨርስ ነው። ከዚያ በኋላ ክሱ ይቀጥላል፤ ምናልባትም ዘብጥያ ሊወርድ ይችላል። “Abuse of power and Obstraction of Congress” በሚል በHouse of Representatives ኢምፒች መደረጉ ደግሞ ፕሬዘዳንቱ ከሕዝብ የተቀበለውን ኀላፊንት በአግባቡ መወጣት እንዳልቻለ ያሳያል። ትራምፕ ኢምፒች ሲደረግ ሦስተኛው የአሜሪካን ፕሬዘዳንት መሆኑ ነው። Michael Isikoff and David Corn, Russian Roulette: The Inside Story of Putin’s War on America and the Election of Donald Trump (New York: Hachette Book Group, 2018). Malcolm Nance, The Plot to Destroy Democracy: How Putin and His Spies are Undermining America and Dismantling the West (New York: Hachette Book Group, 2018).
[10] Luke Harding, Collusion: Secret Meetings, Dirty Money, and How Russia Helped Donald Trump Win (Vintage Books: New York, 2017). ትራምፕ ከፑቲን ጋር ባደረጋቸው ስብሰባዎች ሁሉ አማካሪዎቹን አለማሳተፉና አልፎ ተርፎ የአስተርጓሚዎቹን ማስታወሻ እየነጠቀ መውሰዱ ምስጢሩ ወይም ጉዱ ምንድን ነው? የሚለውን ጥርጣሬ ይበልጥ አጠናክሯል፤ የFBI ተመርማሪም አድርጎታል። በአሜሪካን ታሪክ የአገሪቱ ፕሬዘዳንት በFBI ሲመረመር ትራምፕ የመጀመሪያው ነው። ኢምፒች መደረጉ ደግሞ ሦስተኛው ፕሬዘዳንት አድርጎታል።
[11] እዚህ ላይ አብላጫ ድምፅ ሲባል ሥርዐተ ምርጫው በሌሎች አገሮች ከሚታወቀው ምርጫ እንደሚለይ መገንዘብ ያስፈልጋል። የሚታየው አብላጫ ድምፅ ቢሆን ኖሮ ሂላሪ ክሊንተን ወደ 4 ሚሊዮን በሚጠጋ ድምፅ በልጣዋለች። ሆኖም በአሜሪካን ሥርዐተ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ሳይሆን የሚታየው በኢሌክቶራል ድምፅ ነው።
[12] አሁን አሁን “constitutional crisis” የሚል እሮሮ እየተሰማ ነው። የፕሬዘዳንቱ አለቅጥ አምባገነን ለመሆን መፈለግ ወይም እነ ፑቲን የሚከተሉትን አገዛዝ በአሜሪካን ምድር ለመተግበር መከጀል ከምንጊዜውም በላይ ብሷል፤ ይህም ብዙዎችን አሳስቧል። ፕሬዘዳንቱ አምባገነን እንዳይሆን እንደ “ቃታ መጠበቂያ” የሆኑት የሕዝብ ምክር ቤቱና ሴነተሩ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ በጉጉትና በሥጋት እየተጠበቀ ነው። ፕሬዘዳንቱ በሕዝብ ተወካዮቹ ኢምፒች ተደርጓል። በሴኔቱ ድርጊቱ ተረጋግጦ ከሥልጣኑ ይነሣ ይሆን? ከሕግ የበላይነት ይልቅ የግል ጥቅም የሚበልጥባቸው ከሆነ አሁን ዴሞክራሲያዊ ሥርዐቱ ትልቅ አደጋ ላይ ይወድቃል፤ “constitutional crisis” ይሏል ይህ ነው።
[13] Greg Miller, The Apprentice: Trump, Russia and the Subversion of American Democracy (Custom House: New York, 2018). “ቃታ መጠበቂያ” የሚለውን ሐረግ ብዙ ጊዜ የሚጠቀምበት ወዳጄ Dr. ተስፋዬ ሮበሌ ነው። እርሱ “ቃታ መጠበቂያ” ሲል ነገሮች መረን እንዳይወጡና የታለመላቸውን ግብ እንዳይስቱ መገደቢያው፣ መከላከያውና መለጎሚያው ምንድን ነው? ማለቱ ነው። ጠመንጃ ቃታ መጠበቂያ ከሌለው ድንገት ሊባርቅና ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። እናም እውነተኛ ነጻነት በውስጡ የራሱ መጠበቂያ ሊኖረው ይገባል፤ በመሆኑም ነጻነት ኅሊና ቢስነትና እሴተ ቢስነት ሳይሆን ተጠያቂነትና ኀላፊነት ነው። ራሱን የማይገዛና ራሱን የማይገራ ነጻነት ቃታ መጠበቂያ እንደሌለው መሣሪያ ነው። ነጻነት ካልተለጎመና በሁነኛ እሴቶች ካልተገራ አገር ይፈጃል፤ ሕዝብ ይጨርሳል፤ ያጫርሳል።
[14] Bob Woodward, Fear: Trump in the White House (Simon & Schuster: New York, 2018).
[15] ፕሬዘዳንት ከሆነበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ከ10,000 በላይ ውሸቶችን ተናግሯል። March 2, 2019 ባደረገው 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በፈጀ ንግግሩ ብቻ ከ60 በላይ ውሸቶችን ተናግሯል (https://www.washingtonpost.com/graphics/politics/trump-claims)። በፕሬዘዳንትነት ዘመናቸው (አንዳንዶቹ 4 ሌሎቹ 8 ዓመት አገልግለዋ) የትራምፕን ያህል የዋሸ ፕሬዘዳንት የለም። የአርባ አራቱ ፕሬዘዳንቶች ውሸት በአንድ ላይ ቢደመር እንኳ የእርሱን ያህል አይሆንም። ትራምፕ በሁለት ዓመት የፕሬዘዳንት ዘመኑ ከ10,000 በላይ ውሸቶችን መናገሩ ለሐቅ፣ ለዴሞክራሲና ለአገር ያለው አስተሳሰብ ምን ያህል ዝቅተኛ ብሎም አደገኛ እንደ ሆነ ያሳያል። ፕሬዘዳንቱ “አህያ ከሞተች ሰርዶ አይብቀል” ያለ ይመስላል።
[16] Michael Wolff, Fire and Fury: Inside the Trump White House (Henry Holt and Co., 2018). James Comey, A Higher Loyalty: Truth, Lies and Leadership (Flatiron Books: New York, 2018).
[17] Timothy L. O’Brien, TrumpNation: The Art of Being Donald (Open Road Media: 2015).
[18] Daniel Dale, www.thestar.com/politics. www.thewashingtonpost/donald-trump. www.politifact.com/personalities/donald-trump.
[19] ለአብነት ያህል የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፤ “I love Wikileaks” (Oct. 10, 2016), “This Wikileaks stuff is Unbelievable; It tells you the inner heart, you gotta read it” (Oct. 12, 2016), “It’s been amazing what’s coming out on Wikileaks” (Oct. 13, 2016), “This Wikileaks is like a treasure trove” (Oct. 31, 2016), “Boy, I love reading those Wikileaks” (Nov. 4, 2016). www//businessinsider.com/trump-wikileaks.
[20] “There is no truth” (Rudy Giuliani, Trump attorney). “There is an alternate truth” (Kellyanne Conway, Trump White House counselor). በሮበርት ሙለር የምርመራ ውጤት ላይ እንደ ተመለከተው እጅግ በጣም ጥቂት የዋይት ሃውስ አማካሪዎች ብቻ ናቸው ለእውነትና ለሐቅ ግድ የሚሰጣቸው። ብዙዎቹ አማካሪዎች የፕሬዘዳንቱ ሐሰተኛነት የተመቻቸው ይመስላል። በራሳቸው አነሣሽነትና በፕሬዘዳንቱ ቀስሻሽነት ከዋይት ሃውስ መድረኮች ላይ ብዙ ሐሰቶች ተነግረዋል። ለዝርዝሩ Special Counsel Robert S. Mueller, III: Report On The Investigation Into Russian Interference In The 2016 Presidential Election (Washington, D.C., 2019) ይመ።
[21] የአማርኛና የግእዝ መዛግብተ ቃላት “ነጻ” የሚለውን ቃል ሲያብራሩ “ጌታው የለቀቀው፤ ባርነት የቀረለት፤ በራሱ ሐሳብ ዐዳሪ” ይላሉ። የነገረ መለኮትና የፍልስፍና መዛግብተ ቃላት ግን “ነጻ” እና “ነጻነት” የሚለውን ቃል “ትድግና ማግኘት” ከሚለው ጋር ያዛምዱታል። ነጻነት የሌሎች ባሪያ፣ ተገዥና ተበዝባዥ አለመሆን ነው። ሰዎች ባርነት ሲቀርላቸው ነጻነት ይጎናጸፋሉ፤ አርነት ይወጣሉ።
[22] Richard Bauckham, The Bible in Politics: How to Read the Bible Politically (Louisville: John Knox Press, 1989) 68.
[23] ዝኒ ከማሁ፤ 103-117.
[24] ጳውሎስ እንደሚለው ከሁሉ የሚበልጠው መብት ሳይሆን ፍቅር ነው። ፍቅር የፋይዳዎች ሁሉ ፋይዳ ነው፤ የእሴቶች ሁሉ እሴት ነው። ራሱ እግዚአብሔር ፍቅር በመሆኑ ሥነ ምግባራዊ ፋይዳዎችንና እሴቶችን በተመለከተ ከፍቅር የሚበልጥ ምንም ነገር የለም። በዚህ መልእክት ውስጥ “ብርቱ” የሚል ቅጽል የተሰጠው መብታቸውን ለሚልቀው ፋይዳ ሲሉ ለሚተዉ ነው። መብት ለራስ ፍላጎት መጋደል ነው፤ ፍቅር ግን ለሌሎች ፍላጎት መፋለም ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለራስ መብት መከራከር እንደ ነውር ባይቆጠርም ለሌሎች ሲሉ መሥዋዕትነት መክፈል ግን ይበልጥ ተወድሷል።
[25] Miroslav Volf, Exclusion and Embrace: A Theological Exploration of Identity, Otherness, and Reconciliation (Nashvill: Abingdon Press, 1996). ዘረኛነት ምንኛ እኩይ አስተሳሰብ እንደ ሆነ ለመገንዘብ የሚፈልጉ ሁሉ ይህን መጽሐፍ እንዲያነቡ ከልብ እመክራለሁ። እኔ ዝም ብዬ ስገምት ዶ/ር ዐቢይ የቮልፍን መጽሐፍ ከዳር እስከዳር ያነበበው ይመስለኛል። ግምቴ ከሽፎ ካላነበበው እንዲያነብበው በእርሱም ዙሪያ ያሉ ሰዎች እንዲያነብቡት ከልብ እማጸናለሁ። ቮልፍ በመጽሐፉ ውስጥ ለሰዎች በእጅጉ የሚበጁ እውነቶችን ወይም መርሖዎችን ዘርዝሯል። ፍቅር፣ ፍትሕ፣ ይቅርታና ከልብ መቀባበል ወሳኝ መርሖዎች ናቸው። በአንጻሩም በቀል፣ ዘረኛነት/ብሔርተኛነትና ወጋጅነት እኩይ አስተሳሰቦች ናቸው። በቀልን፣ ዘረኛነትን/ብሔርተኛነትንና ወጋጅነትን ባህሉ ያደረገ ማኅበረ ሰብ ሁልጊዜ በጥፋት ጎዳና ላይ ነው። ከዛሬ 12 ዓመት በፊት “ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፤ ርእሰ ጒዳዮቹና ተግዳሮቶቹ” በሚል ርእስ ባሳተምሁት መጽሐፍ ቮልፍን በእጅጉ መሠረት አድርጌአለሁ። ያኔ ቮልፍ ያነሣቸው ሐሳቦችና ማስጠንቀቂያዎች ዛሬም ጠቃሚ ናቸው፤ ምክንያቱም የያኔው ችግር አሁንም አለ፤ እንዲያውም ብሶበታል። ቮልፍ የሥቁዩን እግዚአብሔርና የስቁሉን ኢየሱስ መንገድ መከተል እንደሚበጅ አመልክቷል። እግዚአብሔር ጠላቶቹን ተቀበለ፤ ኮብላዮችን አቀፈ (የጠፋው ልጅ ምሳሌ)። ይህ ሰዎች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ አምላካዊ ምሳሌ ነው። ተስፋም የሚኖረን በዚህ መንገድ ስንጓዝ ነው፤ ይህ መንገድ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የመቀባበልና የፍትሕ መንገድ ነው። ዘረኛነትና ብሔርተኛነት ያዋግዳል፤ ያተላልቃል።
[26] ዝኒ ከማሁ፤ 57-165። “ወጋጅነት” ሥሩ “ወገደ” ነው፤ በቁሙ ለየ፣ አገለለ፣ አራቀ። እዚህ ላይ “ወጋጅነት” የሚለው ቃል “exclusion” የሚለውን ቃል ይተካል። ቮልፍ ቃሉን የሚጠቀምበት በዘፍጥረ ምዕራፍ 1-2 ላይ ኀጢአት ያስከተለውን ብርቱ ቀውስ ለመግለጽ ነው። እንደ ቮልፍ አባባል ኀጢአት ካስከተለው ብርቱ ቀውስ ውስጥ አንዱ በፍጥረት መካከል ትስስርና ዝምድና እንዳይኖር ማድረግ ነው። ፍጥረት እርስ በእርሱ ተሳስሯል፤ ተዛምዷል። ይህን ትስስርና ዝምድና መለየት አምላካዊ ዕቅዱን ያፋልሳል። ወጋጅነት ብዙ መገለጫዎች አሉት፤ ቮልፍ መገለጫዎቹን ሲገልጽ 1) elimination, 2) assimilation, 3) domination, 4) Passing by or abandonment ይላል (64-79)። በግርድፉ መደምሰስ፣ መመሳለል፣ መበዝበዝ እና አይቶ እንዳላዩ መሆን ልንለው እንችላለን። ከእኔ ዘርና ወገን ካልሆንህ ጥፋ ከዚህ፤ እንድንውጥህ ከፈቀድክልን አንተፋህም፤ ለመኖር ከፈለግህ ጸጥ ለጥ ብለህ ተገዛ፤ አንተም በጠበልህ እኔም በጠበሌ፤ አትድረስብኝ አልደርስብህም። ችግርህን እንዳላይ ከአጠገቤ ወግድ።
[27] Volf, Exclusion and Embrace, 275-306.
[28] በPacifism እና Just War መካከል ብርቱ ክርክር መኖሩ ይታወቃል። እዚህ ላይ ያን ክርክር እያስተጋባሁ አይደለም። ማንዴላም ሆነ ሉተር ሁለቱም በአቋማቸው pacifist ነበሩ፤ በተለይ ሉተር ድብን ያለ pacifist ነበር። ሁለቱም “የሚሻለውና የሚበጀው የትኛው የትግል ስልት ነው?” ከሚለው ጥያቄ ጋር ተፋልመዋል። በመጨረሻ የደረሱበት ድምዳሜ ግን መላውን ዓለም አስደንቋል። ሁለቱም ተከታዮቻቸውን ሲያሳስቡና ሲወተውቱ እንደ ነበረው የዐመፅ መንገድ ምርጥ መንገድ አይደለም። ርግጥ “ዐመፅ ጌጡ ለሆነበት ዓለም” ሰላማዊነት ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል። ሉተር ተገድሏል፤ ማንዴላም ለእስር ተዳርጓል። ድላቸው ግን የሚጣፍጥ ድል ነበር፤ ምሳሌነቱም ወደር አልነበረውም። ታሪክ ሁልጊዜ በመልካም ጎኑ በአክብሮት የሚያወድሰው ሰይፍ የመዘዙ ሰዎችን ሳይሆን ለሰይፍ አንገታቸውን የሰጡ ሰዎችን ነው።
[29] Volf, Exclusion and Embrace, 207-211.
[30] ወደፊት “ፍቅር፣ ፍትሕና ይቅርታ ከመስቀሉና ከትንሣኤው አንጻር” በሚል ርእስ አንድ ጽሑፍ ይቀርባል። ይህን ሐሳብ ይበልጥ ጠለቅ ብለን የምንመለከተው በዚያ ጽሑፍ ላይ ይሆናል፤ አንድዬ ለከርሞ ይበለን።
[31] Allan Bloom, The Closing of the American Mind: How Higher Education Has Failed Democracy and Impoverished the Souls of Today’s Students (New York: Simon and Schuter, 1987).
[32] Immanuel Wallerstein, “Structural Crisis, or Why Capitalists May No Longer Find Capitalism Rewarding,” in Does Capitalism Have A Future? Emmanuel Wallerstein, Randall Collins, Michael Mann, Georgi Derluguian and Craig Calhoun Eds. (New York: Oxford University Press, 2013) 9-35. Alan Wolfe, Does American Democracy Still Work (New haven: Yale University Press, 2006).
[33] www.oxfam.org/2019.
[34] Walter Brueggemann, Money and Possession (Louisville: John Knox Press, 2016).
[35] Walter Brueggemann, The Prophetic Imagination (Minneapolis: Fortress Press, 20180).
[36] Stenley Hauerwas, Richard Bondi, and David B. Burell, Truthfulness and Tragedy: Further Investigations in Christian Ethics (Notre Dame: University of Notre Dame Press, 1977) 90.
[37] Volf, Exclusion and Embrace, 258-259.
[38] ደስታ ተክለ ወልድ “ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት” በተሰኘው ሥራቸው ውስጥ “አሽኔ” በሚለው ተራ ሥር “አሽኔ ኪዳነ ማርያም” የሚባሉ ሰው ይጠቅሱና ሲያትቱ፣ “ብላታ አሽኔ ካጤ ምኒልክ እስከ ቀዳማዊ ዐጤ ኀይለ ሥላሴ የነበሩ መንግሥትን በፍጹም ልባቸው የሚያከብሩ እግዚአብሔርንም የሚፈሩ የዘርና የሃይማኖት ልዩነት ሳያደርጉ ሰውን ኹሉ የሚያፈቅሩ ትሕትናንና ታማኝነትን ቸርነትን ገንዘብ አድርገው የኖሩ ናቸው” ይላሉ (ገጽ 1232)።
[39] ዕድሜ ለዶ/ር አማረ ተግባሩ፤ ሊረሳ የነበረውን የኀይሌ ፊዳን ታሪክ እንደ ገና መለስ ብለን እንድናጤን ዕድል ሰጠን። በእውነቱ የዚህ ሰው ሕልም በእጅጉ ይገርማል። ኀይሌ ነጻነትና እኩልነት ምን ማለት እንደ ሆነ ከገባቸው ጥቂት ሰዎች አንዱ ነበር። ውድ ሕይወቱንም የሠዋው ለዚሁ እውነታ ነበር። ለሚልቀው ፋይዳ ሲሉ ሕይወታቸውን የሚሠዉ ሰዎች ምንኛ ያስገርማሉ! ይህ ሰው ብዙ ነገሩ እንደሚያስደንቅ የሕይወት ምስክርነቱ ያሳያል። የደርግ ክፉና ጨካኝ ሰይፍ ባይበላው ኖሮ እርሱ ያለማት ኢትዮጵያ ትገኝ ነበር። “ሩቅ አልሞ ቅርብ ቀረ” አወይ አወይ እንዴት ያሳዝናል! እንጀት የሚበላ ሰው፤ ሞቱ የሚቆጭና የሚያንገበግብ ሰው፤ ሙሉ ሕይወቱን ለመኖር ታድሎ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ በተጠቀመች ነበር። እግዚኦ ለዳኝነትህ!!! ኃይሌ ፊዳ እና የግል ትዝታዬ (ኔባዳን አሳታሚ፤ አዲስ አበባ፤ 2010)። ይህ መጽሐፍ በኀይሌ ፊዳ ላይ ይሰነዘር የነበረውን አሉታዊ አስተያየት የሚያርቅና ትክክለኛውን ገጽታ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። ኀይሌ በሰይፍ ሳይሆን በውይይትና በክርክር የሚያምን ሰው እንደ ነበር ተዘግቧል። ሰዎችን በመጥፎ ጎራ ከመፈረጅ ይልቅ በሰከነ መንፈስ መነጋገር የተሻለ መፍትሔ እንደሚያመጣ የሚያምን ሰው ነበር። እኔ እንደሚመስለኝ ለሰዎች የሚጠቅመው እንዲህ ዐይነቱ አመለካከት ነው። መፈራረጅ ወደ መፈጃጀት ይወስዳል፤ ይህ ደግሞ አገርንና ትውልድን ይጎዳል እንጂ የትም አያደርስም።
[40] ቴዲ ያቀነቀናቸው ዘፈኖች በአብዛኛው ኢትዮጵያዊነት ታትሞባቸዋል። ይህ ሰው ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅር በእጅጉ ያስደንቃል። እኔ ዘፈኖቹን የምመለከታቸው እንደ ስብከትና ትረካ ነው። ሰው አገሩን እንዲህ ሲወድ አይቼ አላውቅም። በዚህ ላይ ሰላማዊነቱ ለጉድ ነው። ጦር ሳንመዝ ጥይት ሳንተኩስ በትዕግሥት ከተመካከርን ትልቅ አገር ይኖረናል። ጨዋ ሕዝብ አይነካከስም፤ አይበላላም፤ አይገነጣጠልም። ይልቁንም ልዩነቶቹን አቻችሎ ይኖራል። ልዩነትን ማቻቻል መከባበር ነው። የሚቻቻል፣ የሚከባበርና የሚቀባበል ሕዝብ ያድጋል። የሚወጋገድ ሕዝብ ግን ያልቃል። አቤቱ መሓረነ!!!
[41] እዚህ ላይ ለአብነት ያህል እነዚህን አራት ሰዎች ብቻ ጠቀስሁ እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት፣ ዕድገትና ዴሞክራሲ እንዲመጣ መላ ሕይወታቸውን የሠዉ ሰዎች ብዙ ናቸው። አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው። በስም የማናውቃቸው ነገር ግን ለኢትዮጵያ ሲሉ የተሠዉትን ቤት ይቁጠራቸው። የዶ/ር አብይ ጒዳይ ብዙም ስላልለየለት ምንም መናገር አይቻል ይሆናል። እርሱ ለሚያራምደው ለውጥ ጊዜ ይሰጠው ከሚሉ ወገኖች ጋር እስማማለሁ። የኢትዮጵያን ችግር በሙሉ እኔ እፈታዋለሁ በሚል የሚያደርገውን ሩጫ ግን ብዙዎች እንዳልወደዱት ሁሉ እኔም አልወደድኩትም። የኢትዮጵያ ችግር በአንድ ሰውና በአንድ ጀምበር አይፈታም። የሚሻለው የዴሞክራሲ እሴቶችና መሠረቶች ሥር እንዲሰዱ ጧትና ማታ ቢታገል ነው። ምክንያቱም እንዳንዶቹ ችግሮች በዴሞክራሲ እሴቶችና መሠረቶች የሚፈቱ ናቸው። ሌሎቹ ትዕግሥትና መቻቻል የሚጠይቁ ናቸው፤ ሌሎቹ ጊዜና ቀን የሚጠብቁ ናቸው። አቅምንና ውሱንነትን መቀብል ትልቅ ትሕትና ነው።
[42] Christopher J. H. Wright, Old Testament Ethics for the People of God (Downers Grove: InterVarsity Press, 2004) 17-20.
[43] ርግጥ ከእነርሱ በፊት በዚህ ጒዳይ ላይ ብዙ ኢትዮጵያውያን ባገኙት አጋጣሚና መድረክ ላይ ተናግረዋል። ከፍ ሲል የጠቅስኳቸው ሦስት ግለ ሰቦች በክርክራቸው፣ በቀልዳቸውና በግጥማቸው አሳስበዋል። የኀይሌ ፊዳን ታሪክ ያነቧል፤ የታማኝ በየነን ቀልዶች ይሰሟል፤ የቴዲ አፍሮን ግጥሞች ያደምጧል።
[44] ባህሩ ዘውዴ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966 (አዲስ አበባ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፣ 1989) 241-244። Bahru Zewde, A History of Modern Ethiopia: 1855-1991 (Addis Ababa; Addis Ababa University Press, 2001) 81-148, 271-272. እንዲሁም Andargachew Tiruneh, The Ethiopian Revolution 1974-1987: A Transformation from an Aristocratic to a Totalitarian Autocracy (New York: Cambridge University Press, 1993) 4-7. ባህሩ ዘውዴ የራሱን ትንተና እና የሌሎች ምሁራንን ሥጋት መሠረት አድርጎ እንዳቀረበው የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ኩራት ቢያመጣም ሽንፈታቸውን መቀበል ላቃታቸው ምዕራባውያን ቂም በቀልን አርግዟል። በአድዋ ያጡትን ድል በሌሎች መስኮች በተለይም በኢኮኖሚው መስክ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ብዙ ጉድጓዶች ምሰዋል። የኋላ ኋላ እንዲያውም በብዙ ነገር ተሳክቶላቸዋል። ምሁራኑ እንደ ሠጉትም ኢትዮጵያ ከ40 ዓመት በኋላ በጣልያን ዳግመኛ መወረሯ የአድዋው ፖለቲካዊ ድል በኢኮኖሚያዊ ድል ያለመታገዙ ውጤት ተደርጎ ነው የተወሰደው።
[45] Tokunbo Adelekan, The Leaven in the Loaf: A Comparative Analysis of the Social Reconstructionist Projects of John Locke and Martin Luther King, Jr. (PHD Diss., Princeton Theological Seminary, 2002). እንዲሁም Class Lecture, “Public Theology” (Palmer Theological Seminary, 2012).
[46] Michelle Alexander, The New Jim Crow: Mass Incarceration in the Age of Colorblindness (New York: The New Press, 2012). John F. Pfaff, Locked In: The True Causes of Mass Incarceration and How to Achieve Real Reform (New York: Basic Books, 2017). Lauren-Brooke Eisen, Inside Private Prisons: An American Dilemma in the Age of Mass Incarceration (New York: Columbia University Press, 2018). Melvin Mahone, Prison Privatization in America: Costs and Benefits.
[47] James Samuel Logan, Good Punishment? Christian Moral Practice and U.S. Imprisonment (Grand Rapids: Eerdmans, 2008). Mark Lewis Taylor, The Executed God: The Way of the Cross in Lockdown America (Minneapolis: Fortress Press, 2015). በአሜሪካን ከ2.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ እስረኞች አሉ፤ ከ10,000 በላይ የግል እስር ቤቶች አሉ፤ በመላው አገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት እስር ቤቶች ውስጥ 65% የሚሆኑት እስር ቤቶች የግለሰብ ናቸው። የእስር ቤቶች ትርፍ ከባንክ ቤቶችና ከኤሌክትሮኒክስ ማምረቻ ኩባንያዎች ትርፍ ይበልጣል። ሰዎችን በማሰር የሚገኝ ትርፍና ብልጽግና ግፍነቱ የማይቆጠቁጠውና የማይሰቀጥጠው ሥርዐት በእጅጉ ነቅዟል ከማለት ወዲያ ምን ትርጒም ሊሰጠው ይችላል? እነዚህን እስር ቤቶች ለማስተዳደርና የጥገና ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን የአሜሪካን መንግሥ በየዓመቱ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል። የእስር ቤቶቹ ባለቤቶች ደግሞ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ትርፍ ያጋብሳሉ። በማስረጃ ላይ የተደገፈ ተጨማሪ ጥናት የሚፈልጉ በግርጌ ማስታወሻ 47 ላይ የተጠቀሱትን መጻሕፍት ያነቧል።
Share this article:
Genaye Eshetu introduces us a missionary who lost everything he has, but endured to tell the good news to the Burma people.
የታሪክ አጥኚው አፈወርቅ ኀይሉ (ዶ/ር) በዚህ ጽሑፉ፣ ኢትዮጵያዊነት “ጨዋነት” ብቻ አለመሆኑን፤ ይልቁን ጸያፍ የሆነ “የጀብደኝነት” አመለካከት ከማንነታችን ጋር የተጋባ መሆኑን ከታሪካችንና ከአሁኑ ሁናቴ ጋር ያዛምደዋል። “ልቅ” የተባለው ይህ “ጀብደኝነት” በቶሎ ካልላሸቀ ያጠፋናል ይላል ዶ/ር አፈወርቅ።
ጌታችን ስለ ሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ በምናስብበት በሰሙነ ሕማማት፣ ንጉሤ ቡልቻ “እንዴት እንሙት?” የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ። ምላሹ በክርስቶስ ሞት ውስጥ የቀረልን ትልቅ ትምህርት ሆኖ አለ።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment