በወንጌላውያን የሚሲዮን ታሪክ ፋና ወጊ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው በዐፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት (1625 – 1660 ዓ.ም.) እንደ መጣ የሚታመነው ጀርመናዊው ፒተር ሄይሊንግ ነው። ፒተር በኢትዮጵያ ቆይቶ በ1644 አካባቢ ወደ አገሩ ለመመለስ በመንገድ ሳለ፣ ቱርኮች አግኝተው እስልምናን እንዲቀበል ቢያስገድዱትም አሻፈረኝ በማለት አንገቱን ቀልተው ገደሉት። ይህ ሚሲዮናዊ በኢትዮጵያ ሳለ የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ችሎ የነበረ ሲሆን፣ የዮሐንስ ወንጌልን ወደ አማርኛ በመመለስ ለሕዝቡ እንዳበረከተ ታሪክ ዘግቦታል።
በወቅቱ የቱርኮች በአካባቢው ማየል እና ግብፅ በቱርኮች እጅ መውደቅን ተከትሎ የሚሲዮን እንቅስቃሴ ተገድቦ የነበረ ሲሆን፣ የወንጌላውያን ሚሲዮናውያን እንደ ገና ብቅ ማለት የጀመሩት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበሩት ነገሥታት፣ ለምሳሌ በሸዋ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ እና በሰሜን ዐፄ ቴዎድሮስ፣ ከወንጌል ሰብከት ይልቅ የአውሮፓውያኑን ጥበብ፣ የጦር መሣሪያ ሥራና እርዳታን በብርቱ በመሻታቸው፣ ኋላም ዐፄ ዮሐንስ የወንጌል ሥራውን በግልጽ በመከልከላቸው አገልግሎታቸው አመርቂ ሳይሆን ቀረ። በርግጥ ሚሲዮናውያኑ በቤተ እስራኤላውያንና በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ አንዳንድ አማኞችን አፍርተው እንደ ነበር “በመከራ ውስጥ ያበበች ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርእስ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በ1990 ዓ.ም. ያሳተመችው መጽሐፍ ያስረዳል።
“በጌታ አዳኝነት አምነው እርሱን መከተል ከጀመሩበት ጊዜ አንሥቶ ለስንት ሰዎች የክርስቶስን አዳኝነት መስክረዋል?” የሚል ጥያቄ ለበርካታ ክርስቲያኖች ቢቀርብ መልሱ ያን ያህል አጥጋቢ ላይሆን ይችላል። አሁን ባለንበት ጊዜ ወንጌል ስርጭት አላስፈላጊ፣ ጊዜ ያለፈበት፣ ለአንዳንዶችም አሳፋሪና አሸማቃቂ ተደርጎ ቢታሰብም የክርስቲያን ዋነኛ ኀላፊነት መሆኑን ዘመን አይሽረውም። ቤተ ክርስቲያን ሕያውነቷ ከሚገለጥባቸው፣ ለክርስቶስ እና ለሰዎች ያላትን ፍቅር ከምታሳይባቸው ተግባራቷ መካከል አንዱ የወንጌል ስርጭት ነው።
SIM
የሱዳን ኢንቴሪየር ሚሽን (Sudan Interior Mission – SIM) አመሠራረት የሚጀምረው በ1893 ቶሮንቶ ካናዳ ሲሆን፣ የወንጌል መልእክተኛ የነበሩት የሕክምና ባለሙያው ዶ/ር ቶማስ ላምቤ በ1912 ዓ.ም. አካባቢ ከሱዳን ወደ ወለጋ በመግባት፣ ሰዮ አካባቢ የሚሲዮን ጣቢያ ከፍተው ማገልገል እንደ ጀመሩ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። ኤስ.አይ.ኤም. (SIM) በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጌልን ከማሰራጨት አንጻር ቀደምትና ጉልሕ ድርሻን የተወጣና እየተወጣ የሚገኝ አገልግሎት ነው።
መነሻውን ኢትዮጵያ ያደረገ ድንበር ዘለል የወንጌል ሥርጭት በተናጠል እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አብያተ ክርስቲያናትና አገልግሎቶች አማካኝነት ከተጀመረ የተወሰኑ ዓመታት ቢያልፉም፣ ይህንን ሥራ በማዕከላዊነት የሚያስተባብር አካል እስካሁን አልነበረም። አሁን ግን በኤስ.አይ.ኤም. ሥር የሚገኘውና ከተመሠረተ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው ኢስት አፍሪካ ሴንዲንግ ኦፊስ (East Africa Sending O ce) የተሰኘው ተቋም ይህንን ሥራ ለመሥራት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። “እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ ወደ ውጪው ዓለም የወንጌል መልእክተኞችን የላኩ የቃለ ሕይወት፣ መካነ ኢየሱስ፣ ገነት፣ መሠረተ ክርስቶስ እና ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም እንደ ታላቁ ተልእኮ (Great Commission) ያሉ የወንጌል አገልግሎቶች” እንዳሉ የሚናገሩት የኢስት አፍሪካ ሴንዲንግ ኦፊስ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወርቁ ኃይለማርያም ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ፣ ይህ አዲስ ተቋም ሚሲዮናውያንን ዐሥራ አንድ ከሚሆኑ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመላክ ሥራ በማስተባበር ቤተ ክርስቲያን የታላቁ ተልእኮ ኀላፊነቷን እንድትወጣ ድጋፍ የሚሰጥ ነው።
“አገር ውስጥ ተዳርሶ ነው ወደ ውጪው የተሄደው?”
ጥያቄው የተለያዩ ጽንፎችን ያስተናግዳል። የወንጌል ብርሃን ቤተ ክርስቲያን አገልጋይና በኢትዮጵያ የሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት በሚሲዮን ነገረ መለኮት ተማሪው መላከ ሰላም ቦጋለ “የአገር ውስጡንም የውጪውንም የወንጌል ስርጭት እኩል ማስኬድ ይገባል” ሲል፣ የአማኑኤል ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ ተገኝ ሙሉጌታ(መጋቢ) ግን በዚህ አይስማማም። ተገኝ ሐሳቡን ሲያጠናክር፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠርነው፣ የዚህ ማኅበረ ሰብ አባል የሆንነው፣ የአገሩን ቋንቋ ተናጋሪ የሆንነው በዓላማ ነው፤ ይህ ዓላማ ደግሞ ወንጌልን ማዳረስ ነው። ስለዚህ ቅድሚያ ለአገራችን ሊሰጥ ይገባል” ይላል።
አቶ ወርቁ ኃይለማርያም በበኩላቸው፣ “ሐዋርያት ወንጌልን ለዓለም ለማድረስ ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ ዋጋ የከፈሉት ኢየሩሳሌም በወንጌል ባልተዳረሰችበት ጊዜ” እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ ያደርጋሉ። “የአገር ውስጡንም እየሠራን የውጪውን መድረስ አለብን፤ እኛ ʻለአገራችን ብቻʼ ብለን ከተቀመጥን የውጪውን ማን ይድረሰው?” በማለት ይጠይቃሉ። አያይዘውም፣ “የመቄዶንያ ሰዎች ጳውሎስን ʻመጥተህ እርዳንʼ ማለታቸው ድንበር ዘለል የወንጌል ስርጭት ተገቢ እንደ ሆነ አመላካች ነው፤ ምክንያቱም ጳውሎስ አካባቢውን ሳይጨርስ ወደ ሌላ መሄዱን ያሳያል” በማለት ወንጌልን ድንበር ዘለል በሆነ ሁኔታ ለመስበክ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ነገረ መለኮታዊና ታሪካዊ ምክንያት እንዳለ ያስረዳሉ።
ከዚህ በፊት በአገር ውስጥ ሚሲዮናዊነት እንዳገለገሉ የሚናገሩትና የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤት መምህር የሆኑት አቶ ዳዊት ቆጢሶ በበኩላቸው፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቤተ እምነቶች እና አገልግሎቶች ቢኖሩም፣ ወንጌል እንደሚገባ አልተሠራም። ስለዚህ የአገር ውስጡን ሳንዘነጋ ሚሲዮናውያንን ወደ ውጪ አገራት መላክ አነስተኛ የክርስቲያን ቁጥር ያላቸውን አገራት የወንጌል እንቅስቃሴ መርዳት” እንደ ሆነ ያሰምሩበታል። የአገር ውስጥ የወንጌል ሥርጭትን በተመለከተ ኢስት አፍሪካ ሴንዲንግ ኦፊስ በአገር ውስጥ የወንጌል መልእክተኞች የመላክ ሥራም እንደሚሠራ የሚናገሩት አቶ ወርቁ፣ ለምሳሌም አንድ ቤተ ሰብ ወደ ሙርሲ በመላክ በዚያ አካባቢ የወንጌል አገልግሎት በመሰጠት ላይ እንደ ሆነ ያስረዳሉ።
የሚሲዮናዊው ቅድመ ዝግጅት
አንድ ሚሲዮናዊ የሚሄድበትን ማኅበረ ሰብ ባህል፣ አመጋገብ፣ ቋንቋ፣ የአገሪቱን ሕግና የአካባቢውን ዋና ዋና እምነቶች ማጥናት ቀዳሚ ተግባሩ ነው። ኢስት አፍሪካ ሴንዲንግ ኦፊስ ሚሲዮናውያንን የሚልክው አብያተ ክርስቲያናት ያመኑባቸውን አገልጋዮች ከላኩለት በኋላ በቢሮው በኩል አስፈላጊው ማጣራት ከተደረገ በኋላ ነው። ድንበር ዘለል የሚሲዮን ሥልጠና ቀድመው ያገኙ ሚሲዮናውያን ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው የሚናገሩት አቶ ወርቁ፣ አገልጋዮች “የባህል ባይተዋርነትና ግራ መጋባት እንዳይገጥማቸው ስለሚሄዱበት አገር ባህል እና ቋንቋ ሥልጠና እንዲሁም የሥነ ልቦና ጥንካሬ እንዲኖራቸው በባለሙያዎች ምክር ከተገቢው የጤና ምርመራ ጋር ይደረግላቸዋል” ብለዋል።
ሚሰዮናውያንን ለመላክ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ሊወስድ የሚችል ሲሆን፣ ለስድስት ወር የሚሆን ቀለብ ከቢሮው እንደሚያገኙ አቶ ወርቁ ያስረዳሉ። በዚህ ሂደትም፣ “በአሁኑ ጊዜ አውሮፓና አሜሪካን ሳይጨምር አፍሪካና እሲያ ለሚሄዱ ሚሲዮናውያን ለአንድ ሰው በዓመት 250 ሺህ ብር ወይንም 12 ሺ ዶላር እንደሚያስፈልግ” ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የተልእኮው ፈተናዎች
በበርካታ አገራት የተሰማሩ ሚሲዮናውያን ተግዳሮቶች ናቸው የሚባሉት፣ ከአካባቢው ማኅበረ ሰብ የሚሰነዘር ጥቃት አንዱ ሲሆን፣ ይህም ከነባር እምነቶች ወይም ከንጽረተ ዓለማዊ ልዩነት የተነሣ የሚመጣ እንደ ሆነ ይታመናል። ከዚህ ሌላ የወንጌል መልእክተኞች ትልቁ ተግዳሮት በዐውዳዊነት ምክንያት የሚፈጠር ቅይጣዊነት (Syncretism) ችግር ነው። በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት በሚሲዮን ነገረ መለኮት ጥናት በሚያደርጉ ምሁራን መካከል ይደረጋል። ʻየወንጌል መልእክት የት ድረስ ዐውዳዊነትን መከተል ይገባዋል የሚለው ጥያቄ? ወደ ቅይጣዊነት አመራ የሚባለውስ ምን ላይ ሲደርስ ነው?ʼ እና የመሳሰሉት ያላባሩ ጥያቄዎች ናቸው።
የአማኑኤል ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ መጋቢ ተገኝ ሙሉጌታ በዚህ ጉዳይ በሰጠው አስተያየት፣ “ወንጌልን ዐውዳዊ በሆነ ሁኔታ መስበክ ተገቢ ቢሆንም፣ዐውዳዊነት ገደቡ እስከምን ድረስ መሆን አለበት የሚለው ግን በሚገባ አልተመለሰም” ሲል “ዐውዳዊነት ሲበዛ ማመቻመች እንዳይሆን” ስጋቱን ይገልጻል። አቶ ወርቁም ቢሆኑ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፤ “ዐውዳዊነት በባህል ዘለል ሚሲዮን ትልቅ ጥያቄ እንደ ሆነ አለ፤ ለምሳሌ አለባስንና አመጋገብን የተመለከተ፣ አጭር ሱሪ ወይስ ረጅም ሱሪ እንልበስ፣ ጥምጣም እናርግ አናርግ የሚለው እና የጥምቀት አፈጻጸምን የተመለከተ የቅርጽ ጥያቄ” ያን ያህል ችግር ተደርጎ የሚወሰድ እንዳይደል ነው የሚያስረዱት። በወንጌል መልእክት ላይ የሚደረግ የይዘት ለውጥ ግን ወንጌሉ ተጣሞ እንዲደርስ ሊያደርግ ይችላል የሚለው ግን የአቶ ወርቁና የበርካቶች ስጋት ነው። “ለዚህ መፍትሔው” ይላሉ አቶ ወርቁ፣ “ባህልን በወንጌል ብርሃን ማየት ነው። ከዚህ በተገላቢጦሽ ወንጌልን በባህል መነፅር ማየት ሲጀመር ችግር ይፈጠራል” ይላሉ።
የምሥራቹ ቃል የሚያስከፍለውን ዋጋ ተምነው ለተሰማሩት የወንጌል መልእክተኞች እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ድረስ ዋጋ ሊከፍሉ እንደሚችሉ ይታወቃል። ኢስት አፍሪካ ሴንዲንግ ኦፊስ እስካሁን ካሰማራቸው የወንጌል መልእክተኞች ውስጥ አንድ ሚሲዮናዊ ደቡብ ሱዳን ውስጥ በወባ በሽታ ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች ግን ይህ ነው የሚባል የጎላ ችግር እንዳልደረሰ የቢሮው ኀላፊው አቶ ወርቁ ይናገራሉ።
እንደተሳካላቸው በምን እናውቃለን?
“የሚሲዮናውያን ውጤታማነት ምዘና እጅግ ከባድ ነው” የሚለው ወንድይፍራው አዲስ (መጋቢ) ነው። እንደ መጋቢ ወንድይፍራው፣ “የወንጌል መልእክተኛው ፍሬ መመዘን ያለበት ለስንት ሰው ወንጌልን ዐሰማ? ስንት ሰው ዳነ? በአካባቢው ሁለንተናዊ ለውጥ መጥቷል ወይ?” በሚለው መሆን እንዳለበት ያስረዳል። መጋቢ ተገኝ ግን በተቃራኒው፣ “የሰው ድርሻ ወንጌልን መስበክ ሲሆን፣ ማዳን ግን የመንፈስ ቅዱስ ድርሻ ነው፤ ስለዚህ አንድ ሰው እጅግ ቢመሰክርም አንድም ሰው ላይድን ይችላል። የሰው ድርሻ በትጋት ወንጌልን ማድረስ ብቻ ነው” ሲል በቀላሉ መመዘን ከባድ እንደ ሆነ ይሞግታል።
በርግጥ የበርካታ ሚሲዮናውያን ተግዳሮት ለላካቸው አካል መላክ ያለባቸው የሥራ ሪፖርት ሳይሆን አይቀርም፤ ምክንያቱም የሪፖርቱ ይዘት በአገልግሎታቸው ቀጣይነት ላይ የራሱ የሆነ ሚና መጫወቱ ስለማይቀር ነው። ከዚህም የተነሣ የተጋነነ ሪፖርት ሲቀርብ አልፎ አልፎ ይስተዋላል። በርግጥ ለዚህ መፍትሔው እውተኛ የወንጌል መልእክተኞችን ማሰማራት ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የሚሲዮናውያኑ ታማኝነት በመጀመሪያ ደረጃ ለላካቸው ቢሮ ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንደ ሆነ የማወቅ መንፈሳዊም ሆነ ሞራላዊ ብስለት ላይ የደረሱ ይሆናሉ፤ ይህም የአገልግሎቱ የስኬት ጅማሬ ይሆናል። ለጊዜው የሚፈለገው የሰዎች ወደ ክርስቶስ መንግሥት መፍለስና ማኅበራዊ ለውጥ መምጣት ወዲያውኑ ባይታይ እንኳ፣ በሂደት የሚሆነውን በትእግስት መጠበቅ፣ መለወጥ ያለባቸው መንገዶች ካሉ እነሱን ማጤን እና የመሳሰሉትን ማድረግ የሚሲዮናውያኑም ሆነ የሚልካቸው አካል ተግባር መሆን አለበት። መጋቢ ተገኝ ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሰው፣ “በአንድ ወቅት በካምቦዲያ የተሰማራ አንድ የወንጌል መልእክተኛ ለበርካታ ዓመታት ቢደክምም ወደ ጌታ የመጣው ግንአንድሰውብቻነበር፤ነገርግንበዚያሰውበኩል ጌታ የሠራው የወንጌል ሥራ ዛሬ በካምቦዲያ ትልቁ ቤተ ክርስቲያን እንድትተከል ምክንያት ሆኗል” ሲል የአገልግሎቱ ፍሬ በጊዜ ሂደት ሊለካ እንደሚችል ያመለክታል።
የሚሲዮናውያኑ መዳረሻ እና ፍሬ
የሚሲዮን እንቅስቃሴውን በተመለከተ “እስከ አሁን በኢስት አፍሪካ ሚሲዮን በኩል ሰባት ቤተ ሰቦች ወደ ተለያዩ የአፍሪካ እና እስያ አገራት የተላኩ ሲሆን፣ በቃለ ሕይወት ዋናው ቢሮ፣ በመካነ ኢየሱስ፣ በመሠረተ ክርስቶስ፣ በገነት ቤተ ክርስቲያን፣ በግሬት ኮሚሽን እና በሌሎችም አብያተ ክርስቲያትና አገልግሎቶች የተላኩት፣ በግርድፍ ግምት ከኀምሣ የማይበልጡ ሚሰዮናውያን ተልከዋል ለማለት እንደሚቻል” አቶ ወርቁ ኃ/ማርያም ይናገራሉ። በተለያዩ አካላት ሚሲዮናውያኑ የተላኩባቸው አገራትን በተመለከተ አቶ ወርቁ ሲጠቅሱ፣ “ሕንድ መጀመሪያው ሲሆን፣ በፓኪስታን ከስድሣ በላይ የሚሆኑ የቤት ለቤት ቤተ ክርስቲያናት እንደተተከሉ፣ በዛምቢያ የልማድ ክርስቲያን የነበሩ ሰዎች ወደ እውነተኛው ክርስትና እንደተመለሱ፣ በደቡብ ሱዳን በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ አምስት ሺህ ሰዎች ወንጌል ሰምተው፣ 2400 ሰዎች ወደ ጌታ እንደ መጡ” ገልጸዋል።
እነዚህን ሰዎች በቀጣይነት የሚያስተምሩ የረዥም ጊዜ ሚሰዮናውያን እንደተላኩ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ “ወላይታ በሚገኝ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚረዳ አንድ ሚሲዮናዊ ቤተ ሰብ ወደ ቻይና የተላከ ሲሆን፣ እነዚህ ቤተ ሰቦች በቻይና የሚገኙ የቤት ቤተ ክርስቲያናትን ለወንጌል ተልእኮ እንዲያነሣሡና የቻይና ቤተ ክርስቲያናት ሚሲዮናውያን እንዲልኩ” በማስተባበር ላይ እንዳሉ ጠቁመዋል። በተመሳሳይም፣ “በቻድ የክርስትና እምነት ተከታዮች ያልሆኑ ዜጎች ባየሉበት አካባቢ የሚያገለግሉ ሁለት ቤተ ሰቦች እንዳሉ፣ በአገር ውስጥም በሙርሲ አካባቢ አንድ ቤተ ሰብ የጌታን ሥራ እየሠራ” እንደ ሆነ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በዚህ የወንጌል ተልእኮ አማካይነት “እስከ ሰባ የሚሆኑ ይፋዊ እና የቤት ለቤት አብያተ ክርስቲያናት እንደተተከሉ፣ ወንጌልን ለብዙ ሺህ ሰዎች የማሰማት ዕድል እንደተፈጠረ፣ ከሰሙት ውስጥም በአጠቃላይ ከዐሥር ሺህ የማይበልጡ ሰዎች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኛቸው አድርገው ማመናቸውን” ነው አቶ ወርቁ ለሕንጸት የተናገሩት።
ከዚህም የተነሣ፣ “በበርካታ የእስያ እና አፍሪካ አገራት የሚገኙ የአገሬው ተወላጆች ኢትዮጵያውያን የወንጌል መልእክተኞች እንዲመጡላቸው ይጠይቃሉ፤ ይህ ደግሞ በአካባቢው ካሉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ከሌሎች አገራት ከሚመጡ ሚሲዮናውያን ጋር ያላቸው መግባባት፣ የአገልግሎት ውጤታማነት፣ አብሮ የመኖር ባህል እንዲሁም ሥነ ምግባራዊነታችን የፈጠረው” እንደ ሆነ ነው የሚያስረዱት።
ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንድ እርምጃ ይሆን?
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሌሎች አገሮች ወንጌልን መመስከር መቻሏ አንድ እርምጃ እንደሚሆን ይታመናል። በተለይ የአፍሪካ፣ የእስያና የላቲን አሜሪካ አገራትን በወንጌል ለመድረስ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው የአውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት ከገጠማቸው ውድቀት የተነሣ የወንጌል ኀላፊነት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ላይ የወደቀ ይመስላል።
እንደ መጋቢ ወንድይፍራው አዲስ ከሆነ ሚሲዮናውያንን ወደ ተለያዩ አገራት መላክ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ትልቅ ርምጃ የሚቆጠር ብቻ ሳይሆን፣ የተስፋ ቃል ሙላትም ጭምር ነው። “ወንጌልን ከኢትዮጵያ ለዓለም የማድረስ ተልእኮ ኢትዮጵያ የተነገረላት የተስፋ ቃል መፈጸም መጀመሩን ማሳያ ነው” ይላሉ መጋቢ ወንድይፍራው።
ከአገር ውጪ የሚሲዮን ሥራ ላይ ለመሰማራት ራእይ ያላቸው ወደ ዐሥራ አምስት የሚጠጉ አብያተ ክርስቲያናትና አገልግሎቶች በመሰባሰብ አብረው እየመከሩ እንደ ሆነ አቶ ወርቁ ይናገራሉ። ይህም እርምጃ “እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል ሥርጭት ትልቅ ትኩረት መስጠት” እንዳበት አንዱ ማሳያ ነው። “በሕንጻ ግንባታ፣ በሙዚቃ መሣሪያና በኤሌክቶሪኒክስ ግዢ ላይ ለተጠመደችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቢያንስ የዐሥራት ያክል በጀትን ለሚሲዮን ጉዳይ ማዋል እንደሚገባ” ይመክራሉ። አያይዘውም፣ “የሐዋ. ሥ. 13 እንደምናገኛት እንደ አንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ላኪ መሆን አለባት፤ ስትልክ ደግሞ እንደ ሐዋርያት ዋናዋን ነው መላክ ያለባት እንጂ ሥራ የሌለውን አይደለም።” ሲሉ አቶ ወርቁ ያሳስባሉ።
“ዋናው ነገር ዋናውን ነገር ዋና ማድረግ ነው” የሚለው አባባል ለእያንዳንዱ አማኝ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚተው ሆኗል። የሚሲዮን እንቅስቃሴው የሚያመጣውን ሁለንተናዊ ለውጥ ትውልድ እንዴት ይዘክረው ይሆን?
Add comment