
ክርስትና ወደ ኢትዮያ መቼ ገባ?
“የተላኩ” በተሰኘው ዐምድ፣ ገናዬ ዕሸቱ ከምታስነብባቸው ተከታታይ ጽሑፎች ሁለተኛው የሆነው ይህ ጽሑፍ፣ ወንጌል ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል ተብሎ የሚታመንባቸውን ዘመናትና የአገባብ ሒደቶች ቀረብ አድርጋ ታስቃኘናለች።
[the_ad_group id=”107″]
ምኒልክ አስፋው
ካለፉት ሁለትና ሦስት ዐሠርት ወዲህ “ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት” (ethnocentrism and identity-centered movement) ማኅበራዊ ግንኙነቶችን በእጅጉ እየገራ መጥቷል። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ የምንፈልገው ከብሔርተኛነትና ከማንነት ወዳድነት አንጻር ነው። ብሔርተኛነት ሲባል ምን ማለት ነው? ማንነት ወዳድነት ሲባልስ ምን ማለት ነው? በቅድሚያ እነዚህ ሁለት ቃሎች ምን ሐሳብ እንደሚወክሉ እንመለከታለን፤ ከዚያም የእንቅስቃሴዎቹን ጣጣና መዘዝ እንቃኛለን። በመጨረሻም ከዜጎች፣ ከመንግሥትና ከሃይማኖት ተቋሞች የሚጠበቀውን ኀላፊነት እንዳስሳለን።
ብሔርተኛነት የአንድን ብሔር ማንነት የሚያጎላ፣ ሌሎች ብሔሮችን የሚያገልና ለራስ ብሔር ብቻ የሚቆረቆር ጽንፈኛነት ነው። ብሔርተኛነትና ዘረኛነት ተመሳሳይ ናቸው። ዘረኛነት በቆዳ ቀለም ላይ የተመሠረተ አግላይነት ሲሆን፣ ተግባሩም ቅልጥጥ ያለ ወጋጅነት ነው። ብሔርተኛነት የእኔ ብሔር ከአንተ ብሔር ይበልጣል፣ የእኔ ማንነት ከአንተ ማንነት ይበልጣል፣ የእኔ ባህል ከአንተ ባህል ይበልጣል፣ የእኔ ቋንቋ ከአንተ ቋንቋ ይበልጣል፤ እናም አንተና እኔ አንደራረስም፣ በክልሌም ሆነ በጠበሌ ዕድል ፈንታ የለህም የሚል አስተሳሰብ ነው።
ማንነት ወዳድነት ከራስ ወዳድነት ጋር ይመሳሰላል። ራስ ወዳድነት ሁሉም ነገር ለእኔ ብቻ ይሁን የሚል ኢምግባራዊ አስተሳሰብ ነው። ማንነት ወዳድነት የእኔ ዘር፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት ብቻ ይግነን (ይለምልም ይታወቅ) የሚል አስተሳሰብ ነው። የእኔ ማንነት መታወቅ አለበት፤ የእኔ ማንነት መግዘፍ አለበት፤ የእኔ ማንነት መግነን አለበት፤ የእኔ ማንነት መንገሥና መንሰራፋት አለበት፤ ሰዎች ሁሉ በእኔ ማንነት ሥር መጠለል አለባቸው የሚል አመለካከት ነው። ራስ ወዳድነት ራስ ጠቀምነት ነው፤ ሌሎችን ነፍጎና አሳጥቶ ራስን ብቻ ማሳደግ/ማሳረግ ነው። ባንጻሩም ማንነት ወዳድነት ሌሎችን በጥላቻ ዐይን የሚመለከት ደምሳሽነት ነው። ከእኔ ወገን ያልሆኑ ሁሉ በእኔ አገር ወይም መንደር መገኘት የለባቸውም የሚል አስተሳሰብ ነው።
ብሐርተኛነትም ሆነ ማንነት ወዳድነት ራስን የሁሉም ነገር ማእከል ማድረግና ሌሎችን በራስ ዙሪያ ማሾር ነው። ሌሎች ማእከል የላቸውም፤ ሌሎች ማንነት የላቸውም። የሁለቱም ግብ ሌሎችን መወገድ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ላይ መግነንና መሰልጠን ነው። ሌሎች የመኖር መብት የሚያገኙት እኔን ከሆኑና እኔን ከመሰሉ ብቻ ነው ማለት በእውነተኛው ዕብደት ነው። ጠለቅ ብለን ካሰብነው ግን በሰዎች መካከል ብርቱ ቅራኔ ከመፍጠሩም በላይ መቼም ለማይበርድ ጠላትነት ይዳርጋል፤ ጥሎት የሚሄደውም ጠባሳ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ይኖራል።
ሰውነት ከአብሮነት ውጭ ትርጒም የለውም። አንድነት ከሌለ፣ እኩልነት ከሌለ፣ ብልጽግና ከሌለ፣ ሰላም ከሌለ ማኅበራዊ ሕይወት ይተራመሳል፤ አገራዊ ዕድገት ይገታል።
እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፤ ከ80 በላይ ቋንቋዎች ይነገራሉ።2 ሁለት ታላላቅ ሃይማኖቶች አሉ፤ ክርስትናና እስልምና። ቊጥራቸው ትንሽ ቢሆንም ባህላዊ እምነት የሚከተሉ አሉ። ምናልባትም ኢአማንያንም ሊኖሩ ይችላሉ። ታዲያ ተጨባጩ ሁኔታ ይህ ከሆነ ማንነት ወዳድነት (ጥሩ ነገር ነው ቢባል እንኳ) እንዴት መስፈን ይችላል? የእኔ ዘር ብቻ፣ የእኔ ብሔር ብቻ፣ የእኔ ቋንቋ ብቻ፣ የእኔ ባህል ብቻ፣ የእኔ መንደር ብቻ፣ የእኔ ሃይማኖት ብቻ የምንል ከሆነ፣ መቼም መች አብረን መኖር አንችልም። ምክንያቱም ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት ከፋፋይነትና ነጣጣይነት ነው። መከፋፈልና መነጣጠል ደግሞ ለእርስ በእርስ ቅራኔና ቁርቁስ ይዳርጋል። በእውነተኛው ለኢትዮጵያም ሆነ ለመላው ዓለም እንዲህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ከቶ አይበጅም።
ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት የአንድነት ጠር ነው፤ የእኩልነት ጠር ነው፤ የብልጽግና ጠር ነው፤ የሰላም ጠር ነው፤ በጥቅሉ የሰውነት ጠር ነው። ሰውነት ከአብሮነት ውጭ ትርጒም የለውም። አንድነት ከሌለ፣ እኩልነት ከሌለ፣ ብልጽግና ከሌለ፣ ሰላም ከሌለ ማኅበራዊ ሕይወት ይተራመሳል፤ አገራዊ ዕድገት ይገታል። ርግጥ ሌሎችን በማይጎረብጥና በማይሰቀጥጥ መንገድ ስለ ራስ ብሔር፣ ቋንቋና ሃይማኖት መናገር ይቻል ይሆናል። ነገር ግን የእኔ ማንነት ይንገሥ፣ የሌሎች ማንነት ይደምሰስ ማለት ትልቅ ስሕተት፣ ዐልፎ ተርፎም ኢምግባራዊነት ነው። ምክንያቱም ልዩ ልዩነት እንጂ አንድ ዐይነትነት አያምርም፤ ውበትም ሆነ ክብደት የለውም። ልብ እንበል፤ አንድነት ወይም አብሮነት ማለት አንድ ዐይነትነት ማለት አይደለም። ሁሉም ነገር አንድ ዐይነት እንዲሆን መፈለግ የሥነ ፍጥረትን ውበትና ልቀት ይደመስሳል። ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት አንድ ዐይነት ለመሆን መፈለግ ነው።3 አዲስ አበባን እንደ ምሳሌ ብንወስድ አዲስ አበባ ልክ እንደ አሜሪካ “ማቅለጫ ድስት” (melting pot) ናት ማለት ይቻላል። አዲስ አበባ የብዙ ብሔሮች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች መዲና ናት። ታዲያ አዲስ አበባ ከዳር እስከ ዳር እንዴት አንድ ዐይነት መሆን ትችላለች? የማንኛው ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት መታወቂያ መሆን ትችላለች? መጠኑ ይለያይ እንጂ የመላው አገሪቱ ገጽታም ከዚህ ብዙ አይርቅም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት እንዲነግሥ የሚታገሉ ወገኖች ቆም ብለው ራሳቸውን እንዲጠይቁ ልመናዬን አቀርባለሁ። የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲመለከቱ በብርቱ አሳስባለሁ። ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት ትክክለኛ አስተሳሰብ አይደለም። የአገራቸው ዕድገት የሚያሳስባቸው ወገኖች አገራቸው በብሔርተኛነትና በማንነት ወዳድነት እንድትለከፍ መንገዱን አይጠርጉም። ከዚህ በፊት የነበሩ አስተዳደሮች በድለውኛል የሚሉ ወገኖች ካሉ ሌላ በዳይ አስተዳደር እንዲፈጠር መጣደፍ የለባቸውም። ከዚህ በፊት በሌሎች መበደል አዲስ በዳይ ለመሆን መብት አይሰጥም። ተበድለናል በሚል ስም እኛም በተራችን በዳይ እንሁን ማለት ሰውኛነት አይደለም። ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት ከፋፋይ ከመሆኑም በላይ እርስ በእርስ ያባላል፤ ያቆራቁሳል፤ ያቆረቁዛል። አዲስ የበዳይነት (ጨቋኝ በዝባዥነት) ሥርዐት እንዲፈጠር ያደርጋል። እንኳን በብዙ ነገራቸው ተመሳሳይ ያልሆኑ ብሔሮች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች ያሉባት አገር ይቅርና በብዙ ነገራቸው ተመሳሳይ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት ያላቸው አገሮችም አንድነት እያጡ ናቸው፤ እርስ በእርስ በመከፋፈላቸው ሳቢያ።
ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት እንዲሰፍን የሚታገሉ ወገኖች ከዚህ በፊት የነበሩ አስተዳደሮች የፈጸሙትን ትልቅ ስሕተት ለመድገም የሚመኙ ወገኖች ናቸው። ደርግ ርእዮተ ዓለማዊነትን አገነነ፤ ኢሕአዴግ ብሔርተኛነትን አገነነ። ሁለቱም ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ነበሩ። ማንነት ወዳድነት እንዚህን ሁለት ጽንፎች ይበልጥ አጡዞ ያሳርጋል። ማሳረጊያው ግን የባሰ እንዳይሆን እፈራለሁ። ግልጹን እንነጋገር ከተባለ ሰው ሰውን አያርድም። ሲበዛ ካልሴጠንን በስተቀር ሰው የሰውን አንገት ቆርጦ አይሳለቅም። በኢትዮጵያ ምድር ይህ ተፈጽሞ መመልከት ሁላችንንም ሊያስደነግጠን ይገባል። ከሁለት ዓመት በፊት አክራሪ ጽንፈኞች በሊብያ በረሃ ላይ የምስኪን ኢትዮጵያውያንን አንገት ሰይፈው ነበር፤ ድርጊቱ አካይስታዊ ድርጊት ነው ብሎ ያላለቀሰና ልቡ ያልተሰበረ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ያንን ድርጊት ከተጸየፍን አሁን በኢትዮጵያ ምድር እየተፈጸመ ያለውን ድርጊት መጸየፍ አለብን። ያንን ድርጊት የፈጸሙ ግለ ሰቦች ማንነት ወዳድነት (ጽንፈኛ ሃይማኖተኛነት) ወርሷቸው ነበር። በማንነት ወዳድነት የተወረሱ ሰዎች ይሴጥናሉ ለማለት ያስደፍራል። ሰዎች ካልሴጠኑ በስተቀር እንዴት ስለት አንሥተው በሰው አንገት ላይ ያሳርፋሉ? ጭካኔውን ከየት አገኙት? ምን ኀይል ሰጣቸው? ምን ከሰውነት ተራ አወጣቸው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የአቤልንና የቃየንን ታሪክ ማስታወስ ይኖርብናል። ታሪኩን ቀረብ ብለን ስንመለከት ወጋጅነት ምን እንደ ሆነ ብቻ ሳይሆን መዘዙም ምን እንደ ሆነ ያስተምረናል።
አቤልና ቃየል ወንድማማቾች ነበሩ፤ ከአንድ አባትና እናት ተወልደው በአንድ ምድር ይኖሩ ነበር። አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባህል፣ አንድ ዘር ምናልባትም አንድ ሃይማኖት ነበራቸው። ይብስ ብሎም ከእነርሱ በፊት መወጋገድም ሆነ መገዳደል አልነበረም። ይሁንና ቃየል ወንድሙን አቤልን ገደለ። ለምን? ቃየን እንዴት ጨከነ? ሐሳቡንና ኀይሉን ከየት አገኘው? የቃየል ድርጊት ምናልባት የመጀመሪያው ወጋጅነት ሳይሆን አይቀርም። በቃየልና በአቤል መካከል የምናየው ሽኩቻ ከእነርሱ በኋላ የተነሡ የሰው ልጆች ሁሉ ተከትለውታል። ታሪኩን በሌጣው ስንመለከተው ግን ሽኩቻ ብቻ ይመስላል። ነገር ግን ብርቱ መወጋገድም አለበት። እኔ የምፈልገው እንጂ አንተ የምትፈልገው አይሆንም፤ እኔ የምፈቅደው እንጂ አንተ የምትፈቅደው አይሆንም፤ እኔ ያሰብሁት እንጂ አንተ ያሰብኸው አይፈጸምም የሚል ትምክህት አለበት። ይህ የሁለቱ ወንድማማቾች ቅንቅን (መገፋፋትና መከፋፋት) በሰው ልጆች ታሪክ ሲፈጸም የሚታይ መርገፍ ሆነ።4 የሰው ልጆች ይህን መንገድ ሲከተሉና ተግባሩንም ይበልጥ ሲያከፉት ታይቷል።
አቤልና ቃየል በብዙ ነገር እኩል ነበሩ። ሁለቱም ሰው ናቸው (አንዱ ሙሉ ሰው ሌላው ንኡስ ሰው አይደሉም)። ሁለቱም የተመሰገነ ሥራ ነበራቸው። በትረካው ውስጥ ለሁለቱም የተሰጠው ስፍራ እኩል ነው፤ ማለት ተራኪው በአተራረክ ስልቱ አላበላለጣቸውም።5 ልዩነት የተፈጠረው ሁለቱ መሥዋዕት ባቀረቡ ጊዜ ነው። እግዚአብሔር ወዳቀረቡት መሥዋዕት ተመልክቶ የአንዱን ሲቀበል የሌላውን ሳይቀበል ቀረ። ይህ ለመወጋገድ ምክንያት ሆነ። እግዚአብሔር የአንዱን ተቀብሎ የሌላው ያልተቀበለበት ምክንያት አለው። አቤል ከበጎቹ መካከል ምርጥ የሆነውን (ተራኪው እንደሚለው “የሰባውን”) ሲያቀርብ ቃየል ግን ካመረተው ሰብል መካከል እጁ ያነሣውን አቀረበ። አቤል ምርጡን አቀረበ፤ ቃየል መናኛውን አቀረበ። ምርጥነቱንና መናኛነቱን የመዘነው እግዚአብሔር ቢሆንም፣ ተራኪው ግን ምክንያቱን አልነገረንም።6 በሁሉም ነገር ተካክለው ሳለ ቃየል በራሱ ውሳኔ ከእኩልነት ጎደለ።
እግዚአብሔር ወደ አቤል ሲመለከት ወደ ቃየል ግን አልተመለከተም። በዚህም ቃየል ተናደደ፤ በገነ፤ ዐይኑ ደም ለበሰ፤ በገዛ ወንድሙ ላይ ለበቀል ተነሣ። እናም እግዚአብሔርን መግደል ስለማይችል ወንድሙን ገደለ።7 በአዲስ ኪዳን ቋንቋ ነፍሰ ገዳይነት “ከክፉው” መሆን ነው (1ዮሐ 3፥12)። ነፍሰ ገዳይነት “የቃየል መንገድ” ተብሏል (ይሁዳ 11)። እግዚአብሔር ቃየልን ከክፉው መንገድ ለመመለስ ብዙ ጥሯል። አራት ጊዜ ጥያቄ ጠይቆታል፤ 1) ለምን ተናደድህ? 2) መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? 3) ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? 4) ምን አደረግህ? ከዚህም በላይ ምክር ሰጥቶታል፤ “ኀጢአት በደጅ ታደባለች፤ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት”። ቃየል ግን ለመመለስ አሻፈረኝ አለ። ወንድሙን “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። ሜዳ ለምን ተመረጠ? ሜዳ የተመረጠው ተመልካችና ምስክር እንዳይኖር ነው። ቃየል በድርጊቱ ሁለቱንም ማለትም ወንድሙን አቤልንና እግዚአብሔርን ከሕይወቱ ወገደ። ቃየል ወንድም ነበረው፤ እርሱ ግን ወንድም አልነበረም። አምላክ ነበረው፤ እርሱ ግን ከአምላክ አልተወዳጀም። ቃየል “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ ሐሰት ከመሆኑም በላይ ራሱን ከተጠያቂነት አሸሸ። “አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” ሲል የሐሰት አሠራር እንዲነግሥ መፍቀዱ ነበር። ሐሰት በነገሠበት ፍትሕ የለም። ቃየል በውስጡና በውጭ የሚመክረውንና የሚወቅሰውን ድምፅ አፈነ። በዚህም በአንድ ጊዜ ራሱን ከወንድሙና ከአምላኩ እንዲሁም ከአብሮነት ወገደ። 8
እኔ ክርስቲያን እንደ መሆኔ ይህን ጥያቄ በከፊል የምመልሰው እንደ ክርስቲያን ነው። በዚህ ዓለም የምናያቸው ችግሮች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሄደው ሄደው የሚዛመዱት ከውድቀት መዘዝ ጋር ነው። ውድቀት የሰውን ልጆች ሁለንተና በክሏል፤ ሥር ነቀል በሆነ መንገድ አዛብቷል። ጳውሎስ በሮሜ 7፥15 ላይ “የማደርገውን አላውቅምና፤ የምጠላውን ያን አደርጋለሁና፤ ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርገውም” ሲል ሰዎች በክፉው መታሰራቸውን መግለጹ ነበር። ይህን ሐሳብ ይበልጥ ያብራራው በኤፈሶን መልእክቱ ላይ ነው። “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ . . . አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ” ታዛዦች ነበራችሁ ይላል (2፥1-2)። ጳውሎስ “አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ” ሲል ሌላ ማንንም ሳይሆን እኩዩን መንፈስ፣ እርሱም ሰይጣንን ነው።
ሰዎች ከሰውነት ተራ ወጥተው የሚሴጥኑት በእርኩስ መንፈስ ሲያዙ ነው።9 እርኩሳን መናፍስት ሰዎችን ያሳውራሉ፤ ኅሊናቸውን ያደነዝዛሉ፤ ልቡናቸውን ያጨልማሉ። አሁን አምሳያን እኩያን መግደል ነውር አይሆንም። መጥፎውና እኩዩ ተግባር ምንም አይመስልም። ሴጥነን ሳለ ራሳችንን እንደ መልአክ እንመለከታለን (ኤር 6፥13-15፤ ሕዝ 13፥8-16)። ሁሉም ነገር መጥፎነት ወርሶት ሳለ መልካም እንደ ሆነ እናስባለን። ቅዱሳት መጻሕፍት የክፋት አሠራር ምንጩ እርኩሳን መናፍስት እንደ ሆኑ ነው የሚያስተምሩት። ሰዎች በእርኩስ መንፈስ አሠራር ውስጥ ሲወድቁ በቀላሉ ይታለላሉ፤ በቀላሉ ይሸነገላሉ። ሰይጣን ሸንጋይ ነው (ኤፌ 6፥11)። በመሆኑም እርኩሳን መናፍስት ሥራቸው ማሳወር ብቻ ሳይሆን ማታለልም ነው።10 እውነቱን እንዳናስተውል ያሳውሩናል፤ ሐሰቱን እውነት አድርገው ያቀርቡልናል። ለዚህ ነው የምናምናቸው ሰዎችና ሚዲያዎች ነገሩን (የመጨረሻ እኩይ ተግባር ሆኖ ሳለ) እነርሱ ስላዜሙት ብቻ እውነት የሚመስለን። የማናውቀውን ማድረግ ይሄ ነው፤ የምንጠላውን ማድረግ ይሄ ነው፤ የሚወደደውን ሳይሆን የሚጠላውን ማድረግ ይሄ ነው። እናም የጎዳን መታወራችን ነው። ልቡናችን ሲታወር እውነቱን ከሐሰት መለየት ይሳነናል። መልካሙን ለማድረግ አቅምና ጉልበት እናጣለን።
ሰዎች ከሰውነት ተራ ወጥተው የሚሴጥኑት በእርኩስ መንፈስ ሲያዙ ነው። እርኩሳን መናፍስት ሰዎችን ያሳውራሉ፤ ኅሊናቸውን ያደነዝዛሉ፤ ልቡናቸውን ያጨልማሉ።
ታዲያ መታወር ከመሴጠን፣ ማለትም ከዐመፀኛነት ጋር ያለው ዝምድና ምንድን ነው? እንል ይሆናል። ከላይ እንዳመለከትሁት ሰዎች ሲታወሩ ይሴጥናሉ፤ ከሰውነት ተራ ይወጣሉ። ይህ አንዱ ገጽታ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አመለካከታቸውን የሚገራ ማእከል ያጣሉ። በዐጭሩ ማእከለ ቢስ ይሆናሉ። ሰዎች ኅሊናቸውን፣ ስሜታቸውን፣ ፍላጎታቸውን፣ ምኞታቸውን፣ ፈቃዳቸውን የሚገዛና እንደ ልጓም የሚይዛቸው ነገር ከሌላቸው ሕገ አራዊትነት ይወርሳቸዋል። አሁን ሁሉም ነገር ይፈቀዳል። ነውር የሚሆን ምንም ነገር የለም። አሁን ራስነት፣ እኔነት፣ ማንነት ይነግሣል። በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነት፣ ወዘተ እኛን የማይመስሉ ሁሉ ይወገዱ ብለን እንነሣለን። ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት ወጋጅነት የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው። ይህ እንዲሰፍን የሚፈልጉ ሰዎች ብርቱ ጣጣና መዘዝ እንዳለው አይረዱም። ስለታወሩና ማእከለ ቢስ ስለሆኑ ድርጊቱ ትክክል ይመስላቸዋል። ይሁንና ሌሎችን በወገድን ቊጥር ብርቱ ቅራኔ እየጋበዝን ነው። እኔ ብቻ ስንል ሌሎችን ዕድል ፈንታ እየነሳን ነው። ውጤቱ መራራ ወደሆነ መደምደሚያ እየቀዘፍን ነው። እዚህ ላይ በጀርመን ናዚዎችና በሩዋንዳ ብሔርተኞች የተፈጸሙ ሁለት አዋኪ ድርጊቶችን እንደ አብነት ብንመለከት ጣጣውንና መዘዙን ከታሪክ ለመማር ዕድል ይሰጠናል። ብልህና አስተዋይ ሰው ከታሪክ ይማራል፤ በዚህም የሌሎችን ስሕተት ከመድገም ይተርፋል።
የጀርመን ናዚዎች በአይሁዶች ላይ የፈጸሙት ግፍ ከማንነት ወዳድነት የመነጨ ነበር። ሰዎች በማንነት ወዳድነት ሲመጠጡ (ሙሉ በሙሉ ሲወረሱ) ኢሰብአዊነት ይነግሥባቸዋል። በእነርሱ ግዛት ሌሎች ለመኖር አይፈቀድላቸውም። የጀርመን ናዚዎች የእኛ ዘር ብቻ ነው ንጹሕ ዘር ብለው ተነሡ። ቆሻሻ የሚሉትን ዘር (አይሁዶችንና ጂፕሲዎችን) ለመደምሰስ በቅድሚያ ምክንያት መፈለግ ነበረባቸው።11 ርግጥ ይህ በእነርሱ አልተጀመረም። በጥንት ግሪካውያን፣ ግብፃውያንና ፋርሳያን ሥነ ጽሑፎች ውስጥ “አመካኝነት” በጣም የሚታወቅ ተግባር ነበር። ሌሎችን ለመጥላትና ዕድል ፈንታ ለመንፈግ በቅድሚያ ምክንያት መፈለግ ያስፈልጋል። ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ቀላል ይሆናል።12 የጀርመን ናዚዎችም ልክ እንዲሁ ነበር ያደረጉት። በመጀመሪያ አይሁዶችን ተምቾች ናቸው፤ ጥገኞች (parasites) ናቸው በማለት እንዲጠሉ አደረጉ። ከዚያም ሰብእናቸውን የሚያዋርድ ስም ሰጧቸው፤ ከአይጥ ጋር አመሳለሏቸው፤ እንደ ንኡስ ሰው (subhumane) ቈጠሯቸው። በመጨረሻም አንድ በአንድ እየለቀሙ አስወገዷቸው። ለማስወገድ ግን በቅድሚያ ማጥላላት ነበረባቸው (“ጠላት ይቀባል ጥላት” እንዲሉ)። ማጥላላት ከተቻለ ሁሉም ነገር ቀላል ይሆናል።13
አይሁዶችን ያስወገዱበት መንገድ ግን መቼም የማይረሳ ዘግናኝና ሰቅጣጭ መንገድ ነው። እንደ እንስሳ በለቷቸው፤ በጥይት ቆሏቸው፤ በዘይት ቀቀሏቸው፤ በመርዝ ጋዝ አፈኗቸው፤ በእሳት ጠበሷቸው። ይህ ፍጹም ኢሰብአዊ ተግባር ቀላል የሆነላቸው እንደ ሰው ስላልቈጠሯቸው ነው። ንጹሕ ዘር የጀርመኖች ዘር ብቻ ነው፤ የሌሎች ዘር ብርዝ ድልዝ ነው፤ ያልጠራና ያልጠዳ ነው። ስለዚህ አገራችን ከቁሻሻ መጽዳት አለባት ብለው ተነሡ።14 ለናዚዎች አይሁዶች ሰው ሳይሆኑ በሽታ አስተላላፊ አይጦች ነበሩ። ሰብእናቸው ወርዶ ከአይጥ ሲተካከል ለመግደል ቀላል ሆነላቸው።
እዚህ ላይ የሚነሣው ጥያቄ ታዲያ ምን እንዲህ አጨከናቸው? ምን አሴጠናቸው? የሚለው ነው። ፍረጃ ወደ ጥላቻ ይወስዳል፤ ጥላቻም ወደ ውገዳ ያመጣል። ሰዎች በጭካኔ ተግባር የሚሳተፉት (የሚሴጥኑት) ውስጣቸው በብርቱ ጥላቻ ሲሞላ ነው። ልዩ ልዩ ምክንያት ፈጥረን ሌሎችን ከእኛ ስናሳንስና እንደ ንኡስ ሰው መቊጠር ስንጀምር ዘግናኝና ሰቅጣጭ ተግባር ለመፈጸም (ለመሴጠን) ቀላል ይሆናል። የባሪያ ፍንገላም መሠረቱ ተመሳሳይ ነው። የጥቁሮችና የነጮች አፈጣጠር ይለያል፤ ጥቁሮች ከእንስሳ ትንሽ ከፍ ቢሉ እንጂ ሰው አይደሉም፤ መደባቸው በዝንጀሮና በነጮች መካከል ነው፤ በሰብእናም ሆነ በሰውነት ከነጭ አይተካከሉም። ስለዚህ ጥቁሮች ንብረት እንጂ እንደ ሰው መቈጠር አይችሉም የሚል ንቀት ነበር።15 ጥቁሮች ሰው ካልሆኑ ይልቁንም እንደ እንስሳ ከተቈጠሩ በእነርሱ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ግፍ እንደ ግፍ አይቈጠርም፤ ሰው አይደሉማ።
ሌሎችን በራስ አምሳል ለመፍጠር መፈለግ ትልቅ ኢምግባራዊነት ነው።
በሩዋንዳ የተፈጸመውን ዘር ጨፍጫፊነት ስንመለከት ደግሞ አሁንም መሠረቱ ተመሳሳይ ነው። በወቅቱ የሩዋንዳ ሕዝብ ቊጥር ወደ 7 ሚሊዮን ይጠጋ ነበር። በአገሪቱ ውስጥ ሦስት ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ይኖሩ ነበሩ። ሁቱዎች 85% ሲሆኑ፣ ቱትሲዎች 14% እንዲሁም ትዋዎች 1% ነበሩ። አብላጫ ቊጥር የነበራቸው ሁቱዎች ‘ስንበደል ኖረናልና አሁን ነጻ መውጣት አለብን’ ብለው ተነሡ። ነጻ ለመውጣት የመረጡት ስልት ዘር ጨፍጫፊነትን ነበር። በ100 ቀናት ውስጥ ወደ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ ቱትሲዎች ተጨፈጨፉ። እጆች ተቈረጡ፤ እግሮች ተቸረቸፉ፤ አንገቶች ተቀነጠሱ፤ ቤቶች በእሳት ነደዱ፤ ቤተ ጸሎቶች ዐመድ ሆኑ፤ አገር ቀወጠች፤ ሩዋንዳ በደም ተነከረች። ይህ ሁሉ ጥፋት እንደምን ሊደርስ ቻለ? ሁቱዎችን ምን እንደዚያ አጨከናቸው? ምን ለሰይጣናዊ ተግባር ዳረጋቸው? የሚቈርጡት የሰው እጅ፣ የሚቸረችፉት የሰው እግር፣ የሚቀነጥሱት የሰው አንገት እንደ ሆነ እንደምን ጠፋቸው? ምን አሳወራቸው? ምን አደነዘዛቸው? ሰዎች በብሔርተኛነትና በራስ ማንነት ወዳድነት ቊጥጥር ሥር ሲሆኑ፣ አስተሳሰቡ ሲገዛቸውና ሲወርሳቸው ይሴጥናሉ። አቅላቸውን ስተው ከሰውነት ተራ ይወጣሉ። ውስጣችን በጥላቻና በዛቻ ሲሞላ እጃችን ሰይፍ ለመምዘዝና ቃታ ለመሳብ ኀይል ያገኛል። ጥላቻ ዐይን ያሳውራል፤ ኅሊና ያጨልማል። በክፉው መታሰር ለክፉ ተግባር ያነሣሣል።
ርግጥ ከሩዋንዳው አሳዛኝ ታሪክ በስተጀርባ የቅኝ ገዢዎች እጅ አለበት የሚለው ሙግት ሚዛን ይደፋል። ቅኝ ገዢዎች በቀጥታም ይሁን በእጅ አዙር በአፍሪካ ውስጥ ለተፈጠረው ፍጅት ተጠያቂ ናቸው። የአፍሪካ ፖለቲካዊ ችግር እስከ አሁን ድረስ መፍትሔ ማግኘት ያልቻለው ቅኝ ገዢዎች በፈጠሩት ሤራ ነው። ወደ ሩዋንዳ ስንመጣ ጀርመኖችና ቤልጂየሞች ለቱትሲዎች ልዩ ስፍራ ይሰጡ ነበር። በሁለቱ ብሔሮች መካከል ማንነት ወዳድነት እንዲነግሥ መንገዱን የጠረጉት ቤልጂየሞች ናቸው የሚሉ ሰዎች አሉ። ቱትሲዎች ልዩ ስፍራ ባገኙ ቊጥር ሁቱዎች መገፋታቸው አልቀረም። ይህ የቱትሲዎች ልዩ ስፍራ ማግኘትና በአንጻሩም የሁቱዎች ስፍራ መነፈግ ቂም በቀል አርግዞ ቆየ። ከዚያም በራሱ ምቹ ጊዜ ፈነዳ። ሲፈነዳ ግን ጣጣውና መዘዙ ደም የሚያቃባ ነበር።
በሩዋንዳ የደረሰውን ዘር ጭፍጨፋ በዐይናቸው የተመለከቱ ሰዎች እንደ መሰከሩት ሁኔታውን በቃል ለመግለጽ ይከብዳል። በጣም ዘግናኝና አሠቃቂ ነበር። አንዳንድ ሰዎች የተገደሉት በየቀኑ ከሰውነታቸው ላይ አካል እየተቈረጠ ነበር። አንዳንዶች አናታቸው እንደ እባብ ይከተከት ነበር። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ለመሞት እስከ ሰባት ቀን ይወስድባቸው ነበር። ወዲያውኑ የተገደሉት ሰዎች ከብርቱ ሥቃይ ተርፈዋል። በየቀኑ አካላቸው የተፈለጠው ግን ብርቱ ሥቃይ ደርሶባቸዋል።16 ሁቱዎች የቱትሲዎችን አካል እየፈለጡ ከወንዝ/ከሐይቅ ሲጨምሩ ወደ መጣችሁባት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ እያሉ ይዘፍኑና ይሸልሉ ነበር። እንደ ሁቱዎች አባባል እነርሱ ነባሮች ባላገሮች፣ ቱትሲዎች ግን መጤዎች ፈላሾች ናቸው። እናም ሩዋንዳ ለሁቱዎች እንጂ ለቱትሲዎች አትገባም።
እንደ ጀርመን ናዚዎች ሁሉ ሁቱዎችም ለቱትሲዎች ሰብእናቸውን የሚያዋርድ ስም ሰጥተው ነበር፤ በረሮና እባብ (cockroaches and snakes) የሚል። በዚህ ጥላቻ የተሞሉት ሁቱዎች ዕቅዳቸው እንዲያውም የቱትሲዎችን ዘር ከምድረ ሩዋንዳ ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ ነበር። RTLM (Radio Television Libre des Mille Collines) የተሰኘ የሬዲዮ ጣቢያ አንዱና ዋነኛው የዐመፁ ቀስቃሽ ነበር። ሁቱዎች ገጀራ፣ ሳንጃ፣ በምስማር የተጠቀጠቀ ዱላና መሣሪያ ይዘው እንዲወጡ ተጎተጎቱ። እንደ ተባሉትም አደረጉ። ውጤቱ ዘግናኝ ነበር። ብሔርተኛነት ጣጣውና መዘዙ አያድርስ ነው። ሰዎች ከመሬት ተነሥተው አይሴጥኑም፤ ድንገት ወደ አውሬነት አይለወጡም። ሰዎች እንዲሴጥኑና ወደ አውሬነት እንዲለወጡ በቅድሚያ በጥላቻ መጠቅጠቅ አለባቸው። በቅድሚያ ተበድለሃል፣ ተጨቁነሃል፣ ተረግጠሃል፣ አሁን ተራው የአንተ ነውና ተነሥ መባል አለባቸው። በቅድሚያ ሥነ ልቡናቸው በክፉ ሐሳብ ተመርዞ ለጨካኝነት መዘጋጀት አለባቸው። ከዚያም የሚገድሉት ሰው በሰብእናው ወይም በሰውነቱ ከእነርሱ እንደሚያንስ እንዲያውም እንስሳ (አይጥ፣ በረሮ፣ እባብ) እንደ ሆነ መቀበል አለባቸው። አሁን ሁሉም ነገር ቀላል ይሆናል። በእኛም አገር እኮ “ነፍጠኛ” የሚል ቅጽል ስም ወጥቷል፤ ቀጥሎ ምን ስም እንደሚወጣ ባላውቅም። ለምን? ቢባል መልሱ ቀላል ነው። ሌሎችን ለማጥቃት በቅድሚያ ማጥላላት አለብን። በሌሎች ላይ ለመጨከን በቅድሚያ ሁለንተናችን መመረዝና መሰለብ አለበት። አጥላልተን ስንጨርስና ከሰውነት ተራ ወጥተን ስንሴጥን አሁን የምንፈልገውን ነገር ለማድረግ ምቹ ይሆናል። በብሔርተኛነትና በማንነት ወዳድነት ስንመረዝ እንሴጥናለን፤ ስንሴጥን የጥፋት መልእክተኞች እንሆናለን።
አንዳንድ ወገኖች አሁን በአገራችን የተከሰተው ችግር ከውስጥ ሳይሆን ከውጭ የመጣ ነው ይላሉ። የችግሩንም ምንጭ የሚያዛምዱት ከውጭ ኀይሎች ጋር ብቻ ነው። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ችግራችን ጽንፈኛ ሃማኖተኛነት እንጂ ብሔርተኛነት አይደለም ይላሉ። እኔ እነዚህ ሁለት አስተያየቶች ትክክል አይመስሉኝም። ምክንያቱም የአገራችን ችግር ውጫዊ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊም ነው። ጽንፈኛ ሃይማኖተኛነት ብቻ ሳይሆን ብሔርተኛነትም ነው። የውጭ ኀይሎች ኢትዮጵያ እርስ በእርስ ፍጭት እንድትዳከም መፈለጋቸው መቼም የማያባራ ተግዳሮት ነው። ያለፉትን መቶና ሁለት መቶ ዓመታት ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን ብንመለከት ይህንኑ ነው የሚያረጋግጥልን። አሁንም ሆነ ወደፊት አገሮችና ግለ ሰቦች ከውጭ ሆነው ኢትዮጵያን ያጠቃሉ። ግን ደግሞ የራሷ ዜጎችም ከውስጥ ሆነው ሆነ ብለው አስበውና አቅደው ምስኪኗን አገራቸውን ያጠቃሉ። አሁን አሁን እንዲያውም “ኢትዮጵያ ትውደም” የሚል መፈክር የሚያሰሙ የራሷ የኢትዮጵያ ዜጎች ተነሥተዋል። እኔ የአገሩን መውደም የሚመኝ ሰው በሕይወቴ ስመለከት ይህ የመጀመሪያው ነው፤ ለሌሎችም እንዲሁ ነው ብዬ እገምታለሁ። ሰው በአገሩ ቅር ሊሰኝ ይችላል። በአገሩ ውስጥ ባለው ፖለቲካዊ ትርምስ ላይደሰት ይችላል። አገሩ እንድትወድም ግን አይመኝም። የአንድን አገር መውደም የሚመኙት (አይኖሩም ብዬ አልሞግትም) የሌላ አገር ዜጎች ብቻ ናቸው። በአገራቸው ፖለቲካዊ አቋም ምክንያት በደል የደረሰባቸው ሰዎች ሥርዐቱ እንዲለወጥ ይመኛሉ እንጂ አገራቸው እንድትጠፋ አይመኙም። እንዲህ ዐይነቱ ምኞት ሲደመጥ ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። አነጋገሩ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡም በእጅጉ ያውካል። እንዴት ግን ወደዚህ ደረጃ ደረስን? ይህን ጥያቄ ለመመለስ በሁለት አሕጉሮች የተከሰቱ ሁለት የቅርብ ጊዜ ታሪኮችን በመጥቀስ ልንደርደር።
አንደኛው የአሜሪካን ጥቁሮች ታሪክ ነው። በአሜሪካን አገር ጥቁሮች ብዙ ግፍ ደርሶባቸዋል። በባርነት ወደ አሜሪካን ከገቡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ በሥርዐቱ ተበድለዋል። የአሜሪካን ጥቁሮች በጠራራ ፀሓይ ተሰቅለዋል፤ ከእነ ሕይወታቸው በእሳት ተቃጥለዋል። ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው ተደፍረዋል፤ እንደ ሰው ሳይሆን እንደ እንስሳ ተቆጥረዋል። ከአገሪቱም ሲሳይ ተነፍገዋል። ይህ ሁሉ የተደረገው ሆን ተብሎ በዕቅድና በጥናት ነው። ሁለተኛው የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ታሪክ ነው። የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችም ተመሳሳይ ግፍ ደርሶባቸዋል። በጥይት ተቆልተዋል፤ ተናካሽ ውሻ ተለቆባቸዋል፤ ንብረት እንዳያፈሩ ተደርገዋል። አሁንም ይህ ሁሉ ግፍ የተደረገው ሆን ተብሎ በዕቅድ ነው። በአሜሪካንም ሆነ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ጥቁሮች ይህ ሁሉ ግፍ ሆን ተብሎ ተፈጽሞባቸው አሜሪካን ትውደም ወይም ደቡብ አፍሪካ ትውደም አላሉም። ይልቁንም እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግና እንደ ኔልሰን ማንዴላ የመሳሰሉ ሰላማውያን አርበኞችን ከጉያቸው አፈሩ። አገራቸው እንድትወድም ሳይሆን ሥርዐቱ እንዲለወጥ ተመኙ፤ ታገሉ፤ ተሠዉ። ንብረት ማውደም አንድ ነገር ነው። ሰዎችን በአሠቃቂ መንገድ መግደል ግን ሌላ ነገር ነው። ሁለተኛው ድርጊት በጣም ይከፋል። ድርጊቱን የከፋ የሚያደርገው በሰዎች መፈጸም የማይገባው ድርጊት ተፈጽሞ በመገኘቱ ነው። ሰው የሰውን አንገት አይቆርጥም፤ በጭራሽ። ሰው በዘር ጭፍጨፋ ተግባር አይጠመደም፤ ከቶውንም። ይህ ሁሉ የተፈጸመው ደግሞ በራስ ዜጎች ላይ መሆኑ ነገሩን በጣም አዋኪ፣ ማለትም ረፍት የሚነሣ፣ ሁለንተናን የሚያራቁትና የሚቆጠቁጥ ተግባር ያደርገዋል።
አሁን እዚህ ላይ ያመጣሁት ንጽጽር፣ ይኸውም ዘረኛትና ማንነት ወዳድነት እንዴት ሰዎችን ከሰውነት ተራ እንደሚያወጣና ለእኩይ ተግባር እንደሚዳርግ ለመግለጽ ነው። ነጭነት ከጥቁርነት ይበልጣል ብሎ መነሣት ዘረኛነት ነው። በዘረኛነት ምክንያት በሰዎች ላይ ብዙ ግፍና በደል ደርሷል። ቀደም ሲል እንዳመለከትሁት በአሜሪካንና በደቡብ አፍሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቁሮች በዘረኛነት ምክንያት ተሠቃይተዋል። ነገር ግን ይህ ተግባር እንዲቆም የታገሉ ግምባር ቀደም መሪዎች አጸፋው ዐመፅ፣ ሰይፍ፣ አንገት መቊረጥ ነው ብለው አልተነሡም። በደል የደረሰባቸውንም ሰዎች ለዐመፅና ለሰይፍ አላነሳሱም፤ ከቶ አልቀሰቀሱም። እኔን ከምንም በላይ ያስደነቀኝ ዘግናኝ በደል ደርሶባቸው ሳለ ከሰውነት ተራ አለመውጣቸውና አለመሰጤናቸው ነው። ምን ረዳቸው? ምን አቅም ሰጣቸው? ምን ሰው አደረጋቸው? በአንጻሩም በሩዋንዳ ከዛሬ 21 ዓመት በፊት የተፈጸመው ዘር ጨፍጫፊነት ሰዎችን ከሰውነት ተራ ያወጣና ያሴጠነ እኩይ ተግባር ነበር። በዚያ ዘግናኝ ዘር ጭፍጨፋ ተግባር ወደ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በግፍ ተገድለዋል። አሁንም የእኔ ጥያቄ ምን ጨካኝ አደረጋቸው? ምን ጉልበት ሰጣቸው፤ እጅና አንገት እንዲከረትፉ? ምን ከሰውነት ተራ አወጣቸው? የሚል ነው።
ዘረኛነትና ብሔርተኛነት ሰዎችን ከሰውነት ተራ አውጥቶ ያሴጥናል ማለት ነው? የሚመስለው እንደሱ ነው። እንግዲህ ከሰውነት ተራ ስንወጣ ወዴት እያመራን እንደ ሆነ መረዳት አለብን። ከሰውነት ተራ መውጣት ከመልካምነት መጉደል ነው። ከመልካምነት ስንጎድል ሁልጊዜ መጥፎነት ይወርሰናል። ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት ከመልካምነት ያጎድላል። ከመልካምነት በጎደልን ቊጥር ወደ መጥፎነት እንሄዳለን። ሠናይነት ስናጣ እኲይነት ይወርሰናል። ማርቲን ሉተር እንደሚለው ሰዎች ከእግዚአብሔር በራቁ ቊጥር ወደ ሰይጣን ይጠጋሉ። ከእግዚአብሔር ሐሳብና መንገድ የሚርቁ ሰዎች ለሰይጣን ሐሳብና መንገድ ይዳረጋሉ። ለዚህ አባባል ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑን የጀርመን ናዚዎችና ኮሙኒስቶች ናቸው። የጀርመን ናዚዎችና ኮሙኒስቶች በዓለም ላይ የፈጸሙትን ዘግናኝ ተግባር ማንም የሚረሳው አይመስለኝም። ናዚዎችም ሆኑ ኮሙኒስቶች (በእኛም አገር ኮሙኒስታዊው ደርግ ያደረሰው ጥፋት አይረሳም) ለማመን የሚያስቸግር እጅግ ዘግናኝ ተግባሮችን ፈጽመዋል። ተግባሩ መቼም አይረሳም። አንዳንድ ምሁራን እንዲያውም ዘግናኝ ተግባሮችን መርሳት የለብንም ይላሉ። ዘግናኝ ተግባሮችን መርሳት የሌለብን ተመልሰን በክፉ በድርጊቱ እንዳንጠመድ ነው።17
አሜሪካዊው የነጻነት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግና ነጻ እንዲወጡ ውድ ሕይወቱን የሠዋላቸው ጥቁሮች በነጮች ብዙ ግፍ ደርሶባቸዋል። ኔልሰን ማንዴላና የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችም እንደ አሜሪካን ጥቁሮች ሁሉ ብዙ ግፍ ደርሶባቸዋል። ሉተር በግፍ ተገድሏል፤ ማንዴላም ለ27 ዓመታት ታስረዋል። ነገር ግን ሉተርም ሆነ ማንዴላ ግፈኛውን ሥርዐተ ማኅበር ለመፋለም የወሰኑት በዐመፅና በሰይፍ መንገድ አልነበረም። እንደሚታወቀው ሉተር ድብን ያለ ፓሲፊት (ሰላምተኛ) ነበር። እንደ ሉተርም ባይሆን ማንዴላም ፓሲፊስት ነበሩ። ዐመፅና ሰይፍ ግን የትግላቸው ስልት አካል አልነበሩም። እጅግ ብርቱ በደል ቢደርስባቸውም ዐመፅንና ሰይፍን አልመረጡም። በዘር ጭፍጨፋም ተግባር አልተሳተፉም። ርግጥ ሉተር ሃይማኖተኛነቱ በእጅጉ ረድቶታል። ለእርሱ የኢየሱስ መንገድ ምርጥ መንገድ ነበር። የፍቅር መንገድ እንጂ የዐመፅ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ ተረድቶ ነበር፤ ማንዴላም እንዲሁ።18 በእነርሱ እምነት ዐመፅ ሁልጊዜ ዐመፅን ይወልዳል። ሰይፍም ሁልጊዜ ሰይፍን ይወልዳል። እናም እኩይ ዑደቱ ሁልጊዜ ይቀጥላል። ልብ እንበል፤ ከሰውነት ተራ ስንወጣ ዑደቱ እንዲቀጥል ፈቅደናል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በኦሮሞዎች ወይም በሌሎች ብሔሮች ላይ በአሜሪካንና በደቡብ አፍሪካ የደረሰው ዐይነት በደል ደርሷል የሚሉ ሰዎች ካሉ በማስረጃ ቢያሳዩንና በደሉ እንዳይደገም መፍትሔ እንድንፈልግ ቢረዱን መልካም ነው። አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር ከእንስሳ ማለትም ከአይጥ፣ ከበረሮና ከእባብ ጋር ያመሳሰለበት ጊዜ የለም። የአንተ መደብ ከዝንጀሮ መደብ ነው የተባለበት ጊዜ የለም። ሙሉ ሰው ሳይሆን ንኡስ ሰው ነህ የተባለበት ጊዜ የለም። በአንደበትም ሆነ በጽሑፍ (በይፋ) እንዲህ ናችሁ ተብሎ የተነገረበት ጊዜ የለም። ግልጹን ለመናገር በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ በደል አላደረሰም የሚል አቋም የለኝም። ነገር ግን በጥቁር አሜሪካውያንና በደቡብ አፍሪካውያን ላይ እንደ ደረሰው ዐይነት በደል የደረሰበት የአገራችን ብሔር ያለ አይመስለኝም። ደግሞም በኢትዮጵያ ውስጥ ሆን ተብሎ በዕቅድ ግፍ የተፈጸመበት (ዘር ጭፍጨፋ የተካሄደበት) ብሔር አለ ብዬ አላምንም። ሆን ብሎ በዕቅድ አንድን ብሔር ማጥቃት ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው አሁን ነው። የአንድን ብሔር ወገኖች ሆን ብሎ በዕቅድ መግደል፣ ዘግናኝ በሆነ መንገድ አንገት መቁረጥ፣ ሀብት ንብረታቸውን ማውደምና ተወልደው ያደጉበትን መንደር ጥለው እንዲሄዱ ማስገደድ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የማይታወቅ ድርጊት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ እንዲህ ያደረገበት ጊዜ የለም። አሁን ግን ሆነ፤ በግልጽ ጠራራ ፀሐይ ተደረገ። ምን ነክቶን ይሆን? ምን አገኘን? ምን ለከፈን? ምን ተጠናወተን?
የእኔ ዘር ከአንተ ዘር ይበልጣል ስንል ወይም የእኔ ብሔር ከአንተ ብሔር ይበልጣል ስንል ወይም በማንነት ወዳድነት ስንወረስ ከሰውነት ተራ ወጥተን ዘግናኝ ድርጊት እንፈጽማለን። ሌሎችን በራስ አምሳል ለመፍጠር መፈለግ ትልቅ ኢምግባራዊነት ነው። ሌሎች እኔን መምሰል፣ እንደ እኔ መሆንና የእኔን መንገድ (ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ) መከተል አለባቸው ማለት ትልቅ ኢሰብአዊነት ነው። በእኔ እምነት ልክፍቱ ይህ ነው። ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት ነቀርሳ ነው። በዚህ ነቀርሳ ስንለከፍ የሌሎች ሰብእናና ማንነት ተጨፍልቆ በእኛ ሰብእናና ማንነት አምሳል መቀረጽ አለበት እንላለን። ሁሉም ጽንፈኛ አካሄዶች ናቸው። አሁን ኢትዮጵያ በብርቱ የምትፈልገው ብዙ ሆነን ሳለ እንዴት ነው አንድ የምንሆነው? በማለት ራሳቸውን የሚጠይቁ ሰዎች ናቸው።19 ዘረኛነት፣ ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት ክፉ በሽታዎች ናቸው የሚሉ ሰዎች ከምንጊዜውም በላይ ያስፈልጉናል። በእነዚህ በሽታዎች መለከፍ መድረሻው በትክክል ወደሚታወቅ ፍጻሜ መገሥገሥ ነው። ያም መድረሻ ጥፋት ነው፤ ውድመት ነው።
አሁን ኢትዮጵያ በብርቱ የምትፈልገው ብዙ ሆነን ሳለ እንዴት ነው አንድ የምንሆነው? በማለት ራሳቸውን የሚጠይቁ ሰዎች ናቸው።
ንብረት ማውደምና ሰዎችን በአሠቃቂ መንገድ መግደል በበሽታው የመለከፍ አንዱ ምልክት ነው። ሰውነት የሚወሰነው በዘርና በብሔር ከሆነ በጣም ወርደናል፤ በጣም ቆሽሸናል ማለት ነው። ሰውነት ከእነዚህ ሁሉ በላይ ነው። ሰውነት ከዘርና ከብሔር ይበልጣል። ሰውነት ከማንነት ወዳድነት ይበልጣል። ሰዎችን ሁሉ እኩል የሚያደርጋቸው ዘራቸው ወይም ብሔራቸው ሳይሆን በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠራቸው ነው።20 የሰዎች እኩልነት መሠረቱ ሌላ ምንም ሳይሆን አምሳለ እግዚአብሔርነታቸው ነው፤ መልከ አምላክነታቸው ነው። ይህ መብት ደግሞ በማንም የሚሰጥ የሚነጠቅ አይደለም። ሰጪው አንዱ ፈጣሪ ነውና። የሰውነትን መብት መግፈፍ የፈጣሪን ሥልጣን መጋፋት ነው። የእኔ ጸሎት አንድዬ ልቡና እንዲሰጠን ነው። ሰክነን የሚጠቅመውን ከሚጎዳው፣ የሚያለማውን ከሚያጠፋው፣ የሚያሳርገውን ከሚያረክሰው ለይተን እንድናውቅ ነው። አሁን በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ባለማወቅ የመጣ ጥፋት አይደለም። ጽንፈኛ በሆነ ብሔርተኛትና ማንነት ወዳድነት የመጣ እንጂ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ገና ተጀመረ እንጂ የመጨረሻው ደረጃ ላይ አልደረሰም። ሁሉም ነገር ገና ዳዴ በማለት ላይ ነው፤ በሁለት እግሩ የቆመ ምንም ነገር የለም። ዴሞክራሲ የመጨረሻ ደረጃ ይኑረው ወይም አይኑረው ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። ሥርዐቱ ገና በመፈተሽ ላይ ነው። በየጊዜው መሻሻልና መታደስ ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ከአሜሪካን ተመክሮ መረዳት ይቻላል። ብዙዎች እንደሚያምኑት ዴሞክራሲ የማያልቅ የቤት ሥራ ነው። ራሱ የአሜሪካን ዴሞክራሲ ብዙ ሽንቁሮች እንዳሉት ገሃድ ወጥቷል። ሥርዐቱ ችግሮቹን በሽንቁሩ ማንጠባጠብ ጀምሯል። አንድዬ ሽንቁሩን የሚደፍንላቸው ጐበዝ ይስጣቸው። ማንም እንደሚያውቀው ፍጹም የሆነ አስተዳደራዊ ሥርዐት አለ ለማለት አይቻልም። ይሁንና ዴሞክራሲ መልካም አስተዳደር ነው፤ የሰዎችን ነጻነትና እኩልነት ያስከብራል የምንል ከሆነ፣ ሥርዐቱ በምን መርሕ ላይ መተከል እንዳለበት መተማመን አለብን። ይህን ጒዳይ አሁን እዚህ ላይ አላነሣም፤ በሌላ ስፍራ በሰፊው አትቼአለሁና አንባቢ ያን እንዲመለከት እጋብዛለሁ።21 አሁን እዚህ ላይ በመጠኑ ማተኮር የምፈልገው በመንግሥት ኀላፊነት ላይ ነው።
በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ሁለት ዐበይት ኀላፊነቶች ተደቅነውበታል (ከወቅቱ ቀውስ አንጻር ማለቴ ነው)። አንደኛው መንግሥት ዜጎቹን ማስተማር አለበት። መንግሥት ጧትና ማታ ዜጎቹን ማሠልጠን አለበት። መንግሥት ይህን ኀላፊነቱን በትጋት ካልተወጣ ሕዝቡን በዴሞክራሲ ዕውቀት ረኻብ ይገድላል። ዴሞክራሲን በተመለከተ ንቃተ ኅሊናው ያልጎለበተ ሕዝብ ሁልጊዜ ሲተራመስ ይኖራል። ሕዝብ ንቃተ ኅሊናው ካልጎለበተና የዴሞክራሲን ምንነት ካልተገነዘበ በሠለጠነ መንገድ መከራከርና መደራደር ምን እንደ ሆነ አይረዳም። እናም ትምህርትና ንቃት እጅግ ወሳኝ ነው።
ዴሞክራሲ በተወለደባት ግሪክ ሥርዐቱን በተመለከተ ፈላስፎቿ አንድ ትልቅ ሥጋት ነበራቸው። በተለይ ሶቅራጥስ (470–399 ዓ.ዓ.) በሥርዐቱ ስምረት ላይ ጨለምተኛ ነበር ይባላል፤ ታሪኩን የሚነግረን ራሱ ሶቅራጥስ ሳይሆን ደቀ መዝሙሩ አፍላጦን (428–348 ዓ.ዓ.) ነው። ሶቅራጥስ እንደ ብዙ የግሪክ ፈላስፎች ሁሉ፣ የዴሞክራሲን ሥርዐት የሚያነጻጽረው ከመርከብ ጋር ነው። ሶቅራጥስ እንዲህ በማለት ይጠይቅና ሥጋቱን ይገልጻል። በመርከብ ስትጓዙ የመርከቡ አዛዥ እንዲሆን የምትፈልጉት ማን ነው? ከተጓዦቹ አንዱ ወይስ ተገቢው ሥልጠናና ብቃት ያለው የመርከቡ አዛዥ? ሶቅራጥስ መልሱ በጣም ግልጽ የሆነውን ጥያቄ ያነሣው ለአጽንኦት ብሎ ነው። ማንም ጤነኛ ኅሊና ያለው ሰው ሥልጠናና ብቃት የሌለውን የመርከቡ አዛዥ እንዲሆን አይፈቅድም። ሶቅራጥስ ይህን ንጽጽር ከመንግሥት፣ ከዜጎችና ከዴሞክራሲ ሥርዐት ጋር ያዛምደዋል። መንግሥት ብቃት ባላቸው ሰዎች መመራት እንዳለበት ሁሉ ዜጎችም የሚመርጡትን ሰው በዕውቀት መምረጥ አለባቸው።
በመሪነት ስፍራ የሚቀመጡ ሰዎች እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትነው የጠሩ መሆን እንዳለባቸው ሁሉ ዜጎችም የሚፈልጉትን ሥርዐት በዕውቀት መወሰን አለባቸው። የሶቅራጥስ ሥጋት የዕውቀት ረኻብተኛ መሆን ነው።22 ያለ ዕውቀት የሚደረግ ማንኛውም ነገር አንዳች ረብ የለውም። የዴሞክራሲ ሥርዐት የዜጎችን ንቃት ይጠይቃል። ከሶቅራጥስ በፊት ሆሴዕ የሚባል ነቢይ “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል” (4፥6) ብሎ ነበር። ርግጥ ሆሴዕ ነገሩን ያወሳበት ዐውድ ሃይማኖታዊ ነው። ይሁንና እንድምታው በማንኛውም ዐውድ ይሠራል። ዕውቀት ማጣት ለጥፋት ይዳርጋል። ይህ በእውነተኛው ማንኛውንም ሰው ሊያሳስብ የሚገባ ሥጋት ነው፤ በተለይ መንግሥትን። በዴሞክራሲ ሥርዐተ ማኅበር ውስጥ አቦ ሰጥም ሆነ ጭፍንነት ስፍራ የላቸውም። ሁሉም ነገር መደረግ ያለበት በዕውቀት ነው። ዕውቀት ለማግኘት ደግሞ ትምህርት ያስፈልጋል። መንግሥት ሕዝቡን ማስተማር አለበት፤ ሕዝቡን ማንቃት አለበት፤ ሕዝቡን ማስታጠቅ (ጠመንጃ ሳይሆን ዕውቀት) አለበት የሚባለው ለዚህ ነው።
ግር ብሎ የሚሄድ ሕዝብ ራሱን በራሱ ያጠፋል። በስሜት የሚነዳ ሕዝብ አገሩን ይጎዳል፤ ይህን አዝማሚያ ፈረንጆች “democracy without education is demagoguery” ይሉታል። አሁን በአሜሪካን የሚታየው እንዲህ ዐይነቱ አዝማሚያ ነው። የአገር መሪ የሚመረጠው በዕውቀት ሳይሆን በስሜት ከሆነ እንደ ትራምፕ ዐይነት ሰዎች ይመረጡና ጉድ ይሠሩናል። ሶቅራጥስ ከብዙ ምእተ ዓመታት በፊት የጠረጠረው ይህን ነበር። ይህ ጥርጣሬ በኢትዮጵያ ላይ እንዳይፈጸም መንግሥት ተግቶ መሥራት አለበት። ዜጎች ሲመርጡም ሆነ ሲመረጡ በዕውቀት መሆን አለበት። የምመርጠው ሰውና ሥርዐት ለሕዝብ፣ ለአገርና ለዓለም ያላቸው መርሕ ምንድን ነው? የአስተዳደር መርሓቸው ምንድን ነው? የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ (ድኽነቷን፣ የብሔር ብሔረሰቦች አገርነቷን) የሚያስተናግደው እንዴት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ የሚችል ዜጋ መፍጠር አለበት። ሥልጠናና ብቃት የሌለውን ሰው የመርከቡ አዛዥ እንዲሆን መፍቀድ ኀላፊነት የጎደለው ተግባር እንደ ሆነ ሁሉ፣ ያለ ዕውቀት ዴሞክራሲያዊ ሥርዐትን ለመመሥረት የምናደርገው ሩጫ ኀላፊነት የጎደለው ተግባር ይሆናል።
መንግሥት የዴሞክራሲን ምንነት ለሕዝቡ በሚገባ ማስተማር አለበት። በዴሞክራሲ ሥርዐተ ማኅበር ውስጥ የግለ ሰቦች መብት፣ ነጻነትና እኩልነት ቢረጋገጥም፣ መብት ማለት ሥርዐት አልበኛነት እንዳልሆነ፣ ነጻነት ማለት ሕገ ወጥነት እንዳልሆነ፣ እኩልነት ማለት ማናአለብኝነት እንዳልሆነ ዜጎች ሁሉ መገንዘብ አለባቸው። በዴሞክራሲ ሥርዐተ ማኅበር ውስጥ ሐሳብን በነጻነት መግለጽና መከራከር እንጂ ዐመፅ ስፍራ የለውም። ለውጥ እንዲመጣ መፈለግ ያለብን በሰላማዊ ተቃውሞና በሕዝብ ድምፅ ነው። ሕዝብ ይህን እንዲያውቅና በዚህም እንዲያምን መደረግ አለበት።
ሁለተኛው መንግሥት ሕግ ማስከበር አለበት። ሕግ የማስከበር ሥልጣን የማንም ሳይሆን የመንግሥት ብቻ ነው። ግለ ሰቦችና የሃይማኖት ተቋሞች ሕግ የማስከበር ሥልጣን የላቸውም። የሕግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት አገር ሥርዐት አልበኛነት ይሰፍናል፤ መረንነት ይነግሣል። ጥያቄ ሊኖር ይችላል፤ ቅሬታ ሊኖር ይችላል፤ መበደል ሊኖር ይችላል። ሁሉም ግን በተገቢው መንገድ መቅረብ ይችላል። ሰው ሳይገድሉና አገር ሳይቀውጡ ቅሬታን ማሰማት ይቻላል። ሰላማዊ መንገድ አለ። ማንንም የማይጎዳ መንገድ አለ። ይህን መንገድ ያልተከተሉ ግን በሕግ መጠየቅ አለባቸው። የሌሎችን ንብረት (ጥረው ግረው ያፈሩትን) ያወደሙ ሰዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው። አገር ያቀወጡ ሰዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው። ምስኪን ዜጎችን በብሔርተኛነት ስሜት ተነድተው የገደሉ ሰዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው። ሐሳባቸውን በተገቢው መንገድ ሳይሆን በዐመፅ መንገድ ለመግለጽ አደባባይ የወጡ ሰዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው። ገጀራ፣ ቢላ/ዱላ፣ ሰይፍና መሣሪያ ይዘው ሰላም ያደፈረሱ ሰዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው። ተወልደው ያደጉበትን መንደር ጥለው እንዲፈናቀሉ ያደረጉ ሰዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ሕግ መስፈን አለበት። ከሕግ በላይ መሆን እንደማይቻል በተግባር መገለጽ አለበት።
ከዚህ በፊት “የአዲሱ ጅምር አብዮት ዕጣ ፈንታ” በሚለው ጽሑፍ እንዳሳሰብሁት ሕግ ከዴሞክራሲ መርሖዎች አንዱ ነው። የሕግ የበላይነት ካልተረጋገጠ ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም። በአንድ አገር ውስጥ አንዱ ሕግ አክባሪ ሌላው ሕግ ሰባሪ መሆን የለበትም። ሕግ የሚያከብሩ የሚጎዱበት በአንጻሩም ሕግ የሚሰብሩ (የሚጥሱ) የሚጎዱበት ምንም ምክንያት የለም (የመጀመሪያው “የሚጎዱበት” ጠብቆ፣ ሁለተኛው ላልቶ ካልተነበበ ትርጒሙ ይዛባል)። ሰዎች ሁሉ ለሕግ መገዛት አለባቸው። ይህን ማረጋገጥ ደግሞ የመንግሥት ኀላፊነት ነው። ሕግ ሲከበር ግን “innocent until proven guilty” የሚለው የሕግ መርሕ መጠበቁ መረጋገጥ አለበት። መልካም የሕግ መርሕነቱ አያጠያይቅም። አንዱ የሕግ የበላይነት ማረጋገጫ መንገድ ነው። የተጠረጠረ ሁሉ ወንጀለኛ አይደለም። ሆኖም ወንጀላቸው በማስረጃ የተረጋገጠ ሰዎች ከሕግ በላይ እንዳልሆኑ መታወቅ አለበት።
የጦር መሣሪያ በግለ ሰቦች እጅ መቀመጥ አለበት ወይ? የሚል ጥያቄ መነሣትና መሣሪያ ሕገ ወጥ መሆን አለበት እላለሁ። አሁን እዚህ ላይ ይህን ጒዳይ ማንሣት ቦታው ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ሰዎችን መግደል ከተጀመረ፣ ስለትና መሣሪያ ይዞ አደባባይ መውጣት ከተጀመረ፣ አሁን ቆም ማለትና ነገሩን ማጤን አለብን። ዴሞክራሲ አብቧል በሚባልባቸው አገሮች እንኳ መሣሪያ የታጠቁ ዜጎች ሕዝብና ማኅበረ ሰብ ሲያሸብሩ ታይቷል፤ ለምሳሌ አሜሪካን። ነገሩን በሚገባ ያጤኑ አንዳንድ ምዕራባውያን (ለምሳሌ አውስትራሊያ) መሣሪያን ሕገ ወጥ አድርገዋል፤ ከዛሬ 24 ዓመት በፊት በ1996። ኢትዮጵያም ነገ ሊመጣ የሚችለውን ቀውስ ከወዲሁ ተረድታ ለዜጎች የሚጠቅም ሕግ መተግበር አለባት። መሣሪያ መታጠቅ ያለባቸው ሕግ አስፈጻሚ አካሎች እንጂ ግለ ሰቦች አይደሉም። “The right to keep and bear arms” የሚለው የአሜሪካኖች ሕገ መንግሥታዊ መብት ብዙ መከራ አምጥቷል። በአሜሪካን በየዓመቱ 36,000 ሰዎች ከመሣሪያ ጋር በተያያዘ የሞት አደጋ ይደርስባቸዋል፤ በየቀኑ 100 ሰዎች ማለት ነው፤ ቊጥሩም በየጊዜው እየጨመረ ነው።24 ለጋራ ደኅንነት ሲባል ይህን መብት ለምን መተው እንደማይፈልጉ እስከ አሁን ሊገባኝ አልቻለም፤ የመብትነቱም ምስጢር ግልጽ አይደለም። ርግጥ በአሜሪካን አገር መሣሪያ ሕገ ወጥ እንዳይሆነ የሚፈለግበት አንዱ ምክንያት ግልጽ ነው፤ በጣም ሲበዛ አትራፊ ነው።25 ግን የቱ ይበልጣል? ገንዘብ ወይስ የሰው ሕይወት? ፈጣሪ ለሚልቀው ፋይዳ ግምት እንዲሰጡ ይርዳቸው። እኛን በተመለከተ ግን ንጹሕ ዜጎችን መግደል ከተጀመረ መሣሪያ ሕገ ወጥ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም። የብዙ ውድ ሰዎች ሕይወት በግፍ አልፏል። እንግዲህ ይበቃል! የሌሎች ውድ ሕይወት እስኪቀጠፍ መጠበቅ ተገቢ አይደለም። ውይይቱና ክርክሩ አሁን መጀመር አለበት። አፋጣኝ መፍትሔም መሰጠት አለበት። መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥልጣን እንዳለው ሁሉ ሰላማዊ ዜጎቹን የመጠበቅ ኀላፊነት አለበት። ሕገ ወጦችን ለፍርድ ማቅረብና በሕግ እንዲቀጡ ማድረግ አለበት። የመብትና የእኩልነት ጥያቄዎች መቼም መቅረብ ይችላሉ። ነገር ግን ሰው እየገደልንና አገር እየቀወጥን ነው ጥያቄአችንን የምናቀርበው የሚሉ ወገኖች ካሉ ሃይ መባል አለባቸው። ዐመፅን መሣሪያ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች መገታት አለባቸው። መንግሥት መንግሥታዊ ተግባሩን በብቃት መፈጸም አለበት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በአብዛኛው ሃይማኖተኛ ነው። የሁለቱን ታላላቅ ሃይማኖቶች ተከታዮች ቁጥር ብንመለከት እንኳ ሃይማኖተኛነቱ ግልጽ ነው። እዚህ ላይ የሃይማኖት ተቋሞችን ኀለፊነት በተመለከተ ሁለት ነገሮችን ብቻ ነው የምዳስሰው፤ መቻቻልንና ሥልጠናን በተመለከተ። ከዛሬ 40 እና 50 ዓመታት በፊት ሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች እንዴት ተቻችለው መኖር ይችላሉ? የሚል ጥያቄ እምብዛም ተነሥቶ አያውቅም። አሁን ግን ብርቱ ጥያቄ ሆኗል። እናም ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች እንዴት ነው ተቻችለው በአንድ አገር የሚኖሩት? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች (መሪዎች) ትልቅ ኀላፊነት አለባቸው። ርግጥ ነው በሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች መካከል መቼም መች የማይታረቁ አስተምህሮዎች አሉ። ለምሳሌ ድኅነትን፣ እግዚአብሔርንና ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ያሏቸው አስተምህሮዎች መቼም አይታረቁም። ስለዚህ በእነዚህ ነገሮች ላይ መደራደርና ወደ አንድነት መምጣት አይቻልም። በዐጭሩ የአስተምህሮ አንድነት ከሁለቱ ተቋሞች አይጠበቅም። ነገር ግን ሁለቱን ተቋሞች በአንድነት የሚያሰልፉ በርካታ አገራዊ ተግዳሮቶች አሉ። አንዱ ሰላም ነው፤ ሌላው ዕድገት ነው። ሌላው የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ነው፤ የዴሞክራሲንም ግንባታ መጨመር ይቻላል።
በአስተምህሮ መደራደርና ወደ አንድነት መምጣት ካልተቻለ ታዲያ ምርጫው ምንድን ነው? መቆራቆስ? መጻረርና መጻረፍ? እኔ እንደሚመስለኝ ሃይማኖት የሚረዳው በዚህ ጊዜ ነው። ትክክለኛ ሃይማኖት ተጫረሱ፤ እየተጻረራችሁ ተዋገዱ፤ ዐመፅን መሣሪያ አድርጉ አይልም። ለሰዎች መብት ይገድደኛል የሚል ሃይማኖት ገጀራ እንድናነሣም ሆነ አገር ምድር እንድንቀውጥ አይቀሰቅስም። ይልቁንም እንድንቻቻልና እንድንቀባበል ይመክራል። እንደ እውነቱ ከሆነ የሃይማኖቶች ሁሉ ፍላጎት ሰዎች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንገድ እንዲመለሱና የአምላክ ልጆች እንዲሆኑ ከሆነ፣ እየወገድናቸውና እየገደልናቸው ምኑን ጠቀምናቸው? ፍላጎታችን ነፍሳቸው ገነት (ጀነት) እንድትገባ ከሆነ ምኑን ረዳናቸው? ሃይማኖት በውዴታ እንጂ በግዴታ አይስፋፋም። ግዴታ ያለበት ነገር ሁሉ ዐመፅ አለበት። እኔ የምከተለው ኢየሱስ አንድም ቀን ሰይፍ አንሡ ብሎ አላስተማረም፤ ይልቁንም ሰይፋችሁን ወደ ሰገባው ክተቱ አለ እንጂ (ማቴ 26፥52)። በሌላውም እምነት ይህ መርሕ ቅቡል ይመስለኛል። ሰላማዊነት ከዐመፀኛነት እንዲሁም ፍቅር ከጥላቻ እንደሚበልጥ የማያስተምር የሃይማኖት ክፍል ያለ አይመስለኝም። የመቻቻል መሠረቱ ደግሞ ሰላማዊነትና ፍቅር ናቸው። ፍቅር እጅ አይጠመዝዝም፤ በዚህም ሰላም አይነሣም። የሃይማኖት ተቋሞች የሰላምና የፍቅር መንበር ካልሆኑ ሌላ ማንም መሆን አይችልም።
በእኔ እምነት ብሔርተኛነትና ማንነት ወዳድነት ከሁሉ በፊትና ከሁሉ በላይ የሚጋፋው የእግዚአብሔርን አደራረግ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን በራሱ አምሳል ፈጥሯል። እናም ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው። በማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ ልዩ የሆነ ዘር የለም፤ ልዩ የሆነ ብሔር የለም፤ ልዩ የሆነ ቋንቋ የለም፤ ልዩ የሆነ ባህል የለም፤ ልዩ የሆነ ሃይማኖት የለም። የእኔ እምነት ከሌላው እምነት ለእውነቱ ይቀርባል ብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል። ከዚህ አልፎ ግን ሌሎች እምነቶችን ሕገ ወጥ አድርጎ የራስን እምነት ብቻ ሕጋዊ ማድረግ ጽንፈኛነት ነው። ሐሳቡም ከዴሞክራሲ መርሕ ጋር አይሄድም። በዴሞክራሲ ሥርዐተ ማኅበር ውስጥ በሠለጠነ መንገድ መከራከርና ሐሳብን መግለጽ እንጂ ጽንፈኛነት ስፍራ የለውም። ውይይትና ድርድር እንጂ ወጋጅነት ስፍራ የለውም። እናም የሃይማኖት መምህራን ምእመኖቻቸው ምስጉን ተከታይና መልካም ዜጋ እንዲሆኑ መርዳት አለባቸው። ስለ ሕግ፣ ስለ መንግሥት፣ ስለ ዜግነት ስለ ግዴታና ኀላፊነት፣ ስለ መቻቻል፣ ስለ ሰላም ማስተማር አለባቸው። አገር ከሌለ ምንም ነገር እንደሌለ ማሳሰብ አለባቸው። ራሳቸውን ከጽንፈኞች እንዲጠብቁ ማስጠንቀቅ አለባቸው። የሚያነቡትን፣ የሚሰሙትንና የሚመለከቱትን ነገር በጥንቃቄ እንዲመዝኑና ግልቡን ከንጥሩ፣ ሐሰቱን ከእውነቱ እንዲለዩ ማሳወቅ አለባቸው።
ጥያቄ ሊኖር ይችላል፤ ሰው መግደል ግን አይቻልም። መበደል ሊኖር ይችላል፤ ቂም በቀለኛነት ግን አይበጅም። ሐሳብን በነጻነት መግለጽ ይቻላል፤ ሥርዐት አልበኛነት ግን አይፈቀድም። ቅቡልነት ባለው መንገድ መከራከር ይቻላል፤ መወጋገድ ግን አይቻልም በማለት መምከርና መዝከር አለባቸው። እዚህ ላይ ከሃይማኖት ተቋማት ልዕቀት እንደሚጠበቅ ለማሳሰብ እወዳለሁ። የበሰሉ ተከታዮች ለማፍራት የበሰለ ነገር መስጠት ያስፈልጋል። ምእመናን ሁለገብ እንዲሆኑ መርዳት ያስፈልጋል። ሁለገብ ስል በማንኛውም ጊዜና ስፍራ የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ ማለቴ ነው። በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ገበታ፣ በመንግሥት ኀላፊነት ስፍራ በአስተሳሰባቸውና በምግባራቸው ምሳሌ መሆን የሚችሉ ማለቴ ነው። ለሕዝብ፣ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ሐሳብ ማፍለቅ የሚችሉ ማለቴ ነው።
የዜጎችን ምግባር በተመለከተ ግን አንድ በጣም አሳሳቢ ጒዳይ ላንሣ። በኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና ከምን ጊዜውም በላይ ተንሰራፍቶ ይገኛል። ሙስና ለምን ናኘ? ምክንያቱ ምንድን ነው? ብንል መልሱ ግልጽ ነው። የሃይማኖት ተቋማት ሙስና መጥፎ ተግባር ብቻ ሳይሆን አገርንና ወገንን በብርቱ የሚጎዳ ተግባር እንደ ሆነ አላስተማሩም። ሕዝባቸውንም አልመከሩም፤ አልገሠጹም። ሙስና እንዲያውም ከመብትና ከእኩልነት ጋር ይዛመዳል። ሙስና ሲንሰራፋ በአገሪቱ ውስጥ ገንዘብና ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ብቻ ይገንናሉ። ምስኪን ድኾች ይገለላሉ፤ ይበደላሉ። ጉቦ ካልተሰጠ ጒዳይ የማይፈጸም ከሆነ፣ እጅ መንሻ ካልተሸጎጠ አቤቱታ የማይደመጥ ከሆነ፣ “በእግር ሳይሆን በእጅ ካልተሄደ” ሕግ የማይሰፍን ከሆነ ፍትሕ ይዛባል፤ ማኅበራዊ ሕይወት ይናጋል። መንግሥታዊ ተቋሞች በሙሰኞች ተበክለዋል የሚለው ሮሮ የሃይማኖት ተቋማትን ሊያስደነግጣቸው ይገባል።
በሙስና ረገድ ኢትዮጵያ ከአፍሪካዊቷ ናይጄሪያ ባትበልጥም (የወደፊቱን እንጃ) መተካከሏ ግን ሊያሳስባቸው ይገባል። እናም ምን ዐይነት ዜጎችን እያፈራን ነው? በማለት ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው።26 የሃይማኖት መምህራን ምእመኖቻቸውን አትስረቁ፤ ከሰረቃችሁ እዚህ አትምጡ፤ በሥልጣን አትባልጉ (የሕዝብ ሀብት አትዝረፉ፤ በሕዝብ ሀብት አትበልጽጉ)፤ ደኻ አትበድሉ፤ ለባለጠጋ አታድሉ፤ በስንፍና አትታወቁ፤ ትምክህተኞች አትሁኑ፤ ሚዛናችሁ አባያ አይሁን፤ ብሔርተኞች አትሁኑ፤ ማንነት ወዳዶች አትሁኑ፤ ጽንፈኞች አትሁኑ፤ ዐመፀኞችና ሥርዐት አልበኞች አትሁኑ ለማለት ምግባራዊ ብቃት ይኖራቸው ይሆን? እኔ እንደሚመስለኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ እነዚህ ሁለት ነገሮች ማለትም መቻቻልና ሙስናን መጥላት መታወቂያችን ከሆኑ ተስፋ አለን። በአንጻሩም ጎጠኛነትና ሙሰኛነት ከነገሡ ዐመፀኛነትና ሥርዐት አልበኛነት መንገሡ አይቀርም። አንድዬ ልቡና ይስጠን፤ መቻቻልና ፍቅር ይቻረን፤ ለአገር መሪዎችና ለሃይማኖት አባቶች ማስተዋል ይጨምርልን፤ የእኛንም ሆነ የልጆቻችንን አገር የሚጎዳ ሐሳብ ከማስተናገድ ይጠብቀን። ቅኖችንና ሰላምተኞችን ያብዛልን። ምሕረት ለኢትዮጵያ!
እውነታው ይህ ከሆነ ለኢትዮጵያ የሚበጀው አስተዳደር ምን ዐይነት ነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት። አሐዳዊ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ከቶ አይበጅም፤ በኢትዮጵያም ተጨባጭ ሁኔታ ከቶ መተግበር አይችልም፤ አሐዳዊ አስተዳደር በኀይል እንዲተገበር ተፈልጎ ብዙ ምስቅልቅል አምጥቷል። ምናልባት ከብዝኃ ብሔር ፌደራሊዝም ብንጀምር ወይም “ከመደመር” ንድፈ ሐሳብ ብንጀምር ወይም ሁለቱን አጋብተን ከአንድ ሌላ አገርኛ ንድፈ ሐሳብ ብንጀምር ወደሚበጀውና ሁሉንም ብሔሮች ወደሚያቅፈው እንዲሁም ነጻነትን፣ እኩልነትን፣ ፍትሕን ወደሚያሰፍነው የአስተዳደር ሥርዐት መዝለቅ ይቻል ይሆናል። መቼም ፍጹም እንከን አልቦ መስተዳድራዊ ሥርዐት ባለመኖሩ ሁሉም የየራሳቸው caveat or blind spot እንደሚኖራቸው እሙን ነው። ለመንደርደርና ዐውደ ገባዊ ሥርዐት ለመፍጠር ግን በጣም ጠቃሚ ናቸው። የሚበጀውን ለመፈለግ ግን መቀባበል፣መቻቻልና መከባበር ያስፈልጋል። እውነተኞችና ሰላምተኞች መሆን ያስፈልጋል። በሰዎች ሁሉ ውስጥ የሚያደባውን ክፉ መቃወም ያስፈልጋል። ሰውነታችን ይበልጥ የሚገለጥበን መርሕ መከተል ያስፈልጋል። የውይይቱ ሜዳ በሰፋ ቊጥር የቁርቁሱ (የጥላቻውና የውገዳው) ሜዳ እየጠበበ ይመጣል። ወደ መልካሙ መንገድ በቀዘፍን ቊጥር መጥፎው መንገድ እየራቀ ይመጣል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እንዳሳሰብሁት ከዚህ በፊት መጨቆን አዲስ ጨቋኝ ለመሆን መብት አይሰጥም፤ ከዚህ በፊት መበደል አዲስ በዳይ ለመሆን መብት አይሰጥም። ደግሞም ከዚህ በፊት በብሔርና በመደብ ላይ የተመሠረተ ሥርዐት ሰፍኖ ከነበር ይሄው ሥርዐት መቀጠል አለበት ማለት አሁን የንግሥናው ተራ የእኛ ብሔር ነው እንደ ማለት ነው። ምክንያቱም ብሔርተኛነትና አሐዳዊነት ወይም ማንነት ወዳድነትና አሐዳዊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። አንድነት ሳይሆን አንድ ዐይነትነት ናቸው። ከዚህ የሚከተሉት መጽሐፎች ምናልባት ውይይቱን በቅን መንፈስ ለመጀመር ይጠቅሙን ይሆናል። Yonatan Tesfaye Fessha, Ethnic Diversity and Federalism: Constitution Making in South Africa and Ethiopia. Stefan Wolff, Ethnic Conflict: A Global Perspective. Wayen Norman, Negotiating Nationalism: Nation-Building, Federalism, and Secession in the Multinational State. Anthony Giddens, Beyond Left and Right: The Future of radical Politics. Aaron Tesfaye, Political Power and Ethnic Federalism: The Struggle for Democracy in Ethiopia. Asnake Kefale, Federalism and Ethnic Conflict in Ethiopia: A Comparative Regional Study. David Turton, Ethnic Federalism: The Ethiopian Experience in Comparative Perspective. Jan Erk, The Ethnopolitics of Ethnofederalism in Ethiopia. Mulatu Amare, Ethnic Federalism in Ethiopia: Challenges and Prospects. Christopher Van Der Beken, Unity in Diversity-Federalism as a Mechanism to Accommodate Ethnic Diversity: The Case of Ethiopia.
“አንድነት በልዩነት፣ ልዩነት በአንድነት” የሚለው መርሕ በጣም ጠቃሚ መርሕ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በብዙ የዓለም ክፍሎች አንድ ዐይነት የሆነ ባህል፣ ቋንቋ፣ ብሔር፣ ወዘተ ያላቸው ሕዝቦች የሉም። በየአገሩ ብዙ ልዩ ልዩ ነገሮች አሉ፤ ስለዚህ አንድ ዐይነትነት የለም። ልዩ ልዩ ነገሮችን አንድ ዐይነት ለማድረግ ስንፈልግ አስገዳጅ ኀይል መጠቀም አለብን። አሁን የሚያስፈልገው በግድ አንድ ዐይነት መሆን ሳይሆን በውድ አንድ መሆን ነው። አንድ ለመሆን አስገዳጅ ኀይል መጠቀም አያስፈልግም። አሁንም ልድገመውና አንድነትና አንድ ዐይነትነት ትልቅ ልዩነት አላቸው። በመቻቻልና በመቀባበል ቁጭ ብሎ መነጋገር ይቻላል፤ መደራደር ይቻላል፤ መከራከር ይቻላል። ኀይል ለመጠቀም ሰውነት አይጠይቅም፤ ለመነጋገር፣ ለመደራደርና ለመከራከር ግን ሰው መሆንን ይጠይቃል። ኀይል ለመጠቀም አጥፊ መሣሪያ ያስፈልጋል፤ ለመነጋገር፣ ለመደራደርና ለመከራከር ግን ትዕግሥት፣ ኅሊና፣ ጨዋነት፣ ሥልጡንነት፣ ሰላምተኛነት ያስፈልጋል። የፍጥረትን ሕግ ስንመለከት ሁሉም ነገር ፍጹም አንድ ዐይነት ሆኖ አናገኘውም። ሰዎችን እንኳ ብንወስድ በጾታና በመልክ እንለያያለን። ሰው ሁሉ ወንድ አይደለም፤ ሰው ሁሉ ሴት አይደለም፤ ሰው ሁሉ ዐጭር አይደለም፤ ሰው ሁሉ ረጅም አይደለም። ሰው ሁሉ አንድ ዐይነት ቁመና የለውም፤ የእጃችንን አሻራ ብንመለከት ፍጹም አንድ ዐይነት የሆነ የእጅ አሻራ የለንም። ሰዎች በአብሮነት ለመኖር ግን አንድነት ያስፈልጋቸዋል። አንድነት አንድ ዐይነት መሆንን አይጠይቅም፤ አንድነት የሚጠይቀው መነጋገር፣ መደራደር ካስፈለገም መከራከር ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ልዩነታችንን ወደ አንድነት ለማምጣት ስንጥር ይበልጥ ሰዎች ሆነናል።
Claus Westermann, Genesis 1-11: A Commentary. Trans. By John J. Scullion (Minnieapolis: Augsburg, A984) 318.
Miroslav Volf, Exclusion and Embrace: A Theological Exploration of Identity, Otherness, and Reconciliation (Nashville: Abingdon Press, 1996) 94. እርግጥ እናታቸው ለቃየል ልዩ ትኩረት ሰጥታለች። የቃየልን የስሙን ትርጒም ስትነግረን የአቤልን ግን አልነገረችንም። ቃየል ማለት “አገኘሁ” ማለት ሲሆን አቤል ደግሞ “ተን ወይም ከንቱ” ማለት ነው።
Ellen Van Wolde, The Story of Cain and Abel: A Narrative Study (JSOT, 52 1991) 29. ተራኪው ለምን? የሚለውን ጥያቄ አልመለሰልንም። ተራኪው የእግዚአብሔርን ውሳኔ በግልጽ በመናገር ፋንታ አንባቢው ራሱን በትረካው ውስጥ እንዲከትትና ምክንያቱን ራሱ እንዲፈልግ ይጋብዛል። እግዚአብሔር የሚያዳላ ነው (ቃየልን አይወደውም) እንዳንል ቃየል አቤልን ከገደለ በኋላ በቀል እንዳይደርስበት ጥበቃ ተደርጎለታል (ዘፍ 4፥15)። ከብዙ ምእተ ዓመታት በኋላ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የቃየልን ድርጊት መዝነውታል። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ እንዲህ ይላል፤ “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል” (11፥4)። ዮሐንስና ይሁዳ ደግሞ ድርጊቱን ከጥላቻ ጋር አዛምደውታል (1ዮሐ 3፥15፤ ይሁዳ 11)። ወንድምን መጥላት ነፍሰ ገዳይነት ነው። ብሉይ ኪዳን “ቃየን” በማለት ስሙን ሲጠቅስ፣ አዲስ ኪዳን “ቃየል” በማለት ነው ስሙን የሚጠቅሰው (ነባሩ ትርጒም)። ቃየል የወንድሙን ደም አፈሰሰ፤ ኢየሱስ ግን ደሙን ለጠላቶቹ አፈሰሰ (ሮሜ 5፥6-11)። ከቃየል መንገድ ይልቅ የኢየሱስ መንገድ የሚበልጠው የመጀመሪያው የጥላቻ፣ ሁለተኛው የፍቅር መንገድ በመሆኑ ነው። የጥላቻ መንገድ ሁልጊዜ ወደ መወጋገድ ይወስዳል፤ የፍቅር መንገድ ግን ሁልጊዜ ወደ መቀባበል፣ መቻቻልና ልዩነት ቢኖር እንኳ በትዕግሥት ወደ መነጋገርና መደራደር ይወስዳል።
Tremper Longman III, Genesis: The Story of God Bible Commentary (Grand Rapids: Zondervan, 2016) 90.
Walter Wink, Engaging the Powers: Discernment and Resistance in a World of Domination (Minneapolis: Fortress Press, 1992).
አዶልፍ ሂትለር የጀርመን መሪ ሆኖ ሥልጣን ሲጨብጥ በዘር ላይ የተመሠረተ ርዕዮተ ዓለም ይዞ ተነሣ። የጀርመኖች ዘር ከሁሉም የሚበልጥና የሚልቅ ልዩና ምርጥ ዘር ነው (Aryan, Master Race) አለ። ጀርመኖች ቁመተ ረጃጅሞች፣ አፍንጫ ሰልካኮች፣ ባለሰማያዊ ዐይኖች ናቸው አለ። እንዲህ ዐይነት ቁመና የሌላቸው ሁሉ ዝቅተኛ ዘሮች ተደርገው ተቈጠሩ። ከጀርመኖች የሚያንስ ዘር ያላቸው ሁሉ ቢቻል መወገድ ካልሆነም መፈናቀል አለባቸው ተባለ። ሂትለር ባቀረበው ባለ 25 ነጥብ ዕቅድና “Mein Kampf” (“My Struggle” or “My Fight”) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንደ ገለጸው ልዩና ምርጥ ዘር የጀርመኖች ዘር ብቻ ነው፤ አይሁዶች ከጀርመን ምድር መወገድ አለባቸው። ሂትለር ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ ልጆች ትምህርት ቤት የሚመዘገቡት ቁመታቸውና አፍንጫቸው እየተለካ፣ የራሳቸው ቅል እየተመተረና የቆዳ ቀለማቸው እየተጣራ ነበር። ዐጭር ቁመትና በአካላቸው ላይ አንዳች ጉድለት ያለባቸው ልጆች ከደጃፍ ይመለሱ ነበር (አይሁዶችና ሮማኒ ጂፕሲዎች እጅጉን ተገለሉ)። ዘረኛነት ወጋጅነት ነው፤ ብሎም ሌሎችን ደምሳሽነት ነው። እኔ ልዩ ነኝ፤ እኔ ምርጥ ነኝ ማለት ስንጀምር ሌሎችን መናቅና ዝቅ ዝቅ ማድረግ እንጀምራለን።
David Livingstone Smith, Less Than Human: Why We Demean, Enslave, and Exterminate Others (New York: St. Martin’s Press, 2011).
Dwight Bollinger, Language: The Loaded Weapon (White Plains: Longman, 1980).
Volf, Exclusion and Embrace, 74. ጀርመኖች እንዲያውም “ዘራችን ተበክሏል፤ በካዮቹም ለፍርድ መቅረብ አለባችው” ይሉ ነበር። በጀርመን ለተፈጠረው ማኅበራዊ ቀውስ ተጠያቂዎቹ አይሁዶች ናቸው የሚል ሐሰተኛ ወሬ ተነዛ። አይሁዶች የዳዊትን ኮከብ እንደ ምልክት በአንገታቸውና በደረታቸው ላይ መለጠፍ አለባችሁ ተብለው ታዘዙ። ይህ ትእዛዝ የወጣው በቀላሉ ለመለየትና ለመወገድ እንዲያመች ነበር። የአይሁዶች ቤት፣ መደብርና ምኩራብ በእሳት ወደመ። የመንግሥት propaganda (ንዛት) አጥፊ ሚናውን በሚገባ ተጫውቷል። የሃይማኖት ተቋሞች ሳይቀሩ በንዛቱ ተሰለቡ (ንዛት ሥሩ ነዛ ነው፤ በቁሙ አሠራጨ፣ አዘመተ፣ አነፈሰ ወሬን መርዝን፤ ሐሰተኛ ወሬ ልክ እንደ መርዝ ነው፤ ወደ ሰውነት የገባ መርዝ ገዳይ እንደ ሆነ ሁሉ ወደ ኅሊናም የገባ ሐሰተኛ ወሬ ለጥፋት ይዳርጋል። ጀርመኖችና የሩዋንዳ ሁቱዎች የንዛት ሰለባ በመሆናቸው ሴጠኑ)።
J. H. Guenebault, Natural History of the Negro Race (1837). እንዲሁም David B. Davies, The Problem of Slavery in Western Cultures (1966).
Mahamood Mamdani, When Victims Become Killers: Colonialism, Nativism, and the Genocide in Rwanda (Princeton: Princeton University Press, 2001). አንዳንድ ሰዎች በጀርመን ናዚዎች የተፈጸመውን ግፍና በሩዋንዳ ሁቱዎች የተፈጸመውን ግፍ ደረጃውን ማለትም ዘግናኝነቱንና አሠቃቂነቱን ለማወዳደር/ለማነጻጸር ሙከራ አድርገው ነበር። በጀርመን አንድ ሰው ብዙ ሰዎችን ይገድል ነበር፤ በሩዋንዳ ብዙ ሰዎች አንድን ሰው ይገድሉ ነበር። ጀርመኖች በአንድ ጊዜ ዝም ጭጭ የሚያደርግ መግደያ ነበራቸው። በሩዋንዳ ግን መግደያው ገጀራ፣ ቢላ/ዱላና አንዳንዴም መሣሪያ ነበር። እንግዲህ ንጽጽሩ ያለው ከዚህ ላይ ነው። በጀርመን አይሁዶች ወዲያውኑ ይኸውም ለቀናት ሳይሠቃዩ ሲሞቱ፣ በሩዋንዳ ግን ቱትሲዎች የሚሞቱት ውለው አድረው ነበር። አንድን ቱትሲ ለመግደል እስከ አሥር የሚደርሱ ሰዎች መሳተፍ ነበረባቸው። መግደያ መሣሪያቸው ገጀራ፣ ቢላና ዱላ በመሆኑ የሚደንዘውን መሳልና የሚሰባበረውን በአዲስ መተካት ነበረባቸው። ድርጊቱን በዐይናቸው የተመለከቱ ሰዎች እንደ ገለጹት በእጅጉ የሚዘገንንና የሚሰቀጥጥ ነበር፤ ድርጊቱም በሰው የተፈጸመ አይመስልም ነበር።
Miroslav Volf, The End of Memory: Remembering Rightly in a Violent World (Grand Rapids: Eerdmans, 2006). በዚህ ጒዳይ ላይ በጣም የሚጠቅም ሐሳብ ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ይህን መጽሐፍ እንዲያነቡ እመክራለሁ። ቮልፍ ግፍ፣ ዐመፅና ትዝታ/ትውስታ ዝምድናቸው ምን እንደ ሆነ አትቷል። ነገሩን በጥሞና የተከታተለ ሰው ግፍንና በደልን እንዴት መመልከት እንዳለበት ምክር ያገኛል። ቮልፍ እንደሚለው ግፍንና በደልን መርሳት የሌለብን ቂም በቀለኛነት እንዲነግሥብን ሳይሆን የይቅርታና የፍቅር መንገዱ ደልዳላ እንዲሆንልን ነው። የተውጠነጠነ ግፍና ዐመፅ እንዳለ ሁሉ የተውጠነጠነ ይቅርታና ፍቅር መኖር አለበት ነው ሙግቱ። የግፍና የዐመፅ እኩያ ይቅርታና ፍቅር ናቸው። የበደልንና የዐመፅን ጠባሳ መፈወስ የሚችሉት ይቅርታና ፍቅር ብቻ ናቸው። አሁን ቦታው አይደለም እንጂ ይህን ጒዳይ ከሥቁዩና ከስቁሉ ክርስቶስ አንጻር መመልከትና ሐሳቡን ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አንጻር ማጎልበት ይቻላል። ዐመፅን፣ በደልን፣ ሰይፍንና መወጋገድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቀልበስ ምርጡ መንገድ ኢየሱስ የቀየሰውና የተለመው መንገድ ነው። ኢየሱስ የሚሰማ ጆሮ ላላቸው ሁሉ ይህን መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርቧል። እርግጥ ይህ መንገድ ሁልጊዜ መሥዋዕትነትን ይጠይቃል። ለኢየሱስ መስቀል እንጂ ሰይፍ መንገዱ አልነበረም። ኢየሱስ ተሰየፈ እንጂ አልሰየፈም። ፍቅር ማለት ይህ ነው – ሌሎችን መወገድ ሳይሆን ለሌሎች ራስን መስጠት፤ ሌሎችን መስቀል ሳይሆን ለሌሎች መሰቀል።
Menelik Asfaw Fikreselassie, “Nelson Mandela: Icon of Freedom, Forgiveness and Reconciliation” (Unpublished Class Paper, Palmer Theological Seminary, 2012).
አሁን ያለንበትን ሁኔታ በጥቅሉ ስመለከት አገራችን ተስፋ በሚጣልበት መንገድ ላይ የምትጓዝ ይመስላል። የሥልጣን መንበሩን እኔ ብቻ መጨበጥ አለብኝ ካላልን በስተቀር ኢትዮጵያ በመልካም የለውጥ ጎዳና ላይ እንዳለች ለመገንዘብ ምንም አያዳግትም። ለውጡ እንዲፈጥንም እንዲዘገይም የምናደርገው ግን እኛው ነን። በአንድ ሌሊት ለውጥ እንዲመጣ መፈለግ አገሪቱ ያለችበትን እውነታ መካድ ነው። እውነታን ስንክድ እንታለላለን። ገና ብዙ መሠራት ያለባቸው ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ ግን እኛ ራሳችን መሠራት አለብን። ሐቅን፣ እውነትንና ቅንነትን ገንዘባችን ማድረግ አለብን። ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ ዝርፊያንና ቅሚያን ማቆም አለብን። ስንናገር አስበን መናገር አለብን፤ ግልብነትንና ስሜታዊነትን ከእኛ ማራቅ አለብን። የሰዎችን ሥራ ስንገመግም እውነት እንጂ ሐሰት መርሓችን መሆን የለበትም። ሌሎች መልካም ሠርተው ካየን ይበልጥ እንዲተጉ እንርዳቸው። ዳር ተቀምጠን ተቺዎች ብቻ አንሁን። አሁን ያለንበት ችግር እንዲባባስ አለማድረግ በራሱ ትልቅ አስተዋጽኦ ነው። ብሔርተኝነት አይውረሰን፤ ማንነት ወዳድነት አይምጠጠን። ግር ብለን አንሂድ፤ ቆም ብለን ግራ ቀኛችንን እንመልከት። ልኩን ከስሕተቱ ለመለየት ብቃት ይኑረን። የጋዜጠኛነት ሙያው፣ ብቃቱና ሥነ ምግባሩ የሌላቸው ሰዎች አያታልሉን፤ ሰለባም አንሁን (በሩዋንዳ ለዚያ ሁሉ ጥፋት ግምባር ቀደም ተጠያቂዎቹ በራዲዮ ሕዝቡን ለዐመፅ ይቀሰቅሱ የነበሩ ሰዎች ናቸው፤ እነርሱ ከሩቅ ሆነው ሕዝቡን አባሉ)። ያልበሰለ ፖለቲካ የሚያናፍሱ ሰዎች አይንዱን፤ አይጋልቡን። ፍቅር አንጣ፤ ሰላምተኞች እንሁን። አገር እንደ እናት ናት ይባላል፤ በእናታችን ላይ አንጨክን፤ ይልቁንም በርኅራኄ እንደግፋት፤ ልማቷን እንጂ ጥፋቷን አንመኝ። በተለይ ሌላ ሁለተኛ አገር ላይ ተቀምጠን በሁለት ዜግነት የምንመካ ሰዎች አንዲት አገር ብቻ ላለቻቸው ሰዎች እንዘን።
አሁን ስፍራው አይደለም እንጂ በዚህ ጒዳይ ላይ ክርስትና የሚያስተምረውን ባትት ደስ ይለኝ ነበር። በዴሞክራሲ ሥርዐተ ማኅበር ውስጥ ሰዎች ሁሉ ምንም ሆኑ ምን እኩል ናቸው የሚል መርሕ አለ። ማለት እኩልነታቸው የተመሠረተ በማንነታቸው ላይ አይደለም። ይህ መርሕ የተቀዳው ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች እኩልነት መሠረቱ ምን እንደ ሆነ ብቻ ሳይሆን ምክንያቱም ምን እንደ ሆነ ይገልጽልናል። የእኩልነት መሠረቱና ምክንያቱ መልከ አምላክነት ነው። በመሆኑም የእኩልነት መሠረቱ ሰውነት ነው። ሰዎች ደግሞ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረዋል። ይህ በእርግጥም ወሳኝና ብርቱ ምክንያት ነው። ብሔርተኛ ስንሆን ግን ይህን አምላካዊ መብት እንጋፋለን።
ምኒልክ አስፋው፤ የአዲሱ ጅምር አብዮት ዕጣ ፈንታ (Hintset)።
Plato: The Republic, Cambridge Texts in the History of political Thought, Trans. Tom Griffith (Cambridge: Cambridge University Press, 2000) 186-219.
Protest + Vote = Change የሚለው (Peaceful) Protest + Vote = Change በሚል የተሻሻለው በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ነው። ብዙ ዐይነት ተቃውሞ አለ። እኔ የሚመቸኝ (ሰላምተኛነት ይበጃል ብዬ ስለማምን) ሰላማዊ ተቃውሞ ነው። ዐመፅን መሣሪያው የሚያደርግ ተቃውሞ ማብቂያ ወደሌለው ቅራኔ ይወስዳል። ዐመፅ ምርጥ መፋለሚያ መንገድ እንዳልሆነ ለመረዳት የአሜሪካን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልና የጥቁሮች መብት ታጋይ የነበረውን የJohn Lewis (1940-2020) መርሕ መመልከት በቂ ነው። ጆን የማርቲን ሉተር ኪንግ ደቀ መዝሙር ነበር። እንደ መምህሩ ሁሉ እርሱም ምርጡ መፋለሚያ መንገድ ዐመፅ ሳይሆን ሰላም/ፍቅር እንደ ሆነ ተረድቶ ነበር። እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ከዚህ መርሕ አንድም ቀን ፈቀቅ አላለም። በሞተበት ቀን በአንድ ስመ ጥር መጽሔት ላይ እንዲታተም በጠየቀው ጽሑፍ እንዳመለከተው “the way of love and nonviolence is the more excellent way” ብሎ ነበር። ጥቁሮች ከነጮች እኩል የመምረጥ መብት አላቸው የሚለው ሕግ የጸደቀው በሰላማዊ ትግል ነበር። ጆን አንድም ቀን ገጀራ አላነሣም፤ ቢላ/ዱላና መሣሪያ ይዞ አደባባይ አልወጣም። እነዚህ መሣሪያዎች ትግሉን ያጠለሹት እንደሆን እንጂ አያልቁትም፤ አያዘልቁትም። በጆን እምነት ዴሞክራሲ መቼም የማያልቅ ሥራ ነው። እርሱ ከሌሎች ተቀበለ፤ ሌሎችን ሲያሳስብ ትግሉን ቀጥሉ አለ። ነገር ግን ትግሉ ሁልጊዜ መቀጠል ያለበት በዐመፅ መንገድ ሳይሆን በፍቅር መንገድ ነው። በሰይፍ መንገድ ሳይሆን በመቻቻልና በመቀባበል መንገድ ነው። አርበኝነት መንገዱ ሰላም እንጂ ዐመፅ አይደለም። ለኢትዮጵያም የሚበጀው እንዲህ ዐይነቱ መንገድ ብቻ ነው፤ ዐመፅ ሳይሆን ፍቅር።
Thomas Gabor, Confronting Gun Violence in America (New York: Palgrave Macmillan, 2016). በአሜሪካን ከመሣሪያ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቊጥር ከሌሎች ከበለጸጉ አገሮች ለምሳሌ ከእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓን ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ያስደነግጣም። የአሜሪካን ሕዝብ ቊጥር 328 ሚሊዮን ነው፤ ባንጻሩም 393 ሚሊዮን መሣሪያ በግለሰቦች እጅ ይገኛል። በአንድ አሜሪካዊ ቤት ከአንድ መሣሪያ በላይ አለ ማለት ነው። ታዲያ በጥይት ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቊጥር በ25 እጥፍ እንዴት አይበልጥ (ከሌሎች ከበለጸጉ አገሮች ጋር በንጽጽር)?
Timothy D. Lytton, Suing the Gun Industry: A Battle at the Crossroads of Gun Control and Mass Torts (Ann Arbr: University of Michigan Press, 2009). መሣሪያ አምራቾች ከመሣሪያ ሽያጭ በየዓመቱ 28 ቢሊዮን ዶላር ይሰበስባሉ። በአገሪቱ ውስጥ ወደ 6,579 የሚደርሱ መሣሪያ መሸጫ መደብሮች አሉ። እነዚህ መደብሮች በየዓመቱ 11 ቢሊዮን ዶላር ያጋብሳሉ። በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በJanuary እና February (2020) ብቻ በየቀኑ እስከ 100,000 የሚደርስ መሣሪያ ተቸብችቧል (Elizabeth MacBridge, forbes.com)። በእውነተኛው ድርጊቱ ለማመን ያስቸግራል፤ መሣሪያ ሕገ ወጥ እንዳይሆን የሚታገሉ ቡድኖች ያላቸው ተሰሚነትም ለማመን ያስቸግራል። በመንግሥት ኀላፊነት ስፍራ የሚቀመጡ ሰዎች ከእነዚህ ቡድኖች ይሁንታ ካላገኙ መመረጥ አይችሉም፤ ማለት በእነዚህ ቡድኖች ያልተደገፈ ሰው ሥልጣን አያገኝም፤ ለምሳሌ NRA (Philip B. Levine and Robin McKnight, www.brookings.edu)።
Menelik Asfaw Fikreselassie, Bribery and Corruption: A Biblical and Theological Analysis with Special Reference to Ethiopia (Unpublished MTS Thesis, Palmer Theological Seminary, 2013). ይህን ጽሑፍ አንብበው መልካም አስተያየታቸውን ለሰጡኝ ወንድሞቼ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ዮሐንስ መሐመድ፣ መንግሥቱ ታምሬና ሚክያስ በላይ አንድዬ ወሮታችሁን ይክፈል።
Share this article:
“የተላኩ” በተሰኘው ዐምድ፣ ገናዬ ዕሸቱ ከምታስነብባቸው ተከታታይ ጽሑፎች ሁለተኛው የሆነው ይህ ጽሑፍ፣ ወንጌል ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል ተብሎ የሚታመንባቸውን ዘመናትና የአገባብ ሒደቶች ቀረብ አድርጋ ታስቃኘናለች።
ጓደኛዬ ነው፤ “ወደኛ ቸርቸ ካልመጣህ” ብሎ ሁሌ ይነዘንዘኛል መሄድ ባልፈልግም “ስለንዝነዛው” ብዬ አንድ ዕለት ለመታደም ከስምምነት ላይ ደረስን። ከዚያ በፊት ግን ‘ለምን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባለህ ጊዜ ደስ አላለህም?’ ትሉኝ ይሆናል፤ ጥሩ ጥያቄ ነው። ከዚህ ጓደኛዬ ጋር በደባልነት አብረን መኖር ከጀመርን ረጅም ጊዜ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ በኋላ፣ ማለትም “ጠርማሽ ትውልድ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን” ወደ ተሰኘ ጉባኤ መሄዱን ማዘውተር ከጀመረ ወዲህ ነገረ ዓለሙ ተቀይሯል። እንደ እርሱ አባባል “የእምነት እና የኀይል ሰው” ሆኗል።
በወንጌላውያን የሚሲዮን ታሪክ ፋና ወጊ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው በዐፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት (1625 – 1660 ዓ.ም.) እንደ መጣ የሚታመነው ጀርመናዊው ፒተር ሄይሊንግ ነው። ፒተር በኢትዮጵያ ቆይቶ በ1644 አካባቢ ወደ አገሩ ለመመለስ በመንገድ ሳለ፣ ቱርኮች አግኝተው እስልምናን እንዲቀበል ቢያስገድዱትም አሻፈረኝ በማለት አንገቱን ቀልተው ገደሉት። ይህ ሚሲዮናዊ በኢትዮጵያ ሳለ የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ችሎ የነበረ ሲሆን፣ የዮሐንስ ወንጌልን ወደ አማርኛ በመመለስ ለሕዝቡ እንዳበረከተ ታሪክ ዘግቦታል።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment