[the_ad_group id=”107″]

ነፍስም ይርባታል

“በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርስ አንተን ካገኘሁ ምን እሻለሁ?” (መዝ. 73፥25) 

በወርኀ ጥር የፈረንጆቹ ዐዲስ ዓመት ባተ። ሰዉም እንደየፈሊጡ “እንኳን አደረሳችሁ” ሲባባል ከርሟል። ዐውደ ዓመት መጣ በተባለ ቍጥር፣ ዐዳዲስ ዕቅዶች ይነደፋሉ፤ በተስፋ ከተነሣሡ ልቦች የወጡ ፍላጎቶችም “ፀሓይ እንዲሞቃቸው” ይደረጋል፤ መልካም ነው። የመሻቶችና የፍለጋዎች መደምደሚያና ዳርቻ የኾነውን ባለመዘንጋት ቢደረግ ደግሞ እጅግ መልካም ይኾናል፤ ይህ “መደምደሚያ” እግዚአብሔር አምላክን መፈለግና ክብሩን መጠማትን ይመለከታል።

በብዙ ነገሮች አፍነን ልናዳፍነው ብንሞክርም እንኳ፣ እግዚአብሔርን የመራብ ጥልቅ ስሜትና ፍላጎት ያለን ፍጡራን ነን። ይህ ፍለጋ ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊነቃቃ የሚችል መኾኑም እውነት ነው። ብሌይዝ ፓስካል እንዳለው፣ እግዚአብሔር ካልሞላው በቀር ምንምና ማንም ሊሞላው የማይችል ባዶ ኦና በሰው ልብ ውስጥ አፉን ከፍቶ ይኖራል። የትኛውም ነገር አጥለቅልቆን እርሱ ግን ከሌለን መንፈሰ ኰስማና (ኰሳሳ) እንኾናለን። ደካሞች መኾናችንን ማመናችን ብርታትና አቅም ያለው ሌላ ረዳት እንዳለን ብቻ ሳይኾን፣ እርሱን የመፈለጋችንን ጥልቀት ያሳያል። ይህ መንፈሳዊ መርሕ ነው። “ነፍሳችን የትኛውም አመክንዮ የማይገልጠው የራሷ አመክንዮ ስለ አላት” (ቅ. አውግስጢኖስ)፣ በትክክለኛ መንገድ ከተቃኘች፣ እግዚአብሔርን በማግኘት ብቻ ከረኃቧ መጥገብ መቻሏን ትገነዘባለች።

ብዙውንጊዜግን፣የሰውነፍስትግልናጥማትበልዩልዩ ነገሮች ተጠልፎ ሲልከሰከስና በአምልኮተ ጣዖት ሲከሽፍ ተገኝቷል። ለጣዖት መገበር ሲባል፣ እንጨት ጠርቦ፣ ድንጋይ አለዝቦና ብረት አቅልጦ በተቀረፀ ምስል ፊት መንበርከክ ብቻ አይደለም። ዐይነቱና ገጽታው ብዙ ነው (የዶ/ር አፈወርቅ ኀይሉን “ኑ፡- ‘አምላክን’ እንፍጠር” ጽሑፍ ያስቧል)። እንዲያውም፣ በጆን ካልቪን አባባል ለመግለጽ፣ ሰው ይሉት ፍጡር ባለማቋረጥ ጣዖት የሚፈለፈልበት የጣዖት ጎተራ ነው። ከዚህ ቤተ ጣዖት ማምለጫው ደግሞ እግዚአብሔርን ማወቅና በክርስቶስ ቤዛዊ ሥራ መጐብኘት ብቻ ነው። 

በምሕረቱ ባለጸጋ የኾነው ጌታ ከኀጢአት ሰንሰለት ካልፈታን፣ በዐመፃችን ተጠፍረንና በነፍሳችን ችጋር ተንገብግበን ወደ መቃብር እንወርዳለን። የነፍሳችን ረኃብ ማስታገሻ ምስጢሩ የተቋጠረው እግዚአብሔርን በማግኘት ፍስሐ ውስጥ ነው (መዝ. 16)። ለክርስቲያን፣ ከእግዚአብሔር ሌላ፣ ማንኛውንም ነገር አጥብቆ መራብ (መመኘት) ቀንደኛ ጠላቱ የኾነውም በዚህ ምክንያት ነው። ረኃባችን እግዚአብሔርን ብቻ ሲኾን ድልን ያጐናጽፈናል።

ረኀባችን የሕይወታችንን አቅጣጫ ይወስነዋል። የምርጫ ጕዳይ ነው፤ በአንድ በኩል፣ ሆዳችንን በእንጀራ በመሙላት የነፍሳችንን ምኞት ለማስታገስ እንሞክር ይኾናል፤ ካልኾነም ሥልጣንና ክብርን ለማግኘት ለሚንገበገበው ግልብ መጐምዠታችን በማጐብደድ እንገልጸዋለን፤ ወይም ደግሞ መንፈሳችን እግዚአብሔርን በማግኘት ናፍቆት ተመልቶ እርሱን በመፈለግና ሲገለጥልንም እርሱን በማግኘቱ እፎይ እንላለን። 

“በራስ ቍስል እንጨት አይሰዱም”፤ ገመናን ዐይን አያስመቱም። (ርግጥ፣ በሌላው ቍስል ዕንጨት መስደድ የሚሉት ጭካኔም በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።) ይኹን እንጂ፣ አንዳንድ ጊዜ፣ የሚሰማንን ነገር ለሚሰማን ማውጋቱ ክፋት የለውም። እግዚአብሔርን የመፈለግን ያህል ግን አያሳርፈንም።

የተለጠጠ መጐምዠትና ጣዖት አምልኮ በተንሰራፋበት በዚህ ዓለም፣ ነፍስን ከሚያልፈሰፍሱ ነገሮች በመራቅ በቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት፣ በጾም፣ በጸሎትና በጥሞና ሱባኤ … ተወስነን “እግዚአብሔር ሆይ፣ ይህን ያህል ነው የተራብሁህ፣ እጅግም እፈልግሃለሁ፤ እራብህማለሁ” ማለት እንችላለን። ከግርግሩ መኻል ተነጥለንና ወደ “ምድረ በዳው” አቅንተን በመንፈስ መገስገስ ያስፈልገናል።

በአንድ ወቅት ከእምነታቸው ሳያፈገፍጉ፣ ከማኅበረ ምእመናኑ መካከል ስለሚነጠሉ ሰዎች በባልንጀሮቼ መካከል ውይይት ሲደረግ ነበር። እኒህ “ተነጣዮች” ለምን ይህን ያደርጋሉ? ጥያቄው ቀላል ባይኾንም፣ ጥቂት ምክንያቶች መጠቃቀስ ይቻላል።

ይህን ርምጃ ለመውሰድ የግድ በክሕደትና በአምልኮተ ጣዖት መሰደድ አይኖርባቸውም። ምውት ርቱዕነት (dead orthodoxy) ሲከብባቸውና ሕይወት አልባ ሃይማኖተኛነት ሲንሰራፋ ከመንጋው የሚነጠሉ ይኖራሉ። እኒህ ወገኖች ከመንፈስ መታፈን ለመሸሽ “ምድረ በዳው” ሊናፍቃቸው ይችላል። በሕይወት የማይገለጥ ሃይማኖታዊ አስመሳይነት የሠቀጠጣቸው ቅዱሳን ከዚህ መሰሉ ርምጃ ጋር ይፋጠጣሉ።

ምግባራዊ መላሸቅ የእግዚአብሔርን ስም ሲያስነቅፍ መታገሥ የሚችል መንፈሳዊ ሰው የለም። ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ዐይነት ሽሽትና የምድረ በዳ መሸሸጊያ ተመኝቷል። “ሁሉም አመንዝሮች፥ የአታላዮች ጉባኤ ናቸውና፣ ሕዝቤን እተዋቸው ዘንድ ከእነርሱም እለይ ዘንድ በምድረ በዳ የመንገደኞች ማደሪያን ማን በሰጠኝ?” (ኤር. 9፥2) በማለት ጮዃል። የሸንጎ አደባባዩን ለትርምሱ ለቅቆ ፈቀቅ ማለትን መርጧል።

በሌላ በኩል፣ አክራሪ ለዘብተኛነት (extreme liberalism) አንሰራርቶ መንፈሳዊ እውነቶችን በአመክንዮና አንክሮ ሰብ (anthropocentric) መሠዊያ ላይ ሲጥደው የሚቈጩ አማኞች ከዚህ ድባብ ለመራቅ የሚወስዱት “የማምለጥ” ርምጃ ሊኖር ይችላል። በአካዳሚያዊ “የፀጕር ስንጠቃ” ጥናት ስም የሚካሄድ መፋዘዝና ድንጋዜም የሚያስቈጣቸው ይኖራሉ።

በተጨማሪም፣ ግልብ ስሜታዊነት የወጠረው ማኅበረ ሰብ ተበራክቶ አስተምህሯዊ ጤናማነት፣ ምግባራዊ ስክነትና የመንፈስ ጥንካሬ ሲጠፋ ከማኅበሩ የሚሸሹ ክርስቲያኖች አሉ። የስሜት ፍንጠዛና እጅ እጅ የሚል ሰው ሠራሽ ኹካታም ጥሞናን ሲያደፈርስ የመንፈስ መቈጣት የሚገጥማቸው ይገኛሉ።

በተጨማሪ፣ የሕያው እግዚአብሔር መገኘት ውስጥ መንፈሳችን የሚካፈለውን ወትሯዊ መታደስና መታነጽ ለማግኘት ያላቸው ፍል ጕጕት የጥቅስ ለምድ በለበሱ መንፈሳዊ ሽፍቶች ትርኢት ሲተካ “ከእምነታቸው ያላፈገፈጉት” ቅዱሳን መሣቀቃቸው አይቀርም። የቃለ እግዚአብሔር ክብርና የመንፈሳዊ እውነቶች ጥልቅ ግንዛቤ ሳይኾን ደመ ነፍሳዊ ልማድ የነዳው ሰብኮ አደር ዙሪያ ገባውን ሲወር እንደ ዘማሪው፣ “በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ? እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ” (መዝ. 55፥6-7) እያሉ ያምሰለስላሉ። ለሕዝቡ “እስከ መታየታቸው” (ሉቃ. 1፥80) ወይም በአደባባዩ እስከ “መገለጣቸው” ድረስ (1ነገ. 18፥1)፣ “በምድረ በዳ” እና “በዋሻ” እየተቅበዘበዙ (ዕብ. 11፥38)፣ በተባሕትዎ (ብቸኝነትና ጸጥታ) ኑሮ ውስጥ የሚፈጠርን ጥልቅ ስሜት መጋፈጣቸውም አይቀረም።

ጋሽ ንጉሤ ቡልቻ ተመሳሳይ መብሰልሰል ጽፏል፤ “በድምፅ ብርታት የሚያምን፣ ጥሞናን እጅግ የሚፈራ፣ በጸጥታ የሚፈሰውን ሰማያዊ ኅብረ ዜማ ለመስማት ጆሮው ያልተቃኘ፣ የራሱን ድምፅ በመስማት ግን ጮቤ የሚረግጥ፣ የዝማሬ አምልኮ የሚመስል የኹካታ እንቅስቃሴ አለ። ይህ በየስፍራው የምንሰማው ከባድ ጫጫታ የውስጥ ባዶነት ማባበያ ይኾንን እያልሁ እፈራለሁ።ነገርግንከንቱጫጫታባዶነትያባብሳል እንጂ አይፈወሰውም። ዝላይና ግርግር ሊያሳብደን ሲደርስ ልቦናችንን እንዳንስት አንዳንዴ ወደ ምድረ በዳ መሸሽ ያሻን ይሆን? ጌታችን እንደዚህ ማድረግ ልማዱ ነበር” ይላል።

ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከቅዱሱ መንፈስ ዘንድ ከሚያውቁት ልምምድ በተጻራሪ ይህን “ባዶና ከባድ ጫጫታ” የተጸየፉ ወገኖች፣ መዋግደ ኅሊና (መታወክ) እንደ ደረሰበት ሰው ምላሻቸው ምናኔያዊ ማፈግፈግ ቢወልድና በረሓውን ቢናፍቁ ሊያስገርም አይገባም። ካሉበት መገለል ወደ አንድ አካል መቅረብ ያስመኛቸዋልና። “በምድረ በዳው” የሚፈልጉት ግን ሌላ ማንንም እና ምንንም አይደለም፤ እግዚአብሔርን ራሱን ነው። ከፊቱ ብርሃን በሚገኘው ክብር ብርሃን ያያሉና (መዝ. 36፥9)። የነፍሳቸው ቀንዲል ሳትለኰስ ለሌሎች ማብራት እንደማይችሉ ያውቁታል።

ኵራዝ መለኮሱ ብቻ አይበቃም፤ እንዲያበራ በከፍታ ላይ ያኖሩታል። የጋን ውስጥ መብራት ከጨለማ አንድ ነው። ብርሃን ካልሰጠ ጥቅሙ ምንድነው? ስለዚህ፣ “የነበር ናፍቆት” (nostalgia) ነፍሱን እንደሚመዘምዘው አዛውንት “ኵራዛችን” እንዳይጠፋ ወደ መገኘቱ ብርሃን እንዞራለን። በቀንዲላችን ላይ ከጸጋው ዘይት ካልጨመረልን ነዲዱ መክሰሙና በዐመድ መጐፈኑ አይቀርም። ለምንገኝበት ማኅበረ ሰብ ጥያቄዎችም መልስ አይኖረንም።

ያለንበትን ኹኔታ ውስብስብነት ካልተረዳን መፍትሔ አናመጣም። አንዳንዱ ነገር ያልተዳወረ ማግ መስሏል፤ ቢዘነጥሉት ይጐለጐላል። ለእውነት ብንወግንም፣ ሰዎችን በፍቅር ማከም ካላወቅንበት ሳናቈስል አንመለስም። እንደ ቡጢ ሲሰጡት በሚቀለው “መካሪነትና ወጋጅነት” ብቻ ሩቅ መሄድ ይቻላልን? ያለስስት ራሱን የሰጠው ኢየሱስ ፍቅሩን የገለጠው ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ነበር። ለሥራችን ስኬት ከፍ ያለ ግምት በመስጠት፣ ነገር ግን ጌታን ከመፈለግ በማመንታት ብንኖር ሕይወታችን ይጨናጐላል፤ እንደ ገረወይና በቃል ብቻ የሚንኳኳ ሕይወት ለሌሎች አይተርፍም።

አንዳንድ አገልጋዮች በቃላችንና በኑሯችን መካከል ልዩነት መፍጠራችን አሳዛኝ ነገር ነው። የ17ኛው ምእት ዓመት ጸሐፊ የነበረው ሪቻርድ ባክስተር “ብዙ ሰዎች በጥንቃቄ እየሰበኩ በግድ የለሽነት ይኖራሉ” በማለት የሚያለቅሰው ለዚህ ነው። አገልግሎታችን ለብዙዎች መድረስ በቻለበት ጊዜ ብዙ ዐይኖች በእኛ ላይ ያርፋሉ፤ ካልተጠነቀቅን ይህ አታላይ ልባችን በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ አጕል ሊያደርገን ይችላል። ጠንካሮች የምንመስለው እኛ ምንኛ ደካሞች ነን! ረድኤቱን እንዲሰጠን ወደ እርሱ እንገሠግሣለን (መዝ. 63፥1)።

ስለ በላን ብቻ አንጠግብም፤ ስለ አነበብን ብቻ አንጽፍም፤ ስለ ተዘጋጀን ብቻም አንሰብክም። መድረክ ባገኘበት ያገኘውን ነገር እያላዘነ እንደሚደሰኩር ፖለቲከኛ አናስተምርም። የእግዚአብሔር ክብር ባልተገኘበት ምንም አላገኘንም።

አንድ ነገር ስለ ተጻፈ ብቻ አይነበበብም። ስብከት ስለ ተለፈፈ ብቻም አይደመጥም። ዝማሬስ እውነትና የሕይወት መንፈስ ከሌለበት ከዘፈን በምን ይለያል? ማንበብ እንሻለን፤ ግን ያላደፉ ገጾች መኾን አለባቸው። የቃለ እግዚአብሔር ፍታቴም ትርጕም የሚሰጠውና ሌሎችን የሚያክመው እውነትና ፍቅር ከሕይወት ጋር ተዳውረው ሲቀርቡበት ነው። ይህ እንዲኾን እጅግ ከበዛው የመገኘቱ ክብር ቀርበን የጸጋውን ባርኮት መቅዳት ይኖርብናል። አቤቱ ጌታ ሆይ፣ አግኘን። 

የቈረጠች ነፍስ ዜማ የእግዚአብሔር ክብር ነው፤ ሕልሟን ከግዞት ሸምቀቆ ለማስጣል ትተጋለች እንጂ ለረብ የለሽ የዓለም ጮማ አትፏትትም። ብዙዎች በሚቋምጡት የሥጋ ጥረሾ ሆዷን እየሞላች እውነት ላይ ከማላገጥ፣ ለትክክለኛው ምርጫ በመቆም ብትራብ ትመርጣለች። ቍልቍል ሊደፍቃት የተሰነዘረባትን ኵርኵም በመፍራት ከሐሰት ጋር አትሞዳሞድም። ለዚህ ከንቱ ምኞት ለሞላበት ዓለማዊ ማግበስበስም አታሸረግድም። እንዴት ሲደረግ? ሕልሟ የተፀነሰው በቀራንዮ አይደለምን? ደም ተከፍሎበታል እኮ። ወደ ኋላ መመለስ አይታሰብም።

ታዲያ አንድ ነፍስ እንዲህ ለመቍረጥ በራሷ ምን አቅም ይኖራታል? ጌታ በመንፈሱና በቃሉ ድጋፍ አበርትቶ ያሰናዳታል እንጅ። እርሷም ያን እፎይታ የተመላ ጸጥታና መታመን ለማግኘት ደግሞ ወደ ጌታዋ ትማልላለች። 

እኛስ? ‘በሕልማችሁ ለውጥ ከርሳችሁን ሙሉ’ ብንባል፣ መልሳችን ምን ይኾናል? በአብ ፍቅር ተመልቶ በዓለም ላይ ያልሸፈተ መንፈስ ለሥጋ ይገብራል፤ ለሰው ትምህርት ያድራል። ስም ያወጡ እኔ ባይ ባለጊዜዎች ይቀራመቱታል። ዛሬ በስፋት እየኾነ የምናየው ሽንፈት ይህን መስሏል። ከዚህ ዐይነቱ የመንፈስ ሥቅይት በምን ያመልጧል? እግዚአብሔርን በመራብ ውስጥ በሚገኝ የመንፈስ መታደስ አይደለምን?

አውድማው ተራቁቶ፣ ጐተራው ሲጐድል እንዴት ዝም ይባላል? በቍጭት መትከን ይኖራል። “አገር ሲያረጅ እንክርዳድ ያበቅላልና”፣ ሁዳድ ሲከስም አሜከላ ይውጠዋልና መብሰልሰል ያጋጥማል። ኾኖም “ከዘመን ተጣልቶና ተኳርፎ” (ደበበ ሰይፉ) ያረመመውን ለመቀስቀስ የሚበቃ የብራቅ ደወል ወደ የት አለ? “የዘመን ደዌ ሲያስታምም” (ጸጋዬ ገ/ መድኅን) ለባዘነው ቍስለኛ የሚያገግምበት የተስፋ ብሥራት አያስፈልገውምን? ነገር ለጃጀበት ትውልድ፣ የተስፋ ስንቁ ምንድነው? የእግዚአብሔር የፊቱ ብርሃን አይደለምን? “የዘመን ልብስ ሲያድፍ” (ግርማ ተስፋው)፣ ሽበት አንድም የእንጨት ኾኖ ሲቀልል፣ አንድም በዋልጌ ተደፍሮ ሲናቅ በእንባ ሸለቆ መታለፉ አይቀርም፤ ይለቀሳል። 

ርግጥ፣ የታመቀ እንባ ፈንቅሎ መውጣቱ ፈውስ ነው። ጊዜም የሚሰጠው ፈውስ ሊኖር ይችላል። ኾኖም ጊዜና እንባ የማያጥቡት የነፍስ ጉድፍ ሞልቷል። እግዚአብሔር በጸጋው ሲዳብሰን ብቻ የሚገኝ ጥልቅ እፎይታ አለ። ኦዝዋልድ ሳንደርስ “ምንም እንኳ ጊዜ ኪሳራውን ሊያሟላልን ባይችልም፣ የኀዘኑን የመውጊያ ብረት ግን ለጊዜው ሊያዶለዱመው ይችላል። ኾኖም ከጊዜ ይልቅ በኀዘን የቈሰለ የሰዎችን ልብ የመፈወስ ታላቅ ኀይል የተሰወረው ከራሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በምንቀበለው መጽናናት ውስጥ ብቻ ነው” ብሏል። አምላካችን ሆይ፣ እነሆ እንፈልግሃለን፤ እንራብህማለን። በሙላትህ አጥግበን፤ ፈውሰንም (ዮሐ. 4፥13-14)።

በሌላ በማንኛውም ነገር ለመጥገብ ብንሞክር ድካም ነው። ጠቢቡ እንዳለው፣ “የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፥ ነፍሱ ግን አትጠግብም” (መክ. 6፥7)። ዘመናችንን ሁሉ ተራውጠን ልንሞላው ብንሞክር፣ ማንምና ምንም የማይሞላው ሽንቍር በልቦናችን ተጐድቧል። 

ከሊዎ ቶልስቶይ ዝነኛ ሥራዎች መካከል “ለሰው ምን ያህል መሬት ይበቃዋል?” የተባለ ታሪክ (story) ይገኛል። ዋነኛው ባለታሪክ ፓሆም (Pahom)፣ “ሰፊ ጕልት ከኖረኝ ሰይጣን እንኳ አያስፈራኝም” የተሰኘ ድንፋታ ተጠናውቶት፣ መሬት ገዝቶ ሊበለጽግ ሲባትል ኖረ።

በመጨረሻ፣ እጅግ ሰፊ መሬት የነበራቸውና “ሞኛ ሞኝ” ስለ መኾናቸው የሰማው ባሽኪሮች (Bashkirs) ጋር ተገናኝቶ፣ መሬታቸውን ለመግዛት ይዋዋላል። ግብይቱ ያልተለመደ ዐይነት ነበር። አንድ ሺህ ሩብል ብቻ በመክፈል የቻለውን ያህል መሬት ለክቶ መግዛት ያስችለዋል። መሬቱን ለመግዛት ከአንድ ቦታ ተነሥቶ፣ መነሻው ላይ ምልክት አድርጎ፣ የቻለውን ያህል እየሮጠና በአካፋ እያሰመረ ማካለል ይኖርበታል። ከማለዳ ጀምሮ ቀኑን ሁሉ በመሮጥ ማካለል የቻለውን መሬት አዳርሶ ሲያበቃ፣ ጀምበር ከመጥለቋ በፊት ከተነሣበት ቦታ መመለስ አለበት። አለዚያ ግን መሬቱን አያገኝም፤ ገንዘቡም ይከስራል። 

በዚሁ መሠረት፣ በማለዳ መሮጥ የጀመረው ፓሆም፣ ማካለል በቻለው ሳይረካ ከፊቱ የቀረውን ለመጨመር ሲኳትን፣ ጊዜው ነጐደበት። የማታ ማታ፣ ከተነሣበት ለመድረስ ባለ በሌለ ኀይሉ ተጣጣረ። የሞት ሞቱን ታግሎ ደረሰ፤ ፀሓይም ጠለቀች። ነገር ግን፣ ፓሆም በድካም ጣር እየተሳበ ቢደርስም፣ ተዝለፍልፎ ተደፋ፤ ሞተም። ባሮቹም ወስደው ስድስት ክንድ በማትሞላውና “በምትበቃው” መቃብሩ አሳረፉት። ድርጊታቸውም፣ የታሪኩ ርእስ ያነሣውን ጥያቄ በምጸት መለሰ። በአልጠግብ ባይነት ሁሉን ለማግበስበስ የሚናውዘው ሰው፣ ዐጽመ ርስቱ ሞቶ የተቀበረባት ጕድጓዱ ኾነች።

ተመሳሳይ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ቀርቧል። ሞኙ ሀብታም ተጨማሪ ጐተራ ሠርቶ ለነፍሱ ዋስትና ሊሰጣት ሲቋምጥ ዕለቱኑ ነፍሱን ተነጥቆ አደረ (ሉቃ. 12፥16-21)። “ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው” (መክ. 5፥10)።

የመተንፈስ ምኞት እንዲሞላ፣ እውነትን አንምታው። ዓለምን አትርፎ እግዚአብሔርን ያላገኘ ምንም አላገኘም (ማር. 8፥36)። ጎጆን ያለባላ ይሠሯል? ከእግዚአብሔር ተጠግተን መጥገብ ስንችል ከትናንት ጋር ለምን እንጣላለን? ከየኹኔታው ጋር ለምን እንላተማለን? 

እግዚአብሔርን መራብ እርሱን እንድንፈልግ ይጐተጕተናል። የምንፈልገው የተራብነውን ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እግዚአብሔርን የፈለጉና የተጠሙ ሰዎች እርሱን በማግኘት መርካታቸውን አንብበናል። ይህ ነገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ብቻ ሳይሆን የተፈጠርንበትን ዓለማ ይመለከታል፤ ነፍስም ይርባታል።

የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ግብ እግዚአብሔርን ማክበር በእርሱም ብቻ ደስ መሰኘት ነውና፣ የእግዚአብሔርን ክብር መራብና የመንፈሱን አሁንነት መጠማት የሕይወት ዘመን ፍለጋ ነው። አንዴ አግኝቼዋለሁና በቃኝ አይባልም። ጆን ፓይፐር ጥሩ አድርጎ ገልጾታል፤ “ለእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ጠንካራ መጠማት ሊሰማን ካልቻለ፣ እስኪበቃን ጠጥተን ስለ ረካንና ስለ ረሰረስን አይደለም። ይልቅስ፣ በዓለም ገበታ ዙሪያ ቀርበን ለረጅም ጊዜ ባግበሰበስነው ትንንሽ ነገሮች ነፍሳችን ስለ ታፈነች፣ ለትልቁ ያላት ቦታ በመጣበቡ ነው።”

Solomon Abebe G. Medihin

እውነተኛ አምልኮተ ሕይወት

አምልኮን በአንድ ቃል ለመግልጽ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ከራስ ለሚበልጥ አንድ አካል የሚሰጥ ታላቅ አክብሮትና ስግደት፣ ወይም በፍርሀትና መንቀጥቀጥ ራስን ለሌላው ማስገዛት ወይም መስጠት የሚለውን ሐሳብ ይገልጻል፡፡ አምልኮ በዕለተ ሰንበት በጋራ ተከማችተን የምናሰማው የዝማሬ ድምፅ ወይም የምናከናውነው ሃይማኖታዊ ሥርዐትና ልማድ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን መላው ሕይወታችንን በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ለጌታ ማስገዛትና መኖርን ያካተተ ልምምድ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

የአዲሱ ጅምር “አብዮት” ዕጣ ፈንታ

ምኒልክ አስፋው በዚህ ዘለግ ባለ ጽሑፉ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ክርስቲያናዊ የሆነ ዕይታውን ያካፍላል። በዚህም በተለይ ብዙዎች የሚመኙት “ዴሞክራሲ” እውን እንዲሆን መሠረታውያን ያላቸውን መስፈርቶች ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ጋር እያመሳከረ ምክረ ሐሳቡን ያካፍላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.