
[the_ad_group id=”107″]
የዕብራውያን መልእክት የሹመት መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉን ሙሉ ነገረ መለኮታዊ ክብደት የሚሸከመው “በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” የሚለው እውነታ ነው (ዕብ 1፥3፡ 13፤ 8፥1፤ 10፥12-13፤ 12፥2)። ኢየሱስ ከሁሉ እንደሚልቅ ሰባኪያችን ሲሞግት፣ የሚያቀርባቸው መሠረታዊ ማስረጃዎች በሙሉ በዚህ ልዕልና እና እውነታ ላይ የተመረኮዙ ናቸው። እውነታው “ተቀመጠ” (ኧካቲሰን | ἐκάθισεν)” (1፥3) የሚለው ሲሆን፣ ልዕልናው ደግሞ የተቀመጠበት ምጡቅ ሥፍራ ነው፤ “በሰማያት በግርማው ቀኝ” የተባለው። በመሆኑም የሰባኪው ማዕከላዊ መልእክት፣ ‘ኢየሱስ ይልቃል’ የሚል ሲሆን፣ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ “በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጧልና” የሚል ነው። በዚህ ስብከታዊ ደብዳቤ ውስጥ ሁሉም ነገር የተቃኘው በዚህ ዐውድ ሥር ነው።
ይህንን ልዕልና ከዕብራውያን የነገረ መለኮታዊ አቀራረብ ስልት አንጻር በሁለት ንጽጽራት መድበን መመልከት እንችላለን። አንደኛው “ምድራዊ ሰማያዊ” የሚል “የቁም ንጽጽር” ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ “ይኼኛውና የወዲያኛው” ዓለም የሚል “ሰያፍ ንጽጽር” ነው። በሰማያት የተቀመጠበትን ልዕልና በምድር ካሉት ካህናት፣ መሥዋዕት፣ ድንኳን ወዘተ. እንደሚልቅ ያነጻጽራል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ልዕልናውን (ለእኛ ገና ወደ ፊት፣ ለእርሱ ግን አሁን እውን በሆነው) ሊመጣ ባለው ዓለም ውስጥ መጥቆ የተመረቀ በመሆኑ “ይልቃል”። ይኸውም ገና ወደ ፊት የሚገለጠውን ክብር፣ አሁን “የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ” በኢየሱስ ላይ እናያለን (2፥9)። በሁለቱም ንጽጽሮች ውስጥ የምናየው ልጁ በግርማው ቀኝ መቀመጡን ነው። ወደዚያ ልዕልና ያረገና የተቀመጠ ማንም አልነበረም፤ ከእርሱም ሌላ ሊኖር አይችልም። ኢየሱስ ይልቃል!
በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ሁሉም ነገር የጸናው በዚህ መሠረት ላይ ነው! “ፍጹም”፣ “ፍጻሜ”፣ “ፈጻሚ”፣ የሚሉትም ቃላት በመልእክቱ ውስጥ የተራቡት ከዚህ እውነታ የተነሣ ነው። በአገልግሎታቸው እንዳይቀጥሉ ሞት የከለከላቸው የቀደሙት ካህናት ብዙዎች ነበሩ (7፥23)። እነርሱም ዕለት ዕለት “ቆመው” (ኧስቴከን | ἕστηκεν) ያገለግላሉ። ይኸኛው ካህን ግን ለዘላለም ፍቱሕ የሆነውን አንዱን መሥዋዕት “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” አቅርቦ፣ በሰማያት በግርማው ቀኝ “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ … ተቀምጧል” (ኧካቲሰን | ἐκάθισεν)” (10፥11-12)። እነርሱ “ቆመዋል” (10፥11)፤ ኢየሱስ ግን ተቀምጧል (10፥12)! የቆመ ጉድ ጉድ ይላል፤ የተቀመጠ ግን ዐርፏል። የተቀመጠ አጠናቅቋል። የተቀመጠ በእንቅስቃሴ ላይ ስላይደለ ‘ፍጻሜግቡ’ ላይ ደርሷል ማለት ነው።
ከሙታን መካከል “ወጥቶ” (13፥10) በሰማያት አልፎ (4፥14) መቀመጡ፣ ክህነቱ የዘላለም እንደ ሆነ አረጋግጦልናል (7፥24)። እነርሱ ሟች በመሆናቸው ክህነታቸው በትውልድ ሐረግ ላይ የተመሠረተ ነበር (7፥23)። እርሱ ግን ‘በማይጠፋ የሕይወት ኀይል’ ለዘላለም ስለሚኖር፣ ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ዘላለማዊ ነው (7፥17)። የሌዊ ክህነት “ፍጹምነትን” (ተሌይኦሲስ | τελείωσις) አላስገኘም ወይም ግቡን አልመታም (7፥11)። የክህነቱም ሕግ “ማንንም ፍጹም ሊያደርግ” አልቻለም (7፥18–19)። የእንስሳት ደም ይቀርብባት የነበረችው “ፊተኛይቱ ድንኳን” ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገዷ ዝግ በመሆኑ ፍጹም አልነበረችም። ይደጋገሙ የነበሩት የምግብ፣ የመጠጥና የመንጻት ሥርዐቶች፣ አዲሱ ሥርዐት እስኪመጣ ድረስ የሚደረጉ “ሥርዐቶች” ብቻ እንጂ አምላኪውን በሕሊና “ፍጹም” ሊያደርጉት አልቻሉም (9፥9–10)። ይህ “የተቀመጠው” ካህን ግን በሥጋው መጋረጃ ‘መንገዷ ክፍት’ ወደ ሆነችው ወደ ታላቅ እና “ፍጹም” (ተሌይዖስ | τέλειος) ድንኳን ገባ።
ሕጉ ማንንም እግዚአብሔር ወደ ዐቀደው ፍጻሜ (ኧተሌይኦሰንἐτελείωσεν) ማድረስ አልቻለም (7፥19)፤ ማለትም ማንንም ወደ እግዚአብሔር ፍጹም አድርጎ ማቅረብ አልቻለም። ስለዚህ የማይጠቅም ስለሆነ “በሚሻል ተስፋ” ተሽሯል (7፥18)። ይህ “የሚሻል ተስፋ” ምንድር ነው? ኢየሱስ “በመሓላ” ሊቀ ካህናት የሆነበት ክህነት ነው። “እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም … አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” (7፥20-21፤ 5፥6፤ 6፥20፤ 7፥21፤ መዝ 110፥4)። የኢየሱስ ክህነት የተማለበት እንጂ እንደ ሌዊ ክህነት በነቀፌታና በጸጸት የተሞላ አልነበረም፤ “በሕግም ብዙ ሰዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አስነውራችኋል” (ሚል 2፥8) እንደ ተባለው። ስለ ልጁ ግን ሲናገር፣ “ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ፤ አይጸጸትም።” አሮን ሊቀ ካህናት እንዲሆን እንደ “ተሾመ” (5፥1፡ 5)፣ ኢየሱስም በእግዚአብሔር ተሹሟል። ነገር ግን የሌዊ ኪዳን ፍጹም የሆነው እስኪመጣ ሻጥ የተደረገ ጊዜያዊ ሹመት እንጂ፣ እንደ ልጁ “ከመሓላ ጋር” የመጣ አልነበረም (7፥20–21)። እንዲሁም የአዲስ ኪዳኑ ተስፋ ይህም፣ “በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስብም” (8፥12) የሚለው በመልከጸዴቃዊ ካህን የገዛ የደም መሥዋዕት አማካኝነት ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ አንጽቶታል (9፥14)።
የተጠሩት የተሰጠውን ተስፋ አሁን በርግጥ መውረስ ይችላሉ። ምክንያቱም ከሕጉ በኋላ የመጣው መሓላ “የአዲስ ኪዳን መካከለኛ” የሆነውን “ፍጹም ልጅ” ሾሟልና ነው (7፥28)። ይህ ፍጹም ልጅ ፍጽምናን የሚያስገኝ ፍጹም መሥዋዕት አቅርቧል፤ “ለተሻለ ኪዳን ዋስ ሆኗል” (7፥22)፤ “ከኀጢአታቸው ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቷል” (9፥15)። ሰባኪው እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደማይለወጥ “በመሓላ” ያጸናቸውን ሁለት ተስፋዎች እንደ ነበሩ ያሳያል፤ ‘እግዚአብሔር ለአብርሃም ማለ’ እንዲሁም ‘ለዳዊት ልጅ’ በመዝ 110፥4 ላይ ማለ። እኛም የምንመካበትን ተስፋ (3፥6) እስከ መጨረሻ ድረስ አጥብቀን ብንይዝ (3፥14)፣ ተስፋው እስኪሞላ ድረስ ብንጸና (6፥11)፣ የተስፋችንን ምስክርነት (10፥23)፣ ጸንተንም ሃይማኖታችንን ብንጠብቅ (4፥14)፣ በፊታችን ያለውን ተስፋ እንወርሳለን። ለምን? “ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ” ስላለን (6፥17–18)። ግን እንዴት ርግጠኛ መሆን እንችላለን? ምላሹ፣ ተስፋው እንደ ነፍስ መልሕቅ (የርስታችን መያዣ) ተጠምጥሞብናልና ነው። የሕይወታችን ጀልባ ይናወጥ እንጂ፣ ተስፋችን “ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ” የተማለለት ተስፋ ነው። ይህም ተስፋ ውል ዘልቆ “ወደ መጋረጃውም ውስጥ” ይገባል፤ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት “ለዘላለም ሊቀ ካህናት” (6፥20) እንዲሆን በተማለለት ወገብ ላይ ተጠምጥሞ፣ በግርማው ቀኝ ተቀምጧል። በዚያ “ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ” ገብቷል (6፥20)፤ ዘወትር ይማልድልናል (7፥25)፤ በእግዚአብሔር ፊት ይታይልናል (9፥24)።
ሁሉን በአፉ ቃል የሚያንቀሳቅሰው (ፌሮን | φέρων) ይህ መለኮታዊ ልጅ (1፥3)፣ በምድር ላይ ሰው ሆኖ ተንቀሳቅሶ “ኀጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ”፣ በሰማያት አልፎ በግርማው ቀኝ ተቀምጧል። እርሱም በመከራ “ፍጹም” (ተሌዮሳይ | τελειῶσαι) እንዲሆን ተደርጓል (2፥10)፤ በተቀበለውም መከራ “ፍጹም” [ተሌዮቴስ | τελειωθεὶς] ሆኖ ከተገኘ በኋላ፣ “ለሚታዘዙ ሁሉ የዘላለም ድነት ምክንያት ሆነላቸው” (5፥9)። በዕብራውያን መልክት ልጁ ፍጹም ‘መደረጉ’ ከዚህ ቀደም ፍጹም አለመሆኑን የሚያሳይ ሳይሆን፣ ሊገባበት ላለው አገልግሎት (office) ‘ብቁ መሆኑን’ ለማመልከት ነው። ወልድ ሰው ከመሆኑ በፊት እንዲሁም ፍጹም ሰው ሆኖም መከራን እስኪቀበል ድረስ ካህን መሆን አይችልም ነበር (2፥17)። ፍጹም መደረጉም መከራን ከተቀበለ በኋላ ወደ ክህነት ቢሮው ለመግባት የተገባው (qualified) መሆኑን አሥምሮ መናገሩ ነው።
መልከጸዴቃዊ ካህን ከሥራው ዐርፏል፤ ክህነቱም ከሌዋዊ ክህነት ይልቃል። ስለዚህ እስካሁን ያየነው በዕብራውያን መጽሐፍ ነገረ መለኮታዊ አቀራረብ፣ “ተቀመጠ” የሚለው ቃል የኢየሱስን ልቀት ለማጉላት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ነው። ሰባኪው እነዚህን ሁሉ እውነታዎች መመልከት የቻለውም ሁሉንም “ከመቀመጡ” ልዕልና አንጻር” የኋሊት (retrospectively) በመመልከቱ ነው። እንደ እርሱ የተቀመጠ ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ አሁንም የለም። በመሆኑም ኢየሱስ ይልቃል!
እንዲሁም፣ ሥራውን ፈጽሞ የተቀመጠው “በሚመጣው ዓለም | τὴν οἰκουμένην τὴν μέλλουσαν” ላይ ነውና ኢየሱስ ይልቃል (2፥5)። ማናችንም ገና ያልገባንበት ፍጹምነት አሁን ገንዘቡ ነው። ከሞት ትንሣኤው በኋላ በሰማያት ዐርጎ በግርማው ቀኝ ሲቀመጥ፣ “በኵሩን ወደ [መጪው] ዓለም ሲያስገባ” በመንገድ “መላእክት ይስገዱለት” ይላል (1፥6)። ሲቀጥልም፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የነበረውን ዐላማ (2፥6-8፤ ተጓ. መዝ 8፥6፤ ዘፍ 1፥26-28)፣ በአዳም ኀጢአት ምክንያት ግን ፉርሽ የሆነውን ግብ ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ በመገኘት ፈጽሞታል። ከመላእክት ለጥቂት ጊዜ በጥቂት አንሶ የነበረውን፣ አሁን “የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን” (2፥9)። የምናየው ‘አሁን’ ነው፤ የነገሠውም ‘በመጪው ዓለም’ ላይ ነው (inaugurated eschatology)። በጌታ የድነት ትረካ ውስጥ የነበረው ይህ ሰያፍ እንቅስቃሴ አሁን በሰው ልጅ ‘መቀመጥ’ ተመርቋል። ኢየሱስ ተዋርዶ የተዋረድነውን አክብሮናል። በኀጢአት ምክንያት የፎረሸውን ሰው ሊያድን፤ እርሱ የፎራሾችን ሞት ቀመሰ። ፉርሽ ያደረጋቸው ዲያብሎስን እንዲያስፎርሽ (2፥14–15) ወንድሞቹን ሊመስል (2፥10–13፡ 17)፣ በሥጋና በደም ተካፍሎ ፍጹም ሰው ይሆን ዘንድ ተገባው። በግሪኩ፣ እነዚህ ሁለት ዐላማ ገላጭ አናቅጽ፣ “በሞቱ ‘ያ የሞት ኀይል ያለውን’ ይሽር ዘንድ፣ እርሱም ዲያብሎስ ነው” የሚለው እና “ስለ ሞት ፍርሀት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ እንዲያወጣ” የሚሉት “በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ” ለሚለው ዋና ዐረፍተ ነገር ማብራሪያዎች ናቸው። ይህም ‘የሰው ልጅ መሆነ ለምን አስፈለገ?’ የሚለውን የሚያብራሩ አናቅጽ ናቸው።
ስለዚህ ሰባኪው ሲሞግት፣ ኢየሱስ እንደ “እግዚአብሔር ልጅ” በመሾሙ ከመላእክት ይልቃል (1፥5፡ 13)፤ “የሰው ልጅ” በመሆኑም (2፥17) እንደ መልከጸዴቅ ሥርዐትም “ሊቀ ካህናት” ሆኖ ስለተሾመ ከሌዊ ክህነት ይልቃል (7፥26–28)። ግን እንዴት? ለሁለቱም የሰጠን ማስረጃ “ስለ ተቀመጠ” የሚል ነው። በ1፥13 ላይ “ከመላእክት፣ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ያለው ለማን ነው?” ሲል በ8፥1 ላይ እንዲሁ፣ “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን” ይላል። ይህ ካህን ተቀምጧል፤ ስለዚህም ኢየሱስ ይልቃል! ሆኖም ግን ይህ “የተቀመጠው” መልከጸዴቃዊ ካህን ወደ ፊት ዳግም ስለሚገለጥ፣ መገለጡንም (prospectively) እያሰብን በእምነት እንድንጸና (9፥28)፣ በፍርሀት እንድናመልከው (12፥28) ግድ ይለናል፤ “እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፣ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ … ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (4፥14፡ 16)። ኢየሱስ ጸጋ ሰጪ በሆነ ዙፋን ላይ፣ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጧል። ሃሌ ሉያ!
ይህ ብቻ አይደለም። መልከጸዴቃዊ ካህንነቱ እና ንጉሥናው የተለያዩ፣ አሊያም በተለያዩ ዘመናት የተደረጉ ሹመቶች ሳይሆኑ፣ ኢየሱስ ወደ አባቱ ዐርጎ በመቀመጡ የተቀዳጀው ጣምራ ሹመቶቹ ናቸው። ኢየሱስ እንደ “እግዚአብሔር ልጅ” (1፥1-14) ወይም እንደ “ሰው ልጅ” (2፥5-18) ወይም እንደ “ታላቅ ሊቀ ካህናት” (5፥1-10፤ 7፥1-8፡ 6) ሲሾም፣ ሹመቱን ልዩ ያደረገው በትውልድ ሐረግ ተለይተው የነበሩት ሁለት ሹመቶች (“ልጅነትንግሥና” እና “ክህነት”) በጣምራነት ደርቦ በአንድ ጊዜ በሰማያት በግርማው ቀኝ መቀመጡ ነው። ይህ ሹመት ማንም ያልደረሰበት የሹመት ጫፍ ነው።
ሆኖም ግን ኢየሱስ ልጅ እንደ ተባለ፣ ያህዌ ለዳዊትና ለልጆቹም ኪዳን ሲገባ “አንተ ልጄ ነህ (1፥5፤ መዝ 2፥7)” ብሎ ጠርቷቸው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ “ልጅ” ተብሎ መሾሙ በራሱ ልዩ አልነበረም። በተጨማሪም፣ ዳዊት “የበኩር ልጅ” ተብሎ እንደ ነበር (መዝ 89)፣ ኢየሱስም ሁሉን ወራሽ በኩር ተብሏል (1፥3፡ 6)። ኢየሱስ ሊቀ ካህናት ተብሎ እንደ ተሾመም፣ አሮንም እንዲሁ በእግዚአብሔር ተሹሞ ነበር (5፥1–5)። ሆኖም ግን በመዝ 110፥1 ላይ ዳዊት የልጅ ልጁን “ጌታዬ” ብሎ በመጥራት (ማቴ 22፥43-44) ተራ ልጁ እንዳልሆነ ያመለክታል። እንዲሁም ያህዌ ይህንን ልጅ “በቀኜ ተቀመጥ” በማለቱ በመለኮት መደብ ይመድበዋል (መዝ 110፥1)። ደግሞም ወረድ ብሎ፣ በመዝ 110፥4-5 ላይ፣ “እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም ‘አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ’ ” በማለት በነገድ የተለያዩትን ሹመቶች ከይሁዳ ቤት የሆነውን ከሌዊም ነገድ ያልሆነውን መሲህልጅ (7፥13–14) በተለየ ሥርዐት “ካህን” ነህ ይለዋል (መዝ 110፥4)።
ጴጥሮስ በበዓለ አምሳ ቀን ሲሰብክ፣ “ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም መቃብሩ እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ እንደሆነ…” በማለት በድፍረት ይናገራል። ዳዊት ሞቷል፤ በስብሷል፤ አጥንቱም ደርቋል። ሲቀጥልም ይህ በመዝ 110፥1 ላይ የምናየው ከፍታ ግን፣ ዳዊት አንቃሮ የተመለከተው ከፍታ ብቻ እንደ ነበር፣ “ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም” ሲል ጴጥሮስ ያብራራል። በዐጭሩ ይህ ተስፋ ከዚህ ቀደም ፍጻሜ አላገኘም። ምክንያቱም ማንም ወደ ሰማይ ዐርጎ በግርማው ቀኝ የተቀመጠ ስላልነበረ። “ነገር ግን እርሱ፣ ጌታ ጌታዬን፣ ‘ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ [እንዳለው]…እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በርግጥ ይወቅ (የሐሥ 2፥34-35)” ይላል። ጴጥሮስ የክርስቶስን መክበር እና የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ከመዝ 110፥1 ጋር በማገናኘት፣ ክርስቶስ መክበሩ (ዕርገቱና መቀመጡ) ለተስፋው መንፈስ ቅዱስ መሰጠት ምክንያት ሆኗል፤ “በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው (2፥33)”።
የዕብራውያን ሰባኪ ከጴጥሮስ ስብከት ለየት የሚያደርገው፣ ሰባኪው አንድ ደረጃ ከፍ በማለት ኢየሱስ በግርማው ቀኝ “ጌታና ክርስቶስ” ሆኖ መሾሙ ብቻ ሳይሆን፣ “መልከጸዴቃዊ ካህንና ጌታ” ሆኖ መሾሙን ማጉላቱ ነው (ይህም መዝ 110፥1 እና ቁጥር 4ን በአንድ ላይ ከነዐውዱ ማተቱ) ነው። ዳዊት ያንቃረረውን ሹመት የዳዊት የልጅ ልጅ ኢየሱስ “ሁሉን ወራሽ ሆኖ ተሹሞ” እናየዋለን። ስለዚህ ኢየሱስ “መልከጸዲቃዊ ካህን ወ ንጉሥ” ነው። “ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሓላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል” ይላል (7፥28)። ተመለከታችሁ? የቀደመው ሕግ (በም.8 ላይ ተተክቷል የሚለን ሥርዐት) ደካማ “ሰዎችን” ካህናት ያደርጋል። ይህ አዲስ ሥርዐት ግን “ፍጹም የሆነውን ልጅ” ካህን አድርጎ ሾሟል። በደማቅ ቀለም የሚያሠምረው “ልጅ ካህን” የሚለውን ጥምረት ነው። ማንም ልጅ እና ካህን ሆኖ በግርማው ቀኝ የተቀመጠ አልነበረም፤ የለም፤ አይኖርምም። ስለዚህ ኢየሱስ ይልቃል! ወደ ኋላ አትመለሱ። ኢየሱስን በምንም አትለውጡ ይለናል።
ለማጠቃለል፣ ሰባኪያችን ተስፈንጥሮ ወደ ፊት “ጠላቶቹ ሁሉ የእግሩ መቀመጫ” ወደሚሆንበት ቀን (ወደ ዳግም ምጽዓቱ) ሲያሳየን (1፥13፤ 10፥13፤ 9፥28)፣ የኋሊትም ተመልሶ በሥጋው ወራት ስለ ተቀበለው መከራ ሲነግረን (5፥7-8)፣ እንዲሁም የቅድመ ትሥጉት ማንነቱን ሲገልጽልን (1፥3)፣ ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተመላለሰ ስለ ክርስቶስ ማንነት እና ሥራ ሲመሰክርልን፣ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ክርስቶስ ጌታና ካህን ሆኖ በተሾመበት ልዕልና እና እውነታ ላይ ተመርኩዞ ነው። በመልእክቱ ሁሉ፣ ይህንን ስፍራ አይለቅቅም።
ስለዚህም ለዕብራውያን መልእክት ሰባኪ፣ ክርስቶስ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ “ወደ ግርማው ቀኝ ለመቀመጥ” እግረ መንገዱን ያደረገው ነው ብንል ሐሳቡን የሚሰበስብልን ይሆናል። በተለይ ይህ “የመንገድ ላይ” ጉዳይ ማርቆስ ልዩ ትረካዊ ገጽታ ይሰጠዋል። ኢየሱስ ያደረጋቸው ታምራትና ስብከቶች፣ በመስቀል መንገዱ ላይ ሆኖ የፈጸማቸው ናቸው። ሲጀምርም፣ “የጌታና መንገድ ጥረጉ” ብሎ ወንጌሉን ከፍቶታልና። በመጀመሪያ፣ ወደ ዙፋኑ ለመቀመጥ ሲጓዝ በመንገድ ላይ ኀጢአታችንን አነጻ፣ “ኀጢአታችንን ካነጻ በኋላ በግርማው ቀኝ ‘ተቀመጠ’ “ (1፥3)፣ በውጤቱም “የወረሰው ስም ከመላእክት እንደሚበልጥ፣ እርሱም ከመላእክት ይበልጣል” ይላል (1፥4)። ሲቀጥልም፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ራሱን እንደ መሥዋዕት አቅርቦ “ተቀመጠ” (10፥12)፤ ስለዚህ “የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጓቸዋል” ይላል (10፥14)። ሲጨርስም፣ ኢየሱስ በፊቱ ያለውን ክብር (መቀመጡን) እያሰበ፣ ነውርን ንቆ “በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ” ተቀመጠ (12፥2)።
በመሆኑም፣ “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኀጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ” (12፥3) ብሎ ይገስጸናል። “በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፣ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ” ተዋርዶ ነበር። አሁን ግን “ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን” (2፥9)። ስለዚህም ብዙ ልጆችን ወደ ክብር አመጣ (2፥10)፤ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞቱ ሻረ (2፥14-15)፤ በሥጋና በደም ከሰው ጋር የተካፈለ ሁሉ ፍጹም ሰው እንደ ሆነ፣ እርሱም ሰው ሆኖ መከራን ተቀበለ። ሰው ሆኖም መከራን ሲቀበል ኀጢአትን ባለማድረጉም፣ “የሕዝብን ኀጢአት ለማስተስረይ፣ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን” የተገባው ሆነ።
ብዙ ካህናት ነበሩ፤ ሞት የከለከላቸው፤ ኀጢአት ያደከማቸው። እንዲሁም፣ ብዙ የዳዊት ልጆች ነበሩ፤ ዒላማቸውን የሳቱ። ከዚህ የተነሣ በ586 ቅ.ዓ. ላይ ያህዌ የዳዊትን ቤት አሳልፎ ሰጠ (ሕዝ 1፥3 ዮአኪን በተማረከ በ5ኛ ዓመት) መቅደሱም ፈረሰ፤ ክህነቱም በመዓቱ ጽዋ ተንገዳገደ። እግዚአብሔርም ለዳዊት የገባውን ኪዳን ያፈረሰ እስኪመስል ዙፋኑን ከሰው አጸዳ (መዝ 89፥38–40)። ከዚያ ቀን ጀምሮ “የክብሩ ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ” የሆነውን፣ ዓለማትን የፈጠረበትንና ሁሉን የሚመግብበት ልጁን “ወራሽ” (1፥2፤ መዝ 2፥8) አድርጎ በዳዊት ቤት ላይ እስኪሾም ድረስ የዳዊት ዙፋን ባዶ ሆነ። ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ “አንተ ልጄ ነህ፣ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ” ያለው ማንም አልነበረም። ይህን ሲል ግን አሁንም ሰባኪው ዐይኑ ያተኮረው በግርማው ቀኝ ዐርጎ የተቀመጠባት ቀን ላይ ነው። ይህችም “እኔ ዛሬ ወለጄሃለሁ” (1፥5) የምትለው ቀን፣ የዛሬ 2000 ዓመት ልጁ በግርማው ቀኝ ሲቀመጥ ተፈጽማለች። በጴጥሮስ አነጋገር፣ “እናንት የሰቀላችሁትን ኢየሱስን ጌታና ክርስቶስ አደረገው” ይላል። ለዕብራውያን መልእክት ሰባኪ ደግሞ፣ “መልከጸዲቃዊ ካህን ወ ንጉሥ” ሆኖ የተሾመባት ቀን ናት! እሰይ!! “እንግዲህ ለእኛ የሚያስፈልገን ቅዱስ፣ ነቀፋ የሌለበት፣ ንጹሕ፣ ከኀጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ የከበረ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ነው” (7፥26)።
የዕብራውያንን ነገረ ክርስቶስ ለመጨበጥ፣ ይህንን እውነታ አስቀድመን መገንዘብ ግዴታ ይሆናል። ክርስቶስ የላቀ ሆኖ በመልእክታችን ውስጥ እንዲኖር ልባዊ ጸሎቴ ነው። መልእክታችን ‘መልከጸዴቃዊ ካህን እና ንጉሥ’ በሆነው ልጅ ላይ ማዕከል ያድርግ። በቃልና በሥራ የምናደርገው ሁሉ ኢየሱስን ያድምቅ፣ ያጉላ እንጂ አይሸፍነው። “ስለዚህ ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፣ ለሰማነው ነገር አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባናል”፤ “እንዲህ ያለውንም ታላቅ ድነት” ቸል እንዳንል እንጠንቀቅ (2፥1–4)”
ክብር ሁሉ በግርማው ቀኝ ለተሾመው ለኢየሱስ ይሁን! ኢየሱስ ይልቃል!
Share this article:
ለስምንት አመታት የወጣቶች ፓስተር በመሆን ሲያገለግል የቆየው የ42 አመቱ ፓስተር ኑዛዜ አስደንጋጭ ነበር፡፡ መጋቢው በቤተክርስቲያኒቱ አመታዊ ስብሰባ ላይ በጉባኤ ፊት ቆሞ “በእግዚአብሔር፣ በባለቤቴ፣ በልጆቼ፣ በቤተሰቦቼና የክርስቶ አካል በሆነችው ኮሎራዶ የምትገኘው የኢውዛ ባይብል ቸርች ፊት ኃጢአትን አድርጌያለሁ” በማለት ተናገረ፡፡ ላለፉት ስድስት አመታት ከቤተክርሰቲያኒቱ የመባ መሰብሰቢያ እቃ ውስጥና እርሱ ከሚመራው አገልግሎት ከወጣቶች አካውንት ወደ 42,000 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብን በስድስት አመት ጊዜ ውስጥ በመውሰድ ለራሱ ጥቅም ያውል አንደነበርና ይህንን ወንጀሉን ከሚስቱም ሰውሮ ያደርግ አንደነበር በመግለጽ እራሱን በቤተክርሰቲያኒቱ መሪዎች አና በአገሪቱ ህግ ተጠያቂ ለማድርግ አንደወሰነ ተናገረ፡፡ በዚህም ምክንያት በማጭበርበርና በስርቆት ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡
We do not need to grasp all that God is doing. In the end, God will show that his ways, so high above our own, were perfect at every turn.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment