[the_ad_group id=”107″]

እምነታዊ ስሌት

ጓደኛዬ ነው፤ “ወደኛ ቸርቸ ካልመጣህ” ብሎ ሁሌ ይነዘንዘኛል መሄድ ባልፈልግም “ስለንዝነዛው” ብዬ አንድ ዕለት ለመታደም ከስምምነት ላይ ደረስን። ከዚያ በፊት ግን ‘ለምን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባለህ ጊዜ ደስ አላለህም?’ ትሉኝ ይሆናል፤ ጥሩ ጥያቄ ነው። ከዚህ ጓደኛዬ ጋር በደባልነት አብረን መኖር ከጀመርን ረጅም ጊዜ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ በኋላ፣ ማለትም “ጠርማሽ ትውልድ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን” ወደ ተሰኘ ጉባኤ መሄዱን ማዘውተር ከጀመረ ወዲህ ነገረ ዓለሙ ተቀይሯል። እንደ እርሱ አባባል “የእምነት እና የኀይል ሰው” ሆኗል።

እናም እላችሁኋለሁ፣ አሁን ባለፈው ጊዜ በጠዋት ተነሥቶ ከእራታችን ሴቭ ያደረግናትን ትንሽ ሻገት ያለች እንጀራ ለቁርስ ይፈረፍራትና “አንተ ጎበዝ፤ ተነስ!” ይለኛል። እንደ እውነቱ ከሆነ እኔ ድብን ያልኩ እንቀልፋምና ሰነፍ ነኝ፤ እሱ ግን “አዎንታዊ ቃለት አሉታዊ ነገሮችን ይለውጣሉ” ብሎ ያምናል፤ በሆነልኝ! ከዚያ “ሆጵ ሆጵ… ተነሥ፤ ጀግና ልጅ እጅ የሚያስቆረጥም ጥብስ ለቁርስ ደርሷል” ይለኛል።

ከዚያ ማዕዱጋ ለዘመቻ ስንቀርብ፣ “ኦ… እስቲ ለጥብሱ አመስግን” አለኝ። ይህን የሚለው እምነቴን ቼክ ሊያደርግ እንደ ሆነ ይገባኛል። መቼም ትናንት ከመንሱር በዱቤ ሞዴል ስድስት ፈርሜ ያመጣኋትን እንጀራ ዐይኔ እያዬ ‘አንቺ ክሽን ያልሽ ጥብስ’ እያልኩ አላቆለጳጵሳትም ብዬና ለሻገተች እንጀራ ቢሆንም የሚጠራው የታልቁ አባታችን ስም ነውና መዋሸት ስላልፈለኩኝ “ጌታ ሆይ ይህን እንጀራ ስለሰጠኸን አመሰግናለሁ፤ ለጤንነታችን ይስማማ፤ በኢየሱስ ስም አሜ…” አላስጨረሰኝም፤ የሞት ፍርድ እንደፈረዱ ዳኛ ጠረጴዛውን በኀይል ነረተው፤ ቀጥሎ ዐይኑን አጉረጠረጠና ግማሹን ወደ ውጭ አወጣው፤ አንዳንዴ እንዲህ ሲያፈጥብኝ፣ ‘ዐይኑን ካልፈለገው ለምን ለዐይን ባንክ አይሰጠውም?’ እላለሁ። ለምን እንደ ጮኸብኝ ነገሩ ቢገባኝም ተቅለስልሼ “ምንድነው?” አልኩት። አሁንም በቁጣ “Is any ፍርፍር here?” አለኝ እንዳፈጠጠብኝ። በነገራችን ላይ ሲናደድም ሆነ ሲደሰት እንግሊዘኛ ይቀናዋል። እናም ምን ልመልስለት? “yes” ልበለው ጥብሱን ትቶ እኔን ሊበላኝ ነው፤ ‘አይደለም’ ልበለው? ኋላ ይለምደውና ይህቺን ፍርፍር እንኳ ያላገኘን ቀን በባዶ ሆዴ ስንከላወስ “ዛሬ የበላነው ቅቅል እንዴት አባቱ ይጣፍጣል” እያለኝ በቁሜ ሊያሳብደኝ ነው። እናም ለጊዜው የምታገለግል አንድ ዘዴ ዘየድኩና እንዲህ አልኩት፣ “ይኸውልህ ጠርማሹ” (ስሳለቅበት ያወጣሁለት ስም ቢሆንም እሱ ግን ይወደዋል) እኔ ገና በማየት እንጂ በእምነት መመላለስ አልጀመርኩም፤ ስለዚህ አንተ ወደ ደረስክበት የእምነት ደረጃ መድረስ እችል እንደ ሆነ ጸልይልኝ” አልኩት። መቼም የእምነት ሰው ነውና ችግሬን ተረድቶ “any way ነገ አብረን ወደ ቸርች እንሄዳለን። የእግዚአብሔር ሰው ያስተምራል” ሲለኝ ተስማማሁ (ወድጄ እንዳይመስላችሁ)።

ምን ይህ ብቻ አንዳንድ ሁኔታው ጭራሽ ግራ ያጋባችኋል፤ ለምሳሌ “መዋጀት” እያለ የሚጠራት ቀሽት የሆነች የምኞት ሳጥን አለችው። አሁን ባለፈው አንዲት ቆንጆ ወጣት ሴት አዲስ ሞዴል መኪና ስትነዳ አይቶ በቆንጆዋም በመኪናቀም ተማርኮ ትንሽ ወሰድ እንዳደረገው ማወቄ ሲገባው፣ “ይህቺን መኪናና በውስጧ ያሉትን በእመነት ዋጀሁ” ብሎኝ አረፈው።አሁን እንግዲህ ለምን ወደ እግዚአብሔር ቤት ሳይሆን ወደ “ጠርማሾቹ ጉባኤ” መሄድ እንዳልፈኩኝ የተግባባን መሰለኝ።

ያው መቼም የእምነትን ሰው ማስቀየም መልካም አይደለምና ብዬ ሁኔታውን ለመመልከት “ከጠርማሾቹ” ጉባኤ ተገኘሁ። ፕሮግራም መሪው አማርኛ እየቀላቀለ ያወራል (እንግሊዘኛ እየቀላቀለ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ)፤ ምናልባትም ይህቺን “ቤተ ከርስቲያን” “ዓለም አቀፍ” ያስባላት “የመድረክ ቋንቋዋ” እንግሊዘኛ መሆኑ ይሆን እንዴ? ብዬ አሰብኩ። መሪው “Just, must, faith, death…” እያለ እያለ ቆየና፣ ለአዝማሪው ይቅርታ ለአዘማሪው አስረከበ። ዘማሪው በተራው ስለ ተራ የሚያወሩ ብዙ “ተረኛ ነኝ፣ ባለ ተራ ነኝ፣ ተራው የእኔ ነው፤ ያንተ ነው፤ ያንቺ ነው…” የተሰኙ ቢከመሩ ተራራ የሚያህሉ ተራ መዝሙሮችን ተረተረና ለቀጣይ ዋና ተረት አውሪ ማይክሮፎኑን አወረሰው።

ቀጣዩ “ማይክ ወራሽ” “የቤተ ክርስቲያኒቱ መሥራች (ከተመሠረተው መሠረት ሌላ ይሆን?)፣ ባለ ራእይ፣ ሐዋርያ፣ ዋና መጋቢ፣ ነቢይና ሁለ ገቡ የእግዚአብሔር ሰው እንቶኔ” ነው። በነገራችን ላይ የዚህን ሰው የማዕረግ ስሞች ርዝመት ስመለከት “ብፁህ ወቅዱስ….” የሚለው ባለ አንድ አንቀጽ ዝርዝር ማዕረግ ትዝ ይለኝና “የት አባቱ! ይሁን፤ ማን ከማን ያንሳል፤ ይፍካከሩ” እላለሁ። ከዚያ “የቤተ ክርስቲያኒቱ መሥራች ባለ ራእይ” ጥቂት ጎርደድ ጎርደድ ካለ በኋላ እሱም እንደ “ደቀ መዛሙርቱ” ጉራማይሌ ዲስኩሩን “ደስኩሮ” ሲያበቃ ቀጣዩ መርሓ ግብር መስጠት እንደ ሆነ የተረዳሁት በመኻል፣ “give and take ሁሉንም ዐይነት prosperity ማግኛ የማይሻር principle ነው ሲል ነበር። ቀጥሎም አንዳንዶቻችን እስከ አሁን ድረስ ያልተባረክነውና ኑሯችን የቆረቆዘው ስላልሰጠን ብቻ ሳይሆን “ስግብግብና ቆንቋና” ስለሆንን ጭምር እንደ ሆነ “በተስጠው ሐዋርያዊ ሥልጣን” አስገነዘበን። ከዚያም፣ “እኛ ‘ስለ ማርያም’ እያልን የምንለምን የመንገድ ዳር ለማኞች አይደለንምና ለማኪያቶ መጠጫ የማትሆን ፍራንክ እየሰጣችሁ ሰጠን አትበሉ…” አለ። ‘ለምን እንዲህ ትላለህ?’ የሚለው የለም፤ በቃ አለ። ታክሲ ቢሆን ኖሮ ‘ወራጅ አለ’ ብዬ ያለ ፌርማታዬ እወርድ ነበር። ምክንያቱም መባ ለመስጠት የያዝኳት ሳንቲም ስመለስ ለአንበሳ አውቶብስ ብዬ ያስቀመጥኳት “ትዳሬ” ስትሆን፣ በእግሬ ፈርጄ ልስጥ ዐስቤ ነበር። ብቻ ምን አለፋኝ፣ “አትስጥ” ስለተባልኩኝ እያፈርኩ እጄን ወደ ኪሴ መለስኩ። በዚያ ላይ ሐዋርያው ማኪያቶ የት እንደሚጠጣ ስለማውቅ በጣም ተሸማቀኩኝ፤ ምክንያቱም እሳቸው እንትን ሆቴል ገብተው ማኪያቶ የሚጠጡበት ሒሳብና እኔ ላለሁባት አጥቢያ ከገቢዬ ከማወጣው ዐሥራት ጋር ሲነጻጸር የሳቸው ይበላጣልና ነው ነገሩ። ከዚያ ብዙ ጥያቄዎች በአእምሮዬ ተመላለሱብኝ። እኔ ሳላውቅ ዝቅተኛ የመባ ስጦታ ተመን ተወስኖ ይሆን ወይስ ለግዥ አቅም እንዳነሰኝ ሁሉ ለአቅመ መስጠትም አልደረስኩም ይሆን? አቤት ይሄኔ እንደ እኔ ለመስጠት ባለመታደሉ ያፈረና እጁን ወደ ኪሱ የመለሰ ስንት ወገን ይኖር ይሆን? ኪሱ ይቁጠረው።

አባ ጠርማሽ ግን አጠገቤ ሌላ ተኣምር መሥራት ጀመረ። የመባ መጣያ ዕቃው ሲመጣ ከኪሱ ብዕር አወጥቶ በቀኝ እጁ መዳፍ ላይ አንድ ቁጥርን ጻፈና ከኋላው ከዐሥር በላይ ዜሮዎችን ደረድሮ ሲያበቃ፣ ወደ መባ ዕቃው ባዶ እጁን ከነቁጥሩ ጨብጦ ከተተና በደስታ መለሰው። ለምን እንደዚያ እንዳደረገ አልጠየኩትም፤ ምክንያቱም “የእምነት ሰው በእምነት” እየሰጠ ነውና። “በጠርማሾቹ ጉባኤ” ክኅደትና እብደት ቀንድ አብቅለው ታዩኝ። “ሐዋርያው” ሲናፈቅ የነበረውን ትምህርት ሲጀምር እኔ ትእግሰቴ አለቀና ተነሣሁ። የዕለቱን ትምህርት ርእስ ተናገረ፡- “የስኬት ደረጃዎችን መውጣት” የሚል ነበር። እሱ ይህን ሲናገር እኔ የአዳራሹን ደረጃ እየወረድኩ ነበር “ከስኬት ደረጃዎች” እየወረድኩ ይሆን?

መስቀሉ

“መስቀል የሰውን ስቃይ እግዚአብሔር አምላክ የተካፈለበት፣ የኢዮብ ጥያቄ “አንተ የሥጋ ዐይን አለህን?” የሚለው ፍንትው ያለ ምላሽ ያገኘበት፤ ስቃይ ለእግዚአብሔር ባዕድ እንዳልሆነ የተመሠከረበት፣. . . ነው።” በሰሎሞን ከበደ

ተጨማሪ ያንብቡ

እንዴት እንሙት? እንዴት እንኑር?

ጌታችን ስለ ሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ በምናስብበት በሰሙነ ሕማማት፣ ንጉሤ ቡልቻ “እንዴት እንሙት?” የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ። ምላሹ በክርስቶስ ሞት ውስጥ የቀረልን ትልቅ ትምህርት ሆኖ አለ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.