[the_ad_group id=”107″]

እምነት፡- ስጦታ ወይስ ችሎታ?

ብናስተውለውም ባናስተውለም እያንዳንዳችን ለየዕለቱ ኑሯችን እምነት ያስፈልገናል፡፡ የዚህን የእምነት ዐይነት በምሳሌ ለማስረዳታ ያኽል፣ የምንቀመጥባቸው ወንበሮች ክብደታችንን መሸከም መቻላቸውን አምነን መቀመጣችን ከሞላ ጎደል ማሳያ ነው፡፡ የዚህ እምነት መሠረቱ ወይም ድጋፉ የቀድሞ ልምምዳችን ሊሆን ይችላል፡፡ ለተለምዷዊ ሕይወት የሚሆነው እምነት መገኛው ልምምዳችን ቢሆንም፣ የማመን ዐቅም ግን በውስጣችን ሳይኖር አይቀርም፡፡ እንግዲህ ይህ ዐይነቱ እምነት ሰዎችን በፅኑ ባርነት ከቀፈደዳቸው ኀጢአት ለማላቀቅ ከሚያስችለው እምነት ጋር በተወሰነ ደረጃ ሊመሳሰል ይችል ይሆናል፤ በሌላ አካል ላይ መደገፍን ታሳቢ ያደርጋልና፡፡ የሰው ልጅ የኀጢአት ውድቀት ወስጥ ለመግባቱ ዋነኛውን ሚና የተጫወተው አለማመን ሲሆን፣ ከዚህ በሽታ ከሚወጣባቸው መንገዶች መካከል ደግሞ ማመን ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ስለዚህ ማመን በመቻልና ባለመቻል መካከል ልዩነት የመፍጠሩ ጉዳይ አይቀሬ ይሆናል፡፡ እንግዲያውስ፣ የሰው ልጅ ባለማመን ያጣውን ሕይወት መመለስ ይቻለው ዘንድ በውስጡ የታጨቀ እምቅ ኀይል ይኖረው ይሆን? ወይስ ሌላ ማመን የሚያስችል ኀይል ከውጫዊ አካል ይታደለው ይሆን? ወይስ ለማመን ምንም ዐይነት ተስፋ የለውም?

አስቀድምን ያየነው ተፈጥሮዊ እምነትና ለኀጢአት በመፍትሔነት የሚያስፈልገው እምነት በተወሰነ ደረጃ ሊመሳሰሉ እንደሚችሉ ከላይ ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ ከአንድነታቸው ይልቅ ልዩነታቸው ይበልጥ ሊሠመርበት የተገባ ነው፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰዎች የማመን ችሎታ አላቸው ተብሎ የመታመኑ እውነታ በብዙዎች ዘንድ ማለት እስከሚቻል ድረስ፣ ለመዳንም ተመሳሳይ ችሎታ በሰዎች ዘንድ ይገኛል እንዲሉ ሆኖአልና፡፡ በቅድሚያ የዚህን ልዩ እምነት አስፈልጎት መረዳት ከተፈጥሯዊ እምነት ጋር ያለውን ልዩነት ለማስረዳት ይረዳል፡፡

ከክርስቶስ ውጪ ያሉ ሁሉ በኀጢአት ፍጹም ባርነት ውስጥ ናቸው፡፡ ይህ ሲባል ግን ግብረ ገባዊ መልካምነት በየትኛውም ደረጃ አይታይባቸውም ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን መተግበር፣ መነሻ ምክንያቱ መልካም ቢሆንም ባይሆንም ከማኅበረ ሰቡ የግብረ ገብ ብሎም የሥነ ምግባር መለኪያ አንጻር ቅቡል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ እንግዲህ በሥነ ምግባር ጉዳዮች ሥር መታየት የሚኖርበት የሙግት ርእስ ይሆናል፡፡ የኀጢአትን ፍጹም ገዢነት በተመለከተ ሐሳቡ በዋናነት የያዘው ትርጉም “በኀጢአት ባርነት ሥር ያለ ማንኛውም ሰው መንፈሳዊ መልካምነት/በጎነት የለውም” የሚል ይሆናል፡፡ የዚህ መንፈሳዊ በጎነት መገለጫዎች ብዙ ቢሆንም ለአብነት ያኽል ያለ እግዚአብሔር ልዩ ዕርዳታ ሰዎች እርሱን መፈለግ አለመቻላቸው እዚህ ሊጠቀስ የሚችል ነው፤ ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ … እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም” (ሮሜ 3÷11) ተብሎ እንደ ተጻፈው፡፡ እግዚአብሔርን መፈለግ በሌለበት ደግሞ ለእርሱ መገዛትና መታዘዝ የማይታሰብ ነው፡፡ የዚህ ዝንባሌ መሠረታዊ መንሥኤ አለማመን ለመሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 1÷5 በእርሱም [በኢየሱስ] ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን” በማለት ግልጽ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ በኢየሱስ ትምህርቶች ውስጥ እምነት በመመሪያነት ቀርቦ እናገኛለን፡፡ በማርቆስ ወንጌል 11÷22 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ʻበእግዚአብሔር እመኑʼ” ይላል፡፡ ይህ “እመኑ” የሚለው ቃል በግሪኩ ያየነው እንደ ሆነ “እምነት ይኑራችሁ” ወይም “እምነት አላችሁ” ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያውን አማራጭ ከወሰድን ከበላይ ባለ ሥልጣን የሚተላለፍ መመሪያን ይመስላል፤ በብዙዎች ዘንድም የተያዘው ትርጉም ይኸው ነው፡፡ ይህን ለማጠናከር በአንደኛ ዮሐንስ መልእክት 3÷23 ላይ፣ “ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ” ተብሎ እምነት ሲታዘዝ እናያለን፡፡

አስቀድመን ከመጽሐፍ ቅዱስ ከራሱ በኀጢአት ባርነት ሥር ያለ ሁሉ ማመን የሚችልበት አቅም የለውም ካልን የመመሪያው ተቀባይ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው የሚል ጥያቄ ያስነሣል፡፡ ምናልባት ሰዎች ከመሰሎቻቸው ሊያደርጉ የማይችሉትን ድርጊት ሊጠብቁ ይችሉ ይሆናል፡፡ ይህንንም አስገራሚና ድንቅ ስሕተት አድርገን ላንቆጥረው እንችላለን፡፡ ምክንያቱም የትእዛዙ ባለቤቶች የተቀባዩን የመፈጸም አቅም በተመለከተ የእውቀት መዛባት አለባቸውና፡፡ ይህን ማስተባበያ ማመን የማይችሉ ኀጢአተኞች “እመኑ” የሚል መመሪያ ለሰጠ ፈጣሪ ማዛመድ አይቻልም፤ ሁሉን አዋቂ ነውና፡፡ ስለዚህ መመሪያው ፍጻሜውን ማግኘት ካልቻለ ፋይዳው እምን ላይ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ይግባ፡፡

እጅግ ግልጽ በሆነ መልኩ የሚያድን እምነት፣ ማለትም በክርስቶስ ማመን የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኤፊ. 2፥8 “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተፈለገው “የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ” የሚለው ሐረግ ሲሆን፣ ʻየሚወክለው ጸጋን ወይስ እምነትን?ʼ የሚል ጥያቄ እናንሣ፡፡ ጸጋን ይወክላል የምንል ከሆነ የሚገጥመን ችግር አላስፈላጊና ትርጉም የማይሰጥ ድግግሞሽ ይሆናል፡፡ ጸጋ በትርጉም ደረጃ “በነጻ የሚገኝ” ስለሆነ ስጦታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ሐረጉ ጸጋን ይወክላል ማለት “ስጦታው ስጦታ ነው” ብሎ እንደመሞገት ይሆናል፡፡ ስለዚህ የሐረጉ ተጠሪ የጸጋ መቀበያ መንገድ ተደርጎ ለቀረበው ለእምነት መሆን አለበት፤ ስለዚህ ያመኑቱ የእምነት አቅም ኖሯችው ሳይሆን የማመንን ትእዛዝ ከሰጠው ከእግዚአብሔር ስጦታ የተነሣ ነው ማለት ነው፡፡ ኤፊ. 6÷23 ይህንኑ ሲያረጋግጥ እንዲህ ይላል፡- ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን።” በዚህ ጥቅስ የምናየው “ከ” በሚለው ቃል ውስጥ የእምነትን ምንጭ ሲሆን፣ የእንግሊዘኛው ምትክ “from” ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ፊል. 1÷29 “ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም” በማለት እምነት ስጦታ መሆኑ ያጠናክረዋል፡፡

ይህ ውድና የከበረ እምነት (2ጴጥ. 1÷1) የሚገኘው በስጦታነት ከሆነ መመሪያው ለምን አስፈለገ? ምናልባት ለአንዳንዶች በስጦታነት ለሌሎች ደግሞ በውስጣቸው ያለ ችሎታ ይሆናል ብለን እንዳንገምት አስቀድመን ያየናቸው ጥቅሶች ሁሉን ያካተቱ መሆናቸውና በእግዚአብሔር ዘንድ የተደባለቀ አሠራር አለመኖሩ ያፈርስብናል፡፡ ስለዚህ “እመኑ” የሚለው መመሪያ የተሰጠው ለዳኑ ሰዎች እንደ ሆነ አድርገን መረዳት እንችላለን፡፡ ትርጉሙም ʻእምነታችሁ አይቆረጥ፤ ይልቅ ይቀጥል እንጂʼ በሚል መውሰድ ይቻላል፡፡ የማር. 11÷22ቱን መመሪያ ያየን እንደ ሆነ ጴጥሮስ ለጠየቀው ጥያቄ የተሰጠ የኢየሱስ መልስ ሲሆን፣ በጉዞው አብረውት የነበሩትም ደቀ መዛሙርቱ ናቸው፡፡ በ1የሐ. 3÷23ቱ ያለ ምንም ጥርጥር ክፍሉ የሚያወራው፣ በአንደኛ መደብ ድርብ ቅጥር በመሆኑና የጽሑፉ ይዘት ደብዳቤ ስለሆነ ይህም ለአማኞች ስለ ተሰጠ፣ ስለ ቅዱሳን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቢሆንም ግን “እናምን ዘንድ” የሚለው ሐሳብ ቀድሞ የተፈጸመን ድርጊት ያመለክታልና ʻይህ መመሪያ በተሰጠበት ጊዜ ተቀባዮቹ አማኞች ነበሩን?ʼ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

የዚህን መመሪያ ታሪካዊ ዘገባውን በተመለከተ የዮሐንስ ወንጌል አስፈላጊ ይሆናል፤ ምክንያቱም ስለ ትእዛዝ የብሉይ ኪዳኑ ሕግ አላፊ በሆነ መልኩ አስቀምጦ፣ የኢየሱስን ትእዛዝ በአዲስ መልኩ ለመግለጽ ሥራ ላይ የዋለው በሐዋርያው ዮሐንስ ጽሑፎች ነውና፡፡ በዮሐንስ ወንጌል 13÷34 “ትእዛዝ” የሚለው ቃል ከ1ኛ ዮሐንሱ ጥቅስ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ተጠቅሶ የሚገኝበት ምንባብ ነው፡፡ ይህ ጥቅስ ደግሞ የሚገኘው ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻ ባሳለፈው የመጨረሻው ጊዜው ነበር፡፡ ይህ መመሪያ በተሰጠበት ጊዜ ውስጥ ሰፊው ማኅበረ ሰብ ይቅርና ከዳተኛው ይሁዳ እንኳን አልነበረም፤ ቁጥር 30 ላይ ወጥቶ መሄዱን ተራኪው ይነግረንና ቀጣዩ ቁጥር የንግግሩ መጀመር የእርሱን ወጥቶ መሄድ የተከተለ እንደ ሆነ ይጨምራል፡፡ የተቀሩት ከዘህ ሐሳብ ጋር የሚስማሙት በዮሐንስ ወንጌል የሚገኙተ ጥቅሶች በሙሉ የሚገኙት በዚሁ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ባሳለፈው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ እንግዲያውስ የዚህ መመሪያ ትርጉም ʻበእምነት ቀጥሉና ዕደጉʼ መሆን አለበት፤ የማበረታቻና የማሳሰቢያ መመሪያ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡

ስለዚህ በቀጣይነት ማንሠሳት የሚኖርብን ጥያቄ፡- ʻለማያምኑቱ ወንጌልን ስንሰብክ ወደ እምነት ጥሪ ማድረግ ይኖርብን ይሆን?ʼ የሚል ይሆናል፡፡ የወንጌልን ስብከት በተመለከተ ስብከቱ እምነትን እንዲያመጣ በእግዚአብሔር የተደነገገ ሲሆን፣ ከሰባኪው አንጻር ግን ʻእመኑʼ የሚል መመሪያ መስጠትን የሚደግፍ ሐሳብ የለም፡፡ ስለዚህ የወንጌል ስብከቱም ቢሆን እምነትን በመመሪያ መልኩ ለማያምኑቱ ማቅረቡን አያስገድድም፡፡

ስለዚህ በኀጢአት እስር ላሉቱ የማመን ችሎታ የሚባል ነገር የላቸውምና ያለ እግዚአብሔር ልዩ ዕርዳታ የኢየሱስ ተከታይ መሆን አይችሉም፡፡ ለተለምዷዊው ሕይወት የሚሠራውን ተፈጥሮዊ እምነት ባሕርይውንና ዐላማውን በማዛባት የሚያድነውን እምነት የሰዎች እምቅ ኀይል ውስጥ (potential) እንደሚገኝ አድርጎ ማሰቡ ተገቢ አይሆንም፡፡ እምነት ስጦታ እንጂ ችሎታ አይደለምና፡፡

Gedion Agizew

የጆሮ ያለህ!

ተካልኝ ነጋ (ዶ/ር) በዚህ ጽሑፉ፣ ‘አድማጭ መሆን ለምን ተሳነን? ለምን ተናጋሪ ብቻ ሆንን? በማድመጥ ውስጥ እናገኝ የነበረውን ኁልቁ መሳፍርት በረከትኣ ለምን እናጣለን?’ ሲል አንባቢን ይሞግታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

የእግዚአብሔር ሕዝብ

ዘሪቱ ከበደ በሦስት ተከታታትይ ክፍል በምታቀርበው ጽሑፍ፣ “ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ” ምንነት እና መገለጫ ባሕርዩ ታስነብባለች፦ “ይህ ልዩ ሕዝብ በምድራዊ ልዩነቶቹ እንደገና ሊያዝና ሊከፋፈል የሚገባው ሕዝብም አይደለም። በክርስቶስ ከዓለም በተለየው ሕዝብ መካከል እንደ እግዚአብሔር ጥበብና መልካም ፈቃድ የሆነ ‘ልየታ’ እንጂ ልዩነት የለም።” ተጨማሪ ያንብቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ

ድንቅ እና ታምራት ለምን?

አማረ ታቦር በዚህ ጽሑፉ፣ በብሉይ እና በአዲስ ኪዳናት የተደረጉት ድንቆችና ታምራት በዘመን የሚከፈሉ መሆናቸውን በማመልከት፣ ለምን ዐላማ ይደረጉ እንደ ነበረ ያወሳል። በዚህ የመጀመሪያ ክፍል፣ በብሉይ ኪዳን የተደረጉትን ታምራትና ድንቆች በዘመን ሰፍሮ ያስቃኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.