
5 Good Reasons a Church Should Close
It’s no secret thousands of churches are closing every year. While that’s heartbreaking, should it ever happen? Here are 5 reasons a church should close.
[the_ad_group id=”107″]
የክርስትና እምነት ገና ከጅማሬው እውነተኛውን የክርስትናን አስተምህሮ በሐሰት ለመበረዝ በሚጥሩ የኑፋቄ ትምህርት መምህራን ከፍተኛ ተግዳሮት ይደርስበት እንደ ነበር ከመጽሐፍ ቅዱስን እንረዳለን፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት መካከል አንድ ሦስተኛውን ስፍራ የሚወስደው ለመናፍቃን ትምህርት የተሰጠ ምላሽ እንደ ሆነ በዘርፉ ምርምር ያደረጉ የሥነ መለኮት ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡ ይህ እውነት ቅዱሳት መጽሐፍት ለኑፋቄ ትምህርቶች ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ስፍራ እንደ ሰጡ ሁሉ፣ እኛም በዘመናችን ኑፋቄያዊ አስተምህሮዎችን ከተቻለ ለማቅናት፣ ካልሆነም ምእመናንን ለመጠበቅ ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጥ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው፡፡ የዚህ መጣጥፍ ተቀዳሚ ዓላማ የክርስትና እምነት በዘመናት መካከል በኢትዮጵያ ውስጥ የተጋረጠበትን ኑፋቄያዊ አስተምህሮቶችንና በክርስትና ላይ ያነጣጠሩ ዋና ዋና ጥቃቶች ምን ምን እንደ ነበሩ በማስታወስ ማንቃት ሲሆን፣ በዋናነት በኢትዮጵያ ያለችው የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ዓመታት የተጋፈጠቻቸውን ዋና ዋና ኑፋቄያትን ዐለፍ ዐለፍ በማለት ማስቃኘት ነው፡፡ ይህም በሚቀጥሉት ዕትሞች ከዚህ በታች የተጠቀሱትንም ሆነ ሌሎች የኑፋቄ አስተምህሮዎችን በማንሣት ለምንሰጠው ትንታኔ እንደ መግቢያ ሆኖ የሚያገለግል ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አማኞች ከጅማሬያቸው አንሥቶ እስከ ዘመናችን ድረስ የተጋፈጧቸውን ዐበይት ኑፋቄያዊ አስተምህሮዎችንና ውጫዊ ተግዳሮቶችን ከመነጋገራችን በፊት “ኑፋቄ” የሚለውን ቃል ፍች እንመልከት፡፡ ከሳቴ ብርሃን ተሰማ እንደሚሰጡት ፍቺ ከሆነ፣ “ኑፋቄ” “ነፈቀ – ከሃይማኖት ወጣ፣ ተጠራጠረ፣ መናፈቅን፣ ከሓዲን ኾነ ነፈቀ፡፡”[1] የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ በዚህ ትርጉም መሠረት “ነፈቀ” ማለት ከትክክለኛው የእምነት መንገድ ወጣ፣ ሳተ ወይም ትክክለኛውን እምነት ካደ፣ ተጠራጠረ ማለት ነው፡፡ የኪዳነ ወልድ ክፍሌም፤ መጽሐፈ ስዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ደግሞ “መናፍቅ (ቃት፣ ቃን) ናፈቂ፣ አናፈቂ፣ የሚጠራጠር፣ የሚያጠራጥር፣ ጠርጣሪ፤ ሃይማኖቱ ሕጹጽ የሆነ፣ ሙሉ እና ፍፁም ትክክል ያይደለ፤ መንፈቁን አምኖ መንፈቁን የሚክድ፡፡”[2] አለቃ ኪዳን ወልድ ክፍሌ በበኩላቸው መናፈቅ ማለት እምነቱ ትክክል ያልሆነ፣ ግማሽ እውነት ግማሽ ሐሰት የሆነ እምነት ማለት ነው የሚለውን ያክላሉ፡፡
በዚህ ትርጓሜ መሠረት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት ዓመታት ከውስጥም ሆነ ከውጪ መናፍቃንን መጋፈጧን እናስተውላለን፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የታዩት ኑፋቄያት ቁጥርን በዚህ አጭር መጣጥፍ ውስጥ መዳሰስ “ውቅያኖስን በጭልፋ…” እንዳይሆን ዐበይት በሆኑ ኑፋቄያት ላይ ማተኮር አስፈልጓል፡፡
የይሖዋ ምስክሮች ሃይማኖት ጠንሳሽና ጀማሪ መጋቢ ቻርልስ ታዝ ራስል የተባሉ በአሜሪካ፣ ፔንስልቬንያ ስቴት ውስጥ ፒትስበርግ እየተባለ በሚጠራ ከተማ ውስጥ በ1852 (እ.ኤ.አ) የተወለዱ ግለሰብ ናቸው፡፡ ራስል ይህንን የእምነት ቡድን ከመጀመራቸው በፊት የፕርስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን አማኝ የነበሩ ሲሆን፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ይሰጥ በነበረው የቅድመ ውሳኔ ትምህርት እና ኀጢአተኞች ለዘላለም ይቀጣሉ በሚለው አስተምህሮ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሡ፡፡ በመቀጠልም፣ ስድት ግለ ሰቦች ያሉበት የጥናት ቡድን በ1870 አከባቢ አደራጁ፡፡ በመቀጠልም ክርስቶስ በሥጋ ዳግም እንደማይመጣ፣ ነገር ግን የእርሱ ዳግም ምፅዐት መንፈሳዊ እንደሚሆን በስፋት ማስተማር ተያያዙ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ከጅማሬው አንሥቶ በኅትመት ውጤቶች (በተለይም በመጽሔት) አማካኝነት አስተምህሮውን ያሰራጭ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ሃይማኖቱ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይታመናል፡፡ በሀገራችንም የዚህ ሃይማኖት ክፍል የሚታተሙ መጽሔቶች መኖራቸውና ለሃይማኖቱም መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው እሙን ነው፡፡
ይህ የኑፋቄ አስተምህሮ በዓለማችን ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል፡፡ በ1965 ዓ.ም. ቁጥራቸው ወደ 1.1 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላ ቁጥራቸው ወደ 2.2 ሚሊዮን ማደጉ ተገልጿል፡፡ ይህም ቁጥር በ1992 በእጥፍ በማደግ ወደ 4.4. ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. በስብከት አገልግሎት ውስጥ ተሳትፎ የሚያደርጉ በአማካይ 7.53 ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እንዳሉት ይፋ ሆኗል፡፡[3]
“የይሖዋ ምስክሮች” በመባል የሚታወቀው የኑፋቄ አስተምህሮ በኢትዮጵያ ውስጥ መታየት የጀመረው በ1935 ዓ.ም. አታዛኮርታዚያን በተባለ አርመናዊ አማካኝነት ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህ ግለ ሰብ እምነቱ የይሖዋ ምስክሮች እምነት ቢሆንም፣ “የመጠበቂያው ግንብ” ተብሎ በሚታወቀው የሃይሞኖት ተቋሙ አማካኝነት የተላከ ሚስዮናዊ አልነበረም፡፡ ይልቁኑም በእምነት ተቋሙ አማካኝነት የተላኩት የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናዊያን ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በ1950 ዓ.ም. ነበር፡፡ በእነዚህም የድርጅቱ ሚስዮናውያን ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ የገባው የይሖዋ ምስክሮች አስተምህሮ ዛሬ ተንሰራፍቶ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ ይታያል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የይሖዋ ምስክሮች የሚሲዮን ትኩረታቸው ያደረጉት የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያናት መሆኑ ነው፡፡
ይህ የስሕተት አስተምህሮ በዋነኝነት የኢየሱስን መለኮትነት የሚክድና ኢየሱስን ፍጡር የሚያደርግ ሲሆን፣ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት ቁጥሩ በማደግ ላይ ይገኛል፡፡[4] ከዚህ በተጨማሪ የእመነቱ ተከታዮች የክርስትና እምነት አእማድ ተደርጎ የሚታመነውን የአሐዱ ሥሉስ አስተምህሮ ምንጩ ከሰይጣን እንደ ሆነ ያስተምራሉ፡፡ እንዲሁም የክርስቶስን ትሥጉትነትና ትንሳዔን አስመልክተው “ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምር የመጣው ፍጹም ሰው ሆኖ ሳይሆን በክብር የተሞላ መንፈስ ሆኖ ነው”፣ ስለሆኖም የክርስቶስ ትንሳዔ በመንፈስ ነው የሚል ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስትምህሮ ፍጹም የራቀ ትምህርት አላቸው፡፡ በዚህ ሳያበቃ ስለ ክርስቶስ ዳግም ምፅዐት፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ ስለ ኀጢአት፣ በክርስቶስ ደም ስለሚገኝ ስርየት፣ ስለ ገሐነም እሳትና ስለ ዘላለም ፍርድ እና የመሳሰሉ በኑፋቄ የተሞሉ ትምህሮቶች አሏቸው፡፡
የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አስተምህሮ በሦስተኛ ምእተ ዓመት በቤተ ክርስቲያን ጉባኤ የተወገዘው የሰብአልዮስ አስተምህሮ ነው፡፡ የሐዋርያት “ቤተ ክርስቲያን” በ1961 ዓ.ም. ከአሜሪካ በድርጅቱ ሚስዮናዊያንና በአንድ ኢትዮጵያዊ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የገባ የኑፋቄ አስተምህሮ ነው፡፡[5] የዚህ ኑፋቄያዊ አስተምህሮ ዋና ስሕተት ስለ ሥላሴ ያለው አመለካከት ሲሆን፣ በዚህ አስተምህሮ መሠረት ʻአምላክ ራሱን በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ መልክ ገልጧል፡፡ እግዚአብሔር አብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተገለጠ አምላክ ሲሆን፣ ይኸው አምላክ ሰው ሆኖ ወደዚህ ምድር መጥቶ ስለ ሰው ልጆች ኀጢአት ሞተ፤ አሁንም ይኸው አምላክ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ በእኛ ውስጥ ያድራልʼ ይላል፡፡ ይህ አስተምህሮ መሠረታዊውን የሥሉስ አሓዱ አስተምህሮ ስለማይቀበል ኑፋቄ ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ የኑፋቄያዊ አስተምህሮ “እግዚአብሔር በቁጥር ፍጹም አንድ ነው፤ ያም አንድ አምላክ ኢየሱስ ነው፤ አብ፣ ወልድ፣ መንፍስ ቅዱስ የሚባሉ ሦስት አካላት የሉም፣ ያለው አንድ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡” የሚል ነው፡፡
ሌላኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት የሆነው የኑፋቄ አስተምህሮ “የእምነት እንቅስቃሴና የብልጽና ወንጌል” አስተምህሮ ተብሎ ይጠራል፡፡ “የብልጽግና ወንጌል” ከክርስትና እውነት ጋር የሚጣረስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳይታወቅ እንደ ክፉ በሽታ በመዛመት ላይ ያለ ኑፋቄ ነው፡፡
የእምነት እንቅስቃሴ ጀማሪ ተደርገው የሚታሰቡት በ1879 ዓ.ም. የተወለዱት የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ዲያቆን የነበሩት ዊሊያም ኬንዮን ናቸው፡፡ የእርሳቸውን ፈለግ በመከተልም እንደ ሜሪ ቤከር፣ ኬነት ሐጌን፣ ኬነት ኮፕላንድ፣ ቻርልስ ዌለር፣ ኦራል ሮበርትስ፣ ጄሪ ሳቪሊን፣ ዴቪድ ቾይዲፖ እና የመሳሰሉትን በዓለማችን ውስጥ ይህንን የኑፋቄ አስተምህሮ አስፋፍተውታል፡፡
የእምነት እንቅስቃሴን ከሌሎች የኑፋቄ አስተምህሮዎች የሚለየው በተለያዩ ቤተ እምነቶች ውስጥ ሳይታወቅ በቀላሉ ዘልቆ የመግባት ባሕርይ ስላለው ነው፡፡ የእምነት እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ስለ ፈውስና ስለ ብልጽግና በሚያስተምረው አስተምህሮ ግን በደንብ ይታወቃል፡፡ በዋናነት ስለ እምነት (በእምነት ምንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል ማቀንቀኑ)፣ ጸሎት (ጸሎት ከእግዚአብሔር ኅብረት የሚናደርግበት እንዲሁም ልመናችንን የሚናቀርብበት ሳይሆን የሚንፍልገውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጠን እርሱን የሚናዝበት ስለ መሆኑ)፣ አዎንታዊ ዐዋጅ (ከአንደበት የሚወጡ ቃላት የሰው ልጆችን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ስለ መሆናቸው)፣ ሰው መንፈስ መሆኑ (ሰው ነፍስና ሥጋ ያለው ሳይሆን በሥጋ ውስጥ የሚያድር መንፈስ ስለ መሆኑ) እንዲሁም የክርስቶስ ዋጆዋዊ ሥራ ላይ የኑፋቄያዊ አስተምህሮ አላቸው፡፡
የብልጽግና ወንጌልም ከእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ አስተምህሮ ምንም እንኳ “የብልጽግና ወንጌል” በሚል መጠሪያ ቢጠራም፣ “የስግብግቦች ወንጌል” የሚለው ገላጭ ስሙ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አስተምህሮው በዋናነት የሚያተኩረው በሰዎች ከኀጢአት እስራት ነጻ መውጣት ላይ ሳይሆን፣ ቁሳዊ ብልጽግናንና አካላዊ ፈውስን በማግኘት ላይ ማተኮሩ ነው፡፡ በዚህ አስተምህሮ መሠረት ʻአማኞች በምድር ላይ ሊታመሙና ደኻ ሊሆኑ አይገባም፤ ሕመምና ድኽነት የእምነት ማጣት ውጤቶች ናቸው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሠራው ሥራ ድኽነትንና ሕመማችንን ከእኛ አስወግዷልʼ ብለው ማመናቸው ነው፡፡ በዓለም ውስጥ ያለው መከራ፣ ችግር፣ ሕመም፣ ሞት፣ ጉስቁልና በኀጢአት በወደቀ ዓለም ውስጥ የመኖራችን ውጤት የመሆኑን ገሃድ እውነት ይክዳሉ፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተጋፈጠችው ያለችው ተግዳሮት ድኅረ ዘመናዊነት ይዞት የመጣውን እግዚአብሔር የለሽነት ነው፡፡ ይህ በእርግጥ ኑፋቄ አይደለም፤ ምክንያቱም በመጀመሪያም የሚያምነው ነገር የለውምና፡፡ ነገር ግን በዘመናችን እንደ አሸን እየፈሉ ባሉ ሥነ ጽሑፎች ውስጥ ድኅረ ዘመናዊነት ሰፍኖ ይታያል፡፡ የዚህ አመለካከት ሰለባ የሆኑ በጣም ብዙ ሰዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
በዘመናችን ለኅትመት በሚበቁ ልብ ወለድ ጽሑፎችና ግጥሞች እንዲሁም በአንዳንድ ድረ ገጾችና የማኅበረ ሰብ ሚዲያዎች ላይ የሚቀርቡ ጽሑፎች አንኳር ጭብጣቸው በእግዚአብሔር ሐልዎት በሚያምኑ ሰዎች ላይ መዘበት እስኪመስል ድረስ በእግዚአብሔርና በመሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮ ላይ የሚሳለቁ ናቸው፡፡
ድኀረ ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም ሲሆን፣ ከዘመናዊነት ቀጥሎ የመጣና አሁን በበርካታ የምርምር እንዲሁም
የሥነ ጽሑፎች ውስጥ የሚንጸባረቅ አመለካከት ነው፡፡ ይህ ንጽረተ ዓለም ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ዐይነተኛ መገለጫው ግን እውነት አንጻራዊ ናት፣ እውነት የግለ ሰቦችና የማኅረ ሰብ ፈጠራ ናት የሚል ነው፡፡ የድኀረ ዘመናዊነት ንጽረተ ዓለም ወደ ሃይማኖቶች ጎራ ሲመጣ ሁሉንም ሃይማኖቶች ትክክለኝነት የሚያውጅና ሃይማኖቶች የማኅበረ ሰብ ፈጠራዎች እንደ ሆነ የሚያቀነቅ ነው፡፡ ይህንን ንጽረተ ዓለም በመከተል አንዳንድ የሀገራችን ጸሓፍትም ʻሃይማኖቶች ሁሉ ልክ ናቸውʼ ወደ ሚል አልያም ʻአምላክ የለምʼ ወደ ሚል ድምዳሜ መድረሳቸው የሚያመላክት ጽሑፎችን መጻፋቸውን መመልከት ጀምረናል፡፡ ይህም የዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት ሆኖ ይታያል፡፡
በዘመናችን የክርስትና እምነት የገጠሙት ተግዳሮቶች ውስጣዊና ውጫዊ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ “ኢ-አማኒያን” ነን በሚሉ ሰዎች የትችት ናዳ ሲጎርፍበት፣ በእግዚአብሔር ሐልዎት የሚያምኑ ሰዎች ደግሞ ከመሠረታዊው የክርስትና አስተምህሮ የራቀና ጥመት የተሞላበት ኑፋቄያዊ አስተምህሮ ተጋርጦበታል፡፡ ታዲያ ʻበዚህ ሁሉ ውስጥ እንደ ክርስቲያን ከእኛ የሚጠበቀው ምንድን ነው?ʼ ብለን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ በመግቢያው ላይ እንደተጠቆመው፣ በቀጣይ ዕትሞች በሀገራችን አሉ የሚባሉ የኑፋቄ ትምህርቶችን በስፋት በመቃኘት በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት አቋማቸውን ለመፈተሸ ጥረት እናደርጋለን፡፡
ልዑል አምላክ በቸር ያሰንብተን!
Charles Taze Russell (1852 – 1916) – Jehovah’s Witnesses
Evangelist E.W. Kenyon (1867-1948) – Founder of Faith movement
Kenneth E. Hagin (1917-2003)
[1] ከሳቴ ብርሃን ተሰማ፤ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 662፡፡
[2] የኪዳነ ወልድ ክፍሌም፤ መጽሐፈ ስዋሰው ወግስ ወመዘገበ ቃላት ሐዲስ፤ ገጾች 645-646፡፡
[3] 2013 Yearbook of Jehovah’s Witnesses. Watchtower Bible and Tract Society. 2011. p. 31.
[4] ተስፋዬ ሮበሌ፣ ዐበይት መናፍቃን (አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን የሥነ-ጽሑፍ አገልግሎት፣ 2001)፣ 83-86
[5] ዝኒ ከማሁ፣ 49
Share this article:
It’s no secret thousands of churches are closing every year. While that’s heartbreaking, should it ever happen? Here are 5 reasons a church should close.
የትንሣኤን በዓል በምናከብርበት በዚህ ሰሞን፣ ስለ ጌታችን ትንሣኤ ምንነትና ፋይዳ ባትሴባ ሰይፉ የሚከተለውን አስነብባለች።
የጳውሎስ መልእክት ወደ ቲቶ: በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ሰዎች የተሰጠ መመሪያ
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment