[the_ad_group id=”107″]

የመብት ትግል እና የበቀል ምኞት ሚናቸውን ይለዩ

እንደ ወቅቱ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ አገሮችን መምራት በዓለም ላይ ካሉ አስቸጋሪ ተግባራት አንደኛውና ዋነኛው ይመስለኛል። የምሰጠው አስተያየት ይህንን በመገንዘብ ነው። እንደምንጊዜውም ሁሉ አስተያየቴ የደጋፊም የተቃዋሚም አይደለም። የአመለካከት ልዩነት ካለን በጨዋ ደንብ አስተያየት በመስጠት እንማማር፤ አብረን ሰው እንሁን!

የሰሞኑ በአብዛኛው በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው አስከፊና አሰቃቂ የሞት፣ የእልቂት፣ የድንጋጤ፣ የመፈናቀል፣ የመዋረድ፣ የመናቅ እና እንደ እንስሳና ከዚያም በታች የመታየት አደጋ ድንገተኛ አይደለም። አሁን ይህ አረመኔአዊ ክስተት የተፈጸመባቸው አካባቢዎች ከሞላ ጎደል ምስራቅ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ምእራብ አርሲ እንዲሁም ሰበታ ሲሆኑ፣ ቀደም ብሎም በተመሳሳይና በሌሎች ቦታዎች ይኸው ድርጊት ሲከሰት ቆይቷል።

እኔ በግሌ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1973 ዓ.ም. በደደር አውራጃ፣ ከሀራዋጫ በታች በሚገኝ መልካ በሎ ወይም ጀርጀርቱ በተባለ ስፍራ ከተመሳሳይ አደጋ የተረፍኩ ነኝ። አብረውኝ በዚያ ገበሬዎችን ሲያስተምሩ የነበሩ ከአዲስ አበባ የካ አውራጃ የሄዱ ሦስቱ ወጣቶች “ኢስላሚክ ኦሮሞ ነጻ አውጪ” በመባል በባሌና በሐረር ይገኙ በነበሩ ኀይላት በጥይት ተገድለው፣ ደረቅ ሳር ተርከፍክፎባቸው ሲቃጠሉ፣ ሬሳቸውንና ቆስለው የተረፉትን ሌሎቹን ጓደኞቻችንን ይዘን ወደ ሐረር ሆስፒታል መጥተናል። የእኔ ትውልድ ያለፈው ተመሳሳይ መከራ ተዘርዝሮ አያልቅም፤ ይቅር። ጕዳዩ በየጊዜው የሚከሰት እና እየተድበሰበሰ የሚያልፍ ግርሻ እንጂ አዲስ በሽታ አይደለም።

እንዲህ ያለው እኩይ ተግባር፣ ‘በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢ ሳይሆን ለምን በእነዚህ አካባቢዎች ላይ በረታ?’ የሚለው ጥያቄ ሁሉም በማስተዋል ሊመለከተው የሚገባ ነው። በስትራቴጂ በተደገፈ፣ የርእዮተ ዓለም አስተምህሮ በተጠመቁና (ኢንዶክትሪኔት) ለተጠያቂነት በሚያስቸግሩ ቡድኖች መሣሪያነት የተፈጸመ ነው። ይሁን እንጂ ለደረሰውና እየደረሰ ላለው ጭፍጨፋ ከ“ሳቢያና ውጤት” አንጻር የፕሮፓጋንዳና የቀጥታ ተሳታፊነት ደረጃ ተጠያቂዎች የሉም ማለት ግን አይደለም፤ አይገባምም።

ይህ ኀይል ያለ ጥይት ከአፍሪካ በታሪክ ቀደምትነትና በሕዝብ ብዛት እጅግ ታላቅ የሆነችውን ኢትዮጵያ ሊያፈርስ በቃጣ፣ ወደ ፊትም ይህንን መፍረስ በሚፈልግ ኀይል የተፈጸመ ነው። ጥናቶች ተደርገው በአጠቃላይ ቅድመ ኢህአዴግ፣ በዘመነ ኢህአዴግ፣ በተለይ ደግሞ አሁን እያሻቀበ የመጣው ይህ ኢትዮጵያን የሚጠላ ኀይል አስተሳሰቡና ቡድኑ በቂና ተገቢ አገራዊ ምላሽ ሳይሰጠው በዚሁ ዐይነት የተድበሰበሰ ምላሽ የሚቀጥል ከሆነ፣ የረጅም ጊዜ ፍላጎቶቹን በዐጭር ጊዜ ሊያሟላ የማይችልበት ምንም ምክንያት አይታይም።

በአንድ አገር ውስጥ ከመንግሥት እኩል ወይም ደግሞ ተፎካካሪ በሆነ ኀይል ወይም ደግሞ በሚበልጥ ኀይል የሚንቀሳቀስ ቡድን፣ በተለይም ኅብረ ብሔራዊ ሳይሆን አንድ ብሔር ተኮር ከሆነ በሌሎች ላይ የሚፈጥረው የሥነ ልቡና ተጽእኖ ስሜቱም ሆነ ከስሜቱ የሚከተሉ ስጋት ወለድ ምላሾች በቀላሉ የሚገመቱ ሊሆኑ አይችሉም። ይህ በእንዲህ እያለ አብዛኛው ሕዝብ የችግሩን ስም ጠርቶ ከመነጋገር ይልቅ በስሜት በመገፋፋት፣ በመበሻሸቅ፣ በማላገጥ፣ በመናናቅ፣ በመሙለጭለጭና በአይመለከተኝም ባይነት ምላሽ ላይ ይገኛል። እነዚህ ዐይነት ምላሾች ለማንኛውም የፖለቲካ ምኅዳር ሰላም መጋቢያን ሳይሆኑ፣ ግጭት ፈጣሪና አባባሽ ናቸው።   

የብሔራዊ አንድነትንና ይህንንም አንድነት የሚያሳዩ እንደ ባንዲራ ያሉ ምልክቶችን አስቀድሞ በስውር በመተናኮል፣ በኋላም በግላጭ በመቃወምና በምትኩም እጅግ ብሔር ተኮር የሆኑ ዋልታ ረገጥ እንቅስቃሴዎችን፣ ፕሮፓጋንዳዎችን፣ እንዲሁም ከማእከላዊ መንግሥት ተፎካካሪ የሆኑ የእዝ ሰንሰለቶችን በግላጭ በማሳየት የከረመ ኀይል በአንዲት ሉዓላዊት አገር ውስጥ የሚገኝ ከሆነ፣ በአንድ የእንቁላል ክርታስ ውስጥ ሁለት የተለያዩ እንስሶች አስኳል አለ ማለት ነው። በሁለቱ አስኳሎች ዲ.ኤን.ኤ. ውስጥ ተመሳሳይነት ያለው ህያው አካል ቢሆን ኖሮ ችግሩ አይከፋም ነበር፤ በገሀዱ ዓለም አሁን እያየን ያለው ግን መሠረታዊ ልዩነት ያላቸው አካላት ናቸው። ይህ በፍጹም ሊፈቀድና በቀላል ሊታይ የሚገባ ጕዳይ አልነበረም፤ አይደለምም።

መንግሥትን ማንኳሰስ፣ መዋቅርን መነቅነቅ፣ በግልጽ ሰርጎ መግባት (ኢንፊልትሬሽን) ሕገ ወጥና ኢ-መደበኛ ሰራዊት እና ሰራዊት መሰል ማደራጀት፣ እያሰለሱ በሽምቅ እንዲሁም በድንገታዊ ውርጅብኝ (ሬይድ) በመንግሥት ጥላና ከለላ ሥር ነን ብለው የሚኖሩ ንጹሐንን፣ ካህናትን፣ ወንጌላውያንን፣ በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፍ፤ ነዋሪዎችን፣ በኪራይ፣ በገበያ፣ በማኅበራዊ መገኛዎቻቸው ከነቤተ ሰቦቻቸው ማሸማቀቅ፣ ማግለል፣ ተሰብስቦ እንዲህ ዐይነቱን አዋጅና ትእዛዝ በማስተላለፍና በመሳሰሉት መንገዶች ሁሉ ማርበድበድና ወጋጃዊ መሆን፤ በዱላ፣ በገጀራ፣ በድንጋይ እና በጥይት ተደብድበው የተገደሉትን ሬሳቸውን መጎተት፣ መስቀል፣ በሳት ማቃጠል፣ ጉድጓድ ቆፍረው በጅምላ መቅበር በኢትዮጵያ አፈር ላይ ዛሬ በ2012 ዓ.ም. (እ.አ.አ. 2019) በሰብአውያን ላይ ያለማሰለስ እየደረሰ ነው። ይህ ድርጊት ‘እኛን አይወክልም፣ እገሌን አይወክሉም’ የሚሉ ምላሾች የስብስብ ተጠያቂነትን፣ (ኮሌክቲቭ አካውንተብሊቲ) ክልላዊ ተጠይቂነትን፣ ብሔረ ሰባዊ ተጠያቂነትን፣ ሃይማኖታዊ ተጠያቂነትን አገር አቀፋዊ ተጠያቂነትን ሁሉ የሚያስወግዱ የዐመፅ ሰንሰለት መሽከርከሪያ ናቸው። ውጤታቸው አሁን እንደሚታይ በትውልድ ተቀጣጣይ የሚጋባ ዐመፅ ማሽከርከሪያ ነው።

ያለፉ የጥቃት ታሪኮችን ተጨባጭ ባልሆነና በታሪክ ጽሑፍ ላይ ባልተደገፈ መልኩ በማቅረብ እንዲሁም በመቶ ዓመታት ወደ ኋላ የተፈጸሙ የዓለሙ ሁሉ ተግባራት የሆኑትን፣ ከሳሽና ተከሳሽ ሁሉ የሚጠየቁበትን ያለፈ ሥርዐት እየጎለጎሉ አሁን እንዳለ ክስተት ያስመስላሉ። በዓለም አቀፍና ብሔራዊ ደረጃ እንዲሁም በገጠር ላሉ ገበሬዎች ሁሉ ከትልልቅ መገናኛ ብዙኀን አንሥቶ በስልክ መልእክቶች ‘እንዲህ ሆነሃል፤ እንዲህ ተሰድበሃል’ እያሉ፣ ‘ይህ ነገር እንዲህ ይሆንን?’ ብሎ ያልጠየቀ ወይም የመጠየቅ ንቃተ ኅሊናና ልምድ የሌለውን የዋሃንን ሁሉ በጥላቻና ቂም በቀል ይመርዛሉ። ይህን ለክፉ ሥራ የሚነሣ ሚሊዮን ሰራዊት ማነቃነቅ፣ ከምግባር ሁሉ ዝቅተኛ የሆነ ምግባር፣ ከአስተሳሰቦችም ሁሉ ዝቅተኛ አስተሳሰብ መሆኑን ሁሉም ሊያውቁት ይገባል፣ አሳዛኙ ጕዳይ ግን ይህንን የሚያደርጕ ዘመናዊ ትምህርት የጠገቡ መሆናቸው ነው።       

የኢትዮጵያና የኤርትራ አሰልቺ የረጅም ዓመታት ቁርቁስን በመለያየት እንኳ ለመፍታት ተሞክሮ፣ ከአገር ውስጥ ጦርነት ወደ የሁለት አገሮች ጦርነት በመሻገር ሁለቱንም ሕዝቦች እስካሁን ባላለቀ ፍዳ ጎድቷቸዋል። ሁለቱም አገሮች ይህንን ታሪክ ማለፋቸው ብቻ ሳይሆን፣ ‘ከዚህ ታሪክ የተማሩት ምንድን ነው?’ የሚለውን ጥያቄ ማገናዘብ ይጠቅም ነበር። እስካሁን ሁለቱም አገሮች ይህንን ያደረጉ አይመስለኝም። ለዚህ ዐይነት አገራዊ ሪፍሌክሽን ፍላጎትም ሆነ የታሰበበት ስትራተጂ ስላልነበረ፣ በየትውልዱ ተመሳሳይ ችግር እየፈጠርን መኻሉ ዳር መሆኑን ይቀጥላል ማለት ነው።

እንደሚታወቀው አብዛኛው የኢትዮጵያ የውስጥ አገር የሰላም ችግሮች ወይ በውጪ ኀይላት ትንኮሳና ፍላጎት ይከሰታሉ፣ አልያም የውጪ ኀይላት ፍላጎትን ይስባሉ። ይህ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ነባራዊ እውነታ ነው። በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ልዩነት በአንድ አገርነት ሳይሆን፣ በሁለት አገርነት እንዲያከትም ምክንያት የሆኑ እጅግ በርካታ የውጪ ኀይላት መሆናቸው ግልጽ ነው። አስቀድሞ ነጻ የሆነው የኤርትራ ሕዝብ ጥያቄ እያደር ሁለት ጎራ ፈጥሮ ነበር፤ ይህም ጎራ ዩኒየኒስት እና ሴፓሬቲስት በሚባሉ ኀይሎች የተሰየመ ነበር። የጀበሃ ኢስላማዊ ፓርቲ ምሥረታ ለኤርትራ ግንጠላም ሆነ ኢስላማዊ አገር የመሆን ግብ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። የሕዝቡ ጥያቄ ኢስላማዊ አገር የመሆን ጥያቄ አልነበረም፤ የትግሉ ፍጻሜ ውጤት ግን ይኸው ሆኗል። በሉዓላዊትነት አገር አዋጅ ማግስት ኤርትራ የአረብ ሊግ አባል ሆነች። ሰፊው ሕዝብ ግን የጥቂቶች ድብቅ አጀንዳ እንደሆነ የሚገባው እያደር በየግሉ ራሱን መሆን ሲከለከል ነው።

ሰፊው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ በመብቱ ትግልና በፍጻሜው ግብ መካከል ልዩነት እንዳይኖር እና በውጤቱም የበቀል ምኞት በጸጸት ስሜት እንዳይተካ የገዛ ትግሉን የመፈተሽ ኀላፊነት ይኖርበታል። ‘ትግላችንና በስማችን የሚደረገው ትግል፣ ምክንያቱ ምንድን ነው? ግባችን ምንድን ነው? የመጀመሪያ ጥያቄአችንን መልስ አግኝተናል ወይ? ምንድን ነው አሁን የሚያጋድለን?’ ብለን መጠየቅ ጭቆናን የምንታገል ቡድኖች ሁሉ ኀላፊነት ነው።

ቴክኖሎጂ እና ክርስትና

ስለ ቴክኖሎጂ ሲነሣ በአብዛኛው ወደ ሰው አእምሮ አስቀድሞ የሚከሰተው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ኮምፒውተር፣ ገመድ አልባ (ተንቀሳቃሽ) ስልክ ወይም በይነ መረብ (Internet) ነው፡፡ ነገር ግን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ ብዙ ሲሆን፣ ለምሳሌ አውቶሞቢል፣ ባቡር፣ አውሮፕላን፣ ራዲዮ፣ ቴሌቭዥን፣ መገናኛ አውታሮች፣ ኅትመት እና ሌሎችም… ናቸው፡፡ ዛሬ የምንነጋገርበት ጉዳይ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በክርስትና ላይ ያሳረፉትን እና እያሳረፉ ያሉትን በጎ ተጽዕኖ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

የኅብረቱ ውሳኔ በአዲስ ኪዳናዊው የአመራር ዘይቤ ሲታይ

በቅርቡ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት “አጋር አባል” ሲል የተቀበላቸውን ቤተ እምነቶችና መሪዎቻቸውን መነሻ አድርጎ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል። ጉዳዩ እስከ አሁንም የተቋጨ አይመስልም። ይህንን ተከትሎ ኅብረቱ የወሰደው ውሳኔ ከሞላ ጎደል አዲስ ኪዳናዊ አመራርን የሚከተል ሆኖ አግኝቼዋለሁ የሚሉት የሥነ አመራር መምህር የሆኑት ልደቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.