[the_ad_group id=”107″]

ኢየሱስን ብቸኛ አማላጅ አድርገን መውሰድ ያለብን ዐምስት ምክንያቶች

“ቅዱሳን እና መላእክት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አስታራቂ ተደርገው ይታመናሉ። በሌላ አኳያ፣ በአንዳንድ ቤተ ክርስትያናት ‘የእግዚአብሔር ሰው’ በሚለው ስም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የቈሙ አድርገው ራሳቸውን የሚያቀርቡ ወይም እነዚህን ሰዎች እንደ መካከለኛ አድርገው የሚወስዱ ሰዎች አሉ።” ባትሴባ ሰይፉ

አንዳንድ ቀናት በኢትዮጵያ ጎዳናዎች ላይ ሰዎች ይበዛሉ፤ ሻማዎች በየቤቱም ሆነ መሥሪያ ቤቱ ይነድዳሉ፤ ቄሶች በማለዳ ይዘምራሉ። በአብዛኛዎቹ ቀናት ቅዱሳንና መላእክት ወደ እግዚአብሔር እንዲማልዱላቸው ጸሎት ያደርጋሉ። አብዛኛዎቹ የቀን መቍጠሪያ ቀናት ለመላእክት ወይም ለቅዱሳን የተሰጡ ናቸው። ቅዱሳን እና መላእክት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አስታራቂ ተደርገው ይታመናሉ። በሌላ አኳያ፣ በአንዳንድ ቤተ ክርስትያናት “የእግዚአብሔር ሰው” በሚለው ስም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የቈሙ አድርገው ራሳቸውን የሚያቀርቡ ወይም እነዚህን ሰዎች እንደ መካከለኛ አድርገው የሚወስዱ ሰዎች አሉ። ሌሎች አስታራቂዎችን ወይም መካከለኞች ከመውሰድ በተቃራኒ፣ በዚህች ዐጭር ጽሑፍ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛው አማላጅ ወይም መካከለኛ አድርገን መውሰድ የሚኖርብንን ዐምስት ምክንያቶችን አቀርባለሁ። የዚህ ጽሑፍ ዐላማ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ማምጣትና እርሱን እንደ ብቁ እና በቂ አማላጅ መሆኑን ማሳየት ነው።

ምክንያት 1፦ ኢየሱስ ሊቀ ካህናት እንዲሆን በእግዚአብሔር ተሾሟል

እግዚአብሔር ክርስቶስን ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾሞታል። መዝሙር 110፥4 እንደ መልከ ጼዴቅ ያለ ሊቀ ካህናት ለዘላለም እንደሚኖር ያሳያል። በዕብራውያን 5፥10 እና 7 ላይ እንደሚታየው ይህ በክርስቶስ ፍጻሜን አግኝቷል። መዝሙር 110፥4ን በዕብራውያን 5፥6 እና 10 ላይ እንመለከታለን። በተጨማሪም ዕብራውያን 7፥1-25 ይህ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ እንደ ሆነ ይናገራል፤ በመልከ ጼዴቅ ሹመት የዘላለም ሊቀ ካህናት በሚል። ይህ ክህነት ከብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት በተቃራኒ በዘር ሐረግ ሳይሆን፣ እንደ መልከጼዴቅ በእግዚአብሔር ሹመት የተደረገ ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾሞታል፤ ስለዚህም ሌሎች መካከለኞችን መፈለግ የለብንም።

ምክንያት 2፦ ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን ካህናት ጥላና ትንቢቶች ፍጻሜ ነው

ብሉይ ኪዳን የካህናት ተስፋዎች እና ጥላዎች በመሲሑ ላይ እንደሚፈጸሙ ያሳያል። በብሉይ ኪዳን ካህናት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መካከለኛ ሆነው አገልግለዋል። በተጨማሪም መሲሑ የሊቀ ካህንነት ሚናውን እንደሚወጣ የሚገልጹ ትንቢቶች አሉ። እነዚህ ትንቢቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጽመዋል።

በመጀመሪያ፤ የብሉይ ኪዳን ካህናት መካከለኝነት ከሰዎች ወደ እግዚአብሔር ነበር። ዘሌዋውያን 17፥11 “ደም ሳይፈስስ ስርየት የለም” እንደሚል፣ መሥዋዕትን በማቅረብ ይህን አድርገዋል። በኢሳይያስ 52-53 ላይ እንደ ተገለጸው፣ ኢሳይያስ ስለ ብዙዎች የሚሰቃየው አገልጋይ የሚሠዋበትን ትንቢት ተናግሯል (ኢሳይያስ 52-53)። መሲሑ ስለ ብዙዎች በመሞት ብዙዎችን ጻድቅ እንደሚያደርጋቸው ተናግሯል (ኢሳይያስ 53፥5፡ 10-11)። በዮሐንስ ወንጌል፣ በተለይም በዮሐንስ 17 ላይ ኢየሱስ ለተመረጡት ወደ እግዚአብሔር አብ የሊቀ ካህንነት ጸሎት ሲያቀርብ እናያለን። በተጨማሪም፣ በብሉይ ኪዳን በትንቢት እንደተመለከተው፣ ክርስቶስ ለብዙዎች ሞቷል። ለሕዝቡ ኀጢአት በራሱ ሞት መሥዋዕት አድርጓል (ለምሳሌ ዮሐንስ 10፥17ን ይመልከቱ)።

ሁለተኛ፤ ሊቀ ካህናት ከእግዚአብሔር ወደ ሰው መካከለኛ ሆነዋል። ለምሳሌ ሰዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ወደ ሊቀ ካህናቱ ይሄዱ ነበር (ዘኁልቅ 27፥21)፤ እንዲሁም የቤተ መቅደሱን ሥርዐት ጠብቀዋል። በተጨማሪም፣ ኢሳይያስ እንደተነበየው፣ እግዚአብሔር በዚህ ሊቀ ካህናት በኩል ከሕዝቡ ጋር ይሆናል (ኢሳይያስ 7፥14)። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የሊቀ ካህናት ትንቢት በምድራዊ አገልግሎቱ ፈጽሟል። ይህንም ያደረገው ቤተ መቅደሱን በማንጻት፣ ሕግን በማክበርና ሕዝቡን በማስተማር ነው (ማቴዎስ 21፥12-17፤ ሉቃስ 21፥37)። በተጨማሪም፣ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ላይ፣ የኢሳይያስ 7 ትንቢት የእግዚአብሔር ክብር ወደ ምድር የመጣበት በእርሱ በኩል ሲፈጸም እንመለከታለን። ኢየሱስ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው። በተጨማሪም ማቴዎስ 1፥23 በኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር ከሰው ጋር እንደ ሆነ ያሳያል። የመካከለኝነቱ ሚና በክርስቶስ ተፈጽሟል፤ ስለዚህም ሌሎች መካከለኞችን መፈለግ የለብንም። 

ምክንያት 3፦ ኢየሱስ እውነተኛ ሰው በመሆኑ እንደ እኛ ተቈጥሯል 

ኢየሱስ ለእኛ አማላጅ ሊሆን የቻለው ፍጹም ሰው ስለ ሆነ ነው። ሰውነቱ በተለይ በመካከለኝነቱ በጣም አስፈላጊ ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥5 እንደሚነግረን ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው መካከለኛ ነው። ጳውሎስ ሰብአዊነቱን ሲያጎላ እናያለን። የእርሱ ሰብአዊነት ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖና እኛን ወክሎ ለዘላለም ባለበት በሰማያዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ ስለ እኛ ይማልዳልና (ዕብራውያን 2፥17–18፤ 4፥15፤ 5፥7–10፤ 7፥23–25፤ 8፥1-2)። ማንም በማይችለው ሁኔታ ከእኛ ጋር እንደ አንዱ ተቈጥሮ ለእኛ በበቂ ሁኔታ ሊማልድልን ይችላል። ስለዚህ ሌሎች አማላጆችን መፈለግ አይኖርብንም።

ምክንያት 4፦ ኢየሱስ አማላጅነቱ ተቀባይነት ያለው ፍጹም ሰው ነው

ኢየሱስ ስለ ኀጢአት ለእኛ ሊማልድልን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ነው፤ ነገር ግን እንደ መጀመሪያው አዳም እንደ ሌዋውያን ካህናት፣ ሁለተኛው አዳም እና ለአብ በታማኝነት የታዘዘ እውነተኛ ሊቀ ካህናት ሆነ። በመታዘዝ ነውር የሌለበት፣ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ስለ እኛ ሞተ። በመሆኑም ስለ እኛ ለዘላለም ሊማልድ ተነሥቷል። በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር ፍጹም ስለ ነበር መሥዋዕቱ በቂ ነው (ዕብራውያን 4፥15፤ 7፥26)። ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገው በመስቀሉ ሥራው ይማልድልናል። እንዲሁም፣ በሞት መከራ የፈተናውን ምንነት በግል ስለሚያውቅ ሊረዳን ይችላል (ዕብራውያን 2፥17-18)። መላእክት ሰዎች አይደሉም፣ ቅዱሳን ደግሞ ፍጹማን አይደሉም፤ በመሆኑም አማላጆች ሊሆኑ አይቻላቸውም።

ምክንያት 5፦ ኢየሱስ የአዲስ ኪዳን ብቸኛ መካከለኛ ነው

ኢየሱስ የአዲስ ኪዳን ብቸኛ መካከለኛ ነው። በክርስቶስ መሥዋዕትነት የጀመረው አንድ ኪዳን ብቻ፣ ይኸውም አዲሱ ኪዳን ነው። እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር የሚገናኘው በዚህ ኪዳን ብቻ ነው። ስለዚህ፣ በኢየሱስ አማላጅነት የማያምን ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው የቃል ኪዳን ግንኙነት ተገልሏል። በኤርምያስ 31 ላይ፣ አዲስ የቃል ኪዳን ማኅበረ ሰብ ሲቋቋም አይተናል። ይህ ማኅበር፣ በኤርምያስ፣ ምዕራፍ 33 ከቁጥር 20-22 በትንቢት እንደ ተነገረው፣ በሊቀ ካህናቱ ነው። በዚህ ክፍል ላይ አንዱ እንደ ተገለጸው መሲሑ የሌዋውያን ካህናት ፍጻሜ መሆኑ ነው። በተጨማሪም ዕብራውያን ምዕራፍ 8 በሊቀ ካህናቱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ስለ አዲስ ቃል ኪዳን ምሥረታ ይናገራል። በተጨማሪም፣ በማርቆስ 14፥22-25፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አዲሱ ቃል ኪዳን በእርሱ መሥዋዕት እንደ ሆነ እንደ ነገራቸው ተዘግቧል። ስለዚህም እግዚአብሔርን ማምለክ የምንችለው በእርሱ ብቻ ነው (ዕብራውያን 10፥5-10)። ሌላ መካከለኛ ይግባኝ ማለት ቤተ ክርስቲያንን ከአዲሱ ኪዳን ያገልላታል።

ለማጠቃለል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔርና በሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻው መካከለኛ እንደ ሆነ ይነግረናል። የእግዚአብሔር አምልኮ መሆን ያለበት እርሱ ባቋቋመው መንገድ ብቻ ነው። ክርስቶስ የሚከብረው እርሱን ብቻ እንደ በቂ እና ብቸኛ መካከለኛ ስንወስድ ብቻ ነው።

Share this article:

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ስለምትቀበል፥ በውስጡ የሚገኙትን መልእክቶችም ትቀበላለች። ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ (የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች) በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገቡና ለቤተ ክርስቲያን ጥቅምና መታነጽ የተሰጡ ናቸው (ሮሜ ፲፪፥፮- ፰፤ ፩ቆሮ. ፲፪፥፬-፲፩)። ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብታተ መንፈስ ቅዱስን የምትረዳበት፥ የምትተረጕምበት፥ የምታስተምርበትና የምትለማመድበት መንገድ የተለየ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

“በዚያ ያለውን እንድታደራጅ ተውሁህ!”

“አሁን ላይ፣ መከራው በኦርቶዶክስ እንደበዛባት፣ አንዳንዱንም መከራ በጋራ የተቀበልነው መሆኑን ሳስተውል፤ እንዲሁም እነርሱ (ኦርቶዶክሶቹ) እኛን የሚያሳድዱበት አጋጣሚ መኖሩን ስመለከት ለመደጋገፍ ዐብሮ መደራጀቱ ሊገፋበት እንደሚገባ ታይቶኛል።” የሚሉት ባንቱ ገብረ ማርያም፣ የግል ጕዟቸውን ባስቃኙበት በዚህ ጽሑፋቸው፣ ወንጌላውያንና ኦርቶዶክሳውያን ለመደጋገፍ አንድ ላይ የመደራጀታቸውን አስፈላጊነት ከተሞክሯቸው በመጥቀስ ይመክራሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.