
ከአዲስ ወደ ብሉይ?
የብልፅግና ወንጌል ሰባኪያንና ተከታዮቻቸው ብሉይ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ ትምህርታቸውንም በአዲሱ ኪዳን ላይ ለመመሥረት በፍጹም ይቸገራሉ፤ በመሆኑም ተከታዮቻቸውን ከአዲሱና ከበለጠው፣ ወደ ቀድሞውና ደካማው ብሉይ እየጎተቱ ናቸው ሲል አፈወርቅ ኀይሉ (ዶ/ር) ይሞግታል።
[the_ad_group id=”107″]
አንዳንድ ቀን ከቀኖች ሁሉ ልዩ ይሆንና በሞጋች ሐሳብ ያዝ ያደርጋችኋል። በእንዲህ ዐይነቱ አንድ ቀን ነው፣ “ኸረ ለመሆኑ፣ በአዲስ ኪዳን ነን ያለነው ወይስ ከብሉይ ኪዳን አሁንም ገና አልተላቀቅንም?” የሚል ጥያቄ የጠየቅሁት። በአጥቢያይቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለቃል ትምህርት የቆመው ሰው የስብከት ርእስ “ራስ እንጂ ጅራት አትሆኑም” የሚል ነበር። ንባቡ ከዘዳግም 28 የጀመረ ነው። አስተማሪው፣ “የእግዚአብሔር ዐላማ በዚህ ዘመን ለሕዝቡ” ይህ እንደ ሆነ ተነተነ። “የኢኮኖሚ ማማ ላይ መታየት የእኛ ዕድል ፈንታ ነው፤ በሀብት አንደኝነት በክርስቶስ የእኛ ሆኗል …” አለ። በመዝሙር የታጀበም ማጠቃለያ ሰጠ፤ ዝማሬውም “ቃሉ ምን አለ?…ትራባለህ? አላለም! ትታመማለህ? አላለም! ትደኸያለህ? አላለም! ….” የሚል ነበር። የዚያን ዕለት የቁርጥ ሆኖ በተለየ ሁኔታ “የተሰጠን የተስፋ ቃል” ምንነት እንደገና ለማሰብ እና በቅርበት ለማየት ፈለግሁ እንጂ “ክርስቲያን ለበሽ በሽ ኑሮ መጠራቱን” የሚያበስሩና ከብልፅግና ወንጌል ጓዳ የተቀዱ ትንቢቶች፣ ስብከቶችና ዝማሬዎች ለሰሚዎቹ የየዕለት ስንቅ ከሆኑማ እኮ ዐሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል።
የአሁኑ ጽሑፌ ይህንን ትምህርት ከሥረ መሠረቱ አንጻር ይሞግታል። ጥቂት የማይባሉ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ‘አይነካካንም!’ የሚሉት ብሉያዊነት “በሌላ መንገድ ዞረው እንደገቡበት” ማሳያ ያቀርባል።
‘እግዚአብሔር በብዙ ጎዳና እና መንገድ በብሉይ ኪዳን ከተናገረና ሕዝቡን ወደ ራሱ ካቀረበ በኋላ፣ በመጨረሻ በአዲስ ኪዳን በክርስቶስ አዲስን መንገድ ከፈተ’ የሚለው ቃል አስማሚና ገልጽ ነው። ሰለሆነም የአዲስ መኖር ያለፈውን ወይም አሮጌውን (በግዕዙ “ብሉይ”) ኪዳን ማስረጀቱ እንደ ሆነ መጽሐፍ ይናገራል። ያለፈው፣ የአሮጌው ድምፅ ‘አላረጀሁም’ ለማለት እንደሚፈልግ እንኳ ተደርጎ ቢታሰብ አዲሱ በመምጣቱ ምክንያት የሚያሰማው አቤቱታ የጣር ድምፅ ያህል ነው፤ የዚህ የአዲሱ የዜና ዐዋጅ እጅግ ገናና ነውና፤ ለዚህም እውነት መስቀሉ ምስክር ነው። እናም ሰው ከአሮጌው ወደ አዲሱ ተሸጋገረ፤ ወደ ፊት ተራመደ። አሁን ሙሴ አይደለም፤ ክርስቶስ እንጂ!
ያኛው የቀደመው ኪዳን ከሲና ነው። በሙሴ በኩል ከግብፅ ባርነት ለወጣው፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር ፓለስታይን እየገባ ላለው ለእስራኤል ሕዝብ ተሰጠ። ‘ይህን ብታደርጉ ያ ይሆንላችኋል’ ተባሉ። ‘ምድርን እሰጣችኋለሁ፣ ትገቡበታላችሁም፤ ትባረካላችሁ! ለምድራችሁም ፍጹም ጥበቃ ይሆናል፤ የጠላት ጦር ተንጋግቶ ቢመጣ እንኳ የመሸነፍን ስንቅ ሰንቆ ነው። ምድሪቱም ፍሬ ትሰጣለች፤ ስለዚህም ጎተራው ሙሉ ነው።’ ጎተራው ሙሉ ነው ማለት ምን ማለት ነው? ‘ሀብታም ትሆናላችሁ’ ማለቱ ነው። እንደ ሕጉ ቢኖሩ “ራስ እንጂ ጅራት” አይሆኑም፤ ያበድራሉ እንጂ አይበደሩም፤ በሀብታቸው፣ በጦር ኀይል ብርታት ከምድር ሕዝቦች ሁሉ ጎልተው ይታያሉ። ኪዳኑ ነዋ! ለቃሉም ማፅኛ የቃል ኪዳን ታቦት ተሰጣቸው። የዚያ ኪዳን ሕዝብ በርግጥም እንዲያ ሆነለት። ሕጉን ባይጠብቁ ግን “ውርድ ከራስ” ነውና የዚያ ሁሉ በረከት ተቃራኒ ይሆንባቸዋል። ምድሪቷ ትለግማለች፤ ቢዘሩ አይበቅልም፤ ቢነግዱ አያተርፉም። እናም “ራስ” አይሆኑም፣ በኢኮኖሚው ጭምር፤ ፈጽሞ በሀብት ማማ ላይ መቀመጥ አይሆንላቸውም።
እንግዲህ ቁልፉ ነገር እንዲህ ነው፡- ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጠው የዚያ ኪዳን ስጦታ መሬት ነው፤ የፍልስጤም ምድር። ሒሳቡ የሚወራረደውም በዚያው “በምድር ጉዳይ” ነው። ስለሆነም በረከቱም መርገሙም የሚዳሰስ የሚታይ ነው። ሀብት ቢሆን፣ የጦር ብርታት ቢሆን፣ ወዘተ. ሁሉም የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚጨበጥ የቁስ ነው። ስጦታው የቁስ ነውና በረከቱም የቁስ መሆኑ ነው። ሕጉን በጠበቁበት ዘመን፣ ልባቸውን ወደ እግዚአብሔር በመለሱበት ጊዜያት ሁሉ ይህ ቢሆንላቸውም ቅሉ፣ እነዚያን ቅዱሳት ሕግጋት እና ቃሎች በዘላቂነት ለመሸከም የሰው የሥጋ (ባሕርይ) አልቻለም። ቃሎቹ ቅዱሳን፣ ሰው ግን ዱኩም ሆነ። ሕጉ እንደ ሞግዚትም ሆኖ ይህንን ተፍገምጋሚ ሰው ሊረዳ ሞከረ። በመጨረሻም፣ ለሚገላግለውና ዋነኛ ለሆነው ለአዲሱ ኪዳን ‘አዳሜን ተቀበለኝ’ አለ። ይህ የሆነው ‘ወጣሁ፣ ወጣሁ’ ሲል መውደቅ የሚቀናውም የሰው ልጅ ተፍጨርጫሪ ሙከራ የእግዚአብሔርን ጽድቅ፣ የሕጎቹን ንጽሕና ቢናገር እንጂ መፍትሔ አላመጣምና ነው። እነዚያ ሠላሳ ዘጠኙ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ደግመው ደጋግመው የሚናገሩት ይህንን እውነት ነው።
የአዲስ ኪዳን (የገላቲያ መልእክት) ንባባችን እንደሚያሳየው ወደ አዲሱ ግብዣ የገቡ እስራኤላውያን እንኳ አሮጌውን እንዲሁ በዋዛ አልተላቀቁም። የአሮጌው ስበት ብርቱ ነው። እናም እልፍ ማለቱ ለአንዳንድ አይሁዳውያን የማንነት ጥያቄን አስነሣ። ‘ሙሴስ? መገረዝስ? የሲና ክብርስ?’ እነኚህ እንደ ምንም ተደራረቡና በፊታቸው ተራራ ፈጠሩ፤ ባሻገር ያለውን የአዲስ ኪዳን ተስፋ ሰማያዊ አገር ከለሉባቸው። ወደ አሮጌው ሊመለሱ የፈለጉትን የገሰፀው ያው ቃል ነው፤ ብሉዩ ኪዳንም ደግሞ ደጋግሞ ‘ደክማችሁ አታድክሙኝ፣ ሂዱ ወደ ፊት’ ይላል። ይህን ስለዚያ አልኩ እንጂ ዛሬም ቢሆን ያ ኪዳን በሀብት ስም፣ በ’ምድር ጉዳይ’ ስም፣ በመክበር ስም ሆኖ አማኞችን መሳብ መቀጠሉንም አስተውሉ። አዲስ ኪዳን ግን ደጋግሞ የሰማያዊ ውርስ ተስፋ ቃሉን በድንቅ ብርሃን ፍንትው አድርጎ በብሉዩ ምድራዊ ግርማ ሞገስ ሥር የወደቁትን (ባለ ብልፅግና ወንጌለኞችን፣ በሀብት ፍለጋም ሰበብ ከሥሩ ሊወድቁ እየተፍገመገሙ ያሉትን የሆድ እስረኞችን) ‘ምን ነካችሁ ባለ አዲሶች፤ ምነዋ ወደ አሮጌው?!’ ሲል ይጠይቃል። ‘አዲሱን አትለውጡ፣ አትገልብጡ’ ነው ጥሪው።
የአዲሱን ክብር አስቀድመው ያዩት የዚያው ኪዳን ነቢያት ነበሩ። አዲስ ቃል ኪዳን፣ አዲስ ኪዳን። ይህ ኪዳን እንደ ቀደመው፣ ሕዝቡ ከግብፅ ሲወጣ የተቀበለው ዐይነት አይሆንም፤ ምክንያቱም ሰው በዚያ አልጸናምና። በመሆኑም፣ ይሄኛው አዲስ ውል አዲስ ኪዳን ነው (ኤር. 31፥32)። አምላክም ሕጉን በድንጋይ ሳይሆን በልቡናቸው ይጽፋል፤ ጉዳዩ የውጪ ሳይሆን የውስጥ ይሆን ዘንድ። የአዲስ ኪዳኑ የዕብራውያን ጸሐፊ ይህንኑ የነቢዩ ኤርሚያስን ቃል በሰፊው ጠቀሰና፣ ‘አሮጌው (ብሉይ) ኪዳን አበቃለት’ የሚል ብርቱውን መልእክት በግልጽ ደገመው፤ በአዲስ የመድመቅ፣ አዲስ የመልበስ ጥሪን እያሰማ። አዲሱ አስገረመው፤ አሮጌው (ብሉዩ) ግን ውራጅ (second-hand) ሆነበት (ዕብ. 8፥13)።
እናማ የክርስቶስ መምጣት የአዲስ ሥርዐት፣ የአዲስ ውል፣ የአዲስ ቃል ኪዳን መምጣት ሆነ። የዚህ የአዲሱ ኪዳን ትኩረቱ እንደ በፊቱ የእስራኤል ሕዝብ ብቻ አይደለም፤ የዓለሙ ሁሉ እንጂ። የውሉ ማሠሪያ አንድ ክልል የተበጀለት ምድር እና አገር አይደለም፤ አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ እንጂ። ስጦታው ሰማያዊ ከሆነ በረከቱም ሰማያዊ መሆኑም አይደል?! ስለዚህ ሀብታም እና ደኻ ሁለቱም እኩል የተባረኩበት ይህ ውል፣ የውስጥ፣ የመንፈስ የሆነ መሠረት ያለው ነው (የተቃራኒ ጦር ኀይላትም እንዲሁ ሥጋ ለባሽ ሰው ሳይሆን መንፈሳውያን መሆናቸውን አስተውሉ)። በክርስቶስ “ክርስቲያን” የተባለ ይህ ሕዝብ፣ አማኝ፣ ክርስቶስን የለበሰ፣ በክርስቶስ የተወረሰ አዲስ ፍጥረት ሆነ። መንፈሳዊ፣ ዘላለማዊ!
ክርስቶስ ኢየሱስ ሜትር መትሮ ለተቀበልነው አዲስ ኪዳን ውል መሬት አልሰጠንምና ከምድር የሚገኝ፣ ከቁስ የሆነ “በረከት” የሚያሰጥ ቃል ኪዳን አልገባም። እንዳልኩት፣ አሁንም ደግሜ እንደምለው በረከቱ ሰማያዊ፣ ጉልበቱም ሰማያዊ ነው። ሃያ ሰባቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ አንብቡ። በአማኞች ዘንድ ሀብት የነበራቸው እንደ ነበሩ ታያላችሁ። አንድም ቦታ ግን ሀብታቸውን ተንተርሶ ‘ይህን ያገኙት ስለተባረኩ ነው’፣ እነርሱንም በገንዘባቸው ምክንያት ‘የተባረኩ’ ይላቸዋል ብላችሁ አትጠብቁ። “ባለፀጎች” ነው የሚላቸው። ድኾችም (ያውም መብት አልባ ባሪያዎችም) ነበሩ። ግን “ድኾች” ተባሉ እንጂ በማጣታቸው “ያልተባረኩ” አልተባሉም፤ የዚህም የዚያም በረከት ሀብት ሳይሆን ክርስቶስ ነውና። ድኽነትም፣ መራብም፣ ማጣትም፣ መበደርም፣ ኑሮ አልሞላ ብሎ መታየትም “ከኪዳን ውል” መጉደል ሆኖ በጭራሽ አልቀረበም። አንድስ እንኳ። እነዚህ የኪስ ጉዳተኞች “ወርቅ እና ብር” ባይኖራቸውም ያላቸው ግን ነበራቸው፤ ሙላት ነበራቸው፤ ጉልበት ነበራቸው። ይህ አዲስ ኪዳን ነው! ይህ “የኢየሱስ ጉዳይ” ነው!
እንግዲያስ ሀብታም ከድኻው በተለየ ሁኔታ “የተባረከ” የሚመስላችሁና እንዲሁ ይሆን ዘንድ የምትጠብቁ ወደ ክርስቶስ አትምጡ፤ ሌላ ቦታ ፈልጉ፤ ወይም ወደ ብሉይ ኪዳን ተከለሱ፣ ተመለሱ። አብረቅራቂ ቀለማት የተሸለሙ ጌጠኛ ልብስ መልበስን፣ በሀብት ማማ ላይ መቀመጥን “በክርስቶስ የመሆን ምልክት” ወይም “በክርስቶስ የማመን ውጤት” አድርጋችሁ ልትወስዱ ብትፈልጉ እና ልትሰብኩ ጎምለል ጎምለል ብትሉ፣ “ጎልጎታ” ከ“ሲና” ቢምታታባችሁ ነው። ከፍ ያሉቱ፣ ሀብት ያላቸው ባለፀጎች፣ ታዋቂዎች ባለሥልጣናት ከድኻው በተለየ የክብር ቦታ የሚሰጣቸው “ቤተ ክርስቲያን” ብትደርሱ ፈጥኖ የሚመጣላችሁ መደነቅ ሳይሆን ጸሎትና እግዚዮታ ይሁን፤ ምክር ይሁን። የማይሰሙ ከሆነ ከአሮጌው ወጥመድ ሥር የወደቁ ናቸውና ፈጠን ፈጠን ብላችሁ ውጡ፤ እናንተም አዲስ ኪዳናችሁን አፅኑ።
ስተዋል! ደማቆች እና ከዋክብት ብቻ የሚወደሱበት፣ አካል ጉዳተኞች የሚገለሉበት፣ ሕመምተኞች ስለ እምነታቸው ማነስ የሚከሰሱበት፣ ድኾች በድኽነታቸው የሚሸማቀቁበት፣ ያላገቡ እና ያልወለዱ ባለመሳካት የሚኮነኑበት ጉባዔ በ“ስመ ክርስቶስ” ቢሰበሰቡበት እንጂ ከመንፈሱ ወደ ኋላ ሩቅ ናቸው፤ የኪዳን ጎዶሎ ናቸው። እንደነዚህ ያሉበት ቦታ የስሜት ግለት የወለደው ንውፅውፅታ፣ ሆታ እና ጩኸት የስብሰባ አዳራሻቸውን አየር ቢሞላውም “በመጋረጃ ውስጥ” የሚደረግ ወግ ከመሆን የዘለለ አይደለም። ብርሃን ያላየው፣ የክርስቶስ መንፈስ ያልጎበኘው “የጊዜው” ነው። ኪዳን ገልባጭ፣ ለዋጭ ነው።
አዲስ ኪዳንን ያልሆነውንና ሊሆን የማይችለውን ቅርፅ ለማስያዝ ጎንበስ ቀናው አለ። አንዴውኑ በሀብት ማማ ላይ መውጣት የመፈለግ ምኞት ያናወዘው ደግሞ በብሉዩ ኪዳን ተስፋዎች ተስቦ እና ተጎትቶ ብቻ አያበቃም። የሚያየው የአዲስ ኪዳን ጥቅስ በሙሉ “ስለ ገንዘብ የቃል ኪዳን” ውል በመምሰል ይቀየርበታል። እንደ ፊልጵስዩስ 4፥13 የተሠቃየ ጥቅስ ያለ ግን አይመስለኝም። ጥቅሱ “ኀይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ይላል። በየጉባኤውም ‘በል፣ ተባባል’ ይባልበታል። ‘አልራብም፣ አልጠማም፣ ከፍታው የእኔ ነው፣ ማንም አይይዘኝም፣ ወደ ሀብት መውጣት እችላለሁ…’ነው ዐዋጅ ፉከራው።እና ምጥቅሱ ያለ ውዴታው ከእነርሱ ጋር ይጮኽ ዘንድ ይገደዳል። ይህ ድካም ነው፤ እንደ ጥቅሱ ጳውሎስ “የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል” የሚለው ነው ኀይል፤ “መዋረድን አውቃለሁ፣ መብዛትን አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንም መራብንም፣ መብዛትንም መጉደልንም ተምሬያለሁ። ኀይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ያለው ነው በርግጥ የቃሉ፣ የአዲሱ! ግን አንዴ በብሉዩ የተጠመቀውን ምን ታደርጉታላችሁ? ጥቅሱ ሁሉ ለሆድ ይመስለዋል። የሚመስለኝ “ከጅብ ቆዳ የተሠራ ክራር ቅኝቱ ሁሌም ‘እንብላው እንብላው’ ይላል” የሚባለው ሆኖባቸው ነው። ክራሩን ባቲ አድርጋችሁ ቃኙት ወይም ዘለሠኛ፣ አለያም ደግሞ አንቺ ሆዬ፣ ወዘተ. ያው ቅኝቱ “እንብላው፣ እንብላው” ነው፤ ከጅብ ቆዳ ተሠርቷልና። ያንን ክራር ሌላ ማናገር አይቻልም ነው የሥነ ቃሉ መልእክት። አንድ ጊዜ በዚያ የብልፅግና ወንጌል ምትኀት ሥር የወደቀውን፣ ብሉይ ውበት ርስቱ የሆነውን፣ በዚያም አድርጉት በዚህ፣ ያንን ጥቅስ ስጡት ይኼኛውን፣ ብቻ የሚታየው የምድሩ ነው። ግን ግን ቢያውቁም ባያውቁም መነሻውም ሆነ መድረሻው፣ የኪዳን ግልበጣ ሙከራ ነው። መንፈሳዊ ወንጀል ነው።
እንዳያችሁት ‘እንኳን ከአሮጌው ወደ አዲሱ አሸጋገራችሁ’ ነው የአዲስ ኪዳን መልእክት። የአዲሱ ኪዳን ውል እና ቃል ደግሞ “ኢየሱስ ኑሮዬ” ከሚለው መርሕ ጋር ያለውን የእግዚአብሔርን ለየዕለት ኑሮ በጎነት የሚያጸና ስለሆነ ለዚያ አፉን በሰፊው ከፍቶ በትልቁ ለመጉረስ ለተዘጋጀ ፍጥረት ለማያልቅ ምኞቱ አርኪ አልሆነም። እናም ያ ብልጥ “የኢየሱስን ጉዳይ” ለራሱም ለሰሚውም ትርጉም እንዲሰጥ “የምድር ጉዳይ” ለማድረግ ደግሞ ደጋግሞ ይጥራል። ለምኞቱ እርካታ ደግሞ “ቤተ ክርስቲያንን” ጥሎ አይሄድ ነገር ጭንቁ ነው፤ ለምንስ ብሎ?! ‘ኢየሱሴ’፣ ‘ዳንኩ’፣ ‘አዲስ ፍጥረት’ ከሚልበት፣ ‘ክርስቲያን ነኝ’ ብሎ ከሚያዜምበት እምነት ወጥቶ የልቡን ሐሳብ ይሙላ? እንዴት ተደርጎ! ይህንንማ አላደረገውም። ታዲያ ምን? ብልጡ የሰው ሐሳብ የቅርብ መፍትሔ አገኘ፤ ይኸውም ወደ ውጪ ከመውደቅ ወደ ኋላ መውደቅ። በቀኝም ይሁን በግራ በኩል ብቻ ወደ ተሻለለት አማራጭ ወደ ኋላ መዞር። ከአዲስ ኪዳን ወደ ብሉዩ (አሮጌው) መከለስ። ያ ኪዳን ደግሞ እንደምታውቁት “መባረክን” ከቁስ ጋር ያያይዛል፤ ወደ ኪስ ስለሚገባው በሰፊው ይናገራል። ስለሆነም ቀላሉ አቋራጭ እዚህ እንዳሉ ቆጥሮ ወደዚያኛው ማዝገም፣ እዚህ ስምን አስቀምጦ በልብ እዚያ መሆን። ይመቻል። ያለማወቅ ሲጨመርበት ደግሞ ጩኸቱ፣ ‘ግቡበት’ የማለት ስበቱ፣ የድለላውና የደላላው ብዛት አይጣል ነው። እንደምታዩት የመንፈስ ከፍታ ሳይሆን የሀብት ነገር ደግሞ ይጨበጣል፣ ይዳሰሳልና፤ ስለሆነም የብዙ ጀግኖችን ዐይን አልሳበም አይባልም። ስንቱ ጀግና “ራስ” ለመሆን የኋሊት አዝግሟል መሰላችሁ። የኋሊት ነገር የኋላ የኋላ ብዙውን በክርኑ ደቁሷል፤ ለሩቅ ጉዞ የተጠራውን ስቦ ከቅርብ አሳድሮታል።
የአዲስ ኪዳኑ ውል የመንፈስ ነው፤ ሰማያዊ! ያንን ጉልበት ያገኘው ሰው፣ በሰማይ ፀዳል የተነካው የእምነት ጀግና ለምድሩ ኑሮው ብርታትን ያገኘ ነው። ሰጪው አንዱን ከአንዱ የሚለይ ያልሆነ “ለማንም ቸር” በሆነ ማንነቱ ያውቀዋል፤ ስለሆነም ካገኘው በላይ ለሰጪው ይሞታል፤ በዚያም ብርቱ ጉልበት ተራራውን ይረግጣል፣ ሸለቆውን ያልፋል። ሕልሙ የክርስቶስ በሕይወቱ ከፍ ብሎ መታየት ነው። ‘የለውም’ ስትሉት አለው፤ ‘ጠፋ’ ስትሉት ይለመልማል። የመንፈስ ፍሬ የተሞላ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል እና ጉልበት የበረታ ነው። የልቡ ዐይን ያለው እዚያ ነው፤ የክብሩን ጌታ ማየት። ስለሆነም ለምድር የዕለት ተዕለት ኑሮ ክብደት በርግጥ ባለ መፍትሔ እርሱ ነው።
ለ50 ዓመታት ያላነሰ የተሰበከው የብልፅግና ወንጌል ግን መጨረሻ ግቡ ሰውን ከማግኘት ማጣት በላይ ከሚያኖረው ብርቱ ኀይል ማጉደል ነው። ሕዝብን ከምድር አጣብቆ መስፋት፣ ለጠላት ማመቻቸት። ሌላም አለ፡- በርግጥ ለሰባኪዎቹና ለተንባዮቹ የሚሉት ነገር በሕዝቡ ጫንቃ ላይ በጭከና የተገነባ ሆኖ ነው እንጂ’ኮ ሳይሆንላቸው አልቀረም፤ ከሰማይ አልሆነም እንጂ ለእነሱማ ውጤት ተኮር ሆኖ ከሚያገለግሉት ሕዝብ “ራስ” ላይ መውጫ መሰላል ሆኖላቸዋል። ሕዝቡን እንደ ላም ያልቡትና እርሱ ሲገረጣ እነርሱ ያብለጨልጩበታል። እውነታው ይህ ብቻ ነው። ‘ራስ እንጂ ጅራት አንሆንም’ ቢሉ የበላይነታቸው፣ ራስነታቸው ሰብስበው ከሚግጡት ሕዝብ ውጪ አይደለም። እንጂ’ማ እነሱ የሚሉት ዲስኩር ከአዳራሻቸው ዉጪ እንደማይሠራ የሚያውቅ ያውቀዋል።
ስለ ዓለም ዋና ዋና ባለፀጎች የሚተርከውን የForbes (ፎርብስ) መጽሔት ሪፖርት ከመረጃ መረቦች ማየት ትችላላችሁ ወይም ስለ አሜሪካ ሀብታሞች Fortune (ፎርቹን) 500ን ተመልከቱ። ይሄው ከ50 ዓመት በኋላም እንኳ እዚያ ውስጥ የምታውቁት “ራስ ነኝ ባይ ‘ጴንጤ’” አለ? የኢየሱስ የመምጣቱ ግብ አማኞችን “ራስ እንጂ ጅራት” እንዲሆኑ ከሆነ Forbesም ሆነ Fortune አንደኛም ይሁን መቶኛ ላይ ፎካሪ “ራሶችን” ማስቀመጥ ነበረባቸው፤ ግን አልሆነም። ሊባል የሚችለው ወይ ስሞቻችውን ባለመጥቀስ መጽሔቶቹ ተሳስተዋል ወይም ባለብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎቹ ለዘረፋ ይመቻቸው ዘንድ በየሳምንቱ ውሸትን ሳይሰለቻቸው እየደሰኮሩ ነው። መልሱ ግልጽ ነው። የያዝኩት እና የገባሁበት ኪዳን ብርቱ ቢሆንብኝ ጊዜ ማስመለሳቸውን፣ ክፉውን አሳሳታቸውንና ቅጥፈታቸውን “ወግድ!፣ ከአዲሱ ኪዳን ጋር ግን “ወደ ፊት እንሂድ!” ብያለሁ።
Share this article:
የብልፅግና ወንጌል ሰባኪያንና ተከታዮቻቸው ብሉይ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ ትምህርታቸውንም በአዲሱ ኪዳን ላይ ለመመሥረት በፍጹም ይቸገራሉ፤ በመሆኑም ተከታዮቻቸውን ከአዲሱና ከበለጠው፣ ወደ ቀድሞውና ደካማው ብሉይ እየጎተቱ ናቸው ሲል አፈወርቅ ኀይሉ (ዶ/ር) ይሞግታል።
የእሬቻ በዓል በክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ መካከል መነጋገሪያ ሆኖ እንደ ሰነበተ ተከብሮ ዐልፏል። በዓሉ ተከብሮ ይለፍ እንጂ፣ መነጋገሪያነቱ አልቆመም፤ ምናልባትም ለመጭዎቹ ዘመናት እንዲሁ መነጋገሪያ እንደ ሆነ ይቀጥል ይሆናል። ባንቱ ገብረ ማርያም፣ “ኢትዮጵያ የ ‘አረማዊ ደሴት’?” ሲሉ የሰየሙት ይህ ጽሑፍ፣ በሮም ግዛት ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች፣ እንዲህ ላለው የአደባባይ በዓል የሰጡትን ምላሽ በታሪክ መነፅር እያስቃኙ፣ ለዛሬ ክርስቲያኖች መልእክት ያቀብላሉ። የባንቱ ገብረ ማርያም ጽሑፍ፣ የእሬቻ በዓልን በሚመለከት ለሚካሄደው ውይይት መፋፋት የራሱ ፋይዳ አለው በሚል እንደሚከተለው ለንባብ በቅቷል።
ታክሲ ውስጥ ነን። እኔ፣ ምናሴና የምናሴ ባለቤት፣ ዶይ። ታክሲዋ ተጠቅጥቃና ተነቅንቃ ከመሙላቷ የተነሣ፣ እንደ ሰው አፍኗት ብታስነጥስ እንደ እኔ ቀለል ያልን ሰዎች በአፍንጫ እንደሚወጣ የእንጥሻ ፍንጣሪ፣ በር ሳይከፈት እንወጣ ነበር። ወደ መዳረሻችን፣ ̋ተሻግሮ ወራጅ አለ” አንዱ ከኋላ። በረዶና ነጎድጓድ አዘል የስድብ መዓት ስታዘንብ የመጣችው ሴት ደግሞ፣ ̋ሳይሻገር ወራጅ አለ ̋ አለችና ደጋግማ ጮሄች። ሾፌሩ በኀይል መናግሯ ̋ደብሮት ̋ ነው መሰለኝ፣
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment