[the_ad_group id=”107″]

ወደ ቦታችሁ ተመለሱ!

ኢብሳ ቡርቃ

ስፍራን ማወቅ መታደል ነው፤ የት መሰየም እንዳለብን መረዳት ደግሞ በረከት። ከፀሓይ በታች ያለ የፍጥረት መራኮት ኹሉ የጊዜና ቦታ ማእቀፍ አለው። ጊዜውንም ቦታውን ያልጠበቀ ነገር ጠንቅ አያጣውም። ያለ ቦታው የተገኘ ነገር ምንም ክቡር ቢሆን መናኛ ይሆናል፤ ሲከፋም ያለ አገልግሎት ሚጐለት ጕልቻ። ያለ ጊዜውም የደረሰ እንጭጭነት አያጣውም። መጽሐፍም እንደሚል በጊዜና ስፍራ የማይወሰን ልዑል አምላክ ኹሉን በጊዜው ውብ አድርጎ ሠርቶታል። በዐጭሩ፣ ሁሉም በቦታው ሲሆን ልክክ፣ ስክትክት ይላል፤ ይሠምራል።

ፍጥረተ ዓለም ራሱ ምድር ከተጸነሰችበት፣ አጽናፈ ዓለሙም ከተረገዘበት ስፍረ ጊዜ ጀምሮ፣ ቦታቸውን በያዙ ሕግጋቶችና physical cosmological constants የሚተዳደር ሥርዐት ነው። መላ ዓለሙ የሥርዐት እስረኛ ነው። ምንም እንኳ ቁሳዊው/አካላዊው አጽናፈ ዓለም (Physical cosmos) ከ 93 billion የብርሃን ዓመት በላይ ርዝመት/diameter ያለው ግዙፍ ኑባሬ ቢኾንም፣ በአራት መሠረታዊ ኀይሎች ሚዘወር ሥርዐት ነው። የሥነ ፈለክ አጥኚዎች እነዚህን ኀያላት መሠረታዊ የተፈጥሮ ኀያላት (The four fundamental forces of nature) ይሏቸዋል። እነዚህም ኀይላት ስበት/gravity፣ ኤሌክትሮማግኔቲዝም፣ ደካማውና ጠንካራው የኒውክሌር ኀይሎች ናቸው። በአቶም ኒውክለስ/እምብርት ዛቢያ ከሚጦዝ ኤሌክትሮን (From a spinning electron) እስከ በጋላክሲ ማእከል (galactic center) የሚደረግ ዙረት (to a spinning galaxy) ያለ የትኛውም ተፈጥሮአዊ ክስተት በእነዚህ ኀይላት ቁጥጥርና ግዛት ሥር ያለ ነው። እነዚህ ኀይላት ምጥናቸው ተፋልሶ ቢኾን ምድር ሕይወትን የማስገኘት፣ ደግሞም የማሰንበት አቋሟን ትነጠቅ እንደ ነበር በ Intelligent design የሚያምኑ አጥኚዎች ይመሰክራሉ። ከዚህም ግዙፉና ግኡዙ ህዋ ራሱ የሚተዳደርበት ሥርዐት እንዳለው መገንዘብ ይቻላል።

እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ብይን፣ ሥርዐትን ለፍጥረቱ ያበጀ ደግሞም የደነገገ፣ ዐልፎም ያሠለጠነ ራሱ ልዑል አምላክ ነው። ለማእበሉ ገደብን ያበጀ፣ ለሚያንጎዳጉደው መብረቅም መንገዱን ያሳየ፣ በቀንና ሌት ኹሉን የሚያወጣና የሚያገባ ራሱ እግዚአብሔር ነው። በዕውቀቱ ምጡቅ፣ በማስተዋሉም ወደር የሌለው አምላክ ነው ፍጥረቱን በልእልናው የሚመራው።

ታላቁ መጽሐፍ ግን ሥርዐት ስለመኖሩ ብቻ አይደለም የሚያወሳው። የተደነገገው ሥርዐት መልካም እንደ ሆነ፣ የሠራቸው ማወጁን የኦሪት ቀዳሚ የሆነው ዘፍጥረት አበክሮ ተናግሯል። መልክና ቅርጽ ያለነበራትን ምድር መልክ ሰጥቷታል። ባዶነት ተጭኖት የነበረን ዓለም በፍጥረቱ ሞልቶታል። በፍጥረት ታሪክ ውስጥ፣ ተደጋግሞ በአጽንዖት የተነገረ ነገር ቢኖር፣ ያህዌ ያበጀው ኹሉ መልካም መኾኑ ነው። በምድር የሚሳቡ፣ በሰማይ የሚከንፉ፣ ረቂቃን፣ ግዙፋን ኹሉ የጣቱ ሥራዎች መልካም መኾናቸውን ልብ ልንል ይገባል። ዐይተን የምንወድዳቸው፣ አቅርበን የምንንከባከባቸው ብቻ ሳይኾን፣ ቀፋፊና አስቀያሚ ያልናቸው አውሬዎች ኹሉ በሠሪያቸው መልካም ተብለዋል፤ የጥበቡ ማሳያም ናቸው። የሥልታዌ ነገረ መለኮት ተማሪዎች ይኼን ጭብጥ፣ The original goodness of creation ይሉታል።

ቅዱሳት መጻሕፍት ጨምረው እንደሚያትቱት፣ የያህዌ ጥበብ በማስገኘቱ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከማበጀት ዐልፎ የዘረጋውን የፍጥረት ሥርዐት እንዳይዛነፍ በኀያል ቃሉ የሚደግፈው ራሱ የእስራኤል ቅዱስ ነው። አስገኛቸው፤ ደግሞም ደግፎ አጸናቸው! የተዘረጋው ሥርዐት ያልተናደው፣ በዘመናትም መኻል ያልከሰመው ክንደ ብርቱ በኾነ አምላክ ስለ ተደገፈ ነው።

ሥርዐት ግን ለግዑዙ ዓለም ብቻ የተሰጠ አይደለም። በሰው ልጆችም ዘንድ ያሉ ሥርዐቶች አሉ። ቅዱሳት መጻሕፍት የሰው ልጆች በሕያው አምላክ ምሳሌ መበጀታቸውን ያትታሉ። ምንም እንኳ ሰው አካሉ ከምድር ትቢያ ቢዋቀርም፣ በሥሉስ አሃድ አምላክ መልክ የተቀረጸ ክቡር ፍጥረት ነው። ስለዚህም ነው ሰው ሕንጸ ሥላሴ ነው የምንለው። የክብርና ምስጋናን ዘውድ የተጎናጸፈው የሰው ልጅ፣ ከጥንስሱም ወንድና ሴት ሆኖ በምድር እንዲኖር የአምላኩ ፈቃድ ነው። ሁለት የጾታ መደቦች አሉ። ሁለቱም የጾታ መደቦች በመልኩ እንደ ምሳሌው ተፈጥረዋል። ተፈጥረዋል ብቻ ግን አይደለም፤ ኹለቱም ጾታዎች በፍጥረት ጀማሬ የተነገረውን አምላካዊ ቡራኬም ተቀብለዋል። የሁሉ ፈጣሪ በሚሆን አምላክ ርሱ ራሱ በጥበብ በሠራት ምድር እያበጇትና እየጠበቋት እንዲኖሩም ኀላፊነት ተሰጥቷቸዋል። እኩልነትን ከዚህ የተሻለ የሚያስረዳ ምንባብ ያለ አይመስለኝም።

በቤዝዎት ታሪክ ውስጥም አምላካዊው ማዳን ለሁለቱም የጾታ መደቦች የተሰናዳ ሆኖ እናገኘዋለን። ወንዶችን ብቻ ሊያድን በዕንጨት የተንጠለጠለን መድኅን ወንጌላት አያስተምሩም። እንደውም ሴቶች ምስክር ኾነው በማይጠሩበት ማኅበረ ሰብ፣ የትንሣኤው ቀዳሚ ምስክር ሴት ኾና እናነብባለን። በዓለ ኀምሣ በተባለው በጼንጤቆስጤ ቀንም መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉት መኻል፣ የጌታችንን እናት ጨምሮ ሌሎች በኢየሩሳሌም በጸሎት የተጉ ሴቶች ይገኙበታል።

ውድቀት ከበረዛቸው መስተጋብሮች አንዱ በሁለቱ ጾታዎች መካከል የነበረውን ኅብረት ነው። ውድቀትን ተከትሎ ጤናም መቀባበል ሻክሯል። ጭቆናና ጥርጣሬ፣ መነካከስና አለመተማመን በሁለቱ የጾታ መደቦች መኻል ነግሷል። ታሪክም በሁለቱ የጾታ መደቦች መካከል የሰነበተን ቁርሾ፣ ደግሞም ባላንጣነት ዘግቧል። እንደ መጋቢ ሰሎሞን አበበ ገለጻ ውድቀት አንኮታክቶናል። ከአምላካችን፣ ከራሳችን ደግሞም ከተፈጥሮ አቃቅሮናል፤ ቆራርጦናል።

ውድቀት ቢያደባየንም፣ ቸር የኾነ አምላክ ግን ራስ ገዝ ለመኾን ላመፀው የሰው ልጅ የቤዝዎትን ውጥን አዘጋጀ። ጊዜውም ሲደርስ ሁሉን እንደ ፈቃዱ ምክር የሚሠራ አምላክ በኩሩን ወደ ዓለም አገባው። በዚህም የመንግሥቱን መግዛት መጀመር አሳወቀ፤ ፍጥረቱንም ማደስ ጀመረ። ሊመጣ ባለው ዘመን (ማለትም ሙላትን/ፍጽምትን በሚያገኘው መሲሐዊ መንግሥት) ከምንጠብቃቸው መስተካከሎችና መጠገኞች (Restorations) መካከል አንዱ ይኼው የከረመ የሥርዐተ ጾታ መንሸዋረርና ቁርሾ ነው። ያህዌ ኹሉን አዲስ ሲያደርግ በዘመናት የዛገው ይኽም ሥርዐት ይታደሳል።

ጤናማ የሥርዐተ ጾታ መረዳት ለጤናማ ማኅበራዊ ኑሮ መሠረት እንደ ኾነ የሥነ ሰብና ኅብረተ ሰብ ሳይንስ አጥኚዎቸ ይስማማሉ። ሁለቱ የጾታ መደቦች ኀላፊነታቸውንና ቦታቸውን በቅጡ ሲረዱ የብዙ ነገሮች መልክ እየሠመረ ይመጣል። ሴትነትንም ሆነ ወንድነትን የሚያራክስ የማኅበረ ሰብ ሥርዐት ራሱን ለጥፋት ያጋልጣል፤ መፈረካከሱም ሳይታለም የተፈታ ነው።

እውነታው ይኼ ቢኾንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እጅግ እየተንሰራፋ የመጣ አዲስ አስተሳሰብ አለ። ይኽም ዕሳቤ በተለይም Radical left (far left) የፖለቲካ ርእዮት ባላቸው ሰዎች በኵል በስፋት እየተቀነቀነ ያለ ነው። ስሑት ደግሞም መርዛማ የሆነ ዕሳቤ ነው። በእኩልነት ጭምብል የመጣ ሌላ ጨቋኝ ሥርዐት ነው። ያለ ከልካይ በአደባባይ ተሰይሟል፤ የብዙኀንን ይሁንታም እያገኘ ነው። ወንድን የጭቆና ሁሉ መነሻ አድርጎ ይፈርጃል። በምድር ላይ ለታየው ውድመት ኹሉ ወንዶች/አባቶች (patriarchy) ተጠያቂ ናቸው። ስለዚህም ግልጽ የሆነ ጦርነት በወንድነት ላይ ተጎስሟል። ወንድነትን ደግሞም አባትነትን ማጠልሸት፣ ሲከፋም መስበር ተቀዳሚ ዐላማው ነው። ስለሆነም፣ ወንድነት (Masculinity) የሚወክላቸውን ነገሮች በሙሉ ያራክሳል። ጥንካሬን፣ ጥበቃን፣ ደጀንነትን፣ መጋቢነትን ወይም አቅራቢነትን (providence) ይጠየፋል። ወንዶች በአካላቸውና በስሜት ውቅራቸው ወንድ ሆነው በመገኘታቸው ብቻ እንዲሸማቀቁ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይኮንናል። ባስ ሲልም ባሎች፣ ደግሞም አባቶች በማኀበረ ሰብ ግንባታ ውስጥ የረባ አበርክቶት እንደሌላቸውና በቀላሉም ተተኪ እንደ ሆኑ ይደሰኩራል። ልፍስፍስነትን የሚያበረታታ መሰሪ ፍልስፍና ነው። ወንድን ልፍስፍስ አድርጎ እየሳለ ሴትነትን ደግሞ እንከንና ህጸጽ አልባ ምርጫ አድርጎ ያቀርባል። ሲከፋም ሴትነት/femininity የሚወክላቸውን ነገሮች መለኮታዊ (Deification) አድርጎ የመውሰድ ዝንባሌም አለው።

የወንድነትን ተፈጥሮና ሥነ ልቦና አከርካሪውን ለመስበር ብዙ ድንጋይ እየተፈነቀለ ነው። በተለይም ጤና ቢሱ የሆሊውድ መንደር ይኽን አስተምህሮ በገፍ ወደ ተርታው ሕዝብ ለማስረጽ ተግቶ እየሠራ ነው። እናቶች ያለ አባቶች እገዛ ብቻቸውን ልጆችን ያለ እክል ማሳደግ እንደሚችሉ ባገኘው አጋጣሚ ኹሉ ያወሳል። ብቻቸውን ልጆች የሚያሳድጉ ሴቶችን ራስን የመቻል፣ በራስ የመብቃትም ትልቁ ማሳያ ተደርገው እንዲሣሉ ይባትላል። አባቶች የዘር ፍሬ ከመለገስ የዘለለ ግልጋሎት የሌላቸው ድኩም ፍጥረቶች ተደርገው እንዲታዩ በሚዲያ በተደራጀና በተጠና መልኩ ይለፈፋል። በተለይ በፊልሞች በኩል ይኽን አተያይ ለማሾለክ ብዙ እየተደከመ ነው። ጠንካራ፣ ስኬታማ፣ ውሳኔ ሰጭና መሪዎች በስፋት በሴት ገጸ ባሕርያት እንዲወከሉ እየተደረገ ነው። ከዚህም ሲከፋ ደግሞ በፊልሞቻቸው ክፉ ደግ ያለዩ ሕፃናት ጭምር አባቶቻቸውን በዕውቀትም ኾነ በግንዛቤም የሚበልጡ እንደ ሆኑ ተደርገው ይሣላሉ። በዐጭሩ፣ ግራ ዘመሙ የፖለቲካ መደብ አባትነትን በማራከስ ቤተ ሰብ የተባለውን የኅብረተ ሰብ መገንቢያ ዋና መሠረት እያፈራረስ ይገኛል።

የማኀበረ ሰብ ሳይንስ አጥኚዎች እንደሚስማሙበት ባሎችንና አባቶችን ወደ ቤቶቻቸው መመለስ እጅግ የሚበዛውን ኅብረተ ሰባዊ ቀውስ (social evils) ይፈውሳል። ያልተፈለገ እርግዝና፣ የአደንዛዥ እጽ ሱሰኝነት፣ ከትምህርት ገበታ መሰናከል፣ ሴተኛ አዳሪነትና የመሳሰሉት ቀውሶች፣ በአንድም በሌላም ስፍራቸውን ገሸሽ ባደረጉ ባሎችና አባቶች ምክንያት የሚከሰቱ ማኅበራዊ ቀውሶች ናቸው። አባታዊ ሽንቁር (Father wound) እጅግ ለሚበዙ የስሜት ቀውሶች ምክንያት ነው። በምድር ያሉ የሥጋ አባቶቻቸውን ለጋስነት፣ ደግሞም ጥበቃ ሳያዩ የሚያድጉ ልጆች በሰማያት ያለን ቸር አባት ለመቀበል ይቸገራሉ። አባትነት ኹሉ ከሚሰየምበት ዙፋን ፊት መቅረብ ይፈራሉ። በዚህ ብቻ ግን አያበቃም። የአባቶቻቸውን ይሁንታ በለጋ ዕድሜያቸው ያላገኙ ታዳጊዎች፣ በተለይም ወንዶች ራሳቸውን እንደ ሙሉ ሰው ለመቀበል ይቸገራሉ። ለድባቴና ተደጋጋሚ የስሜት መዋዠቅ ያላቸው ተጋላጭነት ይጨምራል። ለጥቃትም እጅግ የተጋለጡ ይሆናሉ። አባቶችን ያንቋሸሸ ማኅበራዊ ቀመር ቀውሱ በዚህ ዐጭር መጣጥፍ ተዳስሶ የሚያልቅ አይሆንም። እነዚህም ለጥቆማ ያህል የቀረቡ ናቸው። በርእሰ ጕዳዩ ላይ መጠነ ሰፊ ግንዛቤ ማግኘት የፈለገ ሰው ተጨማሪ ንባብ እንዲሠራ አበረታታለሁ።

“ታዲያ እኛ ምን እናድርግ?” ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል፤ ተገቢ ጥያቄም ነው። መልሱ ስፍራችሁን ያዙ ነው። በተለይ ባሎችና አባቶች። ስፍራን መያዝ እየተፋለሰ ያለን ሥርዐት ሳይቀር ያክማል። እናቶችም አባቶችም በልጆቻቸው አካላዊና አእምሮአዊ ዕድገት ላይ አይተኬ ሚና አላቸው። በጤናማ ትዳር ተከባብረው ሲኖሩም፣ የአምላክን መልክ በሙላት መከሰት ይችላሉ። አዲሱ ሥርዐት የገፋቸው አባቶችና ባሎች ተገቢ ቦታቸውን ሲይዙ ማኅበራዊ ፈውስ ይጀምራል። ወንድነትን በመርዛማነቱ መረዳት ስናቆም የፈውሱ አካል መኾን እንጀምራለን። ስለሆነም ወንዶች ሆይ፤ በዘመኑ ሽንገላ ሳትደነቃቀፉ የተሰጣችሁን ቦታ ያዙ! ሚስቶቻችሁን በማክበር፣ ለትዳራቹም በመታመን ቤተ ሰብን አትርፉ። በጥድፊያ በተሞላ ዓለም ውስጥ ብትኖሩም፣ ለአብራካቹ ክፋይ የምትቆርሱት ጊዜ ላለማጣት ታገሉ። መከታና ደጀን መኾናቹን በግብራቹ ግለጡ። ጥንካሬ አካላዊም ኾነ የስሜት አውሬነት እንዳልሆነ በኑሯችሁ መስክሩ። በጥቅሉ የተሠራቹለትን ዐላማ ቸል አትበሉ! የአባትነትን ክብር አታራክሱ! ቦታችሁን በመያዝ ለፈውስ ቁሙ! እግዚአብሔርም በነገር ኹሉ ይርዳችሁ!

Ebsa Burka

Ebsa Burka holds BA degree in Geography and Environmental Science from Dilla University. He is an educator by profession and member of Mexico Amanuel United Church. He is passionate about ecological conservation and climate activism. He is also a freelance blogger and poet who enjoys listening bass guitar.

Share this article:

ቤተ ክርስቲያንና የገንዘብ አስተዳደር

ለስምንት አመታት የወጣቶች ፓስተር በመሆን ሲያገለግል የቆየው የ42 አመቱ ፓስተር ኑዛዜ አስደንጋጭ ነበር፡፡ መጋቢው በቤተክርስቲያኒቱ አመታዊ ስብሰባ ላይ በጉባኤ ፊት ቆሞ “በእግዚአብሔር፣ በባለቤቴ፣ በልጆቼ፣ በቤተሰቦቼና የክርስቶ አካል በሆነችው ኮሎራዶ የምትገኘው የኢውዛ ባይብል ቸርች ፊት ኃጢአትን አድርጌያለሁ” በማለት ተናገረ፡፡ ላለፉት ስድስት አመታት ከቤተክርሰቲያኒቱ የመባ መሰብሰቢያ እቃ ውስጥና እርሱ ከሚመራው አገልግሎት ከወጣቶች አካውንት ወደ 42,000 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብን በስድስት አመት ጊዜ ውስጥ በመውሰድ ለራሱ ጥቅም ያውል አንደነበርና ይህንን ወንጀሉን ከሚስቱም ሰውሮ ያደርግ አንደነበር በመግለጽ እራሱን በቤተክርሰቲያኒቱ መሪዎች አና በአገሪቱ ህግ ተጠያቂ ለማድርግ አንደወሰነ ተናገረ፡፡ በዚህም ምክንያት በማጭበርበርና በስርቆት ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

2 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

 • ምርጥ ጽሑፍ! ቃላቱና ፍሰቱም ውብ ነው።

  ውድ ኢብሳ፣
  በጣም አሳሳቢ ነው። እንዳስቀመጥከው፣ የተነሣው አሳብ ለወቅቱና ለትውልዱ ግራ አጋቢ፣ እጅግም አስፈሪ ነው። እነርሱ ሳይፈቅዱ ወንዶቹን “አንተ” አትበሉ መባል ከተጀመረ ሰነባበተ። እና ምን እንበላቸው? ስንል፤ እንደ በግለሰቡ ምርጫ! ወይ “እነርሱ”፣ ወይም “አንቺ”፣ ወይ “እነርሱ”፤ አንዳንዶቹም ምንም ጨምራችሁ አትበሉኝ እያሉ ነው። ምን ሆሊውድ ብቻ! በየሚዲያውና በየጉራንጉሩ —— ከሰሞኑ ልጁን ወደ ዩኒቨርስቲዎች ለዖዲሽን/ኢንተርቪው የወሰደ ወንድም ሲያጫውተኝ፤ መድረክ ላይ ከሚቀመጡት “ፕሮፌሰሮች” እና የተቋሞቹን አስተዳዳሪዎች አለባበስና ሜካፕ ያስደግጥሃል ብሎ ነገረኝ – ብዙ ልምድ ያላቸውና ስንት መጽሐፍትን የጻፉ።

  ታሪክ እየተቋጨ ይመስከኛል። እናም ——-
  የዮሐንስ ራእይ 22
  20፤ ይህን የሚመሰክር፦ አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ፡ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና።

  • – ይህ ነገር ረዝሞ ረዝሞ ረዝሞ
   … ሲስተካከል ሲስተካከል – ሲጨመር ሲጨመር ዛሬ ቀን አንተ/አንቺ ብቻ ሳይሆን፤ እናንተ/እርሳቸው – እነናንተ/እነርሳቸው – ይህ/ያ …

   “Personal pronouns are used in place of specific nouns for people, places and things. For example, we refer to a group of people with the pronouns they (subjective case), them (objective case) and their (possessive case).

   To refer to an individual, it’s respectful to use the pronouns they prefer. For example, someone who identifies as transgender may prefer the pronouns ze, zir and zirs, rather than those associated with their legal sex.

   At CU Boulder, you may select from the following pronouns: she/her/hers, he/him/his, they/them/theirs, ze/zir/zirs and xe/xer/xers.”
   _________________________

   https://www.colorado.edu/registrar/students/records/info/preferred

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.