[the_ad_group id=”107″]

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ

እንደ መንደርደሪያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ስለምትቀበል፥ በውስጡ የሚገኙትን መልእክቶችም ትቀበላለች። ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ (የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች) በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገቡና ለቤተ ክርስቲያን ጥቅምና መታነጽ የተሰጡ ናቸው (ሮሜ ፲፪፥፮- ፰፤ ፩ቆሮ. ፲፪፥፬-፲፩)። ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብታተ መንፈስ ቅዱስን የምትረዳበት፥ የምትተረጕምበት፥ የምታስተምርበትና የምትለማመድበት መንገድ የተለየ ነው። ከአስተምህሮዋ ብንነሣ፥ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰባት ዐበይት ምስጢራት ምእመናንን ታገለግላለች። ምስጢራት የተባሉበትም ምክንያት በዐይናችን ልናያቸው በእጃችን ልንዳስሳቸው የማንችል ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በእነዚሁ ምስጢራት አማካይነት የሚሰጡን ስለ ኾነ ነው” ትላለች (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት ፲፱፻፹፰፣ ገጽ ፴፫)። ይህም በተለይ ከጥምቀት በኋላ ወዲያው በሚሰጠው በምስጢረ ሜሮን አማካይነት የሚከናወን ነው “በቅብዐተ ሜሮን ተጠማቂው የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ይቀበላል።” (ዝኒ ከማሁ ገጽ ፴፮)።

በቀደመው ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ “እናቴ” እያለች የምትጠራትና በትምህርት የምትመስላት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች የመቀበያ መንገዱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን መኾናቸውን፥ በተለይም በምስጢረ ሜሮን አማካይነት እንደ ኾነ ትናገራለች። “መንፈስ ቅዱስን የምንቀበለው ከምስጢረ ጥምቀት በኋላ በሚፈጸመው በምስጢረ ሜሮን አማካይነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ቅባት በ፩ዮሐ. ፪፥፳፡፳፯ ላይ፥ ስለ ሐዋርያት እጅ መጫንም በሐ.ሥ. ፰፥፲፬-፲፯ ይጠቅሳል።” (H.H. Pop Shinoda III, Comparative Theology, 1988, p. 140). ከዚህ በተጨማሪ ፖፕ ሺኖዳ የጻፉት የጸጋ ስጦታዎችን ዝርዝርና አስፈላጊነት፥ ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ስጦታዎች እንዴት መጠቀም እንዳለባት፥ ወዘተ. ላይ በማተኰር ሳይኾን፥ በጸጋ ስጦታዎች አጠቃቀም ዙሪያ የሚታያውን የጰንጠቈስጤያውያንን ልምምድ እንከኖች በማጕላትና ከጸጋ ስጦታዎች ይልቅ በመንፈስ ፍሬዎች ላይ መተኰር ያለበት መኾኑን በማስረዳት ነው (ዝኒ ከማሁ p. 138-150)።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውስጥም ስለ ጸጋ ስጦታዎች ከዚህ ያለፈና በሚገባ የተብራራ ትምህርት አናገኝም። አባ ሳሙኤል / ሊቀ ጳጳስ/ በቅርቡ ያሳተሙትና “ግብረ መንፈስ ቅዱስ” የተሰኘው መጽሐፍ፥ ስለ መንፈስ ቅዱስ የቀደሙት ሊቃውንት ትምህርት በዚህ ዘመን እምብዛም እየተነገረ አለ መኾኑን ገልጦ፥ ብዙ የዘመናችን ጸሓፍያን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ላይ የሠሩት ሥራ አለ ለማለት እንደማያስደፍር ይናገራል። “ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ጸንታ የምትኖርበት ተከታዮች ምእመናንዋን የምትመራበት በነገረ ድኅነትም ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ የሚገኘው ግብረ መንፈስ ቅዱስ በመኾኑ ስለ ግብረ መንፈስ ቅዱስ ጠንክረን ማስተማር እንዳለብን ይሰማናል።” ይላል (፳፻፯፣ ገጽ ፻፴፫)። ይኹን እንጂ ይኸው መጽሐፍ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ከላይ የተጠቀሰውን የአቡነ ሺኖዳን መንገድ በመከተል፥ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንዴት መጠቀም እንዳለባት ከማስተማር ይልቅ፥ በዚህ ረገድ የሚስተዋለውን የጰንጠቈስጤያውያንን ልምምድ እንከኖች በማጕላትና በመተቸት ላይ ያተኰረ ኾኖ ይገኛል (አባ ሳሙኤል /ሊቀ ጳጳስ/፣ ግብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ፳፻፯፣ ገጽ ፻፩-፻፫)።

ቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈስ ቅዱስ እንደ ወደደ ለአማኞች ከሚያድላቸው የጸጋ ስጦታዎች ይልቅ (፩ቆሮ. ፲፪፥፲፩)፥ ክርስቲያን በጥረቱና በተጋድሎው ብዛት ስለሚደርስባቸው የብቃት ደረጃዎች መናገር ሚዛን የሚደፋ ነው። ከዚያ ውጪ ደግሞ በምንኩስና ብቻ ሳይኾን በገዳም ውስጥ ከሰው ተለይተው በዱር በገደሉ የሚኖሩ ቅዱሳን እንደ ተጋድሏቸው ጽናት የሚደርሱባቸው ዐሥር ማዕርጋት አሉ የሚል ትምህርት አለ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻፣ ገጽ ፪፻፶፩)። ስለዚህ ከጸጋ ስጦታዎች ይልቅ ትኵረት የሚሰጠው በብቃት ስለሚደረስባቸው ማዕርጋት ነው።

በጽሑፍ የሰፈሩ ጥንታውያን ጸሎቶች ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን የሚለምን ክፍል ይገኛል። ለምሳሌ፦ በእሑድ ሊጦን (የምልጃ ጸሎት) ላይ፥ በየሳምንቱ እሑድ፥ “በሐዋርያት ላይ ጸጋኽን የገለጽኽ አንተ ነኽ፤ በአንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ እንደ እሳት ወረደ፤ በሀገሩ ኹሉ ቋንቋ ተናገሩ። ሰማይንና ምድርን የፈጠርኽ አንተ ይህን መንፈስኽን ላክልን።” የሚል ልመና ይቀርባል።

ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ጋር በተያያዘ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዘንድ በብዙዎች በስፋት የሚጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሐዲስ ኪዳን ክፍል ለምሳሌ በሮሜ ፲፪፥፮-፰፤ ፩ቆሮ. ፲፪፥፬-፲፩ ላይ ያሉቱ ሳይኾኑ፥ በብሉይ ኪዳን በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፲፩፥፪ ላይ የሰፈሩቱ ናቸው። ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ፥ “ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን ጽፈዋል፥ “መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ ምእመን የመንፈስ ቅዱስ ሀብታት ያድሩበታል። ‘የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኀይል መንፈስ፥የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።’ (ኢሳ. ፲፩፥፪)። በእነዚህ ሀብታት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምናውቅበት፥ የሃይማኖትን ምስጢራት የምናስተውልበት፥ መልካሙንና የሚበልጠውን መንገድ ለመምረጥ ምክርን የምናገኝበት፥ ክፉውን ለማስወገድ ኀይል የሚኾኑንና መልካሙንም ሥራ እንድናከናውን የሚያበቁን መኾናቸውን እንረዳለን። ስለዚህ ክርስቲያኖች ኹሉ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እየተመሩ በመልካም ሥራቸው የሰማይ አባታቸውን በሰዎች ዘንድ እንዲመሰገን በማድረጋቸው ክርስቲያናዊ ሕይወታቸው በዘልማድ ሳይኾን በእውነትና በመንፈስ ቅዱስ ኀይል መኾኑን ያረጋግጣሉ።” (፲፱፻፺፮፣ ፪፻፲፩)።

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የሚከተለውን ጽፈዋል፤ “ቅዱስመንፈስአንድሲኾንሀብቱብዙነው፤የተለያየም ነው፤ ስለዚህ ለያንዳንዱ ሰው የተለያየ ስጦታ አለው፤ ይኸውም እያንዳንዱ ሰው እንደ ሃይማኖቱ ጽናት እንደ ምግባሩ ፍጹምነት እንደ ትሩፋቱ ብዛት ይሰጠዋል። ለምሳሌ ድዉይ የመፈወስ ሀብት ይሰጠዋል፤ ትንቢት የመናገር የማስተማር ሀብት በሐዲስ ልሳን የመናገር ሀብት፥ ሌላም ይህን የመሳሰለ ብዙ ዐይነት አለ። ለአንዱ በብዙ መልክ ሊሰጠው ይችላል። አንድ ብቻም የሚሰጠው አለ። ፈጽሞም የሚነሣው (አንድም የማይሰጠው) ይገኛል።” (ትምህርተ ክርስትና ፪ኛ መጽሐፍ ፲፱፻፹፬፣ ገጽ ፸፩፡፸፪)። ይህ አገላለጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በሐዲስ ኪዳን ከተጻፈው አንጻር የተሻለ አገላለጥ ነው። ኾኖም የጸጋ ስጦታን መንፈስ ቅዱስ ለወደደው እንዲሁ የሚሰጠው መኾኑ ቀርቶ በሰው ጥረት የሚገኝ ተደርጎ መቅረቡና የጸጋ ስጦታ የማይሰጠው አማኝ ሊኖር ይችላል የሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት (፪ቆሮ. ፲፪፥፲፩፤ ፩ጴጥ. ፬፥፲) ሊፈተሹ ይገባል።

በአጠቃላይ ከላይ ከተገለጠው ውጪ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች ዙሪያ የተዘጋጀ ይፋዊ የኾነ ትምህርት ባይኖራትም፥ ከጸጋ ስጦታዎች መካከል አንዳንዶቹን የሚለማመዱ አገልጋዮችና በጸጋዎቹ ተጠቃሚ የኾኑ ምእመናን እንዳሉ ሲነገር እንሰማለን። ይኹን እንጂ የጸጋ ስጦታዎቹ የመንፈስ ቅዱስ መኾን አለ መኾናቸው፥ በመጽሐፍ ቅዱስ መፈተሽና መረጋገጥ ያለበት መኾኑ አጠያያቂ አይኾንም። በዚሁ መሠረት በጕልሕ የሚታዩትን ከፈውስ፥ ከትንቢትና ከመገለጥ ጋር የተያያዙት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ሀብተ ፈውስ

በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብተ ፈውስ (የፈውስ ጸጋ) ከሌሎቹ ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ ይልቅ በጕልሕ የሚታይ ነው ማለት ይቻላል። እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ፈውስ የሚሰጠው ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ በኾነው በምስጢረ ቀንዲል አማካይነት ሲኾን፥ ቀንዲል ለበሽተኞች ተጸልዮበት የሚቀባ ዘይት ነው። ከዚህ አንጻር ፈውሱ የሚሰጠው በተጸለየበት ዘይት ነው መባሉ፥ ሀብተ ፈውሱ በዘይቱ ላይ እንጂ በቀቢው ቄስ ላይ አለ መኾኑን ሊያሳይ ይችላል። ይኹን እንጂ በልዩ ልዩ ደዌ ለሚሠቃዩ፥ በአጋንንት እስራት ተይዘው ፈውስንና ዐርነትን ፈልገው ለሚመጡ፥ በጠበል ፈውስና ነጻ የማውጣት አገልግሎት እንደሚሰጥም ይታወቃል። የሚያጠምቁትም ሀብተ ፈውስ (የመፈወስ ጸጋ) ተሰጥቷቸዋል የሚባሉቱ ናቸው። በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ውስጥ ኹነኛ ስፍራ የተሰጠው ግን ቀንዲል እንጂ ጠበል አይመስልም፤ በተግባር ግን አገልግሎቱን በስፋት እየሰጠ ያለው ጠበል ነው።

“ጠበል፥ ለሚጠቀሙበት ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ለመፈለግ ዐላማና ከጨለማው ኀይል ለመጠበቅ በቄስ የሚባረክ ውሃ ነው።” (The Ethiopian Orthodox Church, 1970, p. 72). እንደ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ ወልደ ዮሐንስ ደግሞ፥ “ቅዱስ ጠበል ሕሙማን የሚፈወሱበት በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚገኝ የምንጭ ውሃ ነው።” ይላሉ። ጠበል በሦስት መንገድ ሊገኝ እንደሚችል የሚያስረዱት መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ሥላሴ፥ የመጀመሪያው “በተአምራት የፈለቀ ወይም ቀድሞ የነበረ በኋላ የፈውስ ተኣምር የተገለጠበት፥ በፈጣሪ ወይም በቅዱሳን ስም የተሰየመ የምንጭ ውሃ” ነው። ኹለተኛው ደግሞ “ከማናቸውም ምንጭ ወይም ወንዝ ተቀድሞ[ቶ] የተጸለየበት የተባረከ ውሃ ነው።” ሦስተኛውም፥ “ጸሎት ተጸልዮበትና ተባርኮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቀመጥ፥ ምእመናን በሚጠይቁበት ጊዜ የሚሰጣቸው መዝገበ ጠበል ነው። ቅዱስ ጠበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ቢኾንም በክርስትናው ዓለም ከመደበኛው የጥምቀት ውሃ ውጭ በቅዱስ ጠበል መጠቀም የተጀመረው በ፬ኛው ምእት ዓመት ነው” ይላሉ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእስራ ምእት በዓል አከባበርና የመስቀል ዝግጅት፣ 2001 ዓ.ም.፣ ገጽ ፲፪)።

በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ ውሎ የሚገኘው ጠበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መኾኑን በ፪ነገ. ፭፥፩- ፲፱፤ ዮሐ. ፭፥፩-፲፬፤ ፱፥፩-፳፯ ላይ ያሉትንና ሌሎችንም በመጥቀስ የሚናገሩ አሉ (ሊቀ ኅሩያን ተግባሩ አዳነ፣ ማኅበራዊ ኑሮና ጠበል ፳፻፫ (2003 ዓ.ም.፣ ገጽ ii፡ iii፤ መርሐ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት ፲፱፹፰፣ ገጽ ፻፬)። በመጠመቅ የፈውስ አገልግሎት የሚሰጥበት ጠበል፥ ጠበል መኾኑ የሚታወቀውና በጠበልነት ተቀባይነት የሚያገኘው ለአንዳንድ የበቁ ለሚባሉ ሰዎች በራእይ ተገልጦ እዚህ ቦታ ላይ ጠበል ፈለቀ ተብሎ እንደ ተኣምር ከተነገረ በኋላ ነው። ከዚያ ስፍራው ይከለልና አጥማቂ ተመድቦለት የፈውስ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል። ለምሳሌ፦ የእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ጠበል አባ ምትኬ የተባሉ መነኩሴ፥ “በዚያ ስፍራ ጥንት ቤተ ክርስቲያን የነበረበትና ጠበል ያለበት መኾኑ በራእይ ተገለጸልኝ” ብለው ከተናገሩ በኋላ አገልግሎት መስጠት እንደ ጀመረ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ ጽፈዋል (የኻያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ ፳፻፪ ዓ.ም.፣ ገጽ ፹፰)። “ነገር ግን ማየ ጸሎት ወይም ጠበል አለበት የሚባል አስቀድሞ ያልታወቀ ቦታ ሲያጋጥም፥ አጋንንት በምታታቸው ተኣምራት ያደረጉ እየመሰሉ ሕዝቡን እንዳያታልሉትና እንዳይጫወቱበት፥ ወይም ወደ ሌላ አምልኮ እንዳያዘነብሉት” ጥንቃቄ እንደሚያሻ የሚናገሩ አሉ (መርሐ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት ፲፱፻፹፰፣ ገጽ ፻፬)።

ሕዝቡ ካሉበት የጤናና ሌሎችም ማኅበራዊና መንፈሳዊ ችግሮች አንጻር እነዚህን ልምምዶች አጥብቆ ስለሚፈልጋቸው፥ በዚህ አቅጣጫ ‘ጸጋው አለን፤ እናገለግላለን’ የሚሉ ኹሉ፥ በውሃ ላይ የተለያዩ ጸሎቶችን አድርሰው በማጥመቅም አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ይታወቃል። በሕዝቡ መካከል የሚታየውን የፈውስ ልምምድ በሚመለከት፥ እንፈውሳለን ብለው የተሰለፉትን ብዙዎቹን ስንቃኝ ግን፥ “እንፈውሳለን” የሚሉበት መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ፥ ፈውሱ በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብቻ የሚከናወን፥ ክብርን ለእግዚአብሔር የሚያመጣና “ተፈወሱ” የሚባሉትን ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንገድ የሚመለስ ኾኖ አይታይም።

በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳንድ የመፈወስ ጸጋ የተሰጣቸውና በትክክለኛው መንገድ በተሰጣቸው ጸጋ ያገለገሉ አባቶች እንዳሉም መረጃዎች ይጠቍሟሉ። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት መካከል አባ ወልደ ትንሣኤ፥ በኋላም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የተባሉት ጳጳስ ተጠቃሽ ናቸው። “ከ1947 ዓ.ም. ጀምሮ ከአራት ዐሥርት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ” የፈውስ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት እኒህ አባት፥ “በአገልግሎት ዘመናቸው በሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ሕሙማንን መፈወሳቸውንና ፈውስን በክርስቶስ ኀይል ማድረጋቸውን” መመስከራቸው፥ ጸጋውና በጸጋው የተከናወነው ፈውስ ከጌታ ለመኾኑ በቂ ማስረጃ ነው (ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር ፵፭፣ ገጽ ፲፩-፲፬)።

ከዚህ በተቃራኒው በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ሳይኾን ከእግዚአብሔር መንገድ ውጪ በሌላ መንገድ ፈውስን እንሰጣለን የሚሉና ለራሳቸው በርካታ ተከታዮችን ያፈሩ፥ እንሰጣለን በሚሉት “ፈውስ” ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ሳይኾን ከሌሎች አካላት ጋር የሚያገናኙ ሐሰተኞች መኖራቸውም የታወቀ ነው። እንዲያውም እውነተኞች መስለው፥ እናጠምቃለን፤ ፈውስም እንሰጣለን በሚል በመናፍስታዊ አሠራር ሕዝቡን የሚያወናበዱ መኖራቸውን የሚናገሩ አሉ (መሪጌታ ሠረቀ ብርሃን፣ ማሳቀል፣ ፳፻፭፣ ገጽ ፷፰- ፸፰)።

ሀብተ ትንቢት

መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ በዘመናቸው ያዩትን አንድ ገጠመኝ እንዲህ ሲሉ በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፤ “በዚህ በ1904 ዓ.ም. ናዝራዊና ባሕታዊ አዲስ አበባ ከተማ ከመቼውም ይልቅ በብዛት ሲታይ ከረመ። ናዝራዊ ጠጕሩን አስረዝሞ፥ ባለ ዐንካሴ የብረት መስቀል ተሸክሞ፥ ባሕታዊም ዳባ ለብሶ፥ ጢሙን አንዠርግጎ በየበዓል ስፍራ እየዞረ በአደባባይ ይሰብክ ጀመር።“ስብከቱም ‘መዓት መጣብህ፥ ጕድ ፈላብህ፥ እግዚኦ በል፥ ንስሐ ግባ፥ ምጽዋት መጽውት የሚል ነው። በተጨማሪም ‘ምጽአት ደረሰ፤ ዓለም ልታልፍ ነው’ ሲሉ ባሕታዊና ናዝራዊ አስደንጋጭ ወሬ ለሕዝቡ አፈሰሱለት። በአጋጣሚ በዚህ ዓመት የስቅለት በዓል መጋቢት27ቀን፥ፋሲካመጋቢት29ቀንላይውሎ ነበር። እንዲህ ኾኖ ሲውል በዚያ ቀን ምጽአት ይኾናል የሚል ወሬ ድሮም ስለ ነበረ፥ ይህ ኹሉ ተጨማመረና ሕዝቡ በሥጋት ላይ ኾነ። የዋሁ ሕዝብ በናዝራዊ ስብከት በእውነት ተደናገጠ። ብልጡ ግን ናዝራዊ ሲያታልል ነው እያለ እያሽሟጠጠ ተቀመጠ።

“እንዲህ ስቅለትና ፋሲካ ደረሰ። ነገር ግን ዓለም አላለፈችም። ባሕታዊና ናዝራዊም ወዲያው ሌላ ዘዴ ፈጠሩና ‘ሕዝቡ እግዚኦ ስላለ ምሕረት ወረደ’ ብለው ሰበኩ። እንደዚያ ዘመን ባሕታዊና ናዝራዊ በዝቶ አይቼ አላውቅም።” (የኻያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ፳፻፪ ገጽ ፹፱፡፺)።

ከዚህ ምስክርነት በቤተ ክርስቲያኒቱ ትንቢትን የመተንበይ ልምምድ ከቀድሞ ጀምሮ በባሕታውያን ዘንድ እንደ ነበረ እንረዳለን፤ ዛሬም ቢኾን ትንቢት ለመተንባት የሚቃጣቸው እነዚሁ ባሕታውያን ናቸው። ባሕታውያኑ በአብዛኛው በቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት ሳይኾን፥ ከዚያ ውጪ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ባለ ስፍራ ላይ ሰዎችን ሰብስበው ትምህርት መስጠታቸው፥ ትንቢትም መተንባታቸው የተለመደ ነው። ከላይ የተገለጠውን ትንቢት በተመለከተ፥ ትንቢቱ በመጽሐፍ ቅዱስና በፍሬው የሚለካ ቢኾንም፥ ሳይፈጸም የቀረው ትንቢት ባሕታውያኑ በሐሰተኛነት ከራሳቸው አንቅተው (አመንጭተው) የተናገሩት እንጂ ከእግዚአብሔር አለ መኾኑ የተረጋገጠ ነው። ባሕታውያኑ ግን “ተሳስተናል” ከማለት ይልቅ ሌላ ምክንያት በመስጠት፥ ሐሰተኛነታቸውን ለመሸፈን የሞከሩበት ኹኔታ እንደ ነበረ ነው የምንገነዘበው። በዘመናችንም በልዩ ልዩ ጕዳዮች ላይ ትንቢት የተናገሩና የሚናገሩም እንዳሉና ላልተፈጸመው ትንቢታቸው ተጠያቂ የኾኑበት ኹኔታ፥ ወይም ተሳስቼ ነው ብለው የታረሙበት አጋጣሚ እንደሌለ ይታወቃል።

በቀድሞው ዘመን እነዚሁ ባሕታውያን ነቢያት ብቻ ሳይኾኑ ሰባክያንም ኾነው በመሰለፍ፥ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ላይ ተመሳሳይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፈዋል። በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥር ይካኼድ የነበረው “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት” ያሳትመው የነበረው “ትንሣኤ” መጽሔት ላይ፥ የሚከተለው ትዝብትና አስተያየት ተጽፏል። “ሰማይ ተንዶ ይጫንኽ፥ መሬት ተከፍቶ ይዋጥኽ፥ ይስበርኽ፥ ይሰንጥርኽ መዓት ያውርድብኽ፥ እያሉ ምእመናንን የሚያባቡና የሚያሸብሩ፥ የሚዘልፉ አንዳንድ በትምህርት ያልተሞረዱ ሰባኪዎች የሚሰጡት ስብከት ቤተ ክርስቲያናችንን ሊያስጠላት ስለሚችል፥ እነርሱ ተወግደው ለዘመናዊው ትውልድ ተገቢውን ትምህርት የሚያበረክቱ ሰባክያን ቢሰለፉ የቤተ ክርስቲያን ሥራ የተቃና ሊኾን ይችላል ተብሎ ይታመናል።” (ልሰነ ወርቅ በዛብህ /ቄስ/ ፲፱፷፬ ነሐሴ፣ ገጽ ፴፫)። ይህ የጸሓፊው ተስፋ በኋላ ተፈጽሞ ለዘመናዊው ትውልድ ተገቢውን ትምህርት የሚያስተምሩ ሰባክያንን በመጠኑም ቢኾን ማፍራት ቢቻልም፥ የባሕታውያኑ ሰባኪነት ቀርቷል ማለት ግን አይደለም።

ይህ ፎቶ የተወሰደው ከተጠቀሰው የትንሣኤ መጽሔት ገጽ ፴፫ ላይ ነው
ይህ ፎቶ የተወሰደው ከተጠቀሰው የትንሣኤ መጽሔት ገጽ ፴፫ ላይ ነው

መገለጥ

መገለጥ መልካምም ይኹን ክፉ የተሰወረውንና ያልተገለጠውን፥ ኀላፍያቱንና መጻእያቱን (ያለፉትንና የሚመጡትን) ወደ ብርሃን ከማውጣት ጋር የተያያዘ ነው። ከላይ እንደ ተገለጡትና እንደ ሌሎቹም የጸጋ ስጦታዎች ኹሉ፥ ስለዚህ ጸጋ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታስተምረው ግልጥ ትምህርት የለም። በገዳማትና በባሕታውያን መካከል ግን ልምምዱ አለ። በዚህ አቅጣጫ ይህ ጸጋ አላቸው ተብለው የሚታሰቡት ከሰው ተለይተው ለብቻቸው ዘግተው የሚኖሩ ናቸው። እነዚህ ባሕታውያን የበቁ ናቸው፤ ብዙ ነገር ይገለጥላቸዋል፤ የተሰወረው ይታያቸዋል ተብሎ ስለሚታመን፥ እነርሱ ወዳሉባቸው ገዳማትና ተለይተው ወደ ተቀመጡበት ስፍራ በመኼድ ስለ ወደ ፊት ዕጣ ፈንታቸው፥ ስለ ንግዳቸው፥ ስለ ሥራቸው፥ ስለ ትምህርታቸው፥ ስለ ትዳራቸው፥ ወዘተ. ይጠይቃሉ። ምላሽም አገኘን ሲሉ ይሰማሉ። ዛሬ ወደ አንዳንድ ገዳማት ጕዞ የሚያደርጉ የእምነቱ ተከታዮች አንዱ ዐላማ በመገለጥ የሚያገለግሉ መናንያንን ለማግኘትና ስለ እነርሱ የሚገለጠውን ነገር ለመስማት እንደ ኾነ ግልጥ ነው።

ይህም አገልግሎት እንደ ላይኞቹ ኹሉ በመጽሐፍ ቅዱስ መመዘንና ከእግዚአብሔር መኾን አለ መኾኑ መረጋገጥ ይገባዋል። መንፈስ ቅዱስ በዚህ ጸጋ ከአማኞች ግላዊ ጕዳይ ጋር የተገናኙ ነገሮችን የሚገልጥ መኾኑ ባይካድም፥ በዋናነት ጸጋው የተሰጠው ለአካሉ ማለት ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ እንደ መኾኑ መጠን በዚህ አቅጣጫ ከሚታየው ውጤት አንጸር መለካት ያለበት መኾኑ አያከራክርም (1ቆሮ. ፲፬፥፲፪፡፳፮)። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያው ጴጥሮስ በኩል የሐናንያና የሚስቱን ማታለል ሲገልጥና እነርሱ በሞት ሲቀጡ፥ በዋናነት የተከተሉት ውጤቶች፦

  • “በቤተ ክርስቲያን ኹሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ኾነ” (ሐ.ሥ. ፭፥፲፩)
  • “የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ” (ቍጥር ፲፬)።
    ዛሬ መገለጥ በሚመስለው አገልግሎት እየኾነ ያለውና የሚታየው ውጤት ጕዳዩን ከእግዚአብሔር ነው ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም። ምክንያቱም “መገለጡ” በሰዎች ዘንድ ጊዜያዊ ስሜትን ከማነቃቃት ያለፈ ነገር ሲያመጣ አይታይም። “መገለጡ” የሚነካቸውም ኾኑ ያዩት ከሌላ አካል ጋር ሲጣበቁና “መገለጡን” ያመጣላቸውን ሰው ሲከተሉ ነው የሚታየው እንጂ፥ ምልክት ኸኗቸው ለጌታ ሲጨመሩለት አይስተዋልም። ከዚህ የተነሣ መገለጥን የመሰለው ይህ አገልግሎት ከመናፍስት አሠራር ጋር የተያያዘ ገጽታ እንዳለው በብዙዎች ይታመናል።

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስና በጸጋ ስጦታዎቹ በጥቅሉ የምታምን ቤተ ክርስቲያን መኾኗ አይካድም። በአንዳንድ ኹኔታ ግን በሀብታተ መንፈስ ቅዱስ ዙሪያ የተብራራና ስለ ሀብታቱ አስፈላጊነትና ጠቃሜታ በግልጥ የሚተላለፍ ትምህርት አናገኝም። ‘የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሚሰጠው በሜሮን አማካይነት ነው’ የሚለው ትምህርት በሐዲስ ኪዳን ዘመን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ብሎ መውሰድ ያስቸግራል፤ ምክንያቱም በዚህ መንገድ ጸጋ ተቀብለዋል የተባሉቱ ጸጋቸው ሲገለጥና ቤተ ክርስቲያን ስትጠቀምበትና ስትታነጽበት ማየት የሚቻልበት ዕድል ያለ አይመስልም። በምስጢረ ሜሮን ሀብታተ መንፈስ ቅዱስን እንቀበላለን የሚለው ትምህርትም ጥቅል እንጂ የተብራራና የተፍታታ አይደለም። ጸጋን ተቀበለ የተባለው ሰውም ጸጋው ተለይቶ እንዲታወቅና ቤተ ክርስቲያን እንድትጠቀምበት የሚያደርግ መንፈሳዊ አሠራርም ኾነ ሥርዐት አለ ማለት አይቻልም። ከመንፈስ ቅዱስ ያልኾኑ የስሕተት አሠራሮችንም ለመቈጣጠር የሚያስችል መመዘኛ የላትም። ስለዚህ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሀብታት ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮዋንና ተያያዥ ጕዳዮችን መፈተሽ ይኖርባታል።

ብዙም ባይኾን የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎችን የሚመስሉ አንዳንድ ጸጋዎችን የሚለማመዱ አገልጋዮችን በተመለከተም አለን የሚሉት ጸጋ ሊፈተሽና ከእግዚአብሔር መኾን አለ መኾኑ ሊታወቅ፥ አላቸው የሚባለው ጸጋ ምንነትና ከማን የተቀበሉት እንደ ኾነ በመጽሐፍ ቅዱስ ሊመዘን ይገባዋል። አንዳንዶች በምትሐት ምልክት ስላደረጉ ብቻ ነገሩን ከእግዚአብሔር ነው ማለት የማይቻል ነውና መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ቤተ ክርስቲያኒቱም እውነተኛውን ከሐሰተኛው መለየት የሚቻልበትን መመዘኛ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማዘጋጀት ይጠበቅባታል። ምእመናንንም ከእግዚአብሔር የኾኑት ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ ምን እንደ ኾኑ እንዲለዩና መጠቀም እንዲችሉ ማስተማርና ማብቃት ያስፈልጋል።

ለኹሉም ግን የእግዚአብሔር ቃል ለእስራኤል ልጆች ስለ ሐሰተኞች ነቢያት የሰጠውን መመዘኛና ማስጠንቀቂያ ማስተዋል ይገባል፤ “በመካከልኽም ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥኽ፥ እንደ ነገረኽም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም፦ ኼደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልኽ፥ አምላካችኹን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችኹ በፍጹምም ነፍሳችኹ ትወድዱት እንደ ኾነ ያውቅ ዘንድ አምላካችኹ እግዚአብሔር ሊፈትናችኹ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም ዐላሚ አትስማ።” (ዘዳ. ፲፫፥፩-፫)።

የኋለኛው ዘመን አሻራ በፍቅር ፍኖት ላይ

የስሜትና የሐሳብ ቁርኝት የፍቅር አካላት ሆነው ይነሣሉ። ያልተነጣጠለ አብሮነታቸውም አንደኛው ከሌለ የሌላው ሕልውና ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርጋል። ለነገሩ፣ ፍቅርን ከተያያዥ ስሜትና ሐሳብ አፋቶ ትርጉም ባለው መልኩ ማሰብስ ማን ይችላል? ተፈቃሪን በምናብ አጣምሮ ራስን ማብገንን ሆነ የመጨረሻዋ ተጠባቂ ሰከንድ አምልጣን ዘላለምን የተቀላቀለች ይመስል በቁንጥንጥ “ውዳችንን” መጠበቃችን በምንስ ይብራራል? በእርግጥም ከፍቅር ጋር ተያይዞ የምናሳየው መሰጠት፣ ሐዘኔታ፣ ቅናት፣ መረበሽ ከስሜትና ከሐሳብ ትሥሥር ጋር ይዛመዳሉ። የስሜቶቻችን እና የሐሳቦቻችን ቁርኝት ከሌሎች ተደምሮ ባዕድነትን ገፎ ተፈቃሪያችን በአንድት የሚገምድ ምስጢር ነው (ዘፍ. 2፥23-24)።

ተጨማሪ ያንብቡ

እንዴት እንሙት? እንዴት እንኑር?

ጌታችን ስለ ሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ በምናስብበት በሰሙነ ሕማማት፣ ንጉሤ ቡልቻ “እንዴት እንሙት?” የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ። ምላሹ በክርስቶስ ሞት ውስጥ የቀረልን ትልቅ ትምህርት ሆኖ አለ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.